ኢየሱስ የሰናፍጭ ቅንጣት ከምድር ዘር ሁሉ እንደምታንስ መናገሩ ስህተት ነውን?

ኢየሱስ የሰናፍጭ ቅንጣት ከምድር ዘር ሁሉ እንደምታንስ መናገሩ ስህተት ነውን?

አንድ ሙስሊም ሰባኪ የወንጌሉ ኢየሱስ ግብርናን በተመለከተ “ስህተቶችን ሠርቷል” የሚል ጽሑፍ አስነብቦናል፡፡ የመጀመርያው ውንጀላ ኢየሱስ በለሲቱ ፍሬ እንዳላትና እንደሌላት “አለማወቁ” የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሰናፍጭ ቅንጣት ያነሱ አዝዕርት በምድር ላይ መኖራቸውን “አለማወቁ” የሚል ነው፡፡ የመጀመርየውን ከዚህ ቀደም ምላሽ ስለሰጠንበት ራሳችንን መድገም አያሻንም፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሁለተኛውን ጥያቄ እንመልሳለን፡-

እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፥ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፥ማርቆስ 431

ኢየሱስ በዚህ አንቀጽ እንደሚነግረን በምድር ካለ ዘር ሁሉ የሚያንሰው ሰናፍጭ እንደሆነ ነው። ይህ ደግሞ ፈጽሞ ስህተት ነው። ዛሬ ሳይንስ እንደሚነግረን ከሰናፍጭም በታች በአይናችን እንኳን ልናያቸው የማንችላቸው 85 ማይክሮ ሜትር ወይንም 0.81 ማይክሮግራም ድረስ የሚመዝኑ ጥቃቅን ዘሮች ይገኛሉ። ይህንን ሳያውቁ በደፈናውበምድር ካለ ዘር ሁሉ ያንሳልማለት የእውቀት ክፍተት ነው። አይደለም አምላክ የሚባል አካል ይቅርና በአምላክ የተላከ እውነተኛ ነብይ እንኳን ይፈጽመዋል ተብሎ የማይጠበቅ ስህተት ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደመከራከሪያይህንን የተናገረው በወቅቱ ለነበሩ የፍልስጤም ሰዎች እንዲገባቸው ነውሲሉ ያቀርባሉ። ይህም ግን ሌላ ስህተት ነው። የመጀመሪያ ነገር ሰዎቹ የሚያውቁት ትንሹ ዘር ብሎ መግለጽና የምድራችን ትንሹ ዘር ብሎ መግለጽ ሁለቱ የተለያዩ ሀሳቦች ናቸው። ሲቀጥል እንደ ፕሮፌሰር ኦልሰን ገለፃ በወቅቱ እንኳን በፍልስጤም ምድር ከዚህ ያነሱ ሌሎች ለምሳሌ መቅረብ የሚችሉ ዘሮች ነበሩ። ያም ሁኖ ግን እነዛንም ዘሮችየምድር ትንሹ ዘርካላቸው የስህተቱ ችግር እሱ ጋር ነው ያለው ማለት ነው። በዚህም አለ በዚያ ይህንን ንግግሩን አስመልክቶ ሊያብራራ የሚችል አመኔታዊ ሙግት ማቅረብ አዳጋች ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ ሀሳቡንከምድር ዘር ሁሉበሚል ጥቅል የስህተት ድምዳሜ አስሮታል። መሠል ስህተቶችን ጌታ ከተባለ አካል ይቅርና ጎበዝ ከሚባል ሳይንቲስት እንኳን ቢገኝ ያሳፍራል።

መልስ

ጌታችን ኢየሱስ በምድረ እስራኤልም ሆነ በዓለም ላይ የሚገኙ የዕፅዋት አዝዕርትን እያነጻጸረ አይደለም፡፡ ነገር ግን በዘመኑ በምድረ እስራኤል የነበሩ ገበሬዎች በማሳቸው ውስጥ ከሚዘሯቸው አዝዕርት ሁሉ ስለምታንስ ዘር እየተናገረ ነው፡፡ ከአውዱ እንደምንረዳው ጌታችን ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በምሳሌ እያስረዳ የነበረ ሲሆን ከግብርና ጋር በማነጻጸር ሲናገር እንመለከታለን፡፡ ጠያቂው ግን ለትችት እንዲያመቸው በማሰብ አውዱን በመቁረጥ ጠቅሶታል፡፡ ሙሉ ሐሳቡ እንዲህ ይነበባል፡-

“እርሱም አለ፦ በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል። እርሱም አለ፦ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን? እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፥ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለችበተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፥ የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታደርጋለች።” (ማርቆስ 4፡30-32)

“ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፥ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአታክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።” (ማቴዎስ 13፡31-32)

ጌታችን ኢየሱስ በወቅቱ ሲያዳምጡት ለነበሩት ሰዎች ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በምሳሌ እያስረዳ እንጂ ስለ ፍጥረተ ዓለም እያስተማረ አልነበረም፡፡ የትምህርቱ ዓላማ ከባድ የሆነውን ጉዳይ በቀላል መንገድ ማስረዳት በመሆኑ ለአድማጮቹ በሚገባቸው መንገድ ተናግሯል፡፡ መልእክቱም በዘመኑ የነበሩ ሰዎች በማሳቸው ውስጥ ከሚዘሯቸው አዝዕርት መካከል በመጣን አነስተኛ የተባለችዋ ሰናፍጭ ከሁሉም አትክልት በላይ በመርዘምና ቅርንጫፎችን በማበጀት ለአእዋፍ ጎጆ መሥሪያ እንደምትሆነው ሁሉ የእግዚአብሔር መንግሥትም ሰዎች በሚንቁትና ትኩረት በማይሰጡት አነስተኛ መንገድ በመጀመር ከሁሉም ምድራዊ ኃይላት ልቆ እንደሚታይ ማስረዳት ነው፡፡ ሰናፍጭ በመጠን አነስተኛ ብትሆንም በውስጧ ያለው የሕይወት ኃይል ከሁሉም አትክልት እንድትበልጥ እንደሚደርጋት ሁሉ በክርስቶስ በጌታችን የተሰበከው የእግዚአብሔር መንግሥትም መለኮታዊ አስተምህሮ በመሆኑ ሌሎች ንፅረተ ዓለማትን ድል በመንሳት በሰው ልጆች ታሪክ ከታዩት ትምህርቶች ሁሉ ይልቅ ብዙ ተከታዮችን ማፍራትና በዓለም ታሪክ ላይ ተፅዕኖን ማምጣት ችሏል፡፡

ጌታችን በዓለም ላይ ስለሚገኙ አዝዕርት ሁሉ እየተናገረ እንዳልሆነ ለመረዳት በሰከነ መንፈስ ማንበብ ብቻ በቂ ነው፡- “…እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለችበተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች…” በዚህ ቦታ “በተዘራች ጊዜ” እና “ከአትክልትም ሁሉ” የሚሉ ቃላትን በትኩረት ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ እነዚህ ቃላት እንደሚያስረዱት ንጽጽሩ ገበሬዎች ከሚዘሩት ዘር ጋር እንጂ ከሁሉም ዓይነት ዘር ጋር አይደለም፡፡ በምድረ እስራኤል የሚበቅለው በሳይንሳዊ ስሙ ብራሲካ ኒግራ (Brassica nigra) በመባል የሚታወቀው የጤፍ መጠን የምታክል ዘር ያለው የሰናፍጭ ዝርያ እስከ 3.7 ሜትር ያህል የመርዘም ሁኔታ ቢኖረውም ከምድር ዛፍ ሁሉ እንደማይበልጥ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ አንድ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን በምድረ እስራኤል የኖረ ሰው ከሰናፍጭ ዘር የሚያንሱ አዝዕርት መኖራቸውን ላያውቅ ይችላል ብንል እንኳ ከሰናፍጭ በላይ የሚረዝሙ ዛፎች መኖራቸውን ለማወቅ የማይችልበት ምንም ዓይነት ተዓምር የለም፡፡ ጌታችን ገበሬዎች በማሳቸው ውስጥ ስለሚዘሯቸው አዝዕርት እየተናገረ እንደሆነ በዚህ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ምናልባት እነዚህን ወገኖች ያሳሳታቸው “በምድር ካለ ዘር ሁሉ” የሚለው ሐረግ ነው፡፡ ነገር ግን የግሪኩን ንባብ ስንመለከት γῆς (ጌስ) የሚለው ቃል ምድርን በሞላም ሆነ የተወሰነውን ክፍል ለማመልከት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ቃሉ በጥቅሱ ውስጥ እርሻን ለማመልከት ጥቅም ላይ መዋሉን የሚያስረዱ ሌሎች ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፤ ለምሳሌ፡-

“ብዙ ጊዜ በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ መሬት (γῆς)፥ ለሚያርሱአትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል፥ ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና፡፡” (ዕብ. 6፡7)

“እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት (γῆς) ፍሬ ይጠብቃል።” (ያዕ. 5፡7)

“መሬት” እና “ምድር” የሚሉት ቃላት በአማርኛ እንኳ ስንመለከት ትርጉማቸው በአውድ የተወሰነ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ስለዚህ በጥቅሱ ውስጥ “ምድር” የሚለው ቃል መላውን ዓለም እንዲያመለከት እንድንደመድም የሚያስችል አውዳዊ ምክንያት የለንም፡፡

ስናጠቃልል ጌታችን በወቅቱ ሲሰሙት የነበሩትን ሰዎች ስለ መንግሥተ ሰማያት እነርሱ በሚያውቁት ምሳሌ እያስተማረ እንጂ ስለ ፍጥረተ ዓለም ትንታኔ እየሰጠ አይደለም፡፡ አነጋገሩም የዘመኑ ገበሬዎች በማሳቸው ውስጥ የሚዘሯቸውን አዝዕርት የተመለከተ እንጂ በመላው ዓለም ይቅርና በምድረ እስራኤል እንኳ የሚታወቁትን በሙሉ የሚያጠቃልል አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው ሙግት ቅንነት የጎደለውና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስህተትን የመፈለግ ቀቢፀ ተስፋዊ ጥረት ነው፡፡

ጥያቄ ለሙስሊሞች!

አሁን ደግሞ ተራው የናንተ ነውና ለተከታዩ ጥያቄያችን መልስ ስጡን፡፡

በቁርአን መሠረት ሁሉም ነገር የተፈጠረው ጥንድ ሆኖ ነው፡-

“እርሱም ያ ምድርን የዘረጋ በሷም ተራራዎችንና ወንዞችን ያደረገ በውስጧም ከፍሬዎች ሁሉ ሁለት ሁለት ዓይነቶችን ያደረገ ነው፡፡ ሌሊትን በቀን ይሸፍናል፡፡” (ሱራ 13፡3)

“ያ ምድር ከምታበቅለው ከነፍሶቻቸውም ከማያውቁትም ነገር ዓይነቶችን ሁሏንም የፈጠረ (አምላክ) ጥራት ይገባው፡፡” Exalted is He who created all pairs – from what the earth grows and from themselves and from that which they do not know. (ሱራ 36፡36)

“ትገነዘቡም ዘንድ ከነገሩ ሁሉ ሁለት (ተቃራኒ) ዓይነትን ፈጠርን፡፡” And of all things We created two mates; perhaps you will remember. (ሱራ 51፡49)

አብዱላህ ዩሱፍ አሊ የተሰኙ ሙስሊም ሊቅ ሁለተኛውን ጥቅስ ሲያብራሩት እንዲህ ብለዋል፡-

“ሁሉም ነገር ጥንድ ነው፤ የእፅዋትና የእንስሳት ፆታ… የማይታዩት የተፈጥሮ ኃይላት፣ ቀንና ሌሊት፣ ፖዘቲቭና ኔጌቲቭ የኤሌክትሪክ ሞገዶች…”

የአማርኛ ቁርአን የግርጌ ማስታወሻም ጥቅሱን በተመሳሳይ መንገድ ይተረጉመዋል፡፡

በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የቁርአን ደራሲ ሁሉም ነገር ጥንድ ሆኖ እንደተፈጠረ በመናገር መገለጡ መለኮታዊ አለመሆኑን ይፋ አውጥቷል፡፡ ባክቴርያን የመሳሰሉት ባለ ነጠላ ሴል ፍጡራን ተባዕታይና እንስታይ ፆታ የላቸውም፡፡ ብዙ የፈንገስ ዝርያዎችም ተመሳሳይ ተፈጥሮ አላቸው፡፡ ተቃራኒ ፆታ የሌላቸው በዓይን የሚታዩ ብዙ የእንስሳት ዝርያዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በኒው ሜክሲኮ የምትገኝ ዊብቴይል ሊዛርድ የተሰኘች የእንሽላሊት ዝርያ እንስታይ ፆታ ብቻ ያላት ስትሆን የራሷን ምስለኔ (Clone) ዕንቁላል በመጣል ራሷን ትተካለች፡፡ ብዙ የዕፅዋት ዝርያዎችም በውስጣቸውም ሆነ ከውጪ ወንዴና ሴቴ ተብሎ ሊፈረጅ የሚችል ፆታ እንደሌላቸው ይታወቃል፡፡ ታድያ የቁርአን ደራሲ መገለጡ ከሰማይ ከመጣለት ይህንን ሃቅ ማወቅ እንዴት ተሳነው?

መሲሁ ኢየሱስ