በግብፅ በደረሰ የሽብር ጥቃት 26 ክርስቲያኖች ሞተው 25 ቆስለዋል
አርብ ግንቦት 18 – 2009 በግብፅ አገር ካይሮ ከተማ አቅራብያ ታጣቂዎች ክርስቲያኖችን ጭኖ ሲኼድ በነበረ አውቶቡስ ላይ በከፈቱት ጥቃት ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ድረስ 26 ሰዎች ሞተው 25 መቁሰላቸው ተነግሯል፡፡ የዓይን እማኞች እንደተናገሩት ጥቃት አድራሾቹ ወደ 10 የሚኾኑ ወታደራዊ ልብስ የለበሱና ፊታቸውን በጭንብል የሸፈኑ ታጣቂዎች ናቸው፡፡ የጥቃቱ ሰለባ የኾኑት ክርስቲያኖች ወደ አንድ ገዳም እየተጓዙ ነበር ተብሏል፡፡
ለጥቃቱ እስከ አሁን ድረስ ኃላፊነት የወሰደ ቡድን ባይኖርም የግብፅ ክርስቲያኖች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይኤስ የተሰኘው እስላማዊ የሽብር ቡድን ጥቃት ዒላማ መኾናቸው ይታወቃል፡፡ ባለፈው ወር በሁለት አብያተ ክርስቲያናት ላይ የደረሱት የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶች ለ75 ሰዎች ሞትና ለብዙዎች መቁሰል ምክንያት መኾናቸው ይታወሳል፡፡