የአዲስ ኪዳን ቀኖና አመጣጥ
እውነታውና የሙስሊም ሰባኪያን ተረት
የኒቅያ ጉባኤና የአዲስ ኪዳን ቀኖና
ብዙ ሙስሊሞች የአዲስ ኪዳን ቀኖናን ጨምሮ መሠረታዊ የክርስትና አስተምሕሮዎች በኒቅያ ጉባኤ የተወሰኑ በማስመሰል ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሐሰን ታጁ የተሰኙ ሙስሊም ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-
“በኒቅያ ጉባኤ ላይ የመጻሕፍት ምርጫ የተደረገው በውይይት ላይ በመመሥረት ሳይሆን ድራማዊ በሚመስል ሁኔታ ነበር፡፡ የኒቂያን ጉባኤ በጥንቃቄ ስንመረምር ድራማዊ የሆኑ ነገሮችን እናገኛለን፡፡ 300 የሚደርሱ መጽሐፍ ቅዱሳን ከአዳራሽ ውስጥ ካለ ጠረጴዛ ስር እንዲቀመጡ ተደረጉ፡፡ አምላክ የወደደውን መጽሐፍ ከጠረጴዛው ላይ ያስቀምጥ ዘንድ ጳጳሳት ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልዩ እንዲያድሩ ታዘዙ፡፡ ጠዋት የአዳራሹ በር ሲከፈት በንጉሱ የምትደገፈው ጳውሎሳዊት ቤተክርስትያን የምትደግፋቸው መጽሐፍ ቅዱሳን ከጠረጴዛው ላይ ተገኙ፡፡ የዚያን ቀን የአዳራሽ ቁልፍ ከማን እጅ እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡”[1]
በኒቅያ ጉባኤ ላይ የመጻሕፍት ምርጫ መደረጉን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ታሪካዊ ማስረጃ የለም! መሰል ተረታ ተረቶችም ታሪካዊ መሠረት የላቸውም፡፡ በኒቅያ ጉባኤ የቅዱሳት መጻሕፍት ምርጫ መደረግ ይቅርና ርዕሱ እንኳ መነሳቱ ማስረጃ የለውም፡፡ ይህንን የተናገረም ሆነ እንዲህ ብሎ የጻፈ አንድም ሊቅ የለም፡፡ “የመጻሕፍት ምርጫ ተደርጓል፣ መጻሕፍት በጳጳሳት ትዕዛዝ ተቃጥለዋል፣ ወዘተ.” የሚለው ቅዠት የሙስሊም ሰባኪያንና የመሰሎቻቸው ፈጠራ ነው፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን ስለ ክርስትና ያላቸው መረጃዎች በእንዲህ ዓይነት አሉባልታዎች ላይ የተመሠረቱ መሆናቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ሐሰን ታጁን የመሳሰሉት ሙስሊም አስተማሪዎች ምሑራዊ ጥናቶችን በማድረግ ሕዝባቸው ትክክለኛ መረጃ ኖሮት ከክርስቲያን ጎረቤቱ ጋር ትርጉም ያለው ውይይት እንዲያደርግ ከማስቻል ይልቅ እንዲህ ዓይነቱን አርቲ ቡርቲ በማስተማር አለመግባባቱን ማክረራቸው ትዝብት ላይ ይጥላቸዋል፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድም ያስጠይቃቸዋል፡፡
የኒቅያ ጉባኤን ታሪክ ስንመለከት ቤተ ክርስቲያን ያለምንም ኦፊሴላዊ ጉባኤ ቀደም ሲል ተቀብላው የነበረው የኢየሱስ ፍፁም አምላክነት አርዮስ በተሰኘ የኑፋቄ አስተማሪ ተግዳሮት ስለገጠመው ጉባኤ መጥራት እንዳስፈለገ እንገነዘባለን፡፡ ጉባኤው ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያን የምታምነውን ትምሕርት በነገረ መለኮታዊ ቃላት ይበልጥ በማብራራት መግለጫ አወጣ እንጂ አዲስ ነገር አልፈጠረም፡፡ የጉባኤው ዋና ትኩረት የነበረውም ኢየሱስ ከአብ ጋር በባሕርይ አንድ ነው (Homoousion) ወይስ ተመሳሳይ (Homoiousion)? የሚል ጥያቄ ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማመሳከር ኢየሱስ በመለኮታዊ ባሕርዩ ከአብ ጋር አንድ ወይም የተካከለ መሆኑን ከተስማማ በኋላ ጉባኤው መግለጫ በማውጣት የአርዮስን ኑፋቄ አውግዟል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ታሪክ ፈጠራ ነው፣ ተረት ነው፣ መሠረተ ቢስ አሉባልታ ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች ቤተክርስቲያን በኒቅያ ጉባኤ አቋም ከያዘች በኋላ ከአስተምሕሮዋ ጋር የሚስማሙትን ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ መርጣለች ይላሉ፡፡ ሆኖም በ397 ዓ.ም. የተደረገው የካርታጎ ጉባኤ ቀደም ሲል አበው ለተቀበሏቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር ዕውቅናን ከመስጠት የዘለለ አዲስ ነገር አልፈጠረም፡፡ ከኒቅያ ጉባኤ በፊት (325 ዓ.ም. በፊት) የተጻፉ የአዲስ ኪዳንን የተለያዩ ክፍሎች የሚጠቅሱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የአበው ጽሑፎችና ሳምንታዊ ንባባት (Lectionaries) ይገኛሉ፡፡ ክርስቲያን ሊቅ የሆኑት ፕሮፌሰር ኖርማን ጌይዝለር እንደጻፉት ቅድመ ኒቅያ በአበው ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱትን ከ 36,289 በላይ ጥቅሶችን አንድ ላይ ብንቀጣጥል ከ11 ቁጥሮች (ከግማሽ ገጽ ያነሰ) በስተቀር ሁሉንም የአዲስ ኪዳን ክፍል መልሰን መጻፍ እንችላለን![2] ይህ የሚያሳየው መጻሕፍቱ ቀደም ሲል ተቀባይነት እንደነበራቸውና የኒቅያ ጉባኤም ሆነ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች በነዚህ ላይ ተመሥርተው የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ማስታወቃቸውን ነው፡፡ (አርዮስና ሰባልዮስን የመሳሰሉት መናፍቃን እንኳ ክርክራቸውን ያቀረቡት አሁን በእጃችን በሚገኙት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ በመመሥረት ነበር፡፡)
የአፖክሪፋ መጻሕፍትና ቀኖና
በሐዋርያትና በቀደሙት አማኞች ስም የተጻፉ የአፖክሪፋ መጻሕፍት ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ወዲህ መታየት መጀመራቸውንና በተባሉት ሰዎች የተጻፉ አለመሆናቸውን ለዘብተኛም ሆነ አጥባቂ የሥነ መለኮት ሊቃውንት ያለ ልዩነት በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት እውነታ ነው፡፡
የቀኖና ሒደት
የቀኖና ምርጫ በአንድ ጀንበር የተከናወነ አልነበረም፡፡ ክርስትና እጅግ ሰፊ በነበረው የሮም ግዛት ውስጥ በመሰራጨቱ ምክንያትና ከበረታው ስደት የተነሳ አንዳንድ መጻሕፍት በሁሉም ስፍራዎች አይታወቁም ነበር፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በመላው ክርስቲያን ማሕበረሰብ ዘንድ የተዳረሱት የስደቱ ዘመን ካበቃ በኋላ ሲሆን በጣም ርቀው ይገኙ የነበሩት የተሟላውን ቀኖና ለማግኘት ረጅም ጊዜ ወስዶባቸው ነበር፡፡ እያንዳንዱ የክርስቲያን ማሕበረሰብ መጻሕፍቱን ለመቀበል የየራሱን የማጣራት ሥራ ይሠራ ስለነበር አንዳንድ መጻሕፍት በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ ወጥ በሆነ ሁኔታ ተቀባይነትን አላገኙም ነበር፡፡ ይህም ደግሞ ሐዋርያዊ ሥልጣን የሌላቸው መጻሕፍት ሾልከው እንዳይገቡ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቋታል፡፡
የመጻሕፍት ዝርዝርና አቀባበል
በ170 ዓ.ም. የተጻፈው የሙራቶራውያን ቁርጥራጭ (The Moratorian Fragment) በመባል የሚታወቀው ጥንታዊ ጽሑፍ ደግሞ አራቱ ወንጌላት፣ አሥራ ሦስቱ የጳውሎስ መልዕክታት፣ የይሁዳ መልዕት፣ ሦስቱ የዮሐንስ መልዕክታትና የዮሐንስ ራዕይ በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እንደነበራቸው ይገልጻል፡፡[3] የቤተ ክርስቲያን ጸሐፌ ታሪክ የነበረው የቂሣርያው ኢዮስቢዮስ (265-340 ዓ.ም.) የቀኖና መጻሕፍትን በሦስት ከፍሎ አቅርቦ ነበር፡፡
- ቀኖናዊነታቸው ከጥርጣሬ በፀዳ ሁኔታ ተቀባይነት ያገኙ 22 መጻሕፍት ሲሆኑ እነዚህም አራቱ ወንጌላት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ የጳውሎስ መልዕክታት (ዕብራውያንን ጨምሮ)፣ 1ዮሐንስ፣ 1ጴጥሮስ እና የዮሐንስ ራዕይ ናቸው፡፡
- አምስቱ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበራቸው ሲሆን ጥቂቶች ብቻ ይጠራጠሯቸው ነበር፤ እነዚህም ያዕቆብ፣ ይሁዳ፣ 2ጴጥሮስ፣ 2ዮሐንስ እና 3ዮሐንስ ናቸው፡፡
- አምስቱ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ነበር፤ እነርሱም የሔርማሱ እረኛ፣ የጳውሎስ ሥራ፣ ራዕየ ጴጥሮስ፣ የበርናባስ መልዕክት[4] እና ዲዳኬ ናቸው (እነዚህ በአዲስ ኪዳን ቀኖና ውስጥ አልተካተቱም)፡፡[5]
በምስራቅ ሃያሰባቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በቀኖናዊነት ለመጀመርያ ጊዜ የጠቀሰው ቅዱስ አትናቴዎስ ሲሆን (367 ዓ.ም.) በምዕራብ ደግሞ በሂፖ ሬጊዩስ (አልጄርያ) (393 ዓ.ም.) እና በካርታጎ (ካርቴጅ) (397 & 419 ዓ.ም.) እነዚሁ መጻሕፍት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት የዮሐንስን ራዕይ የተቀበሉት ዘግይተው ሲሆን የሦርያ ቤተ ክርስቲያን 2ጴጥሮስ፣ 2ዮሐንስ፣ 3ዮሐንስ እና ይሁዳን ለመቀበል ከሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘግይታለች፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ርቃ የምትገኝ ስለነበረችና እነዚህ መጻሕፍት ስላልደረሷት ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ መጻሕፍቷን እንድታስታውቅ ያደረጓት የተለያዩ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ዋነኛው ምክንያት ግን ኑፋቄያዊ ቡድኖች የየራሳቸውን የመጻሕፍት ስብስብ ማዘጋጀታቸው ነበር፤ (ለምሳሌ ያህል መርቂያን/ ማርሲዮን)፡፡ [6]
የቀኖና መስፈርቶች
ክርስቲያኖች የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት በቀኖናዊነት ለመቀበል የተለያዩ መስፈርቶችን በጥንቃቄ ተጠቅመዋል፡፡ የመጀመርያው መስፈርት “ሐዋርያዊ ሥልጣን” የሚል ነበር፡፡ ይህም አንድ መጽሐፍ ተቀባይነት ማግኘት ያለበት በሐዋርያትና በቅርብ ወዳጆቻቸው የተጻፈ እንደሆነ ነው፡፡ ሉቃስና ማርቆስ ከሐዋርያት ጋር የቀረበ ግንኙነት ስለነበራቸው መጻሕፍታቸው ተቀባይነትን አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛው መስፈርት ደግሞ የመጻሕፍቱ ከሌሎች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጋር መስማማት ሲሆን ሦስተኛው መስፈርት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለተከታታይ ዘመናት ተቀባይነትን አግኝተው ጥቅም ላይ መዋላቸው ነው፡፡
ማጠቃለያ
የቀደሙት ክርስቲያኖች ቀኖናዊ መጻሕፍትን ለመለየት ጊዜ መውሰዳቸው ሐዋርያዊ ሥልጣን የሌላቸው መጻሕፍት ሾልከው እንዳይገቡ የነበራቸውን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህን መጻሕፍት በአንድ ጥራዝ የመሰብሰቡ ሒደት ጊዜ የወሰደ ቢሆንም ነገር ግን ተቀባይነት ያገኙት በአንድ ጀንበር አዋጅ ሳይሆን ከሐዋርያት ዘመን ተያይዞ በመጣ ሁኔታ ነበር፡፡
ጉባኤዎችም ሆኑ ግለሰቦች ቀኖናን አልፈጠሩም፡፡ ይልቁኑ እውነተኛ ቅዱሳት መጻሕፍት መሆናቸው በዘመናት ተፈትኖ ለተረጋገጡት መጻሕፍት ዕውቅናን ሰጡ እንጂ፡፡[7] ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ ሙስሊም ሰባኪያን የሌሉና ያልተደረጉ የፈጠራ ታሪኮችን በመጻፍ ክርስቲያኖችን ግራ ለማጋባትና የገዛ ሃይማኖታቸውን ህልውና ለማረጋገጥ ሲውተረተሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡
[1] ሐሰን ታጁ፡፡ የሐመረ ተዋሕዶን ቅጥፈት በእስልምና እውነት፣ ገፅ 45፡፡
[2] Norman Geisler. Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 532
[3] Norman Geisler and Shawn Nelson. Evidence of an Early New Testament Canon; 2015, pp. 50-51.
[4] የመካከለኛው ዘመን ፈጠራ ከሆነው የበርናባስ ወንጌል ጋር መምታታት የለበትም
[5] Bruce Metzger: The New Testament Its background and Content, Abingdon Press, 1982, p. 275
[6] Ibid. 276
[7] Ibid.
መጽሐፍ ቅዱስ