አንዱ እግዚአብሔርና አንዱ አስታራቂ

አንዱ እግዚአብሔርና አንዱ አስታራቂ

የሙስሊም ጥያቄ፡- 1ኛ ጢሞቴዎስ 2:5 ላይ “አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፥ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ” ይላል፡፡ አምላክ ስንት ነው? አንድ፤ እሱም እግዚአብሔር ነው፡፡ ኢየሱስስ? ጥቅሱ “በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ” ይላል፡፡ እርሱ ማነው? ከተባለ “እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ይላል፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር አንድ ከሆነና ኢየሱስ ደግሞ ሰው ከሆነ በምን ስሌት ነው ኢየሱስ የተባለውን ሰው አምላክ ልንለው የምንሞክረው? 

የአንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ትርጉም በትክክል ለመረዳት አጠቃላይ መረጃዎችን ማገናዘብ አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን መልእክት የጻፈው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ አምላክነት በሌሎች ቦታዎች ምን እንደተናገረ አስቀድመን እንመልከት፡፡ በሐዋርያው ትምሕርት መሠረት ኢየሱስ ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘለዓለም የተባረከ አምላክ ነው (ሮሜ 9፡5)፤ ታላቁ አምላክ ነው (ቲቶ 2፡13)፤ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ ክብሩን ጥሎ የመጣ ነው (ፊልጵስዩስ 2፡6)፤ የሁሉ ፈጣሪ ነው (ቆላስይስ 1፡16-17)፤ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነቱ ተገልጦ የሚኖር ነው፣ ይህ ማለት ኢየሱስ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው ነው ማለት ነው (ቆላስይስ 2፡9)፤ የሰው ልጆች ሁሉ አንድ ቀን በእግዚአብሔር የፍርድ ዙፋን ፊት ይቆማሉ (ሮሜ 14፡10) [በቀድሞ ትርጉም “ክርስቶስ” የተባለው በዋናው የግሪክ ጽሑፍ “ቴዎስ” (እግዚአብሔር) ይላል፡፡ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይመልከቱ]፤ የሰው ልጆች በፍርዱ ዙፋን ፊት የሚቆሙት ይህ እግዚአብሔር ኢየሱስ ነው (2ቆሮንቶስ 5፡10)፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሐዋርያው በብሉይ ኪዳን ለያሕዌ እግዚአብሔር የተነገሩትን ጥቅሶች በመውሰድ ለኢየሱስ መነገራቸውን ተናገሯል፤ ይህንን በማድረግም ኢየሱስ ያሕዌ እግዚአብሔር መሆኑን በግልፅ አሳይቷል፡፡ ተከታዮቹን ጥቅሶች ያነፃፅሩ፡- ሮሜ 10፡13 ከኢዩኤል 2፡32 ጋር፣ 1ቆሮንቶስ 2፡16 ከኢሳይያስ 40፡13 ጋር፣ 2ቆሮንቶስ 10፡17 ከኤርምያስ 9፡24 ጋር፡፡

ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱት የሐዋርያው ትምህርቶች ከግምት ውስጥ ሲገቡ ጠያቂያችን በጠቀሱት ጥቅስ ውስጥ ኢየሱስን “ሰው” ብሎ መጥራቱ አምላክ ብቻ አለመሆኑን ነገር ግን ሰውም ጭምር መሆኑን ለማስገንዘብ እንጂ አምላክነቱን አለመቀበሉን የሚያሳይ አይደለም፡፡ በእርግጥ ከእኛ ከሰብዓውያን ወገን ሆኖ ወደ አብ የሚያቀርበን ባሕርዩ ሰብዓዊነቱ በመሆኑ ምክንያት በጥቅሱ ውስጥ አፅንዖት ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ ሰው መሆኑን ተናገረ እንጂ ሰው ብቻ መሆኑን በመናገር በሌሎች ቦታዎች ላይ ስለ አምላክነቱ የተናገራቸውን ነጥቦች አልተጣረሰም፡፡ በጥቅሱ ውስጥ አንድ እግዚአብሔር ተብሎ የተጠቀሰው ፍጥረትን በመዋጀት ሒደት ውስጥ ልጁን የላከልንና መሥዋዕትነቱን የተቀበለው እግዚአብሔር አብ ነው፡፡ ሐዋርያው በሌላ ቦታ ኢየሱስን “አንድ ጌታ” ብሎ መጥራቱ አብ ጌታ አለመሆኑን እንደማያሳይ ሁሉ አብንም አንድ እግዚአብሔር በማለት መጥራቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር አለመሆኑን አያሳይም (1ቆሮንቶስ 8፡6፣ ኤፌሶን 4፡5)፡፡ ለምሳሌ ያህል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አብ መንፈስ መሆኑ ተነግሮናል (ዮሐንስ 4፡23)፤ ወልድም መንፈስ መሆኑ ተነግሮናል (2ቆሮንቶስ 3፡17)፡፡ ነገር ግን በሌላ ቦታ ላይ አንድ መንፈስ (መንፈስ ቅዱስ) ብቻ መኖሩ ተጽፏል (ኤፌሶን 4፡5)፡፡ “አንድ”፣ “ብቸኛ”፣ “ከሁሉ በላይ”፣ “ታላቁ”፣ ወዘተ. የሚሉት ልዩ መሆንን የሚያመለክቱ አነጋገሮች (Exclusive Languages) ለሦስቱም የሥላሴ አካላት በተናጠል ሊነገሩ የሚችሉ ሲሆኑ ሌላውን ያገለሉ አይደሉም፡፡



ጥያቄ ለሙስሊሞች

ቁርኣን ማንም ለማንም አማላጅ መሆን እንማይችል ይናገራል፡-

የእስራኤል ልጆች ሆይ! ያችን በናንተ ላይ የለገስኳትን ጸጋዬንና እኔም በዓለማት ላይ ያበለጥኳችሁ (አባቶቻችሁን በጊዜያቸው ከነበሩት ዓለማት ያበለጥኩዋቸው) መኾኔን አስታውሱ፡፡ (ማንኛዋ) ነፍስም (ሌላዋ) ነፍስ ምንንም የማትመነዳበትን ከርሷም ምልጃን የማይቀበሉባትን ከርሷም ቤዛ የማይያዝበትን፣ እነርሱም የማይረዱበትን ቀን ተጠንቀቁ፡፡” (ሱራ 247-48)

የእስራኤል ልጆች ሆይ! ያችን በናንተ ላይ የለገስኳትን ጸጋዬንና እኔም በዓለማት ላይ ያበለጥኳችሁ መኾኔን አስታውሱ፡፡ (አማኝ) ነፍስም (ከሓዲ) ነፍስ ምንንም የማትጠቅምበትን፣ ከርሷም ቤዛ የማይወሰድበትን፣ ምልጃም ለርሷ የማትጠቅምበትን፣ እነርሱም የማይረዱበትን ቀን ተጠንቀቁ፡፡” (ሱራ 2122-123)

የአማርኛ ተርጓሚዎች በቅንፍ የጨመሯቸው ቃላት ዓላማ እዚህ ጋ ግልፅ አይደለም፡፡ ያለ ብዥታ መልእክቱን ለመረዳት በእንግሊዘኛ ትርጉም እናንብበው፡- “And fear a Day when no soul will suffice for another soul at all, and no compensation will be accepted from it, nor will any intercession benefit it, nor will they be aided.”

ከዚያም የፍርዱ ቀን ምን እንደኾነ ምን አሳወቀኽ? (እርሱማንኛይቱም ንፍስ ለሌላይቱ ነፍስ ምንም ማድረግን የማትችልበት ቀን ነው። ነገሩም ሁሉ በዚያ ቀን አላህ ብቻ ነው።” (ሱራ 8218-19)

“ምንም ማድረግ የማትችልበት ቀን” የሚለውን ልብ ይሏል፡፡ ይህ ምልጃን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር ያጠቃልላል፡፡

ነገር ግን በቁርኣን መሠረት የማማለድ መብት ያለው አላህ ብቻ ነው፤ ከእርሱ ውጪ ሌላ አማላጅ የለም፡-

እነዚያንም ሃይማኖታቸውን ጨዋታና ላግጣ አድርገው የያዙትን ቅርቢቱም ሕይወት ያታለለቻቸውን ተዋቸው፡፡ በእርሱም (በቁርኣን) ነፍስ በሠራችው ሥራ እንዳትጠፋ አስታውስ፡፡ ለእርሷ ከአላህ ሌላ ረዳትና አማላጅ የላትም በመበዢያም ሁሉ ብትበዥ ከርሷ አይወሰድም፡፡ እነዚህ እነዚያ በሠሩት ሥራ የተጠፉት ናቸው፡፡ ለነሱ ይክዱ በነበሩት ምክንያት ከፈላ ውሃ መጠጥና አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡” (ሱራ 670)

አማላጅ ማለት በሁለት ወገኖች መካከል ሆኖ የሚያስታርቅ አስታራቂ ማለት ነው፤ ስለዚህ ምልጃ ቢያንስ ሦስት ወገኖችን የሚያሳትፍ ነው፡- የሚማለድ፣ የሚማልድ፣ የሚማለድለት፡፡ በክርስቲያኖች እምነት መሠረት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር በመምጣት በመስቀሉ ቤዛነት ከአብ ጋር አስታርቆናል፡፡ ይህ ምልጃ አንድ ጊዜ የተፈጸመ ሲሆን ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ ለሚፈልጉት ሁሉ ሕያው ሆኖ የሚኖር ሥራ ነው፡፡ በክርስቲያኖች እምነት መሠረት እግዚአብሔር ሥላሴ ሲሆን ሁለተኛው የሥላሴ አካል ኢየሱስ አምላክም ሰውም ነው፤ ስለዚህ እኛን በመወከል ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርበን ይችላል፡፡ በእስልምና መሠረት ግን አላህ በአንድነቱ ውስጥ ብዝሐነት የሌለበት ሌጣ አንድ ነው፡፡ ቁርኣን ግን አላህ የሙስሊሞች አማላጅ እንደሆነ ስለሚናገር ሌጣ አንድ ከመሆኑ አንጻር ከማን እንደሚያማልድ ሙስሊም ወገኖቻችን ሊነግሩን ይችላሉ?

ብቸኛ እውነተኛ አምላክ – ኢየሱስን ያገለለ ነውን?

መሲሁ ኢየሱስ