እስላም እና ክርስትና ንጽጽራዊ አቀራረብ – ለዶ/ር ሙሐመድ ዓሊ አልኹሊ የተሰጠ ምላሽ – ክፍል አንድ

እስላም እና ክርስትና – ንጽጽራዊ አቀራረብ 

የመጽሐፍ ሒስና ግምገማ

ዘላለም መንግሥቱ

ደራሲ፥ ዶ/ር ሙሓመድ ዓሊ ኣልኹሊ

ትርጉም፥ አይታወቅም

አሳታሚ፥ ሑዳ ፕሬስ ሊሚትድ

የገጽ ብዛት፥ 91 

የኅትመት ዘመን፥ 1989

ክፍል አንድ

መጽሐፍ ቅዱስን ለማንቋሸሽ ሙስሊሞች የሚጽፉአቸው የሚያስተዛዝቡ ብቻ ሳይሆኑ ጸሐፊዎቹንም የሚያሳፍሩና ሃይማኖታቸውንም የሚገልጡ ነገሮች አሉ። በአንድ ወገን ሃይማኖቱ አይሁድንና ክርስቲያኖችን ‘የመጽሐፉ ሰዎች’ ብሎ በመጥራት ሰዎቹንም መጽሐፋቸውንም የሚያከብር ሲመስል በሌላ ጎኑ ደግሞ በሰዎቹም በመጽሐፋቸውም ላይ የሚስለው ስዕል አስጠያፊ ነው።

ይህን ሒስና ግምገማ በአንድ አጭር መጣጥፍ መጨረስ ሲቻል ከአንድ በላይ በሆኑ መጣጥፎች በተከታታይ ለመጻፍ የፈለግኩት ለሚነሡት ተመሳሳይነት ላላቸው ነገር ግን መሠረተቢስ ለሆኑ መከራከሪያዎች ምላሽ ለመስጠትና ክርስቲያኖች በእነርሱ ስላለ ተስፋ ለሚጠይቁአቸው መልስ ለመስጠት የተዘጋጁ እንዲሆኑ ለማድረግና ለማስተማር ሙስሊሞች ደግሞ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ ተስፋ በማድረግና በጸሎት ነው።

ስለ ኢስላም ትክክለኛውን መልክ ማግኘት የምንችለው ከሌላ ከምንም ሳይሆን ከራሱ ከቁርኣን ነው። ሙስሊሞችን በወንጌል ለመድረስ ወይም ለጥያቄዎቻቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽ ለመስጠት ቁርኣንን እና ከተቻለ ተጓዳኝ የሆኑትን የሐዲስ ጽሑፎች ማንበብ አስፈላጊ ነው። በዚህና ቀጣይ መጣጥፎች ስለ ቁርኣንና የሐዲስ ጽሑፎች ረጂ ምንጮችንም አመለክታለሁ።

በዚህ እስላም እና ክርስትና (ንጽጽራዊ አቀራረብ) በተሰኘ መጽሐፍ የጸሐፊው ምሑርነት የተማሩቱ ሙስሊሞች እንዴት ክርስትናንና መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚመለከቱት ስለሚያሳይ ናሙና መጽሐፍ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ። መጽሐፉ የምርምርና ሌሎችን የመጥቀስ፥ ዋቤዎችን የማማከርና የምንጭ ጥናት የማድረግ ሙከራም ሆነ አዝማሚያ አይታይበትም። ደራሲው በራሱ ተማምኖ ስለሚያውቀው ነገር የሰማውን ብቻ የጻፈ ይመስላልና ክርስቲያናዊም ሆኑ እስላማዊ ምንጮችን አይጠቅስም። ስለዚህ የጅምላ ርችት በመተኮስ የማስበርገግ አዝማሚያ ይታይበታል። ይህ መጽሐፍ አንድ ደራሲ ጥንቃቄና በቂ ጊዜ ወስዶ መጻሕፍትን አገላብጦና መርምሮ የጻፈው ሳይሆን ለአንድ የክፍል ተማሪዎች ወይም የጉባኤ አድማጮች የተናገረው ንግግር ወደ ክርስቲያኖች እንዲያነጣጥር ተደርጎ ወደ ጽሑፍ የተመለሰና የታተመ ይመስላል። ስለዚህ ዝግጅቱ ለንግግሩ ወይም ለስብከቱ ብቻ የተዘጋጀበት እንጂ ከዚያ ያለፈ አይመስልም።

50 ሺህ ስሕተቶች!

ይህንን መጽሐፍ ብዙ መጽሐፎችን ከማንበቤ በፊት በመጀመሪያ እንደማደርገው በችኮላ ስሮጥበት እንዳነብ ያነሳሱኝን ጥቂት ነጥቦች አየሁ። አንዱና ትልቁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 50ሺህ ስሕተቶች መኖራቸውን በድፍረት የሚናገረው ክፍል ነው። ዶ/ር ሙሐመድ ዓሊ አልኹሊ በዚህ መጽሐፉ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 50ሺህ ስሕተቶች ስለ መኖራቸው ሲያትት፥ “ክርስቲያን ምሑራን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ30,000 እስከ 50,000 የሚደርሱ በጣም ብዙ ስሕተቶች እንዳሉት አምነው ይቀበላሉ” ብሎአል።[1] እዚህ ላይ በትዝብትም ቢሆን መስተዋል ያለባቸው ነገሮች አሉ። ሰውየው ዶክተር ነው፤ የምንም ነገር ዶክተር ቢሆን ይህ ማዕረግ የመማሩ ምልክት ነው፤ የክብር ሽልማት ካልሆነ በቀር። የተማረ ሰው ከ30ሺህ እስከ 50ሺህ የሚባል አኀዝ ሲጠቀም ይደንቃል። በነሲብ የተወሰደ ቁጥር መሆኑን የ20,000 ልዩነት ማቀፉ ይገልጠዋል። 40ሺህ 1መቶ 12 አላለም። ከ30-50ሺህ!

ሌላው ይህን ያህል ስሕተት እንዳሉበት የሚያምኑና የሚቀበሉት ክርስቲያን ምሑራን መሆናቸው ነው። ታዲያ መጽሐፋቸው 5 እፍል ስሕተቶች አለበት እያሉም “ክርስቲያን ናቸው” ነው የሚለን? ምኑን ክርስቲያን ሆኑት? “መጽሐፉን ከነስሕተቱ አምነው ይቀበሉታል” ነው የሚለን? ወይስ ስሕተቶቹን ቆጥረው እስኪጨርሱ ክርስቲያን ሆነው ሲጨርሱ ሰለሙ ማለቱ ነው? በደፈናው ‘ክርስቲያን ምሑራን’ ይበል እንጂ ምንጩን በመጥቀስ፥ ማን ክርስቲያን ምሑር ይህንን እንዳለና እንዳመነ መጻፍ ነበረበት። ይህ ሰው ይህንን ሲጽፍ ወይ ሲሉ የሰማውን በመድገም በየዋኅነት ተሳስቶ ነው ወይም ሆን ብሎ ፈጥሮ በመዋሸት ነው። በግልጽ እንደሚታወቀው ይህ የተፈጠረ ቅጥፈት ነው። በስንፍና የተደገመም ሆነ ለማሳት የተፈጠረ ቢሆን ሁለቱም ወንጀል ነው።

ደህና! ይባልና 50ሺህ ስሕተቶች አሉ ቢባል፤ ይህ ሁሉ ስሕተት ግን ከምን ውስጥ ነው የወጣው? ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው? ይህ እኮ ከበግ ግልገል ውስጥ አውራሪስ እንደማውጣት ነው! እንዴት ተባዝቶ ነው 50ሺህ የሆነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብሉይ 929፥ በአዲስ 260 በጠቅላላ 1,189 ምዕራፎች ሲኖሩ የጥቅሶቹ ቁጥር ብሉይ 23, 145 አዲስ 7, 958 በጠቅላላ 31, 103 ነው። ይህ ማለት እንግዲህ እያንዳንዱ ጥቅስ ውስጥ አንድ ስሕተት ኖሮ ወደ 19ሺህ በሚያህሉት ጥቅሶች ውስጥ ደግሞ በእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ስሕተት አለ ማለት ነው። ይህ ስሕተት እነርሱ ለቁርኣን ማጠንከሪያ፥ ማለት፥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቁርኣን ይናገራል፤ ስለ ሙሐመድም ይናገራል ብለው በድፍረት የሚወስዱአቸውንና የሚጠቅሱአቸውን ጥቅሶችም የሚጨምሩ ናቸው። ለምሳሌ፥ ጌታ ስለ መንፈስ ቅዱስ (ስለ አጽናኙ) የተናገረው ስለ ሙሐመድ የተናገረው ትንቢት ነው ይላሉ። እና ይህ ከ50ሺህ ስሕተቶች ውስጥ ያልተነከረ መሆኑን እንዴት አውቀው ነው የሚጠቅሱት? እንዴትና በምን ሳሙና አጥበውና አንጽተው ነው ይህንና ይህን የመሰሉትን የሚጠቅሱአቸው? ወይስ ሊበሉ የከጀሏትን አሞራ ጅግራ ይሏታል እንደሚባለው ነው? ለነገሩ ሊጠቅሱ የፈለጉትን አንቀጽ ያልተበላሸ ነው ለማለት ከጥቂቶቹ በቀር መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ የተበላሸ የሚያስመስሉበት ልማድ አላቸው።

የኦርጂናሌዎች መጥፋት!

ደራሲው በመጀመሪያው ምዕራፍ አራቱን ወንጌላት በመደዳው የተሳሳቱ አድርጎ ይፈርጃቸዋል። ስለ ማቴዎስ እንዲህ በማለት ወደ ሌሎቹ ወንጌሎች ይተላለፋል (ገጽ 1)፤

“ማቴዎስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ወይም ሐዋርያ ነው። ወንጌሉን የጻፈው በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲሆን እሱ የጻፈው የመጀመሪያው ኢሪጂናል ቅጂ ጭራሹኑ ጠፍቷል። ዛሬ ያለው ቅጂ የዚያ የጠፋው ቅጂ ትርጉም ብቻ ነው። በመሆኑም ዛሬ የሚገኘው የማቴዎስ ወንጌል ኢሪጂናል ቅጂው የጠፋ በመሆኑ ምክንያት ያን ጊዜ ማቴዎስ ከጻፈው ጋር ተመሳሳይ ስለመሆኑ ማንም ማረጋገጥ አይችልም።”

ይህ ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስን፥ በተለይም አዲስ ኪዳንን፥ ላለመቀበል የሚያቀርቡት ዋና መከራከሪያ ነው። ስለዚህ ለመጽሐፉ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው አሳብ ምላሽ አቀርባለሁ። በመጽሐፉ ውስጥ ለምሳሌ፥ የማቴዎስ ወንጌል ኦሪጂናሉ ጭራሹኑ ጠፍቶአልና አሁን ያለው ከመጀመሪያው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ማረጋገጥጥ አይቻልም ይላል። ይህ በጣም ደካማ መከራከሪያ ነጥብ የሚሆነው ከሌለ መነሻ ስለሚነሣ ነው። ይህን ደካማ መከራከሪያ ነጥብ የሚያነሡት ለማቴዎስ ወንጌል ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጭምር ነው።

ወንጌል ተጽፎ ሲነበብና ሲተላለፍ ከኖረ ከ7 እና 800 ዓመታት በኋላ ጠፋ እንዴት ይባላል? በጤናማ አእምሮ ከታሰበ እኮ ጠፋ የሚባለው ነገር በመጀመሪያ የነበረ መሆኑ ተረጋግጦ ነው። ለምሳሌ፥ ሰው በዝግመት ከዝንጀሮ መጣ እንጂ በቀጥታ አልተፈጠረም የሚሉ ሰዎች ትምህርታቸውን መንፈሳዊ ለማስመሰል ፈለጉ እንበልና፥ “እግዚአብሔር በመጀመሪያ ዝንጀሮን ፈጠረና ያ ዝንጀሮ በዝግመት ሰው እንዲሆን አደረገ” ቢሉ፥ “ይህን ከየት አገኛችሁ?” ተብለው ሲጠየቁ፥ “በመጀመሪያ ሙሴ የጻፈው መጽሐፍ ጠፍቶአል እንጂ እዚያ የጠፋው ጽሑፍ ውስጥ እንደዚያ ነው የሚለው” ቢሉ እንደማለት ነው። የውሸቱ ማረጋገጫ እንዳይመጣ የሚጠሩት ምስክር የለም። ያለውን ምስክር አመለካከታቸውን ወይም ትምህርታቸውን ውሸት ስላደረገው ያልተሳሳቱ ለመሆን ምክንያት መፍተር ኖረባቸው። ነባሩን እውነት ውሸታም ነው ማለት ደግሞ አዲሱን ውሸት እውነት አያደርገውም።

ይህ ከሕግ አንጻር ኢ-ፍትሐዊ መከራከሪያ ነው። ‘አብጤን የገደለው ጎንጤ ነው፤ ማንም አላየውም እንጂ እርሱ ነው ገዳዩ’ ቢባል ማስረጃ የሚሆኑ ነገሮች በሙሉና በዝርዝር እንዲቀርቡ ሕግ ያስገድዳል። ዳኛውም መጠየቅ አለበት። ያለዚያ ፍትህ አልባ ፍርድ ሊበየን ነው። ወንጌል ጠፋ ለሚሉትም መቅረብ ያለበት ዋና ይህ ጥያቄ ነው። ምስክር የማይጠሩት ወንጀለኛው እጅ ከፍንጅ ሲያዝ ብቻ ነው። ለዚያውም እጅ ከፍንጅ የሚይዘው ሊኖር ይገባል። ወንጌል ወይም አዲስ ኪዳን ለመጥፋቱ ማረጋገጫ ብለው የሚያቀርቡት ምንድርነው? የጠፋውን ቅራፊውን ወይም ቅዳጁን ወይም የተደበቀውን ከዋሻ ውስጥ አገኙት? ይህ ውኃ የማያነሣ መከራከሪያ ነው።

እሺ ጠፋ እንበልና ኢንጂል (ወንጌል) ጠፍቶአል ለተባለው “የለም አልጠፋም፤ ይኸው” የሚል ከኖረ ማን ነው መታመን ያለበት? ጠፋ የተባለውን ኤግዚቢት በእጁ ይዞ ያቀረበው ሰው ነው ወይስ ለመጥፋቱም ማረጋገጫ የሌለው በደፈናው ‘ጠፍቷል’ ብቻ እያለ የሚናገረው? ከጠፋ መቼ ጠፋ? እንዴት ጠፋ? መጥፋቱ እንዴት ታወቀ? ወይም ለመጥፋቱ ምን ማረጋገጫ ተገኘ?

‘መጥፋቱ’ የታወቀው ያለው ወንጌል (አዲስ ኪዳን) ከ600 ዓመታት በኋላ ከተጻፈው ከቁርኣን የተለየ ስለሆነ ይህንን አዲሱን ትክክል ለማድረግና ያኛውን ወንጀለኛ ለማድረግ ነው? አንድ ጽሑፍ ከርሱ በፊት ከተጻፈው የተለየና የተበላሸ ነው የሚባለው ዋናው ወይም ቢያንስ የዋናው ቁራጮች ተገኝተው ከዚያ በኋላ ከተፈጠረው ‘ተበላሸ’ የተባለው ጋር ተነጻጽረው መሆን የለበትም? ታዲያ ይህ ተደርጎ ነው አሁን ያለው አዲስ ኪዳን የተበላሸና የተለወጠ ነው የተባለው? ይህ ለመደረጉ ማስረጃ አለው? ወይስ ቁርኣን ከአዲስ ኪዳን ጋር ስላልተስማማ ቁርኣን ሊሳሳት አይገባውምን የተሳሳተው ቀድሞ የተጻፈው አዲስ ኪዳን ነው ለማለት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በመጽሐፉ ውስጥ አልተነሱም፤ አልተመለሱምም።

በሙሐመድ ዘመን አንድ ወንጌል (ማቴዎስ) ብቻ ወደ ዐረብ ቋንቋ መተርጎሙን ታሪክ ያወሳል እንጂ ሙሉ አዲስ ኪዳን ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ሙሐመድ በሚናገረው በዐረብኛ ቋንቋ አልተተረጎመም። የዐረብኛ አዲስ ኪዳን በዚያን ዘመን አልነበረም። አዲስ ኪዳን በዚያ ቋንቋ የተተረጎመው ከሙሐመድ ዘመን በኋላ ነው። እርግጥ አረቢኛ ተናጋሪ ክርስቲያኖች ነበሩ ይጠቀሙ የነበረው አዲስ ኪዳን ግን የግሪኩን፥ የሱርስቱን፥ ወይም የቅብጡን ነው። በጣም ጥንታዊ ተብሎ የሚታወቀው የዐረብኛ መጽሐፍ ቅዱስ በ19ኛው መቶ የተገኘውና በሲና ገዳም ያለው ነው። ይህ የተተረጎመው በ867 ዓ. ም. ነው። ስለዚህ በሙሐመድ ዘመን የዐረብኛ አዲስ ኪዳን ከሌለ ከሙሐመድ ዘመን (570-622) እስከ 9ኛው ምዕት ዓመት መጨረሻ የነበሩት ዐረብኛ ተናጋሪዎች አዲስ ኪዳንን የሚያውቁት በስማ በለው ነው። ይህ ከሆነ እንኳን ስለመሳሳቱ የማስረዳት ችሎታቸውን ቀርቶ ስለሚያስተምረው ነገር እንኳ ያለቻቸውን ትንሽ እውቀትም መገመት አይከብድም።

ሌላው አስገራሚ ነገር ይህ ተሳሳተ የሚባለው ትምህርት የኋላ ትምህርት ነው እንጂ ሙሐመድም እንኳ ተሳሳተ ብሎ አልተናገረም። ሙሐመድ የክርስቲያኖች እና የአይሁድ መጽሐፎች የጎደፉ፥ የተበላሹ፥ የተበረዙ እንደሆኑ አልተናገረም። እነዚህ ጠፉ፥ ጎደፉ፥ ተበረዙ እያሉ የሚናገሩት በኋላ በኋላ መጽሐፉ ከክርስቲያኖቹ እና ከአይሁድ መጽሐፍ ጋር መጋጨቱን ሲያስተውሉ ለዚያ ምላሽ ለመፈለግ በማለት ቁርዓኑ እንከን የለበትም ለማሰኘት የተሳሳተው ቁርዓኑ ሳይሆን ቀድሞ የተጻፈው መጽሐፍ ነው ማለት ጀመሩ። እንጂ ሙሐመድ ተሳስቶአል አላለም። አለማለቱ ግን እርሱን ትክክል አያደርገውም። ቆይቶ ተሳስቶአል ካለና ሌሎቹም ይህን ካሉ ደግሞ እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር ለመኖሩ ይህ ማስረጃ ነው። ቁርኣን የአይሁድ መጽሐፍና የክርስቲያኖች መጽሐፍ ትክክል መሆኑን ይናገራል። እግዚአብሔር እንዳወረደውም ይላል። አይሁድና ክርስቲያኖችም የመጽሐፉ ሰዎች ተሰኝተዋል። በሱረቱ አል ዒምራን እንዲህ ይላል፤

3፥3-4 ከርሱ በፊት ያሉትን መጻሕፍት የሚያረጋግጥ ሲኾን መጽሐፉ (ቁርኣንን) ባንተ ላይ ከፋፍሎ በውነት አወረደ። ተውራትንና ኢንጂልንም አውርዷል።

(ከቁርኣን) በፊት  ለሰዎች መሪ አድርጎ (አወረዳቸው) ፉርቃንንም አወረደ፤ እነዚያ በአላህ ታአምራቶች የካዱ ለነርሱ ብርቱ ቅጣት አላቸው፤ አላህንም አሸናፊ የመበቀል ባለቤት ነው።

ይህ የሚያስረዳን ሙሐመድ በነበረበት ጊዜ የነበሩትን የአይሁድ እና የክርስቲያኖች መጻሕፍት (ተውራት ኦሪት ሲሆን ኢንጂል ወንጌል ነው) ትክክል መሆኑን መቀበሉን ነው። በረዙት፥ ቀየጡት፥ አትቀበሉት ብሏል? አላለም። ታዲያ ምነው ያኔ የተቀበለውን ኋላ ያልተቀበለው? ዛሬስ ምነው የማይቀበሉት?

ከሙሐመድ ዘመን በፊት የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ሙሐመድ በኖረበት ዘመን ከነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ወይም ዛሬ ካለው ጋር ለውጥ የለውም። (ይህ በተለያዩ ቋንቋዎች የተተረጎሙትን ትርጉሞችን ሳይሆን በዋናው ቋንቋ የተጻፈውን ነው) የአሁኑና የያኔው በፍጹም አንድ ነው። ያኔ የነበረው ዛሬ ባለው መልኩ እንደነበረ የቁጥሩ መብዛት እስኪያንገደግድ ድረስ እጅግ ብዙ ማስረጃዎች ይገኛሉ። የአዲስ ኪዳን ተጨባጭ ማስረጃዎች ቁጥር ከ25 ሺህ በላይ የጽሑፍ ቁራጮች፥ የብራና ገጾች፥ የብሉይ ኪዳን ጥቅልሎች ወዘተ፥ ናቸው። ሙሐመድ የኖረው በ7ኛው ምዕት ዓመት ሲሆን በዚያን ዘመን የነበሩ ጽሑፎችም ይገኛሉ። እነዚያ ከሙሐመድ ዘመን በፊት የበሩትና አሁን ያሉት ልዩነት እንደሌላቸው አሁን ያለውን መጽሐፍ ቅዱስ ከዚያ ዘመኑ ጋር ማነጻጸር ይገልጠዋል። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ የቀድሞው ከአሁኑ ጋር ተመሳሳይነቱን የሚያስረዱ አጥጋቢ ማስረጃዎች ያሉት ሌላ ጥንታዊነት ያለው መጽሐፍ በታሪክ ውስጥ የለም። አስተያይቶ አለመለወጡን ማረጋገጥ ይቻላል።[2] አሁን የሚነበበው መጽሐፍ ቅዱስ በሙሐመድ ዘመን ወይም ከዚያ በፊት ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ስለመሆኑ የሚያረጋግጡ መቶ ወይ አምስት መቶ አይደለም፤ ሃያ አምስት ሺህ ሲደመር ማስረጃዎች አሉ።

በተለይ በጣም ግልጽና ታዋቂ የሆኑ ሦስት ጥራዞችን በአስረጅነት ምጥቅስ ይቻላል። እነዚህ ጥራዞች Codex Alexandrinus፥ Codex Sinaiticu፥ እና Codex Vaticanus የተባሉት ናቸው። እነዚህ የመጀመርያው በ5ኛው መቶ ሁለቱ ደግሞ በ4ኛው መቶ የተጻፉ በብሪቲሽ እና በቫቲካን ቤተ መጻሕፍት የሚገኙ ድንቅ ሰንዶች ናቸው። ይህ የሚያረጋግጠው በሙሐመድ ዘመን የነበረውና እርሱ የመጽሐፉ ሰዎች ብሎ የጠራቸው አይሁድና ክርስቲያኖች ያኔና እንዲሁም ከእርሱ 200 ዓመታት ቀደም ሲልም ይጠቀሙበት የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ከዛሬው ምንም ልዩነት የሌለው መሆኑን ነው። እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትም ያልተለወጡ መሆናቸውን የሚያሳዩ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም (Septuagint) እና ባለፈው ምዕት ዓመት አጋማሽ ሙት ባሕር አጠገብ ከሚገኝ ዋሻ የተገኙት The Dead Sea Scrolls፥ በ4ኛው መቶ ወደ ሮማይስጥ የተተረጎመው የላቲን መጽሐፍ ቅዱስ፥ የዕብራይስጥ መዞራውያን ትርጉም (The Hebrew Massoretic Text)፥ እነዚህ በሙሉ ድርብርብ ምስክሮች ናቸው። በጤናማ አእምሮ ማንም ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም አዲስ ኪዳን ከሙሐመድ ዘመን በኋላ ተለወጠ ብሎ ለመናገር አይደፍርም።

ተሳሳተ ተለወጠ ከተባለ ይህ መቼም ትልቅ ክስ ወይም ትልቅ ሐሰት ነው። ክስ ከሆነ ምስክር ያስፈልገዋል። ሐሰት ከሆነም ሐሰት መሆኑን የሚያስረዳ እውነት የሆነ ማስረጃ ያስፈልገዋል። የቀደመው መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ካለው የተለየ ነው ከተባለ ግምት ብቻ መሆን የለበትም። ለመሳሳቱ መረጃ መቅረብ አለበት። ወይም ዋናው ነው የሚሉትን አቅርቦ፥ “ይኸው ዋናው ይህን ይላል፤ የእናንተ ከዘመናት በኋላ የመጣው ወይም ጳውሎስ የበረዘው ይህን ይላል” ብለው የሚነጻጸርበትን ማቅረብ ይጠበቃል። ያለዚያ ግምታዊና ነሲባዊ ሥራ አይሆንም? ይሆናል።

በሱረቱ ዩኑስ ቁጥር 94-95 የተጻፈው በዚያን ጊዜ በእጃቸው የነበረውን ወይም አይሁድና ክርስቲያኖች ያነብቡ የነበረውን መጽሐፍ የጥርጣሬያቸው ማስወገጃ መሆኑን የሚናገር መጽሐፍ መሆኑን ነው።

10፥94 ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትኾን እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ፤ እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል፤ ከተጠራጣሪዎቹም አትኹን። 95 ከእነዚያም የአላህን አንቀጾች ከአስተባበሉት አትኹን፤ ከከሳሪዎቹ ትሆናለህና።

ሌላ ለመጨመር

5፥47 የኢንጅልም ባለቤቶች በውስጡ አላህ ባወረደው ሕግ ይፍረዱ፤ አላህም ባወረደው የማይፈርድ ሰው፣ እነዚያ አመጠኞች እነርሱ ናቸው።

5፥68 እላንተ የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! ተውራትንና ኢንጅልን፣ ከጌታችሁም ወደናንተ የተወረደውን እስከምታቆሙ (እስከምትሠሩባቸው) ድረስ በምንም ላይ አይደላችሁም በላቸው፤ ከጌታህም ወደ አንተ የተወረደው ቁርኣን ከነሱ ብዙዎቹን ትዕቢትንና ክሕደትን በእርግጥ ይጨምርባቸዋል፤ በከሐዲያን ሕዝቦችም ላይ አትዘን።

6፥114 እርሱ ያ መጽሐፉን የተብራራ ኾኖ ወደእናንተ ያወረደ ሲኾን «ከአላህ ሌላ ዳኛን እፈልጋለሁን» (በላቸው)። እነዚያም መጽሐፍን የሰጠናቸው እርሱ ከጌታህ ዘንድ በእውነት የተወረደ መኾኑን ያውቃሉ። ከተጠራጣሪዎቹም አትኹን።

የኢንጅል ባለቤቶች ክርስቲያኖች ናቸው፤ በወንጌሉ ውስጥ በተጻፈው መፍረድ ይችላሉም ይጠበቅባቸዋልም ማለት ነው። ደግሞም ኢንጅል ያልተሳሳተ መሆኑን እነዚህ አባባሎች ይመሰክራሉ። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አናቅጽ የሚያሳዩት በዚያን ጊዜ የነበረውን መጽሐፍ ቅዱስ ሙሐመድ ተቀብሎት እንደነበር ነው። የአይሁድ እና የክርስቲያኖች መጻሕፍትን ተቀባይነት ከሚጠቅሱት ሱራዎች (የቁርኣን ምዕራፎች) መካከል ለናሙና ጥቂት እነሆ፥ 2፥40-42 እና 285፤ 3፥3-4፥71፥93፤ 4፥47 እና 136፤ 5፥47-49፤ 6፥91፤ 6፥ 114-115፤ 10፥37፤ 10፥94፤ 18፥27፤ 21፥7፤ 29፥46፤ 35፥31፤ 46፥12። እነዚህ ሁሉ አንቀጾች በሙሐመድ ዘመን የነበረው የአይሁድ እና የክርስቲያኖች መጻሕፍት ትክክል መሆናቸውን ያወሳሉ እንጂ ከቶም መሳሳታቸውን፥ መጥፋታቸውን፥ መለወጣቸውን አይናገሩም። እንዲያውም ቃላቶቹ የማይለወጡ መሆናቸውን መስክሮአል፤

18፥27 ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፤ ለቃላቶቹ ለዋጭ የላቸውም፤ ከርሱም በቀር መጠጊያን በፍጹም አታገኝም።

ያኔ እርሱ የተቀበለው ከነበረ አሁን ለምን አይቀበሉትም? የዚህ አጭር መልስ ከተቀበሉ ከሁለቱ አንዱ ብቻ ትክክል መሆኑ የሚታይ ስለሆነና ያንን መገዳደር የሚችል ማረጋገጫ ባለመኖሩ ነው። ከዚያ ወዲህ ተለወጠ ወይም ተበረዘ እንዳይባል ከላይ እንዳልኩት ያኔ የነበረው አዲስ ኪዳን ከአሁኑ ጋር ፍጹም አንድ መሆኑን የሚያረጋግጡ ከ25 ሺህ በላይ የጽሑፍ ቁራጮች ብቻ ሳይሆኑ በሙሉ ይዘት የተደጎሱ መጽሐፎችም አሉ። ለማስተያየት የሚወድ በቀላሉ ሊያስተያይ እስከሚችል ድረስም የሚነበብ ጽሑፋቸውና የሚታይ ፎቶአቸው በኢንተርኔት ይገኛል። እላይ በተጠቀሱት ቤተ መጻሕፍትም ይገኛሉ።

ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጦአል የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡት ከልብ አምነውበት ወይም ጠንካራ ማስረጃ አቅርበውበት ሳይሆን ቁርኣን የአላህ ቃል መሆኑን የሚያስረዱበት ሌላ ማስረጃ ስለሌላቸውና ስለማይኖራቸው ነው። ይህ ታሪካቸውንም የማያውቁ ሙስሊሞችንም ሊያስገርም የሚችል ቢሆንም ሙሐመድ ብቻ ሳይሆን ከእርሱ በኋላ የነበሩ ተከታዮቹም መጽሐፉን ተሳሳተ አላሉም። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን አንቋሽሾ ያጣጣለ ሙስሊም ኢብን ካዚም የተባለ ሰው ነው፤ ይህም በ1064 ዓ. ም.፥ ማለትም፥ ሙሐመድ ከሞተ ከ400 ዓመታት በኋላ ቆይቶ ነው። ኢብን ካዚም ይህን ያደረገው የቁርኣንን እና የመጽሐፍ ቅዱስን ልዩነቶችና ቅራኔዎች ካስተዋለ በኋላ ነው። ይህ ሰው ሙስሊምና የቁርኣን ተከታይ በመሆኑ ቁርኣንን ይቀበለዋል፤ ስለዚህ ቁርኣን ሊሳሳት አይችልም ብሎ ያምናል፤ ሙሐመድ ደግሞ የአይሁድንና የክርስቲያኖችን መጽሐፎች እንድናከብር አዝዞናል ብሎ ተቀብሎአል፤ ታዲያ ይህ ልዩነት የመጣው ከዚያ በኋላ ያሉት ክርስቲያኖች በርዘውት ነው ከሚል ድምዳሜ ይደርሳል። ስለዚህ ለክርስቲያኖች የተወረደላቸው ኢንጂል በጣም ጥቂት እውነቶች ብቻ ሲቀሩ የቀሩት ጠፍተውባቸዋል ብሎ ማስተማር ጀመረ። ይህን ሲያደርግ ግን ቁርኣንን ለመጠበቅ ብቻ ሲና ከግል እምነቱ የተነሣ እንጂ ምንም ታሪካዊና ተጨባጭ ማስረጃ ለማግኘት ሳይሞክር ነው።[3]

ሲታሰብ ያኔ የነበረው መጽሐፍ የተበላሸ ኖሮ ቢሆን “መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ” ብሎ ያንን የተበላሸ ሰነድ እንዲጠይቁ አይነግረውም። የአይሁድና የክርስቲያኖች መጽሐፍ ከተበላሸ ይህንን መበላሸት አላህ አያውቀውም ነበር ማለት ነው? ከተበረዘ የትኛው ምን ይል የነበረው ተደለዘና ምን ተብሎ ተለወጠ ወይም ተበረዘ? ቢባል መልስ የለም። ለምን መልስ የለም ቢባል ሐሰት ነዋ! በእውነቱ፥ አዲስ ኪዳን በሙሐመድ ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላም አልተበረዘም። ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ትርጉሞች ሲተረጎሙ ግድፈቶች አይኖሩም ማለት አይደለም። ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች በተተረጎመው ቁርኣንም ይህ መኖሩን ማንም አይክደውም። ለምሳሌ፥ በአንድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ ከ50 በላይ ትርጉሞች አሉ። አንድ አንቀጽ (አል በቀራህ ወይም ምዕ. 2 ቁ. 62) በ31 የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ምን እንደሚል በአንድ ድረ ገጽ ተጽፎአል።[4] በሁሉም የቃላትና የአገላለጥ ልዩነቶች ይታዩባቸዋል። ትርጉሞችን ከምንጭ ጽሑፎች ጋር ለማስተያየት ለሚፈትን አእምሮ ከበቂ በላይ የአዲስ ኪዳን ማስረጃዎች አሉ። ከበቂ በላይ! የአይሁድና የክርስቲያኖች መጻሕፍት ወይም ብሉይና አዲስ ኪዳን (ተውራትና ኢንጂል) ከቶም ያልተበረዙ መሆናቸውን ጠንቅቀን እንረዳ።

ይህ የእስላም እና ክርስትና (ንጽጽራዊ አቀራረብ) መጽሐፍ ንጽጽራዊ እንዲሆን ተነጻጻሪ ጥያቄ ማቅረቡ አስፈላጊ ይሆናል። ለሙሐመድ ከተወረደው ቁርኣን ጥንታዊ ወይም የመጀመሪያ የሚባለው ቅጅ ይገኛል? ከኖረ የት? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይሆናል። ቁርኣን በጣም የጥንቱ፥ የመጀመሪያው በ800 ዓ. ም. የተጻፈ፥ ማለትም፥ ከሙሐመድ በኋላ 200 ያህል ዓመታት ቆይቶ የተጻፈ እንጂ ከዚያ በፊት የነበረው የት ይገኛል? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ የትም አይገኝም ነው። በዓለም ጥንታውያን የሚባሉ የቁርኣን ከፊል ቅጅዎች በታሽኬንት እና ኢስታንቡል ቤተ መዘክሮች የሚገኙ ሲሆኑ በሊቃውንት የተሰጣቸው የጽሑፍ ዘመን ከ790-800 ዓ. ም. ነው። በቅርብ በሰንዓ የተገኘው ሰነድ ደግሞ ወደ 710 ዓ. ም. ገደማ እንደሆነ ይገመታል።[5] ጸሐፊው የዮሐንስን ወንጌል ከ64 ዓመታት በኋላ እንደተጻፈ በመገመት ያን ያህል ለምን ቆየ የሚለውን ማፍረሻ ለቁርኣን መገንቢያስ ይጠቀምበታል?

እስላም እና ክርስትና (ንጽጽራዊ አቀራረብ) ደራሲ ወንጌሉን ማጣጣሉን በመቀጠል ማርቆስ የጴጥሮስ ደቀ መዝሙር እንጂ የኢየሱስ ሐዋርያ ባለመሆኑ ውድቅ መሆን አለበት ይላል። ሉቃስ ደግሞ ጭራሹኑ ራሱም ሐዋርያ ያልነበረው የበርናባስ ደቀ መዝሙር ነውና መረጃዎቹ ትክክለኛነት አይኖራቸውም ይለናል። የዮሐንስ ወንጌልም ዘግይቶ የተጻፈ በመሆኑ ዮሐንስ ሳይሆን በእርሱ ስም ሌላው የጻፈው በመሆኑ ተዓማኒነት የለውም ብሎ ይደመድማል። እንዲህ የመሰሉ ትልልቅ ማጣጣያዎችን ያለ ዋቢና ያለ ማስረጃ ሲደረድር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ እውቀት ያለው ለመምሰልና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የማያውቁትን ለማወናበድ ወይም ጥቂት ብቻ የስሚ ስሚ የሚያውቁትን ደግሞ ለማደናገር ነው። ምናልባት ሊያቀርብ የፈለገው አራት እርስ በርስ የሚጣሉ ወንጌላት አንዳቸውም የሚታመኑ ባልሆኑ ጸሐፊዎች የተጻፉ አድርጎ ለማሳየት መሆኑን ይህ አባባሉ ይገልጣል። (ገጽ 2)፤

“የአላህ የጠራ ቃል ነው ብለው የትኛውን ይመርጣሉ? አራት ተጻራሪ ቅጂዎች ያሉትን፤ ኦሪጂናል ቅጂው የጠፋውንና የሁለተኛ ደረጃ ዘገባና የሦስተኛ ደረጃ ዘገባ የሆነውን ወንጌል? ወይስ አንድ ብቸኛ ቅጂ ያለውን ቁርኣን?”

ይህ አባባል ወንጌላቱን ተጻራሪ አድርጎ የማሳየት ስሕተትን ያስተላልፋል። ይልቅስ የሚያስደንቅ መመሳሰልና መጠባበቅ ያላቸው መሆናቸውን ማንም የሚመረምር አእምሮ ያለው የወንጌል አንባቢ ሊረዳው ይችላል። የኢየሱስ ታሪክ በወንጌላውያኑ ብቻ ሳይሆን ከክርስትና ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ዓለማውያንም የተጻፈ ነው። ያም ከነዚህ ጋር አልተጋጨም። መጽሐፍ ቅዱስ ወይም አዲስ ኪዳን አማካዩ ሙስሊም የእግዚአብሔርን ቃል ከሰማይ እንደወረደ (ወይም በቁርኣን ቋንቋ እንደተወረደ) አድርጎ እንደሚረዳው ተጽፎ ከሰማይ የወረደ ሳይሆን ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ተነድተው የጻፉት ዓላማ ያለው የእግዚአብሔር መልእክት ነው። እርግጥም ማርቆስ የጴጥሮስ ደቀ መዝሙር ነውና ከጴጥሮስ የተረዳውን ቢጽፍ ወይም ሉቃስ ጠይቆና መርምሮ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን ብሎ ከዓይን ምስክሮችና ከወንጌሉ አገልጋዮች የተላለፈውን እውነት ቢጽፍ ይህ ማስገረም የለበትም።

እውነትም ደራሲው እንዳለው (አይደሉም እንጂ) እነዚህ ቅጂዎች ከተለያዩ ምንጮች እንደተቀዱ ሆነው ተጻራሪ መሆን ነበረባቸው። ግን በአስደናቂ ሁኔታ ተመሳሳይ እንጂ ተጻራሪዎች አይደሉም። እነዚህ ጸሐፊዎች ትምህርቱን ወይስ ማንነቱን አጻረሩ? ሞቱን ወይስ ትንሣኤውን አጋጩ? ይልቅስ ብዙ ምስክሮች በአንድ ቃል ሲናገሩ ማስደነቅ የለበትም? ማርቆስንና ሉቃስን ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ዘጋቢዎች አድርጎ የመጀመሪያዎቹን ማቴዎስን እና ዮሐንስን እነ ሉቃስን ባጣጣለበት በዚያ መልክ ሊያጣጥል ስለማይችል ምክንያት መፈለግ ስለኖረበት ማቴዎስን ኦሪጂናሉ ጠፍቶአል፤ ዮሐንስን ደግሞ በስሙ ሌላ ጻፈው እንጂ እርሱ አይደለም በማለት ሊያብራራ ይጥራል።

ስለ ዮሐንስ ዋና ምክንያት አድርጎ የሚያቀርበው የጻፈው እርሱ ቢሆን ኖሮ ለምን ያን ያህል ዘመናት ዘግይቶ ጻፈው? ወዲያው ነው እንጂ መጻፍ የነበረበት የሚል ሙግት አቅርቦአል። መቼ መጻፍ እንዳለበት ጊዜ ሊሰጠው የፈለገ ይመስላል። አሳቡ ወንጌሉ አንገብጋቢ ከሆነ ለመጻፍ ለምን ዘገየ የሚል ነው። ቁም ነገሩ የተጻፈበት ጊዜ ሳይሆን ትምህርቱ ራሱ በጽሑፍ መተላለፉ ነው። የክርስቶስ ተከታዮች በሚነቀፉበትና በሚሰደዱበት ጊዜ ስለ ክርስቶስ መጻፍ ድፍረትንና ዋጋ መክፈልን መጠየቁ ሳይዘነጋ ዮሐንስ ዘግይቶ የጻፈው መልእክቱ (1ኛ ዮሐንስ) በመሠረታዊ ይዘት ከወንጌሉ አለመለየቱን ወዶ ሊያስተውል የሚፈልግ አይመስልም። መቼም ይህኛው መልእክት ስለሆነ ለምን ዘገየ አይባልም። የመልእክቱ ዋና አሳብም እንደወንጌሉ ሁሉ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚያጎላና ልጁ (ኢየሱስ) ያለው ሕይወት እንዳለው፥ ልጁ የሌለው ሕይወት እንደሌለው የሚያስረዳ ነው። ወይስ መልእክቱንም በዮሐንስ ስም ሌላ ሰው ጻፈው ነው የሚለው ደራሲው?

በአጠቃላይ፥ ‘ኢንጂል ጠፍቶአል፤ አሁን ያለው የተለወጠው፥ የተቀየጠው፥ ከዚያ በኋላ የጠፋውን ለመተካት ክርስቲያኖች የፈጠሩት ነው’ ነው የሚሉት። ይህ ቀድሞም የነበረውን አሁንም ያለውን ወንጌል ላለመቀበል የተገመደ ገመድ ነው። ምክንያቱም እንደ ወንጌል ግልጽ ሆኖ የተጻፈና ከውጭ ባሉ የታሪክ ጸሐፍት የተደገፈ ሃይማኖታዊ ጽሑፍ የለም፤ በአንድ ሳይሆን በአራት ጸሐፊዎች የተሰመረ፥ የተደገመ ታሪክ ነው። ወንጌሉ እንደ ቃሉ ትርጉም የምሥራች ቃል ማለት ነው። የክርስቶስ ሞት የኃጢአታችን ስርየት ብቸኛው መንገድ የተሰበከበት ነው። ኢስላም ይህን አይሻምና ኢየሱስ አልሞተም ይላል። ወደፊት ይህንንም እናየዋለን። ከሞተ ለምን ሞተ ሊባል ነው። ለመሆኑ በኢስላም ኢየሱስ ምን አደረገ? ምን ጨመረ? ለሰው ልጆች ምን አደረገ? ቢባል መልሱ ምንም ነው ማለት ይቻላል። በሕፃንነቱ በተአምር ተናገረ፤ አንድ ሁለት ተአምራት አደረገ፤ አስተማረ፤ (የሚገርመው በወንጌታት ውስጥ በዝርዝር የምናነብበው ትምህርቱም አልተዘገበም)። በክርስትና ግን ኢየሱስ ሁሉን አደረገ!! እርሱ ከዘላለም የነበረው ነው፤ በተስፋ ቃል የመጣው ነው፤ ሥጋ ለበሰ፤ ያለ ኃጢአት ኖረ፤ ምትካዊ ሞታችንን ሞተ፤ ሞትን ድል ነስቶ ከሙታን ተነሣ፤ ወደ ሰማይ አረገ፤ በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድም ተመልሶ ይመጣል። ይህ እንዲነገር አይፈለግምና ወንጌሉ ውሸታም ሆኖ ሊቀርብ ተደረገ። የእስላም እና ክርስትና (ንጽጽራዊ አቀራረብ) ደራሲ ይህንን አሳብ ነው በመጽሐፉ ያስተጋባው።

————

[1] ገጽ 5 እና 20።

[2] ጥቂቶቹን ጥንታውያን ጽሑፎችና የአዲስ ኪዳን ቁራጮች ለማየት ለምሳሌ፥ በhttp://en.wikipedia.net/wiki/List_of_New_Testament_papyri የተዘረዘሩትን መመልከት ይቻላል።

[3] http://www.bible.ca/islam/islam-bible-not-corrupted-early-muslims.htm

[4] http://en.wikipedia.net/wiki/English_translations_of_the_Quran

[5] http://www.youtube.com/watch?v=iNdvsLh128Q

እስላም እና ክርስትና – ንጽጽራዊ አቀራረብ – ዋናው ማውጫ


 

ለተጨማሪ ንባብ

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ

መጽሐፍ ቅዱስ