እስላም እና ክርስትና ንጽጽራዊ አቀራረብ – ለዶ/ር ሙሐመድ ዓሊ አልኹሊ የተሰጠ ምላሽ – ክፍል አራት

እስላም እና ክርስትና – ንጽጽራዊ አቀራረብ 

የመጽሐፍ ሒስና ግምገማ

ዘላለም መንግሥቱ

ደራሲ፥ ዶ/ር ሙሓመድ ዓሊ ኣልኹሊ

ትርጉም፥ አይታወቅም

አሳታሚ፥ ሑዳ ፕሬስ ሊሚትድ

የገጽ ብዛት፥ 91 

የኅትመት ዘመን፥ 1989

ክፍል አራት

ባለፉት ሦስት ክፍሎች እስላምና ክርስትና (ንጽጽራዊ አቀራረብ) የተባለውን በዶ/ር ዓሊ አልኹሊ የተጻፈ መጽሐፍ እየተመለከትን ነበር። መጽሐፉን መመልከታችንን እንቀጥላለን። በዚህ ክፍል ግን ቆም ብለን ደራሲው በድፍረት ስለሚናገርበት ስሕተቶች ቁርኣን ምን ይላል? ብለን እንድንጠይቅ እወዳለሁ። ዶ/ር ዓሊ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 50,000 ስሕተቶች አሉ ብሎ በድፍረት የተናገረበት ይህ መጽሐፍ የተበከለው ቁርኣን ከተጻፈ በኋላ ነው ማለት መቼም አይችልም። አሁን የሚገኙትን የተለያዩ ትርጉሞችም ዋና ምስክር አድርጎ መጥራት አይችልም። ይህንን እንዳያደርግ ሙሐመድ በነበረበት ዘመን ወይም ቁርኣን በተጻፈበት ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት የነበሩት የአይሁድና የክርስቲያኖች መጽሐፎች ወይም ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ባልተተተረጎሙባቸው በዋና ቋንቋቸው አሁን ባሉበት መልካቸው እንደነበሩ ማረጋገጥ ይቻላል።

ካለፈው ጽሑፍ በኋላ በዚህ የ50 ሺህ ስሕተቶች ጉዳይ ላይ ስመረምር አንድ መጽሐፍ አገኘሁ። መጽሐፉ በጠቅላላው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በቀላሉ ለማንበብና ለመረዳት ለሚወድዱ ከምስሎች ጋር የተሠራ መጽሐፍ ነው።[1] በዚህ መጽሐፍ ስለ 50 ሺህ ስሕተቶች የሚናገር ነገር አለ። “በ1952 አንድ የታወቀ አሳታሚ ባወጣው መጣጥፍ ርዕሱን፥ በመጽሐፍ ቅዱስ 50 ሺህ ስሕተቶች ተገኙ (Fifty Thousand Mistakes Discovered in the Bible) ብሎ ታተመ። ነገር ግን ወደ ኋላ ራቅ ብለን ወደ 1701 ስንሄድ ጆን ሚል (John Mill) በአዲስ ኪዳን ላይ የሕያሴ ጽሑፍ ያወጣ ሲሆን በዚህ ሥራው ወደ 30ሺህ የሚደርሱ አጠያያቂ ምንባቦችን አግኝቶአል።” ይልና ያገኛቸውን ነገሮች ምንነትና እንዴት እንዳገኛቸው ሲዘረዝር፥ ይህንን ለማድረግ፥ Mill 98 የተለያዩ [የእንግሊዝኛ] ትርጉሞችን በማነጻጸር የቃላትን፥ የቃላት ቁራጮችን (syllable)፥ የአገላለጥ ልዩነቶችን፥ ለምሳሌ፥ await እና wait for ወይም he came እና he arrived የሚመስሉ የትርጉም፥ የማተሚያ ቤት ስሕተቶች የሆኑ የተጨመሩ ወይም የተቀነሱ ፊደላትና አጣጣሎችን፥ ይህንም የመሰሉትን በሙሉ የሚጨምር ነው። ጸሐፊው ሲደመድም፥ “It was trivia of this kind that the journalist found to the number of about 50,000” አለ። ይህን የመሰሉትን ገለባዎች በመቁጠር ነው ጋዜጠኛው 50 ሺህ ያደረሰው።[2]

ይህ ማለት በአዲስ ኪዳን ጥንታውያን ጽሑፎች ሁሉ መካከል ፍጹም መመሳሰል አለ ማለት አይደለም። በመንግሥት ወይም በግለሰብ ቁጥጥር ሳይሆን በነፃ ይሰራጩ ከነበሩት መጻሕፍት ወደ 6ሺህ የሚጠጉ የአዲስ ኪዳን እና በጠቅላላው ወደ 25 ሺህ የሚያህሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታውያን ጽሑፎች ዛሬ በየቤተ መዘክሮችና የምርምር ተቋማት ይገኛሉ። በነዚህ ጥንታውያን ጽሑፎች መካከል የሚገኙት ልዩነቶች እንደዛሬው በፎቶ ኮፒ የማይባዙበት ዘመን ስለሆነ አንባቢ ጸሐፊዎችን ሲያስጽፍ የሚፈጠሩ የድምጸ-ቃላት ልዩነቶች እና የፊደላት አጣጣሎች ልዩነቶች ናቸው። እንጂ አንዱ ጽሑፍ ኢየሱስ ጌታ ነው ሲል ሌላው የለም አይደለም የሚል ወይም አንዱ ኢየሱስ ሞቶአል፥ ከሙታንም ተነሥቶአል ሲል ሌላው የሞተ መሰለ እንጂ አልሞተም አልተቀበረም የሚሉ አይደሉም። ወደዚህ አሳብ እንደገና ወደፊት እመለሳለሁ።

ሌላ ስለዚህ የተጻፉ ነገሮችን እየፈለግሁ ሳለሁ ያጋጠመኝን ሌላ መጽሐፍ በዚህ ማውሳት እፈልጋለሁ። በምሕረቱ ጴ. ጉታ የተጻፈ መልስ ይኖረው ይሆን? የሚል መጽሐፍ ነው።[3] መጽሐፍ ቅዱስ ይጣረሳልን? የሚለውን የአንዋር ሙሐመድን መጽሐፍ ሳነብ ሳለሁ ካየሁት አመላካች ተነስቼ ይህን መጽሐፍ ፈልጌ አገኘሁት። ሳነብበው ያስገረመኝ ጠሊቅ የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ስነ መለኮታዊ መልሶቹ ብቻ ሳይሆኑ መጽሐፉ ራሱ የተጻፈው በዚህ እኔም እያሔስኩ ባለሁት የዶ/ር ዓሊ አልኹሊ መጽሐፍ ላይ መሆኑም ነው። ድግግሞሽ ከሆነ የኔን ለማቆም ወይም ለመቋጨት እያሰብኩ በጥንቃቄ ከተመለከትኩ በኋላ የደረስኩበት ድምዳሜ ይህ ነው። ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጽሑፎች እኔ የሠራሁበትን አቀራረብና የምሕረቱን መጽሐፍና የጽሑፉን አቀራረብ ተመልክቼ 1ኛ፥ በይዘት ቢቀራረቡም በትኩረት አቅጣጫ የየራሳቸው መስመር ስላላቸው፤ 2ኛ፥ የምሕረቱ መጽሐፍ ከቁርኣንም በመጥቀስ በተለይ መጽሐፍ ቅዱስ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስነ መለኮት ላይ በማተኮር የምላሽ ትንተና ሲሰጥ የኔው ደግሞ ለጸሐፊው የክርስትና ማጣጣያዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ የመልስ ቃል በመስጠት ወደ ቁርኣንና ወደ ሐዲስ በመሄድ ምላሽ መስጠት ነው። ከዚህ የተነሣ በጀመርኩት መንገድ ለመጻፍ እየቀጠልኩ በዚህ አቅጣጫ ጥናት የምታካሂዱ ሁሉ የምሕረቱን መጽሐፍ እንድታገኙና እንድታነብቡት በጥብቅ አደራ አሳስባለሁ።

ከላይ በመግቢያው አንቀጽ እንዳልኩት በዚህ መጣጥፍ ወደ ዶ/ር ዓሊ መጽሐፍ ይዘት ብመለስም በመጀመሪያ ቁርዓን ወይም በቁርዓን ውስጥ ሙሐመድ ራሱ ተሳስቷል ያላለውን መጽሐፍ የዛሬዎቹ ሙስሊሞች ለምን ተሳስቷል፥ ተበርዟል፥ ተበክሏል ስለሚሉበት ነጥብ አወሳለሁ። እውነት መጽሐፍ ቅዱስ ተበክሎአል? ማን በከለው? ማን በረዘው? ሙሐመድ ስለ መጽሐፉና ስለ መጽሐፉ ሰዎች ያለው ምንድርነው? ቁርኣንስ ስለአይበከሌነቱ ያለው ምንድርነው? ተበክሎአል የሚሉቱ ይህንን ለምን እንደሚሉ ለራሳቸውም ጥያቄ ሊሆን የተገባ ነው። ግን የማለታቸው ዋና ምክንያት ይህ ነው። አዲስ ኪዳን ያለምንም ማወላወል የሚያስተምራቸው ዐበይት ወይም የወንጌል አዕማድ የምንላቸው ሦስት ትምህርቶች አሉ። እነዚህ ሦስት ዋና ዋና ትምሀርቶች ማንም የመጽሐፍ ቅዱስ አጥኚ የሆነ ክርስቲያን አጥብቆ የሚያውቃቸውና የሚቀበላቸው እውነቶች ናቸው። እነዚህም የኢየሱስ ጌትነት ወይም አምላክነቱ፥ ሞቱ፥ እና ትንሣኤው ናቸው። ክርስቲያን ከሆንኩ በኋላ በመጀመሪያ በቃሌ ያጠናሁት ጥቅስ ሮሜ 10፥9 ነው፤ ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና ይላል። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ኢየሱስ ጌታ መሆኑ፥ መሞቱና ከሙታን መነሣቱ ሦስቱም አብረው ተገምደው ተጽፈዋል። እነዚህ ሦስቱ ከውስጡ ከወጡ ክርስትና ምውት ነው። በድን ነው።

በቁርኣን ውስጥ የምናየው ኢሳ ደግሞ ከሦስቱም የለበትም። ለነገሩ ኢሳና ኢየሱስ ከስማቸውም ጀምሮ አንድ አለመሆናቸውን ጠንቅቀን ልንረዳ ይገባል። ለጊዜውም ቢሆን ኢሳ ኢየሱስ እንደሆነ አስበን ይህን ግምገማ እንቀጥል። ኢስላምና ቁርዓን እነዚህን ሦስቱንም ትምህርቶች አጥብቀው ይክዳሉ። ኢየሱስ ጌታና አምላክ ሳይሆን የአዳም ብጤና የማርያም ልጅ የሆነ ሰው ብቻ ነው። ነቢይና ከብዙ ነቢያት አንዱ እንጂ ሌላ አይደለም ይላሉ። ደግሞም የሞተ መሰላቸው እንጂ አልሞተም፤ እንዲያውም አልተሰቀለም። የተሰቀለው ኢየሱስን እንዲመስል የተደረገ ሌላ ሰው ነው (ብዙዎቹ የአስቆሮቱ ይሁዳ ነው) ይላሉ። ይሁዳ ታንቆ እንደሞተ ሲነበብላቸው ያም እርሱን የሚመስል ሌላ ነው የሚሉ አልጠፉም። ይህንን የይሁዳን ኢየሱስነት የሚያወሱቱ የበርናባስ ወንጌል ከሚባለው የፈጠራ መጽሐፍ በመውሰድ ነው። ይህ የበርናባስ ወንጌል ራሱን የቻለ ሌላ የቅሌት ታሪክ አለው። ምናልባት በሌላ ክፍል አነሣው ይሆናል። 15 ጊዜ የሙሐመድ ስም የተጻፈበት ‘ወንጌል’ ነው! ካጋጠማችሁ አንብቡት። እንግዲህ አልተሰቀለም ብቻ ሳይሆን ስላልሞተ ደግሞ ከሙታንም አልተነሣም ይላል ቁርኣኑ። እንግዲህ ለነዚህ ያገጠጡ ቅራኔዎች የሙስሊሞች መልስ ምን ሊሆን ነው? በእውነቱ ምንም መልስ የላቸውም። ስለ ኢየሱስ መሰቀልና መሞት ክርስቲያን ያልሆኑ ታሪክ ዘጋቢዎችም ጽፈውታል። ከሙታን ተነሣ መባሉንም ጭምር ጽፈዋል። ስለዚህ መልስ ያጡለት ወይም ሊቀበሉት የተከለከሉት ይህ ጉዳይ ከቁርኣን ጋር ከተቃረነ ሌላ የሚሉት ስለሌለ፥ ‘መጽሐፍ ቅዱስ ተሳስቷል ተበክሏል ማለት ነው’ ይሉናል። ትልቁ ጥያቄ ግን፥ ‘ማን በከለው? ደግሞም መቼ ተበከለ?’ የሚለው ነው።

ቁርኣን በተጻፈበት ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ የተበከለ አለመሆኑን በግልጽ በራሱ በቁርኣኑ ተጽፎ እናያለን። ቁርኣኑ የመጽሐፉ ሰዎች፥ የመጽሐፉ ባለቤቶች ወይም መጽሐፉ የተሰጣቸው ሰዎች (አህል አልኪታብ) የሚላቸው የአይሁድና የክርስቲያኖቹ መጻሕፍት ተውራት፥ ዛቡር እና ኢንጂል (ኦሪት፥ መዝሙር እና ወንጌል) ትክክለኛ መሆናቸውን እንጂ የተሳሳቱ መሆናቸውን ከቶም አይናገርም። ከውስጣቸው በከፊልም በጥቂትም ሲያመላክት መሳሳታቸውን ሳይሆን ትክክለኛነታቸውን በማመን ነው። ከተሳሳተ ምንጭ ማን ይቀዳል? ከዚያ ወዲህ ተበከሉ ከተባለ ደግሞ በዚያ ቁርኣን በተነገረበት ወይም በተጻፈበት ዘመን የነበረውና አሁን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ልዩነት የሌላቸው መሆኑን ማንም በአእምሮ መርምሮ ሊደርስበት፥ ሊጨብጠውና ሊገነዘበው ይችላል። በ7ኛውና በ8ኛው መቶ ምዕት ዓመት የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ በእጃችን ካለው ምንም ልዩነት የሌለው መሆኑን እውነትን የሚፈልግ ያገኘዋል።

ቁርኣን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በ3፥3-4 እንዲህ ይላል፤

ከርሱ በፊት ያሉትን መጻሕፍት የሚያረጋግጥ ሲሆን መጽሐፉን (ቁርኣንን) ባንተ ላይ ከፋፍሎ በዉነት አወረደ። ተዉራትንና ኢንጅልንም አውርዷል። (ከቁርኣን) በፊት ለሰዎች መሪ አድርጎ (አወረዳቸዉ)፤ ፉርቃንንም አወረደ እነዚያ በአላህ ታዓምራቶች የካዱ ለነርሱ ብርቱ ቅጣት አላቸዉ፤ አላህም አሸናፊ የመበቀል ባለቤት ነዉ።

ከፋፍሎ አወረደ የሚለው ቃል በእጁ ሊይዛቸው ሊያገኛቸው የሚችሉት መጻሕፍት እውነተኛነታቸውን ሊያረጋግጥ የሚችልባቸው መሆናቸውን መግለጡ ነው። ተውራትና ኢንጅል ኦሪትና ወንጌል ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ የሙሐመድ አቋም ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ያልተበከለ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ያምናል። ያልተበከለ መሆኑን እያመነና እየተቀበለ በውስጡ የተጻፈውን መካዱ፥ ማለትም ኢየሱስ ነቢይ ብቻ እንጂ ጌታ አይደለም፤ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም፤ አልተሰቀለም፤ አልሞተም፤ ከሙታንም አልተነሣም ማለቱ ደግሞ ይህ ራሱን የቻለ ሌላ ችግር ነው።

ቃላቱ ለዋጭ የሌለባቸው ስለመሆናቸው 6፥115 ደግሞ እንዲህ ይላል፤

የጌታህም ቃላት እውነተኛና ትክክለኛ ስትኾን ተፈጸመች። ለቃላቱ ለዋጭ የለም። እርሱም ሰሚው ዐዋቂው ነው።

ማንም ቃሉን ሊለውጥና ሊበክል የማይቻል መሆኑ በዚህ ቃል የተረጋገጠ ነው። 18፥27ም ተመሳሳይ ቃል አለው፤ እንዲህ ይላል፥

ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፤ ለቃላቶቹ ለዋጭ የላቸውም፤ ከርሱም በቀር መጠጊያን በፍጹም አታገኝም።

ይህ ግልጽ ነው። ዶ/ር ዓሊ አልኹሊ የክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የተበከለ ነው ሲል የራሱን መጽሐፍና የራሱን ነቢይ እየተቃረነ መሆኑ ግልጽ ነው። ቁርኣን የሚለው በግልጽ ከዚያ በፊት የነበሩትና በዚያን ጊዜ የሚታወቁት የመጽሐፉ ሰዎች የሚያነብቧቸው ተበርዘዋል አልተባለም። እንዲያውም ትክክል ናቸው፤ ሊለወጡም አይችሉም ነው መጽሐፋቸው የሚለው፤ እና ይህንን መቃወም ምን ይባላል? 5፥43-48 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል (ያሰመርኩት እኔ ነኝ)፤

43፥ እነርሱም ዘንድ ተውራት እያለች በውስጧ የአላህ ፍርድ ያለባት ስትሆን እንዴት ያስፈርዱሃል? ከዚያም ከዚህ በኋላ እንዴት ይሸሻሉ! እነዚያም በፍጹም ምእመናን አይደሉም።

44፥ እኛ ተውራትን በውስጥዋ መምሪያና ብርሃን ያለባት ስትሆን አወረድን፤ እነዚያ ትእዛዝን የተቀበሉት ነቢያት በነዚያ ይሁዳውያን በሆኑት ላይ በርሷ ይፈርዳሉ፤ ሊቃውንቱና ዐዋቂዎቹም ከአላህ መጽሐፍ እንዲጠብቁ በተደረጉትና በርሱም ላይ መስካሪዎች በሆኑት (ይፈርዳሉ)፤ ሰዎችንም አትፍሩ፤ ፍሩኝም፤ በአንቀጾቼም አነስተኛን ዋጋ አትለውጡ፤ አላህም ባወረደው ነገር ያልፈረደ ሰው እነዚያ ከሐዲዎች እነርሱ ናቸው።

45፥ በነርሱም ላይ በውስጧ ነፍስ በነፍስ፣ ዓይንም በአይን፣ አፍንጫም በአፍንጫ፣ ጆሮም በጆሮ፣ ጥርስም በጥርስ (ይያዛል)፣ ቁስሎችንም ማመሳሰል አለባቸው ማለትን ጻፍን፤ በርሱም የመጸወተ (የማረ) ሰው፣ እርሱ ለርሱ (ለሠራው ኃጢአት) ማስተሰሪያ ነው፤ አላህም ባወረደው ነገር የማይፈርድ ሰው፤ እነዚያ በደለኞቹ እነርሱ ናቸው።

46፥ በፈለጎቻቸውም (በነቢያቶቹ ፈለግ) ላይ የመርየምን ልጅ ዒሳን ከተውራት በስተፊቱ ያለውን አረጋጋጭ ሲሆን፣ አስከተልን፤ ኢንጂልንም በውስጡ ቀጥታና ብርሃን ያለበት በስተፊቱ ያለችውን ተውራትንም የሚያረጋግጥ ለጥንቁቆችም መሪና ገሣጭ ሲሆን ሰጠነው።

47፥ የኢንጅልም ባለቤቶች በውስጡ አላህ ባወረደው ሕግ ይፍረዱ፤ አላህም ባወረደው የማይፈርድ ሰው፣ እነዚያ አመጠኞች እነርሱ ናቸው።

48፥ ወደ አንተም መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭና በርሱ ላይ ተጠባባቂ ሲሆን በውነት አወረድን፤ በመካከላቸውም፣ አላህ ባወረደው ሕግ ፍረድ፤ እውነቱም ከመጣልህ በኋላ ዝንባሌዎቻቸውን አትከተል። ከናንተ ለሁሉም ሕግንና መንገድን አደረግን፤ አላህም በሻ ኖሮ አንድ ሕዝብ ባደረጋችሁ ነበር፤ ግን በሰጣችሁ ሕግጋት ሊሞክራችሁ፣ (ለያያችሁ)፤ በጎ ሥራዎችንም (ለመሥራት) ተሽቀዳደሙ፤ መመለሻችሁ በጠቅላላ ወደ አላህ ነው፤ በርሱም ትለያዩበት የነበራችሁትን ነገር ይነግራችኋል።

በቁጥር 47 የተጻፉት የኢንጂል ባለቤቶች ክርስቲያኖች ናቸው፤ በወንጌሉ ውስጥ በተጻፈው መፍረድ ይችላሉም ይጠበቅባቸዋልም ማለት ነው። በቁጥር 43-45 ተውራት ወይም ኦሪት ከ46-47 ደግሞ ኢንጅል ወይም ወንጌል በትክክል የእግዚአብሔር ቃላት መሆናቸው ተጽፎአል። ተበከሉ፥ ተበረዙ፥ ተበላሹ፥ አልተባሉም። በሙሐመድ ዘመን የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬም ካለው ጋር የተለያየ ነው ሊል የሚችል የለም።

10፥94 ደግሞ እንዲህ ይላል።

ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ። እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል። ከተጠራጣሪዎቹም አትሁን።

ይህ ጥቅስ ሁለት ነገሮችን ያሳየናል፤ አንደኛው ሙሐመድ ይጠራጠር እንደነበርና ሁለተኛው ደግሞ ሲጠራጠር ማንን መጠየቅና ማረጋገጥ እንዳለበት ነው። ማድረግ ያለበት መጽሐፉን የሚያነብቡትን የመጽሐፉን ባለቤቶች መጠየቅ ነው። የተበከለ መጽሐፍ መሆኑን ከቶም አይናገርም። ቢሆን ኖሮ ጠይቅ አይባልም ነበር።

እንግዲህ ከላይ ካሉት በርካታ አንቀጾች እንደምንረዳው ቁርኣን ለኦሪትም ለወንጌልም የተከበረ ስፍራ እንደሰጣቸው ይስተዋላል። ይሁን እንጂ ከዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር በግልጽ መቃረኑም ገሃድ ነው። በንጽጽሩ መጽሐፍና በዚህ ምላሽ በስፋት እያየን ያለነውም ይህ ነው።

ውስጣዊ አለመጣጣሞች

ውስጣዊ አለመጣጣሞች በሚለው ክፍል (ገጽ 10) እንዲህ ይላል፥

የሐዲስ ኪዳን ወንጌሎች ተመሳሳይ የሆነ አንድ ሁነት አስመልክተው እርስ በርሳቸው የሚፋለሱ ተጻራሪ ትረካዎች ያቀርባሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አንዱ ወንጌል ራሱን በራሱ ሲቃረን ይታያል፡፡ በአንዱ ወንጌል ውስጥና በተለያዩ ወንጌሎች መካከል በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ቅራኔዎች ይስተዋላሉ፡፡ ይህም የሚያረጋግጠው እነኚህ ወንጌሎች የሰብዓዊ ፍጡራን ዘገባዎች እንጂ መለኮታዊ ራእዮች አለመሆናቸውን ነው፡፡ እግዚአብሔር እውነቱን ሁሉ ስለሚያውቅ እርስ በርሳቸው የሚፋለሱ ተጻራሪ ዘገባዎችን ሊሰጥ አይችልም፡፡

ይህ አሳብ በቀደሙት ክፍሎች ተወስቶአልና ደግሜ አልጽፍበትም። እንደተለመደው ግን ምንም ማስረጃ ሳይቀርብ እርስ በርስ የሚፋለሱ፥ የሚጻረሩ ሲባል ወንጌላትን  ላላነበበና ለማያውቅ ሰው እውነት ሊመስል ይችላል። ይህ የወንጌላት አራትነትና የአራት ሰዎችን ምስክርነት ማንበቡ ቃል በቃል ደግሞ አንድ ያለመሆናቸው (ቢሆኑ ኖሮ አንድ እንጂ አራት ባላስፈለጉም) የፈጠረው አሳብ ይመስላል። እውነቱ ግን፥ እንዲያውም የሰው ውጤት ቢሆኑ ኖሮ ሲበዙ ወይም ከአንድ በላይ ሲሆኑ ዶ/ር ዓሊ እንዳለው መጻረር ነበረባቸው። ይልቅስ ወንጌላት ምንጫቸው መለኮታዊ መሆኑን የምናውቀው በቁጥር በዝተውም ሳለ በይዘት አንድ በመሆናቸው ነው። Simon Greenleaf የተባለው የሐርቫርድ የሕግ ትምህርት ቤት ሊቅ አራቱን ወንጌላት በሕግ ሰውነት መርምሮ የደረሰበትን መድረሻ ሲናገር፥ አራቱም ወንጌላውያን ተመካክረው አለመጻፋቸውን የሚያስረዳ የአገላለጥ ልዩነት ሲኖር በይዘታቸው ልዩነት አለመኖሩ ደግሞ ለየብቻቸው የጻፉት መሆናቸውን ያረጋግጣል ሲል ጽፎአል።[4] ደግሞም የአገላለጥ ልዩነት የሌለባቸው ፍጹም አንድ ዓይነት ቢሆኑም ኖሮ፥ ‘ይኸው አንዱ ካንዱ ኮርጆ ነው’ ወይም፥ ‘አራቱም አፍ ለአፍ ገጥመው ተመካክረው የጻፉት ነው’ ተብሎ መከሰሳቸውም የማይቀር ነበር።

 ጳውሎሳዊነት ወይስ ክርስትና?

ዶ/ር ዓሊ በመጽሐፉ ውስጥ ክርስትና የጳውሎስ ፈጠራ በመሆኑ ጳውሎሳዊነት መባል አለበት እንጂ ክርስትና መባል የለበትም የሚል ጽፎአል (ገጽ 11)።

ክርስትና ዛሬ ባለው መልኩ በአብዛኛው የጳውሎስ ፈጠራ ውጤት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ለጳውሎስ ሚዛናዊ አመለካከት ቢኖራት ኖሮ ሃይማኖታቸውን ጳውሎሳዊነት ብላ እንጂ ክርስትና ብላ ባልጠራች ነበር፡፡ ሃይማኖቱ በስማቸው የተሰየመው ኢየሱስ ክርስቶስ በሃይማኖቱ መሠረታዊ እምነቶች ላይ ጭራሽ አይስማሙምና፡፡ ስለዚህ ክርስትና አላግባብ ነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተሳሰረው፡፡ ጳውሎሳዊነት ይበልጥ ታማኝና ፍትሐዊ መጠሪያ ስሙ ነው፡፡

ወንጌላት የተጻፉበትን ቅደም ተከተል በመውሰድ አንዳንዶች ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶች ከኋላ የመጣ ዓይን አወጣ ዓይነት ከኋላ መጥቶ በርዞና ከልሶ አዲስ ትምህርት በመፍጠር ፊተኛ የሆነ ይመስላቸዋል። ከአንዳንዶች ትምህርትና አጻጻፍ በርካታ የኢስላም ምሑራንም ይህንን አሳብ የሚጋሩት ይመስላል።

ከወንጌላት ቢያንስ አንዱ ከጳውሎስ መሞት በፊት የተጠናቀቀ ስለመሆኑ ግልጽ ማስረጃ እናገኛለን። የሐዋርያት ሥራ ሲያልቅ ጳውሎስ አለመሞቱና የሐዋርያት ሥራ ሲጻፍ ደግሞ ቀድሞውኑ የሉቃስ የተጻፈ መሆኑ እሙን ነው። ይህን ከሐዋርያት ሥራ መግቢያ እናገኛለን። ጳውሎስ የሞተው በ60ዎቹ አጋማሽ እንደሆነ ይገመታል። ሉቃስ ቀድሞውኑ ተጽፎአልና ለታሪኩ ቀራቢ ወንጌል መሆኑ ምንም የማያጠያይቅ ነው። ሌሎቹ ወንጌላት መቼ እንደተጻፉ ማረጋገጥ ባይቻልም እንደሚገመተው ማርቆስም በ50ዎቹ መጨረሻ ወይም በ60ዎቹ መጀመሪያ ነው የተጻፈው። ማቴዎስና ዮሐንስ ግን ዘግይተው እንደተጻፉ ስለሚገመቱ ጳውሎስ መልእክቶቹን ከጻፈ በኋላ ብቻ ሳይሆን ከሞተም በኋላ እንደተጻፉ ቢገመት ትክክል ነው። ስለዚህ ወንጌላቱ የሚሉትን ጳውሎስ ከለሰው ማለት የማይመስል አባባል ነው።

ጳውሎስ ያደረገው ማብራት ነው ማለት ይቻላል። ይህን ያደረገው ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶና ተነድቶ ነው። የጳውሎስን መልእክቶች፥ የጳውሎስን ስብከቶችና ሕይወቱን ራሱንም ስንመረምር ጳውሎስ ዋና ግቡ ክርስቶስን ማጉላት እንጂ ጳውሎሳዊነትን ማጉላት አልነበረም። ምኞቱ እርሱን ፊተኛ ማድረግ፥ እርሱን ማወቅ፥ እርሱን መምሰል (በሞቱ እንኳ ሳይቀር እርሱን መምሰል)፥ ወንጌልን (የምሥራቹን ቃል) መስበክ ነበር እንጂ ክርስትናን የሚተካ ጳውሎስና ፈጥሮ አልሰበከም። የክርስቶስን ጌትነት ቢሰብክ ጌታና አምላክ በመሆኑ ነው። ስለ ሞቱ ቢሰብክ ክርስቶስ ስለሞተልን ነው። ትንሣኤውን ቢሰብክ ስለተነሣ ነው። የተነሣውን ኢየሱስ ራሱም በደማስቆ መንገድ ተገናኝቶታልና ያንን ያየውን ዓይን የሚያሳውር ብርሃን የተላበሰውን ጌታ ትንሣኤ ነው የሰበከው። ዳግመኛ መምጣቱን ቢሰብክ ጌታ ራሱ ያስተማረውን እውነት ነው የተናገረው። ጳውሎስ ጳውሎሳዊነትን ሳይሆን ክርስቶስን ነው የሰበከው። ይህ በመልእክቱ ገጾች ሁሉ ላይ የሚነበብ ነው። ዶ/ር ዓሊ ክርስትና ጳውሎሳዊነት መባል አለበት ሲል የጻፈው ፈጽሞ ከመስመር የወጣ ስሕተት ነው።

ጳውሎስ ክርስትናን ፈጠረው ከተባለ ራሱን የሳተ እብድ ካልሆነ በቀር ክርስትና የራሱ ፈጠራና እውነተኛ ያልሆነ ነገር መሆኑን ያውቀዋል ማለት ነው። እውነተኛ ካልሆነ ደግሞ ላልሆነና ለተፈጠረ ነገር መከራንና ሞትን መቀበል ከጅልነትም የወረደ ነገር መሆኑን ማንም አእምሮ ያለው ሰው ይረዳዋል። ጳውሎስ ወንጌልን ያገለገለው በመከራ፥ በመጎዳትና በመንገላታት ነው። አንዳንዶች ሊያደርጉት ይጣሩ እንጂ እውነተኛ ክርስትና ያኔም ዛሬም ትርፋማ ምድራዊ ንግድ አይደለም። እርሱ የጻፋቸውን መልእክቶች ትተን የሐዋርያት ሥራን ብቻ እንኳ ስናነብብ ይህን በመከራና በጉዳት ማገልገሉን በጉልህ እናስተውላለን። ራሱ ለፈጠረው ሃይማኖት በሮም እስር ቤት ቆይቶ እንደተገደለ ነው ትውፊት የሚነግረን። እና ለራሱ የፈጠራ ሃይማኖት፥ እውነት አለመሆኑን ላወቀው ነገር አንገቱን ለሰይፍ ሰጠ?

ሌላው ዶ/ር ዓሊ በዚያው ገጽ የጻፈው ቃል እንዲህ ይላል፤

የክርስትና እምነቶች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም፡፡ ‹‹ክርስትና›› የሚለው ቃል ራሱ የተፈጠረው በቤተክርስቲያን ሰዎች ነው፡፡ ክርስትና ከእምነቶቹና ከመጠሪያ ስሙ ጭምር የተፈጠረው በኢየሱስ ሳይሆን በቤተክርስቲያን ሰዎች ነው፡፡

እርግጥ ክርስትና የሚል ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። ግን በቤተ ክርስቲያን ሰዎች የተፈጠረ አይደለም። በመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት ‘ክርስቲያን’ የተባሉት በአንጾኪያ ነው፤ በርናባስም ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ መጣ፤ ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው። በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፥ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ። (ሐዋ. 11፥25-26) ይህ ስፍራ ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ በጌታ ተከታዮች መካከል ሆኖ ዓመት ሙሉ ያገለገለበት ነው። ክርስቲያን የሚለውን ስም ሌሎች ያወጡላቸው ነው እንጂ ለራሳቸው ያወጡት አይደለም። አወጣጡም የንቀትና የምጸት እንጂ የቁልምጫና የአድናቆት አይደለም።

የዶ/ር ዓሊ መጽሐፍ ርእስ እስላምና ክርስትና  የሚል ሲሆን እስልምናና ክርስትና አላለም። ግን እስልምና የሚል ቃል በቁርኣን ውስጥ  (9፥74 እና 39፥22) ሲገኝ አጻጻፉ ኢስላምን መካድን ወይም ኢስላምን መቀበልን የሚያመለክቱ ናቸው። እስልምና የተሰኘው የኢስላም ሃይማኖት ነው ማለት ነው። ክርስትና ደግሞ የክርስቲያን ሃይማኖት ስም ነው። ልዩነቱ ምንድርነው? ክርስቲያን የሚል ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈ ሲሆን ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ የሆነ ወይም የክርስቶስ ተከታይ ማለት ነው። ታዲያ ሰዎቹ ክርስቲያን ከተባሉ እምነቱም ክርስትና እንጂ ጳውሎስና ሊባል ኖሯል? ጳውሎስ እያገለገለ ባለበት በዚያው ጊዜና በዚያችው የአንጾኪያ ከተማ ደቀ መዛሙርት ክርስቲያን  ከተባሉ ጳውሎስ በስሙ እንዲሰየሙ ቢያንስ መጣር ነበረበት። ‘እኔ የጳውሎስ ነኝ’ የሚሉ ሥጋውያን ባይጠፉም ጳውሎስ ራሱ ክርስቲያን ነበረ እንጂ ክርስቲያኖች ጳውሎሳውያን አይደሉም። ዶ/ር ዓሊ በእጅጉ ተሳስቶአል፤ በመጽሐፍ ቅዱስና በክርስትናም ላይ ከግምት ያላለፈ የቆሸሸ ነገር ጽፎአል።

የሰላምታና የመልካም ምኞት መግለጫ ደብዳቤዎች

ዶ/ር ዓሊ የሰላምታና የመልካም ምኞት መግለጫ ደብዳቤዎች ባለው ክፍል (ገጽ 12) እንዲህ ይላል፤

ሕዝብ ሁልጊዜ ማታለል ግን አይቻልም፡፡ የጳውሎስ ደብዳቤዎች የጳውሎስ ደብዳቤዎች ናቸው፡፡ ስለ ደብዳቤዎቹ ማለት የሚቻለው እውነትም ይኸው ብቻ ነው፡፡  ጳውሎስ መለኮታዊ ራእይ (ወሕይ) ተቀብሎ አያውቅም፡፡ የኢየሱስን ትምሕርቶች ያቃለለ፣ የሙሴን ሕግ የሰረዘና አዲስ ሃይማኖት የመሠረተ ሰው ነው – ጳውሎስ፡፡

ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የጻፉት የብሉይ እና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በቅርጽና በዓይነት የተለያዩ ናቸው። በብሉይ ሕግ፥ ታሪክ፥ ቅኔያት፥ እና ነቢያት ናቸው። በአዲስ ኪዳንም ወንጌል፥  ታሪክ፥ መልእክቶች፥ እና ትንቢት ናቸው። ዓይነታቸው ወይም ቅርጻቸው መለያየቱ ይዘታቸውን ወይም ምንጫቸውን ከቶም አይለውጠውም።

የጳውሎስ ደብዳቤዎች የጳውሎስ በእርግጥ ናቸው፤ የበርናባስ ወይም የጴጥሮስ አይደሉም፤ ግን እነዚያን ‘ደብዳቤዎች’ ሲጽፋቸው መንፈስ ቅዱስ እንዲጻፉ አድርጎ ነበር። ደብዳቤዎቹ ዶ/ር ዓሊ እንዳለው ሹመት ለተሾመ ወይም ውድድር ላሸነፈ እንደሚጻፍ ‘የመልካም ምኞት መግለጫ’ ደብዳቤ ሳይሆኑ በተጻፉበት በግሪክ ቋንቋ እንደ ስማቸው  ἐπιστολή ኤፒስቶሌ ወይም መልእክት ናቸው። እነዚህ መልእክቶች የመጀመሪያዎቹን አብያተ ክርስቲያናት መልክ የሳሉልን ናቸው። አምልኮ፥ አገልግሎት፥ ተግባራዊ ክርስትና፥ ስደት፥ መጽናት፥ ምን እንደሚመስሉ ያየንባቸው የዘመኑ መስተዋቶች ናቸው። ይህ መለኮታዊ ይዘታቸው ወይም ጸሐፊዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው መጻፋቸው ሳይነካ ነው። ለአንድ ግለ ሰብ ወይም ለቤተ ክርስቲያን ቢጻፉም የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲኖርባቸው ተደርገው ድንበር ዘለልና ዘመን ዘለል ሆነው ዛሬም ለዘላለምም ሕያዋን እና የሚሠሩ ሆነው ይኖራሉ።

የጳውሎስ ደብዳቤዎች የጳውሎስ ደብዳቤዎች ናቸው ካልን እኮ የዳዊት መዝሙር የዳዊት መዝሙር ነው፤ የኢሳይያስ ትንቢትም የኢሳይያስ ነው፤ የዮሐንስ ወንጌልም የዮሐንስ ነው እያልን ምንም መጽሐፍ ቅዱስ የሚባል መጽሐፍ ላይኖር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ስም ራሱን ዶ/ር ዓሊ የሚተችበት አንቀጽ ስላለ በስፍራው እናያለን።

———-

[1] 6000 Years of the Bible, Wegener, G. S., Hodder and Stoughton, Jarrold and Sons Ltb, Norwitch, London, 1958.

[2] Ibid., pp. 262-264.

[3] መልስ ይኖረው ይሆን? ምሕረቱ ጴ. ጉታ፤ ኤስ አይ ኤም ማተሚያ ቤት፤ አዲስ አበባ፤ 1998 (2006)።

[4] Strobel, Lee; The Case for Christ; Zondervan, 1998; p. 48.

እስላም እና ክርስትና – ንጽጽራዊ አቀራረብ – ዋናው ማውጫ


ለተጨማሪ ንባብ

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ

መጽሐፍ ቅዱስ