የአሕመድ ዲዳት አስደንጋጭ ቅጥፈቶች

የአሕመድ ዲዳት አስደንጋጭ ቅጥፈቶች

ሙስሊም ዳዒዎች እስልምና “እውነተኛ” ሃይማኖት መሆኑን ለማሳየት የሚጠቀሙባቸው ስልቶ በእጅጉ አስገራሚ ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅሶች ከአውዳቸው ገንጥሎ በማውጣት በማጣመም ከመተርጎም አንስቶ ራሳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ቋንቋዎች ሊቃውንት በማስመሰል በማቅረብ ግልጽ ቅጥፈቶችን እስከመፈጸም ሲደፍሩ ይስተዋላሉ። ለዚህ እንደ ምሳሌ ሊነሱ ከሚችሉት ግለሰቦች መካከል አሁን በሕይወት የሌሉት ደቡብ አፍሪካዊው አሕመድ ዲዳት ይጠቀሳሉ። በዚህ ጽሑፍ “Christ In Islam” በሚል ርዕስ ተጽፎ “ክርስቶስ በኢስላም” ተብሎ ወደ አማርኛ በተመለሰው አነስተኛ መጽሐፋቸው ውስጥ የፈጸሟቸውን ቅጥፈቶች ለአንባቢያን እናቀርባለን። በመጽሐፉ ገፅ 55 እና 56 ላይ “ግሪካዊ እንጂ ዕብራይስጥ አይደለም” በሚል ርዕስ ስር በጻፉት ጽሑፍ ሚስተር ዲዳት የአዲስ ኪዳን ግሪክ ቋንቋ ችሎታ ያላቸው በማስመሰል ራሳቸውን ለአንባቢያን ያቀርባሉ፡፡ አገልጋይ ከመሆኑ በፊት የግሪክ ቋንቋን ለአምስት አመታት ካጠና አንድ የሥነ መለኮት ሊቅ ጋርም ያደረጉትን ውይይትና ሊቁን እንዴት በክርክር እንደረቷቸውና እንዳሳፈሯቸው ይናገራሉ፡፡

ዲዳት እንዲህ ይላሉ፡ ብጹዕነታቸውን የግሪክ ቋንቋ ያውቁ እንደሆን ጠየቅኳቸው? <አዎ> አሉ፡፡ የብጹዕነት ማእረጋቸውን ከማግኘታቸው በፊት ለአምስት ዓመታት የግሪክ ቋንቋ ማጥናታቸውን አረጋገጡልኝ፡፡ ‹ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ› በሚለው አንቀፅ ውስጥ ‹እግዚአብሔር› (God) ለሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ የተሰጠው ትርጉም ምንድነው? በማለት ጠየቅኩ፡፡ አፈጠጡብኝ፣ መልስ ለመስጠት አልደፈሩም፡፡ ሆሲዬስ (HOTHEOS) የሚለው ቃል እንደሆነ ነገርኳቸው፡፡” [አነባበቡን ተርጓሚው በትክክል አላስቀመጠም፡፡ ሆስዬስ ሳይሆን ሆቴዎስ ነው፡፡]

ሚስተር ዲዳት ቅጥፈታቸውን ከዚህ ይጀምራሉ፡፡ “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” በሚለው ውስጥ “እግዚአብሔር” የሚለው ቶንቴዎን (TONTHEON) እንጂ ሆቴዎስ (HOTHEOS) አይደለም! ሚስተር ዲዳት ዋሽተዋል!

ይቀጥላሉ ሚስተር ዲዳት፡ ለብጹዕነታቸው የሚከተለውን ጥያቄ አቀረብኩ ‹ቃልም እግዚአብሔር ነበር (and the word was God) በሚለው ሐረግ እግዚአብሔር (God) ለሚለው ቃል የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ የሰጠው ትርጉም ምንድነው?› ብጹዕነታቸው ዝም አሉ፡፡ የግሪክ ቋንቋ ስለማያውቁ አልነበረም፡፡ ወይም ግሪክ አውቃለሁ በማለት አልዋሹም፡፡ ነገሩ ገብቷቸዋል፡፡ እንደተሸነፉ አረጋግጠዋል፡፡ አዎ and the word was God በሚለው አንቀፅ ውስጥ ለሚገኘው ‹God› ለሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ በተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠው ትርጉም ‹ቶንቲዎስ› (TONTHEOS) ነው፡፡”

ሚስተር ዲዳት በድጋሜ ዋሽተዋል! “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” በሚለው ውስጥ እግዚአብሔር ለሚለው በግሪክ ቋንቋ የገባው ቃል ቴዎስ (THEOS) የሚል እንጂ ቶንቴዎስ (TONTHEOS) የሚል አይደለም! በግሪክ ቋንቋ ቶንቴዎስ የሚል የቃል አጠቃቀም የለም፡፡ ከግሪክ ቋንቋ ስነ ልሳን አኳያም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ሚስተር ዲዳት በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የአብና የኢየሱስን አምላክነት ለመግለፅ ሐዋርያው ዮሃንስ አንዱን ቃል በተለያዩ መንገዶች በመጠቀሙ ምክንያት “አብ ትልቅ አምላክ ሲሆን ኢየሱስ ደግሞ ትንሽ አምላክ ነው” የሚለውን የይሖዋ ምስክሮች ያረጀ ክርክር ነው ለመጠቀም የሚሞክሩት፡፡ ይሁን እንጂ የክርክሩንም አካሄድ ሆነ የግሪኩን ቃላት አልተረዱም፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁኔታ አንድን የሥነ መለኮት ሊቅ እንደረቱና እንዳሳመኑ ጽፈዋል፡፡ እንግዲህ ይህ ታሪክ የሚስተር ዲዳት ፈጠራ መሆኑና እሳቸውም ምላሳቸውን አጣፍጠው ምሁር መስለው ለመታየት ቢሞክሩም ነገር ግን ሐሳዊ መምህርና አታላይ መሆናቸው በዚህ ታሪክ ውስጥ ለተጠቀሰው ምናባዊ “የሥነ መለኮት ሊቅ” ካልሆነ በስተቀር ለማናችንም ግልፅ ይመስለኛል፡፡ ሙስሊም ወገኖቼ ሆይ ስለምን እንዲህ ዓይነቶቹን ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌላቸውንና ለእውነት ግድ የሌላቸውን ሐሰተኛ መምህራን በመከተል ነፍሳችሁን ታጠፋላችሁ? እስከ መቼስ በሕይወታችሁ ትቀልዳላችሁ? እስከ መቼስ ትታለላላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ የልብ ዓይኖቻችሁን በመክፈት ወደ እውነት ይመራችሁ ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው።  

ሚስተር ዲዳት የክርስቶስን ስቅለት በተመለከት ከጆሽ ማክዱዌል ጋር ያደረጉትን ክርክር ያንብቡ። ክርስቶስ ተሰቅሏልን? 

 

መልሶቻችን