መልስ በአሕመድ ዲዳት

መልስ በአሕመድ ዲዳት

[አሕመድ ዲዳት የመናገርያ ቦታቸውን ሲይዙ ሕዝቡ በጭብጨባ ተቀበላቸው]

ክቡር ሰብሳቢና የችሎቱ ክቡራትና ክቡራን፤ የችግሩ አስኳል – በግልጽ የተቀመጠው የኢየሱስ ንግግር የሚያሳየው ከሞት እንደ ተመለሰ ደቀ መዛምርቱ በስህተት ማሰባቸው ነው፡፡ “በኔ እንደምታዩት መንፈስ ስጋና አጥንት የለውም” በማለት አረጋገጠላቸው፡፡ ይህ የኪንግ እንግሊዘኛ ነው፤ መሠረታዊ እንግሊዘኛ ነው፡፡ ምን እንደሚያመለክት ለማብራራት አንድ ሰው መዝገበ ቃላት ወይንም ደግሞ የሕግ አዋቂ አያስፈልገውም፡፡

በ27ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ርዝመትና ስፋት ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረ “ሞቼ ነበር ከሞት ተመልሼ መጥቻለሁ” የሚል አንድም ንግግር የለም [ሕዝቡ ለዚህ ንግግር አጨበጨበ]፡፡ ክርስቲያኖች ትንሳኤ የሚለውን ቃል አሁንም አሁንም ደጋግመው ያነሳሉ፡፡ አሁንም አሁንም በመደጋገም እውነታን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተደርጎ ተቆጥሯል፡፡ ሰውየው ምግብ ሲበላ ማየታችሁን ቀጥላችኋል ነገር ግን ከሞት ተነስቷል ትላላችሁ፡፡ በላይኛው ሰገነት ላይ ታይቷል – ከሞት ተነስቷል ትላላችሁ፡፡ በ27ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ “ከሞት ተመልሼ መጥቻለሁ” የሚለውን ቃል ትንፍሽ አላለም፤ አንዴም እንኳ!

ለ40 ቀናት ከነርሱ ጋር ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን ንግግር ትንፍሽ አላለም፡፡ ደግሞ ደጋግሞ ያ ራሱ ከሞት ያመለጠው ኢየሱስ መሆኑን እያረጋገጠላቸው ነው፤ በግልጽ እየነገራቸው ነው፡፡ ምክንያቱ እንዳይታወቅ እየተደበቀ ነበርና፡፡ ለአይሁድ ራሱን በግልጽ አላሳየም፡፡ ምልክት ሰጥቷቸዋል፡፡ “ከዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም፡፡” ብሏል፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ምንም ምልክት የለም፡፡ “ይኸው እዚህ አለሁ” በማለት ለነርሱ ለመንገር ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ተመልሶ አልሄደም፡፡ አንዴም እንኳ! እየተደበቀ ነበር፡፡ አሁን እንግዲህ ያለፉትን ነገሮች ደግመን ደጋግመን ማውራት የለብንም፡፡

ኢየሱስ ለመሞት እንቢተኛ አልነበረም የሚል ነጥብ ተነስቷል፡፡ በእርግጥ የመጣው ለዚህ ዓላማ ነበር ተብሏል፡፡ እንግዲህ የኔ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ የሚያሳየኝ እርሱ ፈቃደኛ አለመሆኑን ብቻ ሳይሆን ከአይሁዶች ጋር ግብ ግብ ለመግጠም ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር ነው፡፡ አያችሁ? በመጨረሻው እራት ላይ ራስን የመከላለል ችግር አነሳ፤ ለደቀ መዛሙርቱ “እንደምታታስታውሱት ለስብከትና ለፈውስ በላኳችሁ ጊዜ ምንም ነገር እንዳትይዙ ነግሬያችሁ ነበር፡፡ ያለ ኮረጆና ያለ ምርኩዝ፣ ያለ ብትር ነበር የላኳችሁ፡፡ አንዳች ጐደለባችሁን?” አላቸው፡፡ እነርሱም “በፍጹም” አሉ፡፡ “ነገር ግን አሁን እነግራችኋለሁ፤ ከናንተ መካከል ሰይፍ የሌለው ልብሱን ይሽጥና ይግዛ፡፡” ልብሳችሁን በመሸጥ ሰይፍ መግዛት አለባችሁ እያላቸው ነው፡፡ በሰይፍ ምን ምን ታደርጋላችሁ? የሚል ጥያቄ አቀርብላችኋለሁ፡፡ አፕል ትልጡበታላችሁ ወይንስ የሰው ጎሮሮ ትቆርጡበታላችሁ? በሰይፍ ምን ታደርጋላችሁ? እናም ከመካከላቸው አንዱ እንዲህ አለ “መምህር ሆይ ሁለት ሰይፎች አሉን፡፡” እርሱም “ያ ይበቃል” አለ፡፡

ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን ወሰደ – አስራ አንዱን፡፡ ይሁዳ እርሱን አሳልፎ ለመስጠት ሄዷል፡፡ አስራ አንዱ ደቀ መዛሙርትና እርሱ ሆነው ወደ ጌቴ ሰማኒ ሄዱ፡፡ እናም በጌቴ ሰማኒ – መጽሐፉን አንብቡት፤ ወንጌሎቻችሁን አንብቡ – ኢየሱስ ስምንቱን በበር ላይ እንዳስቀመጠ ይነግራችኋል፡፡ ሲጀመር ወደ ጌቴ ሰማኒ መሄድ ለምን አስፈለገው? ስምንቱን በበር ላይ አስቀምጦ “እዚህ ቆዩና ከኔ ጋር ጠብቁ” ለምን አላቸው?

“እዚህ ሁኑና ጥበቃ አድርጉ” ማለቱ ነው፡፡ ምንድነው የሚጠብቁት? በጌቴ ሰማኒ የሚጠበቅ ነገር ምን አለና? አጥር፣ የወይራ መጭመቂያ፣ ባዶ ቦታ ነው፡፡ ከከተማ አምስት ማይል ርቀት ላይ ደቀ መዛሙርቱ በጌቴ ሰማኒ ምን ነበር የሚጠብቁት? ከዚያም ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ከራሱ ጋር ወሰደ፡፡ በጥቂቱ ከነርሱ መካከል ሁለቱ ሰይፍ ነበራቸው፡፡ የውስጥ መስመር ጥበቃ ካደረገ በኋላ “እናንተ እዚህ ቆዩ፤ እዚህ ተቀመጡና ከኔ ጋር ጠብቁ፡፡ እኔ ፈንጠር ብዬ ሄጄ እጸልያለሁ… እኔ ብቻዬን ወደዚያ ሄጄ እጸልያለሁ፡፡” አላቸው፡፡ ወደ ጌቴ ሰማኒ ለምንድነው የሄደው? ብዬ እጠይቃችኋለሁ፡፡ ለምንድነው ወደዚያ የሄደው? – ሊጸልይ? የመጨረሻውን እራት ሊበላ በላይኛው ሰገነት በነበረ ጊዜ መጸለይ ይችል አልነበረምን? እነርሱ ከነበሩበት ቦታ የዲንጋይ ውርወራ ርቀት ላይ ወደነበረው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ሄዶ መጸለይ ይችል አልነበረምን? ከከተማ አምስት ማይል ርቀት መውጣት ለምን አስፈለገው? ስምንቱን በበር ላይ ማስቀመጥና የውስጥ መስመር መከላከያ ማድረግ ለምን አስፈለገው?

ጥቂት ወደፊት ሄዶ ወደ ፈጣሪ ጸለየ፡፡ “ኦ አባቴ ሆይ… ቢቻልስ ይህች ጽዋ ከኔ ትለፍ፡፡” ይህ ማለት “አስቸጋሪውን ነገር ከኔ አስወግድ፤ ነገር ግን እንደኔ ፍላጎት ሳይሆን እንዳንተ ፍላጎት ይሁን፤ በመጨረሻ ለአንተ እተዋለሁ፤ ነገር ግን እንድትታደገኝ እፈልጋለሁ” ማለት ነው፡፡ እናም በጭንቀት ውስጥ ሆኖ አጥብቆ ጸለየ፣ ላቡ በምድር ላይ እንደሚንጠባጠብ ብዙ የደም ነጠብጣብ ነበር፡፡ አንድ ሰው ራሱን ሊያጠፋ የሚሄደው በዚህ መልኩ ነውን?  ምድር ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ ለመስዋዕትነት የተወሰነ ሰው፤ ወኔው እንደዚህ ነው መሆን ያለበት? እጠይቃችኋለሁ፡፡

በጭንቀት ውስጥ ሆኖ እያላበው አጥብቆ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም በምድር ላይ እንደሚወርድ ብዙ የደም ነጠብጣብ ነበር፡፡ የምህረት አምላክ መልአኩን ላከ ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ መልአክ ሊያበረታው መጣ፡፡ መልአኩ በምን ሊያበረታው ነበር የመጣው? ሊያድነው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የተከሰተውን ነገር ሁሉ ስትመለከቱ ፈጣሪ ሊያድነው ሲያቅድ ታያላችሁ፡፡ ተመልከቱ፡፡ እውነታው፤ የተናገረው ትንቢት እንደ ዮናስ እንደሚሆን ነበር – እርሱ ግን እንደ ዮናስ እንዳልሆነ ተነግሮናል፡፡  አልፈጸመውም፡፡ ዮናስ ሕያው ነበር፣ ኢየሱስ ግን ሞቷል፡፡

ከዚያም ጳንጢዮስ ጲላጦስ – ኢየሱስ መሞቱ በተነገረው ጊዜ ተደነቀ፤ ምክንያቱም ከልምዱ በመነሳት ማንም ሰው በመስቀል ላይ በሦስት ሰዓታት ውስጥ እንደማይሞት ያውቃልና፡፡ ምክንያቱም ይህ ስቅለት የቀስታ ሞት ነው፡፡ ይህ ትክክለኛው የስቅለት ዓላማ ነው፡፡ ሕብረተሰቡን የሚያውክ ስነ ምግባር ያለውን ሰው ሰራዊት በመላክ፣ በማነቅ ወይንም በስለት በመውጋት ለማስወገድ እንደሚደረግ አይደለም፡፡ የቀስታ ሞት ነው፡፡

አጥንቶቹም አልተሰበሩም – ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ ይህ የትንቢት ፍጻሜ ነበር፡፡ እንግዲህ የሞተን ሰው አጥንት ብትሰብሩ ወይንም ደግሞ ባትሰብሩ የሚያመጣው ውጤት ኢምንት ነው፡፡ የአጥንቶቹ አለመሰበር ሊረዳው የሚችለው ሰውየው በሕይወት ካለ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ አያችሁ? ለሁለት ሺህ ዓመታት የሰዎችን ሐሳብ በሚፈለገው መንገድ የመቃኘት ተግባር ተፈፅሟል፤ በማያቋርጥ ሁኔታ የሰዎችን ሐሳብ ወደ አንድ አቅጣጫ መቃኘት፡፡ ጳውሎስ ሁሉንም የኃይማኖት ጉዳይ በአንድ ነጥብ ላይ አስምጧል፤ ሞትና ትንሣኤ ላይ በተባለው ጉዳይ ላይ፡፡ ምክንያቱም በ1ቆሮንቶስ ምዕራፍ  15 ቁጥር 14 ላይ “ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው፤ እምነታችንም ደግሞ ከንቱ ናት” ብሏልና፡፡ ረብ የለሽ ነው! ምንም ያተረፋችሁት ነገር የለም!

ስለዚህ እንግዲህ፣ እየሰጠሙ ያሉ ሰዎች ሳር ይዘው ለመትረፍ እንደሚፍጨረጨሩት ክርስቲያኖች በዚህም ሆነ በዚያ ስቅለት አንድን ሰው በመግደሉ ደህንነት ማግኘት መቻላችንን ማረጋገጥ ግድ ሊላቸው ነው፡፡ እንግዲህ፣ ክቡር ሰብሳቢ እንዲሁም የችሎቱ ክቡራትና ክቡራን ይህንን መጽሐፍ አንድ ጊዜ ደግማችሁ ምስክርነቶቹንም ቃል በቃል ታነቡ ዘንድ እንጠይቃችኋለን፡፡ ትንቢቶቹን ብትመረምሩ – ኢየሱስ የተናገረውንና ያሳየውን ባሕርይ ብትመለከቱ – ክርስቶስ ላለመሰቀሉ የድምዳሜ ማስረጃዎች ሆነው ታገኟቸዋላችሁ፡፡

[ሕዝቡ አጨበጨበ፣ ሚስተር ዲዳት ወደ ቦታቸው ተመልሰው ተቀመጡ፡፡]


ክርስቶስ ተሰቅሏልን? ማውጫ