መልስ በጆሽ ማክዱዌል
[ጆሽ ማክዱዌል የመናገርያ ቦታቸውን ሲይዙ ሕዝቡ በጭብጨባ ተቀበላቸው]
እኔው ራሴ መስማቴን እርግጠኛ አይደለሁም ነገር ግን እርስዎ “በ27ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ኢየሱስ ሞቶ መነሳቱን የተናገረበት አንድም ቦታ የለም” ብለዋልን? ከዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 1 ቁጥር 18 ላንብብሎት እንዴ? [ሕዝቡ ታላቅ ጭብጨባና ጩኸት አሰማ] “ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ” ብሏል፡፡ እንዲሁም ሚስተር ዲዳት ሆይ፤ ለአይሁድ ታይቷል እኮ፡፡ የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ በአይሁዶች ነበር የተጀመረችው፡፡ ለአይሁዳዊው ተቃዋሚ ለጳውሎስ የተርሴሱ ሳውል በነበረ ጊዜ ተገልጦለታል [ጭብጨባ]፡፡
ነገር ግን ክቡራትና ክቡራን፤ ስለ ትንሣኤ እንዲሁም ክርስቶስ ሕይወቴና አዳኜ መሆኑን ሳስብ፤ ለኔ ትልቁ ነገር፤ አንድ ሰው ስለ ኃጢኣታችን የሞተውን፣ የተቀበረውንና በሦስተኛውም ቀን የተነሳውን ክርስቶስን ይቅርታ በመጠየቅ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት የሚመሠርት ከሆነ መንፈስ ቅዱስ ወደ ሕይወቱ በመምጣት እንደሚለውጠው ያሕዌ እግዚአብሔር ቃል መግባቱ ነው፡፡ ለዚህ ትልቅ ማስረጃ ከሆኑት መካከል የኔ የራሴ ሕይወት አንዱ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኜና ጌታዬ ተቀብዬ ፈቃዴን ለርሱ ሳስገዛና እርሱን ሳምን፤ ክቡራትና ክቡራን፤ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ወይንም አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የሕይወቴ አንኳር ክፍሎች ተለወጡ፡፡
መጀመርያ የተቀደሰና እግዚአብሔርን የሚመስል ሕይወት የመኖር ፍላጎት አደረብኝ፡፡ ሁለተኛ ሰላምና እውነተኛ ደስታን መለማመድ ጀመርኩኝ – ግጭቶች ስላልነበሩብኝ አልነበረም – ከግጭቶች ባሻገር እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከሚሰጠው ደስታ የተነሳ ነው፡፡ ሦስተኛ፤ ቁጣዬን መቆጣጠር ችያለሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአንደኛ ዓመት ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ወጣት ሰው ልገድል ደርሼ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ቁጣዬን መቆጣጠር ይሳነኝ ነበር፡፡ ኢየሱስን እንደ አዳኜና ጌታዬ ካመንኩት በኋላ ግን ቁጣዬን ለመቆጣጠር የማልችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሴ በፊት በመንቃት ራሴን መግዛት ጀመርኩኝ፤ እናም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተወገደ!
ወዳጆቼ ያንን ከማወቃቸው ባሻገር ባላንጣዎቼም አስተውለውት ነበር፡፡ ከያሕዌ እግዚአብሔር አብ ጋር ዘላለማዊ ቃል በሆነው በልጁ በኩል ሕብረት ካገኘሁ በኋላ በ22 ዓመታት ውስጥ ቁጣዬን መቆጣጠር የማልችልበት ደረጃ ላይ የደረስኩት አንዴ ብቻ ነበር፡፡ እርሱን ድል የምነሳበትን ልዕለ ተፈጥሯዊ ኃይል አጎናፅፎኛል፡፡
ክቡራትና ክቡራን እዚህ ላካፍላችሁ የምችለው የማመሰግንበት ትልቁ ጉዳይ የእግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ አባቴ የከተማይቱ ታዋቂ ሰካራም ነበር፡፡ አባቴ ሳይሰክር ያየሁበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ ጓደኞቼ በትምህርት ቤት አባቴ ራሱን ሲያጃጅል የሚያሳዩ ቀልዶችን ይቀልዱብኝ ነበር፡፡ የኛ ቀዬ እርሻ ላይ ስለነበር እናቴ ክፉኛ በአባቴ ተደብድባ መራመድ ተስኗት በቦይ ውስጥ በከብቶች አዛባ ውስጥ ተኝታ አገኛት ነበር፡፡
ሊጎበኙን የሚመጡ ወዳጆች ስለነበሩ በፊታቸው ላለማፈር ብዬ አባቴን ወስጄው ጥጋት ውስጥ አስረውና ከጎን መኪና በማቆም አባቴ በጣም አስፈላጊ ለሆነ ጉዳይ መንገድ መሄዱን እናገር ነበር፡፡ ጥጆች ወደሚያድሩበት ጥጋት ወስጄው እጆቹን በሳንቃ ውስጥ አሾልኬ አስረዋለሁ፡፡ ሸምቀቆ በአንገቱ አስገብቼ ጭንቅላቱን በሳንቃ ላይ በማሳለፍ እግሩን ካቀያየረ ራሱን አንቆ ሊገድል በሚችልበት ሁኔታ ገመዱን እግሩ ላይ አስር ነበር፡፡
ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመመረቄ ከሁለት ወራት በፊት አንድ ምሽት ውጪ ቆይቼ ወደ ቤት ተመለስኩኝ፡፡ ልክ በሩን አልፌ ስገባ እናቴ ተንሰቅስቃ ስታለቅስ ሰማኋት፡፡ “ምንድነው የሆንሽው?” ብዬ ጠየቅኋት፤ “አባትህ ልቤን ሰብሮታል፡፡ አሁን የምፈልገው ብቸኛ ነገር ቢኖር ያንተን ምርቃት ማየትና መሞት ነው” አለችኝ፡፡
ታውቃላችሁ? ከሁለት ወራት በኋላ ተመረቅሁኝ፡፡ በሚቀጥለው አርብ በ13ኛው ቀን ላይ እናቴ አረፈች፡፡ ከልብ ስብራት የተነሳ እንደማትሞቱ አትንገሩኝ፡፡ እናቴ ከዚያ የተነሳ ሞታለችና፡፡ ልቧን የሰበረው ደግሞ አባቴ ነው፡፡ ከርሱ በላይ ልጠላው የምችለው ሰው አልነበረም፡፡ ነገር ግን ክቡራትና ክቡራን፤ በዘላለማዊ ልጁ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከያሕዌ እግዚአበሔር ጋር ወደዚህ ሕብረት ከመጣሁ ከትንሽ ጊዜ በኋላ የእግዚአብሔር ፍቅር ሕይወቴን ገዛው፤ ያንን ጥላቻ ከላዬ ላይ ፈጽሞ አስወገደው፡፡
አባቴን ትኩር ብዬ ዐይኖቹ ውስጥ በመመልከት፤ “አባዬ እወድሃለሁ” ማለት ቻልኩኝ፡፡ ያንን ስል ከልቤ ነበር! ከዚያም ዩኒቨርሲቲ ተዘዋወርኩኝ፡፡ ከባድ የሆነ የመኪና አደጋ ስለደረሰብኝ እግሮቼ፣ እጄና አንገቴ ተናግተው ነበር፡፡ ወደ ቤት ተወሰድኩኝ፡፡ አባቴም ሊያየኝ ወደ ነበርኩበት ክፍል ገባ፡፡ ለሞት የተቃረብኩ ስለመሰለው በጣም ያለቅስ ነበር፡፡ እንዲህ የሚል ጥያቄ ጠየቀኝ፤ “እንደኔ ዓይነቱን አባት እንዴት መውደድ ትችላለህ?” እንዲህ አልኩት፤ “አባዬ ከስድስት ወራት በፊት እጠየፍህ፣ እጠላህ ነበር፡፡” ከዚያም እግዚአብሔር አብ ያሕዌ፤ ዘላለማዊ ቃሉ በሆነው በልጁ በኩል ለኛ ለሰው ልጆች ራሱን እንደገለጠ ማወቄን አወጋሁት፡፡ ሚስተር ዲዳት ሆይ፤ እርሱ በሥቃይ ውስጥ በማለፍ ስለኃጢኣታችን ሞቷል፡፡
የዓለምን ሁሉ ኃጢኣት ማሰብ የሚችሉ ከሆነ – የኔና የርስዎ ኃጢኣት ብቻ በቂ ነበር፡፡ ነገር ግን የዓለም ኃጢኣት ሁሉ በወልድ ላይ ነበር፡፡ ያንን በሚያክል ሥቃይ ውስጥ ነበር ያለፈው፡፡ እንዲህ አልኩት፤ “አባዬ ክርስቶስ ይቅር እንዲለኝ ጠይቄዋለሁ፡፡ እንደ አዳኜና እንደ ጌታዬ ወደ ሕይወቴ እንዲመጣ ጋብዤዋለሁ፡፡ አባዬ ከዚህ የተነሳ አንተን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ሰዎች ባሉበት ሁኔታ መቀበል የምችልበትን አቅም አግኝቻለሁ፡፡”
ሚስተር ዲዳት ሆይ፤ ትኩር ብዬ ዓይኖችዎ ውስጥ በማየት እንዲህ ልሎት እችላለሁ፡- “ከልቤ እወድዎታለሁ… በጣም እወድዎታለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኝዎና ጌታዎ ተቀብለው እንዳይ እናፍቃለሁ፡፡” [ሕዝቡ አጨበጨበ] መጨረሻ ላይ አባቴ እንዲህ አለ፡- “ልጄ፣ እግዚአብሔር በሕይወትህ ውስጥ ሲሠራ ያየሁትን ነገር በኔም ሕይወት ውስጥ መሥራት ከቻለ፣ በግሌ ላውቀው እፈልጋለሁ፡፡”
እዚያው ቦታ ላይ ሆኖ አባቴ የሚከተለውን የሚመስል ጸሎት ጸለየ፡- “እግዚአብሔር ሆይ አንተ በእውነት አምላክ ከሆንክ፣ ክርስቶስም ደግሞ ዘላለማዊ ቃል፣ ልጅህ ከሆነ፣ ይቅር ልትለኝና ወደ ሕይወቴ በመምጣት ልትለውጠኝ የምትችል ከሆነ በግሌ ላውቅህ እፈልጋለሁ፡፡”
ክቡራትና ክቡራን፤ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ተኩል ባለው ጊዜ ውስጥ ሕይወቴ መሰረታዊ በሆነ ሁኔታ ተለወጠ፡፡ አሁንም ድረስ እግዚአብሔር ሊለውጣቸው የሚገባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን እስኪ አባቴን ውሰዱት፡፡ ሕይወቱ እዚያው ዐይኔ እያየ ተለወጠ፡፡ ሚስተር ዲዳት ሆይ፤ ልክ አንድ ሰው እጁን ዘርግቶ የመብራት አምፖል እንዳበራ ዓይነት ነበር፡፡ ታውቃላችሁ? ከዚያ በኋላ አንድ ጊዜ ብቻ ነበር ውስኪ በእጁ የነካው፡፡ ከንፈሩን አስነካ፤ ከዚያ ያለፈ ነገር አልነበረም፡፡ ከዚያ በኋላ አላስፈለገውም፡፡ ከአስራ አራት ወራት በኋላ ሞተ፡፡ ምክንያቱም ከ40 ዓመታት በላይ የጠጪነት ሕይወት በኋላ የሆድ እቃው ሦስት አራተኛ ከጥቅም ውጪ ሆኖ ነበርና፡፡ ነገር ግን ታውቃላችሁ? ክቡራትና ክቡራን፤ ከከተማይቱ ሰካራሞች መካከል አንዱ የሆነው ሰው ሕይወት ከመለወጡ የተነሳ ብዙ በከተማ ውስጥና በዙርያው ይኖሩ የነበሩ ነጋዴዎች በዘላለማዊው ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ሰጡ፡፡
ባለቤቴ ዶቲ በዚህ መልኩ ታስቀምጠዋለች፡፡ እንዲህ ትላለች፡- “ክርስቶስ ከሞት ስለተነሳ ሕያው ነው፡፡ ሕያው ስለሆነ ወደ ሰዎች ሕይወት በመግባት በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ውስጣዊውን ማንነታቸውን የመለወጥ ያልተገደበ ኃይል አለው፡፡” ለዚህ ነው ከሞ-ት የተነሳው ሕያው የሆነው ክርስቶስ ከ27ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መካከል በአንዱ ውስጥ “ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ” ያለው፡፡ ስለዚህ እርሱ እንዲህ ማለት ይችላል፡ “እነሆ በሕይወታችሁ ደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፡፡ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ፡፡”
[ሕዝቡ አጨበጨበ፣ ጆሽ ወደ ቦታቸው ተመልሰው ተቀመጡ፡፡]