መክፈቻ በአሕመድ ዲዳት

መክፈቻ በአሕመድ ዲዳት

ክቡር ሰብሳቢ፣ ክቡራትና ክቡራን፤ ስቅለትን በተመከለከተ ሙስሊም የአምላክ የመጨረሻውና የመደምደሚያው መገለጥ በሆነው በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ እንዲህ ተብሎ ተነግሮታል፡-

وَقَوْلِهِمْ إِنَّا قَتَلْنَا الْمَسِيحَ عِيسَى ابْنَ مَرْيَمَ رَسُولَ اللَّهِ وَمَا قَتَلُوهُ وَمَا صَلَبُوهُ وَلَٰكِن شُبِّهَ لَهُمْ ۚ وَإِنَّ الَّذِينَ اخْتَلَفُوا فِيهِ لَفِي شَكٍّ مِّنْهُ ۚ مَا لَهُم بِهِ مِنْ عِلْمٍ إِلَّا اتِّبَاعَ الظَّنِّ ۚ وَمَا قَتَلُوهُ يَقِينًا [٤:١٥٧]

“አልገደሉትም አልሰቀሉትምም፡፡ ግን ለእነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፡፡ እነዚያም በእርሱ ነገር የተለያዩት ከእርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በእርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም አልገደሉትም፡፡”

ክቡር ሰብሳቢ፣ ክቡራትና ክቡራን፤ ከዚህ የላቀውን እምነት ለማወጅ አንድ ሰው ከዚህ በላይ ግልጽና የማያወላውል ንግግር ሊጠቀም ይችላልን? መሰል ቃላትን የመናገር ሥልጣን ያለው ሁሉን አዋቂ የሆነው የአፅናፈ ዓለም ጌታ ብቻ ነው፡፡

ሙስሊም ይህንን ሥልጣናዊ ንግግር እንደማይሻር የአምላክ ቃል ይቀበላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ምንም ጥያቄ አይጠይቅም፣ ምንም ማረጋገጫም አይፈልግም፡፡ “እነሆ የጌታዬ ቃሎች፣ አመና ሰደቅና (አምናለሁ፣ አረጋግጣለሁ)” ይላል፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኑ በተከበሩት እንግዳችን ቃላት ምላሽ ይሰጣል፡፡ ጆሽ ማክዱዌል ከዶን ስቴዋርት ጋር “የአስቸጋሪ ጥያቄዎች መልሶች” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው ገጽ 116 እና 117 ላይ ለዚህ የማያወላዳ የሙስሊም ንግግር የክርስትናን ምላሽ አስፍረዋል፡፡ እንዲህ ይላል፡- “የሙሐመድን ዘገባ ለመቀበል  አስቸጋሪ የሚሆንበት ምክንያት አዲስ ኪዳን የኢየሱስን ሕይወትና አገልግሎት በተመለከተ ቀዳሚ የዐይን ምስክሮችን ዘገባ የሚያቀርብ መሆኑና የርሱ ምስክርነት ነገሩ ከተከሰተ ከ600 ዓመታት በኋላ የተገኘ መሆኑ ነው፡፡”

በአጭሩ የክርስቲያን ጥያቄ “ስቅለት ከተከሰተበት ቦታ በአንድ ሺህ ኪሎ ሜትሮችና በ600 ዓመታት ርቆ የነበረ ሰው በኢየሩሳሌም ውስጥ የተፈጸመውን ክስተት ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው?” የሚል ነው፡፡ የሙስሊም መልስ ግን “እነዚህ የሁሉን ቻዩ አምላክ ቃሎች ናቸው! ስለዚህ ምን እንደተፈጸመ አምላክ ያውቃል!” የሚል ነው፡፡ ይህንን መጽሐፍ፣ ማለትም ቁርኣንን እንደ አምላክ ቃል ቢቀበል ኖሮ በመካከላችን ምንም ዓይነት ክርክር እንደማይኖር ክርስቲያኑ ይገነዘባል፡፡ እንደርሱ ቢሆን ኖሮ ሁላንችንም ሙስሊሞች በሆንን ነበር!

እነዚህን ክስተቶች በተመለከተ ጉዳዩን ያዩና የሰሙ ምስክሮች የሰጡት ዘገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሯል፤ በተለይም ደግሞ በማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ወንጌላት ውስጥ እናገኛለን፡፡ እንግዲህ ይህ ስቅለት የሚያመለክተው የሚከተለውን ነው፡፡ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ አማካይነት በስቅለት ተገድሏል፡፡ በዚህም መሠረት አይሁድ ኢየሱስን በመግደል ወንጀለኞች ሆነዋል፡፡ ክርስቶስ ስላልተገደለና ስላልተሰቀለ እኛ ሙስሊሞች አይሁድ ንጹሃን መሆናቸው ተነግሮናል፡፡ ስለዚህ እኔ አይሁድን ከክርስቲያኖች ክስ እንድከላከላቸው በቁርኣን አደራ ተሰጥቶኛል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ዛሬ ለአይሁድ የምሟገተው የአጎቴ ልጆች በመሆናቸው ምክንያት ሳይሆን ፍትህ ተግባራዊ መሆን ስላለበት ነው፡፡ ከአይሁድ ጋር የየራሳችን የሆኑ ልዩነቶች አሉን – ያ ባጠቃላይ ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ከሰዓት በኋላ ለአጎቴ ልጆች፣ ለአይሁድ ፍትህን ለማምጣት የተቻለኝን አደርጋለሁ፡፡

እንግዲህ በዚህ ሙግት፣ በዚህ ክርክር፣ በዚህ ውይይት፣ እኔ የአይሁድ ጠበቃ ነኝ፤ ጆሽ ማክዱዌል ደግሞ የከሳሽ ወገን ናቸው፡፡ ክቡራትና ክቡራን፣ እናንተ ደግሞ የችሎቱ ታዳሚያን ናችሁ፡፡ ተዝናንታችሁ በመቀመጥ በመጨረሻ አይሁድ በክርስቲያኖች ከተመሠረተባቸው ክስ ነጻ መሆን አለመሆናቸውን ፍርዱን ለልቦናችሁ፣ ለገዛ ህሊናችሁ ትሰጡ ዘንድ እሻለሁ፡፡

እንግዲህ ወደ ነጥቡ ስንገባ፤ እንደ አይሁድ ጠበቃ ከሳሹን ወገን የነዚህን ምስክሮች ምስክርነት፣ ማለትም የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስን ምስክርነት እንዲያቀርቡ እጠይቃለሁ፡፡ ይህንን ጥያቄ በማቅረብ ብቻ ምስክሮቹ መሃላ ፈፅመው በሚቀርቡበት ጊዜ የመጀመርያ ጽሑፎቻቸው በሚያሳዩት መሠረት ብቁ አለመሆናቸውን  በማስረዳት ይህንን ክስ በየትኛውም በሰለጠነ አገር በሚገኝ ፍርድ ቤት በሁለት ደቂቃ ውስጥ ውድቅ ማድረግ እችላለሁ፡፡ ማረጋገጫ ልስጣችሁ – የትኛውንም የኪንግ ጀምስ መጽሐፍ ቅዱስ ወስዳችሁ ብትመለከቱ በያንዳንዱ መክፈቻ ላይ “ወንጌል እንደ ቅዱስ ማቴዎስ፣ ወንጌል እንደ ቅዱስ ማርቆስ፣ ወንጌል እንደ ቅዱስ ሉቃስ፣ ወንጌል እንደ ቅዱስ ዮሐንስ” በማለት ይጀምራሉ፡፡ ክቡራትና ክቡራን፤ እነዚህ “እንደ… እንደ… እንደ…” የሚሉት ምንድናቸው? የሚል ጥያቄ አቀርባለሁ፡፡ ምን ማለት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ? ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ስሞቻቸውን አላሰፈሩባቸውም ማለት ነው፡፡ እነዚህ የነርሱ ሥራዎች መሆናቸው በግምት ብቻ የተነገረ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በሰለጠነው ዓለም ውስጥ በሚገኝ በየትኛውም ፍርድ ቤት በሁለት ደቂቃ ውስጥ ውድቅ ይሆናሉ፡፡

በዚህ ብቻ አያበቃም፤ በየትኛውም በሰለጠነ ዓለም ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት ይህንን ክስ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ሁለት ጊዜ ውድቅ እንዲሆን አደርገዋለሁ፡፡ ሁለት ጊዜ ያልኩበት ምክንያት ከምስክሮቹ መካከል አንዱ የሆነው ማርቆስ በምዕራፍ 14 ቁጥር 50 ላይ በጣም ወሳኝ በሆነው የኢየሱስ የሕይወት መስቀለኛ ጊዜ ላይ ሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ጥለውት እንደሸሹ ስለሚናገር ነው፡፡ ሁሉም! በቦታው ላይ ካልነበሩ በቦታው ላይ ያልነበሩ ሰዎች ምስክርነት ከፍርድ ቤት ይጣላል፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት በሁለት ደቂቃ፣ በ120 ሴኮንዶች ውስጥ ክሱ ያከትማል፡፡ በየትኛውም ፍርድ ቤት፤ በየትኛውም በዓለም ውስጥ በሚገኝ የሰለጠነ አገር [ተቀባይነት የለውም]፡፡

ነገር ግን ምኑ ነው የሚያዝናናው ታድያ? አስፈሪ የሆነው ዝናብ ሳይበግራችሁ ከሩቅ ቦታዎች መጥታችኋል፡፡ እንግዲህ “ክሱ ስለተዘጋ ወደ ቤታችሁ ሂዱ” ብንላችሁ ምኑ ያዝናናል? እናንተን ለማስደሰት፣ ለክርክሩ ብዬ እነዚህን መዛግብት እንደ ተዓማኒ መዛግብት እቀበላለሁ፡፡ አሁን  እነዚህን ምስክሮች ለምርመራ በሳጥኑ ውስጥ እናቆማቸዋለን፡፡ እውነቱ የቱ ጋር እንዳለ እንድታዩ እፈልጋለሁ፡፡

የምጠራው የመጀመርያው ምስክር ቅዱስ ሉቃስን ይሆናል፡፡ በክርስቲያን ሊቃውንት ቅዱስ ሉቃስ ከታላላቅ የታሪክ ጸሐፍት መካከል አንዱ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ እንደ ታሪክ መጽሐፍ፣ የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ለየት ያለ ነው፡፡ አሁን ቅዱስ ሉቃስ ምዕራፍ 24 ቁጥር 36ን አገኘን፡፡ ምን እንዳለ ልነግራችሁ ነው – በግልጽ የተጻፈውን [ላሳያችሁ ነው]፡፡ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን ራት ወደበላበት ወደዚያ የላይኛው ቤት የገባው እሑድ ማታ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ይህ እንግዲህ ተፈፀመ ከተባለው ከስቅለቱ በኋላ ሦስተኛው ቀን ላይ መሆኑ ነው፡፡ ወደ ውስጥ ገብቶ “ሰላም ለናንተ ይሁን” በማለት ምኞቱን ገለጸላቸው፡፡ “ሰላም ለናንተ ይሁን” ባለ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ፈሩ፡፡ እውነት ነውን? እንጠይቃለን፡፡ ደቀ መዛሙርት ስለምን ፈሩ ብዬ እጠይቀዋለሁ፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው የጠፋውን መምህሩን፣ አያቱን፣ ጉሩውን፣ ረቢውን ከብዙ ጊዜ በኋላ ያገኘ እንደሆን – እኛ ምስራቃውያን አቅፈን እንስመዋለን፡፡ ታድያ ደቀመዛሙርቱ ለምን ይሆን የፈሩት? ሉቃስ የፈሩበትን ምክንያት ሲነግረን “መንፈስ ያዩ ስለመሰላቸው ነው” ይለናል፡፡

እኔ እርሱ ያለውን ብቻ ነው የምናገረው፡፡ እናንተ በቤታችሁ ከመጽሐፍ ቅዱሳችሁ ልታረጋግጡ ትችላላችሁ፡፡ ፈሩ፣ ተርበተበቱ ምክንያቱም መንፈስ እንደሆነ መስሏቸዋልና፡፡ መንፈስ ይመስላልን? ብዬ ሉቃስን እጠይቀዋለሁ፡፡ እርሱም “አይ” ብሎ ይመልስልኛል፡፡ በዓለም ላይ የሚገኙትን ክርስቲያኖች ሁሉ ደግሜ ደጋግሜ እጠይቃቸዋሉ፣ መንፈስ ይመስላልን? እነርሱም “አይመስልም” ብለው ይመልሱልኛል፡፡ ታድያ የማይመስል ከሆነ ለምንድነው ሰውየው መንፈስ እንደሆነ ያሰቡት?

እናም ሁሉም ሰው እንቆቅልሽ ይሆንበታል – ጆሽ ካላብራሩልን በስተቀር፡፡ ክርስቲያኖች ሁሉ እንቆቅልሽ ይሆንባቸዋል፡፡ ሰውዬው መንፈስ የማይመስል ከሆነ ለምንድነው መንፈስ ነው ብለው ያሰቡት? ልንገራችሁ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መምህራቸው በመስቀል ላይ መሰቀሉን በወሬ ወሬ መስማታቸው ነው፡፡ ነፍሱን መስጠቱን በወሬ ወሬ ስለሰሙ ነው፡፡ በሌላ አባባል፡- ነፍሱ ወጥታለች፤ ሞቷል፡፡ መሞቱንና ለሦስት ቀናት መቀበሩን በወሬ ወሬ ነው የሰሙት፡፡ የነበራቸው መረጃ ሁሉ የወሬ ወሬ ነው፤ ምክንያቱም መጀመርያ ላይ እንዳልኩት በሌላው ምስክራችሁ መሠረት ወሳኝ በሆነ የኢየሱስ ሕይወት መስቀለኛ ጊዜ ላይ ሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ጥለውት ሸሽተዋልና! በቦታው አልነበሩም!

ስለዚህ ያላችሁ መረጃ ሁሉ የወሬ ወሬ ሆኖ ሳለ ከሞተ ሦስት ቀን የሆነውን ሰው አገኛችሁት እንበል፡፡ እናንተ በመቃብሩ ውስጥ ሆኖ የሸተተ መስሏችኋል፡፡  እንዲህ ዓይነቱን ሰው ስታዩት መፍራታችሁ የማይቀር ነው፡፡ ኢየሱስም እነርሱ የሚያስቡትን እንዳልሆነ ሊያረጋግጥላቸው ፈለገ፡፡ ከሞት የተመለሰ መስሏቸው ነበር፡፡ ትንሣኤን ያገኘ መንፈስ የሆነ አካል [መስሏቸዋል] – እናም እንዲህ አላቸው – እኔ ሉቃስ ያለውን ብቻ ነው የምጠቅሰው – “እነሆ እጆቼና እግሮቼን እዩ፤ እኔው ራሴ መሆኔን እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፡፡ እኔ ተመሳሳይ ሰው ነኝ [አልተለወጥኩም]፣ ምን ሆናችሁ? ለምንድነው የምትፈሩት? ይኸው ዳሳችሁ እዩኝ፡፡ ነክታችሁ እዩኝ፡፡ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና” [አላቸው፡፡]

የትኛውም መንፈስ እኔ እንዳለኝ ሥጋና አጥንት የለውም፡፡ ሥጋና አጥንት ካለኝ መንፈስ አይደለሁም ማለት ነው፡፡ ሁሉም ሰው ከዚህ ጋር ይስማማል፡፡ ሥጋና አጥንት ስላለኝ – እንግሊዘኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋው የሆነውን – እንግሊዛዊውን ሰው ልጠይቀው፡፡ መንፈስ አይደለሁም፤ የሙት መንፈስ አይደለሁም፡፡

እናንተ በምትናገሩት ቋንቋ ከዚህ የተለየ ትርጉም አለውን? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ እናንተ የደቡብ አፍሪካ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ አንድ ሰው በናንተ ቋንቋ የሆነ ነገር ቢነግራችሁ የተጠቀመው ቃል ከምታውቁት የተለየ ትርጉም ይኖረዋል ብላችሁ ታስባላችሁ ወይ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ፡፡ ያ ማለት መንፈስ አይደለም፣ የሙት መንፈስ አይደለም ማለት ነው፡፡ ሁሉም ሰው ከዚህ ጋር ይስማማል፡፡ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም ብሎ አንድ ሰው ሲነግራችሁ በቃ ሥጋና አጥንት የለውም ማለት ነው፡፡ እንደምታዩት እኔ እነዚህ ነገሮች ስላሉኝ እናንተ የምታስቡትን አይደለሁም ማለት ነው፡፡ የሞትኩና ከሙታን የተመለስኩ ከሞት የተነሳሁ መስሏችኋል፡፡ መንፈስ ሥጋና አጥንት ከሌለው የምትመለከቱት አካል የተለወጠ አይደለም ማለት ነው፡፡ የተቀየረ አካል አይደለም፤ የትንሣኤ አካል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከሞት የተነሳ አካል መንፈስ ይሆናልና፡፡

ማነው ይህንን ያለው? መረጃውን ያገኘሁት ከኢየሱስ ነው፡፡ “የት?” ብላችሁ ብትጠይቁኝ ሉቃስ 20፡36ን ተመልከቱ እላችኋለሁ፡፡ ምን አለ? ታውቃላችሁ? አይሁድ ብዙ ጊዜ እንቆቅልሾችን ይዘው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር፡፡ ሁል ጊዜ “መምህር ሆይ ለቄሣር ግብር መክፈል ይገባናልን? መምህር ሆይ ይህችን ሴት የሆነ ነገር ስታደርግ አገኘናት ምን እናድርግ? መምህር ሆይ…” በማለት መልሰው መላልሰው ይጠይቁታል፡፡ አሁንም ደግመው በመምጣት ጠየቁት ይላል፡፡ “መምህር” በእብራይስጥ ረቢ – “መምህር ሆይ በመካከላችን አንዲት ሴት ነበረች፤ ይህችም ሴት እንደ አይሁድ ልማድ ሰባት ባሎች ነበሯት፡፡” አያችሁ? በአይሁድ ልማድ መሠረት አንድ ሰው ወንድሙ ልጅ ሳያፈራ ከሞተ የወንድሙን ሚስት ያገባታል፡፡ እርሱም መውለድ ካልቻለ ሦስተኛው ወንድም ያገባታል፣ አራተኛውም፣ አምስተኛውም፣ ስድስተኛውም፣  ሰባተኛውም እንደዚያው ያደርጋሉ፡፡

ሰባት ወንድማማቾች ይህችን ሴት ተፈራርቀው አግብተዋታል፡፡ በዚህ ምድር ላይ ሳሉ ችግር አልነበረም ምክንያቱም ሁሉም ያገቧት በየተራ ነበርና፡፡ እንግዲህ ሁሉም በምድር ላይ በነበሩ ጊዜ ስላገቧት በሰማይ ማን እንደሚያገባት እንዲያሳውቃቸው ነው የፈለጉት፡፡ በሌላ አባባል ሁላችንም በአንድ ቅፅበት እንደምንነሳ ስለምናምን በሰማይ ጦርነት ሊኖር ነው፡፡ ሁሉም አንድ ላይ በአንድ ጊዜ – ሰባቱም ወንድማማቾች በአንድ ቅፅበት ነቅተው ይህችን ሴት በማየት “ሚስቴ! ሚስቴ!” ይላሉ፡፡ እናም በዚህች ሴት ምክንያት በሰማይ በወንድማማች መካከል ፍልሚያ ሊደረግ ነው፡፡

በሌላ አባባል እርሷን ሊያገኛት የሚችል ማን እንደሆነ እንዲያሳውቃቸው ነው የፈለጉት፡፡ ሉቃስ 20፡36ን ተመልከቱት፡፡ ለዚያ ምላሽ ከሙታን ስለሚነሱ ወንዶችና ሴቶች ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- “ከንግዲህ በኋላ ተመልሰው አይሞቱም፡፡” በሌላ ቋንቋ አንዴ ከተነሱ ኢ-ሟቲ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይኸ ሥጋ ሟች ነው፡፡ ምግብ፣ መጠለያ፣ ልብስ፣ ፍትወት፣ እረፍት ይፈልጋል፡፡ ያለነዚህ ነገሮች የሰው ልጆች ህልውና ያከትማል፡፡ ያ አካል ኢ-ሟቲ በመሆኑ ምግብ፣ መጠለያ፣ ልብስ፣ ፍትወት፣ እረፍት አያስፈልገውም፡፡ ዳግመኛም እንደማይሞቱ ነገራቸው፡፡ ከመላእክት ጋር እኩል ናቸውና፡፡

በሌላ አባባል መልአካውያን ይሆናሉ፤ መንፈሳውያን ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ መንፈሳውያን ፍጥረታት ይሆናሉ፡፡ መንፈስ ይሆናሉ! ከመላእክት እና ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር እኩል ናቸውና፡፡ የትንሣኤ ልጆች እንደዚህ ናቸው – መንፈስ! “በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም” አላቸው፡፡ በሌላ አባባል “ከሞት አልተነሣሁም” እያለ ነው፡፡ ከደስታና ከመደነቅ የተነሳ አላመኑም – አሁንም ሉቃስ 24ን ተመልከቱ፡፡ ከዚያስ ምን ሆነ?

ሰውየው ሞቶ ምናልባትም በመቃብሩ ውስጥ እየበሰበሰ ያለ መስሎናል፡፡ ከደስታ የተነሳ አላመኑም – ከልክ ያለፈ ደስታ ተሰምቷቸዋል – የሆነው ነገር አልገባቸውም፡፡ “በዚህ የተጠበሰ ዓሣና ማር አላችሁን? ማለትም የሚበላ ነገር?” [ብሎ ጠየቃቸው]፡፡ የዳቦ ቁራሽ ሰጡት፣ እያዩትም በፊታቸው በላ፡፡ ምንን ለማረጋገጥ ነው ያንን ያደረገው? ምን ለመግለጥ ፈልጎ ነው? በማለት የችሎቱን ክቡራትና ክቡራን እጠይቃለሁ፡፡ ምን? “እኔ ከዚህ ቀደም የምታውቁት ሰው ነኝ፤ የምታስቡትን አይደለሁም፤ ከሞት አልተመለስኩም” እያላቸው ነው፡፡

ይህ ተከሰተ ከተባለው ስቅለት በኋላ እሑድ ምሽት ነው፡፡

እስኪ ወደ ኋላ እንመለስ፡፡ ጠዋት ምን ሆነ? የናንተ ሌላው ምስክር ዮሐንስ 20፡1 መግደላዊት ማርያም ወደ ኢየሱስ መቃብር የሄደችው እሑድ ማለዳ ከሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደነበር ይነግረናል፡፡ ለምን ወደዚያ ሄደች? ብዬ ዮሐንስን እጠይቀዋለሁ፡፡ ወይንም ደግሞ ሌላውን ምስክራችሁን ማርቆስ 16፡1 በቦታው ላይ እናስቀምጥ፡፡ ማርቆስ ሆይ እስኪ ንገረን – ማርያም ለምንድነው ወደዚያ የሄደችው? ማርቆስም “ልትቀባው ሄደች” ይለናል፡፡ እንግዲህ መቀባት ለሚለው ቃል የእብራይስጥ አቻው መሲህ የሚለውን ቃል ያስገኘው “መሳሃኽ” የሚል ቃል ነው፡፡ በአረብኛ መሲህ ይላል፡፡  አረብኛውና እብራይስጡ ተመሳሳይ ስረወ ቃል ነው ያላቸው፡፡ መሲህ ማለት መዳሰስ፣ ማሸት፣ መቀባት ማለት ነው፡፡

አይሁድ ከሦስት ቀን በኋላ አስክሬን ያሻሉን? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ መልሱ አያሹም የሚል ነው፡፡ እናንተ ክርስቲያኖች ልጠይቃችሁ፤ ሦስት ቀን የቆየ አስክሬን ታሻላችሁን? እንደርሱ ታደርጋላችሁን? መልሱ አሉታዊ ነው፡፡ በሥርዓት አጠባበቅ እኛ ሙስሊሞች ለአይሁድ እንቀርባለን፡፡ ሙስሊሞች የሞተን አካል አሦስት ቀን በኋላ ያሻሉን? አሁንም መልሱ አሉታዊ ነው፡፡ ስለዚህ የሞተና የበሰበሰውን አካል ከሦስት ቀን በኋላ ለምን ሄደው ሊያሹት ፈለጉ? እንደምታውቁት ሴሎች ይጠነክራሉ፣ የመነፍረቅ ሁኔታ ስለሚኖር አስክሬኑ መበስበስ ይጀምራል፡፡ በሦስት ቀናት ጊዜ ውስጥ አስክሬን ከውስጥ ይበሰብሳል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን የበሰበሰ አካል ካሻችሁት ይፈራርሳል፡፡

በሕይወት ያለውን ሰው የምትፈልግ ባትሆን ኖሮ እንዴት ብላ የሞተን አካል ለማሸት ትሄዳለች? አያችሁ? የተዝለፈለፈው አካል ከመስቀል በሚወርድበት ሰዓት የሕይወት ምልክት በውስጡ የግድ አይታ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ምስክሮቻችሁ የዘገቡትን በማንበብ ብቻ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ከአርማቲያሱ ዮሴፍና ከኒቆዲሞስ ጋር በመሆን ለኢየሱስ አስክሬን የመጨረሻውን ሽኝት ያደረገች ብቸኛዋ ሴት ብትኖር እርሷ ነበረች፡፡ የተቀሩት ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ከድተውት ሸሽተዋል፡፡ እዚያ አልነበሩም፡፡ ስለዚህ ይህቺ ሴት የሕይወት ምልክት ብታይ “እዩት በሕይወት አለ! በሕይወት አለ!” ብላ በመጮህ እርግጠኛ ሞት አትጋብዝም፡፡

ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ውስጥ በመግባት ልትቀባው ፈለገች፡፡ እናም ወደ ውቅር መቃብሩ በደረሰች ጊዜ ዲንጋዩ ተንከባልሎ አገኘችው፡፡ የመገነዣ ጨርቆቹ ከውስጥ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ማልቀስ ጀመረች፡፡ ዲንጋዩ ለምን ከቦታው ተነስቶ የመገነዣ ጨርቆቹ ተፈቱ? የሚል ጥያቄ አቀርባለሁ፡፡ ከሙታን ለተነሳ አካል ከመቃብር እንዲወጣ ዲንጋይ ማንከባለል አይጠበቅባችሁም፡፡ ከሙታን ለተነሳ አካል መራመድ እንዲችል የመገነዣውን ጨርቅ መፍታት አይጠበቅባችሁም፡፡ ይህ የቁሳዊው አካል – የዚህ ሟች አካል ባሕርይ ነው፡፡ አንድ ገጣሚ “የዓለት ጊድጊዳም፣ እስር ቤትም፣ የብረት አጥሮችም ማጎርያ አይሆኑም” ብሏል፡፡ ለነፍስ፣ ለመንፈስ እነዚህ ነገሮች ጋሬጣ አይሆኑም፡፡ የብረት አጥሮችም ሆኑ ጊድጊዳዎች አይበግሩትም፡፡ ይህ የቁሳዊ አካሉ ፍላጎት ነው፡፡ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ከሆነ ኢየሱስ ካለበት ቦታ ሆኖ ይመለከታት ነበር፡፡ ከሰማይ ሳይሆን እዚሁ ምድር ላይ ሆኖ [ይመለከታት ነበር]፡፡

ምክንያቱም ታስታውሱ እንደሆን ይህ መቃብር የአርማቲያሱ ዮሴፍ የግል ንብረት ነበር፡፡ ይህ ከበርቴ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሰፊ ክፍል ያለው አዳራሽ ለራሱ አስፈልፍሎ ነበር፡፡ በዚያ አዳራሽ ዙርያ የአትክልት ጓሮ ነበረው፡፡ እንግዲህ ይህ አይሁዳዊ የማንም በጎችና ፊየሎች እንዲግጡት ከከተማ አምስት ማይል ርቀት ላይ አትክልት የሚተክል ደግ ሰው ነበር እንዳትሉኝ፡፡

በእርግጠኝነት ለሰራተኞቹ እንዲሆን ቦታውን ገዝቶት ይሆናል፡፡ የአትክልት ቦታውን የሚጠብቁለት ሠራተኞች እዚያ ይኖሩ ይሆናል፡፡  ምናልባትም በዓላትን ወይንም ደግሞ የሳምንቱን የመጨረሻ ቀናት ለማሳለፍ ከቤተ ሰቡ ጋር የሚሄድበት የገጠር ቤቱ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ኢየሱስ በዚያ ሆኖ ያችን ሴት ይመለከታት ነበር፡፡ ማንነቷንና ወደዚያ ቦታ የመጣችበትን ምክንያት የውቃል፡፡ እርሷ ወደነበረችበት ቦታ ተጠጋ፡፡ ስታለቅስም አገኛት፡፡ “አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሺያለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?” አላት፡፡ አያውቅም ነበርን? አያውቅም ነበርን?  የሚል ጥያቄ አቀርባለሁ፡፡ እንደዚህ ዓይነት የማይረባ ጥያቄ ስለምን ይጠይቃል? ይህ የማይረባ ጥያቄ አለመሆኑን አረጋግጥላችኋለሁ፡፡ በዘይቤኛ ስንናገር እግሯን በቀስታ እየሳበ ነው [ማንነቱን በዘዴ እያሳወቃት ነው፡፡] አትክልተኛ መስሏታል –አትክልተኛ እንደሆነ ለምን አሰበች? ብዬ እጠይቃለሁ – ማስረጃውን ሳልጨምር ሳልቀንስ ልክ ባለበት ሁኔ እያነበብኩላችሁ ነው፡፡  አትክልተኛ አድርጋ ቆጠረችው – ለምን አትክልተኛ አድርጋ ቆጠረችው? ከሞት የተነሱ አካላት አትክልተኛ ይመስላሉን? ይመስላሉ ወይ? ለምን አትክልተኛ መሰላት? ራሱን አትክልተኛ ስላስመሰለ እንደሆነ እነግራችኋለሁ፡፡ ለምንድነው ራሱን አትክልተኛ ያስመሰለው? አይሁድን ስለፈራ ነው እላችኋለሁ፡፡ ለምንድነው አይሁድን የፈራው? ምክንያቱም ስላልሞተ ነዋ! ሞትን አላሸነፈም፡፡ ሞቶ ሞትን ካሸነፈ ከንግዲህ ወዲያ መፍራት አያስፈልገውም ነበር፡፡ ለምን? ምክንያቱም ከሞት የተነሳ አካል ዳግመኛ አይሞትምና፡፡ ማነው ይህንን ያለው? መጽሐፍ ቅዱስ ነው ብዬ እመልሳለሁ፡፡ ምን አለ? “ለሰዎች ሁሉ አንድ ጊዜ ሞት ከዚያም ፍርድ ተወስኗል” ይላል፡፡ ሁለቴ አትሞቱም፡፡

ስለዚህ ሞትን ቢያሸንፍ ኖሮ መፍራት አያስፈልገውም ነበር፡፡ ስላልሞተ ነው የፈራው፡፡ እናም አትክልተኛ ስለመሰላት “ጌዬ አንተ ወስደኸው ከሆነ የት እንዳኖርከው ንገረኝ” አለችው፡፡ ለማረፍ፣ ለማገገም እንጂ የት እንደቀበርከው ለማለት አይደለም፡፡ “እኔ እንድወስደው [የት እንዳኖርከው ንገረኝ]” አለችው፡፡ “እኔ ብቻዬን” – ደካማዋ አይሁዳዊት ሴት [ብቻዋን ልትወስደው ማለት ነው]፡፡ እንደኔ 200 የሆነውን ሳይሆን 160 ፓውንድ የሚመዝን አስክሬን ብቻዋን ተሸክማ ስትወስድ አስቡት፡፡ ገና ወጣት እንደሆነ የሚታሰበውን የፈረጠመ ጡንቻ ያለውን አናፂ፤ ቢያንስ 160 ፓውንድ የሚመዝነውን? ሌላ 100 ፓውንድ የሚመዝን መድኃኒት የተደረገለትን ያንን ሰው (ዮሐንስ 19፡9)፡፡ ከመድኃኒቱ ጋር 260 ፓውንድ ይመዝናል፡፡

በአሜሪካ ፊልሞች ውስጥ እንደምትታየው ልዕለ ተፈጥሯዊ ኃይል እንዳላት ሴት ይህች ደካማ አይሁዳዊት 260 ፓውንድ የሚመዝነውን የተጠቀለለ አስክሬን ልክ እንደ ገለባ ተሸክማ ስትሄድ እስኪ አስቡት፡፡ ወዴት ልትወስደው? እየበሰበሰ የነበረውን አስክሬን ምን ልታደርገው አስባ ነው? እጠይቃችኋለሁ፡፡

ስለዚህ ቀልዱ በጣም ስለበዛ ኢየሱስ – “ማርያም…” አላት፡፡ “ማርም” ካለበት አነጋገር በመነሳት ኢየሱስ መሆኑን አወቀች፡፡ ስለዚህ ልትጠመጠምበት ፈለገች፡፡ ለምን? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ልትነክሰው ይሆን? በፍፁም! አክብሮት ልታሳየው ፈልጋ ነው፡፡ እኛ የምስራቅ ሰዎች እንደርሱ እናደርጋለን፡፡ ልታቅፈው ፈለገች፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ “አትንኪኝ!” አላት፡፡ ለምንድነው እንድታቅፈው ያልፈለገው? ብትነካው ሊነዝራት የሚችል የኤሌክትሪክ ጥቅል፣ ዲናሞ ነውን?  እስኪ ንገሩኝ፡፡ ለምን? ብትነካው ስለሚያመው እንደሆነ እነግራችኋለሁ፡፡ ለምን እንደሆነ ሌላ የምትሰጡኝ ምክንያት ሊኖራችሁ ይችላል፡፡ “ወደ አባቴ ገና ስላላረግሁ አትንኪኝ” አላት፡፡ ዓይነ ስውር ናትን? ሰውዬው አጠገቧ ቆሞ እያየችው? እዚሁ እያለ “ወደ ላይ አልሄድኩም” ሲል ምን ማለቱ ነው? “ወደ አባቴ ገና አላረኩም” አለ፡፡ በአይሁድ ቋንቋ፣ በአይሁድ ዘይቤያዊ አነጋገር እየተናገራት ነው፡፡ “ገና አልሞትኩም” ነው እያለ ያለው፡፡

ዲንጋዩን ያንከባለለው ማነው? የሚል ጥያቄ እንደ ችግር ይነሳል፡፡ እንዴት እርሱ ወዳለበት ልትገባ ትችላለች? ዲንጋዩን ያንከባለለው ማነው? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ክርስቲያኖች በመጻሕፍት ላይ መጻሕፍትን እየጻፉ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱ  የሕግ አዋቂው ፍራንክ ሞሪሰን ነው፡፡ 192 ገፅ ያለው መጽሐፍ ጽፎ 6 መላ ምቶችን አቅርቧል፡፡ ንባባችሁን ከጨረሳችሁ በኋላ በ192ው ገፅ መጨረሻ ላይ አሁንም መልስ አታገኙም፡፡ ዲንጋዩን ያነሳው ማነው? [ክርስቲያኖች] በመጻሕፍት ላይ መጻሕፍትን እየጻፉ ይገኛሉ፡፡ ዲንጋዩን ማን አነሳው? በጣም ግልጽ ሆኖ የተቀመጠውን ለምን ማየት እንዳልቻላችሁ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ መጽሐፋችሁን ለምን አታነቡም? ወንጌላትን [ለምን አታነቡም?] በአፍ መፍቻ ቋንቋችሁ በግልጽ ተጽፎ ተቀምጦላችኋል እኮ፡፡ ይህንን መጽሐፍ በአፍ መፍቻ ቋንቋችሁ እንደማንበባችሁ መጠን ይህንን ማየት አለመቻላችሁ የሚደንቅ ነው፡፡

እንግሊዛዊው በእንግሊዘኛ፣ አፍሪካን ተናጋሪው በአፍሪካንኛ፣ የዙሉው በዙሉ፡፡ እያንዳንዱ የቋንቋ መደብ መጽሐፉን በገዛ ቋንቋው ያነበዋል፡፡ እያንዳንዱ ደግሞ ከሚያነበው በተቃራኒ እንዲረዳ ተረደርጓል፡፡ የተሳሳተ መረዳት ሳይሆን ፍፁም ተቃራኒውን [እንዲረዳ ተደርጓል]፡፡

ተሳስተሃል የምትሉኝ ከሆነ መሳሳቴን በማስረጃ እንድታረጋግጡልኝ እፈልጋለሁ፡፡ እየነገርኳችሁ ያለሁት ነገር… የናንተ ምስክሮች ልክ እንደተናገሩት እንደዚያው ቃል በቃል እየጠቀስኩላችሁ ነው፡፡ በግልጽ ያስቀመጡልንን [እየጠቀስኩላችሁ ነው]፡፡ የሆነ ህቡዕ ፍላጎት እንዳላቸው እየተናገርኩ አይደለም፡፡ ታማኝ ያልሆኑ ምስክሮች ናቸው እያልኩም አይደለም፡፡ እየነገርኳችሁ ነው፡፡ እባካችሁን ይህንን መጽሐፋችሁን ደግማችሁ አንብቡት፡፡ የዓይን ግርዶሾቹን አስወግዳችሁ ደግማችሁ አንብቡት፡፡ ቋንቋችሁን ያልተረዳሁት የቱ ጋር እንደሆነ ንገሩኝ፡፡ እናንተ የእንግሊዘኛ፣ የአፍሪካን፣ የዙሉ ተናጋሪዎች፤ ልታናግሩኝ ከፈለጋችሁ በውይይቱ መጨረሻ ኑና አናግሩኝ፡፡ የተከበረው እንግዳችን ጉዳዩን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ አላቀረበም የምትሉ ከሆነ – ወደ መንግሥት አዳራሻችሁ ወይንም ወደ ትምህርት ቤት አዳራሻችሁ፤ ብቻ የፈለጋችሁበት ቦታ ጋብዙኝ፡፡ ለመምጣት ዝግጁ ነኝ፡፡

ዲንጋዩን ያንከባለለው ማነው? እየጠየኩ ነው፡፡ መልሱ በጣም ቀላል ነው፡፡ 20 ሰዎች ያስፈልጋሉ ይላሉ፡፡ በጣም ግዙፍ ነው፤ እርሱን ለማንቀሳቀስ ልዕለ ተፈጥሯዊ ኃይል ያለው ሰው ከአሜሪካ እንዲመጣ ያስፈልጋል፡፡ ከአንድ ተኩል እስከ ሁለት ቶን ይመዝናል፡፡ እኔ ልንገራችሁ፤ እባካችሁን ማቴዎስንና ማርቆስን አንብቡ፡፡ የአርማቲያሱ ዮሴፍ ዲንጋዩን ብቻውን በቦታው ላይ እንዳስቀመጠ ይነግሯችኋል፡፡ አንድ ሰው – ብቻውን አስቀመጠ፡፡ አንድ ሰው! አንድ ሰው ብቻውን በቦታው ላይ ማስቀመጥ ከቻለ ሁለት ሰዎች መልሰው ማንሳት የማይችሉበት ምክንያት ምንድነው? ብዬ እጠይቃችኋለሁ፡፡

እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ክስተቶች – እንደምታውቁት አስቀድመው የተተነበዩ ናቸው፡፡ አስቀድሞ ተወስኗል፡፡ ከዚያ በኋላ ስለ ተከሰቱት ታሪኮች ሁሉ – ኢየሱስ ክርስቶስ ግልጽ የሆነ ምሳሌ እንደሰጠ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ያም ሌላው ምስክራችሁ በጻፈው የማቴዎስ ወንጌል 12፡38፣ 39፣ 40 ላይ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ተቀምጦላችኋል፡፡

አይሁድ ሌላ ጥያቄ ይዘው ወደ ኢየሱስ ዳግመኛ ተመለሱ፡፡ “ምልክት እንድትሰጠን እንፈልጋለን” አሉት፡፡ “የምንጠብቀው መሲህ መሆንህን ምልክት በማሳየት እንድታሳምነን እንፈልጋለን፡፡” ታውቃላችሁ? በውኀ ላይ መራመድን ወይንም ደግሞ እንደ ወፍ በአየር ላይ መብረርን የመሰለ ልዕለ ተፈጥሯዊ የሆነ ነገር እንዲያሳያቸው ነው የፈለጉት፡፡ “ሰውየው! እስኪ የሆነ ነገር አድርግና አሳየን፤ ያኔ አንተ የእግዚአብሔር ሰው፣ የምንጠብቀው መሲህ መሆንህን ማመን እንችላለን፡፡”

ስለዚህ ኢየሱስ መለሰላቸው፤ እንዲህም አላቸው “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በስተቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡” ለመስጠት የተዘጋጀው ብቸኛ ምልክት የዮናስ ምልክት ነበር፡፡ ሁሉንም እንቁላሎቹን በአንድ ቅርጫት ውስጥ አስቀመጣቸው፡፡ “እውሩን በርጠሜዎስን ታውቃላችሁ አይደል? ፈውሼዋለሁ፡፡ ለዓመታት ደም ሲፈሳት የነበረችዋን ያቺን ሴት ታውቋት የል? ነክታኝ ተፈወሰች፡፡ ታውቃላችሁ? አምስት ሺህ ሰው በጥቂት ዓሣና በጥቂት የዳቦ ቁራሽ መመገብ ችያለሁ፡፡ ያቺን የበለስ ዛፍ ታያላችሁ? ከስሯ ያደረቅኋት እኔ ነኝ” አላለም፡፡ እንዲህ  ዓይነት ነገር በፍፁም አልተናገረም፡፡ “የምሰጣችሁ ብቸኛ ምልክት ይህ ነው፤ የዮናስ ምልክት፡፡” የዮናስ ምልክት ምንድነው?  የሚል ጥያቄ አቀርባለሁ፡፡

መልካም፤ ወደ ዮናስ መጽሐፍ ሂዱ፡፡ [ሚስተር ዲዳት አንድ ወረቀት ለሕዝቡ እያሳዩ] የዮናስን መጽሐፍ አምጥቼላችኋለሁ – ከእግዚአብሔር የሆነ አንድ ገፅ ጽሑፍ – በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰጠው ቦታ አንድ ገፅ ብቻ ነው፡፡ ይህ የዮናስ መጽሐፍ ነው፡፡ አራት አጫጭር ምዕራፎች አሉት፡፡ ለማንበብ ሁለት ደቂቃ አይፈጅባችሁም፡፡ መጽፉን ለማግኘት ከባድ ነው ምክንያቱም በሺዎች በሚቆጠሩ ገፆች ውስጥ አንድ ገፅ ማግኘት በጣም ከባድ ነውና፡፡ ነገር ግን እርሱን ፍለጋ መሄድ አያሻችሁም፡፡ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት ብትሄዱ እኔ እየነገርኳችሁ ያለሁትን ነገር ታስታውሳላችሁ፡፡ ዮናስ ወደ ነነዌ እንደተላከ የሚያወሳውን ታሪክ እየነገርኳችሁ ነው፡፡ ታውቃላችሁ? ሁሉን ቻዩ አምላካ 100,000 ሕዝብ ወዳለባት “ወደ ነነዌ ሂድ” አለው፡፡ ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው ንስሐ እንዲገቡ ለእነርሱ መንገር ነበረበት፤ በጌታ ፊት ራሳቸውን ማዋረድ ይገባቸው ነበር፡፡ ዮናስ ፈቃደኛ አልነበረም ምክንያቱም እነዚህ ቁሳውያን ሰዎች – ዓለማውያን ሰዎች – “አይሰሙኝም፡፡ እኔ የምነግራቸውን ነገሮች መሳለቂያ ያደርጋሉ” የሚል ስጋት ነበረበት፡፡ ስለዚህ ወደ ነነዌ በመሄድ ፋንታ፣ ወደ ኢዮጴ ሄደ፡፡ ይህ ባለ አንድ ገፅ መጽሐፍ የሚነግራችሁ ይንን ነው፡፡ ወደ ኢዮጴ በመሄድ መርከብ ያዘ – የጉዞ አቅጣጫው ወደ ታርሴስ ነበር፡፡ እነዚህን ስሞች የግድ ማስታወስ አያስፈልጋችሁም፡፡

ወደዚያ ሲሄድ ሳለ ማዕበል ተነሳ፡፡ በነዚህ ሰዎች የዘልማድ አስተሳሰብ መሠረት ከጌታው ትዕዛዝ የሚኮበልል ወይም ግዴታውን የማይወጣ አገልጋይ የባሕር ማዕበል እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡ የፈጣሪ ነቢይ እንደመሆኑ መጠን ዮናስ ይህንን አውቋል፡፡ የፈጣሪ ወታደር ስለመሆኑ ግንዛቤ ነበረው፡፡ የፈጣሪ ወታደር እንደመሆኑ መጠን ደግሞ ነገሮችን በዘፈቀደ የማድረግ መብት የለውም፡፡ ስለዚህ “ይኸውላችሁ ጥፋተኛው ሰው እኔ ነኝ፡፡ ሁሉን ቻዩ አምላክ ደሜን ይሻል፡፡ ሊገለኝ ስለፈለገ ጀልባውን ሊያሰምጠው ነው፤ ስለዚህ በዚህ ሂደት እናንተ ንጹሓን ሰዎች ትሞታላችሁ፡፡ ያለጥርጥር አምላክ ደሜን እየፈለገ ስለሆነ ወስዳችሁ ወደ ውጪ ብትጥሉኝ ለናንተ የተሻለ ይሆናል” አላቸው፡፡

“አይሆንም ሰውየው፤ ታውቃለህ? አንተ በጣም ጥሩ ሰው ነህ ነገር ግን ራስህን ለማጥፋት ፈልገሃል፡፡ ያንን እንድታደርግ ልንረዳህ አንችልም፡፡ ትክክለኛውን ትክክል ካልሆነው የምንለይበት የራሳችን የሆነ ዘዴ አለን፡፡” ያንን ዘዴ እጣ መጣል በማለት ይጠሩታል፡፡ ዘውድ ወይም አንበሳ እንደሚባለው ዓይነት ማለት ነው፡፡ እናም እጣ በመጣል ዘዴ ዮናስ ጥፋተኛ ሰው ሆኖ ተገኘ፡፡ ስለዚህ ወስደውት ወደ ባሕሩ ወረወሩት፡፡

አሁን ጥያቄ ልጠይቅ ነው፡፡ ወደ ውጪ በጣሉት ጊዜ ሞቶ ነበር ወይንስ በሕይወት ነበር? መልስ ከመስጠታችሁ በፊት ዮናስ ፍቃደኛ እንደነበር ልብ እንድትሉ እፈልጋለሁ፡፡ “ወርውሩኝ” ብሏል፡፡ ሰውየው ፍቃደኛ ከሆነ ከመወርወራችሁ በፊት ልታንቁት አይገባም፤ ከመወርወራችሁ በፊት በጦር ልትወጉት አይገባም፤ ከመወርወራችሁ በፊት እጆቹንና ጭኖቹን መስበር አያስፈልጋችሁም፡፡ ከኔ ጋር ትስማማላችሁ?

ሰውየው ፍቃደኛ ሆኗል፡፡ ወደ ውጪ በወረወሩት ጊዜ ሞቶ ነበር ወይንስ በሕይወት ነበር? እባካችሁን እገዛችሁን እፈልጋለሁ፡፡ ሞቶ ነበር ወይንስ በሕይወት ነበር? [ሕዝቡ “በሕይወት ነበር” ብሎ መለሰ፡፡] አዎ በሕይወት ነበር፡፡ በጣም ቀላል ጥያቄ ስለሆነ ምንም ሽልማት አታገኙም፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታ አይሁድ በሕይወት መኖሩን ይናገራሉ፤ ክርስቲያኖችም በሕይወት ነበረ ይላሉ፤ ሙስሊሞችም በሕይወት ነበረ ይላሉ፡፡ በሌሎች ነገሮች ሁሉ ላይ ልክ እንደዚሁ ብንስማማ ምንኛ መልካም ነበር፡፡

ወደሚናወጠው ባሕር በተወረወረ ጊዜ ሕያው መሆኑን ሁላችንም እንስማማለን፡፡ ማዕበሉም ተረጋጋ፡፡ ምናልባት አጋጣሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ዓሣ ነባሪ በመምጣት ተስገብግቦ  ዋጠው፡፡ ሙት ወይንስ ሕያው? ሙት ነበር ወይንስ ሕያው ነበር? [ሕዝቡ “ሕያው ነበር” ብሎ መለሰ፡፡] ሕያው ነበር፡፡ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ለእርዳታ ወደ ፈጣሪ እንደ ጮኸ የዮናስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ ሙታን ይጸልያሉን? ይጸልያሉን? ሙታን ይጸልያሉን? አይጸልዩም! ስለዚህ ሕያው ነበር፡፡ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ዓሣው በሆዱ ተሸክሞት በባሕር ውስጥ ወዲያና ወዲህ ይሄድ ነበር፡፡ ሙት ነበር ወይንስ ሕያው? ሕያው ነበር፡፡ በሦስተኛው ቀን በባሕሩ ዳርቻ ሲራመድ ሕያው ወይንስ ሙት? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ሕያው፡፡ ኢየሱስ ምን አለ? “ዮናስ.. እንደነበረ” ነው ያለው፡፡ ልክ እንደ ዮናስ ማለት ነው፡፡ ወደ ራሱ ሲያመለክት “ዮናስ… እንደነበረው እንዲሁ የሰው ልጅ… ይሆናል” አለ፡፡ ዮናስ እንዴት ነበር? – ሙት ወይንስ ሕያው? ሙት ወይንስ ሕያው? ሕያው፡፡ እንደ ክርስቲያኖች እምነት ኢየሱስ በመቃብሩ ውስጥ በምን ዓይነት ሁኔታ ነበር? እንዴት ነበር? ሙት ወይንስ ሕያው? ሙት!

እንደኛ እምነት ሙት ነው፡፡ በሌላ አባባል እንደ ዮናስ አልነበረም ማለት ነው፡፡ አይታያችሁም? እርሱ እንደዮናስ እሆናለሁ ብሎ ተናገረ እናንተ ግን – ወደ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሚሊዮን የምትሆኑት የዓለም ክርስቲያኖች – እንደ ዮናስ አልነበረም ብላችሁ ትነግሩኛላችሁ፡፡ እርሱ እንደ ዮናስ እሆናለሁ ብሎ ተናገረ እናንተ ግን እንደ ዮናስ አልነበረም ትላላችሁ፡፡ እኔ አይሁዳዊ ብሆን ኖሮ የኔ መሲህ አድርጌ አልቀበለውም ነበር፡፡ በቁርኣን ውስጥ ኢየሱስ መሲህ መሆኑ ተነግሮኛል፡፡ ስለዚህ እቀበላለሁ፡፡ እርሱ ከታላላቅ የፈጣሪ መልዕክተኞች መካከል አንዱ ነው – እቀበላለሁ፡፡ በተዓምራዊ ልደቱ አምናለሁ፡፡ በፈጣሪ ፈቃድ ለሙታን ሕይወት መስጠቱን አምናለሁ፡፡ በፈጣሪ ፈቃድ እውራን ሆነው የተወለዱትንና ለምጻሞችን መፈወሱን አምናለሁ፡፡ አይሁዳዊ ብሆን ኖሮ ራሱ በሰጠው ምልክት መሠረት ውድቅ ሆኗል፡፡ ዮናስ ሕያው ነበር – ኢየሱስ ግን ሙት፡፡ አይመሳሰሉም፡፡ በምን ቋንቋ እንደምታመሳስሏቸው አይገባኝም፡፡ አንድ አስተዋይ ሰው፤ ታውቃላችሁ? የሥነ መለኮት ዶክተር፤ የሃይማኖት ፕሮፌሰር፤ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንዳልቻልኩ ነገረኝ፡፡

መጽሐፍ ቅዱሳችሁን እኔ አልረዳም፡፡ ለምንድነው መጽሐፍ ቅዱስን የማልረዳው? [ብዬ ጠየቅሁት፡፡] እርሱም እንዲህ ሲል መለሰልኝ፡- “አየህ ሚስተር ዲዳት ኢየሱስ አጽንዖት እየሰጠ ያለው ለጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ልብ በል ‹ሦስት› የሚለውን ቃል አራት ጊዜ ነው የተጠቀመው፡፡ ‹ዮናስ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደሆነው ሁሉ የሰው ልጅም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት…› ሦስት የሚለውን ቃል አራት ጊዜ ነው የጠቀሰው፡፡”

በሌላ አባባል አፅንዖት የሰጠው ለጊዜ ጉዳይ ነው – ሕያው ስለመሆን አለመሆኑ አይደለም፡፡ ነገር ግን በጊዜ ጉዳይ ውስጥ ተዓምራዊ የሆነ ምንም ነገር እንደሌለ እነግራችኋለሁ፤ ሰውየው ለሦስት ደቂቃዎች፣ ለሦስት ሰዓታት ወይንም ደግሞ ለሦስት ሳምንታት ቢሞት ያ ተዓምር ሊሆን አይችልም፡፡

ሰውየው እንዲሞት ስትጠብቁት የማይሞት ከሆነ ተዓምር ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ዮናስ ወደ ባሕር በተወረወረ ጊዜ እንደሚሞት ነው የምንጠብቀው፡፡ ነገር ግን አልሞተም፤ ስለዚህ ተዓምር ነው፡፡ እንዲሞት ዓሣ ውጦታል፡፡ ነገር ግን አልሞተም፤ ስለዚህ ተዓምር ነው፡፡ ለሦስት ቀንና ለሦስት ሌሊት በዓሣ ሆድ ውስጥ በአየር እጥረትና በወበቅ እንዲሞት ይጠበቅ ነበር፤ አልሞተም፡፡ ተዓምር ነው፡፡ ሰየው እንዲሞት ትጠብቃላችሁ ነገር ግን አልሞተም፤ ስለዚህ ተዓምር ነው፡፡

ሰውየው እንዲሞት ጠብቃችሁት ከሞተ ምኑ ላይ ነው ተዓምርነቱ? እየጠየኳችሁ ነው፤ ምኑ ላይ ነው ተዓምርነቱ? የሆነ ሰው በአንድ ሰው ልብ ላይ ሽጉጥ ስድስት ጊዜ ቢተኩስበትና ሰውየው ቢሞት ያ ተዓምር ነውን? አይደለም፡፡ ነገር ግን ከት ብሎ ቢስቅ፣ አሁንም ድረስ ሕያው ሆኖ ከኛ ጋር መሄድ ቢችል፤ ልቡን ከበታተነው ስድስት ተኩስ በኋላ ኻ…ኻ…ኻ.. ብሎ ቢስቅ — ሕያው ነው፡፡ ስለዚህ ተዓምር ነው እንላለን፡፡ አያችሁ? ተዓምር የሚሆነው ሰውየው እንዲሞት ስንጠብቀው ሳይሞት ሲቀር ነው፡፡ እንዲሞት የሚጠበቅ ሰው ቢሞት ተዓምር አይደለም፡፡

ኢየሱስንም እንዲሞት እንጠብቀው ነበር፡፡ ከደረሰበት ነገር የተነሳ ቢሞት ተዓምር አይሆንም፡፡ ምልክት የለም፡፡ ካልሞተ ተዓምር ነው – እንዴት ነው የማይታያችሁ? ነገር ግን ያ ሰው “አይደለም አይደለም የጊዜ ጉዳይ ነው” አለኝ፡፡ እየሰጠሙ ያሉ ሴቶች ሳር ይዘው ነፍሳቸውን ለማትረፍ ይፍጨረጨራሉ፡፡ እየሰጠሙ ያሉ ወንዶችም እንደዚያው ናቸው፡፡ ያንን ፈፅሞታልን? ብዬ ጠየኩት፡፡ “ያለጥርጥር ፈፅሞታል” አለኝ፡፡ እንዴት ነው የፈጸመው? አልኩት፡፡ ተመልከት አንድ ነገር መናገር በጣም ቀላል ነው፡፡ እንዴት ነው የፈጸመው? እዩ እንግዲህ፡፡ መች ነው የተሰቀለው? እናንተኑ ልጠይቅ፡፡ ሁሉም ክርስቲያኖች በመልካሚቱ አርብ (Good Friday) ነው ይላሉ፡፡ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ሌሶዞ፣ ዛምብያ – በደቡብ አፍሪካ ሕዝባዊ በኣል እናከብራለን – ሁሉም ክርስቲያን አገር መልካሚቱን አርብ አስቧት ይውላል፡፡ መልካሚቱን አርብ መልካም ያደረጋት ምንድነው? የሚል ጥያቄ አቀርባለሁ፡፡

ክርስቲያኖች “ክርስቶስ ስለ ኃጢኣታችን ስለሞተ ነው መልካም የሆነው” ይላሉ፡፡ ስለዚህ በመልካሚቱ አርብ ነው የተሰቀለው፡፡ እርሱም በአዎንታ መለሰልኝ፡፡ ልክ ነው፡፡ መች ነው የተሰቀለው? ጠዋት ወይንስ ከሰዓት? አልኩት፡፡ ክርቲያኖች ከሰዓት በኋላ ነው ይላሉ፡፡ በመስቀል ላይ ለምን ያህል ጊዜ ነው የቆየው? አንዳንዶች ለሦስት ሰዓታት ነው ይላሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ለስድስት ሰዓታት ነው ይላሉ፡፡ እኔም በዚህ ጉዳይ ላይ እናንተን መሞገት አልፈልግም፡፡ ምንም ብትሉ እቀበላለሁ፡፡ ታውቃላችሁ? ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነበብን እንደሆን ሊሰቅሉት በፈለጉ ጊዜ በጣም ይጣደፉ እንደነበር ይነግሩናል፡፡ በዚህ ችኮላ ውስጥ ሳሉ በአሥራ ሁለት ሰዓታት ውስጥ ስድስት የተለያዩ የፍርድ ሂደቶች እንደነበሩ ጆሽ “የትንሣኤው ጉዳይ” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ይነግሩናል፡፡ ስድስት የፍርድ ሂደቶች ነበሩ፡፡

እንደዚህ ዓይነት ነገሮች በፊልም ውስጥ ብቻ ነው ሊሆኑ የሚችሉት፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች – በአሥራ ሁለት ሰዓታት ውስጥ፤ ማለትም ከእኩለ ሌሊት እስከ ቀጣዩ ቀን ጠዋት ድረስ ስድስት የፍርድ ሂደቶች ሊደረጉ የሚችሉት በፊልም ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የምትነግሩኝን ሁሉ አምናለሁ፡፡ የምትሉኝን ሁሉ እቀበላለሁ፤ ስለዚህ አይሁድ ሊሰቅሉት በጥድፊ ላይ ነበሩ፡፡ ለምን እንደ ሆነ ታውቃላችሁ? በሰፊው ሕዝብ ምክንያት ነው፡፡ ኢየሱስ አይሁዳዊ ነበር፡፡ ሰፊው ሕዝብ ይወደው ነበር፡፡ ሰውየው ዕውራንን፣ ለምጻሞችንና ሕሙማንን ፈውሷል፤ እንዲሁም ሙታንን አስነስቷል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩትን ሰዎች ዳቦና ዓሣ መግቧል፡፡ ጀግና ነበረ፤ እናም ሕዝቡ የጀግናቸው ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን ቢያውቁ አመፅ ይነሣ ነበር፡፡

ስለዚህ የሌሊት ችሎት አደረጉ፡፡ ጠዋት በማለዳ ወደ ጲላጦስ ወሰዱት፡፡ ጲላጦስም “እርሱ በኔ ማሰሮ ውስጥ ያለ ዓሣ አይደለም – ወደ ሄሮድስ ውሰዱት” አለ፡፡ ሄሮድስም “እኔ ፍላጎት የለኝም – ወደ ጲላጦስ መልሳችሁ ውሰዱት፡፡ ፍጠኑ፣ ፍጠኑ፣ ፍጠኑ!” በ12 ሰዓታት ውስጥ ስድስት የፍርድ ሂደቶች ነበሯቸው፡፡ ምንም ሌላ ሥራ የሌላቸው ይመስል፡፡ ነገር ግን የምትነግሩኝን ሁሉ አምናለሁ፡፡

እንደ ምስክሮቻችሁ ከሆነ ሰቅለውታል ስለዚህ ተሳክቶላቸዋል፤ እንደ ምስክሮቻችሁ፡፡ እርሱን እዚያ ላይ ለማድረግ እንደተጣደፉት ሁሉ ሲያወርዱትም በጥድፍያ ነበር፡፡ ለምን እንደ ሆነ ታውቃላችሁ? ምክንያቱም አርብ ልክ ፀሐይ ስትገባ፣ ማለትም አሥራ ሁለት ሰዓት ላይ ሰንበት ስለሚጀምር ነው፡፡ ታውቃላችሁ? አይሁድ ቀን የሚቆጥሩት ሌሊትና ቀን፣ ሌሊትና ቀን በማለት ነው፡፡ እኛ ሙስሊሞች ቀናችንን የምንቆጥረው ሌሊትና ቀን፣ ሌሊትና ቀን በማለት ነው፡፡ ቀንና ሌሊት በማለት አይደለም፡፡ ሌሊትና ቀን በማለት እንቆጥራለን፡፡ የኛ ቀን ምሽት አሥራ ሁለት ሰዓት ላይ ይጀምራል፡፡

ስለዚህ ፀሐይ ከመግባቷ በፊት አስክሬኑ መውረድ ይኖርበታል፤ ምክንያቱም በሰንበት ቀን ማንም በእንጨት ላይ ማደር እንደሌለበት በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ ተነግሯቸዋልና፡፡ “እግዚእብሔር አምላክህ ርስት አድርጎ የሰጠህ ምድር እንዳይረክስ” ይላል፡፡ ስለዚህ በጥድፊያ አስክሬኑን አውርደው የቀብር እጥበት በመፈፀም መቶ ፓውንድ የሚመዝን ቅመማ ቅመሞችን አደረጉበት፡፡ ከዚያም በዋሻው ውስጥ አኖሩት፡፡ መቃብር ሳይሆን – ዋሻ፡፡ ከመሬት በላይ ያለ ሰፊ አዳራሽ፡፡ ስለዚህ መሽቷል፡፡ ከሰዓት በኋላ ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ለምታደርጉት ለማንኛውም ነገር ዝርዝሩ በጆሽ መጽሐፍ ውስጥ ተሰጥቷል፡፡ የቀብር እጥበቶች ብዙ ጊዜ ከአንድ ሰዓት በላይ ይወስዳሉ፡፡ አይሁዳዊ የቀብር እጥበት ለሙት እንዴት እንደሚፈጽም ዝርዝሩን ማንበብ ትችላላችሁ፡፡ ያ በራሱ ከአንድ ሰዓት በላይ ይወስዳል፡፡ ነገር ግን እስኪ እነዚህን ሁሉ በጥድፊያ፣ ጥድፊያ ለመፈጸም ችለዋል እንበል፡፡ በችኮላ ውስጥ እንደነበሩ ታውቃላችሁ፡፡ ስድስት የፍርድ ሂደት በ12 ሰዓታት ውስጥ፡፡ አሁን ደግሞ በዋሻ ውስጥ አኑረውታል፡፡

እርሱን እዚያ ውስጥ ባደረጉበት ሰዓት መሽቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ተመልከቱ – ጣቶቼን ተመልከቱ፡፡ አርብ ሌሊት በመቃብር ውስጥ እንደነበር ይታሰባል፡፡ ጣቴን ተመልከቱ [ሚስተር ዲዳት ጣቶቻቸውን ለሕዝቡ ያሳያሉ]፡፡ ቅዳሜ አሁንም በመቃብር ውስጥ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ትክክል ነኝ ወይ? ቅዳሜ ሌሊት አሁንም ድረስ በመቃብር ውስጥ እንዳለ ይታሰባል፡፡ ነገር ግን እሑድ ጠዋት ማለትም ከሳምንቱ በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ በሄደች ጊዜ መቃብሩ ባዶ ነበር፡፡

ያ የናንተ ምስክሮች ያሉት ነገር ነው፡፡ ልጠይቃችሁ – ስንት ቀንና ስንት ሌሊት ነበር? እንደምታስታውሱት ይታሰባል፣ ይታሰባል፣ ይታሰባል ነበር ያልኩት… ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ መች እንደወጣ ስለማይናገር ነው፡፡ አርብ ምሽት ወጥቶ ሊሆን ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደወጣ አይናገርም፡፡ ስለዚህ አርብ ምሽት፣ ቅዳሜ ቀን፣ ቅዳሜ ምሽት፡፡ ስንት ቀንና ስንት ሌሊት እንደሆነ ልጠይቃችሁ፡፡ እባካችሁን የምታዩ ከሆነ፣ ዐይኖቻችሁ ችግር ከሌለባቸው ስንት እንደሆነ ንገሩኝ፡፡ ስንት ነው የምታዩት? [የተወሰኑ ሰዎች “ሁለት ሌሊትና አንድ ቀን” በማለት ሲመልሱ ይሰማል፡፡] ትክክል! ሁለት ሌሊትና አንድ ቀን ነው፡፡ ይህንን ተመልከቱ [ሚስተር ዲዳት ጣቶቻቸውን እያሳዩ] “ዮናስ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደሆነው እንዲሁ የሰው ልጅ ይሆናል” ብሎ ከተናገረው ጋር አንድ ነውን? ይህንን ተመልከቱ፤ [ሚስተር ዲዳት አሁንም ጣቶቻቸውን እያሳዩ] ሁለትና አንድ፡፡ እባካችሁን አሁን አንድ ዓይነት ነገር ነው ብላችሁ ንገሩኝ፡፡

እናንተ እያነበባችሁ ያላችሁት ምን እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ በገዛ መጽሐፋችሁ ውስጥ እያነበባችሁት ያላችሁት ምን እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ! መጪው ክስተት እንደ ዮናስ ዓይነት እንደሆነ ሰውየው እየነገራችሁ ነው፡፡ የዮናስ ምልክት ደግሞ ተዓምር ነው፡፡ ከዚህ ሰው ጋር ልታያይዙት የምትችሉት ብቸኛው ተዓምር ቢኖር እንደሚሞት ስንጠብቀው አለመሞቱ ነው፡፡ ኢየሱስ – እርሱም እንደሚሞት ስንጠብቅ ነበር፡፡ ከሞተ ምልክት አይደለም፡፡ ካልሞተ ግን ምልክት ነው፡፡

ክቡር ሰብሳቢ እንዲሁም የችሎቱ ክቡራትና ክቡራን፤ እንደምትመለከቱት ሰዎች የተወሰነ ነገር ብቻ እንዲያስቡ አስተሳሰባቸው ተቃኝቷል፡፡ ከልጅነታችን ጀምሮ ሁላችንም አስተሳሰባችን ተቃኝቷል፡፡ ወደ አሜሪካ ሄጄ ሳን ፍራንሲስኮ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ንግግር ሳደርግ እናንተ ሰዎች አዕምሯችሁ ታጥቧል አልኳቸው፡፡ “አዕምሯችሁ ታጥቧል” ብዬ ነገርኳቸው፡፡ በእርግጥ ለነርሱ ያሻኝን መናገር እችል ነበር – አሜሪካዊ ይቀበለዋል፡፡ እርሱ ሁሉን ቻይ ነው፡፡ አንድ ትልቅ ሰው ታውቃላችሁ ምንም ብትናገሩ ሊሰማችሁ ይችላል፡፡ ስለዚህ “እናንተ ሰዎች አዕምሯችሁ ታጥቧል” አልኳቸው፡፡ አንድ አሜሪካዊ ፕሮፌሰር ጣልቃ ገብቶ “አይ የአዕምሮ እጥበት ሳይሆን – አዕምሯችን በተወሰነ የአስተሳሰብ አቅጣጫ ተቃኝቷል” አለኝ፡፡ “አዕምሮው የተቃኘው ሰውዬ ይቅርታ እጠይቃለሁ” አልኩት [ሳቅ ይሰማል]፡፡ ስለዚህ ክቡር ሰብሳቢ፣ ክቡራትና ክቡራን፣ ይህ ስብሰባ ካለቀ በኋላ መጽሐፉን ከዚህ ቀደም እንደትረዱት በተቃኛችሁበት መንገድ ሳይሆን ባለበት ሁኔታ ማንበብ እንደምትጀምሩ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በጣም አመሰግናለሁ ክቡራትና ክቡራን፡፡

[ሕዝቡ አጨበጨበ፣ ሚስተር ዲዳት ወደ ቦታቸው ተመልሰው ተቀመጡ፡፡]


ክርስቶስ ተሰቅሏልን? ማውጫ