መክፈቻ በጆሽ ማክዱዌል
[ጆሽ ማክዱዌል በተለያዩ ቋንቋዎች ሰላምታ አቀረቡ፡፡ ሕዝቡም ታላቅ ጭብጨባ አሰማ]
ክቡራትና ክቡራን እንደምን ዋላችሁ፡፡ ሚስተር ዲዳትና የዚህች ከተማ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ ድንቅ ሕዝቦች፤ ስለ ስቅለትና ስለ ትንሣኤ በእስልምናና በክርስትና ውስጥ ስለሚገኙት አመለካከቶች የሚያወሳውን ሲምፖዝየም እንድታደም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
ዝግጅት ሳደርግ ሳለሁ ስቅለትን በተመለከተ በእስልምና ውስጥ እጅግ የበዙ የተለያዩ አመለካከቶች እንደሚያጋጥሙኝ አላውቅም ነበር፡፡ የደረስኩበት ቀዳሚው ነገር በመላው ዓለም የሚገኙ አብዛኞቹ ሙስሊሞች “የመተካካት መላ ምት” (Substitution Theory) የተሰኘውን መላ ምት እንደሚደግፉ ነው፡፡ በቁርኣን ውስጥ ሱራ 4 ላይ ሌላ ሰው በኢየሱስ ምትክ እንደተሰቀለና ኢየሱስ ደግሞ ወደ ሰማይ እንደተወሰደ ይናገራል፡፡ በሌላ አባባል [የተሰቀለው] ሌላ ሰው ነው፡፡ ከዚያም ብዙ የተለያዩ አመለካከቶችን በሙስሊሞች ዘንድ አገኘሁ፡፡ አንዳንድ ሙስሊም ጸሐፊያን በእርሱ ፋንታ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሌላ ጦበረኒ የተሰኘ ጸሐፊ ኢብን ኢስሐቅን ዋቢ በማድረግ እንደተናገረው በመስቀል ላይ የዋለው ሰርጉስ ወይንም ሰርጊዩስ የተባለ ሰው ነው፡፡ ባይዳዊ የተባለ ሌላ ሙስሊም የተናገረው ቲታኑስ የተባለ አይሁዳዊ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ ነው፡፡ ሌላ አት-ታላቢ በተባለ ሰው መሠረት የተሰቀለው ፈል ተያኑስ የተሰኘ አይሁዳዊ ነው፡፡ አሁንም ወሃብ ኢብን ሙነባህ የተባለ ሌላ ሙስሊም ጸሐፊ አሽዩ የተባለ የአይሁድ ረቢ መሰቀሉን ተናግሯል፡፡
ንጹሕ ሰው መሰቀሉ ትክክል እንዳልሆነ የተሰማቸው አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የተሰቀለው የአስቆሮቱ ይሁዳ መሆን እንዳለበት ተናሩ፡፡ እንግዲህ አሁን ሚስተር ዲዳት ሊያርሙኝ ይችላሉ፤ ይህንን የሚደግፍ ምንም ዓይነት ማስረጃ በቁርኣን ውስጥ እንዳለ አላምንም፡፡ ከእስልምና በሚቀድሙ አንዳንድ ቡድኖች ውስጥ ያንን የሚያመለክቱ አስተሳሰቦች ነበሩ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ለምን ሌላ መተካት እንዳስፈለገው ሁል ጊዜ ይገርመኛል፡፡ ለምን ዝም ብሎ ኢየሱስን አልወሰደውም ነበር?
ሌሎች ደግሞ እንዲህ ይላሉ – ይህ ግን አብዛኞቹ ሙስሊሞች የሚያምኑት አይደለም – ከስቅለቱና ተከሰተ ከተባለው ትንሣኤው የተወሰኑ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ተፈጥሯዊ ሞት ሞቷል፡፡ በሌላ አባባል “ሀዝራት ዒሳ”፣ ኢየሱስ ሞቷል! ይህ በእስልምና ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተከታዮችን እያፈራ የመጣ አስተሳሰብ ነው፡፡ እኔ ግን አዳዲስ የሚፈጠሩትን አመለካከቶች ሁሌም ቢሆን በጥርጣሬ ነው የማያቸው፡፡
የተጀመረው ቬንቹሪኒ በተሰኘ ሰው ሲሆን ይህ ሰው ኢየሱስ በትክክል በመስቀል ላይ እንዳልሞተ ነገር ግን እራሱን ከሳተ በኋላ ተቀብሮ እንደገና በማንሰራራት እንደተነሳ ተናግሮ ነበር፡፡ አሕመዲያ የተሰኘው አጥባቂ የእስልምና አንጃ ይህንን አመለካከት ያራምዳል፡፡ መሥራቻቸው በሆነው “ነቢይ” ብለው በሚጠሩት በሚርዛ ግሁላም አሕመድ ከተሰበኩ አበይት አስተምህሮዎቻቸው መካከል አንዱ ሲሆን የቃዲያኒዝም አስተምህሮ አካል ነው፡፡
አንዳንዶች መሰቀል ማለት መሞት ማለት ነው ይላሉ፡፡ እናም ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስላልሞተ አልተሰቀለም፡፡ ያንን ትርጓሜ ከየት እንዳመጡት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እኔ ማድረግ የሚገባኝ ይህንን ነው፡- ልክ በመጽሐፍቴ ውስጥ ባሰፈርኩት መልኩ እውነታዎቹን ለናንተ ማቅረብና ሚዛናዊ ህሊና እንዳላቸው አስተዋይ ሰዎች ትክክለኛ ውሳኔ ላይ መድረስ እንድትችሉ ፍርዱን ለናንተ መተው ነው፡፡ አሁን የማቀርባቸው ነጥቦች የተጠነሰሱት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እያለሁ ክርስትናን በመቃወም መጽሐፍ ለመጻፍ ሳስብ በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ምሑራዊ በሆነ መንገድ ውድቅ የማድረግ መሻት ነበረኝ፡፡ ክርስቲያን የመሆን ምንም ዓይነት ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን ብዙ ገንዘብና ጊዜ ከፈጀ የሁለት ዓመታት ጥናትና ምርምር በኋላ እውነታዎችን አገኘሁ – እግዚአብሔር ቃሉ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተናገራቸውን እውነታዎች ብቻ ሳይሆን በታሪክ ምንጮች ውስጥ የተመዘገቡትን እውነታዎች ጭምር አገኘሁ፡፡ ክቡራትና ክቡራን፤ በማስከተል ክርስትናን ውድቅ ለማድረግ ሞክሬ ሳይሳካልኝ ሲቀር ካገኘኋቸው እውነታዎች መካከል የተወሰኑትን አቀርብላችኋለሁ፡፡
የደረስኩበት የመጀመርያው እውነታ ኢየሱስ ለመሞት አለመፍራቱን ነው፡፡ በእርግጥ ስለ ራሱ ሞትና ትንሣኤ አስቀድሞ ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ “እነሆ ወደ ኢሩሳሌም እንሄዳለን፤ የሰው ልጅ ለሞት አልፎ ይሰጣል፡፡ ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው፡፡” [ከማቴዎስ 12:18-20 የተጠቀሰ]
በሌላ ቦታም እንዲሁ ብዙ ነገሮች እንደታዩት ያስተምራቸው ጀመር፡፡ በሽማግሌዎችና በካህናት አለቆች እንዲሁም በጻፎች እንደሚጣል፣ እንደሚገደልና በሦስተኛውም ቀን እንደሚነሳ ጨምሮ ነገራቸው (ማቴዎስ 20፡18-19)፡፡ በማቴዎስ 17 ላይ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፡ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፥ ይገድሉትማል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፡፡”
የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት ሳጠና የተረዳሁት ሁለተኛው ነገር ኢየሱስ ለመሞት ፈቃደኛ መሆኑን ነው፡፡ በማቴዎስ 26 ላይ “አባት ሆይ፥ ቢቻልስ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ” ብሏል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ይህንን የተናገረበትን አውድ ብዙ ሰዎች ቆርጠው ያስቀሩታል፡፡ እንዲህ አለ፡- “ነገር ግን አባት ሆይ አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን፡፡” (ማቴዎስ 26፡39)
እንግዲህ ኢየሱስ ራሱን አልሰወረም፡፡ አድራሻውን ግልፅ አድርጓል፡፡ በዮሐንስ 18 ላይ ብዙ ጊዜ እርሱን ወደሚያገኙበት ቦታ እንደሄደ ይናገራል፡፡ ከባለ ሥልጣናቱ ለመሰወር አልፈለገም፡፡ ሊሆን ያለውን ያውቅ ነበር፡፡ በዮሐንስ 18፡4 ላይ፡- “ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ…” ይላል፡፡ አውቆታል! እናም የሚደርስበትን ለመቀበል ዝግጁ ነበር፡፡ በማቴዎስ ላይ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡ “እንዲጠብቁኝ አሥራ ሁለት ሌጊዎን መላእክትን መጥራት እንደምችል አታውቁምን?” ነገር ግን “አባት ሆይ ፈቃድህን መፈፀም እሻለሁ” አለ፡፡ “የአብን ፈቃድ” ይፈጽም ዘንድ ጸሎቱ ተመለሰለት፡፡ በዮሐንስ 10 ላይ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- “ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ”፡፡ ሰውም አምላክም የሆነው ኢየሱስ የዓለምን ሁሉ ኃጢኣት በራሱ ላይ ለመውሰድ እንደ እግዚአብሔር ወልድ፣ እንደ ዘላለማዊ ቃል መምጣቱን ማስታወስ ያስፈልጋችኋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እግዚአብሔር ኢየሱስን ስለ እኛ ኃጢኣት አደረገው (1ቆሮንቶስ 5፡21)፤ እስኪ ከቻላችሁ ዘላለማዊው ቃል፣ ወልድ በወቅቱ ያሳለፈውን ሠቆቃ በልባችው ውስጥ አስቡ፡፡
የተረዳሁት ሦስተኛው እውነታ አይሁድ ለኢየሱስ ስቅለት ተጠያቂዎች አለመሆናቸውን ነው፡፡ ሚስተር ዲዳት እርስዎ የአይሁድ ተሟጋች (ጠበቃ) እንዲሆኑ ማስፈለግዎ በጣም አስገርሞኛል [ሕዝቡ ጭብጨባ አሰማ]፡፡ እንደዚያ ዓይነት የተሳሳተ አመለካከት የነበራቸው ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በታሪክ ውስጥ ነበሩ፡፡ በማቴዎስ 20፡18-19 ላይ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- “ወደ ኢሩሳሌም እንሄዳለን፡፡ ለሞት አሳልፈው ይሰጡኛል፣ እንዲዘብቱብኝ፣ እንዲገርፉኝም እንዲሰቅሉኝም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡኛል” [ሕዝቡ ጭብጨባ አሰማ]፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- “ነፍሴን አኖራታለሁ፡፡” ለሞቱ ማንም ሰው ተጠያቂ መሆን ካለበት ኢየሱስ ራሱ ነው፡፡ እንዲህ ብሏል፡- “ነፍሴን ላኖራት ሥልጣን አለኝ፣ ላነሳትም ሥልጣን አለኝ፡፡”
እንዲሁም ሚስተር ዲዳት እኔም እርሶም ሁላችንም ተጠያቂዎች እንደሆንን ይሰማኛል [ሕዝቡ ጭብጨባ አሰማ]፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር እንዲህ ይላልና፡- “ሁሉም ኃጢኣትን ሰርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል” (ሮሜ 3፡23)፡፡ ኢየሱስን ወደ መስቀል የወሰደው የኛ ኃጢኣት ነበር፡፡
አራተኛው የተረዳሁት እውነታ ክርስቲያኖች ወደ ጭፍን እምነት ሳይሆን ማስተዋልና ዕውቀት ወደሞላበት እምነት መጠራታቸውን ነው፡፡ “የዮናስ ምልክት ምንድነው?” በሚል ርዕስ በሚስተር አሕመድ ዲዳት የተጻፈችውን ክታብ ሳነብ በጣም ነበር የተገረምኩት፤ ምክንያቱም ከአንድ ሺህ ሚሊዮን በላይ ክርስቲኖች በጭፍን የናዝሬቱ ኢየሱስን ክርስቶስ ነው ብለው እንደተቀበሉት ተነግሯልና፡፡ ሚስተር ዲዳት እኔ ትንሽ ግራ ተጋብቻለሁ፤ ምክንያቱም እርሶ ቁርኣንን አንብበውት እንደተቀበሉት ይናገራሉ፤ ተጨባጭ እውነታዎች ግድ አይሉዎትም፤ ምንም ዓይነት ማስረጃም አያሻዎትም፡፡ ዝም ብለው ብቻ ይቀበሉታል፤ ከዚያም እኛ ክርስቲያኖች ያሕዌ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን የገለጠውን መቀበላችንን “ጭፍን እምነት ነው” ብለው ይጠሩታል፡፡ እኔ ግራ ገብቶኛል፤ ምክንያቱም በሙስሊሞች መጽሐፍ በቁርኣን ውስጥ እንደሚናገረው ለኢየሱስ ከተሰጡት መጠርያዎች መካከል አንዱ “አል-መሲህ” የሚል ነውና፡፡ በዚያ ሁኔታ ወደ 11 ጊዜ የተጠቀሰ ይመስለኛል፡፡ ቁርኣንን ወደ እንግሊዘኛ የተረጎመው ሙስሊሙ ተርጓሚ ዩሱፍ ዐሊ አረብኛውን “ክራይስት” (ክርስቶስ) በማለት ወደ እንግሊዘኛ ተርጉሞታል፡፡ ኢየሱስን እንደ ክርስቶስ በመቀበላችን ስለምን ጭፍኖች ተብለን እንወቀሳለን ታድያ?
በአገሬ ውስጥ እስካሁን ድረስ ከኖሩት ታላላቅ የሕግ አዋቂዎች መካከል አንዱ የሆኑት – የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ገናና ስም እንዲኖረው ያደረጉት ሰው – ዶ/ር ሳይመን ግሪንሊፍ ነበሩ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ ቃል መሆኑንና ትንሣኤውን ውድቅ ለማድረግ ሲሞክሩ ሳሉ ነበር ክርስቲያን የሆኑት፡፡ በመጨረሻም ያንን ለማድረግ ጥረት ካደረጉ በኋላ በፍትህ ችሎት ሊቀርቡ በሚችሉ ሕጋዊ መረጃዎች መሠረት የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ እጅግ ከተረጋገጡ የታሪክ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው ወደሚል ድምዳሜ ደረሱ፡፡
የዘመናችን የሥነ ጽሑፍ ታላቅ ባለተሰጥኦ የሆኑት ሲ.ኤስ. ሌዊስ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛውና የዘመነ ሕዳሴ ሥነ-ጽሑፍ ፕሮፌሰር ነበሩ፡፡ በራሳቸው የጥናት ዘርፍ እጅግ የታወቁ ነበሩ፡፡ የርሳቸውን ምሑራዊ ክህሎት የሚጠራጠር ማንም የለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኝና ጌታ ወደ ማመን የመጡት የአዲስ ኪዳንን ተዓማኒነት ውድቅ ለማድረግ ጥረት አድርገው ሳይችሉ በመቅረታቸው ነበር፡፡ እኚህ ሰው እንዲህ አሉ፡- “እኔ በጣም ግትር ከነበሩ ክርስትናን ከተቀበሉ ሰዎች መካከል አንዱ ብሆንም ወደ ክርስቶስ መምጣት የቻልኩት በአዕምሮዬ ምክንያት ነው፡፡”
የኢንግሊዝ ዋና የፍትህ አለቃ የነበሩት ሎርድ ካልዴኮት በኢንግሊዝ የሕግ ሥርኣት ውስጥ አንድ ሰው ሊኖረው የሚችለውን የመጨረሻ ሥልጣን የያዙ ሰው ነበሩ፡፡ እንዲህ አሉ፡- “…ለክርስትና ያሉትን መረጃዎች በመረመርኩ ቁጥር ምንም የማያከራክር እውነታ እንደሆነ ወደማመን መጥቻለሁ፡፡”
ቶማስ አርኖልድ ለአሥራ አራት ዓመታት ያህል የሜጀር ቨርሲቲና ዩኒቨርሲቲ ዋና አስተዳዳሪ ነበሩ፡፡ የታሪክ ተመራማሪና ሦስት ተከታታይ ቅፆች ያሉትን “የሮም ታሪክ” የተሰኘውን መጽሐፍ የጻፉ ደራሲ ነበሩ፡፡ እንዲህ አሉ፡- “ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በላይ በተሟላና በተሻለ ማስረጃ የተረጋገጠ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የሚገኝ አንድም እውነታ አላውቅም፡፡”
የጀርመኑ ሳይንቲስት – ዶ/ር ወርነር ቮን ብራውንት – በስደት ወደ አገሬ የመጡት ሰው – የአሜሪካን የጠፈር ፕሮግራም ከፈጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አንዳኝና አምላካቸው እስኪያውቁት ድረስ እውነተኛ ሳይንቲስት እንዳልሆኑ ተናገሩ፡፡
የደረስኩበት አምስተኛው እውነታ የክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ትክክለኛነት እንዳለው ነው፡፡ የክርስቲያን አዲስ ኪዳን በትክክለኛነቱና በተዓማኒነቱ እንዲሁም በታሪክ ውስጥ በትክክል ተጠብቆ በመቆየት ረገድ የተለየ ነው፡፡ በእጅ ጽሑፎች ሥልጣን ወደር የለሽ ነው፡፡ የእጅ ጽሑፍ የማተምያ ማሽን ከመፈጠሩ በፊት በእጅ የተገለበጠ ነው፡፡ ክቡራትና ክቡራን ለክርስቲያን አዲስ ኪዳን ብቻ ከ24,000 በላይ የእጅ ጽሑፎች አሉ፡፡ ሚስተር ዲዳት ሆይ፤ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች አይደሉም፤ የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፎች ግልባጮች ናቸው እንጂ፡፡ ክቡራትና ክቡራን፤ በእጅ ጽሑፎች ሥልጣን በታሪክ ውስጥ ሁለተኛው መጽሐፍ 643 ግልባጮች ብቻ ያሉት የሆሜር ኢልያድ ነው፡፡ በታሪክ ውስጥ በእጅ ጽሑፎች ሥልጣን ሁለተኛው መጽሐፍ!
ሰር ፍሬዴሪክ ኬንዮን በሰው ልጆች ታሪክ ስለ እጅ ጽሑፎች ሥልጣናዊ ንግግር በማድረግና በዕውቀት ረገድ ከማንም ቀጥለው ሁለተኛ ያልሆኑ (አንደኛ የሆኑ) ሰው ነበሩ፡፡ የቀድሞ የብሪቲሽ ቤተ-መዘክር ኃላፊና ዳይሬክተር የነበሩት እኚህ ሰው እንዲህ አሉ፡- “ቅዱሳት መጻሕፍት ልክ መጀመርያ በተጻፉበት ይዘት ወደኛ በመምጣቸው ላይ የነበረው የመጨረሻው የጥርጣሬ መሠረት ተወግዷል፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ተዓማኒነትና አጠቃላይ ተግባቦት በመጨረሻ እንደተረጋገጠ ሊቆጠር ይችላል፡፡”
የሥነ-ጽሑፍ ታሪካዊ ገጽታ ዕውቀት የጎደላቸው ጉዳዩን የአራቱ ወንጌላት ጸሐፊያን ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ስማቸውን ካላሰፈሩበት ትክክለኛ ምክንያት ውጪ ሊያደርጉ የሚሞክሩ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ እባካችሁን ክቡራትና ክቡራን ይህንን እንዴት እንዳደረጉ ለማወቅ በታሪክ ውስጥ ወደ ኋላ መሄድ ያስፈልገናል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የእጅ ጽሑፎቹ በወቅቱ ትክክለኛነታቸው በሚገባ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ሁሉም ሰው ማን እንደጻፋቸው ስለሚያውቅ ስሞቻቸውን ማስፈር አላስፈለጋቸውም ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕከላዊ ጉዳይ ከማድረግ ዓላማ እንዳያፈነግጡ ጸሐፊያኑ ሆነ ብለው ስሞቻቸውን ላለማስፈር መምረጣቸውንም መናገር ትችላላችሁ፡፡ እንዲሁም የጸሐፊያኑ መዛግብት፣ ማለትም የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ጽሑፎች በዘመነ ሐዋርያት (Apostolic Age) ውስጥ አልፈው ነበር፡፡ እርግጠኛነታቸውን፣ ትክክለኛነታቸውንና ተዓማኒነታቸውን ለማረጋገጥ በመጀመርያው ምዕተ ዓመት የሐዋርያት ዘመን ምርመራ ውስጥ አልፈዋል፡፡
ሌሎች ሰዎች ደግሞ ውሱን በሆነ ንባብና ያለ ምንም የረባ ጥናት “የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌላት የወሬ ወሬ ናቸው ምክንቱም ጸሐፊያኑ በኢየሱስን ስቅለትና ትንሣኤ ወቅት የተፈፀሙትን ክስተቶች የተመለከቱ የዐይን እማኞች አልነበሩምና” በማለት ይናገራሉ፡፡
ይህንን የሚሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ ማርቆስ 14፡50ን ይጠቅሳሉ፡፡ ሁሉም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጥለውት ስለሸሹ በሁለት ደቂቃዎች ውስጥ ክርክሩን ውድቅ እንደሚያደርጉም ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ በእነርሱ አመለካከት ሁሉም ነገር ስማበለው ነበር፡፡ ክቡራትና ክቡራን፤ እንደዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በእጃችን ከሚገኙት ማስረጃዎች አንጻር ሲገመገም በጣም ግለፅ የሆነውን ጉዳይ የዘነጋ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ ያህል እስኪ ዝም ብላችሁ ከዚያ በኋላ የሚገኙትን አራት ቁጥሮች አንብቡ፡፡ “ጴጥሮስም ተከተለው” ይላል፡፡ አያችሁ? – በቡድን ሆነው ጥለውት ሸሹ ነገር ግን ወዲያውኑ ተነጣጥለው ተመልሰው መጡ፤ ሚስተር ዲዳት፡፡ [ሕዝቡ ጭብጨባ አሰማ]
ቁጥር 54 እንዲህ ይላል፡- “ጴጥሮስም በሩቁ ተከተለው፡፡” በቀጥታ ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ ገባ፡፡ እዚያው ከሎሌዎቹ ጋር ተቀምጦ ነበር፡፡ እስኪ አስቡት፡፡ ከሎሌዎቹ ጋር እሳት ይሞቅ ነበር፡፡ በማርቆስ 14 ላይ እንዲህ ይላል፡- “ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ በታች በኩል ነበር፡፡” ክቡራትና ክቡራን፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠናችሁ እንደሆን ማርቆስ በወንጌሉ ውስጥ የጴጥሮስን ምስክርነት እንዳሰፈረ ትገነዘባላችሁ፡፡ ጴጥሮስ እዚያው ነበር፡፡ ከዚያም ወደ ዮሐንስ 18፡15 እንሄዳለን፡- “ስምዖን ጴጥሮስም ሌላውም ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ፡፡ ያም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፥ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፡፡” ዮሐንስ 19፡26 እንዲህ ይላል፡- “ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት፡፡ ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን እናትህ እነኋት አለው፡፡” በቦታው ላይ ነበሩ ስለዚህ የዐይን ምስክሮች ናቸው፡፡
በሕግ ችሎት መፈቀዱን በተመለከተ፤ በብዙ ሕጋዊ ሁኔታዎች ውስጥ የጥንታዊ መዝገብ ሥርዓት ተብሎ የሚታወቅ ነገር አለ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ነገሮች ግልፅ እንዲሆኑላችሁ ወደ ሕግ መሄድ ሊያስፈልጋችሁ ነው፡፡ ዶ/ር ጆን ዋርዊክ ሞንትጎሜሪ የሕግ አዋቂና የሳይመን ግሪንሊፍ የሕግ ትምህርት ቤት ዲን ሲሆኑ በስትራስቦርግ (ፈረንሳይ በሚገኝ) ዓለም አቀፍ የሥነ መለኮትና የሕግ ትምህርት ቤት ውስጥ ደግሞ በመምህርነት ያገለግላሉ፡፡
“በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሰነዶች ላይ፤ በተለይም በአራቱ ወንጌላት ላይ የጥንታዊ መዛግብት ስርኣት ሲተገበር” ይላሉ – ልብ በሉ ይህ የሕግ ትምህርት ቤት ዋና ኃላፊ ንግግር ነው – “በወንጌላት ጽሑፎች ላይ ተግባራዊ ሲደረግና ኃላፊነት በተሞላበት መለስተኛ የንባብ ሕየሳ ሲታገዝ ይህ ደንብ በየትኛውም የሕግ ችሎት ብቃት እንዳላቸው ያረጋግጣል፡፡”
ትልቁ የዐይን እማኞች ምስክርነት የሚገኘው በወንጌላት ውስጥ አይደለም፡፡ ከ55 እከ 56 ዓ.ም. በሐዋርያው ጳውሎስ በተጻፈው 1ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ላይ ነው፡፡ ያንን የሚክድ ስመ ጥር ምሑር እስካሁን ድረስ አላየሁም፡፡ ጳውሎስ እንደተናገረው (ከ29 ዓመታት በፊት መሆኑ ነው፡፡ ከተለወጠ በኋላ – መሪዎቹን አግኝቷል፡፡ የጌታን ወንድም ያዕቆብንም በኢየሩሳሌም አግኝቶታል)፤ ከ500 በላይ የሚሆኑ የትንሣኤ ምስክሮች መኖራቸውን የሚያረጋግጥ ትውፊት ተቀብሏል፡፡ ያንን ወደ ችሎት ብትወስዱትና ለዐይን ምስክሮቹ ስድስት ስድስት ደቂቃ ብቻ ብትሰጡ 3,000 ደቂቃዎች ወይንም የ50 ሰዓታት የዐይን እማኞችን ምስክርነት ታገኛላችሁ፡፡
ነገር ግን ዋናው ነጥብ እርሱ አይደለም፡፡ ያ እርሱ ራሱ በግሉ የመረመረው የተላለፈለት ትውፊት ነው፡፡ ከዚያም ጳውሎስ ከመካከላቸው አብዛኞቹ አሁንም ድረስ በሕይወት መኖራቸውን ተናገረ፡፡ ትውፊቱ በተላለፈበት ጊዜ ኣይደለም፤ ነገር ግን አሁን፡፡ ክቡራትና ክቡራን ጳውሎስ “እኔን ካላመናችሁኝ እነርሱን ጠይቋቸው” እያለ ነው፡፡
እንዲሁም፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መልዕክትና አዲስ ኪዳን በሐዋርያት ሲሰበክ በነበረበት ወቅት በጥላቻ የተሞሉና ተቃዋሚ የነበሩ ምስክሮች የመኖራቸውን እውነታ ብዙ ሰዎች ትኩረት ይነፍጉታል፡፡ ከታወቀው እውነታ ቢያፈነግጡ ኖሮ ወዲያውኑ ሊያርሟቸው የሚችሉ ተቃዋሚ ምስክሮች ነበሩ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ምስክርነት በሕግ ሥርዓት መሠረት የመስቀለኛ ምርመራ መርህ በመባል ይታወቃል፡፡ ከእውነት የማፈንገጥ ሙከራ አላደረጉም፡፡ በተጨማሪም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የሆኑ ብዙ ዓለማውያን ምንጮችን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ፖሊካርፕ በመባል የሚታወቅ ሰው የሐዋርያው ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ነበር፡፡ ወደ 2,000 ዓመታት ያህል ዕድሜ ባላቸው ሥራዎቹ ውስጥ እንዲህ በማለት ጽፏል፡- “እነዚህ ወንጌላት የተመሰረቱበት መሰረት በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ የኑፋቄ መምህራን እንኳ ሊያጣጥሉት አልቻሉም፡፡” የራሳቸውን የኑፋቄ ትምህርት ለማዳበር ያለውን መረጃ ተንተርሰው መነሳት ግድ ይላቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ይህንን አላለም፣ ኢየሱስ ያንን አላደረገም ሊሉ አይችሉም ነበርና፡፡ ስለዚህ እነርሱ ከተናገሩት ነገር በመነሳት የኑፋቄ ትምህርታቸውን መገንባት ነበረባቸው፡፡
ብዙ ምሑራን የክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ተዓማኒ መሆኑን ከድምዳሜ ደርሰዋል፡፡ ሚስተር ሚለር ቡሮውስ በአገሬ ውስጥ ከሚገኙት ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የዬል ዩኒቨርሲቲ አመራር ነበሩ፡፡ እንዲህ አሉ፡- “በአዲስ ኪዳን ጽሑፍ አስተላለፍ ላይ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣ መተማመን አለ፡፡” ተመራማሪና የሥነ ቁፋሮ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሆዋርድ ቮክስ እንዲህ አሉ፡- “ከሥነ ጽሑፋዊ ማስረጃ አኳያ ብቸኛው አመክንዮአዊ ድምዳሜ የአዲስ ኪዳን ተዓማኒነት ከየትኛውም ሌላ የጥንት መዝገብ የላቀ መሆኑ ነው፡፡”
ያረጋገጥኩት ስድስተኛው እውነታ ክርስቶስ መሰቀሉን ነው፡፡ ታሪካዊና ተዓማኒ የሆነው ሰነድ ምንድነው የሚያመለክተው? ይህንን የሚያስገነዝበን የክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ አይደለም፡፡ “ፍርድ የሚሻ ማስረጃ” በሚለው መጽሐፌ ጀርባ ላይ የሰፈሩት ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት ኢየሱስ በስቅለት እንደሚሞት መተንበይ ብቻ ሳይሆን በእርግጥም ተሰቅሏል፡፡ ኢየሱስ እንደሚገረፍና ለስቅላት ተላልፎ እንደሚሰጥ ተናግሯል፡፡ በዮሐንስ 19፡17-18 ላይ እንዲህ ይላል፡- “ኢየሱስንም ይዘው ወሰዱት፤ መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ… በዚያም ሰቀሉት፥ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሁለት፥ አንዱን በዚህ አንዱን በዚያ ኢየሱስንም በመካከላቸው ሰቀሉ፡፡”
እስኪ የሆነውን ነገር እንከታተል፡፡ መጀመርያ ኢየሱስ በሮማውያን መገረፉን እናያለን፡፡ ምን ማለት ነው? ሮማውያን አንድን ሰው እስከ ወገቡ ድረስ ልብሱን ይገፉትና ጠርቀው ያስሩታል፡፡ ከዚያም አንድ ከግማሽ ያህል ጫማ የሚረዝም መያዣ ያለው መግረፍያ ያመጣሉ፡፡ በመያዣው ጫፍ ላይ ክብደት ያላቸው የአጥንት ወይም የብረት ጉጠቶች ወጣ ገባ ብለው የተሰኩባቸው አራት የቆዳ አለንጋ ቅርንጫፎች ይገኛሉ፡፡ ጉጠቶቹ በጥቂቱ አምስት ይሆናሉ፡፡ የተለያየ ርዝመት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሮማውያኑ በግለሰቡ ጀርባ ላይ ጅራፉን ሲያሳርፉ የብረቶቹ መይንም የአጥንቶቹ ጉጠቶች በአንድ ጊዜ ሰውነቱን ይመቱታል፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ መግረፊያውን ወደ ታች ሻጥ ያደርጉታል፡፡ አይሁድ 40 ጅራፍ ብቻ ነው የሚፈቅዱት፡፡ በስህተት የቆጠሩ እንደሆን ህጉን እንዳይተላለፉ ከ39 በላይ አያደርጉም፡፡ ሮማውያን ግን ያለገደብ ነው የሚገርፉት፡፡ ስለዚህ ሮማውያን አይሁዳዊ የሆነን ሰው ሲቀጡ ለአይሁዳውያን ካላቸው ንቀት የተነሳ 41 ወይንም ከዚያ በላይ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ በጥቂቱ 41 ግርፋቶች ደርሰውበታል ማለት ነው፡፡
ብዙ የሕክምና አዋቂዎች በስቅለት ላይ ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ ከነዚህ ባለሙያዎች መካከል ዶ/ር ባርቤት ከፈረንሳይ እና የአሪዞና ግዛት ነዋሪ የሆኑት የአገሬ ሰው ዶ/ር ሲ. ትሩማን ዴቪስ ይገኙበታል፡፡ ከሕክምና አኳያ በስቅለት ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት ያደረጉ የሕክምና ዶክሮች ናቸው፡፡ የሮማውያንን ግርፋት ውጤት እንደሚከተለው ያቀርባሉ፡
“ከባድ የሆነው መግረፍያ [በግለሰቡ] ትከሻ፣ ጀርባና እግሮች ላይ በሙሉ ኃይል እንዲያርፍበት ይደረጋል፡፡ በመጀመርያ ጠንካራው ጠፍር ቆዳውን ወደ ውስጥ ይቆርጣል፡፡ ከዚያም ግርፋቱ ሲቀጥል ከላይ የሚገኙትን ጡንቻዎች እየከተፉ ስለሚገቡ ከቆዳ ሥር ከሚገኙት የደም ማስተላለፍያዎች ደም እየተስፈነጠረ ይወጣል፤ በመጨረሻም ከስር ከሚገኙት ጡንቻዎች ደም-ሥር ደም መፍሰስ ይጀምራል፡፡ የብረት ጉጠቶቹ በመጀመርያ ሰፋፊና ጥልቀት ያላቸው ቁስሎች እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ፤ ከዚያም የበለጠ እየቆረጡ ያሰፉታል፡፡ በመጨረሻም የጀርባ ቆዳ ተበጣጥሶ አጠቃላይ ቦታው ተለይቶ እስከማይታወቅ ድረስ የተቀዳደዱ የሚደሙ ቲሹዎች ብቻ ይሆናል፡፡”
እኔ የመዘገብኳቸው ሌሎች ምንጮች እንደሚናገሩት ከሆነ አንዳንድ ጊዜ ጀርባ ተከፍቶ አንጀት ስለሚወጣ ብዙ ሰዎች ከግርፋቱ የተነሳ ይሞታሉ፡፡
ከግርፋቱ በኋላ ኢየሱስን ወደ መግደያው ስፍራ በመውሰድ የእጆቹን አንጓዎችና እግሮቹን በሾሉ ብረቶች ቸነከሩት፡፡ በዚያ አርብ ከሰዓት በኋላ ከኢየሱስ ጋር የተሰቀሉትን የሁለቱን ወንበዴዎች ጭኖች ሰበሩ ነገር ግን የእርሱን እግሮች አልሰበሩም ይላል፡፡ ለምንድነው ጭኖችን የሚሰብሩት? በመስቀል ላይ በምትንጠለጠሉበት ጊዜ ከስር እግሮቻችሁን አጠፍ ያደርጉና ይቸነክራሉ፡፡ በስቅለት ወቅት ብዙ ጊዜ የሳባችሁት አየር አፍኗችሁ ነው የምትሞቱት፡፡ የደረት ጡንቻዎች ጫና ስለሚያርፍባቸው አየር ወደ ውጪ ማስወጣት ይሳናችኋል፡፡ ወደ ውስጥ ታስገባላችሁ ነገር ግን ወደ ውጪ ማስወጣት አትችሉም፡፡
ስለዚህም እዚያ ላይ ተንጠልጥላችሁ ስለምትታፈኑ አየር ለማስወጣት እግሮቻችሁን ወደ ላይ ትገፋላችሁ ከዝያም ለማስገባት ወደታች ታወርዳላችሁ፡፡ ቶሎ እንዲሞቱ ስለፈለጉ እግሮቻቸውን ሰበሯቸው፤ ስለዚህ ወደ ላይ መግፋት ስለማይችሉ ይሞታሉ፡፡ የኢየሱስ እግሮች አልተሰበሩም፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በገለጠው ቃሉ መሠረት ኢየሱስ ሞቶ ነበር፡፡ ክቡራትና ክቡራን፤ እግሮቹን ቢሰብሩት ኖሮ የኛ መሲህ ሊሆን አይችልም ነበር፡፡ ዘላለማዊው ቃል ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ያሕዌ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ እግሮቹ እንደማይሰበሩ ተናግሯልና፡፡ አጥንቶቹ እንደማይሰበሩ ተናግሯል፡፡ ክቡራትና ክቡራን ያሕዌ እግዚእብሔር ይሆናል ብሎ የተናገረውን እየፈጸመ ነበር፡፡
ቀጥሎ ያገኘሁት እውነታ ክርስቶስ… [ጆሽ ወደኋላ ዘወር ብለው ሰዓት ተቆጣጣሪውን ምን ያህል ጊዜ እንደቀራቸው ሲጠይቁት ይታያል፡፡ “20 ደቂቃ” የሚል መልስ ከተቀበሉ በኋላ ንግግራቸውን ቀጠሉ] …ክርስቶስ መሞቱን ነው፡፡ ያ የደረስኩበት ሰባተኛው እውነታ ነው፡፡ ክቡራትና ክቡራን በዮሐንስ 19፡30 ላይ ኢየሱስ ለመሞት መፍቀዱ ተነግሯል፤ ለዚያም ነው ረጅም ጊዜ ያልወሰደው፤ ለመሞት ነበር የመጣው፡፡ “ሕይወቴን አኖራታለሁ” አለ፡፡ በዮሐንስ 19 ላይ ደግሞ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱንም አዘንብሎ መንፈሱን ሰጠ፡፡ ለመሞት ፈቀደ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ በዮሐንስ 19፡34 ላይ ስለ ደም እና ስለ ውኀ የሚያመለክት ነገር ታገኛላችሁ፡፡ ሚስተር ዲዳት ግን በመጽሐፋቸው ውስጥ ኢየሱስ ላለመሞቱ እንደማስረጃ ጠቅሰውታል፡፡
መስቀል ላይ ሳለ ወታደሮቹ ፈጽሞ መሞቱን አረጋግጠዋል፤ ነገር ግን የመጨረሻውን ማረጋገጫ ማግኘት ፈለጉ፡፡ ጦር ወስደው ጎኑን ወጉት፡፡ የዐይን ምስክሮች ዘገባ እንደሚለው ውኀና ደም ተለያይቶ ወጣ፡፡ ሚስተር ዲዳት በመጽሐፋቸው ውስጥ ኢየሱስ እስከዚያ ድረስ በሕይወት ስለመቆየቱ እንደ ማስረጃ ጠቅሰውታል፡፡ ይህንን ለመደገፍ በቲንከርስ ዳይጀስት 1949 ውስጥ በአንስቴሲዎሎጂስት [ስለ ማደንዘዣ መድኃኒቶች የሚያጠና ሰው] የተጻፈ ሐሳብ በጽሑፋቸው ውስጥ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ በተለያዩ ሰዎች የተሰሩ የሕክምና ጥናቶችን ለማግኘት ችያለሁ፡፡
ካለኝ ጊዜ አንፃር ሁለቱን ብቻ እጠቅሳለሁ፡፡ የመጀመርያው ከምሑራዊ ዕይት አኳያ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ይህንን ጆርናል ይዘው የነበሩት ብዙ የሕክምና እና የዩኒቨርሲቲ ቤተ መጽሐፍት አሁን አስወግደውታል፡፡ በሕክምናው ዓለም ውስጥ በሚገኙ ብዙ ሰዎች ዘንድ ጊዜ እንዳለፈበት ብቻ ሳይሆን ከዘመናዊው ሕክምና አንፃር ኋላ ቀር እንደሆነ ይቆጠራል፡፡
ሁለተኛ ከሕክምና ዕይታ አኳያ ነው፡፡ አንድ ሰው በሕይወት ቢኖርና ኢየሱስ የደረሰበት ዓይነት ቁስለት ቢደርስበት ወደ ውጪ ከመድማት ይልቅ ወደ ደረት የውስጠኛው ክፍል በመድማት ውስጣዊ የደም መፍሰስን ያስከትልበታል፡፡ በቁስሉ ክፍተት በኩል ደሙ ወደ ውጪ የመፍሰሱ ሁኔታ በጣም አነስተኛ ነው የሚሆነው፡፡ ከረጋ ደም የሚገኘው ውሃ መሰል ፈሳሽ እንዲሁም ደም መውጣት የሚችልበትን ክፍተት ጦሩ ማበጀት የሚችለው ወደ ውስጥ ጠልቆ ከወጋ ብቻ ነው፡፡ በስቅለት ምክንያት ከባድ የሆነ ውስጣዊ ጉዳት የደረሰበት ሰው ልቡ ላይ በጦር ቢወጋ ያለ ጥርጥር ወዲያውኑ ይሞታል፡፡ የአይሁድ የቀብር ስርኣት ዝርዝር ሂደት የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ሳይጨምር ማለት ነው፡፡
በማሳቹሴት ግዛት በሚገኝ ከፍተኛ ሆስፒታል በልብ ድካም ምክንያት በሞቱ ሰዎች ላይ ለረጅም ዓመታት ምርምር ሲደረግ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ የሰው ልብ 20 ሲሲ የሚሆን የካባቤ ልብ ፈሳሽ ይኖረዋል፡፡ አንድ ሰው በልብ ድካም ምክንያት የሚሞት ከሆነ ከ500 ሲሲ በላይ የሚሆን የካባቤ ልብ ፈሳሽ የሚገኝበት ሲሆን በፈሳሽ እና በረጋ ደም መልክ ይወጣል፡፡ በወቅቱ የታየው ይህ ሊሆን ይችላል፡፡
የአይሁድ የቀብር ሥርኣት ደግሞ የመጨረሻው የሞት ማረጋገጫ ነው፡፡ “የዮናስ ምልክት ምንድነው?” በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 9 ላይ ሚስተር ዲዳት በአይሁድ የቀብር ሥርኣት መሠረት እጥበት ካደረጉለት በኋላ 100 ፓውንድ በሚሆን እንስላልና ከርቤ አሸጉት ብለዋል፡፡ እንግዲህ ጀርባችሁ እስኪከፈት ድረስ ተገርፋችሁ፣ እጆችና እግሮቻችሁ ተቸንክረው፣ በመስቀል ላይ ተሰቅላችሁ፣ ጎናችሁ በጦር ተወግቶ፣ ከመስቀል ላይ ወርዳችሁ እንደ ሲሞንቶ በሚያጣብቅ 100 ፓውንድ ቅመም ብትታሸጉ – በዚያ ውስጥ አልፋችሁ በሕይወት መኖር መቻል ከትንሣኤ የበለጠ ተዓምር የሚጠይቅ ነው!
በማስከተል ደግሞ ጥብቅ የሆነው የሮማውያን ሕግ አለ፡፡ ክርስቶስ ወዲያውኑ በመሞቱ ወይንም ብዙም ሳይቆዩ አስክሬኑን በመጠየቃቸው ጲላጦስ ትንሽ ተደንቆ ነበር፤ እኔም ሁኔታው ትንሽ ሊያስገርመኝ ይችላል፡፡ የመቶ አለቃውን በመጥራት፡- “ሄደህ ኢየሱስ መሞቱን እንድታረጋግጥልኝ እፈልጋለሁ” አለው፡፡ እንግዲህ ክቡራትና ክቡራን ይህ የመቶ አለቃ ሞኝ ሰው አልነበረም፡፡ ሚስቱ መበለት ሆና እንድትቀር ለማድረግ ዝግጁ አልነበረም፡፡
የመቶ አለቃው የአንድን ሰው ሞት በአራት የተለያዩ የሞት ቅጣት አስፈጻሚዎች ያረጋግጣል፡፡ የዘመኑ የሮማውያን ሕግ እንደዚያ ነበር፡፡ አራት የሞት ቅጣት አስፈጻሚዎች መኖር አለባቸው፡፡ አንደኛው ትንሽ ግዴለሽ ቢሆን ሁለተኛው ይይዘዋል፣ እናም የሞት ማረጋገጫውን ለመፈረም አራቱም ግዴለሾች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የሮማውያን ቅጣት ከባድ ነበርና፡፡
ለምሳሌ ያህል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በሐዋርያት ሥራ 12 ላይ መልአክ ጴጥሮስን ከእስር ቤት ባዳነው ጊዜ ሄሮድስ ጠባቂዎቹን ሁሉ ገደላቸው – አንድ ሰው ከእስር እንዲያመልጥ በማድረጋቸው ብቻ ነው የገደላቸው፡፡ በክርስቲያን አዲስ ኪዳን ውስጥ በሐዋርያት ሥራ 16 ላይ ለጳውሎስና ለሲላስ የወህኒ ቤት በሮች ተከፈቱላቸው፤ እስራቶቻቸው ተፈቱ፤ ስለዚህ ጠባቂው ያንን ባየበት ቅጽበት ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ፡፡ ጳውሎስም “ተው!” በማለት ጮኸ፡፡ አያችሁ? ያ ጠባቂ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያውቅ ነበር፡፡ በሮማውያን ከመገደል ይልቅ በራሱ ሰይፍ መሞትን ነበር የመረጠው፡፡
ክርስቶስ ሞቷል፡፡ ፍላቪየስ ጆሲፈስ [ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን] የተሰኘው አይሁዳዊው ጸሐፌ ታሪክ በ70 ዓ.ም. ታይተስ ኢየሩሳሌምን ሲያጠፋ ሳለ ወደዚያ ሄዶ ነበር፡፡ በቦታው ሲደርስ ሦስት ጓደኞቹ ሲሰቀሉ አየ፡፡ ገና መሰቀላቸው ነበር፡፡ ተገርፈውና ሁሉም ነገር ተፈጽሞባቸው ነበር፡፡ ወደ ጠባቂዎቹ አዛዥ ሄዶ “እባክህን ልቀቃቸው” በማለት ለመነው፡፡ ፍላቪየስ የሚለው ስም የሮም ንጉሥ ጆሲፈስን ወደ ቤተሰቡ ስለቀላቀለው የተሰጠው ስም መሆኑን ልብ በሉ፡፡ አይሁድ ሆኖ ሳለ ተቀባይነትን ያተረፈው በዚያ ምክንያት ነበር፡፡ እናም ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ወዲያውኑ የሮማውያን ጠባቂዎች አዛዥ ሦስቱንም ሰዎች ከመስቀል ላይ አወረዳቸው፤ ሆኖም ግን ክቡራትና ክቡራን ከሦስቱ ሁለቱ ሞቱ፡፡ ገና ከመሰቀላቸው ነበር ወዲያውኑ በፍጥነት የወረዱት፡፡ ስቅለት ያን ያህል አሣቃቂ ነው፡፡
አይሁድ ኢየሱስ መሞቱን አውቀው ነበር፡፡ በማቴዎስ 27 ላይ ወደ ሮማዊው መሪ በመሄድ “በሕይወት በነበረ ጊዜ የተናገረውን አስታወስን…” አሉት፡፡ በሌላ አባባል አሁን ምንድነው ማለት ነው? ሙት ነው! “በሕይወት በነበረ ጊዜ ከሦስት ቀን በኋላ እነሳለሁ ብሏል” አሉት፡፡ ሚስተር ዲዳት “አይሁድ ስህተት መስራታቸውን ተረዱ” በማለት መጻሕፍታቸው ውስጥ አስፍረዋል፡፡ አሁን እንኳ እነዚያን መጻሕፍት ይዘው የተቀመጡ ይመስለኛል፡፡ “ነፍሱ ባለመውጣቷ ሁለተኛ ስህተት መስራት እንደሌለባቸው ስላሰቡ የጠባቂዎችን ቡድን አምጥተው በዚያ ስፍራ አቆሙ” ብለው ጽፈዋል፡፡ መልካም፤ አይሁድ ራሳቸው እኮ በገዛ አንደበታቸው መሞቱን ተናግረዋል፡፡ “ማንም ሰው ሬሳውን በመስረቅ ምንም ዓይነት ማታለል እንዳይኖር ማረጋገጥ እንፈልጋለን፡” ነበር ያሉት፡፡ አይሁድ በብዙ ነገር ተወንጅለዋል ነገር ግን በሞኝነት የተወነጀሉበት ጊዜ እምብዛም ነው [የሕዝቡ ሳቅ]፡፡ እንደሞተ ያውቃሉ፡፡
በማስከተል የደረስኩበት እውነታ የአይሁድ የቀብር ሂደት ነው፡፡ “ሰንበት በመድረሱ ምክንያትና ተሸክመውት መመለስ ስለሌለባቸው በጣም ተጣድፈው ነበር” በማለት አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ክቡራትና ክቡራን፤ ጥልቅ ምርመራዎችን በማድረግ ይህንን አረጋግጫለሁ፡፡ “የትንሣኤው ሁኔታ” በሚለው መጽሐፌ ውስጥ እንዳሰፈርኩት የቀብሩ ሂደት በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ በሰንበት እንኳ ሊያከናውኑት ይችላሉ፡፡ ሰንበት ስለመምጣቱ መጨነቅ አያስፈልጋቸውም፡፡ አስክሬኑ ሰንበት ከገባ በኋላ በመስቀል ላይ እንዲቆይ ባይፈልጉም ተረጋግተው ሊቀብሩት ይችላሉ፡፡ በቅመሞች ያሽጉታል – በዚህም መሰረት 100 ፓውንድ የሚመዝኑ መልካም መዓዛ ያላቸው ቅመሞች – የማጣበቅ ባሕሪ ካለው ጠንካራ ንጥረ ነገር ጋር ማለት ነው፡፡
አስክሬኑን ቀጥ አድርገው ይዘረጉታል፡፡ ከዝያም ሠላሳ ሴንቲ ሜትር ስፋት ባለው ከተልባ እግር በተሠራ ጨርቅ አስክሬኑን ከእግር ጀምረው ይጠቀልሉታል፡፡ በመተጣጠፍያዎች መካከል የሚያጣብቀውን ንጥረ-ነገር ከቅመሙ ጋር ያደርጉበታል፡፡ እስከ ብብት ድረስ ከጠቀለሉት በኋላ ክንዶቹን ወደ ታች ይዘረጉታል፤ ከንደገና ከጣቶቹ በመጀመር እስከ አንገት ድረስ ይጠቀልላሉ፤ ከዚያም ሌላ ቁራጭ ጨርቅ በራሱ ዙርያ ይጠመጥማሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ በዙርያው የተደረገው ነገር ክብደቱ ከ117 እስከ 1120 ፓውንድ እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡
በማስከተል የደረስኩበት እውነታ በኢየሱስ መቃብር አካባቢ በጣም ጥብቅ የሆነ ጥበቃ ማድረጋቸውን ነው፡፡ በጣም ትልቅ የሆነ ድንጋይ በመቃብሩ ላይ እንደገጠሙ ተነግሯል፡፡ ማርቆስ ድንጋዩ በጣም ግዙፍ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከአንደኛው ክፍለ ዘመን የተገኘ አንድ ታሪካዊ ዘገባ ሃያ ሰዎች ድንጋዩን ሊያንቀሳቅሱት እንደማይችሉ ይናገራል፡፡ እዚያ ጋ ትንሽ የተጋነነ ይመስለኛል፤ ሆኖም ስለ ድንጋዩ መጠን የሚሰጠን ጠቃሚ መረጃ አለ፡፡ ስለ ድንጋዩ ንግግር ሳደርግ የሰሙ ሁለት የምህንድስና ፕሮፌሰሮች ወደ እስራኤል ተጉዘው ነበር፡፡ እነዚህ የምህንድስና ፕሮፌሰሮች ክርስቲያኖች አልነበሩም፡፡ አራት ከግማሽ እስከ አምስት ጫማ በሚሆኑ የአይድ መቃብሮች ላይ የሚገጠሙትን የድንጋይ መጠኖች አስልተው በጥሩ ሁኔታ የተጻፈ ደብዳቤ ላኩልኝ፤ እናም በጥቂቱ ከአንድ ከግመሽ እስከ ሁለት ቶን ድረስ እንደሚመዝን አስታውቀውኛል፡፡
ሚስተር ዲዳት በመጽሕፍታቸው ውስጥ አንድ ወይንም ሁለት ሰዎች ዲንጋዩን በማንከባለል በሩ ላይ መግጠማቸውን ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ወይንም ሁለት ሰዎች ዲንጋዩን መልሰው ሊያነሱት ይችላሉ፡፡ የአርማቲያሱ ዮሴፍ ዲንጋዩን አንከባሎ በሩ ላይ እንደገጠመ ተነግሯልና፡፡ በዛሬው ውይይት ላይ ልትተገብሩት የማትችሉትን ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ወይንም በቁርኣን ላይ በኃይል ባትጭኑ መልካም ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል፡- ትላንትና እስታዲየሙን ለመመልከት ስመጣ እዚህ ካገኘኋቸው ሰዎች መካከል አንዱን “እነዚህ ሁሉ ወንበሮች እንዴት እዚህ ሊመጡ ቻሉ?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡ እርሱም “ሚስተር ዲዳት ናቸው ያመጡት” አለኝ፡፡ ሚስተር ዲዳት ልጠይቅዎት፤ እነዚህን ሁሉ 700 ወንበሮች ወደዚህ ያመጡት ብቻዎትን ነበር እንዴ? [የሕዝቡ ጭብጨባና ሳቅ] አይደለም! በብዙ ሰዎች አማካይነት ነው የመጡት፡፡ ይህንን ሲምፖዚየም ያመቻቹት ሚስተር ዲዳት እንደሆኑ ልናገር እችላለሁ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ሁኔታዎች ለማቀናጀት የረዷቸው ሌሎች ሰዎች መኖራቸውን አምናለሁ፡፡
ታሪክ ሂትለር ፈረንሳይን ወረረ ይለናል [የሕዝቡ ሳቅ]፡፡ በፈረንሳይ ውስጥ ብቻውን ሞክሮት ሊሆን ይችላል ነገር ግን በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ብቻውን የሞከረ አይመስለኝም፡፡
የአርማቲያሱ ዮሴፍን የረዱት ብዙ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም ወደ ኋላ መለስ ብላችሁ ስታጠኑ መቃብሮቹ ተዳፋት ላይ የተሰሩ ቦዮች እንዳሏቸው ትመለከታላችሁ፡፡ ድንጋዮቹን እዚያ ውስጥ ነው የሚያስቀምጧቸው፡፡ ከድንጋዩ ስር ታኮ አለ፡፡ ክቡራትና ክቡራን የሰባት ዓመቷ ልጄ ልታንከባልለው ትችላለች፤ ምክንያቱም ድንጋዩ በራሱ ጊዜ ወደ ታች ተንከባሎ የመቃብሩ መግቢ ላይ እንዲገጥም ታኮውን ወደ ላይ ስባችሁ ማውጣት ብቻ ነው የሚጠበቅባችሁ፡፡
ከዚያም መቃብሩን የሚጠብቁ ጠባቂዎች ተመደቡ፡፡ አይሁድ ያንን ማድረግ ስለፈለጉ ወደ ሮማውን በመሄድ የጥበቃ ቡድን እንዲሰጧቸው ጠየቁ፡፡ ክቡራትና ክቡራን፤ የግሪኩ ቃል ኩስቶዲያ የሚል ሲሆን፤ 16 ሰዎችን ያካተተ የጠባቂዎች ቡድን ያመለክታል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ስድስት ካሬ ጫማ ቦታ እንዲጠብቅ ሰልጥኗል፡፡ የሮማውያን ታሪክ እንደሚያሳየው አስራ ስድስቱ ሰዎች ስድስት እስኩዌር ያርድ ቦታ ከአንድ ባታልዮን መከላከል መቻል ይኖርባቸዋል፡፡ እያንዳንዱ ጠባቂ አራት መሳርያዎችን ይታጠቃል፡፡ እጅግ ቀልጣፋ ተዋጊዎች ናቸው፡፡ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችም ከሞላ ጎደል እንደርሱ ናቸው፡፡
በማስከተል የሮም ምልክት ያለው ማህተም በመቃብሩ ላይ ተደረገ፡፡ ያ ማህተም የሮምን ግዛተ መንግሥት ኃይልና ሥልጣን ይወክላል፡፡ የክርስቶስ አካል 100 ፓውንድ በሚሆን ማጣበቂያና መኣዛ ያላቸው ቅመማ ቅመሞች ተጠቅልሏል፡፡ ከአንድ ተኩል እስከ ሁለት ቶን የሚመዝን ድንጋይ የመግቢያው በር ላይ ተገጥሟል፡፡ የሮም ማህተም ታትሞበታል፤ እንዲሁም የ16 ሰዎች የጥበቃ ቡድን በቦታው ላይ ቀቆሟል፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ተከሰተ፡፡ ይህ የታሪክ ሰነድ ጉዳይ ነው፤ ከሦስት ቀናት በኋላ መቃብሩ ባዶ ነበር፡፡
እዚያ ላይ መከራከር አያስፈልገኝም፤ ምክንያቱም መቃብሩ ባዶ መሆኑን ሚስተር ዲዳት ራሳቸው አምነዋልና፡፡ ስለዚህ እዚያ ላይ ምንም ጊዜ አላጠፋም፡፡
የዮናስ ምልክት – ያንን በማንሳትዎ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ የዮናስ ምልክት – ብዙ ጊዜ የሚፈልግ አይደለም ምክንያቱም ከተባለው ነገር አኳያ አስፈላጊ አይመስለኝምና፡፡ አንድን ነገር በዚያ ዘመን በነበረው ቋንቋና ባሕል ማጥናት ይኖርባችኋል፡፡ እንግዲህ አሁን በዚያ ዘመን ወደነበረው የአይሁድ ቋንቋና የአይሁድ ባሕል መመለሰ ግድ ሊላችሁ ነው፡፡ የአሁኑ ዘመን አይደለም – የደቡብ አፍሪካ፣ የሕንድ ወይም የአሜሪካ አይደለም፡፡ የዚያ ዘመን የኢስራኤላዊ-አይሁድ ባሕል፡፡
ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ማለት ምን ማለት እንደሆነ እስኪ እንመልከት፡፡ በመጽሐፈ አስቴር ምዕራፍ 4 ላይ፤ በይሁዶ-ወክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ማለቴ ነው፤ ለሦስት ቀናትና ለሦስት ሌሊቶች ያህል ጾም እንደታወጀ ይናገራል፡፡ ከዚያም በመቀጠል ጾሙን በሦስተኛው ቀን ላይ አጠናቀቁ ይላል፡፡ አያችሁ? በአይሁድ አነጋገር “ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት” ማለት “እስከ ሦስተኛው ቀን” ወይም “በሦስተኛው ቀን” ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ በማቴዎስ 12፡40 ላይ ለሦስት ቀንና ለሦስት ሌሊት በመቃብር ውስጥ እንደሚሆን ተናገረ፡፡
በማቴዎስ 20 ላይ፤ በሦስተኛው ቀን እንደሚነሳ ኢየሱስ ተናገሯል – ከሦስተኛው ቀን በኋላ አላለም፡፡ በማቴዎስ 27፡63 ላይ አይሁድ ጲላጦስ ዘንድ ሄደው እንዲህ አሉት፡- “ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች… ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ…” ስለዚህ ሮማዊ ጠባቂ እንዲሰጣቸው ጠየቁት፡፡ “ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት መቃብሩን እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ” አሉት፡፡ ከሦስተኛው ቀን በኋላ አላሉም፡፡ ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደነበር ያውቃሉ፤ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ማለት እስከ ሦስተኛው ቀን ደረስ ማለት መሆኑን ያውቃሉ፡፡
አርብ ከአሥራ ሁለት ሰዓት በፊት እርሱን ለመቅበር ሦስት ሰዓታት ነበሯቸው፡፡ የቀብር ሥርኣቱ አንድ ሰዓት አይፈጅም፡፡ በአይሁድ ታልሙድና በባቢሎናውያን ኢየሩሳሌም ታልሙድ ውስጥ በተጠቀሰው መሠረት (ክቡራትና ክቡራን ታልሙድ የአይሁድ የሐቲት መጻሕፍት ናቸው) የአይሁድ የሰዓት አቆጣጠር – ማንኛውም ክፍል “ዖናን” – ማንኛውም የቀን ክፍል እንደ ሙሉ ቀን ነው የሚቆጠረው፡፡ አርብ ከአስራ ሁለት ሰዓት በፊት በአይሁድ አቆጣጠር ማንኛውም ደቂቃ አንድ ቀን እና አንድ ሌሊት ነው፡፡ ከአርብ ምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቅዳሜ 12 ሰዓት ሌላ ቀንና አንድ ሌላ ሌሊት ነው [ሕዝቡ ጭብጨባ አሰማ]፡፡
ክቡራትና ክቡራን፤ በአይሁድ አቆጣጠር – በኛ አይደለም – ከቅዳሜ በኋላ ያለ የትኛውም ቅጽበት ሌላ ቀንና ሌላ ሌሊት ነው፡፡ በአገሬ ውስጥ ተመሳሳይ ልማድ አለን፡፡ ልጄ በዴሴምበር 31 ላይ ከእኩ ሌሊት በፊት አንድ ደቂቃ ቀደም ብሎ ቢወለድ፤ በዚያ ዓመት ካሉት 365 ቀናትና 365 ሌሊቶች መካከል በየትኛውም ላይ እንደተወለደ በማመልከት ለመንግሥት በምከፍለው የገቢ ግብር ላይ ላስመዘግበው እችላለሁ፡፡ ፡፡ [ዓመቱ ሊያልቅ አንድ ደቂቃ ስለቀረው ዕድሜውን በአንድ ዓመት አላሳንስም ለማለት ነው፡፡]
የሮም ጠባቂ ወታደሮች ግዳጃቸውን በትክክል ካልተወጡ ወዲውኑ ነበር የሚገደሉት፡፡ አንዱ የሚገደሉበት መንገድ ልብሶቻቸው ተገፈው በሕይወት እያሉ በገዛ ልብሶቻቸው በተቀጣጠለ እሳት መቃጠል ነበር፡፡ እንግዲህ ማሕተሙ ተሰብሯል፡፡ ክቡራትና ክቡራን፤ ማሕተም ከተሰበረ ወታደሮች ማሕተሙን የሰበረውን ሰው እንዲፈልጉት ይደረጋል፤ ከተገኘ ተዘቅዝቆ እንዲሰቀል ይፈረድበታል፡፡
ድንጋዩ ተንከባሏል፤ ክቡራትና ክቡራን፤ ሚስተር ዲዳት ያንን በጥንቃቄ እንዲያረጋግጡ እጠይቃቸዋለሁ፡፡ በክርስቲያን አዲስ ኪዳን ውስጥ፤ በኦሪጂናል ግሪክ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያመለክተው (ቁርኣን በአረቢኛ እንደተጻፈው ሁሉ አዲስ ኪዳን ደግሞ በግሪክ ነው) ከአንድ ተኩል እስከ ሁለት ቶን የሚመዝነው ድንጋይ ከበሩ ላይ ብቻ ሳይሆን ልክ የሆነ ነገር ተሸክሞት የሄደ በሚመስል ሁኔታ መቃብሩ ካለበት ከቁልቁለት ወደ ላይ ተንከባሎ ነበር፡፡ እንግዲህ ቀስ ብለው ኮቴ ሳያሰሙ እየተራመዱ ድንጋዩን በማንሳት ኢየሱስ እንዲያመልጥ ሊረዱት ፈልገው ቢሆን ኖሮ ከአንድ ተኩል እስከ ሁለት ቶን የሚመዝን ዲንጋይ ዋሻው ካለበት ወደ ላይ ተሸክሞ መበመሄድ ለዚያ ሁሉ ልፋት መዳረግ ስለምን አስፈለጋቸው? እነዚያ ጠባቂዎች ያንን ላለመስማት ጥጥ ጆሮዎቻቸው ውስጥ በመወተፍ ከላይ ደግሞ የጆሮ ማሞቂያ መሸፈኛ በመደረብ ተኝተው መሆን አለበት፡፡
ከዚያም በዮሐንስ 20 ላይ እንደተጻፈው ማርያም ወደ መቃብሩ ሄዳለች፡፡ ሚስተር ዲዳት እንደተናገሩት ወደዚያ የሄደችው አስክሬኑን ለመቀባት ሲሆን “መቀባት” የሚለው ቃል “ማሸት” ማለት እንደሆነ ነግረውናል፡፡ እንግዲህ ልንገራችሁ፤ ያ እውነት ቢሆን – በእርግጥ እውነት አይደለም – ነገር ግን እውነት ቢሆንና ሙስሊሞች እንደርሱ የሚያደርጉ ቢሆን፤ ኢየሱስን ይገድለው ነበር፡፡ እኔ በስቅለት ውስጥ ባልፍ፣ እጆቼና እግሮቼ ተቸንክረው፣ ጀርባዬ እስከ አንጀቴ ድረስ ተከፍቶ፣ 100 ምናምን ፓውንድ በኔ ላይ ቢደረግ፣ አንድም ሰው እንዲያሸኝ አልፈልግም፡፡ “መቀባት” የሚለው ቃል “ቡራኬ መስጠት (consecrated)” ማለት ነው፡፡ ሚስተር ዲዳት በመጽሐፋቸው ውስጥ ግልጽ እንዳደረጉት ካህናትና ነገሥታት ለአገልግሎte ሲሾሙ ይቀባሉ፡፡ “አትንኪኝ” ሲል “ስለሚያመኝ – አትንኪኝ” ማለት እንደሆነ ሚስተር ዲዳት ተናግረዋል፡፡ መልካም፤ ሚስተር ዲዳት ተከታዩን ሐረግ እባክዎትን ያንብቡ፡፡ እንዲህ ይላል “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፡፡”
ለዚያ ነው ሊነኩት ያልተገባው፤ ምክንያቱን ሲገልፅ “ገና ወደ አባቴ አላረግሁም” ብሏል፡፡ ከዚያ እንደዚህ አለ፡- “ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ ‹ወደ አባቴ አርጋለሁ› ብሏል ብለሽ ንገሪያቸው፡፡” ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ ደግሞ “ልትነኩኝ ትችላላችሁ፡፡ እግሮቼን ንኩ” አለ፡፡ ለምንድነው እንደርሱ ያደረገው? ኦ! ክቡራትና ክቡራን፤ ይህ በጣም ውብ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እንደተነገረው፤ በድንኳኑ ውስጥ የአይሁድ ሊቀ ካህን መስዋዕቱን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይወስዳል፡፡ ሕዝቡም በውጪ ይጠብቃሉ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር መሥዋዕቱን ካልተቀበለ ካህኑ ተቀስፎ እንደሚሞት ያውቃሉና፡፡
ሊቀ ካህኑ ተመልሶ እንስኪመጣ በጉጉት ይጠብቁታል፡፡ እናም ሊቀ ካህኑ ተመልሶ ሲመጣ ሁሉም ሰው በደስታ ይጮሃል! ምክንያቱ “እግዚአብሔር መሥዋዕታችንን ተቀብሎታል!” ይላሉና፡፡ ኢየሱስ “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና… አትንኪኝ” አለ፡፡ ኢየሱስ በዚያ ጊዜና ሌሎች እንዲነኩት በፈቀደበት ጊዜ መካከል ወደ እግዚአብሔር አብ አርጎ ራሱን እንደ መሥዋዕት አሳየ፤ እናም ክቡራትና ክቡራን! ኢየሱስ ተመልሶ ባይመጣ ኖሮ፤ ሌሎች እንዲነኩት ባይፈቅድ ኖሮ፤ ያ ማለት መሥዋዕቱ ተቀባይነት አላገኘም ማለት ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ተመልሶ በመምጣት “ንኩኝ!” ስላለ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ ተቀባይነት አግኝቷል! [ሕዝቡ ታላቅ ጭብጨባና አሜንታ አሰማ]፡፡
የኢየሱስን መንፈሳዊ ቁሳዊ አካል በተመለከተ፤ ሚስተር ዲዳት ሆይ፤ የቅዱሳት መጻሕፍታችን የአዲስ ጀማሪ ጥናት ማድረግ የሚገባዎት ይመስለኛል [ሕዝቡ ጭብጨባ አሰማ]፡፡ እኔ የናንተን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደማጠናው ሁሉ እርሶም ማንበብ የሚገባዎት ይመስለኛል፡፡ 1ቆሮንቶስ 15፡44-51 ላይ የሚገኘውን ቃል ማንበብ የሚገባዎት ይመስለኛል፡፡ የከበረውና የማይጠፋው አካል ምንነት በዚያ ቦታ ተብራርቷል፡፡ መንፈሳዊ አካል ነው፤ ነገር ግን ቁሳዊ ባሕርይ አለው፡፡ በተዘጋ በር ውስጥ በማለፍ በመካከላቸው መታየት ይችል ነበር፡፡ ምግብ አያስፈልገውም ነገር ግን ምግብ በልቷል፡፡ እንደርሱ ባይሆን ኖሮ “አንተ ሙሉ በሙሉ መንፈስ ነህ” ይሉት ነበር፡፡ አይደለም፤ መጽሐፍ ቅዱስ የትንሣኤ፣ የከበረ፣ የማይጠፋ አካል ብሎ የሚጠራውን አካል ለብሷል፡፡ እኔ በዚያ ክፍል ውስጥ ብኖርና እንደተሰቀለ፣ እንደተቀበረና ሌሎች ነገሮች ሁሉ እንደተከናወኑ ባውቅ፤ ከዚያም እንደ ድንገት በሩ ተዘግቶ ሳለ በስብስቡ መካከል ቢከሰት ትንሽ ፍርሃት ቢጤ የሚሰማኝ ይመስለኛል፡፡ ክቡራትና ክቡራን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ተነስቷል! አመሰግናለሁ፡፡ [ሕዝቡ አጨበጨበ፣ ጆሽ ወደ ቦታቸው ተመልሰው ተቀመጡ፡፡]