ሃምሳ ሺህ ስህተቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ? የአሕመድ ዲዳት ቅጥፈት
ወቅቱ የይሖዋ ምስክሮች “የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም” የተሰኘውን የተጭበረበረ ትርጉማቸውን ለማስተዋወቅ የሚሯሯጡበት ነበር፡፡ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ይጠቀሙ የነበሩት የኪንግ ጀምስን ትርጉም ስለነበር የይሖዋ ምስክሮች የራሳቸውን ትርጉም እንደ አማራጭ በማቅረብ የኪንግ ጀምስን ትርጉም ተቀባይነት ለማሳጣት ፈለጉ፡፡ ስለዚህ በመጽሔቶቻቸው ላይ የኪንግ ጀምስ ትርጉም 50,000 ስህተቶች አሉበት በማለት መጻፍ ጀመሩ፡፡ ይህ ማለት በእያንዳንዱ የኪንግ ጀምስ ትርጉም ጥቅስ ውስጥ ከአንድ በላይ ስህተት ማለት ነው! የይሖዋ ምስክሮች ይህንን ውሸት የፈጠሩት የተጭበረበረውን ትርጉማቸውን ወደ ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚያሰርጉበትን በር ለመክፈት እንጂ እውነት የኪንግ ጀምስ ትርጉም ይህን ያህል የጎላ ችግር ኖሮበት አልነበረም፡፡ ሚስተር ዲዳት ይህንን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ከዚህ የሐሰተኞች መጽሔት ላይ በመቅዳት የመጽሐፋቸው ማዳመቅያ አደረጉት፡፡ ከዝያን ጊዜ ጀምሮ እነሆ ለ40 ዓመታት ያህል ሙስሊም ወገኖቻችን ተመሳሳይ የሐሰት ነጋሪት እየደለቁ ይገኛሉ!
የኪንግ ጀምስ ትርጉም እንደ ማንኛውም ትርጉም የራሱ የሆኑ ውሱንነቶች አሉበት፡፡ ምክንያቱም ፍፁም የሆነ ትርጉም የለምና፡፡ የቁርአን ትርጉሞችም እንደዝያው ናቸው፡፡ ቁርአን ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ሲታተም የምዕራፍ 26 ሱረቱ ሹዓራእ 33ኛ አንቀፅ ተረስቶ ነበር፡፡ እጅግ ብዙ የፊደል ግድፈቶችና የቃላት ስህተቶችም ስለነበሩበት የማስተካከያ አባሪ አብሮ ታትሞ ነበር፡፡ የቆዩ የእንግሊዘኛ ትርጉሞችንም ስንመለከት ተመሳሳይ ችግሮች አሉባቸው፡፡
የኪንግ ጀምስ ትርጉም ችግሮች ስላሉበት መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት አለበት ብሎ መናገር የአማርኛው ትርጉም ስህተቶች ስላሉበት ቁርአን ስህተት አለበት ብሎ እንደመናገር ነው፡፡ ይህንን ብንል “ቁርአን መጀመርያ የተጻፈው በአረብኛ በመሆኑ የአማርኛው ትርጉም ስህተት ስላለበት ቁርአን ስህተት አለበት ብላችሁ ልትናገሩ አትችሉም” በማለት ሙስሊም ወገኖቻችን እንደሚያርሙን ግልፅ ነው፡፡ ቁርአን በአረብኛ እንደሆነ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም፡ ብሉይ ኪዳን በእብራይስጥ እና አዲስ ኪዳን ደግሞ በግሪክ ነው፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን ስለ ስህተቶች ማውራት የሚፈልጉ ከሆነ ስለ ኦሪጅናል ቋንቋዎቹ መነጋገር እንችላለን፡፡ ነገር ግን ትርጉሞችን በማየት መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት አለበት በማለት የሚናገሩ ከሆነ አለማወቃቸውንና በአባይ ሚዛን የሚመዝኑ ሰዎች መሆናቸውን ከማረጋገጥ በዘለለ ሙግታቸው ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡