አይኤስ እስላማዊ ነው

Œአይኤስ እስላማዊ ነውን?

ይህ መልስ የሚሻ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ በአጭር ቃል አይኤስ እስላማዊ ነው፡፡ አባላቱ በእስልምና ያደጉና ብዙዎቹ እስልምናን በሚገባ ያጠኑ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ አቡበከር አል-ባግዳዲ (ኢብራሂም አወድ ኢብራሂም አል በድሪ) የተሰኘው መሪያቸው በእስላማዊ ጥናቶች ከባግዳድ ዩኒቨርሲቲ ፒ.ኤች.ዲ. የተቀበለ ነው፡፡[1] የኢትዮጵያውያኑን ጭፍጨፋ በሚያሳየው ቪድዮ ውስጥ ሲናገር የሚታየው የሰዑዲ አረብያ ዜግነት እንዳለው የሚነገረው አነስ አል-ነሽዋን (የሚስጥር ሥሙ አቡ ማሊክ አል-ተሚሚ) ደግሞ በሸሪኣ ህግ የማስተርስ ድግሪ ያለው ነው፡፡[2] እነዚህ ሰዎች እስልምናን የማያውቁ፣ በስሜት የሚነዱ ስራ አጦች አይደሉም፡፡ እነዚህ እስልምናን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ለእምነታቸው ሲሉ የተሻለውን ኑሯቸውን በመተው ጦርነት ውስጥ የገቡ ሙስሊም ሊቃውንት ናቸው፡፡ ያልተማሩና በአንድ ሰው ስብከት በቀላሉ የሚወሰዱ መሃይማንም አይደሉም፡፡ ብዙዎቹ በምዕራብ አገራት ውስጥ ኑሯቸውን የመሰረቱ፣ ፊደል የቆጠሩና ጥሩ ገቢ የነበራቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል የአይኤስ ዋና አራጅ የሆነው ሙሐመድ ኤምዋዚ[3]  የኮምፒውተር ሳይንስ ባለሙያና የእንግሊዝ ዜግነት ያለው ሰው ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሰዎች እስልምናን የማያውቁ፣ ያልተማሩ ተራ ወሮበሎች አድርጎ መፈረጅ እውነታን የሚፃረር ነው፡፡

አይኤስ የሚጠቀሟቸው ቃላት (Vocabulary) እስላማዊ ናቸው፡፡ ደቢቅ የሚለው የመጽሔታቸው ሥያሜ በሦርያ ውስጥ ከሚገኝ የቦታ ሥም የተወሰደ ሲሆን በእስላማዊ ትንቢቶች መሠረት በሙስሊሞችና በክርስቲያኖች መካከል የመጨረሻው ጦርነት ይደረግበታል ተብሎ የተነገረ ቦታ ነው፡፡[4] አል-ፉርቃን የሚለው የቪድዮ ፕሮዳክሽን ሥያሜ “መመርያ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን የቁርኣን ሌላኛው መጠርያ ነው፡፡ ቃሉም በቁርኣን ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ተደጋግሞ ተጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያውያን ስደተኞቹን ጨምሮ የእርድ ቪድዮዎችን እየቀረፀ የሚያሰራጨው ይኸው የአይኤስ የሚድያ ክንፍ ነው፡፡

የአይኤስ ሥያሜ፣ የአባላቱ መጠርያዎች፣ ቅፅል ሥሞቻቸው፣ የዘመቻ ሥያሜዎቻቸው፣ ወዘተ. ሁሉ እስላማዊ ናቸው፡፡ እስላማዊ ያልሆነ ንግግር አይጠቀሙም፡፡

የአይኤስ ጥቁሩ ባንዲራ የጂሃድ ባንዲራ ነው፡፡ በላዩ ላይም በአረብኛ ተጽፎ የምናየው ሌላ ነገር ሳይሆን ሸሃዳ (የእስልምና የእምነት አቋም) ነው፡፡ ላ ኢላ ሀኢለላ መሐመደን ረሱልአላህ (ከአላህ በስተቀር አምላክ የለም ሙሐመድም መልእክተኛው ናቸው) የሚል ነው፡፡ ይህ የአንድ ሙስሊም የመጀመርያና የመጨረሻ ቃሉ ነው፡፡ በእስላማዊ ትንቢቶች መሠረት ይህንን ጥቁር ባንዲራ የያዘ የጂሃድ ቡድን በመጨረሻው ዘመን ይነሳል፡፡ ሙስሊሞችም ሁሉ ይህንን ቡድን መቀላቀል ይኖርባቸዋል፡፡

በአይ ኤስ ባንዲራ ላይ የሚገኘው ጽሑፍ  ሸሃዳ (የእስልምና የእምነት አቋም) ነው፡፡ ላ ኢላ ሀኢለላ መሐመደን ረሱልአላህ (ከአላህ በስተቀር አምላክ የለም ሙሐመድም መልእክተኛው ናቸው) ይላል፡፡

አይኤስ አለባበሳቸው፣ አመጋገባቸው፣ የጋብቻ ሁኔታቸው፣ ጢም አቆራረጣቸው፣ ሙስሊም ካልሆኑት ሰዎች ጋር ያላቸው መስተጋብር፣ የማህበረሰብ አደረጃጀታቸው፣ ባጠቃላይ የኑሮ ዘይቤያቸው ሁሉ ፍፁም እስላማዊ ነው፡፡ ከእስልምና ጋር የሚጣረስ፣ በሙሐመድ ሱና (ምሳሌነት) ያልተረጋገጠ፣ በቁርኣንና በሐዲሳት ያልፀደቀ ምንም ነገር የላቸውም፡፡

ለሚያደርጉት ለእያንዳንዱ ነገር ቁርኣንና ሐዲሳትን ጨምሮ እስላማዊ ምንጮችን ይጠቅሳሉ፡፡ የቁርኣንን አተረጓጎም በተመለከተ የሱኒ ነባር ሐታቶችን (Classical Sunni Commentators) ይጠቀማሉ፡፡ ምናልባት እስላማዊ ቃላትን መጠቀማቸውና እስላማዊ የኑሮ ዘይቤዎችን መከተላቸው በራሱ ትክክለኛ ሙስሊሞች ሊያደርጋቸው አይችልም የሚል ሐሳብ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ አባባል የተወሰነ እውነታነት አለው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ድርጊቶች በእስላማዊ ቅዱሳት መጻሕፍት መደገፋቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ትክክለኛ ሙስሊሞች ናቸው ብሎ መናገር አዳጋች ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች የሚፈፅሟቸው ነገሮች ሁሉ ፍፁም እስላማዊ መሆናቸውን ቁርኣንና ሌሎች እስላማዊ ምንጮችን ያነበበ ሰው ሁሉ የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡ ከእስልምና የወጣ ምንም ነገር አላደረጉም፡፡ ነገር ግን ችግሩ ብዙ ሰዎች ስለ እስልምና ያላቸው መረጃ በመገናኛ ብዙኃን በሚነገሩ ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን በተከተሉ ንግግሮችና ሙስሊም ዐቃቤ እምነታውያን በሚናገሯቸው የተቀመሙ ንግግሮች ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ብዙ ድምፆች ውዥንብሮችን በሚፈጥሩበት ዘመን ዋናዎቹን ምንጮችና የእምነቱን መስራች የሙሐመድን ሕይወት ካላጠናን በስተቀር የእስልምናን ትክክለኛ ገፅታ ማወቅ ቀላል አይሆንም፡፡ የሚፈፀሙ የሽብር ጥቃቶችንም የእምነቱን ሽፋን በመጠቀም የተወሰኑ የግል ጥቅም አሳዳጆች ወይንም እምነቱን በተሳሳተ መንገድ የተረዱ ሰዎች እንደሚፈፅሙት የውንብድና ተግባር ልንቆጥር እንችላለን፡፡ ይብዛም ይነስም እንዲህ ዓይነት ሰዎች በሁሉም እምነቶች ውስጥ እንደሚገኙ ይታመናልና፡፡

ዛሬ አንድ ክርስቲያን ተነስቶ በእምነቱ ሥም የሽብር ተግባር ቢፈፅም ድርጊቱ ክርስቲያናዊ አለመሆኑን መጽሐፍ ቅዱስን በመጥቀስ ማስረዳት እንችላለን፡፡ ለድርጊቱ ማፅደቅያ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅሶች ቢጠቅስ ከአውድ ውጪ እንደጠቀሰና በተሳሳተ መንገድ እንደተረጎመ በማስረዳት ልናርመው እንችላለን፡፡ የእምነታችን ጀማሪና ፈጻሚ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ የሚል የማያወላዳ ትዕዛዝ ሰጥቶናልና፡-

ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ። ማቴዎስ 5፡43-48

አንድ ክርስቲያን ከዚህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ በማፈንገጥ በስመ እግዚአብሔር የሽብር ድርጊቶችን ቢፈፅም በክርስቲያኖች ዘንድ በፅኑ ይወገዛል፡፡ ክርስቲያን ተብሎም ሊጠራ አይችልም፡፡ በእስልምና ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እውነተኛና ትክክለኛ የሙሐመድ እስልምና አይኤስን በመሳሰሉት የጥላቻ ቡድኖች እየተተገበረ የሚገኘው እንጂ በተከሸኑ ቃላት ተሽሞንሙኖ በሚድያዎች፣ በፖለቲከኞችና በሙስሊም ዐቃቤ እምነታውያን የሚሰበከው ክርስትና የተነሳ እስልምና አይደለም፡፡ ቁርኣንና የሙሐመድን ግለ ታሪክ ቀረብ ብለን ብንመለከት ነቢዩ ሙሐመድ በዳዕሾች ተሠግዎ በዘመናችን እንደተገለጡ ማስተዋል እንችላለን፡፡ በአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ የእስልምና ታሪክ ፕሮፌሰር የነበሩትና እስልምናን በመተው ክርስትናን የተቀበሉት ማርክ ገብርኤል (በቀድሞ ሥማቸው ሙስጠፋ) የቁርኣንን አስተምህሮና የእስልምናን ታሪክ በተመለከተ የሚከተለውን ይላሉ፡-

በቁርኣን ውስጥ የተገለጠው አምላክ፣ አላህ አፍቃሪ አባት አይደለም፡፡ ሰዎችን በተሳሳተ መንገድ መምራት ይፈልጋል (ሱራ 6፡39፣ 126)፡፡ በእርሱ ወደ ተሳሳተ መንገድ የተመሩትን አይረዳቸውም (ሱራ 30፡29)፡፡ ገሃነምንም ለመሙላት ይጠቀምባቸዋል (ሱራ 32፡13)፡፡ እስልምና በሴቶች ላይ፣ ሙስሊም ባልሆኑት ላይ፣ በክርስቲያኖች ላይ እና በተለይም ደግሞ በአይሁዶች ላይ አድሎን በማድረግ የተሞላ ነው፡፡ ጥላቻ የኃይማኖቱ አካል ነው፡፡ የእኔ ልዩ የጥናት መስክ የሆነው የእስልምና ታሪክ የደም ወንዝ በመባል ብቻ ነው ሊገለፅ የሚችለው፡፡[5]

ሁለቱ የማደናገርያ ጥቅሶች

የአክራሪ እስልምና ትክክለኛ ገፅታ ገሃድ እየወጣ ባለበት በዚህ ወቅት ብዙ ወገኖች እነዚህ ቡድኖች እስላማዊ አለመሆናቸውንና እስልምናም የሰላም ሃይማኖት መሆኑን እየሰበኩ ይገኛሉ፡፡ እስልምና የሰላም ሃይማኖት መሆኑንም ለማሳየት ከቁርኣን ውስጥ የተወሰኑ ጥቅሶችን ከታሪካዊና ምንባባዊ አውዳቸው ውጪ በመጥቀስ ሊያሳምኑን ይሞክራሉ፡፡ አሳዛኙ ነገር ብዙ ሰዎች በነዚህ ከንቱ ስብከቶች ተታልለው የአክራሪ እስልምናን ፀረ ሰላም መሆን መጠራጠራቸው ነው፡፡ የእስልምናን ሰላማዊነት ለማስረዳት በተደጋጋሚ የሚጠቀሱት ሁለት ጥቅሶች ሲሆኑ እንደሚከተለው እንመለከታቸዋለን፡፡

በሃይማኖት ማስገደድ የለም፡፡ ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ፡፡ (ሱራ 2፡256)

ይህ ጥቅስ ቁርኣንን የማያነበውንና የእስልምናን ታሪክና አስተምህሮ በወጉ የማያውቀውን ህዝብ ለማደናገር በእጅጉ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የቁርኣን ሐታቾች እንደሚናገሩት ይህ ጥቅስ ጊዜው አልፎበታል፡፡ እስልምና ናሲክ የተሰኘ አስተምህሮ አለው፡፡ ናሲክ መሻር የሚል ትርጉም ያለው የአረብኛ ቃል ሲሆን በዚህ አስተምህሮ መሠረት ሁለት እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ የቁርኣን ጥቅሶች ቢኖሩ የኋለኛው የፊተኛውን ይሽረዋል፡፡ ይህንን በተመለከተ ኢብን ከሢር የተሰኘ ትልቅ ተቀባይነት ያለው የሱኒ ሐታች የጥቅሱን ትክክለኛ ትርጉም፤ ማለትም ሰዎች እምነታቸውን እንዲቀይሩ ማስገደድ አስፈላጊ አለመሆኑን እንደሚናገር ካብራራ በኋላ እንዲህ ይላል፡- “… ነገር ግን ይህ ጥቅስ በውጊያ ጥቅሶች ተሽሯል ስለዚህ ሁሉም የዓለም ህዝቦች ወደ እስልምና እንዲመጡ ጥሪ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ማናቸውም ሰዎች ያንን ለማድረግ ፍቃደኛ የማይሆኑ ከሆነ ወይም ጂዝያን ለመክፈል እምቢ የሚሉ ከሆነ እስኪገደሉ ድረስ ውጊያ ሊደረግባቸው ይገባል…”[6]

አይኤስ ክርስቲያን ኢትዮጵያውኑ የተገደሉበትን ምክንያት ሲገልፅ ጂዝያን ለመክፈል ፍቃደኞች ባለመሆናቸው ይህ ፍርድ እንደተላለፈባቸው ተናግሯል፡፡ ሌሎች ብዙ ሙስሊም ሐታቾች ይህ ጥቅስ በኋለኞቹ መገለጦች መሻሩን ይገልፃሉ፡፡ ስለዚህ ጥቅሱ ካፊሮችን ከማደናገር የዘለለ ጥቅም የለውም፡፡

የእስልምና ሰላማዊነት ለማሳየት የሚጠቀሰው ሌላው ጥቅስ ሱራ 5፡32 ላይ የሚገኘው፡- “ያለ ነፍስ (መግደል) ወይም በምድር ላይ ያለማጥፋት (ካልሆነ በስተቀር) ነፍስን የገደለ ሰው ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው፤ ሕያው ያደረጋትም ሰው ሰዎቹን ሁሉ ሕያው እንዳደረገ ነው” የሚለው ነው፡፡ ነገር ግን ሙስሊም ሊቃውንት ይህንን ጥቅስ ከአውድ ውጪ ነው የሚጠቅሱት፡፡ ሙሉ አውዱ እንዲህ ይላል፡- በዚህ ምክንያት በእስራኤል ልጆች ላይ እነሆ ያለ ነፍስ (መግደል) ወይም በምድር ላይ ያለማጥፋት (ካልሆነ በስተቀር) ነፍስን የገደለ ሰው ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው፤ ሕያው ያደረጋትም ሰው ሰዎቹን ሁሉ ሕያው እንዳደረገ ነው ማለትን ጻፍን፡፡ መልክተኞቻችንም በግልጽ ተዓምራት በእርግጥ መጡዋቸው፡፡ ከዚያም ከዚህ በኋላ ከእነሱ ብዙዎቹ በምድር ላይ ወሰንን አላፊዎች ናቸው፡፡

የቁርኣን ጸሐፊ ይህንን ሐሳብ የቀዳው ከአይሁድ መጻሕፍት ላይ ነው፡፡ ጥቅሱ የሚናገረው ይህ ትዕዛዝ የተሰጠው ለእስራኤላውያን መሆኑን ነው፡፡ ለሙስሊሞች ደግሞ ምን ዓይነት ትዕዛዝ እንደተሰጠ ቀጣዩ አንቀፅ ይናገራል፡- የእነዚያ አላህንና መልክተኛውን የሚዋጉ በምድርም ላይ ለማጥፋት የሚተጉ ሰዎች ቅጣት መገደል ወይም መሰቀል ወይም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በማፈራረቅ መቆረጥ ወይም ከአገር መባረር ነው፡፡ ይህ በነሱ በቅርቢቱ ዓለም ውርደት ነው፡፡ በመጨረሻይቱም ለእነርሱ ከባድ ቅጣት አላቸው፡፡” ሱራ 5፡35

ቀደም ሲል የተጠቀሰው በጎ ትዕዛዝ የተሰጠው ለእስራኤላውያን ሲሆን በማስከተል የተቀመጠው የጭካኔ ትዕዛዝ ደግሞ ለሙስሊሞች የተሰጠ መሆኑን እናያለን፡፡ አላህንና መልክተኛውን መዋጋት ማለት በእስላማዊ አተረጓጎም መሠረት ማንኛውንም ቁርኣንንና እስላማዊ ህግጋትን መፃረር እንዲሁም የሙሐመድን ነቢይነት አለመቀበል ማለት ነው፡፡ በምድር ላይ ማጥፋት ደግሞ ለሙስሊም ማህበረሰብ እንቅፋት የሚሆን ማንኛውንም ነገር ማድረግን ያመለክታል፡፡ ይህም ወንጌልን መስበክን ያጠቃልላል፡፡ ስለዚህ “ሂዱና ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” የሚለውን የጌታን ትዕዛዝ በሸሪኣ ህግ በሚተዳደር የሙስሊም ማሕበረሰብ መካከል የምንተገብር ከሆነ በሸሪኣ ህግ መሠረት ቅጣቱ በጥቅሱ ውስጥ የተዘረዘረው ነው፡፡

“ጅብ እስኪይዝ ያነክሳል” እንደሚለው የአገራችን ብሒል አክራሪ እስልምናም እነዚህን የመሳሰሉ ጥቅሶችን በመጠቃቀስ ምቹ ጊዜ እስኪመጣለት ድረስ ይሸነግላል፡፡ የበላይ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ግን ትክክለኛ ገፅታውን ያሳያል፡፡ በመታረድና ለእርሱ በመገዛት መካከል ያስመርጣል፡፡ ሦስተኛ አማራጭ የለም፡፡

 


ማጣቀሻዎች

[1] http://www.wikipedia.net/wiki/Abu_Bakar_al-Bagdadi (Accessed on 5/18/2015)

[2] http://www.geopolintelligence.com/isis-video-shows-militants-killing-groups-of-ethiopian-christians (Accessed on 5/18/2015)

[3] አሊ አዶሩስ የተሰኘው የቅርብ ጓደኛው ለሽብር ተግባር ሲንቀሳቀስ ተይዞ ኢትዮጵያ ውስጥ በእስር ላይ ይገኛል http://www.dailymail.co.uk/news/article-2983850/The-Londoner-went-Tanzanian-safari-Jihadi-John-currently-jail-Ethiopia-terrorism-offences.html (Accessed on 5/19/2015)

[4] Sahih Muslim, 41:6924

[5] Mark Gabriel: Islama and Terrorism, 2002, p. 5

[6] Tafsir of Ibn Kathir, Al-Firdous Ltd., London, 1999: First Edition, Part 3, pp. 37-38

 

አይኤስ እስላማዊ ነውን? ዋናው ማውጫ