የኢየሱስ ማንነት ጉዳይ (ክፍል 2)

ምዕራፍ አንድ

የኢየሱስ ማንነት ጉዳይ (ክፍል 2)

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡

 

21. ሮሜ 8፡17 ላይ “ልጆች ብንሆንወራሾች ደሞ ነን፣ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በእርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን፡፡” ይላል፡፡ ክርስቶስ እውን አምላክ ከሆነ፣ እንዲሁም የሥላሴ አንዱ አካል ከሆነ ወራሽ ነው ወይንስ አስወራሽ? ነገ የእግዚአብሔርን ገነት ሊወርስ ነው ማለት ነውን? እንዲህም ሆነ አምላክ ትሉታላችሁን?

መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑት ቅዱሳን ስለሚወርሱት ነገር ሲናገር በእስልምና እምነት ውስጥ ከተጠቀሰው የገነት ዓይነትም ሆነ አንዳንድ ክርስቲያኖች በተለምዶ ከሚያስቡት በእጅጉ የተለየ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ኢየሱስ የአባቱን ግዛት (Dominion) ነው የሚወርሰው፡፡ በስሙ ያመኑት ቅዱሳንም ይህንን ግዛት ከእርሱ ጋር እንደሚካፈሉና እንደሚነግሡ መጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ ይናገራል (2ጢሞቴዎስ 2፡12፣ ራዕይ 3፡21፣ ራዕይ 22፡5፣ ኤፌሶን 2፡5-7)፡፡

በነዚህ ጥቅሶች መሠረት ቅዱሳን ከክርስቶስ ጋር በመሆን የአባቱን ግዛት ይወርሳሉ፡፡ ወራሽ መሆን ኢየሱስን አምላክ እንዳይሆን የሚያደርገው ከሆነ በቁርኣን መሠረት የአሕመዲን አምላክ አላህም ወራሽ በመሆኑ አምላክ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡-

“ከከተማም ኑሮዋን (ምቾቷን) የካደችን (ከተማ) ያጠፋናት ብዙ ናት፡፡ እነዚህም ከእነሱ በኋላ ጥቂት ጊዜ እንጅ ያልተኖረባቸው ሲኾኑ መኖሪያዎቻቸው ናቸው፡፡ እኛም (ከእነርሱ) ወራሾች ነበርን” (ሱራ 28፡58)፡፡

“ዘከሪያንም «ጌታዬ ሆይ! ብቻዬን አትተወኝ፡፡ አንተም ከወራሾች ሁሉ በላጭ ነህ ሲል» ጌታውን በተጣራ ጊዜ (አስታውስ)” (ሱራ 21፡89)፡፡[1]

“እኛ ምድርን በእርሷም ላይ ያለውን ሁሉ እኛ እንወርሳለን፡፡ ወደኛም ይመለሳሉ” (ሱራ 19፡40)፡፡

ጠያቂው ወራሽነት ከአምላክነት ደረጃ ዝቅ የሚያደርግ እንደሆነ የሚያምኑ ከሆነ አምላካቸው እውነተኛ አምላክ ላይሆን ነው፡፡

22. እንደ ሉቃስ ወንጌል 23፡43 አገላለጽ መስቀል ላይ ሆኖ አብሮት ከተሰቀለው ለአንዱ “በእውነት እልሃለሁዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው” ይላል፡፡ ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ አምላክ ከሆነ እንዴት አምላክ ገነት ይገባል? አምላክ ገነት ይገባል ወይንስ አማኞችን ያስገባል?”

በጠያቂው አባባል ኢየሱስ አምላክ ለመሆን ገነት አካባቢ ድርሽ ማለት የለበትም፡፡ ገነት ውስጥ መታየት በቅፅበት ከአምላክነት መስፈርት ውድቅ ያደርጋል፡፡ ይህ መስፈርት ለራሳቸው አምላክ ይሰራ ይሆን?

ጌታችን ኢየሱስ በሠልስቱ ቀናት ውስጥ ወደ ገነት ብቻ ሳይሆን ወደ ሲዖልም በመሄድ ታስረው ለነበሩት ነፍሳት የምስራቹን እንደሰበከ ተጽፏል (2ጴጥሮስ 2፡4-5)፡፡ ኡስታዙ ከተናገሩት በተፃራሪ ጌታችን ኢየሱስ ሰዎችን ገነት የማስገባት ሥልጣን እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ በበርካታ ቦታዎች ላይ ይናገራል፡- (ማቴዎስ 24፡31-40፣ ዮሐንስ 14፡1-3፣ ራዕይ 2፡7፣ ራዕይ 22፡12)፡፡

23. ዕብራውያን 1፡13 ላይ“እግዚአብሔር፤ “ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” ያለው ከቶ ለማን ነው?” ይላል፡፡ ይህ ጥቅስ እንደሚነግረን “በቀኜ ተቀመጥ ” የተባለው ኢየሱስ ብቻ ከሆነ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመለስ ያሻል ፡-

ሀ. ኢየሱስም አምላክ ነው እየተባለ እንዴት በጊዜ ተወስኖ ከእግዚአብሔር ቀኝ እንዲቀመጥ ይፈቀድለታል? ከአምላክ ማን በልጦ ይህን ያዘዋል?

ክርስቶስ ፍጥረትን የመዋጀት ተልዕኮውን ከፈፀመ በኋላ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ይህም ትቶት ወደመጣው ክብሩ መመለሱን የሚያመለክት ተምሳሌታዊ ንግግር እንጂ እግዚአብሔር መንፈስ በመሆኑ በዚህ መልኩ ሊገለፅ የሚችል ግራና ቀኝ አለው ማለት አይደለም፡፡ ቀኝ በመጽሐፍ ቅዱስ የኃይልት፣ የከፍታ፣ የፅድቅ፣ የመልካምነት፣ የአንድነት፣ ወዘተ. ተምሳሌት ነው (ዘጸአት 15፡6፣ 12፣ መዝሙር 20:6፣ 98፡1፣ መክብብ 10፡2፣ ኢሳይያስ 48፡13፣ 62፡9፣ ማቴዎስ 26:4, ማርቆስ 14፡62፣ ሉቃስ 22፡69፣ ገላትያ 2፡9፣ ዕብራውያን 1፡3)፡፡

ለ. ጠላቶቹን የእግሩ መረገጫ ካደረገ በኋላ ኢየሱስን እግዚአብሔር ከቀኙ ያነሳዋል ማለት ነው፡፡ ለምን? ቢሉ “የእግር መረገጫ እስከማደርግልህ” ነው ያለውና፡፡ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ቀኝ ከተነሳ በኋላ ምን ይሆናል?

“የእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ” ስለተባለ ከዚያ በኋላ ይነሳል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል እስኪ የሚከተሉትን ጥቅሶች ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፡-

“እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና” (ዘፍጥረት 28፡15)፡፡ ከዚያ በኋላ ይተወዋል ማለት ነው?

“የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም” (1ሳሙኤል 6፡23)፡፡ ከዚያ በኋላ መውለድ ትችላለች ማለት ነው?

“እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ” (ማቴዎስ 5፡18)፡፡ ከተፈፀመ በኋላ ያልፋል ማለት ነው?

“እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴዎስ 28፡20)፡፡ ከዚያ በኋላ ይለያቸዋል ማለት ነው?

“እግዚአብሔርም ለአብርሃም የማለለት የተስፋው ዘመን ሲቀርብ፥ ዮሴፍን የማያውቀው ሌላ ንጉሥ በግብፅ ላይ እስኪነሣ ድረስ፥ ሕዝቡ እየተጨመሩ በግብፅ በዙ” (የሐዋርያት ሥራ 7፡17-18)፡፡ ከዚያ በኋላ መብዛት አቆሙ ማለት ነው?

እንዲህ ዓይነት አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቁርኣንም ውስጥ ይገኛል፤ ለምሳሌ፡-

“አላህም ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ዒሳ ሆይ! እኔ ወሳጂህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ፡፡ ከነዚያም ከካዱት ሰዎች አጥሪህ ነኝ እነዚያንም የተከተሉህን እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ ከነዚያ ከካዱት በላይ አድራጊ ነኝ፡፡ ከዚያም መመለሻችሁ ወደእኔ ነው፡፡” (ሱራ 3፡55)፡፡ ከዚያ በኋላ የበታቾች ይሆናሉ ማለት ነው?

“እርግማኔም እስከ ፍርዱ ቀን ድረስ ባንተ ላይ ይኹን” (ሱራ 38፡37)፡፡ ከፍርዱ ቀን በኋላ የአላህ እርግማን ከሰይጣን ላይ ይነሳል ማለት ነው?

ስለዚህ “እንዲህ እስኪሆን ድረስ” የሚል ሐረግ ስለገባ ብቻ ድርጊቱ የሆነ ጊዜ ላይ ያቆማል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የተባለው ነገር እስኪፈፀም ድረስ ድርጊቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው የሚገልፅ የተለመደ አባባል ነው፡፡ ስለ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጥም በዚሁ መልኩ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ሐ. ኢየሱስ ከመላእክት ቢለይም ያው ከእግዚአብሔር እገዛን የሚሻ አይደለምን?

ኢየሱስ የመላእክት ጌታ መሆኑ ጠያቂው በጠቀሱት በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ተነግሯል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ ሲሆን መላእክት ግን የእርሱ ተፈጣሪዎችና አገልጋዮች ናቸው፡፡ ይህንን ነጥብ ከቀጣዩ ጥያቄ በኋላ ያሰፈርነው የዕብራውያን 1 ሙሉ አውድ የበለጠ ግልፅ ያደርገዋል፡፡

መ. አምላክ እግዚአብሔር ነው ወይንስ በጊዜ ገደብ ከ “ቀኝ” እንዲቀመጥ የተፈቀደለት ኢየሱስ?

የኢየሱስ በቀኝ መቀመጥ በጊዜ የተገደበ ስለመሆኑ ጠያቂው ያቀረቡት ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በቁርኣን መሠረት ውድቅ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ይህ ጥያቄ ከነጠላ አሃዳዊነት አስተሳሰብ የመነጨ ነው፡፡ አብ አምላክ ከሆነ ኢየሱስ አምላክ ሊሆን አይችልም የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን አብም ኢየሱስም የአንዱ ግፃዌ መለኮት አካላት በመሆናቸው አብ አምላክ መሆኑ ኢየሱስን አምላክ እንዳይሆን አያደርገውም፡፡ ለዚህ ነው የዕብራውያን ጸሐፊ በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ኢየሱስ አምላክ፣ ጌታ፣ የሁሉ ፈጣሪና ዘለዓለማዊ መሆኑን እግዚአብሔር አብ እንደመሰከረ የጻፈው፡፡ አሕመዲን አንዷን ጥቅስ ብቻ ነጥለው ከሚጠቅሱ ሙሉውን ቢጠቅሱ ኖሮ እግዚአብሔር አብ ስለልጁ ጌትነት፣ አምላክነት እና ፈጣሪነት የመሰከረውን ማየት በቻሉ ነበር፡፡ እሳቸው ቆርጠው የጣሉትን ታማኝነት ማጉደላቸውን የሚያጋልጠውን የምዕራፉን ቀዳማይ ክፍል ጨምሮ ሙሉውን ምዕራፍ እንደሚከተለው እንጠቅሳለን፡-

ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል፡፡ ከመላእክትስ፦ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም፦ እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ፦ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል፡፡ ስለ መላእክትም፦ መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ ይላል፤ ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው፡፡ ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ ይላል፡፡ ደግሞ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል፡፡ ነገር ግን ከመላእክት፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን? (ዕብራውያን 1)፡፡

የተከበሩት ጠያቂያችን የኢየሱስን አምላክነት፣ ፈጣሪነት፣ የመላእክት ጌታ መሆኑን እና ዘለዓለማዊነቱን እንዲህ ባለ ሁኔታ ከሚናገር ክፍል ውስጥ አምላክነቱን የሚቃወሙበትን ሐሳብ መፈለጋቸው መታወር እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?

24. ኢየሱስ አምላክ ነው ወይንስ የአምላክ አምሳል? ቆላስይስ 1፡15 እና 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡4 ኢየሱስ የእግዚአብሔር አምሳል መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እንዲሁም በዘፍጥረት 1፡26 ላይ ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩ ተገልጿል፡፡ ታዲያ ኢየሱስ እንደማንኛውም ሰው የእግዚአብሔር አምሳል ከሆነ ልዩነቱ ምን ላይ ነው? ያው መቼም አምላክ አምላክ ነው፡፡ ክርስትና እንደሚለው ደግሞ ኢየሱስ አምሳሉ ነው፡፡ ኢየሱስ “አምላክም”፣ “የአምላክ አምሳልም” ሊሆን ይችላል? እንዴት ራሱና አምሳሉ አንድ ይሆናሉ?

አሕመዲን በጠቀሷቸው ሁለቱ ጥቅሶች ውስጥ ኢየሱስ የእግዚአብሔር አምሳል መሆኑን ለመግለፅ ጥቅም ላይ የዋለው ቃል “ኤይኮን” የሚል ሲሆን የአንድን ነገር ምስል ወይም ቅርፅ ያመለክታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር አብን ያየ ማንም እንደሌለ ይናገራል (ዮሐንስ 1፡1-3፣ 14፣ 18፣ ሮሜ 1፡20)፡፡ ነገር ግን የማይታየው እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ልጁ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዓለም ራሱን ገልጧል፡፡ በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራል (ቆላስይስ 1፡19፣ 2:9)፡፡ በእርሱና በአብ መካከል የባሕርይ ልዩነት ስለሌለ እርሱን ያየ ሁሉ አብን አይቶታል (ዮሐንስ 14፡8-10)፡፡ እርሱና አብ አንድ ናቸው (ዮሐንስ 10፡30)፡፡ በእርግጥ አሕመዲን አጀንዳቸውን ስለሚያፈርስ ጥቅሱን ለመጻፍ አልደፈሩም እንጂ ቆላስይስ 1፡15 የኢየሱስን አምላክነት በግልፅ ቋንቋ ያስቀምጣል፡- “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፡፡

(የብኩርና ትርጉም ጥያቄ ቁጥር 5 ላይ ተብራርቷል፡፡)

ኢየሱስ የእግዚአብሔር አብ አምሳል መሆኑ የተጠቀሰበት አምላክነቱን በማያጠራጥር ሁኔታ የሚገልጥ ሌላ ጥቅስ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ይገኛል፡- “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” (ዕብራውያን 1፡3)፡፡

“የባሕርዩ ምሳሌ” ተብሎ የተተረጎመው “ሁፖስታሴዎስ ካራክቴር” የሚል የግሪክ ሐረግ ሲሆን ካራክቴር የአንድን ነገር ትክክለኛ፣ ያልተሸራረፈ፣ ከዚያኛው አካል ያላነሰ፣ እኩል የሆነ ቅጂ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ “ምሳሌ” ከዚያኛው አካል ጋር በሁሉም ረገድ ፍፁም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ቃል ወልድ ከአብ ልዩ መሆኑን፤ ነገር ግን ደግሞ ከአብ ጋር ፍፁም እኩል መሆኑን ከምንም ዓይነት ጥርጣሬ በፀዳ ሁኔታ የሚገልጥ ነው፡፡[2] “እንዴት ራሱና አምሳሉ አንድ ይሆናሉ?” የሚለው የአሕመዲን ጥያቄ እግዚአብሔር አንድ አካል ብቻ አለው በሚል የተሳሳተ ቅድመ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የሥላሴን ፅንሰ ሐሳብ የማያውቅ ሰው የሚጠይቀው ከዕውቀት ጉድለት የመነጨ ጥያቄ ነው፡፡

25. ኢየሱስ አንድ ጊዜ “ፍፁም አምላክ” በሌላ ጊዜ “ፍፁም ሰው” ይሆናል ካልን በክርስቶስ ማንነት ላይ ብዥታው ይጎላል፡፡ ምክንያቱም አምላክ “እኔ እግዚአብሔር አልለዋወጥም፡፡” ሲል በሚልክያስ 3:6 ላይ ገልጿል፡፡ ታዲያ አምላክ ይህንን ቃሉን አጠፈ ማለት ነውን?

ኢየሱስ አንድ ጊዜ “ፍፁም አምላክ” በሌላ ጊዜ “ፍፁም ሰው” ይሆናል ብሎ የሚያምን ክርስቲያን የለም፡፡ አሕመዲን ይህንን ቅጥፈት ከራሳቸው የተሳሳተ መረዳት ነው ያገኙት፡፡ ይህ ደግሞ ቁጭ ብሎ ያለማንበብና ያለመማር ውጤት ነው፡፡ ኢየሱስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ነው ስንል አንድ ጊዜ ሰው ሌላ ጊዜ ደግሞ አምላክ ይሆናል ማለታችን ሳይሆን ድህረ ትስብዕቱ እነዚህ ሁለቱ ባሕርያት ሳይነጣጠሉና ሳይደባለቁ በአንዱ የኢየሱስ ማንነት ውስጥ በአንድ ጊዜ ይኖራሉ ማለታችን ነው፡፡ ቅድመ ትስብዕቱም ሆነ ድህረ ትስብዕቱ የኢየሱስ መለኮታዊ ባሕርይ ስላልተለወጠ እግዚአብሔር አለመለወጡን ከሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር የሚጣረስ ምንም ነገር የለም፡፡ ነገር ግን እስላማዊ ትውፊቶች አላህ እንደሚለዋወጥ ስለሚናገሩ ጸሐፊው ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የሚያመልኩትን አምላክ በተመለከተ እንደ መስፈርት ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸው ያጠራጥራል፡፡ የግርጌ ማስታወሻውን ይመልከቱ፡፡[3]

26. በማርቆስ 9:21-23 ላይ “ኢየሱስ የልጁን አባት “ይህ በሽታ ከጀመረው ምን ያህል ጊዜ ነው? ሲል ጠየቀው፡፡ አባትየውም እንዲህ አለ «ከህጻንነቱ ጀምሮ ነው፡፡ ሊገድለውም እየፈለገ ብዙ ጊዜ በእሳትና በውሀ ውስጥ ይጥለው ነበር፤ ግንቢቻልህ እባክህ እዘንልን እርዳንም፡፡» ኢየሱስ «ቢቻልህ ትላለህን? ለሚያምን ሁሉ ነገር ይቻላል፡፡» አለው፡፡ ይላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቲያኖች እንደሚያስቡት «አምላክ» ከሆነ ታዲያ በማን አምኖ ነው ተዓምር ማድረግ የቻለው? ለምን ቢሉ «ለሚያምን ሁሉ ነገር ይቻላል፡፡» በማለት «ቢቻልህ» ተብሎ የተጠየቀውን ጥያቄ መልሷል፡፡ አምላክ ስለሆንኩ ምን ይሳነኛል አለማለቱም አስተውሎት ሊቸረው ይገባል፡፡

ኢየሱስ ይህንን ያለው ሰውየው ስለ ተጠራጠረው “ብታምን ይሆንልሃል” ለማለት ፈልጎ እንጂ ስለ ገዛ እምነቱ ለመጥቀስ ፈልጎ አይደለም፡፡ አሕመዲን ቀጣዩን ቁጥር ቢያነቡ ኖሮ ይህ ሃቅ በተገለጠላቸው ነበር፡፡ ዳሩ ግን እንደ ግብር አባታቸው ጥቅሶችን መቆራረጣቸውና ከአውድ ገንጥለው ማውጣታቸው ተሳስተው ሌሎችንም ለስህተት እንዲዳርጉ አድርጓቸዋል፡፡ ቀጣዩ ቁጥር እንዲህ ይላል፡- “ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ፦ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው አለ” (ቁ. 24)፡፡ የብላቴናው አባት ኢየሱስ ስለ እርሱ እምነት መናገሩን አውቆ አለማመኑን እንዲረዳ ተማፅኖታል፡፡ ታዲያ አሕመዲን ምን ቤት ናቸው በመሰለኝ እና በደሳለኝ የሚተረጉሙት?

27. የኢየሱስን ሥልጣን መቀበል በተመለከተ በጥያቄ ቁጥር 12 ላይ የጠየቁትን ስለደገሙ ታልፏል፡፡

28. ኢየሱስን «ጌታ» ይሉታልን? ይህ ከሆነ መንግሥተ ሰማያት መግባት አይፈልጉምማለት ነው፡፡ ለምን ቢሉ በማቴዎስ ወንጌል 7:20-23 ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፡፡ «በሰማያት ያለውን የአባቱን ፍቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! የሚለኝ ሁሉ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያን ቀን ብዙዎቹ፡- ጌታ ሆይ!ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህ ብዙ ተአምራት – አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ በዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብዬ አመሠክርባቸዋለሁ፡፡» ይላል፡፡ ኢየሱስን «ጌታ» የሚለው ማነው? ሙስሊሞች ወይስ ክርስቲያኖች? «አላውቅኋችሁም፣ እመሰክርባቸኋለሁ» ያለውስ ማንን ነው? ክርስቲያኖችን የትኞቹን ክርስቲያኖች? የሚል ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ «ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ» ብሎ ኢየሱስ ገልጾታል፤ እና መንግስተ ሰማያት መግባት አይፈልጉም? ለምን ሌላ ትርጉም በመስጠት ራስዎን ያታልላሉ? ኢየሱስን ጌታ ከማለት ውጭ የአምላክን ተእዛዛት መጠበቅና የአምላክን ፈቃድ መተግበር ትተዋል፡፡ ታዲያ እንዴት ተዘናጉ?

ይህ ጥያቄ የአሕመዲን መጽሐፍ ቅዱስን እንደልባቸው የመተርጎም ድፍረት ጣርያ ነው፡፡ በመሠረቱ ጌታ መሆኑን የተናገረው ራሱ ኢየሱስ ነው፡-

“እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ፡፡ እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል” (ዮሐንስ 13፡13-14)፡፡

“እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው” (ማርቆስ 2፡28)፡፡ እግዚአብሔር ለራሱ ክብር እና አምልኮ በፈጠራት ቀን ላይ ጌታ መሆን የሚችል ከእርሱ በስተቀር ማነው?

የኢየሱስ ጌትነት መታወጅ የጀመረው በብሉይ ኪዳን ነው፡፡ ዳዊት “ጌታ” ብሎ ጠርቶታል (ማቴዎስ 22፡41-46 ከመዝሙር 110፡1 ጋር ያነፃፅሩ)፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ ጌታ ብሎታል (ሚልክያስ 3፡1)፡፡ ገና በማህፀን ሳለ ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ “ጌታዬ” ብላዋለች (ሉቃስ 1፡43)፣ መላእክት ጌትነቱን መስክረዋል (ሉቃስ 2፡11)፣ እግዚአብሔር አብ ራሱ ጌታ መሆኑን መስክሯል (ዕብራውያን 1፡10)፡፡ እኔ ባደረኩት ቆጠራ መሠረት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ250 ጊዜያት በላይ “ጌታ” ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ሰዎች ጌታ ሲሉት አንድም ቀን ተቃውሞ አሰምቶ አያውቅም፡፡ ነገር ግን አሕመዲን የቋንቋ ችግር ያለባቸው ይመስል ኢየሱስ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፍቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” በማለት የተናገረውን አጣመው በመተርጎም ኢየሱስ “ጌታ አትበሉኝ” ያለ ለማስመሰል ሞክረዋል፡፡ ኢየሱስ እያለ ያለው በተግባር አማኝ ሆናችሁ ካልተገኛችሁ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ስላላችሁ ብቻ አትገቡም ነው፡፡ ጠያቂው የአገራቸው ቋንቋ ካልገባቸው በእንግሊዘኛ እንዲያነቡት ከታች አስቀምጠናል፡፡[4] በኢየሱስ ስም ትንቢት መናገርም ሆነ ተዓምራትን ማድረግ ለመንግሥተ ሰማያት አያበቃም፡፡ በኢየሱስ ስም ተዓምር ማድረግ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ዋስትና ከሆነ ጌታውን የሸጠው ይሁዳም ሊገባ ነው፡፡ ለመንግሥተ ሰማያት የሚያበቃው የአብን ፈቃድ በመፈፀም እስከ መጨረሻው ድረስ እውነተኛ አማኝ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ መፈፀም ያለበት ቀዳሚው የአብ ፈቃድ ደግሞ እርሱ በላከው በአንድ ልጁ ማመን ነው (ዮሐንስ 6፡40)፡፡

አሕመዲን ህሊናቸውን በመጨቆን የእግዚአብሔርን ክቡር ቃል ለማጣመም እስከዚህ ጥግ ድረስ መሄዳቸው በእውነቱ ከሆነ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች አንድ ሰው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሙስሊሞችን መጽሐፍ ሲያጣምም ቢመለከቱ ከመገሰፅ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ተመሳሳይ ነገር በክርስቲያኖች መጽሐፍ ላይ ሲፈፀም ህሊና ያላቸው ሙስሊሞች ሁሉ ሊቃወሙ ይገባል፡፡ ወዳጆች ሆይ ስለ ነፍስ ጉዳይ ነው እያወራን ያለነው፡፡ አንዳችን የሌላችንን ቅዱስ መጽሐፍ እያጣመምን እንዴት ነው ልንተማመንና አንዳችን ሌላችንን የእውነት አምላክ ወደሆነው ፈጣሪያችን ልንመራ የምንችለው? ፈጣሪ በሀሰት እና በማጭበርበር ደስ ይሰኛልን?

29. እንደ ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 7 ከቁጥር 16-17 ከሆነ፡- «ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፡- የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው፡፡ ማንም የእግዚአብሔር ፈቃድ ለማድረግ ቢፈልግየእኔ ትምህርት ከእግዚአብሔር ወይም ከራሴ የመጣ መሆኑን ለይቶ ያውቃል፡፡» ሲል ተናግሯል፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ «ከእግዚአብሔር ወይም ከራሴ» ሲል እግዚአብሔርና እርሱ የተለያዩ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡ ታዲያ ኢየሱስና እግዚአብሔር የተለያዩ ከሆኑ ክርስቲያኖች ስንት አማልከትን ነው እየተገዙ ያሉት? ኢየሱስን ወይስ እግዚአብሔርን?

እኛ በሦስት አካላት የተገለጠ አንድ አምላክ ነው የምናመልከው፡፡ ወልድ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ መለኮትነቱ ባይቋረጥም ፍፁም ሰው ሆኖ ስለተመላለሰ የራሱን ፈቃድ ለአብ በማስገዛት እንደ አገልጋይ ተመላልሷል፡፡ ከላይ የተጠቀሰውን ቃል የተናገረው ከዚያ አኳያ ነው፡፡

30. ዕብራውያን 1:4-5 እንዲህ ይላል፡- «ስለዚህ የወረሰው ስም ከመላእክት ስም እንደሚበልጥ ሁሉ እርሱም ከመላዕክት እጅግ የላቀ ሆኖአል፡፡ እግዚአብሔር «አንተ ልጄ ነህ» እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ወይስ ደግሞ“እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፡፡» ያለው ከመላዕክት ከቶ ለማን ነው? » በዚህ ጥቅስ ላይ «ዛሬ ወልጄሀለሁ» ሲለው “ዛሬ” የሚለው ቃል የሚያሳየን ይህ አገላለጽ “ዓለም” እና “ጊዜ” ከተፈጠረ በኋላ መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም ጊዜ ፍጡር ስለ ሆነ ጊዜ ከመፈጠሩ በፊት “ትናንት ዛሬ ነገ ወዘተ የሚሉና ጊዜን አመልካች የሆኑ ቃላት አልነበሩምና፡፡ “ዛሬ” ተብሎ የተገለፀው ቀን ከመወለዱ በፊት ነበርን? እንዲሁም “የወረሰው ስም ከመላእክት ስም እንደሚበልጥ ሁሉ፡” ይላል፡፡ ኢየሱስ “የእግዚአብሐር ልጅ” የመባልን ስም ከመውረሱ በፊት ምን ነበር? እንዲሁም “እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል” ይላል፡፡ “እኔ አባት እሆነዋለሁ” ሲል “አባቱ ነኝ” ማለት እንዳልሆነ ልብ ብለዋል? “እሆነዋለሁ” ማለት የወደፊት ጊዜን አመለካች አይደለምን? እንዲሁም ጥቅሱ “እኔ አባት እሆነዋለሁ፡ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፡” ያለው ከመላዕክት ከቶ ለማን ነው?” ይላል፡፡ በጥቅሱ ላይ “ያለው ከመላዕክት ከቶ ለማን ነው? ሲል «ያለው በማለት መግለፁ ምንን ያመለክታል? “ያለው” ሲል በተምሳሌታዊ አገላለጽ (symbolical exprerssions) “ልጄ ነህ” ማለት እንጂ በተግባር መወለዱን አያመለክትም፡፡ ይህ ባይሆንማ ኖሮ በጭራሽ ከመላዕክት ጋርም ባልተነፃፀረ ነበር፡፡

የዕብራውያን ጸሐፊ ኢየሱስን ከመላእክት ጋር ያነፃፀረበት ምክንያት የመልእክቱ ተቀባዮች የኢየሱስ ታላቅነት ከመላእክት የላቀ መሆኑን ማወቅ ስለሚገባቸው ነው፡፡ እነዚህ አማኞች ከአይሁድ እምነት የመጡ፣ በመላእክት መካከለኛነት የሚያምኑና መላእክትን ወደ አማልክትነት ደረጃ ያስጠጉ በመሆናቸው ጌታችን የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ፣ የመላእክት ፈጣሪና የእነርሱ ጌታ መሆኑን ከብሉይ ኪዳን ክፍሎች በመጥቀስ ማስረዳት አስፈላጊ ነበር፡፡ ስለዚህ የዕብራውያን ጸሐፊ ንፅፅሩን እንዲያደርግ ያስገደደው የተደራሲያኑ አመለካከት እንጂ የኢየሱስን ዘለዓለማዊ የአብ ልጅነት የመቃወም ሐሳብ ኖሮት አይደለም፡፡ “ዛሬ ወልጄሃለሁ” የሚለው አነጋገር ጊዜን አመላካች አይደለምን? በዚህ ላይ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፡፡ ኦሪጎን እና አትናቴዎስን የመሳሰሉት የቤተ ክርስቲያን አባቶች እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ በመሆኑ “ዛሬ” የተባለው እግዚአብሔር የሚኖርበትን ዘለዓለም አመላካች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር “ዛሬ” በሰውኛ አነጋገር ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊነት መታየት ስላለበት ይህ አባባል የኢየሱስን ዘለዓለማዊ የእግዚአብሔር ልጅነት እንደሚያመለክት አትተዋል፡፡[5] ቁርኣን እንኳ የሰውና የአላህ የጊዜ አቆጣጠር እንደሚለያይ ይናገራል (ሱራ 22፡47)፡፡

የቅርብ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐታቾች (Commentators) ደግሞ ይህ ንግግር ኢየሱስ በትንሣኤው ወቅት የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ ለፍጥረት መረጋገጡን የተመለከተ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በዚህ መረዳት መሠረት “ዛሬ ወልጄሃለሁ” ማለት ከዚህ ቀደም ልጅ አለመሆንን የሚያመለክት ሳይሆን ኢየሱስ ከሠራው ታላቅ ሥራ የተነሳ አብ ደስ መሰኘቱን የገለፀበት መንገድ እና የባርያን መልክ ይዞ በመምጣቱ ምክንያት የተሸፈነውን መለኮታዊ ልጅነቱን ዳግመኛ በማቀዳጀት ለፍጥረት ሁሉ ማረጋገጫ የሰጠበት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሮሜ 1፡3-4 እንደ ማስረጃ ይጠቀሳል፡፡

አሕመዲን “እኔ አባት እሆነዋለሁ” ሲል “አባቱ ነኝ” ማለት እንዳልሆነ ልብ ብለዋል? በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን መላእክት በብሉይ ኪዳን ውስጥ “የእግዚአብሔር ልጆች” ስለተባሉ ከዚህ ጥቅስ በመነሳት የኢየሱስ ልጅነት እንደ እነርሱ ሁሉ ከእግዚአብሔር ባሕርይ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት እንደሌለው ለመሟገት የሚሞክር ሰው የዕብራውያን ጸሐፊ ነጥብ የኢየሱስ ልጅነት ከመላእክት የተለየና የላቀ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሆነ ዘንግቷል፡፡ “እኔ አባት እሆነዋለሁ” የሚለው አነጋገር አብ የኢየሱስ አባት መሆኑ የማይቋረጥና ቀጣይነት ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህንን አነጋገር በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ተከታዮቹን ጥቅሶች ልብ በሉ፡-

ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል” (ራዕይ 21፡7፡፡

በዚህ ቦታ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአማኝ አምላክ እንደሚሆን ይናገራል፡፡ ነገር ግን ይህ አባባል እስከ መጨረሻው የፍርድ ቀን ድረስ ኢየሱስ የአማኞች አምላክ አይደለም የሚል ትርጉም የለውም፡፡

“ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ” (ዘጸአት 6፡7)፡፡

ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር ከዚያ ቀደም የእስራኤል አምላክ አልነበረም ተብሎ ሊተረጎም አይችልም፡፡ ጠያቂያችን የጠቀሱትንም ጥቅስ በዚህ መልኩ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

31. መጽሐፍ ቅዱስ ላይ «ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፡ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፡ መጀመሪያ በኩራት የሆነው ክርስቶስ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት፡፡ ከዚያም ግዛትን ሥልጣንና ኃይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላመንግስትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ ያን ጊዜ ፍፃሜ ይሆናል፡፡ ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስኪያደርግ ድረስ ሊነገሥ ይገባዋልና፡፡» (1ኛ ቆሮንቶስ 15:22-24) እንዲሁም «ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል» ይላል፡፡ (1ኛ ቆሮንቶስ 15:28) (የ1980 አትም) ኢየሱስ ሥልጣን እንደ ተሰጠው ተናግሯል፡፡ ግን ይህ ጥቅስ በሚገርም መልኩ ስልጣኑን እንደሚያስረክብ ይገልፃል፡፡ ታዲያ ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ከስልጣን የሚወርድ ከሆነ ምኑ ላይ ነው የእርሱ አምላክነት? ኢየሱስ ከስልጣኑ ወርዶ ለአምላኩ የሚገዛ ከሆነ ምኑን አምላክ ሆነ? ክርስቲያኖች አሻፈረን አሉ እንጂ ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለም አምላኩን ሲገዛ አልነበረም? ኢየሱስ የሚነግሠው በጥቅሱ “ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስኪያደርግ ድረስ ሊነግስ ይገባዋል፡፡” በማለት እንደተገለፀው ከሆነ የእርሱ “ንግስና” በጊዜ የተገደበ ነው፡፡ አምላክ ግን ከዘለዓለም እሰከ ዘለዓለም ንጉስ ነው፡፡ ስልጣንን ለማንም አያስረክብም፡፡ ኢየሱስ ግን “መንግስትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክበው፡ ያን ጊዜ ፍፃሜ ይሆናል፡፡” ተብሎ እንደተገለፀው ስልጣኑን ያስረክበዋል፡፡ ታዲያ ኢየሱስን አምላክ ልንለው እንዴት ይቻለናል? ጥቅሱ እግዚአብሔርን ነው እንጂ “እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን” ያለው ኢየሱስን አይደለም፡፡ አልያም “አንድ እግዚአብሔር የሚሆኑት አብ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን” አላለም፡፡ ታዲያ እንዴት ኢየሱስ አምላክ ሊባል ይችላል?

1ኛ ቆሮንቶስ 15፡28 ላይ የኢየሱስን ለአብ መገዛት ለማመልከት ጥቅም ላይ የዋለው ቃል “ሁፖታጊሰታይ” የሚል ሲሆን ደረጃን እንጂ ባሕርይን የሚያመለክት አይደለም፡፡ ይህ የግሪክ ቃል የሚነበብበት ድምፀት ወልድ ተገዶ ወይም ትዕዛዝ ተሰጥቶት ሳይሆን በፍቃደኝነት ራሱን በራሱ ለአብ እንዳስገዛ ያሳያል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ የግሪክ ቋንቋ ሊቅ የሰጡትን ሐተታ በግርጌ ማስታወሻው ላይ ይመልከቱ፡፡[6]

በሥላሴ አስተምህሮ መሠረት ልጅ ለአባት እንደሚገዛ ሁሉ ወልድም ለአብ ይገዛል፡፡፡ ነገር ግን አባትና ልጅ እንደ ሰው ያላቸው እሴት (Value) እኩል እንደሆነ ሁሉ አብና ወልድም እኩል ናቸው፡፡ ወልድ በአምላካዊ ባሕርዩ ከአብ ያነሰ አይደለም፡፡ አብም በአምላካዊ ባሕርዩ ከወልድ የበለጠ አይደለም፡፡ ስለ ሥላሴ አካላት እኩልነት ስንናገር በመለኮታዊ ባሕርይ ማለታችን እንጂ በሥራ ድርሻቸው (Function) ማለታችን አይደለም፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ወልድ ለአብ መገዛቱን መናገሩ የሥላሴን አስተምህሮ የሚያፀና እንጂ የሚፃረር አይደለም፡፡ ሌላው መረሳት የሌለበት ጉዳይ የኢየሱስ ፍፁም ሰው መሆን ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ሲያርግ ፍፁም ሰው የሆነውን ደግሞም ከሙታን የተነሳውንና የከበረውን ሥጋውን በመተው አይደለም፡፡ ይህ ማለት ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ሆኖ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሁኔታ ለአብ እንደሚገዛ ለመነገሩ እንደ ተጨማሪ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ኢየሱስ ከሥልጣን የሚወርድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ንግሥናውስ ይሻር ይሆን? የዚህን ጥቅስ ትክክለኛ ትርጉም ከማስቀመጣችን በፊት እስኪ መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ዘለዓለማዊ ንግሥና በተመለከተ ምን እንደሚል እንይ፡-

“እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም” (ሉቃስ 1፡32-33)፡፡

“በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት፡፡ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው” (ዳንኤል 7፡13-14 ከማርቆስ 14፡61-62 ጋር ያነፃፅሩ)፡፡

“ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው” (ዕብራውያን 1፡8)፡፡

“እንዲሁ ወደ ዘለዓለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋልና” (2ጴጥሮስ 1፡11)፡፡

“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል” (ኢሳይያስ 9፡6-7)፡፡

“ሰባተኛው መልአክ ነፋ፤ በሰማይም፦ የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፥ ለዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ” (ራዕይ 11፡15)፡፡

ሌላ ቦታ ላይ ቅዱሳን የሚወርሱት መጪው መንግሥት የአብ እና የወልድ መሆኑ ተነግሯል፡-

“ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም” (ኤፌሶን 5፡5)፡፡

ስለዚህ መጪው መንግሥት የክርስቶስ እና የእግዚአብሔር አብ መሆኑ ከተነገረ ኢየሱስ ግዛትን ሥልጣንና ኃይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለአብ ማስረከቡ የተነገረው ለአብ መገዛቱን አፅንዖት ለመስጠት እንጂ ንግሥናው ጊዜያዊ እንደሆነ ለማመልከት አይደለም፡፡ ከዚህ ትርጓሜ በተፃራሪ መጽሐፍ ቅዱስ በመጪው ዓለም አብ እና ወልድ አንድ ዙፋን እንደሚኖራቸው ይናገራል፡-

“በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን [ነጠላ] የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ፡፡ በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፥ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ፡፡ ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም፡፡ የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን [ነጠላ] በእርስዋ ውስጥ ይሆናል፥ ባሪያዎቹም ያመልኩታል፥ ፊቱንም ያያሉ፡፡” (ራዕይ 22፡1-7)፡፡

32. በማርቆስ 11:12-14 ላይ “በማግስቱ ከቢታንያ ሲወጣ ተራበ ቅጠል ያለበት በለስ በሩቁ አይቶ ምናልባት አንዳች አገኘባት እንደሆነ ብሎ ወደርሷ መጣ፡ ነገር ግን የበለሰ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም፡፡ ከዚያም ዛፏን፡ ከአሁን ጀምሮ ለዘለዓለም ማንም ፍሬ ከአንቺ አይብላ አላት፡፡ ደቀመዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙት፡፡ ይላል፡፡ “አምላክ ነው” የሚበላው ኢየሱስ እርሱ እንኳን ባለበት ሆኖ ፍሬ ይኑራት አልያም አይኑራት የሚለውን ማወቅ ተስኖት ለማረጋገጥ ቀርቦ ቢያጣባት ለምን ይረግማታል? እርሷ ምን ታድርግ? የበለሰ ወቅት አልነበረም፡፡ ኢየሱስ አምላክ ቢሆን ኖሮ እንዴት ከፊቱ ራቅ ብላ ያለች በለሰ ፍሬ ይኑራት አይኑራት ማወቅ ይሳነዋል? በለሷንስ አምላክ አይደል ፍሬ እንድታፈራ የሚያደርጋት? አምላክስ ከበለስ ምን ጉዳይ ኖሮት ሲያጣባት ይረግማታል?

መጽሐፍ ቅዱስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአት ያልነካው ፍፁም ሰው እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከሰማይ የወረደ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ ግን ሁሉን የሚያውቅ መለኮት ነው (ለጥያቄ ቁጥር 10 የተሰጠውን መልስ ይመልከቱ)፡፡ ስለዚህ የእውቀት ውሱንነት ቢታይበት ወይም ቢራብ ፍፁም ሰው መሆኑን የሚያረጋግጥ እንጂ መለኮታዊ ባሕርዩን የሚነካ አይደለም፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ የበለስ ወራት እንዳልሆነ እያወቀ ስለምን ሄደ? ለምንስ ረገማት? በለስ የፍሬ ወራትዋ ሲቀርብ ቅጠሏ ይለመልማል፡፡ በዚህ ጊዜ በጫፎቿ ላይ ለምግብነት ሊውሉ የሚችሉ በአረብኛ ታቅሽ የተሰኙ እንቡጦች ይኖሯታል፡፡ እነዚህ እንቡጦች ካልታዩ በለሲቱ በዚያን ዓመት ፍሬ የማፍራት ተስፋ የላትም፡፡ ስለዚህ በለሲቱ ለብዙዎች መሰናክል የሆነች፣ ብዙዎችን ያሳዘነች መካን ነበረች፡፡[7] ኢየሱስ በለሲቱን በመርገም እንድትደርቅ በማድረጉ እንቅፋትን ከማስወገዱም በላይ ሁለት መንፈሳዊ ትምህርቶችን አስተላልፏል፡፡ የመጀመርያው ለደቀ መዛሙርቱ እምነትን ማስተማር ሲሆን (ማርቆስ 11፡21,24) ሁለተኛው ደግሞ ለእስራኤል በተግባራዊ ምሳሌ የተደገፈ መልእክትን መስጠት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅደስ መሠረት በለስ የእስራኤል ምሳሌ ስትሆን ፍሬ ካላፈራች ወይም ፍሬዋ መልካም ካልሆነ እግዚአብሔር እንደሚያደርቃት በነቢያቱ በኩል በተደጋጋሚ ተናግሯል (ሆሴዕ 9፡10-16፣ ሚክያስ 7፡1-4፣ ናሆም 3፡12፣ ኤርምያስ 29፡15-19)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የእስራኤልን እንደ ፍሬ አልባ በለስ መድረቅ አስቀድሞ ተናግሯል (ሉቃስ 12፡5-9)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ መካኒቱ በለስ ፍሬ አልባ የሆነችው እስራኤል እንደምትደርቅ ተግባራዊ ምሳሌ እየሰጠ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ታላቅ መንፈሳዊ መልእክት ያዘለ ታሪክ ጠምዝዞ የኢየሱስን አምላክነት ለመቃወም መጠቀም አግባብ አይደለም፡፡

33. እንደ ክርስትና እምነት “ኢየሱስ ሰውም አምላክም ነው”፡፡ ኢየሱስ ፍጡር ነውን? አይደለም” ከሆነ ምላሽዎ ኢየሱስ ሰው አይደለም ማለት ነው፡፡ “አዎን” ካሉ ደግሞ “አምላክ” አይደለም፡፡ ምክንያቱም አምላክ ፍጡር አይደለምና፡፡ ታዲያ ምን ሊሆን ነው?

የኢየሱስ ሰብዓዊ ባሕርይ ከተሠግዎ በኋላ የተገኘ ነው፡፡ መለኮቱ ግን በጊዜ ባልተገደበ ዘለዓለማዊነት ከአብ የተገኘ በመሆኑ ፈጣሪ እንጂ ፍጡር አይደለም፡፡ ኢየሱስ ሰብዓዊና መለኮታዊ ባሕርያት ቢኖሩትም አንድ ማንነት እንጂ ሁለት ማንነቶች የሉትም፡፡ ይህ አንዱ ማንነት ደግሞ መለኮት በመሆኑ ፈጣሪ እንጂ ፍጡር አይደለም፡፡ ሁለቱ የኢየሱስ ባሕርያት ያልተነጣጠሉና ያልተደባለቁ በመሆናቸው “አምላክ ከሆነ ሰው አይደለም፤ ሰው ከሆነ ደግሞ አምላክ አይደለም” የሚል አመክንዮ አይሠራም፡፡ ሁለቱም ባሕሪያት በአንድ ጊዜ አንድ ላይ እንዳይኖሩ የሚከለክል ምንም ምክንያት የለም፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የክርስትናን አስተምህሮ ከተረዳ ሰው ፈፅሞ አይጠበቅም፡፡

34. በማቴዎስ 19:16-17 እንደተዘገበው ኢየሱስ የዘለዓለም ሕይወትን ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚገባ ሲጠየቅ “ትዕዛዝን ጠብቅ” ሲል መልሷል፡፡ የመጀመሪያው ትዕዛዝ በአምላክ አንድነት ማመን ነው (ዘፀአት 20:3)፡፡ ታዲያ ኢየሱስ በሥላሴ ካመነና የሥላሴ አባልም ከሆነ ለምን እንዲህ ሲል መለሰ? ቤተክርስቲያን የሚዳነው በሥላሴ በማመን እና ኢየሱስ ለሰው ልጆች ኃጢአት ቤዛ መሆኑን በማመን እንደሆነ ታስተምራለች፡፡ ታዲያ እውነተኛው አስተምህሮት የትኛው ነው? የኢየሱስ ወይንስ የቤተክርስቲያን?

አሕመዲን ክፍሉን እስከ መጨረሻው ድረስ ቢያነቡት ኖሮ የኢየሱስን መልእክት በትክክል በተረዱ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዛትን ቢጠብቅ እንደሚድን ለባለጠጋው ከነገረው በኋላ ባለጠጋው ትእዛዛትን ሁሉ እንደጠበቀ ነገረው፡፡ ኢየሱስ ግን “ይህ ይበቃል፣ በቃ ድነሃል” አላለውም ነገር ግን ያለውን ሁሉ ሽጦ ለድሆች በመስጠት እንዲከተለው ነገረው፡፡ ይህም ማለት አንድ ሰው መዳን ከፈለገ ሕግን ሁሉ እንኳ የጠበቀ ቢሆን ሙሉ በሙሉ ሕይወቱን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመስጠት ሊከተለው ይገባል ማለት ነው፡፡ አሕመዲን በአምላክ አንድነት ማመን ማለት የነጠላ አሃዳዊነት እምነት ተከታይ መሆን ማለት እንደሆነ በማስመሰል ደግመው ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ እስከ አሁን ድረስ እንደተመለከትነው ይህንን እምነታቸውን የሚደግፍ እና ሥላሴያዊ አሃዳዊነትን (Trinitarian Monotheism) የሚቃወም ምንም ዓይነት የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃ ሊያቀርቡ አልቻሉም፡፡

35. በዮሐንስ ወንጌል 8:40 ላይ “ኢየሱስ እንዲህ ሲል ለአይሁዶች ተናገረ፡-«ከእግዚአብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኳችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፡» ይላል፡፡ ታዲያ እርሱ “ከእግዚአብሔር የሰማሁት፡” ሲል እርሱ እንደማን ሆኖ ነው ከእግዚአብሔር የሚሰማው? እንደ ክርስትና አስምህሮት “እግዚአብሔር፡” ማለት ሥላሴ የሆነና ኢየሱስን የሚጨምር አይደለምን? ስለ ኢየሱስ ከርሱ የበለጠ ክርስቲያኖች ያውቃሉ ማለት ነው? እርሱ ስለ ራሱ “እውነቱን የነገርኳችሁን ሰው” ሲል “ሰው” መሆኑን ገልጿል፡፡ ክርስቲያኖች ግን “አምላክ” ይሉታል፡፡ ማንኛው ነው የዋሸው?

አሕመዲን ኢየሱስን በተሳሳተ መንገድ መረዳታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ፍፁም ሰው በመሆን ከአብ እየሰማ መሲሃዊ አገልግሎቱን ሲፈፅም ነበር፡፡ አምላክ እንደመሆኑ የዘለዓለምን ሕይወት እንደሚሰጥ (ዮሐንስ 10፡27-28)፣ በምድር ላይ እንኳ እያለ በዚያው ቅፅበት በሰማይ እንደሚኖር (ዮሐንስ 3፡13)፣ ፀሎትን እንደሚሰማና እንደሚመልስ (ዮሐንስ 14:13-14)፣ በመጨረሻው የትንሣኤ ቀን በሁሉም ላይ እንደሚፈርድ (ማቴዎስ 25፡30-46)፣ ለአብ የሚገባው ክብር ሁሉ ለእርሱም እንደሚገባ (ዮሐንስ 5፡22-23)፣ ወዘተ. ቢናገርም ነገር ግን ደግሞ እንደ ሰው ከአብ እንደሚሰማና የአብን ፈቃድ ብቻ እደሚፈፅም ተናግሯል፡፡ አሕመዲን እነዚህ ሁለቱ የኢየሱስ ባሕርያት እና ግብራት ባይምታቱባቸው ኖሮ ድንግርታ ውስጥ ባልገቡ ነበር፡፡ አሁን ግን የዚህ ሃቅ ውሉ ስለጠፋባቸው በጨለማ ውስጥ እንደሚዳብስ እውር ሆነዋል፡፡ እስኪ ኢየሱስ ስለ አምላክነቱ የተናገራቸውን ሁለት ነጥቦች ከዚህ ምዕራፍ እንመልከት፡-

“እንግዲህ፦ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው፡፡ እንግዲህ፦ አንተ ማን ነህ? አሉት፡፡ ኢየሱስም፦ ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ (ዮሐንስ 8፡24-26)፡፡

“አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው፡፡ አይሁድም፦ ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት፡፡ ኢየሱስም፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው፡፡ ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ፡፡” (ዮሐንስ 8፡56-59)፡፡

በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ኢየሱስ ከመጀመርያው ለአይሁድ የተናገረው እንደሆነና “እኔ አለሁ” በማለት ተናግሯል፡፡ የእነዚህ ንግግሮች ትርጉም ስለገባቸው አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ከያሕዌ እግዚአብሔር በስተቀር ማንም ሊናገራቸው የማይችላቸውን ንግግሮች በመናገር ለአይሁድ አምላክነቱን ግልፅ አድርጓል፡፡ “እኔ አለሁ” ተብሎ የተተረጎመው ሐረግ “እኔ ነኝ” ተብሎ ቢተረጎም የበለጠ ትክክል ይሆናል፡፡ ግሪኩ “ኢጎ ኤይሚ” የሚል ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት የተተረጎመው የሰብዓ ሊቃናት (ሰብቱጀንት) ትርጉም ኢሳይያ 48፡12 ላይ የሚገኘውን “ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ” በማለት ያሕዌ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል በተመሳሳይ መንገድ ተርጉመዋል፡፡ እንደርሱ በማለት መናገር የሚችለው ያሕዌ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ስለሚያውቁ ነው አይሁድ የኢየሱስን ንግግር እንደ ክህደት በመቁጠር ሊወግሩት ድንጋይ ያነሱት፡፡

36. ማቴዎስ 12፡28 ላይ ኢየሱስ «እኔ ግንበእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንኩ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግስት ወደ እናንተ ደርሳለች፡፡» ብሏል፡፡ ታዲያ ኢየሱስ አጋንንትን በእግዚአብሔር መንፈስ የሚያወጣ ከሆነ ምኑ ነው የሚገርመው? ኢየሱስ “በራሴ” አላለ “በእግዚአብሔር መንፈስ” ነው ያለው፡፡ ተዓምሩስ የማነው? ታዲያ አምላክ ሁሉን ቻይ አይደለምን? ነቢያት በእግዚአብሔር መንፈስ ተዓምራት አሳይተው የለምን? ኢየሱስ በፈጣሪ እገዛ ተአምር ቢሰራ ምን ይለየዋል?

ኢየሱስ የመሲህነት አገልግሎቱን ይፈፅም በነበረበት በሥጋው ወራት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አገልግሏል፡፡ ነገር ግን ከሰማያት የወረደ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መሆኑ ከሌሎች ነቢያት ልዩ ያደርገዋል፡፡ የሚያስወጣቸው አጋንንት እንኳ ይህንን በማወቅ ሲንቀጠቀጡና ሲገዙለት እንመለከታለን (ማርቆስ 5፡1-10፣ ሉቃስ 4፡41)፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ አጋንንትን የማስወጣት አገልግሎት የተጀመረው በጌታችን መሆኑን እንመለከታለን፡፡ በብሉይ ዘመን እንዲህ ያለ ሥልጣን የነበረው ነቢይ ስለመኖሩ የተጻፈ ቃል የለም፡፡ ይህም ኢየሱስን ልዩ ያደርገዋል፡፡ ኢየሱስ አጋንንትን ማስወጣት ብቻ ሳይሆን ተከታዮቹም በስሙ እንዲያስወጡ ሥልጣንን መስጠቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያረጋግጣል (ማቴዎስ 10:1፣ ማርቆስ 6፡7፣ 16፡17፣ ሉቃስ 9፡1፣ 10:17፣)፡፡ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ በኢየሱስ ስም ሰዎችን ከአጋንንት እስራት ነፃ የማውጣት አገልግሎት ቀጥሏል (የሐዋርያት ሥራ 8፡7፣ 16፡16-18፣ 19፡11-17)፡፡ እዚህ ጋ የአሕመዲን ሃይማኖት ጀማሪና ነቢይ የነበሩት ሙሐመድ በአጋንንት ላይ ስልጣን እንዳልነበራቸውና እንዲያውም በአንድ ወቅት አስማት ተሰርቶባቸው ሲሰቃዩ እንደነበር የገዛ መጻሕፍታቸው የተናዘዙትን መጥቀስ ተገቢ ይመስለናል፡-

“አይሻ እንዳስተላለፈችው ላቢድ ቢን አል-አስማ የተባለ ከበኒ ዙራይቅ ወገን የሆነ እና የአይሁዶች ተባባሪ የነበረ ሰው በነቢዩ ሙሐመድ ላይ አስማት (Magic) በመስራቱ ሳብያ ሙሐመድ ሚስቶቻቸው በሌሉበት ከሚስቶቻቸው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እየፈፀሙ እንደሆነ በአዕምሯቸው ውስጥ እስኪታያቸው ድረስ የአስማቱ ኃይል በእሳቸው ላይ መስራት ችሎ ነበር፡፡”[8]

እውነተኛ ነቢይ ሰዎችን ከሰይጣን እስራት ነፃ ያወጣል እንጂ እንዴት ሰይጣን እንዲህ ባለ ሁኔታ ሊጫወትበት ይችላል? ነቢዩ ሙሐመድ በጣም አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ እሳቸውም ሆኑ ተከታዮቻቸው ከሰይጣን ጋር እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡-

“የአላህ መልእክተኛ ሲናገሩ እንዲህ አሉ፡- ከእናንተ መካከል ሰይጣን ያልተመደበበት የለም፡፡ ሱሃባዎቹም የአላህ መልእክተኛ ሆይ በእርስዎም ላይ ሰይጣን ተመድቦበዎታልን? ብለው ጠየቁ ሲመልሱ አዎን! ተመድቦብኛል ነገር ግን አላህ በእርሱ ላይ እረዳኝና ተቃወምኩት ከሃይሉ እኔ ነጻ ነኝ አሁን የሚያዘኝ ወደ መጥፎ ስራ ሳይሆን ወደ መልካም ስራ ነው፡፡ አብዱላህ ኢብን መሱድ የዘገበው ሐዲስ ነው፡፡”[9]

“ሰይጣን ተመድቦብኛል ግን ወደ መልካም ነገር ነው የሚመራኝ” ብሎ ማለት የሰይጣንን ባሕርይ ያለማወቅ ነው፡፡ ምናልባት ነቢዩ መልካም እንደሆነ የተናገሩት ምግባራቸው ክፉ ቢሆንስ? ሰይጣን የያዘው ሰው ክፉው መልካም፤ መልካሙ ደግሞ ክፉ መስሎ ሊታየው ይችላል፡፡

“የአላህ መልእክተኛ ከእናንተ የትኛውም ሰው ከመኝታው ሲነሳ ውዱ ያድርግ አፍንጫው ውስጥ ውሃ እያስገባ እያስወጣ ሦስቴ በመደጋገም ይጠበው፡፡ ምክንያቱም ሰይጣን በአፍንጫው የላይኛው ክፍል ሌሊቱን ሙሉ አድሮ ሊሆን ይችላልና አሉ፡፡  አቡ ሁሬይራ የዘገቡት ሐዲስ ነው፡፡”[10]

37. ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ አብሮት ስለሆነ አምላክ የምናደርገው ከሆነ ከኢየሱስ ሌላ በርካታ መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው የነበሩትን ሁሉንም አምላክ ልናደርጋቸው ነው?

ኢየሱስ አምላክ የሆነው መንፈስ ቅዱስ አብሮት ስለነበረ ነው ስላልተባለ ይህ ጥያቄ የሚመጥንና ጊዜያችንን ልንሰጠው የሚገባ አይደለም፡፡

38. ኢየሱስ በርካታ ነገሮችን ማድረግ ሲያቅተው ተስተውሏል፡፡ ምንም ከራሱ ማድረግ እንደማይችልም በዮሐንስ 5:30 (የ1879 አትም)“እኔ ብቻዬን ከራሴ ምንም ማድረግ አልችልም፡» ሲል በግልጽ ተናግሯል፡፡ አምላክ ከራሱ ብቻውን ምንም ማድረግ አይችልምን? አምላክ ከሌላ አካል እገዛ ይሻልን? እንዲሁም ሆኖ ምንም ማድረግ የማይችል አምላክ ነበርን?

አሁንም የተከበሩት ጠያቂያችን ኢየሱስ ሰውም አምላክም መሆኑን ዘንግተዋል፡፡ በፍፁም ሰውነቱ ያንን መናገሩ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የኢየሱስ ንግግር ከዚህም የጠለቀ ትርጉም አለው፡፡ ክርስቲያኖች ሦስቱም የሥላሴ አካላት ተነጣጥለውና ተለያይተው ይሠራሉ የሚል እምነት የላቸውም፡፡ አብ የሚሠራው ዘለዓለማዊ ቃሉ በሆነው በወልድ እና የእርሱ መንፈስ በሆነው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ስለዚህ ሦስቱን የሥላሴ አካላት መነጣጠል ፈፅሞ የማይቻል ነው፡፡ አንዳቸው ከሌላቸው ተለይተው መስራት ከባሕርያቸው ጋር አይሄድም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ይህንን መናገሩ ከአብ ጋር ያለውን የማይነጣጠል አንድነት የሚያሳይ እንጂ አምላክነቱን የሚቃወም አይደለም፡፡

39. በዮሐንስ 14:1 ላይ «ልባችሁ አይጨነቅ ፡በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ!» ሲል ኢየሱስ እግዚአብሔርና ኢየሱስ የተለያዩ መሆናቸውን አልገለፀምን? በእኔ ደግሞ እመኑ! ሲል ራሱን ከእግዚአብሔር ለይቶ ለምን ጠየቀ?

በአዲስ ኪዳን ውስጥ አውዱ ካላመለከተ በስተቀር “እግዚአብሔር” ከተባለ የተጠቀሰው የሥላሴ አካል አብ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ቦታ ላይ ኢየሱስ ሐዋርያቱ በእርሱና በአብ እንዲያምኑ መጠየቁ አምላክነቱን የሚያሳይ እንጂ የሚፃረር አይደለም፡፡

40. ማቴዎስ 26:29 ላይ«በአባቴ መንግስት አዲሱን የወይን ፍሬ ጭማቂ ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ የወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም እላችኋለሁ» ይላል፡፡ ኢየሱስ አምላክ ነው ካልን ነገ አምላክ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ገነት ገብቶ የወይን ጭማቂ ሊጠጣ ነው? አምላክ ገነት ይገባል ወይንስ ያስገባል?

አምላክ ገነት የመግባትም ሆነ የማስገባት መብት አለው፡፡ ገነት ውስጥ ተገኝቶ ከሕዝቡ ጋር መሆኑ አምላክነቱን ውድቅ የሚያደርገው እንዴት ሆኖ ነው? የእግዚአብሔር የማዳን ዓላማ የሰው ልጆችን በሙሉ በፍጥረት ጅማሬ ላይ ወደነበረው ወደዚያ ፍፁም ወደሆነ ሕበረት መመለስ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በመስቀል ላይ ዋጋን በከፈለው በከበረው የትንሣኤ አካል ሆኖ ፊቱን እያየን በመንግሥተ ሰማያት ውስጥ እንደምንኖር ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ይህ ከሁሉም የላቀ ደስታን የሚያጎናፅፍ የክርስቲያኖች ተስፋ ነው፡፡ የትንሣኤ አካሉ መለኮታዊ ክብርን ከመጎናፀፉ ሌላ ከኛ የትንሣኤ አካል የተለየ ባለመሆኑ “አዲሱ የወይን ጠጅ” ተብሎ የተጠቀሰውን ሰማያዊ “የወይን ጠጅ” መጠጣትን ጨምሮ እኛ በመንግሥተ ሰማያት ውስጥ ማድረግ የምንችላቸውን ነገሮች ሁሉ ማድረግ ይችላል፡፡ በቁርኣን ውስጥ የተገለፀው የሙስሊሞች ገነት ግን የወይን ጠጅ እንደ ልብ የሚጠጣበት ቦታ ከመሆኑም በተጨማሪ ሙስሊም ወንዶች ቁጥር ስፍር ከሌላቸው ሴቶች ጋር ፍትወት እየፈፀሙ የሚኖሩበት ቦታ መሆኑን ቁርኣን ይናገራል፡፡[11] በእስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ ደግሞ አንድ ሙስሊም ወንድ በገነት ከ72 ሴቶች ጋር ጋብቻ እንደሚፈፅም ተጽፏል፡፡[12] ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በገነት እንዲህ ያለ ነገር አለመኖሩንና እንደ መላእክት በደስታ እንደምንኖር ነግሮናል (ሉቃስ 20:34-36፣ ዮሐንስ 14፡1-3)፡፡

ማጣቀሻዎች


[1] And [mention] Zechariah, when he called to his Lord, “My Lord, do not leave me alone [with no heir], while you are the best of inheritors.” (Sura 21:89)

[2]Vines Complete Expository Dictionary of Old and New Testament Words, Thomas Nelson Publishers, Nashville Camden New York, 1984, P. 319.

[3] “…Allah will come to them in a shape other than they know and will say, ‘I am your Lord.’ They will say, ‘We seek refuge with Allah from you. This is our place; (we will not follow you) till our Lord comes to us, and when our Lord comes to us, we will recognize Him.’ Then Allah will come to then in a shape they know and will say, ‘I am your Lord.’ They will say, ‘(No doubt) You are our Lord,’ and they will follow Him. Then a bridge will be laid over the (Hell) Fire…” (Sahih al-Bukhari, Volume 8, Book 76, Number 577)

[4] “Not every one that saith unto me, Lord, Lord, shall enter into the kingdom of heaven; but he that doeth the will of my Father which is in heaven.” (KJV) John 7:21

[5] As to the phrase, “This day have I begotten thee,” there is a difference of view among both ancient and modern expositors. The word “begotten” (γεγέννηκα) naturally suggests μονογενὴς, and is hence taken by some as referring to the eternal generation of the Son; in which case it can have had no application in any conceivable sense to the human type. “This day” has also in this case to be explained as denoting the ever-present today of eternity. So Origen, in a striking passage,”It is said to him by God, to whom it is always today, for God has no evening, nor (as I deem) any morning, but the time which is coextensive with his own unbegotten and eternal life is (if I may so speak) the day in which the Son is begotten, there being thus found no beginning of his generation, as neither is there of the day.” Athanasius takes the same view; also Basil, Primasius, Thomas Aquinas, and many others. Source: Pulpit Bible Commentary

[6] The translation of the verb as “the Son Himself also will be subjected to the One” is very misleading. It is taken as a passive, whereas the exegesis demands that it should be taken as a middle voice which means that the Lord Jesus Christ at the completion of His mediatorial work subjects Himself to the One who had subjected all things unto Him. It is a voluntary act and not a compulsory subjugation of one person of the Trinity to the other. This is not something which took place while the Lord Jesus was the God-Man on earth, but it is something that will take place in the future when all people will be made subject unto Christ, and then He will finally subject Himself with the finished work of redemption before God the Father. (Spiros Zodhiates, New American Hebrew-Greek Key Word Study Bible, 1990, p. 1530)

[7] F.F. Bruce, Are the New Testament Documments Reliable?: Intervarsity Press; Downers Grove, III, Fifth Revised Edition, 1992, pp. 73-74.

[8] Sahih al-Bukhari, Vol. 7, 71:660

[9] Sahih Muslim 39 ፡ 6757

[10] Sahih al-Bukhari Vol. 4, 54 ፡ 516

[11] فِيهِنَّ قَاصِرَاتُ الطَّرْفِ لَمْ يَطْمِثْهُنَّ إِنسٌ قَبْلَهُمْ وَلَا جَانٌّ [٥٥:٥٦]

“በውስጣቸው ከበፊታቸው (ከባሎቻቸው በፊት) ሰውም ጃንም ያልገሰሳቸው ዓይኖቻቸውን (በባሎቻቸው ላይ) አሳጣሪዎች (ሴቶች) አልሉ፡፡” (ሱራ 55፡56፣ 38፡52፣ 44፡54፣ 52፡20፣ 56፡22 78፡33፣)

[12] Sunan al-Tirmidhi Vol. IV, ch. 21, hadith 2687


 

የኢየሱስ ማንነት ጉዳይ (ክፍል 1)

የኢየሱስ ማንነት ጉዳይ (ክፍል 3)

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ