መግብያ

መግብያ

ጊዜው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1970ዎቹ ውስጥ ሲሆን አሕመድ ዲዳት የተሰኙ ሙስሊም ዐቃቤ እምነት በዓለም ዙርያ በመዘዋወር ስለ እስልምና በቂ ዕውቀት ያልነበራቸውን ክርስቲያን አገልጋዮች የሚሞግቱበትና ክርስቲያናዊ አስተምህሮዎችን የሚያብጠለጥሉ ትንንሽ መጽሐፍትን በገፍ እያሳተሙ የሚያሰራጩበት ወቅት ነበር፡፡ ለእስላማዊ ሙግቶች የተዘጋጁ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እምብዛም ባለመኖራቸው እንዲሁም ሙስሊም ወገኖች ሆነ ብለው ለክርክር የሚመርጧቸው ክርስቲያኖች የክርክር ልምድ የሌላቸውና ስለ እስልምና ያላቸው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ሚስተር ዲዳት በአብዛኞቹ መድረኮች ላይ አሸናፊ መስለው ይታዩ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ ጥሩ ዕውቀትና ልምድ ያለው ክርስቲያን ምሑር ከሚስተር ዲዳት ጋር ቢወያይ የሚል መሻት በብዙዎች ዘንድ ነበር፡፡ ዲዳት በወቅቱ ዓለም አቀፍ እውቅና ለነበራቸው ክርስቲያን ምሑር ጆሽ ማክዱዌል ወደ ደቡብ አፍሪካ በመምጣት ሙግት እንዲገጥሟቸው በደብዳቤ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ በ1981 ዓ.ም. ይህ የብዙዎች ምኞት  እውን ሆነ፡፡ ውጤቱም አሕመድ ዲዳትን የመሳሰሉ ሙስሊም ወገኖች ስለ እስልምና ዕውቀት የሌላቸውንና የክርክር ልምድ የሌላቸውን ክርስቲያኖች በመምረጥ ከመገዳደር ይልቅ ልምድና ዝግጅት ካላቸው ክርስቲያን ምሑራን ጋር ቢወያዩ ሊሆን የሚችለውን ነገር በግልፅ ያሳየ ነበር፡፡

የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በተመለከተ አሕመድ ዲዳት የሚያራምዱት አቋም አብዛኞቹ ሙስሊሞች ከሚያምኑት የተለየ ቢሆንም (በተለይም ደግሞ ራሳቸው ሚስተር ዲዳት ከነበሩበት የሱኒ እስልምና አስተምሕሮ ጋር የሚጣረስ ቢሆንም) ሙስሊም ሊቃውንት የክርስትናን አስተምሕሮ የሚገዳደር ሆኖ እስከተገኘ ድረስ ከቁርኣንና ከእስላማዊ ትውፊት ጋር ቢፋለስ ግድ የሌላቸው በሚመስል ሁኔታ ተቃውሞን ከማሰማት ይልቅ ትምህርቶቻቸውን እየተረጎሙ ማሰራጨትና የርሳቸውን የመከራከርያ ነጥቦች ማስተጋባታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የርሳቸውን እግር ተከትለው የወጡት ዶ/ር ዛኪር ናይክን የመሳሰሉ ሙስሊም ተሟጋቾች በዚህ ዘመን እነዚህን የመከራከርያ ሐሳቦች እና የክርክር ዘዴዎች በመጠቀም ልምድ የሌላቸውን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ሲሞግቱ ይስተዋላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ዶ/ር ዛኪር ናይክ ሩክኑዲን ፒኦ ከተሰኙ እምብዛም ከማይታወቁ ሚስዮናዊ ጋር የክርስቶስን ስቅለት በተመለከተ ሙግት በገጠሙበት ወቅት የዲዳትን ሙግቶች ቃል በቃል፣ መስመር በመስመር ቀድተው ማቅረባቸው የሚታወቅ ነው፡፡

አሕመድ ዲዳት ብዙ አዳዲስ የሙግት ሐሳቦችንና ስልቶችን ለሙስሊሞች ያስተዋወቁ የ20ው ክፍለ ዘመን ታላቅ ሙስሊም ዐቃቤ እምነት እንደነበሩ በብዙዎች ይነገርላቸዋል፡፡ ጥሩ የንግግር ክህሎትና በራስ መተማመን የነበራቸው ተሟጋች መሆናቸውም የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ነገር ግን የተሳሳተ ትምህርት በጥሩ ቃላት ተከሽኖ ለሰዎች ጆሮ በሚጣፍጥ መልኩ መቅረቡ ስህተትነቱን እንደማይለውጥ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ስለዚህ የሰውየው መከራከርያ ነጥቦች ማራኪ ከሆነው ፈገግታቸውና አስደማሚ ከሆነው የቃላት አሰዳደር ክህሎታቸው ተፋተው በእውነት ሚዛን ላይ ሲቀመጡ እጅግ የቀለሉ ሃቀኝነትና ተዓማኒነት የራቃቸው ፈጣን ንግግሮች ብቻ ሆነው ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ ጥልቀት ባለው ጥናት ላይ ያልተመሠረቱ የቃላት ጫወታዎች ሲሆኑ መጽሐፍ ቅዱስንና ቁርኣንን የማያነበውን ብዙኃኑን ሕዝብ ለማደናገር ሆነ ተብለው የተቀነባበሩ አሳሳች ፈጠራዎች ናቸው፡፡ ከአሕመድ ዲዳት ጋር ከተወያዩ ክርስቲያን ምሑራን መካከል ይህንን እውነታ በተሳካ ሁኔታ ፍንትው አድርገው በአደባባይ ማሳየት የቻሉት ጆሽ ማክዱዌል ናቸው፡፡

ዲዳት ስለ ክርስትናና ስለ እስልምና ያሰራጯቸው የተሳሳቱ መረጃዎች እንዳሉ ሆነው የእምነት ወንድሞቻቸው የሆኑት ሙስሊሞች ክርስቲያኖችን በሩቁ ከመሸሽ ይልቅ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንዲችሉ ያበረታቱና ምሳሌ የሆኑ ሰው በመሆናቸው ለዘመናዊው የክርስቲያን-ሙስሊም ውይይት መፋፋም ያደረጉት አስተዋፅዖ እውቅና ሊሰጠው ይገባል ብለን እናምናለን፡፡

አሕመድ ሁሴን ዲዳት (Ahmed Hussein Deedat) በ1918 ዓ.ም. በሕንድ አገር የተወለዱ ሲሆን ገና የ9 ዓመት ልጅ ሳሉ ነበር አባታቸውን ተከትለው ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀኑት፡፡ ለዐቃቤ እምነት አገልግሎታቸው ምሳሌ የሆናቸው ሚስተር ፋይርፋክስ የተሰኘ ከክርስትና ወደ እስልምና የተለወጠ ሰው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እኚህ ሰው ከ1942 – 1996 ዓ.ም. የቆየ የ50 ዓመታት አገልግሎት የነበራቸው ሲሆን “ለእስልምና መስፋፋት ላበረከቱት አስተዋፅዖ” በ1986 የንጉሥ ፈይሰል ዓለም አቀፍ ሽልማት ከሳዑዲ አረብያ መንግስት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በእስልምናው ዓለም ታላቅ ሽልማት እንደሆነ የሚቆጠረው ይህ ሽልማት የሚስተር ዲዳት ዝና በመላው ዓለም በሚገኙ ሙስሊሞች ዘንድ እንዲናኝ ምክንያት ሆኗል፡፡ የኒህ ሰው የ 50 ዓመታት አገልገሎት ወደ ፍጻሜ የመጣው በ1996 ዓ.ም. እንደ ድንገት ባጋጠማቸው ከአንገታቸው በታች የነበረውን አካላቸውን ሁሉ ሽባ ባደረገ እስትሮክ ምክንያት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ መንቀሳቀስም ሆነ መናገር የተሳናቸው ሚስተር ዲዳት በንጉሥ ፈይሰል ሆስፒታል የህክምና ርዳታ ሲደረግላቸው በነበረ ጊዜ ትንሽ ተሽሏቸው የዐይን እንቅስቃሴ ተግባቦት ተለማምደው ነበር፡፡ ሚስተር ዲዳት ለ9 ዓመታት ከአልጋ ሳይነሱ በደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ በባለቤታቸው ሐዋ ዲዳት እንክብካቤ ሲደረግላቸው ከቆየ በኋላ በ87 ዓመታቸው ኦገስት 8/2005 ይህችን ዓለም በሞት ተሰናብተዋል፡፡ ዋና ጽሕፈት ቤቱን በደርባን፣ ደቡብ አፍሪካ ያደረገው “ኢስላሚክ ፕሮፓጌሽን ሴንተር ኢንተርናሽናል” በመባል የሚታወቀው ድርጅት መሥራችና መሪ የነበሩ ሲሆን ከህልፈታቸው በኋላም ቢሆን ድርጅቱ ውርሶቻቸውን የማስቀጠል ኃላፊነቱን በትጋት እየተወጣ ይገኛል፡፡

ጀስሊን (ጆሽ) ማክዱዌል በ1939 ዓ.ም. የተወለዱ ሲሆን ዓለም አቀፍ ክርስቲያን አስተማሪና ዕውቅ ደራሲ ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታና አዳኛቸው መሆኑን አውቀው የተከተሉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳሉ ክርስትናን የሚቃወም መጽሐፍ ለመጻፍ ጥናት ያደርጉ በነበረበት ወቅት ባገኟቸው መረጃዎች ምክንያት እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በክርስቲያኑ ዓለም ውስጥ ዕውቅናን ያተረፈላቸውን “Evidence that Demands a Verdict” (ፍርድ የሚሻ ማስረጃ) በሚል ርዕስ የጻፉትን ቀዳሚ መጽሐፋቸውን ጨምሮ ወደ 115 የሚሆኑ መጻሕፍትን በግላቸውና ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን ጽፈዋል፡፡ ጆሽ ማክዱዌል በአገልግሎታቸው ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅዖ በ1982 ከግሪንሊፍ ስኩል ኦፍ ሎው (አሁን ትሪኒቲ ሎው ስኩል በመባል ከሚታወቀው) የክብር ዶክትሬት የተበረከተላቸው ሲሆን በተለያዩ ዓለማዊና መንፈሳዊ ዘርፎች ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ዲግሪዎችን አግኝተዋል፡፡ የ 77 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት ጆሽ ማክዱዌል በተለያዩ ክርስቲያናዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትምህርቶችንና ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ እንዲሁም የተለያዩ መጽሐፍትንና መጣጥፎችን ይጽፋሉ፡፡ ከልጆቻቸው መካከል አንዱ የሆነው ዶ/ር ሺያን ማክዱዌል የእሳቸውን ፈለግ በመከተል በክርስቲያን ዓቀበተ እምነት አገልግሎት ላይ ተሰማርቶ አበረታች ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ሙግት በ1981 የተደረገ ሲሆን ቦታው ደግሞ ደርባን፣ ደቡብ አፍሪካ ነው፡፡ ዝናባማ የነበረው የደርባን የአየር ሁኔታ ሳይበግራቸው ይህንን ታሪካዊ ክርክር ለመከታተል በስታዲየሙ ከተገኙ ወደ 6,000 ከሚሆኑ ታዳሚያን መካከል አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ ሁለቱም ወገኖች እያንዳንዳቸው ለመክፈቻ ንግግር 50 ደቂቃዎች፣ ለመልስ ንግግር 10 ደቂቃዎች እንዲሁም ለመዝጊያ ንግግር 3 ደቂቃዎች ነበሯቸው፡፡ ይህ ክርክር በድምፅና በምስል ተቀድቶ የሚገኝ ቢሆንም ብዙ ሙስሊም ወገኖች ስለመከናወኑ እንኳ መናገር የሚፈልጉ አይመስሉም፡፡ የሚስተር ዲዳትን ትምህርቶችና ክርክሮች በሚያሰራጩ ብዙ እስላማዊ ድረ-ገፆች ላይም ሆነ የካሴት መሸጫ መደብሮች ውስጥ አናገኘውም፡፡ ምናልባት የክርክሩን ውጤት ስላልወደዱት ሊሆን ይችላል፡፡ የክርክሩ ርዕስ “ክርስቶስ ተሰቅሏልን?” የሚል ሲሆን ሚስተር ዲዳት የሙግትና የንግግር ክህሎታቸውን አሳይተውበታል፡፡ ለሚስተር ዲዳት የሙግት ሐሳቦች መልስ በመስጠት ረገድ ጆሽ ማክዱዌል ያሳዩት ከፍተኛ ብቃትም የሚደነቅ ነበር፡፡ በሁለቱ የሃይማኖት ሰዎች መካከል የነበረው ጨዋነት የተሞላበት አቀራረብና መከባበር ደስ የሚያሰኝና ለአገራች ዐቃቤ እምነታውያንም ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው፡፡

በአደባባይ በንግግር የተደረጉ ክርክሮችን ወደ ጽሑፍ ለውጦ ሰፊው ሕዝብ ተረጋግቶ የተባሉትን ነገሮች እንዲመረምር ማስቻል በሌላው ዓለም የተለመደ ቢሆንም ነገር ግን በአገራችን የሚታወቅ አይመስልም፡፡ ምናልባትም ይህ መጽሐፍ በዓይነቱ የመጀመርያው ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረው ጽሑፍ በቀጥታ በመድረክ ላይ የተደረገ ንግግር ትርጉም እንደመሆኑ መጠን አንባቢውም ይህንን በመረዳት በዚሁ መንፈስ ያንብበው እንላለን፡፡[1]

መልካም ንባብ!


[1] የክርክሩን ቪድዮ ለመመልከት የሚፈልግ ሰው በተከታዩ የዩቲዩብ አድራሻ ማግኘት ይችላል፡ www.youtube.com/watch?=-7nxQ5_QlvE


ክርስቶስ ተሰቅሏልን? ማውጫ