ምዕራፍ 10
የመጽሐፍ ቅዱስ ህልውና
ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ ካቆምንበት እንቀጥላለን
በዚህ ርዕስ ስር አሕመዲን ጀበል የመጽሐፍ ቅዱስን ተዓማኒነት በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ከመጽሐፋቸው ርዕስ ጋር የሚሄድ ባይሆንም ነገር ግን የመጽሐፋቸው ማሳረጊያ ለማድረግ መርጠዋል፡፡
ጠያቂው መጽሐፍ ቅዱስ መታመን የለበትም ለሚለው ሙግታቸው እንደ ማስረጃ የሚጠቅሱት የመጀመርያው ነጥብ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊት ያንፀባረቋቸውን ድካሞች ነው፡፡ ተከታዮቹንም ነጥቦች አንስተዋል፡-
- ሐዋርያት ኢየሱስ የሚላቸውን ለመረዳት ሲሳናቸው ነበር (ማርቆስ 4፡13፣ 6፡52፣ 8፡18-17፣ 9፡32፣ ሉቃስ 8፡9 እና 9፡45)፡፡ ኢየሱስ እምነት እንደጎደላቸው ነግሯቸዋል (ማቴዎስ 8፡26)፡፡ ነቅተው እንዲጠብቁ ሲያዛቸው ተኝተው አግኝቷቸዋል (ማቴዎስ 26፡36-43)፡፡ ኢየሱስ ሲያዝ “አናውቀውም” በማለት ክደውታል (ማርቆስ 14፡66-72)፡፡ ከስቅለቱ በኋላ ወደ ቀድሞ ሥራቸው (አሣ ወደማጥመድ) ተመልሰዋል (ዮሐንስ 21፡2-3)፡፡ ኢየሱስን የከዳው ሐዋርያ የነበረው ይሁዳ ነበር (ማቴዎስ 26፡14-16)፡፡ ሰይጣን ሐዋርያ ወደ ነበረው ወደ ይሁዳ ገባ፤ ወደ ጴጥሮስም ለመግባት ሞክሮ ነበር (ሉቃስ 22፡3፣ 31)፡፡ ኢየሱስ ዋናውን ሐዋርያ ጴጥሮስን ሰይጣን ብሎታል (ማቴዎስ 16፡23)፡፡ የኢየሱስ ትንሣኤ ምስክሮች ከነበሩት መካከል አንዷ የነበረችው መግደላዊት ማርያም በሰባት አጋንንት የተያዘች ነበረች፤ ምስክርነቷንም ሐዋርያት አላመኑም (ማርቆስ 16፡9፣ 10)፡፡ ሐዋርያት ሴቶች መቃብሩ ባዶ መሆኑን ሲነግሯቸው ቅዠት መስሏቸው አላመኗቸውም (ሉቃስ 24፡11)፡፡
ጠያቂው ከላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች በመጥቀስ “ታዲያ የነዚህ ሰዎች ጽሑፍና ምስክርነት ይታመናልን?” የሚል ጥያቄ ይሰነዝራሉ፡፡
የታሪክ ተመራማሪዎች የአንድን ጥንታዊ ሰነድ ሐቀኝነት ከሚመዝኑባቸው መንገዶች መካከል አንዱ “የሐፍረት መስፈርት” (The Criteria of Embarrassment) ይሰኛል፡፡ ይኸውም አንድ ሰው ስለ ራሱ ወይም ስለሚወደውና ስለሚያከብረው ሰው እርሱ ራሱ ሊያፍርበትና ሊሸማቀቅበት የሚችለውን ነገር ከጻፈ የታሪኩ ተዓማኒነት ከፍ ያለ ነው የሚል ነው፡፡ አሕመዲን ጀበል በብዙ ሙስሊሞች ዘንድ “የታሪክ ምሑር” ተብለው የሚሞካሹ ሆነው ሳሉ ይህንን መሠረታዊ ግንዛቤ ማጣታቸው አስገራሚ ነው! የሐዋርያት ድካምና ውድቀት ያለ ምንም መሸፋፈን መነገሩ ምስክርነታቸውን እንድናምን የሚያደርግ እንጂ እንድንጠራጠር የሚያደርግ አይደለም፡፡ ይልቁኑ ምንም ድካም ያልነበረባቸው ፍፁማን ሰዎች እንደነበሩ በተጋነነ ሁኔታ ቢጻፍ ነበር ምስክርነታቸውን በጥርጣሬ ማየት ተገቢ የሚሆነው፡፡ ድካማቸውንና ውድቀታቸውን በተመለከተ አብዛኞቹ ሰዎች በማያደርጉት ሁኔታ ሳይዋሹ በግልፀኝነትና በሐቀኝነት እንዲጻፍ ያደረጉ ሰዎች ምስክርነት ካልታመነ የማን ሊታመን ነው?
ይሁዳ ወንጌልን አልጻፈም፤ ስለ ኢየሱስ ትንሳኤም አልመሰከረም፡፡ ከአሥራ ሁለቱ መካከል አንዱ ስለነበረና ኢየሱስን በገንዘብ ስለለወጠ የተቀሩትን የአሥራ አንዱን ምስክርነት እንዳናምን ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ መግደላዊት ማርያም ከሰባት አጋንንት ነፃ በማውጣት ኢየሱስ ተዓምር ያደረገላት ነፃ የወጣች ሴት በመሆኗ ምስክርነቷ ከማንም በላይ የሚታመን ነው፡፡ ዛሬም በክርስቶስ አምነው ከአጋንንት ነፃ በመውጣት የሚያገለግሉት ብዙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይገኛሉ (ኤፌሶን 2፡1-7)፡፡
ጠያቂው “ነቢይ” በማለት የሚከተሏቸው ሰው ከአጋንንት ነፃ እንዳልነበሩ በአንደበታቸው መናገራቸው ሳያሳስባቸው ከአጋንንት ነፃ የወጣችው የመግደላዊት ማርያም ጉዳይ ለምን እንዳሳሰባቸው የሚያስገርም ነው (የመጀመርያውን ምዕራፍ 36ኛ ቁጥር ይመልከቱ)፡፡
ኢየሱስ ሲያዝ ሐዋርያቱ እንዲሸሹ ያደረጋቸው ስለ መሲሁ ተልዕኮ የነበራቸው የተሳሳተ አስተሳሰብ ነበር፡፡ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን በነበረው የአይሁድ አስተሳሰብ መሠረት መሲሁ ጠላቶቻቸውን ድል ነስቶ የሚነግሥ እንጂ በጠላት ተይዞ የሚገደል አልነበረም፡፡ ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው ተስፋ እንዲቆርጡና እንዲበተኑ ያደረጋቸው፡፡ ኢየሱስ ስለ ሞቱ ሲናገር በሰማ ጊዜ ጴጥሮስ ለብቻው ወስዶ ሊገሥፀው የሞከረው ይህ የተሳሳተ አመለካከት ስለነበረው ነበር፡፡ የኢየሱስ ምላሽ ግን “ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል” የሚል ነበር (ማቴዎስ 16፡22-23)፡፡ የእግዚአብሔር ዓላማ ክርስቶስ በመስቀል ሞቶ ዓለምን እንዲያድን ቢሆንም ጴጥሮስ ግን እንደ ዘመኑ አይሁድ ሁሉ መሲሁ እንደማይሰቀል ያምን ስለነበር ኢየሱስ ለመስቀል ራሱን አሳልፎ እንዳይሰጥ በመምከር ሳያውቀው የእግዚአብሔር ፈቃድ ተቃዋሚ ሆኖ ነበር፡፡ “ሰይጣን” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ተቃዋሚ”፣ “ከሳሽ” ወይም “ተገዳዳሪ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን “ሰይጣን” የተሰኘውን ክፉ መንፈስ ወይንም ደግሞ ማንኛውንም ተቃዋሚና ተገዳዳሪ የሆነ አካል ለማመልከት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ ዘኁልቁ 22:22፣ 22:32፣ 1ሳሙኤል 29:4፣ 2ሳሙኤል 19:22፣ 1ነገሥት 5:4፣ 11:14፣ 11:23፣ 11:25፣ ወዘተ. በመሳሰሉት ክፍሎች ላይ “ሰይጣንን” በማያመለክት ሁኔታ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በተለያዩ መንገዶች ተተርጉሟል፡፡ ኢየሱስ ጴጥሮስን በዚህ ሁኔታ ሲገስፀው ተቃዋሚ መሆኑን ለማመልከት ብቻ ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ክርስቶስን ከተልዕኮው ለማደናቀፍ የሚፈልገውን የሰይጣንን ሐሳብ በማስተናገዱ ምክንያት የሐሳቡ አመንጪ የሆነው ከበስተጀርባው የሚገኘውን ሰይጣንን ለመገሰፅ ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡
ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊት ብዙ ድካሞች የነበሩባቸው ቢሆኑም መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ግን ድካሞቻቸው በብርታት ተለውጠዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚናገረው በይሁዳ ቦታ የተተካው ማቲያስን ጨምሮ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል የተፈጥሮ ሞት የሞተው ሐዋርያው ዮሐንስ ብቻ ነበር፡፡ አሥራ አንዱ ግን ስለ እምነታቸው ሰማዕታት ሆነዋል፡፡ በአንድ ወቅት ፈሪዎችና ተጠራጣሪዎች የነበሩ ሰዎች ከመቅፅበት ተለውጠው በድፍረት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነስቶ እንደታያቸው በሃይማኖት መሪዎችና በባለ ሥልጣናት ፊት ቆመው እንዲመሰክሩ፣ ምስክርነታቸው እውነት መሆኑን ደግሞ እስከ ሞት ድረስ በመታመን እንዲያረጋገጡ፣ የዓለምንም ታሪክ እስከ ወዲያኛው እንዲለውጡ ያደረጋቸው አንዳች ተዓምር መኖር አለበት! ጌታ ኢየሱስ በመጨረሻዋ ሰዓት ጥለውት ስለሸሹ አልጣላቸውም፡፡ ከትንሣኤው በኋላ እንደገና እንዲመለሱ ዕድልን በመስጠት ይቅር ብሏቸዋል፤ ለታላቅ አገልግሎትም ሾሟቸዋል (ማቴዎስ 28፡18-20፣ ሉቃስ 24፡45-53፣ ዮሐንስ 20፡19-31፣ 21፡15-20፣ የሐዋርያት ሥራ 1-14)፡፡ መንፈስ ቅዱስንም በመላክ ኃይልን ሰጥቷቸዋል (የሐዋርያት ሥራ 2፡1-21)፤ ከዚህ የተነሳ የሐዋርያት አገልግሎት በድንቅ እና በአስገራሚ ተዓምራት የታጀበ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 2፡43፣ 3፡1-11፣ 5፡15-16)፡፡ ዲያብሎስ የተሰኘው እርኩስ መንፈስ ከሚታወቅባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ክስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ይቅር ያላቸውንና ከድካማቸው ያነሳቸውን ሰዎች በቀደመው ኃጢአታቸውና ድካማቸው ይከሳቸዋል፡፡ በአሕመዲን ጀበል ጽሑፍ ውስጥም የሚንጸባረቀው ይኸው ነው፡፡
ጠያቂው የአራቱን ወንጌላት ተኣማኒነት አጠራጣሪ ለማስመሰል ምሑራን ስለተጻፉበት ቦታና ዘመን እርግጠኛነት በጎደላቸው ቃላት መናገራቸውን እንደ ማስረጃ ይጠቅሳሉ፡፡ ገፅ የሚሞሉ ረጃጅም ጥቅሶችን የጠቀሱ ሲሆን አብዛኞቹን ሆነ ብለው ከአውድ በመገንጠል እና ሲያሻቸው የራሳቸውን ሐሳብ በመጨመር አንዳንዴም በገፁና በቦታው ላይ የሌለውን የራሳቸውን ቅጥፈት በማከል ጽፈዋል፡፡ ምናልባት የእሳቸውን መጽሐፍ የሚያነቡ አብዛኞቹ ሰዎች የተጠቀሱትን መጽሐፍት አግኝተው እንደማያነቡ አለዚያም እሳቸው ያሉትን አምኖ ከመቀበል ውጪ ገፁን እንደማይገልጡ አስበው ይሆናል፡፡ አንባቢያን በትክክል የተባሉትን ነገሮች ማየት እንዲችሉ ጠያቂው በትክክል ያልጠቀሷቸውን ክፍሎች ከትክክለኞቹ ጥቅሶች ጋር በሳጥን ጎን ለጎን በማስቀመጥ እናሳያለን፡፡
የሉቃስ ወንጌልን በተመለከተ ያነሷቸው ነጥቦች
አሕመዲን የጻፉት ስለ ሉቃስ ወንጌል የክርስቲያን ምሑራን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡- “ምናልባት የሉቃስ ወንጌል የተጻፈው በ60 ዓ.ም. ገደማ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ሉቃስ ክርስቲያን ከሆነ ቢያንስ አሥር ዓመት ወይም ከዚያ በላይ በክርስትና የቆየ ሊሆን ስለሚችልና ኢየሱስን በሥጋ የሚያውቁትን ብዙ ሰዎችን ሊያገኝ ወደሚችልበት ወደ ፖልስታይን ሳይሂድ አልቀረም፡፡ ምናልባትም ጳውሎስ በእስር ቤት በነበረበትን ዘመን ሉቃስ የኢየሱስን ምድራዊ ሕይወትና እንቅስቃሴ ለመመዝገብ ብዙ ጊዜ ሳይወስድበት አልቀረም፡፡ ስለእርሱ ብዙ ከሰማው ተነስቶ ስለ ጳውሎስ ሚስዮናዊ አገልሎትም ብዙ ሳይመረምር አልቀረም፡፡ … የማርቆስን ወንጌል መሠረት በማድረግ ሳይጽፍ እንዳልቀረ ስለሚታመን የሉቃስ ወንጌል የተፃፈው በኋለኛው ዘመን ሳይሆን አይቀርም፡፡ በወንጌሎቹ መካከል ያለው የሥነ ጽሑፍ መመሳሰልን በተመለከተም በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክርስቶስ ይሰብክ የነበረው አንድ አይነት የሆነ ወንጌል ስብከትን እንደሆነ ለመገመት ይቻላል፡፡ ዮሐንስ ማርቆስ በመጀመሪያ ከበርናባስና ከሳኦል ጋር ወደ አንፆኪያ በሄደ ጌዜ ሉቃስና ማርቆስ እዚያው ተገናኝተው የቆየ ትውውቅ ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡ 60ኛው ዓ.ም. የሉቃስ ወንጌል የተጻፈበት ጊዜ ነው ብሎ በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ተቀራራቢው ዓመት ነበር ብሎ መውሰድ ግን ይቻላል፡፡ የሉቃስ ወንጌል የት ቦታ እንደተፃፈ የተሠጠ አንዳችም ፍንጭ የለም፡፡ ምንም እንኳ ታሪኮቹ በቂሣርያ ሊጠናቀሩ ቢችሎም ከፓለስቲና ውጪ ሳይጻፍ እንዳልቀረ ግን ይገመታል፡፡ ሮምን፣ ቂሣሪያን፣ አካይን፣ ትንሹ ኢስያን እና አሌክሳንደራያን ጨምሮ የሚሰጡት ከግምታዊ አስተያየትነት አይዘሉም፡፡” |
መጽሐፉ የሚለው “ሉቃስ ስለ ጳውሎስና ስለ አሟሟቱ ምንም ዓይነት ተጨማሪ አሳብ ስላልጻፈ የሐዋርያት ሥራን ጽፎ የጨረሰው ጳውሎስ ከእስር ቤት ከመውጣቱና እንደገና ከመታሰሩ በፊት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ስለሆነም የሐዋርያት ሥራ በ63 እና 64 ዓ.ም. መካከል እንደጻፈ ይገመታል፡፡ ይህም የሉቃስ ወንጌል ከዚያ በፊት እንደተጻፈ ያመለክታል፡፡ ስለሆነም ሉቃስ ወንጌሉን ከ59-63 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንዳጠናቀቀ ይገመታል፡፡ ሉቃስ የማርቆስን ወንጌል እንደ ምንጭ ተጠቅሟል የሚሉ ምሑራን መጽሐፉ የተጻፈበትን ዘመን ወደ 70 ዓ.ም. ያመጡታል፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት ይህን ወንጌል እንደ አንዱ ምንጭ አድር ከመጠቀሙ በፊት የማርቆስ ወንጌል ተጽፎ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እስኪሰራጭ ድረስ ጊዜ ሳይወስድ እንዳልቀረ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የማርቆስ ወንጌል ቀደም ብሎ ተጽፎ ተቀባይነትን ካገኙት ወንጌላት እንደ አንዱ ሆኖ ካገለገለባት በኋላ በሮም የራሱን መጽሐፍ ጽፎ ይሆናል ብለው ይገምታሉ፡፡ ሉቃስ ከ63 ዓ.ም. በኋላ ጽፎታል የሚለው ግምት ግን ይህን ያህል ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው በየት ስፍራ እንደሆነ በውል አይታወቅም፡፡ በአማራጭነት የሚጠቀሱት አገሮች 1) ሉቃስ ብዙ ጊዜ ያሳለፈባት ፊልጵስዩስ፣ 2) ጳውሎስ ለሁለት ዓመታት የታሰረባት ቂሣርያ ወይም 3) ጳውሎስ ታስሮ የቆየባት ሮም ናቸው፡፡ ከእነዚህ በአንዱ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል፡፡ ሆኖም ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው በቂሣርያ ወይም በሮም በቆየባቸው ጊዜያት ይመስላል፡፡” (ቲም ፌሎስ የአዲስ ኪዳን መምሪያና ማብራሪያ በትምህርተ መለኮት ማስፍፊያ (ት.መ.ማ.) መልክ የተዘጋጀ፣ 1ኛ መጽሐፍ፣ ገፅ 339) |
ምርመራ
- ከ2ኛ የት.መ.ማ. መጽሐፍ ላይ እንደሆነ የጠቀሱት ሁሉ በ1ኛ መጽሐፍ ውስጥ እንጂ በ2ኛ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ አይደለም፡፡ 2ኛው መጽሐፍ ከሮሜ ጀምሮ ባሉት መልዕክታት ላይ የተጻፈ እንጂ ወንጌላትን የተመለከተ አይደለም፡፡
- አሕመዲን የጠቀሱት እና በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኘው የሐሳብ መመሳሰል ቢኖረውም በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረ አይደለም፡፡ ጸሐፊው ሐሳቡን በራሳቸው አባባል እንዳሰፈሩ ሳይሆን “ስለ ሉቃስ ወንጌል የክርስቲያን ምሑራን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-” ካሉ በኋላ ተጽፏል ያሉትን ሐሳብ በትዕምርተ ጥቅስ (“”) ውስጥ በማስቀመጥ ስለነገሩን የፈጸሙት ተግባር ከቅጥፈትና ታማኝነትን ከማጉደል ይቆጠራል፡፡
አሕመዲን የጠቀሱት “የጳውሎስ የወንጌል አገልግሎት ባልደረባ የነበረው ሉቃስ የዚህ ወንጌል ደራሲ መሆኑን ሁሉም የጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች በአንድ ድምፅ ይስማሙበታል፡፡ ምሑራን ሉቃስ የዚህ ወንጌል ጸሐፊ መሆኑን መጠራጠር የጀመሩት ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ምሑራን ጥርጣሬያቸውን ያቀረቡት ከሉቃስ ዘመን በኋላ ስለ ተነሱት የቤተ ክርስቲያን ችግሮች የሚዘግቡ አሳቦች በመጽሐፉ ውስጥ እንደሚገኙ በመግለፅ ነው፡፡ … እንደ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ሁሉ ስለ ሉቃስም ያለን መረጃ የተወሰነ ነው፡፡” (ቲም ፌሎስ፣ የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ በትምህርተ መለኮት ማስፋፍያ (ት.መ.ማ) መልክ የተዘጋጀ፣ 2ኛ መጽሐፍ፣ ገጽ 336 |
በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው ሙሉ ሐሳብ “የጳውሎስ የወንጌል አገልግሎት ባልደረባ የነበረው ሉቃስ የዚህ ወንጌል ደራሲ መሆኑን ሁሉም የጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች በአንድ ድምፅ ይስማሙበታል፡፡ ምሑራን ሉቃስ የዚህ ወንጌል ጸሐፊ መሆኑን መጠራጠር የጀመሩት ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ምሑራን ጥርጣሬያቸውን ያቀረቡት ከሉቃስ ዘመን በኋላ ስለ ተነሱት የቤተ ክርስቲያን ችግሮች የሚዘግቡ አሳቦች በመጽሐፉ ውስጥ እደሚገኙ በመግለፅ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ሉቃስ የዚህ ወንጌል ደራሲ አለመሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ መረጃ አልተገኘም፡፡ እንደ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ሁሉ ስለ ሉቃስም ያለን መረጃ የተወሰነ ነው፡፡ ከሦስቱ የጳውሎስ መልእክቶች እንደምንረዳው፣ ሉቃስ በሙያው ሐኪም የነበረ ሲሆን፣ የጳውሎስ የቅርብ ጓደኛና የሥራ ባልደረባ ነበር፡፡ ሉቃስ ሌሎች ስደትን ፈርተው ገሸሽ ባሉ ጊዜ ከጳውሎስ ያልተለየ ሰው ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ስለ ሉቃስ የምናውቃቸውን ነገሮች የምናገኘው ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ነው፡፡ (ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 336) |
ምርመራ
- አሁንም ከአንደኛ መጽሐፍ የጠቀሱትን ከሁለተኛ መጽሐፍ እንደሆነ በመግለፅ ስህተታቸውን ደግመዋል፡፡
- ሉቃስ የዚህ ወንጌል ደራሲ አለመሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ መረጃ አለመገኘቱን የሚናገረውን አረፍተ ነገር ሆነ ብለው ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- ሉቃስ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የቅርብ ወዳጅና በሙያው ኀኪም እንደነበረ የሚናገረውን ክፍል ቆርጠው በማስቀረት የማይታወቅ ሰው ለማስመሰል ጥረት አድርገዋል፡፡
አሕመዲን የጠቀሱት “ሉቃስ አይሁድ አልነበረም አንድን ሙሉ መጽሐፍ የጻፈ ብቸኛው አህዛብ ያደርገዋል፡፡ የት ተወልዶ እንዳደገ አናውቅም፡፡ በተጨማሪም ሉቃስ ጥሩ የታሪክ ጸሐፊ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ኢየሱስን በዓይኑ ባያየውም፣ ሉቃስ እንደ አንድ የታሪክ ጸሐፊ ስላመነበት ስለ ክርስቶስ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት አድርጓል፡፡ … ሉቃስ ይህንኑ መረጃ ለማግኘት የተጠቀመባቸውን መንገዶችን ይዘረዝርልናል፡፡ አንደኛው፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገሩ መዛግብትን አገላብጧል፡፡ ምናልባት ከእነዚህ መዛግብት መካከል የማቴዎስና የማርቆስ ወንጌላት ይገኙበት ይሆናል፡፡ ሁለተኛው፣ የዓይን ምስክሮችና የተከበሩ የቤተክርስቲያን መሪዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡ …ሁሉንም መረጃ ካሰባሰበና ታሪኮቹን ፈር ካስያዘ በኋላ፣ ሉቃስ ስለ ክርስቶስ በሚጽፈው መጽሐፍ ውስጥ የትኞቹ መካተት እዳለባቸው ወሰነ፡፡”(ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ ገፅ 337) |
በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው ሙሉ ሐሳብ “ሉቃስ አይሁድ አልነበረም አንድን ሙሉ መጽሐፍ የጻፈ ብቸኛው አህዛብ ያደርገዋል፡፡ የት ተወልዶ እንዳደገ አናውቅም፡፡ የምዕራብ ቱርክ ሰው ቢሆንም በአንጾኪያ አካባቢ እንዳደገ የሚያስረዳ መረጃ አለ፡፡ ሐኪም እንደመሆኑ ፣ ሉቃስ የግሪክን ባሕል እንደተማረ ምንም አያጠራጥርም፡፡ በተጨማሪም ሉቃስ ጥሩ የታሪክ ጸሐፊ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ኢየሱስን በዓይኑ ባያየውም፣ ሉቃስ እንደ አንድ የታሪክ ጸሐፊ ስላመነበት ስለ ክርስቶስ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት አድርጓል፡፡ እርሱ ስደትና ሞትን መቀበል ካለበት ጽናቱ በተራ ወሬ ላይ ሳይሆን በእውነተኛ መረጃ ላይ እንዲደገፍ ፈልጎ ነበር፡፡ ሉቃስ ይህንኑ መረጃ ለማግኘት የተጠቀመባቸውን መንገዶችን ይዘረዝርልናል፡፡ አንደኛው፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገሩ በጽሑፍ የሰፈሩ መዛግብትን አገላብጧል፡፡ ምናልባት ከእነዚህ መዛግብት መካከል የማቴዎስና የማርቆስ ወንጌላት ይገኙበት ይሆናል፡፡ ሁለተኛው፣ የዓይን ምስክሮችና የተከበሩ የቤተክርስቲያን መሪዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡ ለምሳሌ ሉቃስ የኢየሱስ እናት ከሆነችው ከማርያም ጋር በመነጋገሩ ምክንያት ታሪኳን ብቻ ሳይሆን በልቧ ውስጥ ስለነበረው ነገር ገልጾአል (ሉቃስ 2፡19)፡፡ ሁሉንም መረጃ ካሰባሰበና ታሪኮቹን ፈር ካስያዘ በኋላ፣ ሉቃስ ስለ ክርስቶስ በሚጽፈው መጽሐፍ ውስጥ የትኞቹ መካተት እዳለባቸው ወሰነ፡፡ እንደ ሌሎቹ የወንጌላት ጸሐፊዎች ሁሉ ታሪክን ብቻ አልጻፈም፡፡ ይልቁንም ስለ ክርስቶስ ለማስተማር ፈልጎ ነበር፡፡ ይህንንም ያደረገው ሰዎች ለእምነታቸው ጽኑ መሠረት እንዲኖራቸውና ክርስቶስን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ እርሱን እንዲያውቁ ለማድረግ ነበር፡፡ ሉቃስ መረጃውን በሚሰበስብበትና በሚጽፍበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ይመራው ነበር፤ ዛሬ በእጃችን ያለው ወንጌል በሰው የተጻፈ ታሪክ ብቻ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዳችን እንድናውቅ፣ እንድናምንና ከሕይወታችን ጋር እንድናዛምድ የሚፈልገውን እውነት ሁሉ እንዲጽፍ አድርጎታል፡፡” ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 337 |
ምርመራ
- ምንጩን በተመለከተ ስህተታቸውን ለሦስተኛ ጊዜ ደግመዋል፡፡
- ሉቃስ በአንጾኪያ አካባቢ እንዳደገ የሚያሳይ መረጃ መኖሩን የሚናገረውን አረፍተ ነገር ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- በክርስትና እምነቱ የነበረው ፅናት በተራ ወሬ ላይ ሳይሆን በእውነተኛ መረጃ ላይ የተደገፈ እንዲሆን መፈለጉን የሚናገረውን አረፍተ ነገር ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- ሉቃስ በጽሑፍ የሰፈሩ መዛግብን በመረጃ ምንጭነት መጠቀሙን የሚናገረውን ሐረግ ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- ሉቃስ የጌታን እናት ማርያምን ማነጋገሩንና ከእርሷ መረጃ ማግኘቱን የሚናገረውን አረፍተ ነገር ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- ሉቃስ መረጃዎቹን ሲያሰባስብ መንፈስ ቅዱስ ይመራው እንደነበርና በመንፈስ ቅዱስ ምሪት መጻፉን የሚናገረውን ክፍል ቆርጠው አስቀርተውታል፡፡
አሕመዲን የጠቀሱት
የመጽሐፍ ቅድስ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል፡- “የሉቃስ ወንጌል የተጸፈው በ60 ዓ.ም. ገደማ ይመስላል፡፡” (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ 5) |
መጽሐፉ የሚለው ሉቃስ ወዳጁ ለሆነው ቴዎፍሎስ በአክብሮት ሲጽፍ ያላያቸውን ነገሮች ካዩአቸው የዓይን ምስክሮች አረጋግጦ በብዙ ጥንቃቄ ተርኳል፡፡ የአጻጻፉ ዘዴ የተማረና በድርሰት ልዩ ሙያ ያለው ሰው መሆኑን ያሳያል፤ ሉቃ. 1፡1-4፤ ሐ.ሥ. 1፡1-3፡፡ ሉቃስ የጻፈው ታሪክ የአርኪኦሎጂ ምርመራ ትክክለኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ ጳውሎስ በሮም ታስሮ ሳለ “የሐዋርያትን ሥራ” በ64 ዓ.ም. ገደማ ከጻፈው ወንጌሉን ደግሞ ከዚህ በፊት በ62 ዓ.ም. ገደማ የጻፈ ይመስላል፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ገፅ 15) |
ምርመራ
- ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ገፅ 5” በማለት የጠቀሱት በተባለው ገፅ ላይ አይገኝም፡፡ ስለ ሉቃስ የሚናገረው ክፍል ገፅ 15 ላይ ይገኛል፡፡
- የተጻፈውን ቃል በቃል ካለመጥቀሳቸውም በላይ 62 ዓ.ም. የሚለውን ወደ 60 ዓ.ም. ለውጠውታል፡፡
- ይህ ክፍል ሉቃስ ከዓይን ምስክሮች አረጋግጦ እንደጻፈ፣ የተማረና በድርሰት ልዩ ሙያ የነበረው ሰው እንደሆነና እርሱ የጻፈው ታሪክ በአርኪኦሎጂ ምርመራ ትክክል መሆኑ የተረጋገጠ እንደሆነ ስለሚናገር አሕመዲን ጀበል ለሚነዙት ፕሮፓጋንዳ እጅግ አውዳሚ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሊጠቅሱት ያልወደዱት፡፡
በማስከተል ጠያቂው እንዲህ የሚል ጥያቄ ይሰነዝራሉ፡-
2. ከላይ ያየናቸው የክርስቲያን ምሑራን ሁሉም በስምምነት የጻፉት በጥርጣሬና ግምት ላይ ተመስርተው ነው፡፡ በመላምት ተንተርሰው ነው፡፡ ታድያ “ይሆናል” ፤ “ይገመታል” ፤ “ሊሆን ይችላል” ፤ “ይመስላል” ፤ “ሳይሆን አይቀርም” በሚሉ መላምቶች ተመስርተን እንዲሁም በማንና መቼ እንደተጻፈ ስምምነትና ተጨባጭ ማስረጃ በሌለበት የሉቃስ ወንጌል የአምላክ ቃል ነው፣ በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ ጻፈ” ወዘተ. ብለን በድፍረት መከራከር ከቶ እንደምን ይቻላል?
እነዚህን አስተያየቶች ከመጥቀሳቸው በፊት ጠያቂው ሉቃስ ስለ ወንጌሉ በመግቢያው ላይ የጻፈውን በመጥቀስ እንዲህ ብለዋል፡-
የሉቃስ ወንጌል 1፡1-4 “በእኛ መካከል ስለ ተፈፀሙት ነገሮች ብዙዎች ታሪኩን የተቻላቸው ያህል ጽፈውት ይገኛል ፤ ይህም ታሪክ ከመጀመሪያው አንስቶ የዐይን ምስክሮች የቃሉ አገልጋዮች የነበሩት ያስተላልፉልን ነው፡፡ ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ! እኔም በበኩሌ ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመርሁ በኋላ ፤ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ ፤ ይህንንም የማደርገው የተማርከው ነገር እውነተኛ መሆኑን እንድታውቅ ነው” ይላል፡፡ ታድያ ሉቃስ መቼ በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ ጻፈ? እዚህ ላይ “ብዙዎች ታሪኩን የተቻላቸውን ያህል ጽፈውት ይገኛል” ይላል፡፡ ይህ የሚያሳየን የቻሉትን ያህል መጻፋቸውን እንጂ መንፈስ ቅዱስ ያስጻፋቸውን ያህል እንዳልጻፉ ነው፡፡ ከችሎታቸው ጋር ነው የተያያዘው፡፡ ሉቃስ በመንፈስ ቅዱስ ተነድቼ ጻፍኩ መቼ አለ? በጥንቃቄ እኔው ጻፍኩ ነው ያለው፡፡ ታድያ ክርስቲያኖች ምን ነካቸው?
ጠያቂው ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት መገለጥ ያላቸው ግንዛቤ እስላማዊ በመሆኑ ይህንኑ አመለካከታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ ሙስሊሞች ቁርኣን “የተገለጠበትን” ሁኔታ ታንዚል ወይም ናዚል በማለት ይጠሩታል፡፡ ታንዚል ማለት “ከላይ የወረደ መገለጥ” ማለት ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ የነበረው ክርስቲያናዊ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ከላይ የወረደ መገለጥ ነው የሚል ሳይሆን የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት (በመመራት) የጻፉት ቃል ነው የሚል ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የነበራቸውን እውቀት፣ ባህል እና ቋንቋ እንዲጠቀሙ መንፈስ ቅዱስ ፈቅዷል፡፡ ጸሐፊያኑ “የመንፈስ ቅዱስ የትየባ ማሽኖች” ስላልነበሩ ሲጽፉ በችሎታቸው መጠን እንጂ ከችሎታቸው በላይ እንዲጽፉ አልተደረጉም፡፡ አቅማቸውና ነባራዊ ሁኔታዎች በፈቀዱላቸው መጠን ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን መልዕክቱ የእግዚአብሔር ስለሆነ በሰዎቹ አቅምና በነበረው ሁኔታ ሳይገደብ ለትውልዶች ብርሃን መሆኑን ቀጥሏል፡፡ ሉቃስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ እንደጻፈ ባይናገርም ነገር ግን የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች ጽሑፉን እንደ እግዚአብሔር ቃል በመቀበል መስክረውለታል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ሙሴ የጻፈውንና ሉቃስ የጻፈውን አንድ ላይ አጣምሮ በማስቀመጥ ሁለቱም መጻሕፍት እኩል ቅዱሳት መጻሕፍት መሆናቸውን አረጋግጧል!
“መጽሐፍ፦ የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፥ ደግሞ፦ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል ይላልና፡፡” 1ጢሞቴዎስ 5፡18፡፡
“የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” የሚለው ዘዳግም 25፡4 ላይ የሚገኝ ሲሆን “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” የሚለው ደግሞ ሉቃስ 10፡7 ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የሚያሳየን የሐዋርያት ዘመን ከማለፉ በፊት ቢያንስ የሉቃስ ወንጌል ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እኩል ተቀባይነት ማግኘቱን ነው፡፡ ሐዋርያው እንደ ዘዳግም ሁሉ የሉቃስ ወንጌልን በስም አለመጥቀሱ በወቅቱ የሉቃስ ወንጌል በክርስቲያኑ ማሕበረሰብ መካከል በሚገባ የሚታወቅ እንደነበረ ያሳያል፡፡ ስለዚህ የሉቃስ ወንጌል የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እራሱ አረጋግጧል ማለት ነው![1]
የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መቼ እንደተጻፉ ለማወቅ የተለያዩ ውጭያዊና ውስጣዊ መረጃዎችን ይጠቀማሉ፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሉቃስ ወንጌል ሁለተኛ ክፍል መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ዝርዝር ታሪካዊ ክስተቶችን በማካተቱ ምክንያት መቼ እንደተጻፈ ለማወቅ የሚያስችሉ በቂ መረጃዎችን ይሰጣል፡፡ በአጠቃላይ ለዘብተኛ እንዲሁም አጥባቂ ከሆኑት ሊቃውንት መካከል የሚበዙቱ የሐዋርያት ሥራ ከ63 ዓ.ም. በፊት የተጻፈ መሆኑን ይስማማሉ፡፡ ኮሊን ሐመር የተሰኙ የሮም ታሪክ ሊቅ የሐዋርያት ሥራ በ61 እና 62 ዓ.ም መካከል የተጻፈ መሆኑን የሚያሳዩ 17 ምክንያቶችን ዘርዝረዋል፡፡[2] ወንጌሉ ደግሞ ቀደም ሲል የተጻፈ በመሆኑ (ሉቃስ 1፡1 እና የሐዋርያት ሥራ 1፡1 ያነፃፅሩ) ቢያንስ ከ61 ዓ.ም. በፊት እንደተጻፈ መናገር ይቻላል፡፡ ጠያቂው የዘነጉት ትልቁ ቁምነገር የሊቃውንት ዋና ትኩረት ወንጌሉ በተጻፈበት ቁርጥ ባለ ጊዜ ላይ ሳይሆን የተጻፈበት ዘመን (Era) ላይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሰነድ ሐዋርያት እና የመስቀሉ ትውልድ በሕይወት በነበሩበት ዘመን ከተጻፈ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነትና ሥራ ለማወቅ አስተማማኝ ምንጭ መሆኑ ስለሚረጋገጥ ለተዓማኒነቱ በቂ ማስረጃ ነው፡፡
የሉቃስን ማንነት በተመለከተ በአዲስ ኪዳን ውስጥም ሆነ ከአዲስ ኪዳን ውጪ መረጃዎችን እናገኛለን፡፡ ሊቃውንት በሁለተኛው ክፍለ ዘመን መገባደኛ አካባቢ እንደተጻፈ የተናገሩለት አንድ ምንጭ የሉቃስ የትውልድ ከተማ አንፆኪያ መሆኗን ይናገራል፡፡[3] የሐዋርያው ጳውሎስ ወዳጅ እና በሙያው ኀኪም እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ፊልሞና 1፡24፣ ቆላስይስ 4፡14)፡፡ “እኛ” (We Sections) ተብለው የሚታወቁት የሐዋርያት ሥራ ክፍሎች ሉቃስ በፊልጵስዩስ ከተማ ይኖር እንደነበር፣ ከጳውሎስ ጋር አብሮ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱንና ወደ ሮም አብሮት መጓዙን ያስረዳሉ (16፡10-17፣ 2O፡5-I5፣ 21፡1-18፣ 27፡1-28፡16)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ 4፡10-14 ላይ አርስጦኮስ፣ ዮስጦስ እና ማርቆስ “ከተገረዙት ወገን” አብረውት የሚያገለግሉ ብቸኛ ወንድሞች መሆናቸውን ከገለፀ በኋላ ኤጳፍራ፣ ሉቃስና ዴማስን መጥቀሱ ሉቃስ አይሁዳዊ ላለመሆኑ እንደ ማስረጃ ይጠቀሳል፡፡ አሁን በእጃችን የሚገኘው ቀዳሚ የሆነው የሉቃስ ወንጌል የእጅ ጽሑፍ (180-200 ዓ.ም.)[4] የሉቃስን ስም ይዟል፡፡ “የሙራቶራውያን ቀኖና” በመባል የሚታወቀው በ170 ዓ.ም. አካባቢ የተጻፈው ጽሑፍ እና የቤተ ክርስቲያን አባት የሆነው የኤሬኔዎስ ጽሑፍ (180 ዓ.ም.) የወንጌሉ ጸሐፊ ሉቃስ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡[5] ቀዳሚያን ሰነዶች የዚህ ወንጌል ጸሐፊ ሉቃስ መሆኑን ቢያረጋግጡም ከ100 ዓመታት ወዲህ ግን አሳማኝ ያልሆኑ ምክንያቶችን እየፈጠሩ የወንጌሉ ጸሐፊ በመሆኑ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው የሚገልፁ የተወሰኑ ለዘብተኛ ምሑራን ተፈጥረዋል፡፡ በዚህች ምድር ላይ ምሑራን የማያቀነቅኑት መላምት የለም፡፡ በተለይ መንፈሳዊ መጻሕፍትን በተመለከተ የትኛውንም አማራጭ አመለካከቶች የሚደግፉ ለዘብተኛ ሊቃውንትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አመለካከቶቹ ትክክል መሆናቸውን ቀዳሚ የታሪክ ሰነዶችን በመጥቀስ ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ ማስረጃ አልባ አመለካከቶችን ማራገብ ርቱዕ ሙግት ሊሆን አይችልም፡፡
ሰር ዊልያም ራምሰይ የተባሉ እንግሊዛዊ የታሪክ ምሑር የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ተዓማኒነት እንደሌላቸው የሚያምኑ ሰው ነበሩ፡፡ በተለይም ደግሞ የሉቃስ ጽሑፍ የሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሁለተኛው ክፍለ ዘመን ሥራ እንደሆነ አጥብቀው ያምኑ ነበር፡፡ ነገር ግን እኚህ ምሑር በትንሹ ኢስያ (Asia Minor) ውስጥ የተለያዩ የሥነ ቁፋሮ ግኝቶችን ሲመረምሩ ሳሉ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው የሚገኙ ብዙ ነገሮች እውነት መሆናቸውን የሚያረጋግጡ የትየለሌ ማስረጃዎችን አገኙ፡፡ እኚህ ምሑር ሉቃስ መጽሐፉን የጻፈው በመጀመርያው ምዕተ ዓመት (ሐዋርያት በነበሩበት ዘመን) መሆኑን ብቻ ሳይሆን ሉቃስ ከታላላቅ የታሪክ ጸሐፊዎች መካከል መመደብ እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡[6]
የዮሐንስ ወንጌልን በተመለከተ ጸሐፊው ተከታዮቹን ነጥቦች በክርስቲያኖች ከተጻፉ መጻሕፍት ይጠቅሳሉ፡-
3. “በዮሐንስ ወንጌልና በሌሎች ሦስት ወንጌላት መካከል በግልጽ የሚታይ ልዩነት በመኖሩ የወንጌሉ ተአማኒነት አጠያየቂ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል፡፡ መልሱ ያለው ግን በወንጌሉ ምንጭና ዓላማ ላይ ነው፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ትዉፊት መሠረት ይህ ወንጌል የተጻፈው በዘብዴዎስ ልጅ በዮሐንስ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ የመጨረሻው የሕይወት ዘመኑን ያሳለፈው በኤፌሶን ሲሆን ከጌታ ሐዋርያት መካከል የመጨረሻው ሰው ነበር፡፡ ምንም እንኳ ይህ አባባል ተቃውሞ ቢገጥመውም እስከ ዛሬ ድረስ ከተሰነዘሩ ሌሎች መላምቶች ውስጥ ይሄኛው ይበልጥ ተቀባይነት አለው፡፡ በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት መጨረሻ አካባቢ ስለ ነበራቸው የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚታወቀው በጣም በጥቂቱ በመሆኑ የዚህን ወንጌል አወቃቀር አስመልክቶ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እጅግ አስቸጋሪ ሆኖአል፡፡” (ሜሪል ሲ.ቲኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ አሳታሚ፦ የኢትዮጵያ ቃለ ሕወት ቤተክርስታን የኮሚዮኒኬሽንና ስነ ጹሑፍ መምሪያ ገጽ 281)
አሕመዲን ጀበል የምሑራንን አቋም የሚጠቅሱበት መንገድ እጅግ ተዓማኒነት የጎደለው ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቅ የሆኑት ዶ/ር ቴኒ የተለያዩ ምሑራን የሚሰነዝሯቸውን አስተያየቶች ባገናዘበ መልኩ ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ቢናገሩም ነገር ግን የዮሐንስ ወንጌል ተዓማኒ መሆኑንና በዮሐንስ በራሱ የተጻፈ መሆኑን በተመለከተ የደረሱበትን ድምዳሜ እንዲህ አስቀምጠዋል፡፡
“አራተኛው ወንጌል የተጻፈው በሐዋርያው ዮሐንስ ሳይሆን ስሙ ዮሐንስ ተብሎ በሚጠራ አንድ ማንነቱ የማይታወቅ ሰው ነው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ መሠረት የለሽ ነው፡፡ ከኢራንየስ ዘመን ጀምሮ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን አበው እንደመሰከሩት የዚህ ወንጌል ጸሐፊ ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው፡፡ የእስክንድርያው ቀለሜንጦስ (190 ዓ.ም.)፣ አርጌንስ [ኦሪጎን] (220 ዓ.ም.)፣ ሂፓላይትስ [ሂጶሊጦስ] (225 ዓ.ም.)፣ ተርቱልያንና [ጠርጡሊያኖስ] (200 ዓ.ም.) የሙራቶራውያን ጽሑፍ (170 ዓ.ም.) በአንድነት የሚስማሙት የዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ መሆኑን ነው፡፡”[7]
በተጨማሪም ዶ/ር ቴኒ የወንጌሉ ጸሐፊ የኢየሱስ ደቀመዝሙር የነበረ መሆኑን የሚያሳዩ አራት ማስረጃዎችን ከወንጌሉ ይዘት በመነሳት አስቀምጠዋል፡፡[8] የወንጌሉ ጸሐፊ ዮሐንስ ስለመሆኑ ፅኑ እምነት መኖሩንም አበክረው ይናገራሉ፡፡[9]
አሕመዲን የጠቀሱት “ከአራቱ ወንጌሎች የትኞቹም ስለ ጸሐፊው የሚናገሩት ነገር እንደሌለ ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ ነገር ግን ይህ መጽሐፍ ከተጸፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ “የዮሐንስ ወንጌል” የሚል ስያሚ ተሰጠው፡፡ በዚህ መንገድ አንባቢያን ጸሐፊው ማን እንደሆነ ሊያውቁ ይችላሉ፡፡ ከጥንት ጊዜ አንስቶ የቤተክርስቲያን መሪዎች የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስ አራተኛውን ወንጌል እንደጻፈ ያምኑ ነበር፡፡ ይህ አመለካከት በአብዛኛው የክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ተይዞ ቆይቷል፡፡ … ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን የሆኑ ምሁራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ፡፡ (ቲም ፌሎስ የአዲስ ኪዳን መምሪያና ማብራሪያ በትምህርተ መለኮት ማስፍፊያ (ት.መ.ማ.) መልክ የተዘጋጀ፣ 1ኛ መጽሐፍ፣ ገፅ 440) |
በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው ሙሉ ሐሳብ “ከአራቱ ወንጌሎች የትኞቹም ስለ ጸሐፊው የሚናገሩት ነገር እንደሌለ ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡[10] ነገር ግን ይህ መጽሐፍ ከተጻፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ “የዮሐንስ ወንጌል” የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡ በዚህ መንገድ አንባቢያን ጸሐፊው ማን እንደሆነ ሊያውቁ ይችላሉ፡፡ ከጥንት ጊዜ አንስቶ የቤተክርስቲያን መሪዎች የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስ አራተኛውን ወንጌል እንደጻፈ ያምኑ ነበር፡፡ ይህ አመለካከት በአብዛኛው የክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ተይዞ ቆይቷል፡፡ በ115 ዓ.ም. ኢግናቲየስ የተባለ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከዮሐንስ ወንጌል ጠቅሶ ጽፎአል፡፡ ከእርሱ በኋላ መጽሐፍ የጻፉት ሌሎች ሰዎች ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን ወንጌል በኤፌሶን ሆኖ እንደጻፈው ገልጸዋል፡፡ በጥንት ጽሑፎች ውስጥ ዮሐንስ ይህንን መጽሐፍ እንደጻፈ የሚያጠራጥር ነገር የለም፡፡ ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን ያልሆኑ ምሁራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ፡፡ ምክንያታቸውም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ የቀረበው ትምህርት በጣም የጠነከረ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በ100 ዓ.ም. ላይ ከዚህ ደረጃ መድረስ አትችልም የሚል ነው፡፡ … የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስ ይህንን መጽሐፍ እንደጻፈው የሚያስቡ ሰዎች የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስና ሽማግሌው ዮሐንስ አንድ ሰው ነው የሚል አሳብ አላቸው፡፡ ይህ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ያስተማረችው አሳብ ሲሆን ለመጠራጠር የሚያበቃ ምክንያት የለንም፡፡ (ቲም ፌሎስ የአዲስ ኪዳን መምሪያና ማብራሪያ በትምህርተ መለኮት ማስፍፊያ (ት.መ.ማ.) መልክ የተዘጋጀ፣ 1ኛ መጽሐፍ፣ ገፅ 440) |
ምርመራ
- ኢግናጢዮስ በ115 ዓ.ም. ከወንጌሉ ጠቅሶ መጻፉን፣ ከእርሱ በኋላ የነበሩት ሰዎች ዮሐንስ ወንጌሉን በኤፌሶን እንደጻፈ መግለፃቸውን፣ ወንጌሉ በዮሐንስ የተጻፈ መሆኑን የሚያጠራጥር ነገር እንደሌለ፣ ወዘተ. የሚናገሩትን አረፍተ ነገሮች ሆነ ብለው ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- አሕመዲን ወንጌላውያን ምሑራን እንኳ ሳይቀሩ የዮሐንስ ወንጌል በዮሐንስ እንደተጻፈ የማያምኑ ለማስመሰል “ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን የሆኑ ምሁራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ” በማለት ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን “የሆኑ” የምትለዋ ቃል ራሳቸው ፈጥረው የተኳት እንጂ በቦታው ላይ እንደሌለች ልብ ይሏል፡፡ ጽሑፉ በትክክል የሚለው እንዲህ ነው፡- “ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን ያልሆኑ ምሁራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ፡፡”
አሕመዲን የጠቀሱት
በዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ ማንነት ላይ የሚደረገው ክርክር የተጻፈበትን ቦታና ጊዜ ይወስነዋል፡፡ ይህ ወንጌል ወደ በኋላ እንደተጻፈ የሚያስቡ ሰዎች ጊዜውን ወደ 150 ዓ.ም. አከባቢ ይወስዱታል፡፡ ሌሎች ደግሞ የዮሐንስ ወንጌል ከ59-70 ዓ.ም. መጀመሪያ የተፃፉት መጽሐፍት አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ደራሲው አዛውንቱ ዮሐንስ ነው የሚሉትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ምሁራን ከ85-95 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተጻፈ ይስማማሉ፡፡” (ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ ገፅ 444) |
በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው ሙሉ ሐሳብ በዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ ማንነት ላይ የሚደረገው ክርክር የተጻፈበትን ቦታና ጊዜ ይወስነዋል፡፡ ይህ ወንጌል ወደ በኋላ እንደተጻፈ የሚያስቡ ሰዎች ጊዜውን ወደ 150 ዓ.ም. አከባቢ ይወስዱታል፡፡ ሌሎች ደግሞ የዮሐንስ ወንጌል ከ59-70 ዓ.ም. መጀመሪያ የተፃፉት መጽሐፍት አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ደራሲው አዛውንቱ ዮሐንስ ነው የሚሉትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ምሁራን ከ85-95 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተጻፈ ይስማማሉ፡፡ በምሑራን እጅ የሚገኘው የዮሐንስ ወንጌል ጥንታዊ ቅጂ በ125 ዓ.ም. የተገለበጠ ነው፡፡” ( ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 444) |
ምርመራ
- በምሑራን እጅ የሚገኘው የዮሐንስ ወንጌል ጥንታዊ ቅጂ በ125 ዓ.ም. የተገለበጠ መሆኑን በመግለፅ ከ150 ዓ.ም. በኋላ እንደተጻፈ የሚገምቱትን ሰዎች መላ ምት ውድቅ የሚያደርገውን አረፍተ ነገር ሆነ ብለው ቆርጠው አስቀርተውታል፡፡
በማስከተል አሕመዲን ጀበል እንዲህ በማለት ይጠይቃሉ፡-
“ስለ ዮሐንስ ወንጌል ካሉት አለመግባባቶች መካከል ለአብነት ከላይ አይተናል፡፡ ነገር ግን ተራው አማኝ እርግጠኛነት እንዲሰማው ስለተደረገ በጭፍን ሲከራከር ይስተዋላል፡፡ ወንጌሉ በማንና መቼ እንደተጻፈ ቁርጥ ያለ መረጃ የሌለበት ተአማኒነቱ አጠያያቂ በሆነበት ሁኔታ “የአምላክ ቃል ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ጻፉት ወዘተ.” ማለት ምን ያህል ያዛልቃል፡፡ የወንጌሉ ተአማኒነት ላይ ጥያቄ እያለ እንዲህ ያለውን መረጃ በመሰወር “ተራውን አማኝ” ማደናገር ለምን አስፈለገ?”
የሜሪል ቴኒ መጽሐፍም ሆነ የት.መ.ማ. መጻሕፍት ለአጠቃላይ አማኞች የተዘጋጁ በመሆናቸው “መረጃ መሰወር” የሚለው የአሕመዲን ጀበል ክስ መሠረተ ቢስ ነው፡፡ የቴኒ መጽሐፍ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ጥቅም ሲባል ተተርጉሞ በመጻሕፍት መደብሮች ውስጥ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ የት.መ.ማ. መጻሕፍት ደግሞ ትምህርተ መለኮትን ለእያንዳንዱ አማኝ በቤቱ ለማድረስ በማለም የተዘጋጁ ናቸው፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ እያንዳንዱ አማኝ ጋር እንዲደርሱ ታልመው በተዘጋጁ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ሐሳቦችን ከጠቀሱ በኋላ እነዚህኑ ጉዳዮች “በመሰወር” እና አማኞችን “በማደናገር” ክርስቲያን መሪዎችን መወንጀል እንዲሁም የእነዚህን ሊቃውንት ጽሑፎች በመቆራረጥ እና ዓላማቸውን በማጣመም የወንጌሉ ተዓማኒነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ማስመሰል በእውነቱ ከሆነ ከአንድ የሃይማኖት አስተማሪ የማይጠበቅ ነውረኛ ተግባር ነው፡፡ አፀፋ መመለስ ባይሆንብንም የቅዱስ መጽሐፋቸውን ተዓማኒነት በተመለከተ አማኞቻቸውን እያደናገሩ የሚገኙት እነማን እንደሆኑ ከአፍታ በኋላ ስለምንመለከት እውነቱ ግልፅ ይሆናል፡፡
የዮሐንስ ወንጌል ዘግይቶ እንደተጻፈ የሚናገሩ የለዘብተኛ ሥነ መለኮት ሊቃውንት የተጨበጠ የሰነድ ማስረጃ ኖሯቸው ሳይሆን ሥነ መለኮታዊ ይዘቱ ከፍ ያለ በመሆኑ እንዲህ ያለ የተደራጀ ሥነ መለኮት ያለው ጽሑፍ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን የተጻፈ ሊሆን አይችልም ከሚል ግምት በመነሳት ነው፡፡ ነገር ግን በሃምሳዎቹ ውስጥ በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተጻፈ ሊቃውንት በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት የሮሜ መልዕክት[11] ከዮሐንስ ወንጌል የጠለቀ ሥነ መለኮታዊ ይዘት የሚታይበት በመሆኑ ይህ ሙግት አሳማኝ አይደለም፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ በግብፅ ነጅ ሐማዲ በተባለ ስፍራ የተገኘው p52 ወይም “ጆን ሪላንድ ፐፓይረስ” የሚል መጠርያ የተሰጠው የዮሐንስ ወንጌል ክፍል ወንጌሉ ዘይግይቶ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ የሚናገሩትን ወገኖች መላ ምት ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርጋል፡፡ ዮሐንስ 18፡31-33፣ 37-38 የያዘው ይህ ጽሑፍ መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም ዕድሜው በ114-138 ዓ.ም. መካከል መሆኑ ስለተረጋገጠ ወንጌሉ በአንደኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈ መሆኑን ከጥርጣሬ በፀዳ ሁኔታ ያረጋግጣል፡፡ በትንሹ ኢስያ የተጻፈ መጽሐፍ በ114-138 ዓ.ም. መካከል በወዲያኛው የሜድትራንያን ባሕር ጫፍ በሚገኙ ትንንሽ ከተሞች ውስጥ የሚዘዋወር ከሆነ በአንደኛው ክፍለ ዘመን ለመጻፉ ምንም ጥርጥር የለውም![12]
የማቴዎስ ወንጌልን በተመለከተ ያነሷቸው ነጥቦች
አሕመዲን የጠቀሱት ስለ ማቴዎስ ወንጌል በክርስቲያን ምሑራን የሚከተለው ተጽፏል፡- “የማቴዎስ ወንጌል፡- “ወንጌሉን የጻፈው ማቴዎስ ነው” ያሉት የቀደሙ የቤተክርስቲያን አባቶች ናቸው እንጂ የጻፈው ስም አልተጻፈበትም፡፡ መች እንደተጻፈ አልታወቀም፡፡” ቲቶ (ጥጦስ) በሚባል በሮማ መንግሥት የጦር መሪ እጅ ኢየሩሳሌም የፈረሰችው በ70 ዓ.ም. ሲሆን ወንጌሉ ከዚያ በፊት ወይም ከዚያ በኋላ ተፅፎ እንደሆነ መምህራን አልተስማሙበትም፡፡ በ60 ዓ.ም. እና 80 ዓ.ም. መካከል ሳይፃፍ አይቀርም ይባላል፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ ገፅ 41) |
መጽሐፉ የሚለው “እንደ ጥንት ቤ.ክ. ትውፊት የመጀመርያውን ወንጌል የጻፈው ማቴዎስ ነው፡፡ ዛሬ አንዳንድ ሊቃውንት ይህን ሐሳብ ባይቀበሉትም የወንጌሉ አጻጻፍ በጥንቃቄ ከሚጽፍና ከሚሠራ ወደ ወንጌላዊነት ከተለወጠ ቀራጭ አሠራር ጋር ይስማማል፡፡ የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈባቸው ዘመናት በብዙ ሊቃውንት የተለያዩ እንደሆኑ ቢጠቀስም አንዳንዶች ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ከ50 ዓ.ም. በፊት እንደሆነ ሲያመለክቱ ሌሎች ግን ጸሐፊው የማርቆስን ወንጌል ተመልክቶ ኢየሩሳሌም ከወደቀችበት ከ70 ዓ.ም. በኋላ እንዳዘጋጀው ይናገራሉ፡፡” (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ ገፅ 53) |
ምርመራ
- የተጠቀሰው የመዝገበ ቃላቱ ገፅ ላይ አሕመዲን ጀበል ያሰፈሩት ሐሳብ በዚህ መልኩ አልተጻፈም፡፡ “ማቴዎስ” የሚለው ማውጫ ገፅ 52-53 ላይ የሚገኝ ሲሆን አሕመዲን ከጠቀሱት የተለየ ነው፡፡ ሰውየው ያሳዩት የጥንቃቄ ጉድለትና አንባቢያንን ለማሳሳት ያደረጉት ጥረት አሳፋሪ ነው፡፡
አሕመዲን የጠቀሱት ስለ ማቴዎስ ወንጌል ክርስቲያን ምሑራን ሲገልጹ፡- “ከስሙና ከሚሠራው ሥራው በቀር ስለዚህ ሰው በውል የታወቀ ነገር የለም፡፡ ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ከሐዋርያት የስም ዝርዝር ውስጥ ከመጠቀሱ በስተቀር፡፡ (የሐዋ. ሥራ 1፡13) ታሪኩን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በግልፅ አናገኘውነኘውም፡፡ በአፈ ታሪክ ጽሑፎች ውስጥ ግን የተባሉ ነገሮች መኖራቸውን ልብ ይሏል፡፡ በወንጌሉ ውስጥ ማቴዎስ ጸሐፊው እንደሆነ አልተናገረም፡፡ (ሜሪል ሲ. ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ ገፅ 217) |
በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው ሙሉ ሐሳብ “በታሪክ የመጀመርያውን ወንጌል እንደጻፈ የሚነገርለት ቀረጥ ሰብሳቢ ወይም ሕዝብን ያማከለ ሙያ የነበረው የሌዊ ልጅ ማቴዎስ ሲሆን ይህ ሰው ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ ይሆን ዘንድ ኢየሱስ መርጦታል፡፡ ከስሙና ከሚሠራው ሥራው በቀር ስለዚህ ሰው በውል የታወቀ ነገር የለም፡፡ ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ከሐዋርያት የስም ዝርዝር ውስጥ ከመጠቀሱ በስተቀር፡፡ (የሐዋ. ሥራ 1፡13) ታሪኩን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በግልፅ አናገኘውም፡፡ በአፈ ታሪክ ጽሑፎች ውስጥ ግን የተባሉ ነገሮች መኖራቸውን ልብ ይሏል፡፡ በወንጌሉ ውስጥ ማቴዎስ ጸሐፊው እንደሆነ አልተናገረም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ማቴዎስ እንደጻፈው ግን አረጋግጠዋል፡፡ በአረማይክ ቋንቋ ይተረጉመው እንደነበረ ጳጲያስ (100 ዓ.ም.) መናገሩን አውሳቢየስ [ኢዮስቢዮስ] (325 ዓ.ም.) የተባለ ሰው ጠቅሷል፡፡ ከአውሳቢያስ 150 ዓመት ቀደም ብሎ የኖረው ኢራኒዮስ የተባለ ሰው ሲገልፅ “ጴጥሮስና ጳውሎስ በሮም እየሰበኩ የቤተ ክርስቲያንን መሠረት በሚጥሉበት ዘመን ማቴዎስ ደግሞ በዕብራውያን ቋንቋ የተጻፈውን ወንጌል ለዕብራውያን አበርክቶ ነበር” ብሏል፡፡ የመጀመርያውን ወንጌል መነሻ በተመለከተ ከእነኚህ ጥንታዊ ገለፃዎች ብዙ ማጠቃለያ አሳቦች ማግኘት ይቻላል፡፡ አንደኛ የማቴዎስ ጸሐፊነት የሚያከራክር አይደለም፤… ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ ገፅ 217-218 |
ምርመራ
- የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ወንጌሉን ማቴዎስ እንደጻፈው ማረጋገጣቸውን፣ 100 ዓ.ም. አካባቢ ፓፒያስ ወንጌሉ በማቴዎስ የተጻፈ መሆኑን መናገሩን፣ 150 ዓ.ም. አካባቢ ኢሬኔዎስ ተመሳሳይ ምስክርነት መስጠቱን፣ የወንጌሉ ጸሐፊ ማቴዎስ መሆኑ የማያከራክር መሆኑን፣ ወዘተ. የሚገልፁትን አረፍተ ነገሮች በሙሉ ቆርጠው ጥለዋል፡፡
አሕመዲን የጠቀሱት
ወንጌሉ የተጻፈበት ስፍራ እንጾኪያ ሊሆን ይችላል፡፡ … በተጨማሪም በአንጾኪያ የነበረችይቱ ቤተክርስቲያን በአመዛኙ አሕዛብን በውስጧ በማቀፏ የመጀመሪያ ብትሆን ወንጌሉም የት ተጻፈ ለሚለው ሁነኛ ማረጋገጫ ባይገኝለትም ከአንጾኪያ የተሻለ ተስማሚ ቦታግን አይታሰብም፤ … ስለዚህ ወንጌሉ ከ50-70 ዓ.ም. ባሉ ጊዜያት መካከል ሳይጻፍ እንዳልቀረና በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያ ውስጥ በሚሰሩትና በዚያች ቤተ ክርስቲያን በሆኑቱ መካከል እንደተሰራጨ ይገመታል፡፡ (ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ፣ ገፅ 220) |
በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው ሙሉ ሐሳብ ወንጌሉ የጻፈበት ስፍራ እንጾኪያ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ጵጲያስ እና ኢግናትየስ [ኢግናጢዮስ] በመሳሰሉ ጥንታዊ የአባቶች ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱ የወንጌል ጥቅሶች ከማቴዎስ ወንጌል ጋር እጅግ በተቀራረበ ሁኔታ የሚስማሙ ሲሆን ይህ የመጀመርያው ወንጌል ሳይሮ አይሁድ [የሦርያ አይሁድ] ቤተ ክርስቲያን ዘንድ እጅግ የተወደደ እንደነበረ ያሳያል፡፡ በተጨማሪም በአንጾኪያ የነበረችይቱ ቤተክርስቲያን በአመዛኙ አሕዛብን በውስጧ በማቀፏ የመጀመሪያ ስትሆን ወንጌሉም የት ተጻፈ ለሚለው ሁነኛ ማረጋገጫ ባይገኝለትም ከአንጾኪያ የተሻለ ተስማሚ ቦታግን አይታሰብም፤ በተጨማሪም በከተማዋ የአረማይክና የግሪክ ቋንቋ መነገሩንም ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ ወንጌሉ ከ50-70 ዓ.ም. ባሉ ጊዜያት መካከል ሳይጻፍ እንዳልቀረና በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያ ውስጥ በሚሰሩትና በዚያች ቤተ ክርስቲያን በሆኑቱ መካከል እንደተሰራጨ ይገመታል፡፡ (ቴኒ፣ ገፅ 220) |
በማስከተል አሕመዲን እንዲህ በማለት ይጠይቃሉ፡- “ታዲያ እንዴት በግምትና በ”ሊሆን ይችላል”አፈታሪክና የክርስቲያን ምሁርራን ራሳቸው ባላወቁትና ባልተስማሙበት ፅሁፍ እንዴት ‹‹የአምላክ ቃል ነው እመኑ›› ይባላል?”
የማቴዎስ ወንጌል በሐዋርያው ማቴዎስ እንደተጻፈ የሚያረጋግጡትን መረጃዎች ቆርጠው በመጣል ስለ ማቴዎስ ግለ ታሪክ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አለመጻፉን በተመለከተ የተባለውን ብቻ ስለጠቀሱ እንጂ ሙሉ መረጃው ዓላማቸውን የሚደግፍ አይደለም፡፡ የጸሐፊያኑን ሐሳብ ቆራርጠው በማቅረብ ከፈጠሩት የተሳሳተ ምስል በመነሳት የጠየቁት ይህ ጥያቄ መሠረት አልባ መሆኑ ከላይ በሳጥኖቹ ውስጥ በንፅፅር በቀረቡት መረጃዎች ተጋልጧል፡፡
የማርቆስ ወንጌልን በተመለከተ የሚከተሉትን ነጥቦች አንስተዋል
4. “ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ስለዚህኛው ወንጌል ጸሐፊ ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ መጽሐፉ በየትኛውም ሥፍራ ስሙን አይጠቅስም፤ …የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚገልፀው ጸሐፊው የክርስቲያን ቤተሰብ አባል የሆነ ዮሀንስ ማርቆስ መሆኑንና የጳውሎስ፣ የበርናስና ምናልባትም የጴጥሮስ ረዳትና ተማሪ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል፡፡” (ሜሪል ሲ ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት ገፅ 236)
ተርጓሚዎቹ የደራሲውን ሐሳብ በትክክል ካለመተርጎማቸው የተነሳ ከላይ አሕመዲን የጠቀሱት ክፍል የተሳሳተ ምልከታን ይሰጣል፡፡ ቴኒ የጻፉት የእንግሊዘኛ ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፡- “Traditions identify him as John Mark, the scion of a Christian family in Jerusalem, the assistant and understudy of Paul, Barnabas and perhaps Peter. He was the son of Mary, a friend of the apostles, who is mentioned in Acts 12.”
ትርጉም፡- “በኢየሩሳሌም ከሚኖር ክርስቲያን ቤተሰብ የተገኘ የጳውሎስና የበርናባስ፣ ምናልባትም የጴጥሮስ ረዳትና ደቀ መዝሙር የሆነው ዮሐንስ ማርቆስ መሆኑ በትውፊቶች ተገጿል፡፡ የሐዋርያት ወዳጅ የሆነችው በሐዋርያት ሥራ 12 ላይ የተጠቀሰችው የማርያም ልጅ ነበር፡፡”
በዚህ ቦታ “በምናልባትነት” የተቀመጠው የጴጥሮስ ረዳትና ደቀ መዝሙር የመሆኑ ጉዳይ እንጂ ሌሎች መረጃዎች አይደሉም፡፡ ማርቆስን የተመለከተ በ115 ዓ.ም. የተነገረ ከፓፒያስ የተገኘ መረጃ ኢዮስቢዮስ (375 ዓ.ም.) በጻፈው ጽሑፍ ውስጥ ተጠብቋል፡፡ ይህ መረጃ በቀዳሚነት የተላለፈው ከሽማግሌው ከዮሐንስ (ከሐዋርያው ዮሐንስ) ሲሆን፤ ማርቆስ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ደቀ መዝሙር ባይሆንም የጴጥሮስ አስተርጓሚ የነበረ መሆኑን፤ ቅደም ተከተል ባይጠብቅም መረጃዎቹን ሳይጨምርና ሳይቀንስ ያለ አንዳች ስህተት በታላቅ ጥንቃቄ መጻፉን ያስነብበናል፡፡[13] የጸሐፊውን ማንነት በተመለከተ አበው ስለሰጡት መረጃ ተዓማኒነት ቴኒ እንዲህ ይላሉ፡-
“የእነኚህ ታሪኮች አስተማማኝነት አጠያያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ የሁለተኛው ወንጌል ጸሐፊ ማርቆስ መሆኑን ሁሉም ተስማምተዋል፤ ወንጌሉንም ከጴጥሮስ ስብከት ጋር ያያይዙታል፡፡”[14]
አሕመዲን የጻፉት
“የማርቆስ ወንጌል ደራሲው (ጸሐፊው) በሮማይስጥ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስ ነው፡፡ |
መጽሐፉ የሚለው የጠቀሱት የመዝገበ ቃላቱ ገፅ ላይ አሕመዲን ጀበል ያሰፈሩት ሐሳብ በዚህ መልኩ አልተጻፈም፡፡ “ማርቆስ” የሚለው የመዝገበ ቃላቱ ማውጫ ገፅ 50 ላይ የሚገኝ ሲሆን ስለ ጸሐፊው ማንነትና ወንጌሉ ስለተጻፈበት ዘመን እንዲህ ይላል፡- ማርቆስ ወንጌልን እንደጻፈ የቤ.ክ. አባቶች ይናገራሉ፡፡ በአይሁድ ዘንድ ስሙ ዮሐንስ ሲሆን በሮማውያን ዘንድ ማርቆስ ይባላል፡፡ እናቱ ማርያም ትባላለች፤ ሐ.ሥ. 12፡12፡፡ ቤትዋ በኢየሩሳሌም ነበር፡፡ ምዕመናን በቤትዋ ለጸሎት ይሰበሰቡ ነበር፤ ሐ.ሥ. 12፡12-17፡፡ አጎቱ በርናባስና ጳውሎስ ለስብከት ሥራ ሲጓዙ ማርቆስ ያገለግላቸው ነበር፤ ቆላ. 4፡10፤ ሐ.ሥ. 12፡25፡፡ ከእነርሱ ጋር እስከ ጴርጌ ሄዶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ ሐ.ሥ. 13፡13፡፡ ጳውሎስና በርናባስ በእርሱ ምክንያት ሲለያዩ ማርቆስ ከበርናባስ ጋር ወደ ቆጵሮስ ሄደ፤ ሐ.ሥ. 15፡36-39፡፡ በኋላ ግን ጳውሎስ አመስግኖታል፤ ቆላ. 4፡10፣ 2ጢሞ. 4፡11፣ ፊልሞና 24፡፡ ማርቆስ ከጴጥሮስ ጋር ሰርቷል፤ 1ጴጥ. 5፡13፡፡ ብዙ ሊቃውንት በማርቆስ 14፡51-52 ላይ የተጠቀሰው ወጣት ማርቆስ ነው ይላሉ፡፡ በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንን እንደመሠረተ አበው ይናገራሉ፡፡ እስካሁን የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን አባት ይባላል፡፡ የማርቆስ ወንጌል፤ ጸሐፊው ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ነው፡፡ የቀደሙት የቤ.ክ. አባቶች ይህ ወንጌል ለሮማውያን በ60 ዓ.ም. ገደማ በሮም ሳይጻፍ እንዳልቀረ ጠቁመዋል፡፡ የተጻፈውም ሮማውያን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እንዲያምኑ ነው፤ ወንጌሉ ሮማዊ የሆነ መቶ አለቃ እንዴት እንዳመነ ይተርካል፤ 1፡1፣ 15፡39፡፡ ብዙዎች “ማርቆስ የሐዋርያው ጴጥሮስ የመንፈስ ልጅ ነውና ይህ ወንጌል ጴጥሮስ ያስተማረው ነው” ይላሉ፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ ገፅ 50) |
አሕመዲን እንዲህ በማለት ይጠይቃሉ፡-
የተጨበጠ ማስረጃ የሌለበት በመላምትና በግምት “የማርቆስ” ወንጌል የአምላክ ቃል ነው፡፡ ማለት ይቻላልን?
የማርቆስ ወንጌል በአርባዎቹ መጨረሻ ወይም ከስድሳዎቹ በፊት እንደተጻፈ የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ወንጌሉ ከ70 ዓ.ም. በኋላ እንደተጻፈ የሚያምኑ ወገኖች በ13ኛው ምዕራፍ ላይ ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም ውድቀት በዝርዝር የተናገረው ትንቢት ከከተማዋ ውድቀት በፊት የተጻፈ ሊሆን አይችልም ከሚል ግምት በመነሳት ነው፡፡ የነዚህ ሰዎች ሙግት ሙሉ በሙሉ ያረፈው ኢየሱስ ስለ መጪው ሁኔታ እንደዚያ ዓይነት ዝርዝር ትንቢቶችን ሊናገር አይችልም በሚል እምነት ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ግለሰቦቹ በልዕለ ተፈጥሯዊ ኃይል ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ የሚያሳይ እንጂ ኢየሱስ ትንቢቱን ላለመናገሩ ማስረጃ የሚሆን አይደለም፡፡[15] ቀደም ሲል እንደተባለው የሊቃውንት ትኩረት ወንጌላት በተጻፉበት ቁርጥ ያለ ዓመት ላይ ሳይሆን በተጻፉበት ዘመን ላይ በመሆኑ የማርቆስ ወንጌል ከ70 ዓ.ም. በኋላ እንደተጻፈ ብንቀበል እንኳ የመስቀሉ ትውልድ ከማለፉ በፊት ስለሚሆን ስለ ክርስቶስ በሚሰጠው ምስክርነት ላይ ሙሉ በሙሉ ልንተማመን እንችላለን፡፡
ጸሐፊው ስሙ በተደጋጋሚ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰው ማርቆስ ዮሐንስ ስለመሆኑ በጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጽሑፎች ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ምስክርነቶች እናገኛለን፡፡ ኢሬኔዎስ፣ ጠርጡሊያኖስ፣ የእስክንድርያው ቀለሜንጦስ፣ ኦሪጎን፣ ጀሮም እና የሙራቶራውያን ቀኖና የዚህ ወንጌል ጸሐፊ ማርቆስ ዮሐንስ የተሰኘው የሐዋርያው ጴጥሮስ ደቀመዝሙር መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡ የወንጌሉ ጸሐፊ ማርቆስ መሆኑን የሚያወሳው ቀዳሚ ምስክርነት ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን የተገኘ ሲሆን መስካሪው ብዙዎች ሐዋርያው ዮሐንስ መሆኑን የሚያምኑት “ሽማግሌው ዮሐንስ” ነው፡፡ መረጃው የተገኘው ፓፒያስ ከተሰኘ ሐዋርያዊ አባት ሲሆን ኢዮስቢዮስ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ በጻፈው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ መዝግቦታል፡፡[16]
አሕመዲን ጀበል እንዲህ በማለት ይጠይቃሉ፡-
“ወሳኝ” የሚባሉት አራቱ ወንጌላት ይህን ያህል አጨቃጫቂ፣ ስምምነት የሌላቸውና ጸሐፊያቸው እንኳ ያልታወቀ ከሆነ የሌሎች መጽሐፍት እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
ክርስቲያን ምሑራን በአዲስ ኪዳን ጽሑፎች ላይ የተጋነነ ጥርጣሬ ያላቸውን የለዘብተኛ ሥነ መለኮት ምሑራን (Libral Scholars) አስተያየቶችንም ሆነ የአጥባቂ ሊቃውንት (Conservative Scholars) አስተያየቶችን ያገናዘቡ መረጃዎችን በታማኝነት ለአማኞች ለማስተላለፍ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ከላይ የተጠቀሱትን ዓይነት ጽሑፎች ይጽፋሉ፡፡ ነገር ግን ከክርስትና አኳያ ሲታይ የወንጌላቱን ጸሐፊያን ማንነት እንድንጠራጠር የሚያበቃን ምንም ነገር የለም፡፡ እያንዳንዱ ወንጌል የጸሐፊው ማንነት በሁለተኛውና በሦስተኛ የክርስቲያን ትውልዶች ስለተመሰከረላቸው፤ በተጨማሪም እስካሁን በእጃችን የሚገኙት ቀዳሚያን ጽሑፎች እነዚህ ወንጌላት አሁን በሚታወቁት ሰዎች የተጻፉ እንዳልሆኑ የሚጠቁም ነገር ስለሌላቸው (እንዲያውም በተቃራኒው የጸሐፊያኑን ስሞች ይዘው በመገኘታቸው) ያልተገባ ጥርጣሬና ሥጋት ውስጥ መግባት ምክንያታዊ አይደለም፡፡ አሕመዲን እንዳደረጉት የእነዚህን ክርስቲያን ምሑራን አስተያየቶች ከአውድ ውጪ ካልተረጎምን በስተቀር ወንጌላት አጠራጣሪ እንደሆኑ የሚያሳስብ የተጨበጠ መረጃ የለም፡፡ የፈጠራ ጽሑፎች ተዓማኒነታቸውን ከፍ ለማድረግ ታዋቂ በሆኑት ሰዎች ስም እንደሚጻፉ ይታወቃል፡፡ ከዮሐንስ በስተቀር የተቀሩት ሦስቱ ጸሐፊያን በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጎላ ተፅዕኖ ስላልነበራቸው እነዚህ መጻሕፍት በተባሉት ሰዎች የተጻፉ ባይሆኑ ኖሮ በእነዚህ ሰዎች ስም መሰየም አስፈላጊ ባልሆነም ነበር፡፡
አሕመዲን ጥያቄዎቻቸውን ይቀጥላሉ፡-
- ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ “ብሉይና አዲስ ኪዳን” የሚባለው መጽሐፍ ከየት ተገኘ?
5. የክርስቲያን ምሑራን እንዲህ ጽፈዋል፡፡ “ከመጀመሪያ ጀምሮ ቤተክርስቲያን አይሁድ ያወቋቸውን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ተቀበለች፡፡ በሐዋርያት ወይም በሐዋርያት ሥልጣን የተጻፉትን መጽሐፍት ሰብስባ እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቀበለቻቸው፡፡ የቤተክርስቲያን አባቶች የአዲስ ኪዳን መጽሐፍትን እየጠቀሱ አስተማሩ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ በ367 ዓ.ም በጻፈው በፋሲካ ዕለት ቃል በረከት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሃያ ሰባት ብቻ መሆናቸውን ተናግሮአል፡፡ እንደዚሁም በ397 ዓ.ም በካርታ (በካርቴጅ) የተደረገው ሲኖዶስ ሃያ ሰባቱን መጻሕፍት አጸደቀ፡፡” (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኀበር፡፡ ገጽ 35)
በግርጌ ማስታወሻ ደግሞ እንዲህ የሚል ነጥብ አክለዋል፡-
“ከላይ እንዳየነው በዶክተር ፓውል እንዝ የተጻፈው “ታሪካዊ ሥነ-መለኮት አመጣጡና ትንተናው” የሚለው መጽሐፍ አትናቴዎስ በ387 ዓ.ም እንደጻፈ ገልጾዋል፡፡ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ጊዜውን 367 ያደርገዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው 27ቱን የአዲስ ኪዳን መጻሐፍት በደብዳቤው ላይ ጻፈ የሚባለው አትናቴዎስ የጻፈበት ጊዜም በውል አለመታወቁን ነው፡፡ ይህንን ነው እንግዲህ የካርቴጅ ጉባኤ ሳይወያይ ያጸደቀው፡፡”
ትክክለኛው ዓመት 367 ሲሆን የመጽሐፉ ተርጓሚዎች 387 ማለታቸው የትየባ ስህተት ነው፡፡ የቅዱስ አትናቴዎስ ጽሑፍ የተጻፈበትን ዘመን በተመለከተ በታሪክ ምሑራን መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት ባለመኖሩ ጠያቂው በተርጓሚዎቹ ስህተት ላይ ተመስርተው ያቀረቡት አንካሳ ሙግት ቦታ የሚሰጠው አይደለም፡፡ ተርጓሚዎቹ ራሳቸው በዚሁ መጽሐፍ ገፅ 30 ላይ “አትናቴዎስ ደግሞ በ367 ዓ.ም. ሁሉንም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አስመዘገበ” በማለት ትክክለኛውን ዓመት አስቀምጠዋል፡፡ ጠያቂው ለክርክራቸው የሚመቻቸውን ሐሳብ ለመቃረም እንደ ፌንጣ ከገፅ ገፅ እየዘለሉ ከሚያነቡ መጽሐፉን በሞላ በእርጋታና በሰከነ መንፈስ ቢያነቡ ኖሮ ያለፈውን ስህተትና ይኸኛውን በማገናዘብ ከተሳሳተ ድምዳሜ በዳኑ ነበር፡፡ የካርቴጅ ጉባኤ መወያየት ያላስፈለገው መጻሕፍቱ ከዚያ ቀደም ተቀባይነት ያገኙ ስለነበሩና ለእንግዳ አመለካከቶች ክፍተት ላለመስጠት ኦፊሴላዊ ውሳኔ ማውጣት ስለነበረባቸው ብቻ ስለተሰበሰቡ ነበር፡፡ የመጻሕፍቱ ቀኖናዊነት ቀደም ሲል ስለታመነበት የውሳኔ ቃል እንጂ ውይይት አስፈላጊ አልነበረም፡፡
- ከዚህ የምንረዳው ቤተክርስቲያን ከመጽሐፉ ቀድማ መመስረቷን፤ “ብሉይ ኪዳን” የሚባለው ከአይሁድ እንደተገኘና ሃያ ሰባቱ (የአዲስ ክዳን) መጻሕፍት 397 ዓ.ል በካርቴጅ ጉባኤ መጽደቃቸውን ነው፡፡
በእርግጥ ቤተ ክርስቲያን በ33 ዓ.ም. በበዓለ ሃምሳ ዕለት ነበር በሐዋርያት የተመሠረተችው፡፡ በዚያን ወቅት ደግሞ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አልተጻፉም ነበር፡፡ ሐዋርያት ጌታችን ያስተማራቸውን ትምህርቶችና ታሪኮቹን ከትውስታቸው ያስተምሩ ነበር፡፡ እነዚህን ትምህርቶችና ታሪኮች በመጻሕፍት ማስፈር ያስፈለገው የምዕመናን ቁጥር እየበዛ በመምጣቱ ምክንያት ነበር፡፡ ጠያቂው ቁርኣን ራሱ በጽሑፍ መስፈር የጀመረው እስላማዊው ማሕበረሰብ ከተመሠረተ በኋላ እንደነበር የሚያውቁ አይመስሉም፡፡
- ለመሆኑ ክርስቲያኖች “ብሉይ ኪዳን” የሚባለውን መጽሐፍ ከአይሁድ ሲቀበሉ (“እነርሱ መጽሐፉን ጠብቀው ስላቆዩ”) በብሉይ ኪዳን ስለ ሥላሴ፣ ስለ ኢየሱስ መሰቀልና ሌሎችም ክርስቲያኖች የሚያምኑባቸውን እንዲሁም “መጽሐፉን ጠብቀው ያቆዩት” አይሁዶች የማይቀበሉትንና ፈጽሞ ሀሰት በማለት የሚያስተባብሉትን እምነት እንዴት “መጽሐፉን ጠብቀው ካቆዩት” ልቀው ክርስትናን በትንቢቱ አረጋግጠው ተቀበሉ? ሃያ ሰባቱን መጻሕፍት የአምላክ ቃላት ናቸው ብሎ በምን መስፈርት ሊቀበሉ ቻሉ?
አይሁድ የኢየሱስን መሰቀል ይቀበላሉ፤ ቁርኣን እንኳ ይህንን ይመሰክራል (ሱራ 4፡57-158)፡፡ ጠያቂው ይህንን ስህተት መስራታቸው በግብታዊነት እንጂ በእርጋታና በማስተዋል እየጠየቁ እንዳልሆነ ያመለክታል፡፡
የአይሁድ አለማስተዋል የሥላሴ ትምህርት እና ስለ ክርስቶስ የተነገሩት ትንቢቶች በብሉይ ኪዳን ውስጥ አለመኖራቸውን ሊያረጋግጥ የሚችለው እንዴት ሆኖ ነው? አይሁዶች እነዚህን የመጽሐፋቸውን ክፍሎች አልተገነዘቡም ቢባል እንኳ የአይሁድን አለማስተዋል እንጂ የክርስትናን ስህተት መሆን አያሳይም፡፡ ሲጀመር አይሁድ ሁሉ እነዚህን ጉዳዮች አያውቁም ያለው ማን ነው? የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች በሙሉ አይሁድ እንደነበሩ ለጠያቂው ማን በነገራቸው! አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አይሁድ ነበሩ፡፡ መቶ ሃያዎቹ በአንድ ቤት ሲጸልዩ የነበሩት ደቀ መዛሙርት አይሁድ ነበሩ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በወቅቱ ታዋቂ በነበረው (እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁድ ታሪክ ከተነሱት ሦስት ረበናት መካከል አንዱ በሆነው!) በገማልያል እግር ሥር ተቀምጦ የተማረና እርሱን ሊተካ ይችል የነበረ ታላቅ አይሁዳዊ ምሑር ነበር፡፡ በበዓለ ሃምሳ ቀን ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ የተነገሩትን ትንቢቶች ከብሉይ ኪዳን ጠቅሶ ያሳመናቸው ሦስት ሺህ ሰዎች አይሁድ ነበሩ፡፡ ሽባውን ከፈወሰው በኋላ ያመኑት አምስት ሺህዎቹ አይሁድ ነበሩ (የሐዋርያት ሥራ 2፡1-41፣ 4፡4)፡፡ የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲያመልኩ የነበር፡፡ በዚያን ዘመን ብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናት መነሻቸው የአይሁድ ምኩራቦች ነበር፡፡ ዛሬም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አይሁድ ክርስቲያኖች በዓለም ዙርያ ይገኛሉ፡፡ ኢየሱስ ራሱ አይሁዳዊ እንደነበርስ አሕመዲን ጀበል ያውቁ ይሆን? (ዮሐንስ 4፡22፣ ማቴዎስ 1፡1-17)፡፡ እስኪ የገዛ ጥያቄያቸውን መልሰን እናቅርብላቸውና መልስ ይኖራቸው እንደሆን እንይ፡፡ ሙስሊሞች ስለ ነቢያቸው ስለ ሙሐመድ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንደተተነበየ ይናገሩ የለምን? ታድያ አይሁዶችም ሆኑ የአዲስ ኪዳን ባለቤቶች የሆንነው እኛ ክርስቲያኖች ያላየነውን “ትንቢት” እንዴት ከኛ ልቀው ሊያዩት ቻሉ? በራሳቸው እምነት መሠረት እንኳ ሙግታቸው ውድቅ መሆኑ ግልፅ ነው!
- ይህ ራሱ አቋም ከያዙ በኋላ መጻሕፍቱን እንደተቀበሉ አያሳይምን? ይህ ጉባኤ በ397 ዓ.ል መካሄዱ ራሱ ከዚያ በፊት “የትኞቹ መጻሕፍት የአምላክ ቃል ናቸው?” “የአዲስ ኪዳን አካል ናቸው?” የሚለው በውል አለመታወቁን አይገልጽምን? የኒቂያ ጉባኤ ራሱ የተካሄደው በ325 ነው፡፡ ይህም ማለት ይህ መጽሐፍ በ397 የጸደቀበት የካርቴጅ ጉባኤ ሳይካሄድ 72 አመታት አስቀድሞ ነው፡፡ እምነቱ በ325 ተወሰነ፡፡ መጽሐፋ በ397 ተቀባይነት አገኘ! በ325 ከተወሰነው እምነት ጋር የሚሄደው (የሚስማማውን) ብቻ መርጠው እንደሆነስ?
ጠያቂው የክርስትና እምነት በኒቅያ ጉባኤ የተወሰነ በማስመሰል የተናገሩት በእጅጉ የተሳሳተ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያለምንም ኦፊሴላዊ ጉባኤ ቀደም ሲል ተቀብላው የነበረው የሥላሴ ትምህርት አርዮስ በተሰኘ የኑፋቄ አስተማሪ ተግዳሮት ስለገጠመው ነበር ጉባኤ መጥራት ያስፈለገው፡፡ ጉባኤው ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያን የምታምነውን ትምህርት በሥነ መለኮታዊ ቃላት ይበልጥ በማብራራት መግለጫ አወጣ እንጂ አዲስ ነገር አልፈጠረም፡፡ በተጨማሪም የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች አቋም ከያዙ በኋላ አልነበረም ቅዱሳት መጻሕፍታቸውን ያጸደቁት፡፡ ቀደም ሲል እንደገለፅነው ከኒቅያ ጉባኤ በፊት የነበሩት አባቶች ከ11 ቁጥሮች በተረፈ የአዲስ ኪዳንን ጥቅሶች በሙሉ በጽሑፎቻቸው ውስጥ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው መጻሕፍቱ ቀደም ሲል ተቀባይነት እንደነበራቸውና የኒቅያ ጉባኤም ሆነ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች በእነዚህ ላይ ተመስርተው የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ እንዳስታወቁ ነው፡፡ (አርዮስና ሰባልዮስን የመሳሰሉት መናፍቃን እንኳ ክርክራቸውን ያቀረቡት አሁን በእጃችን በሚገኙት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ በመመስረት ነበር!) በሐዋርያት እና በቀደሙት አማኞች ስም የተጻፉ የአፖክሪፋ መጻሕፍት ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ወዲህ መታየት መጀመራቸውንና በተባሉት ሰዎች የተጻፉ አለመሆናቸውን ለዘብተኛም ሆነ አጥባቂ የሥነ መለኮት ሊቃውንት ያለ ልዩነት በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት እውነታ ነው፡፡
የቀኖና ምርጫ በአንድ ጀንበር የተከናወነ አልነበረም፡፡ ክርስትና እጅግ ሰፊ በነበረው በሮም ግዛት ውስጥ በመሰራጨቱ ምክንያትና ከበረታው ስደት የተነሳ አንዳንድ መጻሕፍት በሁሉም ስፍራዎች አይታወቁም ነበር፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በመላው ክርስቲያን ማሕበረሰብ ዘንድ የተዳረሱት የስደቱ ዘመን ካበቃ በኋላ ሲሆን በጣም ርቀው ይገኙ የነበሩት የተሟላውን ቀኖና ለማግኘት ረጅም ጊዜ ወስዶባቸው ነበር፡፡ እያንዳንዱ የክርስቲያን ማሕበረሰብ መጻሕፍቱን ለመቀበል የየራሱን የማጣራት ሥራ ይሰራ ስለነበር አንዳንድ መጻሕፍት በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ ወጥ በሆነ ሁኔታ ተቀባይነትን አላገኙም ነበር፡፡ የመጀመርያውን ቀኖና የጠቀሰው የቤተ ክርስቲያን ጸሐፌ ታሪክ የነበረው የቂሣርያው ኢዮስቢዮስ ሲሆን መጻሕፍቱን ለሦስት ይከፍላል፡፡ ሀ) ቀኖናዊነታቸው ከጥርጣሬ በፀዳ ሁኔታ ተቀባይነት ያገኙ 22 መጻሕፍት ሲሆኑ እነዚህም አራቱ ወንጌላት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ የጳውሎስ መልዕክቶች (ዕብራውያንን ጨምሮ)፣ 1ዮሐንስ፣ 1ጴጥሮስ እና የዮሐንስ ራዕይ ናቸው፡፡ ለ) አምስቱ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበራቸው ሲሆን ጥቂቶች ብቻ ይጠራጠሯቸው ነበር፤ እነዚህም ያዕቆብ፣ ይሁዳ፣ 2ጴጥሮስ፣ 2ዮሐንስ እና 3ዮሐንስ ናቸው፡፡ አምስቱ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ነበር እነርሱም የሔርማሱ እረኛ፣ የጳውሎስ ሥራ፣ የጴጥሮስ ራዕይ፣ የበርናባስ መልዕክት[24] እና ዲዳኬ ናቸው (እነዚህ በአዲስ ኪዳን ቀኖና ውስጥ አልተካተቱም)፡፡ ኢዮስቢዮስ የዮሐንስን ራዕይ በወቅቱ ገሚሶቹ ሲቀበሉት ገሚሶቹ ደግሞ ስለማይቀበሉት ምናልባት ከእነዚህ መደብ ሊጨመር እንደሚችል የጠቆመ ሲሆን እርሱ ግን ሃያ ሰባቱንም እንደሚቀበል ገልጿል፡፡[25]
በምስራቅ ሃያሰባቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በቀኖናዊነት ለመጀመርያ ጊዜ የጠቀሰው ቅዱስ አትናቴዎስ ሲሆን (367 ዓ.ም.) በምዕራብ ደግሞ በሂፖ ሬጊዩስ (አልጄርያ) (393 ዓ.ም.) እና በካርቴጅ (397 & 419 ዓ.ም.) እነዚሁ መጻሕፍት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት የዮሐንስን ራዕይ የተቀበሉት ዘግይተው ሲሆን የሦርያ ቤተ ክርስቲያን 2ጴጥሮስ፣ 2ዮሐንስ፣ 3ዮሐንስ እና ይሁዳን ለመቀበል ከሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘግይታለች፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ርቃ የምትገኝ ስለነበረችና እነዚህ መጻሕፍት ስላልደረሷት ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ መጻሕፍቷን እንድታስታውቅ ያደረጓት የተለያዩ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ዋነኛው ምክንያት ግን ኑፋቄያዊ ቡድኖች የየራሳቸውን የመጻሕፍት ስብስብ ማዘጋጀታቸው ነበር፤ (ለምሳሌ ያህል መርቂያን/ ማርሲዮን[26])፡፡[27]
ክርስቲያኖች የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት በቀኖናዊነት ለመቀበል የተለያዩ መስፈርቶችን በጥንቃቄ ተጠቅመዋል፡፡ የመጀመርያው መስፈርት “ሐዋርያዊ ሥልጣን” የሚል ነበር፡፡ ይህም አንድ መጽሐፍ ተቀባይነት ማግኘት ያለበት በሐዋርያትና ከእነርሱ ጋር የቀረበ ግንኙነት በነበራቸው ሰዎች የተጻፈ እንደሆነ ነው፡፡ ሉቃስና ማርቆስ ከሐዋርያት ጋር የቀረበ ግንኙነት ስለነበራቸው መጻሕፍታቸው ተቀባይነትን አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛው መስፈርት ደግሞ የመጻሕፍቱ ከሌሎች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጋር መስማማት ሲሆን ሦስተኛው መስፈርት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለተከታታይ ዘመናት ተቀባይነትን አግኝተው ጥቅም ላይ መዋላቸው ነው፡፡ የቀደሙት ክርስቲያኖች ቀኖናዊ መጻሕፍትን ለመወሰን ጊዜ መውሰዳቸው ሐዋርያዊ ሥልጣን የሌላቸው መጻሕፍት ሾልከው እንዳይገቡ የነበራቸውን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህን መጻሕፍት በአንድ ጥራዝ የመሰብሰቡ ሂደት ጊዜ የወሰደ ቢሆንም ነገር ግን ተቀባይነት ያገኙት በአንድ ጀንበር አዋጅ ሳይሆን ከሐዋርያት ዘመን ተያይዞ በመጣ ሁኔታ ነበር፡፡ ጉባኤዎችም ሆኑ ግለሰቦች ቀኖናን አልፈጠሩም፡፡ ይልቁኑ እውነተኛ ቅዱሳት መጻሕፍት መሆናቸው በዘመናት ተፈትኖ ለተረጋገጡት መጻሕፍት ዕውቅናን ሰጡ እንጂ፡፡[28]
አሕመዲን ጥያቄያቸውን ይቀጥላሉ፡-
- የክርስቲያን ምሑራን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ጽፈዋል፡- “መጽሐፍ ቅዱስ ፤ የተቀደሰ ወይም የተለየ ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱሳን መጻሕፍት መዝገብ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ናቸው፡፡ ብሉይ ኪዳን በ 1400-400 ከክርስቶስ በፊት በልዩ ልዩ ቦታዎች፣ አርባ በሚያህሉ ልዩ ልዩ ጸሐፊዎች እንደተጻፈ ይነገራል፡፡” (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ ቃላት፤ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ መኅበር ገጽ 34)፡፡ አርባ ሰዎች የጻፉት የመጻሕፍቶች ስብስብ ከክፍለ ዘመናት በኋላ በአንድነት ተጠረዘ፡፡ እንዲያው የአንዱ መጽሐፍ ጸሐፊ “በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ” መጽሐፉን ቢገልጽ ይህ በሌሎች 39ኙ ሰዎች ተጽፈው በኋላ ላይ በአንድነት አብረው የተጠረዙትን ሁሉንም ሊወክል ይችላልን? መጽሐፍ ቅዱስ በአርባ ሰዎች የተጻፉ መጻሕፍት ስብስብ አይደለምን?
መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ሰዎች፣ በተለያዩ ዘመናት፣ በተለያዩ ቦታዎች የተጻፈ መጽሐፍ ሆኖ ሳለ ማዕከላዊ መልዕክቱ አንድ መሆኑ መለኮታዊነቱን ከሚያሳዩ ነገሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከአንድ ግለሰብ ምስክርነት ይልቅ የአርባ ሰዎች ምስክርነት ይታመናል፡፡ አንድ ግለሰብ እርስ በርሱ የተስማማ አንድ መጽሐፍ ማዘጋጀት ይችላል፡፡ ነገር ግን የማይተዋወቁ፣ በክፍለ ዘመናት የተራራቁና በቦታ የማይገናኙ 40 ሰዎች ወጥ መልእክት ያለው መጽሐፍ ማዘጋጀት በእጅጉ ከባድ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ግን በአንዱ የእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው ስለጻፉ ይህንን ማድረግ ተችሏቸዋል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ሁሉም ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው እንደጻፉ ስለምናምን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ሁሉ ያለ ምንም ልዩነት በእኩል ሁኔታ እንቀበላለን፡፡ ጠያቂው አንድ መጽሐፍ እውነተኛ መሆን የሚችለው በአንድ ግለሰብ የተጻፈ እንደሆነ ብቻ ነው የሚሉ ይመስላሉ፡፡ እስላማዊ “አመክንዮ” በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡
- ለአብነት “የማቴዎስ ወንጌልን የጻፈው ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ ነው” ተብሎ ይታመናል፡፡ ነገር ግን በቀላሉ በእርሱ እንዳልተጻፈ መረዳት ይቻላል፡፡ በማቴዎስ 9፥9 ላይ “ኢየሱስ ከዚያ ቦታ ተነስቶ ሲሄዱ ሳለ ማቴዎስ የተባለውን ቀራጭ በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ አየውና “ተከተለኝ” አለው፡፡ ማቴዎስም ተነስቶ ተከተለው” ይላል፡፡ ማቴዎስ ይህን ቢጽፍ “ተቀምጦ አየው”፡፡፡፡ ሳይሆን “ተቀምጬ አየኝ”፣ “ተነስቶ ተከተለው” ሳይሆን “ተነስቼ ተከተልኩት” ወዘተ. እያለ ነበር የሚጽፈው፡፡ እንዴት ራሱን ሦስተኛ ወገን አድርጎ ያቀርባል?
ስለ ራስ በሦስተኛ ወገን መጻፍ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በጥንት ሥነ-ጽሑፎች ውስጥ የተለመደ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አጻጻፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቁርኣንም ውስጥ እናገኛለን፡፡ አላህ በቁርኣን ውስጥ ኁልቁ መሳፍርት በሌላቸው ቦታዎች ላይ ራሱን እንደ ሦስተኛ ወገን ይጠቅሳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንደኛና ሦስተኛ ተውላጠ ሥሞችን እያቀያየረ ከመናገሩ የተነሳ ቁርኣንን ለመጀመርያ ጊዜ የሚያነብ ሰው ከአንድ በላይ ማንነት እንዳለው እስኪመስለው ድረስ ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል እስኪ የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት፡-
“ያ ባሪያውን ከተከበረው መስጊድ ወደዚያ ዙሪያውን ወደ ባረክነው ወደ ሩቁ መስጊድ በሌሊት ውስጥ ያስኼደው (ጌታ) ጥራት ይገባው፡፡ ከተዓምራቶቻችን ልናሳየው (አስኼድነው)፡፡ እነሆ እርሱ (አላህ) ሰሚው ተመልካቺው ነው፡፡” (ሱራ 17፡1)
“ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊ አዛኝ ነው፡፡ ጌታህም ሙሳን «ወደ በደለኞቹ ሕዝቦች ኺድ» በማለት በጠራው ጊዜ (አስታውስ)፡፡” (ሱራ 26፡8-9)
“አላህ በነሱ ይሳለቅባቸዋል፤ በጥመታቸውም ውስጥ የሚዋልሉ ሲኾኑ ያዘገያቸዋል፡፡” (ሱራ 2፡14)
“እርሱ ያ በምድር ያለውን ሁሉ ለእናንተ የፈጠረ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ሰማይ አሰበ፤ ሰባት ሰማያትም አደረጋቸው፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡” (ሱራ 2፡28)
አንድ ሰው ራሱን በሦስተኛ ወገን ማመልከቱ የመልእክቱ ተናጋሪ እርሱ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ከሆነ በተመሳሳይ በነዚህ የቁርኣን ጥቅሶች ውስጥ ተናጋሪው አላህ ከሆነ ለምን በሦስተኛ ወገን ራሱን ይጠቅሳል?
- የመጽሐፍ ቅዱስ ግርጌ ልብ ብለን ብናይ (በተለይ የ1980 ውን የቀላል ትርጉም እትም) በተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል ልዩነት መኖሩን አንዱ ጥቅስ በሌላኛው መጽሐፍ ቅዱስ አለመኖሩን፣ በጥንት ቅጅ ያለው ከዚህኛው እንደሚለይ፣ ተጨማሪ ቃል፣ ሀረግ፣ ዓረፍተ ነገር እንዳለው አልያም እንደተጨማረ በብዛት ይገልጻል፡፡ ይህ ምንን ያሳየናል? በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ልዩነት፣ ቅራኔ እና ግጭት መኖሩን አያሳይምን? ታዲያ ይህ ሁሉ እያለ ክርስቲያኖች እንዴት በየዋህነት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥብቅና ይቆማሉ?
በጥንት ዘመን የጽሕፈትና የኮፒ ማሽኖች ስላልነበሩ መጻሕፍት ይገለበጡ የነበሩት በጽሑፍ ባለሙያዎች ነበር፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች በሚገለብጡበት ወቅት ፊደላትን መግደፍ፣ ቃላትን መዝለል፣ ቦታ ማቀያየር እና የመሳሰሉት ስህተቶች ይፈጠራሉ፡፡ የኃይማኖት መጻሕፍትን ጨምሮ የትኛውም ጥንታዊ ሰነድ ከንደነዚህ ዓይነት ችግሮች የፀዳ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ስልጣን ከርሱ በፊትም ሆነ በኋላ ከተጻፉ ጥንታዊ መዛግብ ሁሉ የላቀ በመሆኑ የግልበጣ ስህተቶች ተዓማኒነቱን አጠራጣሪ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ በአንዱ ብራና ውስጥ የተዘለለ ወይንም ደግሞ የተገደፈ ክፍል ቢኖር በሌሎች ብራናዎች ውስጥ ተስተካክሎ ይገኛል ወይንም ደግሞ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመነሳት ትክክለኛውን አጻጻፍ ማወቅ ይቻላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ ከተባሉት የግልበጣ ስህተቶች መካከል አብዛኞቹ እዚህ ግቡ የሚባሉ ካለመሆናቸው የተነሳ ሊተረጎሙ እንኳ የማይችሉ ናቸው፡፡ የከፉ የሚባሉቱ ደግሞ እንደ ስም እና ቁጥር ስህተቶች ያሉ ዋናውን መልዕክት ሊነኩ የማይችሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል በቀድሞ የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም (1954 እትም) 2ነገሥት 8፡26 አካዝያስ በነገሠ ጊዜ እድሜው 22 ዓመት እንደነበር ሲገልፅ 2ዜና 22፡2 ግን 42 ዓመቱ እንደነበር ይናገራል፡፡ ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎችን ስንመለከት የእብራይስጡ 42 ሲል የሱርስት እና አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ቅጆች 22 እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት የጥንታውያን መዛግብት ምሑራን ትክክለኛው 22 እንደሆነና 42 የሚለው የግልበጣ ስህተት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ (አዲሱ መደበኛ ትርጉም 2ዜና 22፡2 የግርጌ ማስታወሻ ይመልከቱ)፡፡ እንደነዚህ ባሉ ጥቃቅን ችግሮች ምክንያት የትኛውም ጥንታዊ ሰነድ ተዓማኒነት እንደሚጎለው አይታሰብም፡፡ በዘርፉ እውቀት ያላቸው ምሑራን እነዚህን ችግሮች እንደ አሳሳቢ ችግሮች አይቆጥሯቸውም ነገር ግን ስለጉዳዩ እውቀት የሌላቸው ወገኖች ግራ ሊጋቡ ይችላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒ እንዳልሆነ ለማሳየት የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ የሚገኙ ተቃዋሚዎች የሚነዙት የተጋነነ ፕሮፓጋንዳ ሲታከልበት ደግሞ ውዥንብሩ ይብሳል፡፡ ዶ/ር ባርት አህርማንን (Bart Ehrman) የመሳሰሉ ለክርስትና ጥላቻ ያላቸው ምሑራን በጥንታዊ መዛግብት ጥናት ዘርፍ ያላቸውን እውቅናና የሚድያ ሽፋን በመጠቀም ለገንዘብ ትርፍ በማሰብ ይህንን ጉዳይ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲያውሉት እና የዋሁን ሕዝብ ሲያወናብዱ ይታያሉ፡፡ ሙስሊም ወገኖች ደግሞ ፕሮፓጋንዳውን ከነብጉሩ በመቅዳት ያስተላልፉታል፡፡ እነዚህ ወገኖች ለሚሰሟቸው ሰዎች የማይነግሩት አንድ እውነታ ቢኖር የእነርሱ መጽሐፍ የከፋ ችግር እንዳለበት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ የሆነውን ቁርኣንን ብንወስድ የመጀመርያዎቹ ቅጂዎች ብዙ መለያየቶችና ግጭቶች ስለነበሩባቸው ዑስማን የተባሉ ኻሊፋ (የሙስሊሞች መሪ) በአራት ሊቃውንት አማካይነት እርማት ተደርጎ አንድ መደበኛ ቅጂ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ የበፊቶቹ ቅጂዎች እንዲቃጠሉ እንዳደረጉ በጥንታውያን የእስልምና የታሪክ መዛግብት ውስጥ ተጽፎ የተቀመጠ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ጥንታውያን ቅጂዎቹ በመቃጠላቸው ምክንያት ሙስሊም ወገኖች አሁን ያሉት ቁርአኖች ከቀዳሚያን ጽሑፎች ጋር አንድ መሆናቸውን ሊያረጋግጡ የሚችሉበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም፡፡ እነዚያን ቀዳሚያን ጽሑፎች የሚያውቁ ሙስሊሞች ጥለዋቸው ያለፏቸው ሰነዶች እንደሚያመለክቱት አሁን ባሉትና በቀደምት ቁርአኖች መካከል የሚገኙት ልዩነቶች በእጅጉ አስደንጋጭ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት የተገኙ የተለያዩ አሁን ያሉትን ቁርአኖች ያስገኙ የእጅ ጽሑፎች ብዙ የግልበጣ ስህተቶችና እርማቶች እንዳሏቸው ታውቋል፡፡[29] (በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ኋላ የምንለው ይኖረናል፡፡)
ነገር ግን የጥንት ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን እንኳንስ ሊያቃጥሉ ይቅርና ሊያቃጥሏቸው ለሚፈልጉ ሰዎች አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ ሞትን በመምረጥ ብዙዎቹ ሰማዕታት ሆነዋል፡፡ ክርስቲያን አባቶች ጥንታዊያን የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፎች የግልበጣ ስህተቶች ቢኖሩባቸውም እንኳ ከማቃጠል ይልቅ በክብር ያስቀምጧቸው ነበር፡፡ ይህም ደግሞ ትክክለኛውን አነባበብ በመመርመር ማወቅ እንድንችል ረድቶናል፡፡ ስለ ቁርኣን የግልበጣ ስህተቶች ያነሳንበት ምክንያት ሙስሊም ወገኖቻችንን ለማስከፋት ወይንም ደግሞ ኃይማኖታቸውን ለመንቀፍ ፈልገን አይደለም፡፡ ነገር ግን ብዙ ጸሐፊያኖቻቸው መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ የሚጠቅሷቸው አንዳንድ ችግሮች በከፋ ሁኔታ በቁርኣን ላይ የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን እንዲያውቁና ሁለቱንም መጻሕፍት በአንድ ሚዛን መመዘን እንዲጀምሩ ለማሳሰብ ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የግልበጣ ስህተቶች የተለያዩ የእጅ ጽሑፎችን ጎን ለጎን በማስተያየት ትክክለኛዎቹ ምንባቦቻቸው ሊታወቁ የሚችሉ ናቸው፡፡ በሊቃውንት እጅ የሚገኙት አብዛኞቹ ብራናዎች በስደት ዘመን የተገለበጡ በመሆናቸው ጸሐፍቱ ሌሊት መብራቶችን በመጠቀም ወይም ዋሻዎች ውስጥ በመደበቅ ነበር ሲገለብጡ የነበሩት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ብዙ ጸሐፍት በአንድ ክፍል ውስጥ ይሰበሰቡና አንድ አንባቢ ከፊት ሆኖ እያነበበላቸው ይገለብጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ስህተቶች የመፈጠራቸው ሁኔታ ይሰፋል፡፡ ነገር ግን ነባር ሊቃውንት በዚህ ሁኔታ ችግር እንዳለበት ያረጋገጡት የአዲስ ኪዳን ክፍል ከሁለት በመቶ ያነሰ ነው፡፡ 98.33 ከመቶ የሚሆነው የአዲስ ኪዳን ክፍል ከመሰል ችግሮች የፀዳ ነው፡፡ ብሩስ መዝገር የተሰኙ ዕውቅ የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ሕየሳ (Textual Criticism) ሊቅ አዲስ ኪዳን 99.5 ከመቶ የተጠበቀ መሆኑን በማረጋገጥ ጽፈዋል፡፡[30] ከእነዚህ በጣት ከሚቆጠሩት ችግሮች መካከል ዋናውን የእምነት መሠረት የሚነካ አንድም እንኳ የሌለ ሲሆን የምንባቡን ትርጉም ሊለውጡ የሚችሉትን ልዩነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ የግርጌ ማስታወሻዎች በማስቀመጥ አንባቢያን እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ ቁርኣንን ጨምሮ ከጥንት ሰነዶች መካከል በዚህ የጥራት ደረጃ የተጠበቀ መሆኑ የተረጋገጠ አንድም ጽሑፍ የለም! (በእርግጥ ቁርኣን ከ600 ዓ.ም. ወዲህ ስለተጻፈ በሊቃውንት ዘንድ እንደ ጥንታዊ ሰነድ አይቆጠርም፡፡) የመጀመርያው የመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት በነዚህ ምንባቦች ውስጥ የተጠበቀ በመሆኑ በእውነቱ ከሆነ መሰል ችግሮች ሊያሳስቡን የሚገቡ አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር እነዚህ ችግሮች እንዳይከሰቱ የማድረግ ኃይል ቢኖረውም ነገር ግን ቅዱስ ቃሉ በተፈጥሯዊ መንገድ ተጠብቆ እንዲኖር መርጧል፡፡
በሙስሊም ሊቃውንትና በክርስቲያን ሊቃውንት መካከል ያለው ልዩነት ክርስቲያን ሊቃውንት እነዚህን የተለያዩ ምንባቦች በታማኝነት ይፋ በማድረግ እያንዳንዱ ምዕመን እንዲያውቅ የሚያደርጉ ሲሆኑ ሙስሊሞቹ ግን መሰል ልዩነቶች እንዳይታወቁ መሸሸጋቸው ነው፡፡ የቁርኣንን የእጅ ጽሑፎች ልክ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ በጥልቀት ለማጥናት የሞከሩ ሊቃውንት ተገድለዋል፡፡[31] አንዳንድ የቁርኣን ተርጓሚዎች እነዚህን ልዩነቶች ይፋ ለማድረግ የደፈሩ ሲሆን ዶ/ር ረሻድ ኸሊፋ የተሰኘው ተርጓሚ አንድ የቁርኣን ጥቅስ ጭማሬ መሆኑን በመግለፅ ከትርጉሙ ውስጥ እንዲወጣ በማድረጉ ምክንያት ተገድሏል፡፡[32] “አትላንቲክ መንዝሊ” የተሰኘ መጽሔት የቁርኣንን በትክክል ተጠብቆ መቆየት የሚገመግም ጽሑፍ ይዞ በመውጣቱ ምክንያት በሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር፡፡[33] ሙስሊም ወገኖች ስለ ቁርኣን በትክክል ተጠብቆ መቆየት የሚናገሩት ንግግር ሁሉ ትክክለኛ ምሑራዊ ጥናት በማድረግ ላይ ያልተመሠረተና ከባዶ መፈክር ያላለፈ ነው፡፡
6. አሕመዲን ወንጌልን በተመለከተ እንዲህ በማለት ይጠይቃሉ፡-
- የዛሬዎቹን አራቱን ወንጌሎች ስናይ በአብዛኛው “የኢየሱስ ታሪክ” ነው የሚተርኩት፡፡ ስለ አወላለዱ፣ ስለ አሰባበኩ እና ስለደረሰበት ችግር ወዘተ. ያወራሉ ነገር ግን ኢየሱስ በሚከተሉት ስፍራዎች የሚያስተምረው (የሚሰብከው) ከአምላክ እንደሰጠው ገልጿል፡-
- “እኔ ከራሴ አልተናገርሁም፤ ነገር ግን የላከኝ አብ ምን እንደምናገርና እንዴት እንደምናገር አዘዘኝ፡፡ የእርሱ ትእዛዝ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እንደሚያደርስ አውቃለሁ፤ ስለዚህ የምለው ሁሉ አብ እንድናገረው የነገረኝን ነው፡፡” (ዮሐንስ 12፡49-50)
- “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው፡፡ ማንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ቢፈልግ የእኔ ትምህርት ከእግዚአብሔር ወይም ከራሴ የመጣ መሆኑን ለይቶ ያውቃል፡፡”
(ዮሐንስ 7፡16-17) - “ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰው ልጅን ከፍከፍ ባደረጋችሁ ጊዜ፤ ያ ያልሁት እርሱ እኔ እንደምናገር፤ በራሴም ፈቃድ ምንም እንደማላደርግ ታውቃላችሁ” (ዮሐንስ 8፡28)
- “ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም፡፡” (ዮሐንስ 14፡24)
- “እግዚአብሔር ለእርሱ የሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ራዕይ ይህ ነው፡፡” (የዮሐንስ ራዕይ 1፡1)
- “ወንጌል” ማለት ኢየሱስ ከአምላክ የተሰጠውና የሰበከው ከሆነ እንዲሁም ዛሬ ያሉት ወንጌሎች “ትክክለኛ ናቸው ” ከተባለ ኢየሱስ ከአምላክ የተሰጠውና የሰበከው ስለ አወላለዱና የሕይወት ታሪኩ ነበርን? እንዴት እንደተወለደ፣ እንዴት እንደሚሰቃይ ወዘተ. ነበርን? ምክንያቱም አራቱ “ወንጌሎች” ይህንን ነው በአብዛኛው የሚተርኩት፡፡
ከአራቱ ወንጌላት መካከል ማርቆስና ዮሐንስ የኢየሱስን ልደት ስለማይተርኩ ጸሐፊው በተሳሳተ ዓረፍተ ነገር ነው ጥያቄያቸውን የቋጩት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር እንዴትና ለምን ዓላማ እንደመጣ (ዮሐንስ 8፡42፣ 56-58)፣ ስለ ሞቱና ስለ ትንሳኤው (ማቴዎስ 17፡22-23፣ ማርቆስ 9፡30-31፣ ሉቃስ 18፡32-33)፣ እነዚህ የሕይወቱ ገፅታዎች ለሰው ልጆች ያላቸውን እንድምታ (ማቴዎስ 20፡28)፣ ስለ ዳግም ምፅዓቱ (ማቴዎስ 24፡30)፣ ወዘተ. አስተምሯል፡፡ ጠያቂው በጠቀሷቸው ጥቅሶች መሠረት ኢየሱስ ከአብ የሰማውን ብቻ ካስተማረና ከራሱ አንዳች ካላስተማረ፤ ከአብ የተቀበላቸው ትምህርቶች እነዚህንም ያጠቃልላሉ ማለት ነው፡፡ “ወንጌል” የሚለው ቃል “ኢዋንጌሊዮን” ከሚል የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን “የምስራች/ መልካም ዜና” ማለት ነው፡፡ ወንጌል የኢየሱስን ልደት፣ ትምህርቶቹን፣ እኛን በደሙ መዋጀቱን፣ ትነሣኤውን፣ ዕርገቱንና ዳግም ምፅዓቱን ያጠቃልላል፡፡ ወንጌል በአጠቃላይ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነትና ሥራ ነው (ሮሜ 1፡3-4፣ የሐዋርያት ሥራ 8፡35)፡፡ ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ የሰበኩት ወንጌል ይህ ነው፡፡ “አራቱ ወንጌላት” በመባል የሚታወቁት መጻሕፍት አንዱን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በአራት መንገዶች የሚያቀርቡ እንጂ አራት የተለያዩ ወንጌላት አይደሉም፡፡
ጠያቂው የጠቀሷቸውን ጥቅሶች ከአውድ ገንጥለው አውጥተዋቸዋል፡፡ በዮሐንስ 12፡49-50 ላይ የሚገኘው ከቁጥር 24 ጀምሮ ኢየሱስ ለተናገረው ሐሳብ ማጠቃለያ ሲሆን እንደሚሞትና እንደሚነሳ የተናገረውን ቃል ማመን ለተሳናቸው አይሁድ የተነገረ ነበር፡፡ ኢየሱስ ሞትና ትንሳኤው የአብ መልእክትና ትዕዛዝ መሆኑን እየተናገረ ነው፡፡ ዮሐንስ 8፡28 ላይ “የሰው ልጅን ከፍከፍ ባደረጋችሁ ጊዜ” በማለት ሲናገር ስቅለቱን ለማመልከት ነው (ዮሐንስ 12፡32-33 ይመልከቱ)፡፡ በምዕራፉ ውስጥም የተናገራቸው አብዛኞቹ ነገሮች የእርሱን ማንነትና ከአብ ጋር ያለውን አንድነት የሚገልጡ ናቸው፡፡ ዮሐንስ 14 ምዕራፉ በሙሉ የሚናገረው ኢየሱስ እና አብ አንድ ስለመሆናቸውና መንፈስ ቅዱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ በመምጣት ኢየሱስ የጀመረውን አገልግሎት ስለመቀጠሉ ነው፡፡ የዮሐንስ ራዕይ የዓለምን ፍጻሜ የተመለከተ ሲሆን የኢየሱስን ምፅኣት ይተነብያል፡፡ የተጠቀሱት ጥቅሶች ሁሉ ወንጌል የኢየሱስን ማንነትና ሥራ የተመለከተ መሆኑን የሚያረጋግጡ እንጂ የጠያቂውን የተሳሳተ ግንዛቤ የሚደግፉ አይደሉም፡፡ ኢየሱስ “ኢንጂል” የተሰኘውን እስላማዊ መጽሐፍ መቀበሉን የሚያመለክት ምንም ዓይነት ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም፡፡
ቁርኣን “ኢንጂል” የተሰኘው መጽሐፍ ለዒሳ እንደተሰጠ የሚናገር ሲሆን ይዘቱ ምን እንደሆነ አያብራራም፡፡ ነገር ግን ይህ “ኢንጂል” በሙሐመድ ዘመን በነበሩት ክርስቲያኖች እጅ እንደሚገኝ ይናገራል (ሱራ 5፡47፣ 5፡68)፡፡ በሙሐመድ ዘመን በክርስቲያኖች እጅ የነበረው ብቸኛ ወንጌል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በአራቱ መጻሕፍት ውስጥ የሰፈረው እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ወንጌል ደግሞ ለኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠ መጽሐፍ ሳይሆን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት ነው፡፡ የቁርኣን ጸሐፊ የወንጌልን ምንነትና ትክክለኛ ይዘት ፈፅሞ የማያውቅ ሰው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
- ዮሐንስ 20፡30-31 “ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌሎች አያሌ ታምራዊ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጎአል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እንድታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተፅፎአል” ይላል፡፡ ታድያ የኢየሱስ ታሪክ በሙሉ አልተጻፈም ማለት ነውን? ታድያ ሙሉ ሳይሆን ይህ የተጻፈው ለምን ይሆን? ወይስ ሌሎች በርካታ በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ያልተፃፉ ታሪኮች ኢየሱስ ተዓምር ሲያሳይ ስለ አምላክ የተናገራቸውና ጸሐፊዎቹ እንዳናውቅ የፈለጉት ነገር ኖሮ ይሆን?
ውድ አሕመዲን ጥርጣሬና ግምት ማስረጃ ሊሆን ይችላልን? የኢየሱስን ደቀ መዛሙርትና ጓዶቻቸውን ለመጠራጠር የሚያበቃ ምን ምክንያት አለ? ከእነርሱ ዘመን በኋላ 600 ዓመታትን በመዘግየት የተጻፈውን ሐሰተኛ ሰነድ ከስህተቱ ለማዳን የሚችሉበትን ቀዳዳ ለማግኘት ይህን ያህል ከመፍጨርጨር ለእውነት እጅ መስጠት የሚሻል አይመስልዎትም?
ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነትና ሥራ ማወቅ የሚያስፈልገንን ያህል ተጽፎልናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በማመን የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት የተጻፈው በቂ ነው፡፡ የእርሱን ሥራና ትምህርት በተመለከተ ሙሉ ምስል ማግኘት የሚያስችለንን መረጃ ስላገኘን ምንም የቀረብን ነገር የለም፡፡ መጽሐፍ ሲጻፍ ጊዜና ቦታን ባገናዘበ ሁኔታ በመሆኑ አንድ ጸሐፊ ሁሉንም መረጃዎች የሚወክሉ ነገሮችን እንጂ ሁሉንም መረጃዎች አያካትትም፡፡ ዮሐንስ ደግሞ ኢየሱስ ያደረጋቸው ሁሉ እርሱ በጻፈው መጽሐፍ ውስጥ እንዳልተካተቱ እንጂ በሌሎች መጻሕፍት ውስጥ እንዳልተጻፉ አልተናገረም፡፡ ዮሐንስ ኢየሱስ ካደረጋቸው ተዓምራት መካከል ሰባቱን የዘገበ ሲሆን አምስቱ በሌሎች ወንጌላት ውስጥ አይገኙም፡፡ በሦስቱ ተመሳሳይ ወንጌላት ውስጥ 29 ተዓምራት ተጠቅሰዋል፡፡
7. የትኞቹ መጽሐፍት ናቸው “ቅዱሳን” በሚለው ላይ ብርቱ ክርክር ነበር፡፡ በመጨረሻም ጉዳዩ በድምፅ ብልጫ ነው የተወሰነው፡፡ ክርክር መነሳቱ በራሱ ዛሬ ባሉበት መጽሐፍት ላይ ጥቂትም ቢሆን ጥርጣሬን አያጭርምን?
አዲስ ኪዳንን በተመለከተ “ብርቱ” ክርክር መኖሩንም ሆነ በድምፅ ብልጫ መወሰኑን የሚያመለክት የታሪክ ማስረጃ የለም፡፡ ነገር ግን ቁርኣንን በተመለከተ የትኞቹ ሱራዎች መካተት እንዳለባቸው በመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች መካከል ብርቱ ክርክር ነበር፡፡ በመጨረሻም ጉዳዩ ኡስማን በተሰኘው ካሊፋ አስገዳጅነት ወደ ፍፃሜ የመጣ ሲሆን እርሱ የመረጠው ጸድቆ በፊት የነበሩት መጻሕፍት በሙሉ እንዲቃጠሉ ተደርጓል፡፡
8. በማቴዎስ 16፡28 ላይ “እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ” ይላል፡፡ ነገር ግን እንኳን ኢየሱስ ተመልሶ ሲመጣ ሊያዩ ይቅርና ያኔ ከነበሩት ውስጥ አንዱም ሰው ያን ክፍለ ዘመን የተሻገረ የለም፡፡ በዚያው ክፍለ ዘመን ሞትን ያልቀመሰ የለም፡፡ ሁሉም ያኔ ጥንት ነው! ከ1900 ዓመታት በፊት ነው ሁሉም ያለቁት፡፡ ታድያ ጥቅሱ ስህተት ነውን?
ጥቅሱ ስህተት አይደለም፡፡ ስህተቱ ያለው በጠያቂው መረዳት ውስጥ ነው፡፡ ማቴዎስ 16፡28 የክርስቶስን መለኮታዊ ክብር መገለጥ የሚያመለክት እንጂ ዳግመኛ ምፅኣቱን የሚያመለክት አይደለም፡፡ ይህ ቃል ከስድስት ቀናት በኋላ እንደተፈጸመ በማቴዎስ 17፡1-3 ላይ እንዲህ ተጽፎ እናነባለን፡-
“ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው፡፡ ፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ፡፡ እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው…”
2ጴጥሮስ 1፡16-18 ላይ የተጻፈው ቃልም ይህንኑ የሚረጋግጥ ነው፡-
“የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ፡፡ ከገናናው ክብር በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን፡፡”
በተጨማሪም ይህ ትንቢት በበዓለ ሃምሳ እለት የክርስቶስ መንግሥት በምድር ላይ በሚታይ ሁኔታ መመሥረቱን የተመለከተ ሊሆን ይችላል (የሐዋርያት ሥራ 2)፡፡
9. በቀላል ትርጉም የ1980 እትም መጽሐፍ ቅዱስ የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 16 ቁጥር 8 ሥር በቀረበው የግርጌ ማስታወሻ ላይ “በአያንዳንድ የጥንት መጽሐፍት በዚህ ምዕራፍ በቁጥር 8 ቀጥሎ ያለው ቃል ይገኛል” ይልናል የሚከተለውን አስፍሯል፦ “ሴቶቹ ወደ ጴጥሮስና ወደ ጓደኞቹ ሄደው መልአኩ የነገራቸውን ሁሉ አወሩላቸው፣ ከዚያ በኋላ ኢየሱስ እራሱ ለዘለዓለም ድነት የሆነውን የማይለወጠውንና ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያ ድርስ በደቀ መዛሙርቱ አማካኝነት ላከ” ይላል፡፡ ያ የተላከው ወንጌል የት ሄዶ ነው ሌላ የተጻፈው? ጠፋ? በጉባኤ ድምፅ ብልጫ ውድቅ ተደርገ?
በእርግጥ ይህ ጥቅስ በማቴዎስና በሉቃስ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን የታላቁ ተልዕኮ መልዕክታት ጨምቆ የሚያቀርብ ቢሆንም ተዓማኒ በሆኑት ጥንታዊ የማርቆስ ወንጌል ቅጂዎች ውስጥ አይገኝም፡፡ ቢሆንም ግን የጠያቂውን የተሳሳተ መረዳት የሚያንጸባርቅ ምንም ነገር በዚህ ቦታ አይገኝም፡፡ ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ አማካይነት የላከው ወንጌል (የምስራች) የተጠረዘ ወይም የተጠቀለለ መጽሐፍ ሳይሆን የአዳኝነቱን መልዕክት ነው፡፡ ይህ መልዕክት ነው ከጊዜ በኋላ በመጽሐፍ የሰፈረው፡፡
10. የኢየሱስ ተከታዮች ጠላት የነበረው ሳውል (በኋላ ጳውሎስ የተሰኘው) አማኞን አሳዷል፡፡ እንዲታሰሩ ተስማምቷል፡፡ በኋላ ላይ ጳውሎስ “ኢየሱስ ተገልጦልኛል ሐዋርያት ነኝ” ብሎ ስለ ራሱ ተናገረ፡፡ ተቀበሉት፡፡ ግና በ1ኛ ቆሮንቶስ 8፡40 ላይ “እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ያለ ይመስለኛል ፡፡”ብሏል፡፡ እምነት በይመስለኛል ያስኬዳልን?
ሐዋርያው ለምን ይህንን እንዳለ ከመግለጻችን በፊት እስኪ ስለ ጥሪው ያለውን እርግጠኛነት የሚያሳዩ ጥቅሶችን እንመልከት፡-
“ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ” (1ቆሮንቶስ 14፡37)፡፡
“በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤” (ገላቲያ 1፡1)
“ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም” (ገላቲያ 1፡12)፡፡
“ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል፤ አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ” (ኤፌሶን 3፡2-3)፡፡
“እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም” (1ቆሮንቶስ 2፡4-5)፡፡
“እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና” (2ጢሞቴዎስ 1፡7)
“ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው” (2ቆሮንቶስ 1፡22)
በሐዋርያው ጳውሎስ ጸሎት አማካይነት ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎች ይቀበሉ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 19፡1-7)፡፡ የእርሱ ጽሑፎች ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት እኩል እንደሆኑ ሐዋርያው ጴጥሮስ መስክሯል (2ጴጥሮስ 3፡15-16)፡፡ እውነተኛነቱ በድንቅና በተዓምራት ተረጋግጧል፡- “እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር፡፡” (የሐዋርያት ሥራ 19፡11-12፣ በተጨማሪም 14፡8-11፣ 16፡16-18፣ 20፡8-12)፡፡
ታዲያ በዚህ ቦታ “ይመስለኛል” በማለት ጥርጣሬን በሚያሳይ ቃል ስለምን ተናገረ? ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ ጊዜ በምፀታዊ ንግግር ለተቃዋሚዎቹ መልስ የመስጠት ልማድ ነበረው፡፡ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳለባቸውና ነቢያት እንደሆኑ በትዕቢት የሚናገሩ፣ ደግሞም አለን በሚሉት መንፈሳዊ ዕውቀት የሚታበዩ ወገኖች ነበሩ፡፡ ሐዋርያው ምፀታዊ በሆነ መንገድ ለእነርሱ ምላሽ ለመስጠት እንጂ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ እንዳለ ጥርጣሬ ስላለው አይደለም (8፡1-3፣ 14፡37)፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስን ለመንቀፍ እንዲህ የተጣደፉት አሕመዲን የጥንት ሙስሊሞች ሐዋርያው ጳውሎስ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ መሆኑን መመስከራቸውን ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? መቼስ ለገዛ መጻሕፍታቸው እንግዳ ስለሆኑ እኛው እናሳያቸው እንጂ፡፡
ኢብን ኢስሐቅ የተሰኘው ቀዳሚውን የሙሐመድ ግለ ታሪክ የከተበ ሙስሊም እንዲህ ሲል ጽፏል፡-
“ዒሳ የመርያም ልጅ የላካቸው ደቀ መዛሙርትና ከእነርሱ በኋላ የመጡት በአገሪቱ ውስጥ የነበሩት እነዚህ ነበሩ፡- ደቀ መዝሙሩ ጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ደግሞ ጳውሎስ ወደ ሮም ተላኩ፡፡ (ጳውሎስ ከተከታዮቹ መካከል ሲሆን ደቀ መዝሙር አልነበረም፡፡) እንድርያስና ማቴዎስ ወደ በላዔ-ሰብዕ ምድር፤ ቶማስ በምስራቅ ወደሚገኘው ወደ ባቤል ምድር፤ ፊልጶስ ወደ ካርቴጅና ወደ አፍሪካ፤ ዮሐንስ የዋሻዎቹ ወጣቶች ምድር ወደሆነው ወደ ኤፌሶን…”[34]
የኢብን ኢስሐቅ ጽሑፍ ሳሂህ አል-ቡኻሪ እና ሳሂህ ሙስሊምን ከመሳሰሉት ሐዲሳት እንኳ የሚቀድም የሙሐመድ ግለ ታሪክ ነው፡፡ በቅንፍ ውስጥ የተቀመጠው ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የእርሱ ተከታይ እንዳልነበረ በትክክል የሚገልፅ በመሆኑ ስህተት የለበትም፡፡
የእስልምና ጀማሪ የሆኑት ሙሐመድ ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈውን ከጠቀሱ በኋላ የአላህ ቃል መሆኑን መመስከራቸውንስ አሕመዲን ጀበል ያውቁ ይሆን?
“ነገር ግን፦ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን” (1ቆሮንቶስ 2፡9)፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ሐዋርያው ጳውሎስ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱትን የእግዚአብሔር ተስፋዎች በራሱ አባባል ጨምቆ ያስቀመጠበት ዓረፍተነገር ሲሆን ከእርሱ በሚቀድም በየትኛውም ምንጭ ውስጥ በዚህ መልኩ ተጽፎ አይገኝም፡፡ ሙሐመድ እንዲህ ጠቅሰውታል፡-
“አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ እንዲህ አለ ‹እኔ ለታማኝ ባርያዎቼ ዓይን ያላየችውን፣ ጆሮ ያልሰማውን የሰው ልብ ሊያስበው የማይችለውን (አስደናቂ ነገሮች)› አዘጋጅቻለሁ፡፡››”[35]
አሕመዲን ጀበልን የመሳሰሉት ሙስሊም ጸሐፊያን በጌታ ተጠርቶ እስከ ሞት ድረስ በመታመን ሰማዕት የሆነውን ቅዱስ ሐዋርያ ለማብጠልጠል አንደበታቸውን ከመክፈታቸው በፊት የገዛ ምንጮቻቸውን ማጥናት ነበረባቸው፡፡
11. ጳውሎስ በ 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡8 ላይ “ከሙታን የተነሳውን፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፣ የእኔም ወንጌል ይሄው ነው” ብሏል፡፡ ጳውሎስ “የእኔ ወንጌል ይኸው ነው፡፡” ሲል እርሱም ወንጌል አለው እንዴ? የሌሎቹ ወንጌልስ? እንዲሁ ጳውሎስ “በክርስቶስ ፀጋ የጠራችሁን እርሱን ትታችሁ ወደ ተለየ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ መዞራችሁ ደንቆኛል፡፡” (ገላትያ 1፡16) ብሏል፡፡ ጳውሎስ ይህንን ሲናገር ዛሬ የምናውቃቸው አራቱም “ወንጌላት” (የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌላት) አንዳቸውም አልተጻፉም ነበር፡፡ ይህንን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትም ሆነ ስለ መጽሐፎቹ አጻጻፍ ቅድመ ተከተል ከሚገለፁ መጻሕፍት መረዳት ይቻላል፡፡ ታድያ ጳውሎስ “የእኔ ወንጌል” እና “ወደ ተለየ ወንጌል” ሲል የጠራቸው ወንጌላት የትኞቹ ናቸው?
ሐዋርያው በአሕዛብ መካከል ስለሚሰብከው ወንጌል እንጂ ስለ ተጻፈ መጽሐፍ እየተናገረ አይደለም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በአሕዛብ መካከል፤ ጴጥሮስ ደግሞ በአይሁድ መካከል የሚደረጉትን ስብከተ ወንጌል እንዲመሩ እግዚአብሔር እንደጠራቸው ካረጋገጡ በኋላ ወደየ አገልግሎታቸው እንደተሰማሩ ተጽፏል (ገላቲያ 2፡7-9)፡፡ ሐዋርያው በአሕዛብ መካከል የሚሰብከውን የወንጌል መልዕክት ነው “የእኔ ወንጌል” በማለት የጠራው፡፡ “የተለየ ወንጌል” በማለት የጠራው ደግሞ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንደሚድኑ የሚናገረውን የፀጋ ወንጌል የሚፃረረውን “መዳን በመገረዝና ሕግን በመጠበቅ ነው” የሚለውን ሰው ሰራሽ “ወንጌል” ነው፡፡ አንዳንድ አይሁድ ክርስቲያኖች ይህንን የተለየ “ወንጌል” ይሰብኩ ስለነበር ጳውሎስና በርናባስ ከእነርሱ ጋር ክርክር ከገጠሙ በኋላ ለመጀመርያው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ መጠራት ምክንያት ሆኖ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 15)፡፡
12. ሉቃስ 1፡1-4 ላይ “በእኛ መካከል ስለ ተፈፀሙት ነገሮች ብዙዎች ታሪኩን የተቻላቸውን ያክል ጽፈውት ይገኛል፣ ይህም ታሪክ ከመጀመሪያው አንስቶ የዐይን ምስክሮች የቃሉ አገልጋዮች የነበሩ ያስተላለፋልን ነው፡፡ ክብር ቴዎፍሎስ ሆይ! እኔም በበኩሌ ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመርሁ በኋላ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ልጻፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ፣ ይህንን የማደርገው የተማርከው እውነት መሆኑን እንድታውቅ ነው” ብሏል፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ “ብዙዎች ታሪኩን የተቻላቸው ያክል ጽፈው ይገኛል” ያለው ይሁን ሌላኛው ወንጌል?
አይደለም፣ የክርስቶስን ወንጌል በማጣመም አንዳንድ ቀናዒ አይሁዳውያን የሰበኩትን “ወንጌል” ነው፡፡ የገላቲያ መልዕክት ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ ይህንን የተለየ “ወንጌል” ለመቃወም የተጻፈ ነው፡፡ ጠያቂው የማይገናኙ ጥቅሶችን በማገናኘት አዲስ ምናባዊ ታሪክ ለመፍጠር ከሚደክሙ በሰከነ መንፈስ እውነትን ለማወቅ መረጃዎችን ቢያገላብጡ መልካም ነበር፡፡
13. ወንጌሎቹ አንድ አይነት ከሆኑና ልዩነት ከሌላቸው ጳውሎስ ለምን “ወደ ተለየ ወንጌል” ሲል ወቀሳቸው?
አንድ ዓይነት ናቸው ያለ የለም፡፡ ጳውሎስና ሐዋርያት የሰበኩት ወንጌል በክርስቶስ ትምህርት፣ የቤዛነት ሥራና ትንሳኤ ላይ ያተኮረ ሲሆን “የተለየ ወንጌል” የተባለው ደግሞ ስለመገረዝና የአይሁድን ሕግ ስለመጠበቅ የሚናገር ነበር፡፡
14. ሉቃስ “ብዙዎቹ ታሪኩን የተቻላቸው ያህል ጽፈውት ይገኛል” ሲል ብዙ ሰዎች የኢየሱስን ታሪክ እንደጻፉ ነግሮናል፡፡ ታድያ እነዚያ ብዙዎቹ የጻፉት የት ገቡ?
መጻሕፍቱ የክርስቶስን ታሪክ ለማስተማር በወቅቱ አገልግለው ይሆናል፡፡ ነገር ግን የክርስቶስን ታሪኮች ለመጻፍ የተደረጉ ሙከራዎች መሆናቸውን እንጂ እንደ አራቱ ወንጌላት በሐዋርያት እጅና ዕውቅና የተጻፉ ስለመሆናቸው ምንም ማስረጃ የለም፡፡ ነገር ግን አሁን በእጃችን ከሚገኙት ወንጌላት የተለየ መረጃ ሊሰጡን እደማይችሉ እርግጠኞች ሆነን መናገር እንችላለን፡፡ ሉቃስ የሚያውቃቸው ጽሑፎች ይዘት እርሱ ከጻፈው የተለየ ቢሆን ኖሮ ባልጠቀሳቸው ነበር፡፡ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመታት የተጻፉ መጻሕፍት ተጠብቀው መቆየት የሚችሉት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ባለ አክብሮትና ጥንቃቄ ከተያዙና ከተገለበጡ ብቻ ነው፡፡
15. እውን መንፈስ ቅዱስ ነድቶ የወንጌል ጸሐፊዎች እንዲጽፉ ካደረገ ለምን አራት ጊዜ ስለ አንድ ታሪክ መጻፍ አስፈለገ? አንዱ የረሳውን ሌላኛው እንዲሞላው? ወይስ ወንጌሎች ሲጋጩ እንድናነብ ፈልጎ ይሆን?
አራቱም ወንጌላት የየራሳቸው ዓላማ አላቸው፡፡ ማቴዎስ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ትንቢት የተነገረለት መሲህ መሆኑን ያስረዳል፣ ማርቆስ ኢየሱስ አገልጋይና ተዓምር አድራጊ መሆኑን ያስረዳል፣ ሉቃስ ኢየሱስ የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ መሆኑን ያስረዳል፤ ዮሐንስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ማቴዎስ አይሁድን፣ ማርቆስ ሮማውያንን፣ ሉቃስ አሕዛብን፣ ዮሐንስ ደግሞ የሰው ልጆችን በሙሉ ታሳቢ በማድረግ የተጻፉ ናቸው፡፡ ጠያቂው ይህንን ጥያቄ የጠየቁት በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ለማላገጥ እንጂ ለማስተማር እንዳልሆነ የመጨረሻው አባባላቸው ግልፅ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን የገዛ ቁርአናቸው አንድን ታሪክ እጅግ አሰልቺና እርስ በርሱ በሚጣረስ መልኩ መደጋገሙ ለምን እንደሆነ ብንጠይቃቸው መልሳቸው ምን ይሆን? ለምሳሌ ያህል ሱራ 2፡58-59 እና 7፡161-162፤ 27፡7፣ 20፡9-24 እና 28፡29፤ 20፡22 እና 28፡32፤ 7፡123፣ 20፡71 እና 26፡49፤ 2፡35 እና 7፡19፤ 20፡38-40 እና 28፡7-13፤ 7፡12-18፤ 15፡32-42፤ 17፡61-65፤ 38፡75-85 ያነፃፅሩ፡፡ ስለ ወንጌላት “ግጭት” ሊነግሩን የሚዳዳቸው ጠያቂው መጽሐፍ ቅዱስን ለመመዘን የሚጠቀሙትን ተመሳሳይ መስፈርት ቁርኣንን ለመመዘን የሚጠቀሙ ከሆነ እነዚህን አልተገናኝቶ ምንባቦች እንዴት ያስታርቋቸው ይሆን?
16. “የሐዋርያት ሥራ 20:35 ላይ “በጉልበታችን ደክመን ችግረኞችን መርዳት እንዳለብም ባደርግሁት ሁሉ አሳይቻለሁ፡፡ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው ያለውን የጌታ የኢየሱስን ቃል እናስታውስ” ይላል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ይህንን ያለበት ስፍራ በአራቱም ወንጌሎች ውስጥ ቢፈለግ አይገኝም፡፡ ታድያ ጳውሎስ ከየትኛው ወንጌል ይሆን ይህን ያገኘው? ምን አልባት በጉባኤና በድምፅ ብልጫ ካልተመረጡ ወንጌላት መካከል ይሆንን?
ኢየሱስ የተናገረውና ያደረገው በአራቱ ወንጌላት ውስጥ የተጻፈው ብቻ እንደሆነ የተናገረ ማንም የለም፡፡ ነገር ግን ጌታችን ስለ መስጠት አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ስላስተማረ ይህ ቃል በወንጌላት ውስጥ አለመመዝገቡ ምንም የሚያጎድለው ነገር የለም (ሉቃስ 6፡38፣ )፡፡ የኢየሱስ ንግግሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስከተጠቀሱ ድረስ በአራቱ ወንጌላት ውስጥ ብቻ እንዲሰፍሩ የሚያስገድድ ምን ሁኔታ አለ? አሕመዲን ጀበል “በድምፅ ብልጫ ስለተደረገ ምርጫ” ደጋግመው ቢናገሩም አንድም ጊዜ ማስረጃ እንዳልጠቀሱ ልብ በሉ! “ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል” የሚለውን ብሂል ከልባቸው የሚያምኑ ይመስላሉ፡፡
- ወንጌሎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርው ተጻፋ ብለው ያምናሉን? ወንጌሎች ይህንን ያረጋግጣሉን? እንደውም በተቃራኒ ቢያረጋግጡስ?
ቁርኣን ከላይ የወረደ መገለጥ ነው ብለው ያምናሉን? ቁርኣን “ወርጃለሁ” ከሚለው ባዶ ንግግር ባለፈ ይህንን ያረጋግጣልን? በተቃራኒው ቢያረጋግጥስ?
17. ጳውሎስ ደብዳቤዎቹን ያኔ ጽፎ ሲልክ ዛሬ እንደሆነው ለዓለም አስቦ ነበርን? ቢሆንማ ለምን አንዴም ቢሆን ለኢትዮጵያ/አፍሪካ ወዘተ. አልላከም? የተጻፈው ለዓለም ከሆነ ለምን “ለቆሮንቶስ”፣ “ለሮሜ”፣ “ለገላትያ”፣ “ለኤፌሶን ሰዎች” ወዘተ. ተላከ?
ዋናው ቁምነገር ጳውሎስ ማሰብ አለማሰቡ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ በእርሱ መጠቀሙ ነው፡፡ የጳውሎስ መልእክቶች በወቅቱ ክርስትናን ለተቀበሉት ሕዝቦች የተጻፉ ነበሩ፡፡ የጳውሎስ መልእክቶች ለተጠቀሱት አብያተ ክርስቲያናት የተላኩ ቢሆኑም ነገር ግን ዓለም አቀፋዊ ይዘት ስላላቸው ከዚያን ዘመን ጀምሮ እስከዚህ ዘመን ድረስ ላሉት በዓለም ዙርያ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ሁሉ መመርያ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ይህም የመልዕክቱ ደራሲ ሐዋርያው ጳውሎስ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ያሳያል፡፡ ቁርኣን ለዓለም ሁሉ የተላከ መጽሐፍ ከሆነ ለምን በሙሐመድ ዘመን በአረብያ የተከናወኑት ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኩራል? ባለፈው ክፍለ ዘመን በካይሮና በአማን በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ ሙስሊም ሊቃውንት እስኪፈቅዱ ድረስ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም ስለምን ተከልክሎ ቆየ?[36]
18. እውን ክርስቲያኖች እንደሚሉት እያንዳንዱ መጽሐፍት በመንፈስ ቅዱስ መጻፉን ቢያረጋግጡ ኖሮ የትኞቹን መቀበል እንዳለባቸው ለመወሰን ለምን በቀደምት ቤተ ክርስቲያን በርካታ ጭቅጭቅ ጉባኤ ተደርገ? ለምንስ ሰው ሰራሽ መስፈርቱ ለአምላክ ቃል ተቀመጠ? ለምንስ በድምፅ ብልጫ ፀደቀ? ለምን ዛሬም ድርስ የልዩነት ምንጭ ሆነ?
አብያተ ክርስቲያናት ልዩነቶችን ያንጸባረቁት በአዲስ ኪዳን ላይ ሳይሆን በብሉይ ኪዳን ላይ ነው፡፡ የአፖክሪፋ መጻሕፍትን እንደ ቃለ እግዚአብሔር የማይቀበሉትም ቢሆኑ መንፈሳዊ እሴት እንዳሏቸው መጻሕፍት ስለሚቆጥሯቸው ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ሙስሊም ወገኖች እንኳ “ሐዲስ ቁድሲ” በመባል የሚታወቁት ሐዲሳት እንደ ቁርኣን ሁሉ የአላህ ንግግሮች በመሆን አለመሆናቸው ላይ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ አንዳንዶች ከቁርኣን እኩል የሚቀበሏቸው ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ እንደ ሌሎቹ ሐዲሳት ይቆጥሯቸዋል፡፡
በአዲስ ኪዳን ዙርያ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ምንም ዓነት ልዩነት የለም፡፡ እነዚህንም መጻሕፍት ለማፅደቅ ምንም አይነት ጭቅጭቅ አልተደረገም፡፡ ጥቅም ላይ የዋሉት መስፈርቶችም ቢሆኑ መንፈሳዊ መስፈርቶች እንጂ ሰው ሰራሽ አይደሉም፡፡ በድምፅ ብልጫ የጸደቀ አንድም የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ የለም፡፡ በአዲስ ኪዳን ቀኖና ላይ ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡ ጠያቂው ለተናገሯቸው ነገሮች ምንም ዓይነት ማስረጃ ሊጠቅሱ አልቻሉም፡፡
19. እውን መጽሐፎቹ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉና ይህንንም የሚያረጋግጡ ከሆነ ለምን ዛሬም ድረስ በኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ እና ፕሮቴስታንት የተለያየ መጽሐፍ ቅዱስ አገልግሎት ላይ ዋለ? ለምንስ ነው ዛሬም ድረስ ስምምነት ላይ መድረስ ያልተቻለው?
ይህ ጥያቄ ሰፋ ያለ መልስ የሚሻ በመሆኑ እኔ ከማምንበት የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትና አቋም አኳያ እንደሚከተለው መልስ እሰጣለሁ፡፡
ቀኖና የሚለው ቃል “ካኖን” ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጓሜውም “የመለክያ ብትር” ወይም “ደንብ” ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል እስትንፋሰ-መለኮት መሆናቸው የሚታመንባቸውን የቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር ያመለክታል፡፡ ቀኖናን በተመለከተ በሰፊው የሚናፈሱ የተሳሳቱ አመለካከቶች ከመኖራቸው አንፃር እነዚህን ውዥንብሮች ለማጥራት አንድ መሰራታዊ የሆነ እውነት መጠቀስ ይኖርበታል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያን የቀኖና ውጤት እንጂ የቀኖና እናት አለመሆኗ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሠረት የሐዋርያት እና የነቢያት ትምህርት በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይህኛው ቀኖና ነው ያኛው ደግሞ ቀኖና አይደለም በማለት ሲለዩ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበትን መሠረት በማጤን እንጂ ለቤተ ክርስቲያን መሠረት እያጣሉላት አልነበረም ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደተባለው ቅዱሳን አባቶች የነቢያትና የሐዋርት ምንጭ ያላቸውንና የቤተ ክርስቲያን መሠረት የሆኑትን መጻሕፍት በመለየት አስታወቁ እንጂ አዲስ ነገር አልፈጠሩም፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የቀኖና ልጅ እንጂ የቀኖና እናት አይደለችም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቀኖና አገልጋይ እንጂ የቀኖና የበላይ አይደለችም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቀኖና ምስክር እንጂ የቀኖና ወሳኝ አይደለችም፡፡ የቀኖና ወሳኙ እግዚአብሔር እራሱ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመንፈሱ ምሪት በተጻፉት ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የራሱን “አሻራ” በማስቀመጥ ቀኖናን ወስኗል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ድርሻም ይህ “አሻራ” ያረፈባቸውን መጻሕፍት መለየት ነው፡፡[37]
የመጽሐፍ ቅዱስን ቀኖና በተመለከተ በተለያዩ የክርስትና ቤተ እምነቶች መካከል ልዩነቶች ይታያሉ፡፡ የወንጌላውን አብያተ ክርስቲያናት ቀኖና 66 መጻሕፍትን የያዘ ሲሆን የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 73 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ 81 መጻሕፍትን የያዙ ናቸው፡፡ በስድሳ ስድስቱ መጻሕፍት ዙርያ በነዚህ የክርስትና ቤተ እማነቶች መካከል ስምምነት ያለ ሲሆን ልዩነቱ የተፈጠረው አፖክሪፋ በመባል በሚታወቁት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዙርያ ነው፡፡ አፖክሪፋ ማለት የተሰወረ ወይም አጠራጣሪ ማለት ሲሆን እነዚህን መጻሕፍት እንደ እስትንፋሰ መለኮት የሚቀበሏቸው ወገኖች ዲዩትሮካኖኒካል (ሁለተኛ ቀኖና) በማለት መጥራትን ይመርጣሉ፡፡ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን መጻሕፍት እንደማይጠቅሙ ወይንም ደግሞ በውስጣቸው ምንም እውነት እንዳልያዙ አይቆጥሯቸውም፡፡ ይልቁኑ በነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጠቃሚ እውነቶች እንዳሉና ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ጎን ለጎን ለተጨማሪ እውቀት መነበብ እንሚገባቸው ያምናሉ ነገር ግን በሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ደረጃ ላይ አያስቀምጧቸውም፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ ከነዚህ መካከል አራቱ የሚከተሉት ናቸው፡-
- የአፖክሪፋ መጻሕፍት ነቢያት በነበሩበት ዘመን ሳይሆን በዝምታ ዘመን የተጻፉ ናቸው፡፡ በነቢዩ ሚልኪያስ እና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል የነበረው የ400 ዓመታት ጊዜ “የዝምታ ዘመን” በመባል ይታወቃል፡፡ በነዝያ ዘመናት የተከናወኑ ልናውቃቸው የሚገቡ ታሪኮች ቢኖሩም ነገር ግን እግዚአብሔር የሚናገራቸው ነቢያት ስላልነበሩ በወቅቱ የተጻፉት ጽሑፎች ሁሉ የሰው ስራዎች እንጂ እስትንፋሰ መለኮት ሊሆኑ አይችሉም፡፡
- እነዚህ መጻሕፍት ወደ ክርስቲያን ቀኖና የተጨመሩት በቀደሙት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዘመን ሳይሆን በመካከለኛው ዘመን ነበር፡፡ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች እነዚህን መጻሕፍት የጠቀሷቸው ቢሆንም መንፈሳዊ እሴት እንዳሏቸው ጠቃሚ መጻሕፍት እንጂ እንደ ስልጣናዊ ቃለ እግዚአብሔር አልነበረም፡፡ በ382 ዓ.ም. በሮም የተደረገውን የመሳሰሉ የአፖክሪፋ መጻሕፍት ቀኖናዊ መሆናቸውን የሚናገሩ ጉባኤዎች አካባቢያዊና የተወሰኑ ሰዎች ድምዳሜ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን የሚወክሉ አይደሉም፡፡ እንዲያውም ኦሪጎን፣ የኢየሩሳሌሙ ቄርሎስ፣ አትናቴዎስ እና ጀሮምን የመሳሰሉ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች አፖክሪፋን ተቃውመዋል፡፡[38] መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ላቲን ቋንቋ የተረጎሙት ቅዱስ ጀሮም እነዚህን መጻሕፍት አፖክሪፋ (የተሰወሩ ወይንም አጠራጣሪ) የሚል ስያሜ በመስጠት ከስድሳ ስድስቱ መጻሕፍት በመለየት ተርጉመዋቸዋል፡፡ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እነዚህን መጻሕፍት በቀኖናነት ያጸደቀችው የተሓድሶ (Reformation) እንቅስቃሴ አንዳንድ አስተምህሮዎችዋን መገዳደር በጀመረበት ዘመን (በ1546 ዓ.ም.) “የትረንት ጉባኤ” በመባል በሚታወቅ የቤተክርስቲያኒቱ ጉባኤ ላይ ሲሆን ለነዚህ አስተምህሮዎች ድጋፍ ሊሰጡ የሚችሉ ሐሳቦች በአፖክሪፋ ውስጥ እንደሚገኙ ስላመነች ቤተ ክርስቲያኒቱን ለሁለት የከፈለውን እንቅስቃሴ ለመቋቋም እንዲጠቅሟት በማለም ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያን ዘመንም ቢሆን ካርዲናል ካጄታንን የመሳሰሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት የሪፎርሜሽን እንቅስቃሴን ይቃወሙ የነበሩ ቢሆኑም ነገር ግን የአፖክሪፋ መጻሕፍትን ወደ ቀኖና መጨመር ተቃውመው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ብትሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እነዚህን መጻሕፍት በሰላሳ ዘጠኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እና በአዲስ ኪዳን መካከል የተለየ ቦታ በመስጠት ዲዩትሮካኖኒካል (ሁለተኛ የቀኖና መጻሕፍት) የሚል ስያሜ በመስጠት እንዲታተሙ ታደርግ ነበር፡፡ ነገር ግን በ2000 ዓ.ም. በታተመው የሰማንያ አሐዱ እትም ላይ እነዚህን የአፖክሪፋ መጻሕፍት ከሌሎች የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጋር በመቀላቀል እንዲታተሙ ተደርጓል፡፡
- ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እና የግሪክ ኦርቶዶክስን የመሳሰሉት አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን መጽሐፍት እንደ ቃለ እግዚአብሔር የማይቀበሉበት ሌላው ምክንያት ደግሞ እነዚህ መጻሕፍት በአይሁድ ቀኖና ውስጥ የማይገኙ መሆናቸው ነው፡፡ በ90 ዓ.ም. ዮሐናን ቤን ዛካይ በተባለ ረቢ መሪነት በጃምኒያ በተደረገ የአይሁድ ሊቃውንት ጉባኤ ላይ በአይሁድ ታሪክ ውስጥ በቀኖናነት ተቀባይነት እንደነበራቸው ተረጋግጠው እስትንፋሰ መለኮት መሆናቸው ዕውቅና የተሰጣቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሰላሳ ዘጠኙ ብቻ ነበሩ፡፡ የጉባኤው አላማ ቀኖናን ማጽደቅ ሳይሆን የትኞቹ መጻሕፍት በቀኖናነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ እንደነበሩ ለይቶ ዕውቅና መስጠት እንደ ነበር ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የአይሁድ መምህር የነበረው የእስክንድርያው ፋይሎ (20 ዓ.ዓ. – 40 ዓ.ም.) ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚቻልበት ሁኔታ ከሁሉም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የጠቀሰ ሲሆን ከአፖክሪፋ ግን አንድም ጊዜ አልጠቀሰም፡፡ የአይሁድ ጸሐፌ ታሪክ የነበረው ጆሲፈስ ፍላቪየስ (ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን) (30 ዓ.ም. – 100 ዓ.ም.) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት 22 ብቻ መሆናቸውን በመጥቀስ የአፖክሪፋን መጻሕፍ ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡ አይሁድ አንዳንድ መጻሕፍትን እንደ አንድ መጽሐፍ ስለሚቆጥሯቸው እንጂ እነዚህ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ቆጠራ መሠረት 39 ከሆኑት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተለዩ አይደሉም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሮሜ 3፡1-2 ላይ እንደጻፈው እግዚአብሔር ብሉይ ኪዳንን በአደራ የሰጠው ለአይሁድ ሕዝብ ነው፡-
“እንግዲህ የአይሁዳዊ ብልጫው ምንድር ነው? ወይስ የመገረዝ ጥቅሙ ምንድር ነው? በሁሉ ነገር ብዙ ነው፡፡ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጡአቸው፡፡”
ስለዚህ አይሁድ የትኞቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከእግዚአብሔር እንደሆኑና እንዳልሆኑ ለይተው ያውቃሉ፡፡ የአይሁድ ሕዝብ ቅዱሳት መጻሕፍትን በታላቅ ፍርሃት እና በታላቅ አክብሮት በጥንቃቄ ይዘው እንደቆዩ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ የጥንቃቄያቸውን ብዛት ለመረዳት እና ለማድነቅ እስኪ የሚከተሉትን እውነታዎች ከግምት ውስጥ አግቡ፡
- የጽሑፍ ሥራው ከመጀመሩ በፊት በእድሜ የሁሉ ታላቅ የሆነ ረቢ ተነስቶ በመቆም አንድ ፊደል እንኳ መቀነስ ወይንም ደግሞ መጨመር ለጥፋት እንደሚዳርጋቸው ጸሐፍቱን ያስጠነቅቃል፡፡
- ጸሐፍቱ ሥራቸውን እየሰሩ ሳሉ ንጉሥ እንኳ ቢገባ ስህተት ላለመስራት የጀመሩትን ገፅ እስኪጨርሱ ድረስ ቀና ብለው ማናገር እንደ ሌለባቸው ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል፡፡
- ብሉይ ኪዳን የሚጻፍበት ብራና ከንፁህ እንስሳት ቆዳ በአይሁዳዊ እጅ ብቻ መዘጋጀት አለበት፡፡
- እያንዳንዱ ወርድ ከ 48 በታች እና ከ 60 በላይ መስመሮች ሊኖሩት አይገባም፡፡
- ቀለሙ ጥቁር ብቻ መሆን አለበት፣ በተለየ ሁኔታም ይዘጋጃል፡፡
- ከትውስታ የሚጻፍ ምንም ዓይነት ቃል ወይንም ፊደል መኖር የለበትም፡፡ ጸሐፊው ተኣማኒ የሆነ ኮፒ ከፊት ለፊቱ ማስቀመጥ አለበት፣ ከመጻፉ በፊትም ከፍ ባለ ድምፅ በትክክል ሊያነበው ይገባል፡፡
- ጸሐፊው ከመጻፉ በፊት አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ መጻፍያውን መወልወል አለበት፡፡
- ጸሐፊው ያሕዌ የሚለውን የእግዚአብሔርን ስም ከመጻፉ በፊት መላ ሰውነቱን መታጠብ አለበት፡፡
- ጸሐፊው ያሕዌ የሚለውን የእግዚአብሔርን ስም ለመጻፍ አዲስ ብዕር ይጠቀማል፡፡ ያሕዌ የሚለውን ስም የጻፈበትን ብዕር ሌላ ቃል ለመጻፍ አይጠቀምበትም፡፡
- በአንድ ገፅ ላይ የሚፈጠር አንድ ስህተት ገፁን በሙሉ ያበላሸዋል፡፡ በአንድ ገፅ ላይ ሦስት ስህተቶች ከተገኙ ብራናው በሙሉ ከጥቅም ውጪ ይሆናል፡፡
- እያንዳንዱ ቃል እና እያንዳንዱ ፊደል ተቆጥሮ ተመዝግቧል፡፡[39]
ስለዚህ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የብሉይ ኪዳንን ቀኖና በተመለከተ እግዚአብሔር ታማኝ አድርጎ ቆጥሮ ቃሉን በአደራ ከሰጣቸውና እንዲህ ባለ ጥንቃቄና አክብሮት የእግዚአብሔርን ቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያስተላልፉ ከኖሩት ሕዝቦች ጋር ይስማማሉ፡፡
- ጌታችን ኢየሱስ ዕውቅናን የሰጠው ለአይሁድ ቀኖና ብቻ ነበር፡፡ በጌታ ዘመን ብሉይ ኪዳን ሕግ፣ ነቢያት እና መዝሙራት በመባል ለሦስት ተከፍሎ ነበር (ሉቃስ 24፡44)፡፡ በነዚህ ሦስቱ ክፍሎች ውስጥ የአፖክሪፋ መጻሕፍት አልነበሩም፡፡ በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ “ከአቤል ደም እስከ ዘካርያስ ደም” በማለት ብሉይ ኪዳን ከአቤል ጀምሮ እስከ ዘካርያስ ዘመን ድረስ የሚገኘውን የታሪክ ዘመን እንደሚሸፍን አመላክቷል (ማቴ 23፡35፣ ሉቃ 11፡51)፡፡ ይህም ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ መጨረሻዎቹ ነቢያት ድረስ የሚገኘው ዘመን ነው፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ እና ነቢዩ ሚልኪያስ በአንድ ዘመን የኖሩ ሲሆኑ ከእነርሱ በኋላ እስከ ክርስቶስ ዘመን ድረስ የነበረው ዘመን የዝምታ ዘመን በመባል ይታወቃል፡፡ በይሁዳ መልዕክት ቁጥር 14-15 ላይ ከአፖክሪፋ መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነው መጽሐፈ ሄኖክ መጠቀሱ መጽሐፉ ትምህርት ሰጪ የሆነን መልዕክት በውስጡ የያዘ መሆኑን የሚያመለክት እንጂ መጽሐፉ ሙሉ በሙሉ እውነት መሆኑን የሚያመለክት አይደለም፡፡ የጌታ ሐዋርያት ለተደራሲያኖቻቸው ትምህርት ሊሰጡ የሚችሉ የግሪክ ጽሑፎችንና ሌሎች የአይሁድ መጻሕፍትን እንኳ ሲጠቅሱ እንመለከታለን፡፡ ይህ ጽሑፎቹን እስትንፋሰ መለኮት አያደርጋቸውም፡፡
አሕመዲን ጥያቄዎቻቸውን ይቀጥላሉ፡-
20. ኦርጂናል መጽሐፍ ቅዱስ እንደሌለ ያውቃሉን? ይህንንማ ለነገሩ ክርስቲያኖችም አያስተባብሉም፡፡ ቢኖርማ ለምን ከበርካታ መጽሐፍት መካከል ለመለየት የድምፅ ብልጫ ይደረግ ነበር? ክፍፍል፣ ጭቅጭቅ፣ ልዩነት ይከሰት ነበርን?
ኦሪጅናል ቁርኣን እንደሌለ ያውቃሉን? የመጀመርያዎቹ የቁርኣን ጽሑፎችስ ተሰብስበው መቃጠላቸውን ያውቃሉን? ይህንንማ ለነገሩ ሙስሊሞችም አያስተባብሉም፡፡ ታድያ የኦሪጅናል ቁርኣን አለመኖር ቁርኣንን እንዲጠራጠሩ ካላደረጎት መጽሐፍ ቅዱስን ስለምን ይጠራጠራሉ? ክርስቲያኖች የመጀመርያዎቹን ጽሑፎች እንደ ሙስሊሞች ሰብስበው አላቃጠሉም፡፡ ከማተሚያ ማሽን ዘመን በፊት የተጻፉትን ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የአዲስ ኪዳን ገፆችን ጨምሮ ከኦሪጅናሎቹ ላይ የተገለበጡ ኮፒዎች ዛሬ በእጃችን ይገኛሉ፡፡ ሙስሊሞች ግን የመጀመርያዎቹ ቁርአኖች ሆነ ተብለው እንዲወድሙ ስለተደረጉ አሁን ያለው ቁርኣን ከኦሪጅናሉ ጋር እንደሚመሳሰል ለማመን የሚያስችላቸው መሠረት የላቸውም፡፡ ቁርኣንን በአንድ ጥራዝ መሰብሰብ፣ የትኞቹ ሱራዎች መካተት እንዳለባቸው እና ኦሪጅናሎቹን ማቃጠልን በተመለከተ በቀደሙት ሙስሊሞች መካከል ብዙ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ፣ አለመቀባበልና ልዩነት ተከስቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበረው ገዢ ኸሊፋ ኡስማን የራሱን ፍላጎት በኃይል አስፈፅሟል፡፡ (ወደ በኋላ ላይ በሰፊው እንመለከታለን፡፡)
21. ከበርካታ መጽሐፍቶች መካከል ዛሬ የሚገኘውን ሲመርጡ የአምላክን ቃል በምን ሚዛን ለዩት? እውነትና ሐሰት የሚለውን አምላካዊ አስተምህሮት የሚረጋገጠው ያ የሚመረጠው መጽሐፍ ሆኖ ሳለ ለምን ወደ ድምፅ ብልጫ ተገባ?
ኡስታዝ አሕመዲን ቅጥፈት ይብቃዎት! ድምፅ ብልጫ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለጸው የቀኖና ውሳኔ ረጅም ዘመናትን የፈጀ ሂደት እንጂ በአንድ ጀምበር የድምፅ ብልጫ የተወሰነ አልነበረም፡፡ የመጀመርያዋ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በሐዋርያት ትምህርትና በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ላይ ነበር፡፡ የሐዋርያት ትውፊትና የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስለነበሯት ሚዛን አልባ አልነበረችም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመቀበል ጥቅም ላይ ውለው የነበሩት መመዘኛዎች ሐዋርያዊ ሥልጣን፣ ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ያላቸው ተግባቦት እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበራቸው ታሪካዊ ተቀባይነት የሚሉትን የመሳሰሉት መንፈሳዊና ምክንያታዊ መስፈርቶች ስለነበሩ ተመሳስለው የተጻፉ ሌሎች የፈጠራ ጽሑፎች ሾልከው ሊገቡ አልቻሉም፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ሀሰተኛ ነቢያት እንደነበሩት ሁሉ በአዲስ ኪዳን ዘመንም ስላሉ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጓ ትክክል ነበር (2ጴጥሮስ 2፡1)፡፡
22. ክርስቲያኖች ስለእምነታቸው አቋም ይዘው ነው መጽሐፍቶችን የመረጡት ወይስ መጽሐፍቶችን ከመረመሩ በኋላ ነው አቋም የያዙት?
ይህ ጥያቄ አሁንም የቤተ ክርስቲያንን አመሰራረት ካለማወቅ የመነጨ ነው፡፡ መጀመርያ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በሐዋርያት ትምህርት እና በብሉይ ኪዳናት መጻሕፍት ላይ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን እየሰፋች ስትመጣ ሐዋርያት ትምህርቶቻቸውን በጽሑፍ ማስፈር ስለነበረባቸው ያንን አደረጉ፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በክርስቲያኖች ዘንድ ይታወቁ ስለነበር በአጠቃላይ መግባባት ተቀባይነት አግኝተው የአስተምህሮ ምንጭ በመሆን ያገለግሉ ነበር፡፡ ኋላ ላይ የኑፋቄ አስተማሪዎች የራሳቸውን ቀኖና ማዘጋጀት ሲጀምሩ ቤተ ክርስቲያን አቋሟን ግልፅ ለማድረግ ኦፊሴላዊ የሆኑ ጉባኤዎችን በመጥራት ቀኖናዋን አረጋገጠች፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ሳይፋቱ አብረው የመጡ ቢሆኑም በሃይማኖት መግለጫ መልክ እንዲቀመጡ የተደረጉት ኑፋቄያዊ አስተምህሮዎች በፈጠሯቸው ተግዳሮቶች ምክንያት ነበር፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን አቋም ይዛ ቅዱሳት መጻሕፍትን አልመረጠችም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን መርምራ እምነቷን ያስታወቀችበት ሁኔታ ቢኖርም ነገር ግን እምነቷና ቅዱሳት መጻሕፍት የተፋቱበት ጊዜ አልነበረም፡፡
23. “አጭሩ” ና “ረጅሙ” የሚባሉ የማርቆስ ወንጌሎች እንዳሉ ያውቃሉን? አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች የማርቆስ ወንጌልን በ16፡8 ሲያቆሙ ረጅሙ ደግሞ በ16፡20 ይጠቃለላል ፡፡ ይህ ለምን ሆነ? እንዴት ተለያዩ?
የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ማርቆስ 16፡9-20 ድረስ የሚገኘውን ክፍል ተዓማኒነት በተመለከተ ወጥ አቋም የላቸውም፡፡ ገሚሶቹ በአብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ስለተካተተ ተዓማኒ እንደሆነ ሲናገሩ የተቀሩት ደግሞ ይህንን ክፍል ላለመቀበል ተከታዮቹን ምክንያቶች ያቀርባሉ፡-
- እነዚህ ቁጥሮች ቀዳሚና ይበልጥ ተዓማኒ በሆኑት የግሪክ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አይገኙም፡፡ በተጨማሪም በቀደመው ላቲን፣ ሢርያክ፣ አርመንያ እና ኢትዮጵያ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አይገኙም፡፡
- ቀለሜንጦስ፣ ኦሪጎን እና ኢዮስቢዮስን የመሳሰሉት ብዙ የጥንት አባቶች እነዚህን ቁጥሮች አያውቋቸውም፡፡ ጀሮም ከሞላ ጎደል በእርሱ ዘመን በነበሩት በሁሉም የግሪክ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አለመገኘቱን አስታውቋል፡፡
- ይህንን ክፍል የሚያጠቃልሉት ብዙ የእጅ ጽሑፎች አጠራጣሪ መሆኑን ለማሳየት ምልክት ያደርጉበታል፡፡
- በአንዳንድ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ሌላ አጠር ያለ የማርቆስ ወንጌል መዝጊያ ይገኛል፡፡
- አንዳንዶች ደግሞ አጻጻፉና የሰዋሰው ይዘቱ ከተቀረው የማርቆስ ወንጌል ጋር እንደማይመሳሰል ይናገራሉ፡፡
ይህ ክፍል በኦሪጅናል የማርቆስ ወንጌል ውስጥ መገኘት አለመገኘቱ አጠያያቂ እንደሆነ ቢቀጥልም ነገር ግን የያዘው እውነት ከተቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢወጣ ምንም የሚጎድል ትምህርት የለም፡፡ ያዘለው ትምህርት በሌሎች ክፍሎች እንደመገኘቱ መጠን ደግሞ ባለበት ቦታ ቢቆይ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ የሚጨምረው ነገር የለም፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት በልሳን የመናገር ስጦታ፣ የጥምቀት ሥርዓት እና በእባብ መርዝ ያለመጎዳት ተዓምር በሌሎች ክፍሎች ላይ ተጠቅሰዋል (የሐዋርያት ሥራ 2፡1-21፣ 10፡44-48፣ 19፡1-7፣ 28፡3-5)፡፡[40]
24. የዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ “ዮሐንስ የተባለው የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነው” ተብሎ ይገመታል፡፡ የዮሐንስ ወንጌል 21፡24 ላይ “…ስለዚህ ነገሮች ሁሉ የመሰከረና እነዚህን ነገሮች የጻፈው ይህ ደቀመዝሙር ነው፡፡ የእርሱም ምስክርነት እውነት እንደሆነ እናውቃለን” ይላል፡፡ ይህ የማን ንግግር ነው? “እናውቃለን” የሚለውን እያለ ያለው ማነው? ዮሐንስ ስለ ራሱ ነው እንዲህ የሚለው ወይስ ሌላ ዮሐንስ ደቀመዝሙር ነው ይህን እየፃፈያለው?
ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ሊጽፍ ቢችልም ነገር ግን ይህ ክፍል በዮሐንስ ደቀ መዛሙርት የተጻፈ ሊሆን እንደሚችል ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ማርቆስና ሉቃስ የሐዋርያት ደቀ መዛሙርት ሆነው ሳሉ ሙሉ መጻሕፍትን የመጻፍ ሥልጣን ካገኙ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ምስክርነቱ እውነት መሆኑን እንደሚያውቁ ቢገልፁና የጸሐፊውን ማንነት የሚያስረግጥ ምስክርነት ቢሰጡ በጎ ነገር ነው፡፡ መጽሐፉ በዚህ መልኩ እንዲጠናቀቅ የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ነበር፡፡
25. ዘዳግም 31፡24-29 “ሙሴ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የዚህን ቃል በመጽሐፍ ጽፎ እንዳበቃ የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት የሚሸከሙ ሌዋውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፣… የቱን ያህል አመፀኞችና አንገተ ደንዳኖች እንደሆናችሁ አውቃለሁና፡፡ እኔ በህይወት ከእናንተ ጋር እያለሁ እንደዚህ ካመፃችሁ፣ ከሞትሁ በኋላማ የቱን ያህል ልታምፁ! …እኔ ከሞትሁ በኋላ ፈፅማችሁ እንደምትረክሱ፣ ካዘዝኋችሁም መንገድ ዘወር እንደምትሉ አውቃለሁና” ይላል፡፡ ታዲያ ሙሴ ይህን ተናግሮ ሳለ እንዴት መጻሕፍቶቹን አይሁድ ጠብቀው አቆዩ ይባላል?
ይህንንስ ቃል ቢሆን ጠብቆ ያቆው ማነው? አይሁዶች አይደሉምን? መጽሐፉን ለውጠውት ቢሆን ኖሮ እንዲህ የሚገስጻቸውንና ክፉዎች መሆናቸውን የሚገልፀውን ክፍል ስለምን ሳይለውጡት ቀሩ? ክፍሉ እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ቃል አለመታዘዛቸውን እንጂ ቃሉን ስለመለወጣቸው የሚናገር አይደለም፡፡ የቃሉ ጠባቂ ራሱ እግዚአብሔር ነው! እስራኤላውያን ለቃሉ ባይታዘዙም ነገር ግን እንዲለውጡት እግዚአብሔር አልፈቀደም፡፡ ደግሞም በየዘመናቱ እግዚአብሔርን የሚፈሩና የሚያገለግሉት ታማኞች ከሕዝቡ መካከል ጠፍተው አያውቁም፡፡ እስከ ባቢሎን ምርኮ ዘመን ድረስ ነቢያት የነበሩ ሲሆን ከባቢሎን ምርኮ መልስ አይሁድ ጠንካራ የሃይማኖት ማሕበረሰቦች ከመሆናቸው የተነሳ ለቅዱሳት መጻሕፍት ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር፡፡ አይሁድ በብዙ ክፉ ነገሮች ሊከሰሱ ይችላሉ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል በመለወጥ ሊከሰሱ አይችሉም!
በማስከተል አሕመዲን የአፖክሪፋ መጻሕፍት ሴቶችን በተመለከተ ከሚናገሯቸው ነገሮች በመነሳት ጥያቄዎችን ይሰነዝራሉ፡፡ እኛ የአፖክሪፋ መጻሕፍት ቃለ እግዚአብሔር እንደሆኑ ስለማናምን መልስ ለመስጠት ጊዜ ማጥፋት አያስፈልገንም፡፡ ነገር ግን የገዛ ሃይማኖታቸው ሴቶችን በተመለከተ ምን እንደሚል በማሳየትና እውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ምን እንደሚል በማስነበብ ርዕሱን እናልፈዋለን፡፡ ጽሑፉን ለማንበብ እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ፡፡
ማጣቀሻዎች
[1] አዲሱ መደበኛ ትርጉም 1ጢሞቴዎስ 5፡18 የግርጌ ማጥኛ ገፅ 1844 ይመልከቱ፡፡
[2] Norman Geisler. Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 5-6
[3] Horatio B. Hackett. A Commentary on the Original Text of the Acts of the Apostles; Sheldon, Blakeman & co., 1858, p. 12 (pdf)
[4] Robert H. Gundry. A Survey of the New Testament, 3rd Edition, The Paternoster Press, Carlise UK, 1994, p. 89
[5] Raymond E. Brown. An Introduction to the New Testament; Anchor Bible, 1st Edition, 1997, P. 267
[6] Sir William Ramsay. Saint Paul: the Traveller and the Roman Citizen, New York, G. P. Putnam’s Sons, 1896. [Dr. Ramsey stated: “Luke is a historian of the first rank; not merely are his statements of fact trustworthy … this author should be placed along with the very greatest of historians.”]
Ramsey further said: “Luke is unsurpassed in respects of its trustworthiness.” (Josh McDowell. The Best of Josh Mcdowell: A Ready Defense, pp. 108-109)
[7] ሜሪል ሲ.ቲኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስታን የኮሚዩኒኬሽንና ስነ ጹሑፍ መምሪያ፣ ገጽ 282
[8] ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 282-283
[9] ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 83
[10] የዮሐንስ ወንጌል የጸሐፊውን ማንነት ስለሚናገር ይህ አባባል ስህተት መሆኑ ይሰመርበት፡፡
[11] John Barton & John M.: The Oxford Bible Commentary, Oxford University Press, 2001, p. 1084 (በጣም ለዘብተኛ በሆኑ ሊቃውንት የተጻፈ ነው፡፡)
[12] Craig L. Blomberg: Jesus and the Gospels, Broadman & Holman Publishers, Nashville, Tennesse, 1997, p. 74
Norman Geislere: Encyclopedia of Christian Apologetics, pp. 389
[13] ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ ገፅ 239
[14] ዝኒ ከማሁ
[15] Robert H. Gundry: Survey of the New Testament, pp. 127-128
[16] Craig L. Blomberg: Jesus and the Gospels, pp. 123-124
[17] FF Bruce, The New Testament Documents, Are They Reliable?, 1959, p. 11 of (pdf)
[18] Ibd
[19] FF Bruce. The New Testament Documents, Are They Reliable?, 1959, pp. 7-9 (pdf)
[20] Josh McDowell. Evidence That Demands a Verdict; New and Revised, 1999, p. 34
[21] Norman Geisler. Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 532
[22] FF Bruce. The New Testament Documents, Are They Reliable?, 1959, p. 11 (pdf)
[23] Norman L. Geisler፡ Ensyclopedia of Christian Apologetics, pp. 188
[24] የመካከለኛው ዘመን ፈጠራ ከሆነው የበርናባስ ወንጌል ጋር መምታታት የለበትም
[25] Bruce Metzger: The New Testament Its background and Content, Abingdon Press, 1982, p. 275
[26] መርቂያን/ ማርሲዮን የብሉይ ኪዳን አምላክና የአዲስ ኪዳን አምላክ እንደሚለያዩ ያምን የነበረ ሲሆን ከተወሰኑት የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክቶችና የተወሰነ ክፍሉ ተቆርጦ ከወጣ የሉቃስ ወንጌል ውጪ ሌሎቹን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አይቀበልም ነበር፡፡
[27] Ibid. 276
[28] Ibid.
[29] በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት “ድብቁ እውነት ሲገለጥ” በሚል ርዕስ በሳሂህ ኢማን የተጻፈውን መጽሐፍ ታነቡ ዘንድ እንጠቁማችኋለን፡፡
[30] “Most other ancient books are not so well authenticated. New Testament scholar Bruce Metzger estimated that the Mahabharata of Hinduism is copied with only about 90 percent accuracy and Homer’s Illiad with about 95 percent. By comparison, he estimated the New Testament is about 99.5 percent accurate.” (Norman L. Geisler. Baker Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 532)
[31] http://www.rim.net/muslim/texts.htm
[32] Rashad Khalifa, Ph.D., Quran The Final Testament Revised Edition
[33] http://www.theatlantic.com/issues/99jan/koran.htm
http://answeringislam.net/Quran/Text/atlantic_mr.html
[34] Alfred Guillaume. The Life of Muhammad: a Translation of Ibn Ishaq’s Sirat Rasul Allah, p. 653
[35] Sahih Al-Bukhari, Vol. 9, Book 93, Number 589
[36] የአማርኛ ቁርኣን መቅድም ገፅ 1
[37] በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት Norman Geisler, Baker Encyclopeadea of Christian Apologetics pp. 80 – 85 ያንብቡ፡፡
[38] Ibid., p. 33-34
[39] Paul Roost. Proofs that the Bible is the word of almighty God, Book 147, pp. 30, Evangelical Bible College of Western Australia
[40] Norman L. Geisler & Thomas Howe. When Critics Ask: A Popular Hand Book on Bible Difficulties, Victor Books, p. 321-322 (pdf)