የኢየሱስ ማንነት ጉዳይ (ክፍል 3)

ምዕራፍ አንድ

የኢየሱስ ማንነት ጉዳይ (ክፍል 3)

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡

41. ኢየሱስ ምድር ሳለ ምንም ማድረግ እንደማይችል በርካታ ስፍራ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ወደ ምድር ሲመጣ አምላክነቱ ትቶ ሰው ሆኖ መጣ ማለት ነውን? ሰው ከሆነ ታዲያ የተሰቀለው ኢየሱስ የተባለው ሰው እንጂ አምላክ እንዳልሆነ አያሳይም?

ኢየሱስ ምንም ማድረግ እንዳማይችል ሳይሆን ከአብ ተለይቶ ምንም ማድረግ እንደማይችል ነው የተናገረው፡፡ አረፍተ ነገሩ ይስተካከል፡፡ ይህንን ደግሞ ለምን እንዳለ በጥያቄ ቁጥር 38 ላይ አብራርተናል፡፡

42. ኢየሱስ በተደጋጋሚ ለአምላኩ ሲጸልይ ነበር፡፡ ይህም በማቴዎስ 26:39፣ ማቴዎስ 26:42፣ ማቴዎስ 26:44፤ ማርቆስ 1:35 ማርቆስ 14:35፣ ማርቆስ 14:39፣ ሊቃስ 5:16፣ ዮሐንስ 17:1-3፣ ዕብራባዊያን 5:7 እና ሉቃስ 6:12 ላይ ተገልጿል፡፡ ኢየሱስና አምላክ እኩል ቢሆኑ ኖሮ ለምን ኢየሱስ ለአምላኩ ጸለየ? አምላክ የሚጸልይለት ሌላ አምላክ አለውን? ይጸልያልን? ኢየሱስ አምላክ ከሆነ ለማን ነው ልመናን ያቀረበው? አምላክ ከሆነ ለራሱ ነው ልመናን ያቀረበው ማለት ነው?

አሁንም ጠያቂያችን እስላማዊ መነፅራቸውን ማውለቅ ተስኗቸዋል፡፡ ኢየሱስ የጸለየው ወደ ራሱ ሳይሆን ወደ አብ ነው፡፡ የጸለየበት ምክንያት ደግሞ ፍፁም ሰው ሆኖ ወደ ምድር በመምጣቱ ነው፡፡ ፍፁም ሰው በመሆኑ አብ አምላኩ ተብሏል (2ቆሮንቶስ 1፡3፣ 11፡31፣ ኤፌሶን 1፡3፣ 1ጴጥሮስ 1፡3-5)፡፡ ፍፁም አምላክ በመሆኑ ደግሞ ለአብ የምንሰጠው ክብር ሁሉ ይገባዋል (ዮሐንስ 5፡22-23)፡፡ ኢየሱስ እንደ አምላክነቱ እንኳ ወደ አብ ቢጸልይ የጸሎት ክርስቲያናዊ ትርጓሜ ግልፅ እስከሆነ ድረስ ከአምላካዊ ባህርይ ጋር የሚጣረስበት ሁኔታ የለም፡፡ ጸሎት (ሰላት) በእስልምና አንድ ሰው ለአላህ መገዛቱንና ባርያ መሆኑን የሚገልፅበት ሥርኣት ሲሆን በክርስትና ግን የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ከእርሱ ጋር የምንነጋገርበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ወልድ አንድያ የአብ ልጅ በመሆኑ ከአባቱ ጋር ቢነጋገር መለኮትነቱን አይቀንስም፡፡

43. በመጽሐፍ ቅዱስ አብ ኃያል፣ አዳኝ፣ ላኪ፣ ፈጣሪ፣ ልዑል መሆኑ ሲገለፅ ኢየሱስ ደግሞ ከራሱ ምንም ማድረግ የማይችል ኃይል የለሽ ሟች እና መልዕክተኛ መሆኑን እናነባለን ፡፡ እንደሚባለው ክርስቶስ በአምላክ የሚላክ፣ ሟች፣ ምንንም ማድረግ የማይችል ከሆነና ሁሉም ነገር በአብ የተሠጠው ከሆነ እንዴት ዘለዓለማዊ አምላክ ይሆናል?

በዚህ ጥያቄ ውስጥ የተዘረዘሩት ነጥቦች ሁሉ ቀደም ሲል መልስ የተሰጠባቸው በመሆኑ ራሳችንን መድገም ጉንጭ ማልፋት ይሆንብናል፡፡ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህ የተዘረዘሩት የአብ ባሕርያት ሁሉ እንዳሉት ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎችን በመስጠት ይህንን ጥያቄ እናልፈዋለን፡-

  • ሃያል ስለመሆኑ፡- “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳይያስ 9፡6)፡፡
  • አዳኝ ስለመሆኑ፡- “…እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” (ማቴዎስ 1፡21)፡፡
  • ላኪ ስለመሆኑ፡- “የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ” (ማቴዎስ 13፡41)፡፡ “እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል፡፡ እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ” (ዮሐንስ 16፡7)፡፡
  • ፈጣሪ ስለመሆኑ፡- “ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” (ዮሐንስ 1፡3)፡፡ “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፡፡” (ቆላስይስ 1፡15)፡፡
  • ልዑል ስለመሆኑ፡- “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤ ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል” (ቆላስይስ 2፡9-10)፡፡ “እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ” (ራዕይ 17፡14)፡፡ “እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ” (1ጴጥሮስ 3፡22)፡፡ እነዚህ ሁሉ የሉዓላዊነት ባሕሪያት የፈጣሪ ብቻ ስለመሆናቸው የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቦ መረዳት ይቻላል (1ዜና 29፡11፣ መዝሙር 83፡18 95፡3-7፣ 97፡5-9፣ 113፡5፣ ዘፍጥረት 14፡19-22)፡፡

44. ይህ ጥያቄ ማቴዎስ 28፡18 ላይ የሚገኘውን ቃል በመጥቀስ ስለ ኢየሱስ ሥልጣን መቀበል የሚጠይቅ ነው፡፡ መልሱ በጥያቄ ቁጥር 12 ላይ ስለተሰጠ አልፈነዋል፡፡

45. ኢየሱስ በአምላክ አንደተላከ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ለአብነት በማቴዎስ 10:40፣ ማርቆስ 9:37 ፣ ሉቃስ 9:48፣ ሉቃስ 10:16፣ ዮሐንስ ወንጌል 4:34፣ ዮሃንሰ 5:24፣ 5:30 5:36፣ 6:57 7:16-18፣ 7:28-29፣ 7:33፣ 8:14-16፣ 8:18፣ 8:26፣ 8:28-29፣ 8:42፣ 9:4-5፣ 1:41:42፣ 12:44፣ 12:49፣ 13:20፣ 14: 24፣ 15:21፣ 16:5፣ 17:6-9፣ 17:18፣ 18:23 18:25፣ 20:21 እና 13:3 ላይ ተገልጿል፡፡ ክርስቲያኖች “ኢየሱስን አምላክ ነው” እንደሚሉት ቢሆን ኖሮ አምላክን ማን ይልከዋል? አምላክ ሌላ የሚልከው አምላክ አለውን?

በአሕመዲን መረዳት መሠረት አምላክ በአካልም በመለኮትም ነጠላ በመሆኑ ኢየሱስ እንደተላከ መነገሩ አምላክ አለመሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ የሥላሴን ፅንሰ ሐሳብ ፍፁም የዘነጋና ከነጠላ አሃዳዊነት ንፅረተ ዓለም አስተሳሰብ አኳያ የቀረበ ጥያቄ በመሆኑ ክርስቲያኖችን የሚመለከት አይደለም፡፡ እኛ የነጠላ አሃዳዊነት አስተምህሮን ስለማንከተልና በአሃዱ ሥሉስ የምናምን ስለሆንን ኢየሱስ በአብ የተላከ መሆኑ ከምንከተለው አስተምህሮ ጋር የሚጣጣም እንጂ የሚጣረስ አይደለም፡፡ የተከበሩት ጠያቂያችን በገዛ ራሳቸው አጥር ውስጥ ተቀምጠው ለክርስቲያናዊ አስተምህሮ ባይተዋር ከሆነ አዕምሯቸው የመነጩ ጥያቄዎችን ከመጠየቃቸው በፊት ክርስትናን ቢያጠኑ ኖሮ የራሳቸውንም ሆነ የአንባቢዎቻቸውን ጊዜ ባላባከኑ ነበር፡፡

46. በሐዋሪያት ሥራ 7:55 ላይ «እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና “እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ» አለ ይላል፡፡ እንዲሁም በማርቆስ ወንጌል 16:19 ላይ «ጌታ ኢየሱስ ይህን ከተናገራቸው በኋላ ወደሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ፡፡» ይላል፡፡ አምላክ እግዛብሔር ነው ወይስ ከእግዚአብሔር ቀኝ የቆመው ኢየሱስ ነው? ወይንስ ሁለቱም? ታድያ ምኑ ላይ ነው “እግዚአብሔር አንድ ነው” የሚባለው? “አምላክ (እግዚአብሔር)” ስንል ኢየሱስን ይጨምራል ወይስ አይጨምርም? እግዚአቤሔር በዙፋን ላይ ያለው ነው ወይስ ከቀኙ የቆመው ኢየሱስ? አንድሁም በክርስትና “መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው”፡፡ ታድያ እስጢፋኖስ የተሞላው በአምላክ ነውን ? እስጢፋኖስ ኢየሱስ ካረገ በኋላ ከእግዚአብሔር ጎን ሲቆም “የሰው ልጅ” ሲል ጠራው ታድያ ካረገም በኋላ ሰው መሆኑን ሊነግረን ፈልጎ አይደል?

አሁንም ይህ ጥያቄ በተደጋጋሚ ከገለፅነው የአሕመዲንን ዕይታ ከጋረደው አስተምህሮ የመነጨ ነው፡፡ እግዚአብሔር አሃዱ ሥሉስ በመሆኑ በዚህ ቦታ ላይ የሥላሴ አካላት፣ ማለትም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በሦስት አካላት መገለፃቸው ታሪካዊው የክርስትና ነገረ መለኮት (Historical Christian Theology) መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እስጢፋኖስ ኢየሱስን “የሰው ልጅ” ብሎ መጥራቱ ኢየሱስ የትንሣኤውን ሥጋ ይዞ ማረጉን የሚገልፅ በመሆኑ አሁንም ጥቅሱ ክርስቲያናዊውን አስተምህሮ የሚደግፍ እንጂ የሚቃወም አይደለም፡፡ ነገር ግን “የሰው ልጅ” የሚለው ማዕርግ ከሰውነቱ ባለፈ ኢየሱስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ መሆኑን ያሳያል (ዳንኤል 7፡13-14)፡፡ ለዚህ ነው በዚህ ቦታ ላይ እስጢፋኖስ የወጋሪዎቹን ኃጢአት ይቅር እንዲል ነፍሱንም እንዲቀበል ወደ ኢየሱስ የጸለየው (የሐዋርያት ሥራ 7፡59-60)፡፡

የኢየሱስን አምላክነት ያልተቀበለ ሰው እንዲህ ዓይነት ጸሎት ሊያቀርብ አይችልም፡፡ የትኛውም ሙስሊም “ጌታ ሙሐመድ ሆይ ነፍሴን ተቀበል” ወይም “ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” በማለት ወደ ሙሐመድ አይጸልይም፡፡ ምክንያቱም ይህ ሙሐመድን አምላክ ማድረግ ነውና፡፡ የኢየሱስን አምላክነት በመመስከር የመጨረሻ እስትንፋሱን የተነፈሰውን የእስጢፋኖስን ንግግር በማጣመም የኢየሱስን አምላክነት እንደካደ በማስመሰል መናገር ህሊና ቢስነት ነው፡፡

ጠያቂያችን ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር አንድነት የሚያምኑ መሆናቸውን ነገር ግን አንዱ አምላክ ሦስት የማይነጣጠሉና የማይደባለቁ አካላት እንዳሉት፣ ወልድ በሥጋ እንደተነሳና እንዳረገ ማመናቸውን ቢያውቁ ኖሮ ይህንን ጥያቄ ባላቀረቡ ነበር፡፡ አለማወቅ ኃጢአት አይደለም፡፡ ነገር ግን የማያውቁትን ለማወቅ ማንበብና መማር እንጂ በቁንፅል እውቀት የሞነጫጨሩትን በመጽሐፍ በማሳተም የሌላውን ሃይማኖት ማብጠልጠል አግባብ አይደለም፡፡

47. ኢየሱስ በሰይጣን ተፈትኗል መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ አምላክ በሰይጣን እደማይፈተን ይናገራል፡፡ «ማንም ሲፈተን “እግዚአብሔር ፈተነኝ” አይበል ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፡፡ እርሱም ማንንም አይፈትንም፡፡» (ያዕቆብ 7:13) በተቃራኒው «ከዚህ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን በዲያብሎስ ይፈትን ዘንድ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፡፡» (ማቴዎስ 4:1)፡፡ አምላክ የማይፈተን መሆኑ ተነግሮ ሳለ ኢየሱስ አምላክ ቢሆን ኖሮ እንዴት በሰይጣን ይፈተን ነበር? ታድያ ኢየሱስ በሰይጣን እየተፈተነ አምላክ ነው ይባላልን? አንድም ቦታ ላይ የኢየሱስ “ሰዋዊ ባህሪ ተፈተነ” አይልም፡፡ ታድያ ኢየሱስ አምላክ አለመሆኑን አያሳይምን?

ያዕቆብ ላይ የተጻፈው ቃል እግዚአብሔር ኃጢአትን ወይም ክፋትን እንዲያደርግ የሚገፋፋው ባሕርይ በውስጡ እንደሌለ የተነገረ በመሆኑ ከእርሱ ውጪ የሚገኝ አካል ሊፈትነው እንደማይሞክር ለማሳየት እንደ ማስረጃ ሊጠቀስ የሚችል አይደለም፡፡ ይህ ሐሳብ ቁጥር 14ን ጨምረን ስናነብ ግልፅ ይሆናል፡- “ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም፡፡[1] ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል” (ያዕቆብ 1፡13-14)፡፡

ስለዚህ ያዕቆብ እየተናገረ ያለው ከውስጥ በክፉ ምኞት ምክንያት ስለሚፈጠር ፈተና ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍፁምና ቅዱስ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ አይፈተንም፡፡ ነገር ግን ሰዎች እግዚአብሔርንና መንፈሱን እንደተፈታተኑ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ተጽፏል (መዝሙር 106፡4፣ ዘጸአት 17፡1-2፣ ዘኁልቁ 14፡22፣ ዕብራውያን 3፡8-9፣ የሐዋርያት ሥራ 5፡9)፡፡

እንደ አብ እና እንደ መንፈስ ቅዱስ ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መለኮት በመሆኑ ክፋትን እንዲያደርግ የሚገፋፋው ባሕርይ በውስጡ የለም፡፡ ስለዚህ በክፉ አይፈተንም፡፡ ነገር ግን እስራኤላውያን በምድረ በዳ እግዚአብሔርን እንደ ተፈታተኑት ሁሉ ሰይጣን በምድረ በዳ ተፈታትኖታል፡፡ እርሱ ግን ፈተናውን በማሸነፍ ሰይጣንን አሳፍሮታል፡፡ ወልድ ፍፁም ሰው በመሆን ወደ ምድር እንደመጣም መዘንጋት የለብንም፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ጥቅሶች ችላ ብለን አምላክ በምንም መንገድ ሊፈተን እንደማይችል ብንቀበል እንኳ ኢየሱስ በሰዋዊ ባሕርዩ በሰይጣን ሊፈተን ይችላል፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ የኢየሱስ በሰይጣን መፈተን ከያዕቆብ 7፡13 ጋር የሚጣረስበት መንገድ የለም፡፡

ጠያቂያችን እንደተለመደው ቁርጥራጭ ጥቅሶችን መዘው ከማውጣት ይልቅ ሙሉውን የያዕቆብን መጽሐፍ በማስተዋል ሆነው ቢያነቡት ኖሮ ያዕቆብ ስለ ኢየሱስ አምላክነት የጻፈውን ማየት ባልተሳናቸው ነበር፡-

የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን” (ያዕቆብ 1፡1)፡፡

ያዕቆብ የእግዚአብሔር አብ እና የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የኢየሱስን ፈጣሪነት ባይቀበልና ፍጡር እንደሆነ ቢያምን ኖሮ ፈጣሪና ፍጡርን አንድ ላይ በማጣመር የሁለቱም ባርያ መሆኑን ባልተናገረ ነበር፡፡ ይህ የማይገባው ሙስሊም ካለ “የአላህ እና የሙሐመድ ባርያ ነኝ” በማለት መናገር ይችል እንደሆን እንጠይቀዋለን፡፡ “ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ” (ያዕቆብ 2፡1)፡፡

እስኪ ይህንን አባባል ለያሕዌ ከተነገረው ከዚህ ቃል ጋር ያነፃፅሩት፡- “እናንት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘለዓለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ፡፡ ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱና ኃያል፥ እግዚአብሔር ነው፥ በሰልፍ ኃያል” (መዝሙር 24፡7-8)፡፡

48. የዘብዴዎስ ልጆች እናት ሁለቱ ልጆቿን በመንግስት ሰማያት በቀኝና በግራው ያስቀምጥላት ዘንድ ኢየሱስን ጠይቃ እንዲህ ሲል መልሶላታል «ኢየሱስም “በእርግጥ እኔ የምጠጣውን የመከራ ፅዋ ትጠጣላችሁ”ነገርግን በቀኝና በግራዬ እድትቀመጡ የማደርገው እኔ አይደለሁም ይህ ቦታ የሚሰጠው አባቴ ላዘጋጀላቸው ነው፡፡ (ማቴዎስ 20፡23) ታድያ ኢየሱስ ክርስቲያኖች እንደሚሉት አምላክ ከሆነ እንዴት መንግስት ሰማያት የማስገባው “እኔ አይደለሁም” ሲል ይመልሳል? ክርስቲያኖች እንደሚሉት ከሆነ ለበርካታ ጊዚያት የተለያዩ ነገሮችን ማድረግ የተሳነው “ሥጋ ለብሶ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ስለመጣ” ነው፡፡ “ነገር ግን በዚህኛው ጥቅስ እየሱስ “እኔ አይደለሁም” ሲል እንደማይችል የተናገረው ስጋ በለበሰበት ጊዜ ሳይሆን በመጭው ዓለም በመንግስተ ሰማያት ነው፡፡ ታድያ አምላክ ከሆነ እርሱስ ለምን እንደ አብ ገነት ማስገባት ይሳነዋል?

መንግሥተ ሰማያት በማስገባት ረገድ የመጨረሻውን ብያኔ የሚሰጠው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ቀደም ሲል በማስረጃዎች አስደግፈን ገልጠናል፡፡ ነገር ግን ይህ ጥቅስ መንግሥተ ሰማያት ስለማስገባት የሚናገር አይደለም፡፡ ለኢየሱስ የቀረበለት ጥያቄ የሥልጣን ጥያቄ እንጂ መንግሥተ ሰማያት የመግባት ጥያቄ ባለመሆኑ አሕመዲን ያልተባለውን ሐሳብ በራሳቸው ፈጥረው ማስገባታቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ አስተያየት የመስጠት አቅምም ሆነ ዝግጅት እንደሌላቸው ያመለክታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በእስራኤል ላይ ነግሦ ይገዛል የሚል እምነት ስለነበራቸው (የሐዋርያት ሥራ 1፡6-8) ንጉሥ እንደመሆኑ በቀኝና በግራ የሚቀመጡ ሰዎች ይኖራሉ፤ ስለዚህ ያንን ቦታ ለመያዝ መሽቀዳደማቸው ነው፡፡ ጌታችን ወደ ምድር ተመልሶ ለአንድ ሺህ ዓመት እንደሚነግሥ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ራዕይ 20)፡፡ በዚህ ወቅት በግራና በቀኝ የሚቀመጡትን የመወሰኑ የሥራ ድርሻ የአብ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ የሥላሴ አካላትን የግብር ክፍፍል (Function) የሚያሳይ እንጂ የመለኮታዊ ባሕሪ መበላለጥን የሚያሳይ አይደለም፡፡

49. ከጥያቄ 42 ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ታልፏል፡፡

50. ሉቃስ 22:43-44 ላይ «መልአክም ከሰማይ ተገልጦለት አበረታው፡፡ አጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፡፡ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስ ነበር፡፡» ይላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቲያኖች እንደሚሉት ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ከሆነ ላለመሞት ፈርቶ ይሄን ያህል ሲጨነቅ የአምላክ ፍጡርየሆነውን መልአክ ከሰማይ ተገልጦለት ከሚያበረታታው የራሱ አምላካዊ ባህሪው አለለት አይደለምን? ለምን እራሱን አያበረታውም ነበር? “አምላክ” እጅግ ሲጨነቅ መልአክ ያበረታታዋል ማለት ነውን? ምንስ አስጨነቀው? ክርስቲያኖች እንደሚነግሩን ሞትን የፈጠረው ራሡ አይደለምን?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም ሰው እንደመሆኑ ከፊቱ የነበረው የመስቀል መከራ አስፈርቶታል፡፡ የመስቀሉን የሥቃይ ስሜት በሙሉ በሥጋው ያስተናግዳል፡፡ ከዚህም በላይ የመላውን ዓለም ኃጠአት በመሸከም ነው የሚሰቃየው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ስሜት አልባ ሮቦት ሳይሆን ፍፁም ሰው በመሆን ሰዎች ሊሰማቸው በሚችለው የሥቃይ ስሜት ሁሉ ውስጥ በማለፍ ነው ሊሞት ያለው፡፡ በሥጋ የተገለጠ አምላክ እንደመሆኑ የስቃይ ስሜቱንም ሆነ ፍርሃቱን ማስወገድ ይችል ነበር ነገር ግን ያንን ሊያደርግ አልወደደም፡፡ በመስቀል ላይ በነበረ ጊዜ በሮማውያን ልማድ መሠረት የሥቃይ ስሜቱን ሊቀንስ የሚችል መጠጥ ሲሰጠው ሊጠጣው አለመፈለጉ የተዘገበው ያለምክንያት አይደለም (ማርቆስ 15፡23)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ኃይሉን ሳይጠቀም ፍርሀቱን፣ ጭንቀቱንም ሆነ ሥቃዩን ሊቀበል በመወሰኑ ምክንያት ሰብዓዊ ባሕርዩ እስከ መስቀል ይሄድ ዘንድ የሚያበረታታው መልአክ ከአብ ዘንድ ተልኮለታል፡፡ መለኮታዊ ሥልጣኑን ለመጠቀም አለመፈለጉ መለኮት አለመሆኑን አያሳይም፡፡ አሕመዲን ኢየሱስ ሞትን እንደፈጠረ ክርስቲያኖች ማመናቸውን ከየት እንደሰሙ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በቁርኣን መሠረት አላህ ሞትንና ሕይወትን እንደፈጠረ ስለተነገረ መጽሐፍ ቅዱስም ተመሳሳይ ትምህርት ያለው መስሏቸው ይሆናል (ሱራ 67፡2)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሞት የሰዎች ያለመታዘዝ ውጤት እንጂ የእግዚአብሔር ፍጡር ስለመሆኑ የተጻፈ ነገር የለም፡፡ ጨለማ የብሃን አለመኖር እንደሆነ ሁሉ ሞትም የሕይወት አለመኖር ነው፡፡ እግዚአብሔር ብርሃንን እንጂ ጨለማን እንዳልፈጠረ ሁሉ ሕይወትን እንጂ ሞትን አልፈጠረም፡፡ የሕይወት እስትንፋስ የሆነችው ነፍሳችን ከሥጋችን ስትለይ ሥጋችን ይሞታል፡፡ ነፍሳችን ደግሞ የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ስትለይ ትሞታለች፡፡ እግዚአብሔር ሞትን ፈጥሯል የምንል ከሆነ የሞት ምክንያት የሆነውንም ኃጢአትን ፈጥሯል ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ቅዱስ ከሆነው የእግዚአብሔር ባሕርይ ጋር ይጣረሳል፡፡ ጠያቂያችን የራሳቸውን የተወላገደ አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ባይጭኑ መልካም ነው፡፡

51. የማርቆስ ወንጌል 16:19 «ጌታ ኢየሱስ ይህን ከተናገራቸው በኋላ ወደሰማይ ዐረገበእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ» ይላል፡፡ ክርስቲያኖች “በአንዱ አምላክ እናምናለን” ይላሉ፡፡ አንዱ አምላክ ብለው ሲለምኑ እግዚአብሔርን ነው ወይንስ ከእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠውን ኢየሱስን ነው? ወይስ ሁለቱንም? ታድያ ስንት ፈጣሪ ነው ያለው?

ወልድ በአብ ቀኝ መቀመጡ እና ልዩ አካላት መሆናቸው መገለፁ የአሃዱ ሥሉስን አስተምህሮ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ለበለጠ ማብራርያ ለጥያቄ ቁጥር 23 የተሰጠውን ምላሽ ይመልከቱ፡፡

52. ከጥያቄ ቁጥር 16 ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ታልፏል፡፡

53. ከቁጥር 21 ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ታልፏል፡፡

54. ዕብራውያን 1:4 «ስለዚህ የወረሰው ስም ከመላዕክት ስም እንደሚበልጥ ሁሉ እርሱም ከመላዕክት እጅግ የላቀ ሆኗል፡፡» ይላል፡፡ “ኢየሰስ ከመላዕክት እጅግ የላቀ ሆኗል“ ሲል “የላቀ ነው” ከሚለው ጋር እጅጉን ይለያያል ፡፡ “ሆኗል” ሲል መጀመሪያ አልሆነም በኋላ ላይ ሆነ የሚል ትርጉም ያሲዘናል፡፡ ታድያ አምላክ ነው የሚባለው ኢየሱስ ከመላእክት ያንስ ነበርን?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር በመምጣቱ ምክንያት በሰውነቱ ከመላእክት በጥቂት አንሶ እንደነበር በዕብራውያን መልዕክት ውስጥ ተጽፏል፡፡ አሕመዲን የዕብራውያንን መልዕክት እየቆራረጡ ከሚያነቡ አንድ ምዕራፍ ጨምረው ቢያነቡ ኖሮ ይህንን ጥቅስ ባገኙ ነበር፡-

“ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ፥ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን” (ዕብራውያን 2፡7-9)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት ተፈጥሮ ያነሰውን የሰውን ተፈጥሮ ስለወሰደ ለጥቂት ጊዜ ከመላእክት አንሶ ቢታይም አሁን ግን እንደ እግዚአብሔር ወልድ ወደነበረው የቀድሞ ክብሩ ስለተመለሰ ከመላእክት እጅግ ልቆ ይገኛል፡፡ ለተጨማሪ ማብራርያ መልስ ቁጥር 21 እና ቁጥር 30ን ይመልከቱ፡፡

55. መጽሐፍ ቅዱስ በ2ኛጴጥሮስ 1:2 ላይ «እግዚአብሔርና ጌታችን ኢየሱስን በማወቅ ፀጋና ሰላም ይብዛላችሁ» ይላል፡፡ ክርስቲያኖች “በአንዱ በእግዚአብሔር እናምናለን” ሲሉ ይህ አባባል ኢየሱስን ይጨምራልን? ታዲያ ለምን በዚህኛው ጥቅስ እግዚአብሔርንና ኢየሱስን ሁለት የተለያዩ አድርጎ አቀረበ?

አዲስ ኪዳን “እግዚአብሔር” ሲል አውዱ ካላመለከተ በስተቀር በመደበኛነት አብን እንደሚያመለክት በተደጋጋሚ ገልፀናል፡፡ ሌሎች የሥላሴ አካላትን ወይም አንዱን ግፃዌ መለኮት ለማመልከት ከተፈለገ አውዱ ያንን ግልፅ ያደርጋል (ዮሐንስ 1፡1፣ የሐዋርያት ሥራ 5፡3-4)፡፡ ስለዚህ በዚህ ሥፍራ የተጠቀሱት አብ እና ወልድ ናቸው፡፡ አሕመዲን ከጠቀሱት ጥቅስ በላይ የሚገኘው ቁጥር ሐሰተኛነታቸውን ስለሚያጋልጥ እንደልማዳቸው ቆርጠው አስቀርተውታል፡፡ እኚህ ሰው ምን ያህል ለቃለ እግዚአብሔር ክብር የጎደላቸውና ሕሊናቸውን የጨቆኑ እንደሆኑ ሁሉም ሰው ማየት ይችል ዘንድ እንጠቅሰዋለን፡- የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ የሆነ ስምዖን ጴጥሮስ፥ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ፤ የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ” (2ጴጥሮስ 1፡1)፡፡

56. የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ራዕይን” እንዲህ በማለት ይተረጉማል ፦ “ራዕይ”፦ ሰው ሳያንቀላፋ በተመስጦ የሚያየውና የእግዚአብሔር ቃል የሚገለጥበት፡፡ ራዕይ ከህልም ይለያል፡፡ ራዕይ እግዚአብሔርን ለሚያውቁ የእግዚአብሔር መንፈስ ላደረባቸው ይሠጣል” ይላል፡፡ የዮሐንስ ራዕይ 1:1 ላይ «ቶሎ መሆኑን የሚገባውን ነገር ለአገልጋዮቹ እንዲያሳይ እግዚአብሔር ለእርሱ የሰጠዉ የኢየሱስ ክርስቶስ ራዕይ ይህ ነው፡፡» ይላል፡፡ ክርስቲያኖች እንደሚያምኑት ኢየሱስ አምላክ ከሆነ ሁሉንም ያውቃል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር ለሱ የሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ራዕይ ይላል፡፡ ታዳያ አምላክ ቢሆን ሁሉን አዋቂ መሆን አልነበረበትምን? ራዕይ ሊሠጠው ይገባ ነበርን? እርሱስ ቢሆን የሦስቱ ሥላሴዎች አባል አይደለምን?

አሕመዲን የጠቀሱትን መዝገበ ቃላት ልብ ብለው ቢያነቡት ኖሮ ራዕይን እንዲያዩ የሚሰጠው በምደር ላይ ለሚገኙት ሰብዓውያን እንጂ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ለሚኖሩት አለመሆኑን በተገነዘቡ ነበር፡፡ ይህ ቃል ኢየሱስ ራዕይ ማየቱን ሳይሆን ራዕዩን ለባርያው ለዮሐንስ እንዲያሳይ አብ እንደሰጠው የሚናገር ነው፡፡ አንዱ የሥላሴ አካል ከሌላው መቀበሉ ከአንዱ ግፃዌ መለኮት ውጪ ከሚገኝ ሌላ አካል እስካልተቀበለ ድረስ አምላክነቱን ሊያጠራጥር አይችልም፡፡ ጠያቂያችን እንደልማዳቸው ቆራርጠው ባያነቡ ኖሮ በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ የኢየሱስን አምላክነት የሚያረጋግጡ ብዙ ሐሳቦችን ባገኙ ነበር፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሚከተሉትን ነጥቦች እናስተውላለን፡-

  • ኢየሱስ መልአኩን እንደላከ ተነግሯል (ቁ.1)፡፡ መላእክት የፈጣሪ እንጂ የፍጡራን ናቸውን? ከፈጣሪ በስተቀርስ ሊያዛቸውና ሊልካቸው የሚችል አካል አለን?
  • ከደመና ጋር እንደሚመጣ እና የወጉትም እንደሚያዩት ተነግሯል (ቁ.7)፡፡ ይህ ዳንኤል በራዕይ ያየው የምድር ሕዝቦች ሁሉ የሚገዙለት፣[2] የማያልፍ ዘለዓለማዊ ግዛት ያለው የሰው ልጅ መሆኑን ያሳያል (ዳንኤል 7፡13-14)፡፡ የወጉት እንደሚያዩት መነገሩ ደግሞ ያሕዌ እግዚአብሔር “ወደወጉኝ ወደ እኔ ይመለከታሉ” በማለት የተናገረውን የሚገልፅ በመሆኑ ኢየሱስ ያሕዌ መሆኑን ያሳያል፡፡[3]
  • ቁጥር 7 ላይ ኢየሱስ እንደሚመጣ ከተናገረ በኋላ ቁጥር 8 ላይ፡- ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፦ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላልበማለት ኢየሱስ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክ መሆኑን ያስረዳል፡፡
  • ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እርሱ መሆኑን ተናግሯል (ቁ.17)፡፡ ይህንን ሊናገር የሚችለው ብቸኛው አካል ያሕዌ እግዚአብሔር ነው፡- “የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም” (ኢሳይያስ 44፡6)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአንዱ ግፃዌ መለኮት አካል ባይሆን ኖሮ ይህንን ባልተናገረ ነበር፡፡

አሕመዲን የኢየሱስን አምላክነት ለማስተባበል የጠቀሱት ጥቅስ ከአውድ የተገነጠለና በተሳሳተ መንገድ የተተረጎመ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ የሆነውና ስለ በደላችን ነፍሱን አሳልፎ የሰጠው ገናናው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክ መሆኑን እንድናረጋግጥ ዕድል ስለፈጠሩልን ጠያቂያችንን ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡

57. በማቴዎስ 19:28 ላይ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው «በእውነት እላችኃለሁ የሰው ልጅ በክብር ዙፋን ላይ በሚቀመጥበት በአዲሱ ዘመን የእኔ ተከታዮች የሆናችሁ እናንተም በአስራ ሁለት ዙፋን ላይ ትቀመጣላችሁ በአስራ ሁለቱም የእስራኤል ነገዶች ላይ ተሾማችሁ ትፈርዳላችሁ፡፡» ይላል፡፡ ከነዚህ አስራ ሁለት ሐዋሪያቶች መካከል አንዱ ይሁዳ ኢየሱስን ክዶታል ፡፡ ነገርግን ኢየሱስ አጠገቡ የነበሩትን 12ቱን ሐዋሪያት “እናንተ ትፈርዳላችሁ” ሲል ይሁዳን ጨምሮ ነው የገለፀው፡፡ ታዲያ ይሁዳም ይፈርዳልን? ሌላ ሰው በካህዲው ምትክ ይተካል እንዳንል “እናንተም” ”ትፈርዳላችሁ” ”የሆናችሁ“ ”አላቸው” እና ”ትቀመጣላችሁ” የሚሉት ቃላት በወቅቱ እዚያ ለነበሩት ለ12ቱ ብቻ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ታድያ ኢየሱስ ይህን አያውቅምን? ደግሞ ኢየሱስ ስለሚፈርድ ”አምላክ” ከተባለ አስራ ሁለቱም ሐዋርያትም አምላክ ሆኑ ማለት አይደለምን? አያውቅምን? ደግሞ ኢየሱስ ስለሚፈርድ “አምላክ” ከተባለ አስረሰ ሁለቱም ሀዋርያትም አምላክ ሆኑ ማለት አይደለምን?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቦታ ላይ ሁሉን ትተው ለተከተሉት ደቀ መዛሙርቱ የተስፋን ቃል እየሰጣቸው ነው፡፡ ነገር ግን ይሁዳ ይህንን ዕድል በመተው ለሌላ ሰው ታልፎ እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ አስቀድሞ የተተነበየ ነው (የሐዋርያት ሥራ 1፡15-26)፡፡ ኢየሱስም ይህንን እንደሚያውቅ በተደጋጋሚ ተገልጿል (ማቴዎስ 26፡21፣ ማርቆስ 14፡18፣ ሉቃስ 22፡21፣ ዮሐንስ 6፡64፣ 6፡70-71፣ 13፡11፣ 13፡21)፡፡ ስለዚህ ይሁዳ ጌታችን ይህንን ተስፋ ሲሰጥ ቢሰማም ስላልፀና ዕድሉ ለሌላ ሰው ተላልፏል፡፡ ጌታችን የመፍረድን ሥልጣን ከአብ የተቀበለው በሥጋ የተገለጠ መለኮት ስለሆነ ነው (ዮሐንስ 5፡27)፡፡ አብ የፍርዱን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ለኢየሱስ አሳልፎ የሰጠው ሰዎች እርሱን በሚያከብሩበት በዚያው ሁኔታ ልጁንም ያከብሩ ዘንድ ነው (ዮሐንስ 5፡22-23)፡፡ አምላክ ሊከበር በሚገባው በዚያው ሁኔታ ሊከበር የሚገባው አምላክ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ መፍረድ መለኮታዊ መብቱ ነው፡፡ ለዚህ ነው ለሌሎች የመፍረድን ሥልጣን ለመስጠት የቻለው፡፡ ለሐዋርያት የተሰጠው ሥልጣን ውሱን በመሆኑ ምክንያት አምላካዊ መብት እንዳላቸው ሊቆጠር አይችልም፡፡ እነርሱም ቢሆኑ በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት የሚቆሙ ሰብዓውያን ናቸው (ሮሜ 14፡10)፡፡ ክርስቶስ ከአብ የተቀበለው የመፍረድ ሥልጣን ግን ያልተገደበና ፍፁም ነው (ዮሐንስ 5፡27)፡፡ እንዲህ ያለ ሥልጣን ለፍጡር ሊሰጥ አይችልም፡፡

58. ፊልጵስዩስ 2፡9 ስለ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገልጿል፡፡ “ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፡፡ ስሙ ሳይሰጠውና ከፍ ከመደረጉ በፊትስ ምን ነበር? ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ “አምላክ” ከሆነ አምላክ ከፍ ያደርጋል ወይንስ ከፍ ይደረጋል? ከስም ሁሉ በላይ የሆነው ስምስ ምንድነው? “የአምላክ ልጅ” መባል? ይህ ከስም ሁሉ በላይ የሆነው ስም ሳይሰጠው በፊት ኢየሱስ ምን ነበር? ይህ ስሙን ከማግኘቱ በፊት ጊዜ እንደነበረ አያሳይምን?

ጌታችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአታችን ሊዋጀን የባርያን መልክ ይዞ ወደ ምድር በመምጣቱ ምክንያት ራሱን እንዳዋረደና ተልዕኮውን ከፈፀመ በኋላ አብ ከፍ ከፍ እንዳደረገው ነው ይህ ጥቅስ የሚናገረው፡፡ ነገር ግን ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በምን ሁኔታ እንደነበር አሕመዲን እንደልማዳቸው ቆርጠው የጣሉት የጥቅሱ ቀዳማይ ክፍል ይገልፃል፡- “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ በእናንተ ዘንድ ይሁን፡፡ እርሱ በባሕርዩ አምላከ ሆኖ ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቆጠረውም፡፡ ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ በሰውም አምሳል ተገኝቶ ራሱን ባዶ አደረገ፡፡ ሰው ሆኖ ተገልጦ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡ እስከ ሞት ያውም በመስቀል ላይ እስከመሞት ታዛዥ ሆነ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፡፡ ይኸውም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው፡፡” (ፊልጵስዩስ 2፡5-11 አ.መ.ት.)፡፡

አሕመዲን የኢየሱስን አምላክነትና ከአብ ጋር እኩል መሆን ያለምንም ብዥታ እንዲህ ባለ ሁኔታ ጥርት አድርጎ ከሚናገር ክፍል ውስጥ አንዷን አረፍተ ነገር በግብር አባታቸው መቀስ ቆርጠው በማውጣት የኢየሱስን አምላክነት ለማስተባበል ይሞክራሉ፡፡ በእውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ቅጥፈት በእጅጉ አስደንጋጭና ሕሊና ካለው ሰው የማይጠበቅ ነው፡፡ ይህ ተግባራቸው ሰውየው የዋኀንን ለማወናበድ ምን ያህል የቆረጡና ለጥፋት ራሳቸውን የሸጡ እንደሆኑ ያሳያል፡፡

59. ዕብራውያን 5:5-6 «እንዲሁም ክርስቶስ ሊቀ ካህናት የመሆንን ክብር ለራሱ አልወሰደም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር “አንተ ልጅ ነህ! እኔ አባት ሆንኩህ” አለው» በሌላ ስፍራ ደግሞ እንደ መልክ ጼዴቅ ሹመት ለዘለዓለም ካህን ነህ ይላል፡፡ ይህ ጥቅስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት የመሆንን ክብር ለራሱ አልወሰደም» ይላል፡፡ የእርሱ ስልጣን ዘለዓለማዊ ከሆነና ከነበረ እንዴት ከጊዜ በኋላ የመወሰድና ያልመውሰዱ ጥያቄ ይነሳል? በራሱ ባይወስድም ከመውሰዱ በፊት ምን ነበር?

የክርስቶስን ልጅነት ለተመለከተው ጥያቄ በቁጥር 30 ላይ በቂ መልስ ስለተሰጠ አንደግምም፡፡ ክህነቱን በተመለከተ ግን የምንለው ይኖረናል፡፡ ጌታችን ወደ ምድር በመምጣት ሥጋን እስከለበሰበት ጊዜ ድረስ ሊቀ ካህን አልነበረም፡፡ ክህነት እንደ ነቢይነት ሁሉ ለሰው የሚሰጥ አገልግሎት በመሆኑ ከትስብዕቱ በፊት ኢየሱስ ካህን ነበረ ብሎ ማለት አይቻልም፡፡ ከትስብዕቱ በኋላ ይህንን አገልግሎት መቀበሉ ዘለዓለማዊ አምላክ መሆኑን ለማስተባበል የሚቀርብ የሙግት ሐሳብ ሊሆን አይችልም፡፡

60. የሐዋርያት ስራ 5፡31 ላይ “እርሱም ለእስራኤል ንስሀንና የኃጢአትን ሰርየት ይሰጥ ዘንድ፣ እግዚአብሔር የሁሉ ራስና አዳኘ አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው፡፡” ይላል፡፡ እግዚአብሔር በቀኙ ከፍ ሳያደርገውስ በፊት ኢየሱስ ምን ነበር? የሃጢአት ስርየትስ ለማን ነው ይሰጥ ዘንድ የተላከው? ለእስራኤል! ታዲያ ምን ነካቸው?

ለጥያቄው የመጀመርያ ክፍል መልስ ቁጥር 58ን ይመልከቱ፡፡ አሕመዲን በቃለ አጋኖ በመጮኽ ኢየሱስ ለእስራኤል ብቻ ንስሐና የኃጢአትን ስርየት የሚያመጣ እንደሆነ ለማስመሰል ቢሞክሩም ጥቅሱ ግን ለእስራኤል ብቻ እንደማይል ልብ ይሏል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም አዳኝ መሆኑና የወንጌሉ መልዕክት ለዓለም ሁሉ የተሰጠ መሆኑ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ተጠቅሷል (ማቴዎስ 24፡14፣ 28፡19-20፣ ማርቆስ 16፡15፣ ዮሐንስ 1፡29፣ 3፡17፣ 4፡42፣ 6፡51፣ 8፡12፣ 11፡27፣ 17፡18፣ 1ጢሞቴዎስ 1፡15፣ 1ዮሐንስ 4፡14፣)፡፡

61. ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታንካ በ2006 እትሙ ላይ እንደገለፀው የክርስቲያኖች ክፍፍል (የክርስትና አይነት) 33,000 (ሠላሳ ሦስት ሺህ) ደርሷል፡፡ (Encyclopedia britannica 2006 /Ultimate Reference suited D V D/ electronic) “ሁሉም “በመንፈስ ቅዱስ ተነድተናል፣ ተሞልተናል፣ ሰርፆብናል” ወዘተ. ይላሉ፡፡ እውን መንፈስ ቅዱስ የሚያድናቸው ከሆነ እንዴት ክርስቲያኖች በመለያየት 33,000 ቦታ ከፋፈላቸው? የትኛውስ ነው ትክክለኛ ክርስትና?

አሕመዲን ጥያቄ ያለቀባቸው ይመስላል፡፡ ትክክለኛው ክርስትና የመጽሐፍ ቅዱስ ክርስትና ነው፡፡ አንድነት የሚገለጸው በቃሉ ውስጥ ራሱን የገለጠውን አንዱን አምላክ በማምለክ እንጂ በአንድ መዋቅራዊ አስዳደር ስር በመግባትም ሆነ በያንዳንዱ ጥቃቅን ትምህርት ላይ በመስማማት አይደለም፡፡ በክርስትና ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ቤተ እምነቶች መሠረታዊ በሆኑ ትምህርቶች ላይ የሚስማሙ ሲሆኑ ልዩነታቸው እጅግ በጣም የጠበበና በአስተዳደራዊ መዋቅር ብቻ የተከፋፈሉ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ መሠረታዊ ከሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር የማይስማሙት አርዮሳውያንና ሰባልዮሳውያንን የመሳሰሉት ቡድኖች ቃሉን የካዱ ቡድኖች ስለሆኑ ክርስቲያኖች ተብለው ሊጠሩ አይችሉም፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ታሪካዊውን ክርስትና የሚወክሉት የሥላሴ አማኞች የዳር ዳር በሆኑ ትምህርቶች እና በአስተዳደራዊ መዋቅር እንዲሁም በአምልኮ ሥርኣት የተለያዩ መሆናቸው የትክክለኛውን ክርስትና ድንበር የሚያስት አይደለም፡፡ ክፍፍሉም “በእኔ ስር ካልገባህ” በማለት በሰይፍ የሚያስገድድ አምባገነን አካል አለመኖሩንና ክርስትና የሰዎችን ነፃ አስተሳሰብ የሚያከብር እምነት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ አሕመዲን መንፈስ ቅዱስ ክርስቲያኖችን በአንድ የአስተዳደር መዋቅር ስር እንዲጠቀለሉና በያንዳንዱ ጉዳይ ላይ እንዲስማሙ እንደሚያደርጋቸው የተጻፈበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዲያሳዩን እንጠይቃቸዋለን፡፡ ስለ ክርስትና ያነሱትን ተመሳሳይ ጥያቄ ብንጠይቃቸው ኡስታዙ መልስ እንደሌላቸውና መግቢያ እንደሚጠፋቸው ግልፅ ነው፡፡ እስልምና በውስጡ ለቁጥር የሚያታክቱ ክፍፍሎች እንዳሉበትና እነዚህ አንጃዎች ደም እስከመቃባት ድረስ ጥላቻቸው የከረረ መሆኑ እንዲሁም በከሃዲነት መፈራረጃቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የገዛ ነቢያቸው ሙሐመድ እንኳ ሕዝባቸው 73 ቦታ እንደሚከፋፈልና ከእነዚህ ቡድኖች መካከል አንዱ ብቻ ገነት እንደሚገባ መተንበያቸውን ትውፊቶች ዘግበዋል፡፡[4] ክፍፍሉ ከዚያ እጅግ በዝቶ ትንቢቱ ሀሰት መሆኑ ቢረጋገጥም ነገር ግን እነዚህን ቡድኖች አንድ ላይ ጨፍልቆ የሌሎችን ህልውና በመካድ 73 ለማድረግ የሚታገሉ ሙስሊም ሊቃውንት አልታጡም፡፡ ሆኖም ግን ከሰባ ሦስቱ ቡድኖች መካከል ገነት የሚገባው የትኛው እንደሆነና እሳቸውም በትክክለኛው ቡድን ውስጥ ስለመገኘታቸው ያላቸውን እርግጠኛነት ቢጠየቁ መልሳቸው መንተባተብ እና መደነጋገር እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ ታድያ ለእስልምና የማይሰራውን መመዘኛ በክርስትና ላይ መጫን ለምን አስፈለገ? “የራሷ አሮባት…”

62. እንደ ክርስቲያኖች አስተምሮት: “የዮሐንስ ራዕይ” የተባለው መጽሐፍ ሲጽፍ ኢየሱስ ወደ ሰማይ አርጎ ነበር፡፡ ታዲያ ለምንድነው በዮሐንስ ራዕይ 1፡6 እና 3፡12 ላይ በሰማይ ያለው አብ አምላኩ እንደሆነ የተገለፀው?

ኢየሱስ የትንሳኤ አካሉን ይዞ ወደ ሰማይ በማረጉ ምክንያት በሰማይም ቢሆን ሰውም አምላክም ነው፡፡ ስለዚህ ሰብዓዊ ባሕርዩን ስላልተወ አብ አምላኩ መሆኑ መነገሩ የክርስቲያኖችን እምነት የሚያረጋግጥ እንጂ የሚቃወም አይደለም፡፡ ጠያቂያችን ይህንን ጥያቄ ማቅረባቸው መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት ዕውቀት የጎደላቸው መሆኑን ያሳያል፡፡

63. በመዝሙረ 89፡27 ዳዊት “የአምላክ ልጅ” ተብሏል፡፡ እንዲሁም ሰለሞን (1ኛ ዜና መዋዕል 22፡10)፣ እስራኤል (ዘፀአት 4:22፣ በመዝሙር 82፡6)፣ ኤፍሬም (ኤርምያስ 31:9)፣ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ (ሮሜ 8:14)፣ ሰላም አስፋኞች (በማቴዎስ 5፡9)፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ያመኑ (ገላትያ 3:13)፣አዳም (ሉቃስ 3:38) እና ኢየሱስን የተቀበሉት ሁሉ (ዮሐንስ 1፡10) “የአምላክ ልጅ” ተብለዋል፡፡ የኢየሱስ “የአምላክ ልጅ” መባል ከሌሎች የተለየና የሥጋ (እውነተኛ) ከሆነ ለምን ኢየሱስም ሆነ አምላክ ለይተው ይህን አልገለፁም? ያለ ማስረጃ በራሳችን ለምን እንለያለን፡፡

ጠያቂያችን “የኢየሱስ የአምላክ ልጅነት የተለየና የሥጋ (እውነተኛ) ከሆነ” ሲሉ በቁርኣን ውስጥ የሚገኘውን ስሁት መረዳት እያንፀባረቁ ነው፡፡ የቁርኣን ደራሲ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መባሉን እግዚአብሔር ሚስት አግብቶ ልጅ እንደወለደ የተነገረ በማስመሰል ይተረጉማል፡፡ አላህ ሚስት ስለሌለችው ልጅ ሊኖረው እንደማይችል በመናገርም የአላህን ሁሉን ቻይነት ውድቅ ያደርጋል (ሱራ 6፡101)፡፡ ጠያቂያችን መጽሐፍ ቅዱስን በጥቂቱም ቢሆን የማንበብ ዕድል በማግኘታቸው ምክንያ ክርስቲያኖች እንደርሱ እደማያምኑ ከቁርኣን ጸሐፊ በተሻለ ሁኔታ ማወቅ ነበረባቸው፡፡ “አባት” እና “ልጅ” የሚሉት ቃላት በሁለቱ የሥላሴ አካላት መካከል የሚገኘውን ዘለዓለማዊ ቁርኝት የሚገልፁ ቃላት እንጂ ቀጥተኛ ትርጉም ያላቸው አይደሉም፡፡ ግብፃውያን “የአባይ ልጆች” ተብለው መጠራታቸው ከወንዙ ጋር ያላቸውን ቁርኝት የሚገልፅ እንጂ አባይ ሚስት አግብቶ ልጅ ወለደ ተብሎ ሊተረጎም እንደማይችል ሁሉ ለሁለቱ የሥላሴ አካላት የተሰጡት እነዚህ መጠርያዎችም ቁርኝታቸውን የሚገልፁ እንጂ ቃል በቃል ሊተረጎሙ የሚገባቸው አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር አብም ሆነ ራሱ ኢየሱስ ልጅነቱ የተለየና በመካከላቸው ቀጥተኛ ቁርኝት መኖሩን የሚገልፅ መሆኑን ግልፅ አድርገዋል፡፡ አብ በኢየሱስ የአገልግሎት ዘመን ቢያንስ ሁለት ጊዜ የሚወደው በእርሱም ደስ የሚለው ልጁ መሆኑን መስክሯል (ማቴዎስ 3፡17፣ 17፡5፣ ማርቆስ 1፡10፣ 9፡17፣ ሉቃስ 3፡22፣ 9፡35)፡፡ እግዚአብሔር አብ በእንዲህ ያለ ሁኔታ የመሰከረለት አንድም ፍጥረት የለም፡፡ መላእክትና አማኞች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ቢሆኑም የኢየሱስ ልጅነት የተለየ መሆኑንና አብ ለማንም አባትነቱን ባልገለፀበት የተለየ መንገድ ለኢየሱስ መናገሩን መጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ አስፍሮልናል (ዕብራውያን 1፡5፣ ሉቃስ 20፡13)፡፡ ጌታችን ራሱን “አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ (ሞኖጌኔስ)” በማለት ነው የገለፀው (ዮሐንስ 1፡13)፡፡ ይህ ደግሞ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነበት መንገድ ማንም አለመሆኑንና የእርሱ ልጅነት የተለየ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከአብ ወጥቶ ወደ ዓለም መምጣቱንም በመናገር የአብ ባሕርይ ተካፋይ መሆኑን በግልፅ ተናግሯል (ዮሐንስ 8፡42፣ 16:28)፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ አይሁድ ኢየሱስን ለምን ሊገድሉት ይፈልጉ እንደነበር ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡- “እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ፦ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር” (ዮሐንስ 5፡18)፡፡

አሕመዲን ከሀኬተኛነታቸው የተነሳ ለማስረጃዎቹ ትኩረት ሳይሰጡ ክርስቲያኖችን ያለማስረጃ እንደሚናገሩ በማስመሰል መወንጀላቸው አስገራሚ ነው፡፡

64. በሐዋርያት ሥራ 3:26፣ 4:27 እና 4:30 ላይ የእንግሊዝኛዎቹን መጽሐፍ ቅዱሳት ብንመለከት ኢየሱስን “የአምላክ ባሪያ” በማለት ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን የአማርኛዎቹ ይህን ትርጉም እንዳይዙ ሆነው “ባሪያ፣ አገልጋይ” በሚለው ምትክ “ብላቴና፣ ልጅ” በሚለው ተተክቷል፡፡ በማስከተል ከእንግሊዘኛው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚከተሉት ሰባቱ ኢየሱስን “የአምላክ ባሪያ “ብለው መግለፃቸውንና “ባሪያ” በሚለው ቃል ላይ በማስመር እንመለከታለን፡- (ጠያቂው ‘Servant’ የሚለው ቃል የተጠቀሰባቸውን 7 የሚሆኑ የእንግሊዘኛ ትርጉሞችን ጠቅሰዋል፡፡)

ሀ) “ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው” (የሐዋርያት ሥራ 3፡26)፡፡

ለ) “ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ” (ጠያቂው ‘Servant’ የሚለው ቃል የተጠቀሰባቸውን 7 የሚሆኑ የእንግሊዘኛ ትርጉሞችን ጠቅሰዋል፡፡)

ሐ) “በእርግጥም ሄሮዶስና ጳንጥንዮስ ጲላጦስ ከአህዛብና ከእስራኤል ህዝብ ጋር በዚች ከተማ አንተ በቀባኸው በቅዱስ ብላቴናህ ላይ ክንድና ፈቃድ ጥንት የወሰኑት እንዲፈፅም ነው፡፡” (የሐዋርያት ሥራ 4:27) (ጠያቂው ‘Servant’ የሚለው ቃል የተጠቀሰባቸውን 7 የሚሆኑ የእንግሊዘኛ ትርጉሞችን ጠቅሰዋል፡፡)

ከላይ የጠቀስናቸው የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ጥቅሶች በሙሉ ስለ ኢየሱስ የአምላክ አገልጋይ እንጂ ስለ አምላክነቱ፣ አይደለም የሚገልፁት!!! ይህ እንግሊዝኛው ሲሆን የ 1980 ቀላል ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከበፊቱ በተለየ መልኩ ልክ እንደ እንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን አገልጋይ ይለዋል፡፡ “በእርግጥም ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአረማውያንና ከእስራኤል ህዝብ ጋር በዚህች ከተማ ተሰብስበው መሲህ ባደረግኸው በቅዱስ አገልጋይህ በኢየሱስ ላይ ተነሱ፡፡ (የሐዋርያት ሥራ 4፡27) እንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ “Your servant Jesus” “አገልጋይህ ኢየሱስ” ይላል፡፡ ለምን በአማርኛው ይህን አገልጋይህ የሚለውን በ“ብላቴናህ” ቀየረው??? ኢየሱስ የአምላክ ባሪያና አገልጋይ ከሆነ እንዴት አምላክ ሊሆን ይችላል?? የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎቹስ ምነው “የአምላክ አገልጋይ” የሚለውን፣ በ“ብላቴና” መለወጣቸው? ኢየሱስ አምላክ እንዲሆን ፈልገው ይሆን?

የአማርኛ ተርጓሚዎች “ብላቴና” በማለት መተርጎማቸው ስህተት አይደለም፡፡ “ፓሂስ”[5] የሚለው የግሪክ ቃል ትርጉም “ብላቴና” ማለት ሲሆን በአማራጭነት “ልጅ (Child)” ወይም “አገልጋይ (Servant)” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ ነገር ግን መብት አልባ ባርነትን በሚገልፅ መልኩ ሊተረጎም አይችልም፡፡[6] የተወሰኑ የእንግሊዘኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቃሉን “ልጅ (Child)” በማለት የተረጎሙ ሲሆን አሕመዲን ጀበል ግን ከዓላማቸው ጋር ስለማይሄዱ እነዚህን የእንግሊዘኛ ትርጉሞች በመተው ሌሎቹን ብቻ በመጥቀስ ከእነርሱ ውጪ ሌላ ትርጉም የሌለ ለማስመሰል ሞክረዋል፡፡[7] በአዲስ ኪዳን ውስጥ የጌታችንን የእግዚአብሔር ልጅነት ለመግለፅ “ሁዮስ”[8] የሚል የተለየ የግሪክ ቃል ጥቅም ላይ ውሏል፡፡[9] ጌታችን በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የባርያን መልክ ይዞ መለኮታዊ ክብሩን በመተው እንደ መመላለሱ አገልጋይ ተብሎ ቢጠራ ሰብዓዊ ባሕርዩን እንጂ መለኮታዊ ባሕርዩን ስለማይነካ አምላክነቱን ለማስተባበል የሚውል ሙግት ሊሆን አይችልም (ፊልጵስዩስ 2፡4-12)፡፡ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ቃሉን የሚለውጡበት ምንም ምክንያት የላቸውም፡፡ ነገር ግን ኡስታዙ በቁንፅል ዕውቀት ተነስተው ቃለ እግዚአብሔርን በጥንቃቄ እና በታማኝነት በተረጎሙልን አባቶች ላይ እንዲህ ዓይነቱን ማስረጃ አልባ ውንጀላ መሰንዘራቸው ትልቅ ድፍረት ነው፡፡

65. ኢየሱስ መሞቱን ክርስቲያኖች ያምናሉ፡፡ አምላክ ግን እንደማይሞት እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡ “የተባረከውና ብቻውን ገዥ የሆነው የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ጌታ እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ የሚያሳየው ነው፡፡ እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፡፡ ሊቀረብ በማይችል ብርሃን ውስጥ ይኖራል፡፡ እርሱን ያየ ማንም የለም፡፡ ሊያየውም የሚችል የለም፡፡ ለእርሱ ክብርና ኃይል ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! አሜን፡፡” (1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡16)፡፡ እንዲሁም “ብቻውን አምላክ ለሚሆን፣ ለማይሞተው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉስ ምስጋናና ክብር እስከ ዘለዓለም ድረስ ይሁን፣ አሜን” (1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡17)፡፡ ታዲያ ኢየሱስ ሟች ከሆንና አምልክ የማይሞት ከሆነ ኢየሱስ አምላክ እንዳልሆነ አያሳይምን? እንዲሁም “ብቻውን አምላክ ለሚሆን” ሲል ጥቅሱ አምላክ ብቸኛ እርሱም እግዜአብሔር መሆኑንና ኢየሱስ የሚባል ሌላ አምላክ እንደሌለ አያሳይምን?

የክርስቶስ መሞት አምላክ አለመሆኑን እንደማያሳይ እና እግዚአብሔር ኢ-ሟቲ መሆኑን ከሚናገሩት ጥቅሶች ጋር እንደማይጣረስ በቁጥር 8 ላይ ተብራርቷል፡፡ በተመሳሳይ ልዩ መሆንን የሚያመለክት የቋንቋ አጠቃቀም (Exclusive Language) አምላክነቱን ለማስተባበል የሙግት ግብአት እንደማይሆን በቁጥር 5 ላይ ስለተብራራ ራሳችንን መድገም አያስፈልገንም፡፡ በእርግጥ የግሪኩ በኩረ ጽሑፍ በጥልቀት ሲጠና 1ጢሞቴዎስ 6፡16 ላይ የሚገኘው ቃል ለክርስቶስ የተነገረ መሆኑን እንደሚያመለክት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ በጥቅሱ ውስጥ የተዘረዘሩት ባሕርያት እርሱን የሚያመለክቱ መሆናቸውን ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መረዳት ይቻላል (2ጢሞቴዎስ 1፡8-11፣ ራዕይ 17፡14፣ 19፡11-16፣ 1፡5 ይመልከቱ)፡፡ ለአሕመዲን ጀበል ብዙዎቹ ጥያቄዎች ምንጭ የሆኑትና የኢየሱስን አምላክነት የማይቀበሉት የይሖዋ ምስክሮች (አርዮሳውያን) እንኳ ሳይቀሩ በጽሑፎቻቸው ውስጥ ይህንን አምነው መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡[10] 1ጢሞቴዎስ 1፡17 ላይ የሚገኘው ደግሞ ለአሐዱ ሥሉስ የተነገረ አለመሆኑን እርግጠኛ ሊያደርገን የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ ኢየሱስ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ የተነጠለ ሌላ አምላክ ሳይሆን እንደ አብ እና እንደ መንፈስ ቅዱስ ሁሉ የአንዱ ግፃዌ መለኮት አካል ነው፡፡

66. በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፡18 ላይ “ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅንም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው” ይላል፡፡ በክርስትና ጽንሰ ሐሳብ አምላክ “ከሰማየ ሰማያት ወርጄ ከድንግል ማርያም ተወልጄ አድንሃለሁ” ስላለ ወርዶና ተዋርዶ አዳነን ይባላል፡፡ ነገር ግን ጥቅሱ ”በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን” ይላል፡፡ አምላክ የሚባለው ክርስቶስ ነው ወይንስ በክርስቶስ አማካኝነት ከራሱ ጋር የስታረቀው ነው? ጥቅሱ ይቀጥልና የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው” ይላል፡፡ “አንዱ እግዚአብሔር” ሲባል ክርስቶስ ይጨምራል ወይንስ አይጨምርም? ከጨመረ እንዴት አንዴም ቢሆን ይህ አልተገለጸም? ከጨመረስ ክርስቶስ ስንተኛ አምላክ ሊሆን ነው?

ጠያቂያችን የጠቀሱት አባባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ባለመሆኑ ጥብቅና ልንቆምለት አያሻንም፡፡ በተደጋጋሚ እንደገለፅነው አውዱ ግልፅ ካላደረገ በስተቀር አዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ሲል የተጠቀሰው አካል አብ ነው፡፡ ሐዋርያው እየተናገረ ያለው አብ በክርስቶስ መስዋዕትነት በኩል ከራሱ ጋር እንዳስታረቀንና የምስራቹን በማስተላለፍም ሌሎችን ወደዚህ እርቅ እንድናመጣ የማስታረቅን አገልግሎት እንደሰጠን ነው፡፡ አሕመዲን የክርስቶስን መስዋዕትነት ክደው ከእግዚአብሔር ጋር ጥለኛ ሆነው ከሚኖሩ ንስሐ በመግባት ቢመለሱና ለእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እንደ አምላክነቱ የሚገባውን ክብር ቢሰጡ ይሻላቸዋል፡፡

67. በዕብራውያን 3:3 ላይ ስለ እየሱስ ሲገልጽ “ቤትን የሚያዘጋጀው ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው መጠን እንዲሁ እርሱ ከሙሴ ይልቅ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተቆጥሮአልና፡፡” ይላል፡፡ ታዲያ ኢየሱስ አምላክ ነው ከተባለ እንዴት ከሙሴ ጋር ይነጻጸራል? አምላክ ከማን ጋር ሊነጻጸራል ይችላል?

የዕብራውያን ጸሐፊ ኢየሱስን ከሙሴ ጋር እንዲያነፃፅር ያስገደደው የሕዝቡ የተሳሳተ አመለካከት እንጂ ኢየሱስ የሙሴ ፈጣሪ መሆኑን ዘንግቶ አይደለም፡፡ አሕመዲን አላስተዋሉትም እንጂ በዚሁ ቦታ ላይ ጸሐፊው ኢየሱስ የሙሴ ፈጣሪ መሆኑን እየተናገረ ነው፡፡ ኢየሱስ ከሙሴ ያለው ብልጫ አንድ ሰው የራሱ እጅ ሥራ ከሆነው ቤት ባለው ብልጫ ተመስሏል፡፡ ቤትን የሚሰራ ሰው በእጁ ከሰራው ቤት የበለጠ ክብር የተገባው የሆነበት ምክንያት ቤቱ በእርሱ የተሰራ መሆኑ ነው፡፡ ኢየሱስም ከሙሴ የበለጠ ክብር አለው፤ ምክንያቱም ሙሴ የኢየሱስ ፍጥረት ነውና፡፡ ጸሐፊው ኢየሱስ የአፅናፈ ዓለም ፈጣሪ፣ የሁሉ ጌታ ዘለዓለማዊ አምላክ መሆኑን በምዕራፍ 1 ላይ በመግለፅ ነው የጀመረው፡፡ የሕዝቡን የተሳሳተ አመለካከት ለማረም ኢየሱስን ከፍጥረታት ጋር በማነፃፀር ማቅረቡን ጠያቂያችን ከስህተት ከቆጠሩ የቁርኣን ጸሐፊ አላህን ከፍጥረታት ጋር እያነፃፀረ ማቅረቡን ምን ሊሉት ነው? ለምሳሌ ያህል አላህ ከመሓሪዎች ጋር (ሱራ 7፡155)፣ ከፈራጆች ጋር (ሱራ 12፡80)፣ ከሰዓሊዎች ጋር (ሱራ 23፡14)፣ ከሲሳይ ሰጪዎች ጋር (ሱራ 20፡131፣ 5፡114)፣ ወዘተ. ተነፃፅሯል፡፡

68. በኢሳይያስ 44:7 ላይ አምላክ እንዲህ ማለቱን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፦ “የእስራኤል ንጉሥ ቤዛ እግዚአብሔር፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የፊተኛው እኔ ነኝ፣ የኋላኛውም እኔ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እስቲ እንደኔ ማን አለ? ይናገር፡፡” ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ አምላክ ከሆነ እና አምላከ ሥላሴ (ሦስትም አንድም) ከሆነ እንዴት አንዱ አምላክ “ከኔ በቀር ሌለ አምላክ የለም” ይላል? እንዲሁም እንዴት “እስቲ እንደ እኔ ማን አለ? ይናገር” ይላል? ምናልባት ያኔ አየሱስ ገና ስላልተወለደ ይሆንን? በፍጹም! እንዲህማ ቢሆን ኖሮ “የፊተኛው እኔ ነኝ፤ የኋላኛውም እኔ ነኝ፣ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም” ሲል ይናገራልን??

ጠያቂው አምላክ በአካልም በመለኮትም ነጠላ ነው የሚል የተሳሳተ ቅድመ ግንዛቤ ስለያዙ “ከእኔ በቀር አምላክ የለም” የሚለውን አባባል “አምላክ አንድ አካል ብቻ አለው” ለሚለው ማስረጃ አልባ አመለካከታቸው እንደ ማስረጃ ቆጥረዋል፡፡ በክርስቲያኖች ግንዛቤ መሠረት ግን ይህንን እየተናገረ ያለው አሐዱ ሥሉስ የሆነው አንድ አምላክ ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንኑ አባባል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በመድገም የራሱ አድርጎ የተናገረው (ዮሐንስ 8፡56-58፣ ራዕይ 1፡8፣ 17 አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥”)፡፡

እስልምና አጥብቆ እንደሚያስተምረው ፈጠሪን የሚመስል ምንም ነገር የለም ከተባለ በአንድነቱም የሚመስለው ምንም ነገር መኖር የለበትም፡፡ ነገር ግን የአሕመዲን አምላክ አንድነት በብዙ ምሳሌዎች ሊገለፅ የሚችል ተራ አንድነት ነው፡፡ የአምላካቸው አንድነት ከበሀኢዎች፣ ከሰይጣን አምላኪዎች ከዞራስትራውያን፣ ከአርዮሳውያን፣ ወዘተ. አማልክት አንድነት ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው፡፡ የአምላካቸው አንድነት እንደ ሰው፣ እንደ መላእክት፣ እንደ ሰይጣን፣ እንደ እንስሳት፣ ወዘተ. አንድነት ነው፡፡ ስለዚህ በራሳቸው እምነት መስፈርት እንኳን አምላካቸው እውነተኛ አምላክ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ በተፃራሪ የክርስትናን አምላክ አንድነት በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ እንኳ የሚመስል ምንም ነገር የለም፡፡ በአፅናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኝ የትኛውም ፍጥረት ምሳሌ ሆኖ ሊገልፀው አይችልም፡፡

69. የማቴዎስ ወንጌል 12:18 ስለ አየሱስ ፦ “እነሆ የመረጥሁት የምወደውና በእርሱ ደስ የሚለኝ አገልጋዬ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ እርሱ ለአሕዛብ ፍትህን ያውጃል፤” ሲል ይገልጻል፡፡ በዚህ ጥቅስ ኢየሱስ የአምላክ አገልገይ መሆኑ ተጠቅሶዋል፡፡ ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ ”አምላክ” ነው ወይንስ ይህ ጥቅስ እንደሚለው የአምላክ አገልጋይ? አምላክ ”አገልጋዬ” አያለው ክርስቲያኖች እንዴት አምላክ ነው ይሉታል?

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው ከሥላሴ አካላት መካከል አንዱ የሆነው ወልድ በባሕርዩ አምላክ ቢሆንም ነገር ግን ሥጋን በመልበስ እንደ አገልጋይ ሆኖ ወደ ምድር መጥቷል (ፊልጵስዩስ 2፡5-11)፡፡ ማቴዎስ መሲሁ አገልጋይ ሆኖ ስለመምጣቱ በነቢዩ ኢሳይያስ የተተነበየውን ትንቢት በጠቀሰበት በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ኢየሱስ የሰንበት ጌታ መሆኑን የተናገረውን ቃል አስፍሯል (ቁ. 8)፡፡ እግዚአብሔር ለራሱ ክብርና አምልኮ በፈጠረው ቀን ላይ ጌታ መሆን የሚችለው እርሱ ብቻ በመሆኑ ይህ ንግግር ኢየሱስ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት አንድ መሆኑን ያሳያል፡፡ ስለዚህ ማቴዎስ በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ስለ ኢየሱስ ጌትነትና አገልጋይነት ተናግሯል፡፡ ጌትነቱ መለኮት መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን አገልጋይነቱ ደግሞ እንደ መሲህ የነበረውን ግብር ያመለክታል፡፡

70. በማቴዎስ 15፡12 ለይ “በዝያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው ፈረሳውያን “ይህን ቃል ሰምተው እንደተሰናከሉ አወቅህን?” አሉት” ይላል፡፡ ደቀመዛሙርቱ “ኢየሱስ ኃያሉ አምላክ ነው” ብለው ቢያምኑ ኖሮ እንዴት “አወቅህን?” ብለው ይጠይቁታል? አምላክ መሆኑ ከታመነ ሁሉን አዋቂ ነውና “አወቅህን” ተብሎ ይጠየቃልን?

ኢየሱስ አእማሬ ኩሉ ስለመሆኑ ቁጥር 10 ላይ ማስረጃዎችን ሰጥተናል፡፡ ሐዋርያት እዲህ ያለ አነጋገር በመጠቀም መጠየቃቸው ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው የሚገልፅ እንጂ የኢየሱስን ሁሉን አዋቂነት መጠራጠራቸውን የሚያሳይ አይደለም፡፡ በተጨማሪም ሐዋርያት የኢየሱስን ማንነትና ተልዕኮ በትክክል የተገነዘቡት ከትንሳኤው በኋላ በመሆኑ በዚህ ወቅት ትክክለኛ ማንነቱን ሳይገነዘቡ ቀርተው እንዲህ ያለ ንግግር ቢጠቀሙ የሚያስገርም አይደለም፡፡ ይህ ሐዋርያቱ የእርሱን ትክክለኛ ማንነት በሙላት እንደልተገነዘቡ የሚያሳይ እንጂ ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ አለመሆኑን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ከትንሳኤው በኋላ ግን ሁሉን አዋቂ አምላክ መሆኑን ተገንዝበው ሲመሰክሩና ተገቢውን ክብር ሲሰጡ እንመለከታለን (ዮሐንስ 20፡28፣ 21፡17)፡፡

71. አሕመዲን ቀደም ሲል በዝርዝር የጠየቋቸውን ጥያቄዎች በመጭመቅ ስለደገሙ ቦታና ጊዜ ላለማባከን ይህንን ጥያቄ አልፈነዋል፡፡

72. ከጥያቄ 51 ጋር ስለሚመሳሰል ታልፏል፡፡

73. ይኸኛውም ከጥያቄ 51 ጋር ስለሚመሳሰል ታልፏል፡፡

74. የአምላክ ሕልውና በማንም ላይ ጥገኛ አይደለም፡፡ አይሆንምም፡፡ በዮሐንስ ወንጌል 5:26 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ “አብ በራሱ ሕይወት እንደለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታል ፡፡፡” ይላል፡፡ ነገር ግን እንደዚህኛው ጥቅስ ገለጻ የኢየሱስ ህልውና በአብ (አምላክ) ላይ ጥገኛ ነው፡፡ “ለወልድ በራሱ ሕይወት አንዲኖረው ሰጥቶታል፡፡” ይላል፡፡ ወልድ ህልውና (ሕይወት) ያገኘው አብ ስለሰጠው ነው፡፡ የኢየሱስ ሕልውና በአብ ላይ ጥገኛ ነው፡፡ ኢየሱስ ያለ አብ በራሱ ህልውና ሊኖረው ካልቻለ እንዴት አምላክ ሊሰኝ ይችላል?

ይህ የኢየሱስን ዘለዓለማዊ መገኘት (Eternal Generation) የሚያመለክት በመሆኑ የሥላሴን አስተምህሮ የሚደግፍ ነው፡፡ በሥላሴ አስተምህሮ መሠረት ኢየሱስ በዘለዓለማዊ መገኘት ከአብ የተገኘ ነው፡፡ ለዚህ ነው የኒቅያ የሃይማኖት መግለጫ “ከአምላክ በተገኘው አምላክ፣ ከብርሃን በተገኘ ብርሃን፣ ከእውነትኛ አምላክ በተገኘ እውነተኛ አምላክ፣ በተፈጠረ ሳይሆን በተወለደ…” የሚሉ አንቀፆችን ያካተተው፡፡ የኢየሱስ ሕይወት ከአብ የተገኘ ነው፡፡ ይህ መገኘት ዘለዓለማዊና በጊዜ ያልተገደበ ሲሆን የኢየሱስን መለኮታዊ ባሕርይ ከአብ አያሳንስም፡፡ አብ ያሉት ባሕርያተ መለኮት ሁሉ ወልድም አሉት፡፡ እግዚአብሔርን በትክክል መግለፅ የሚችል ምሳሌ ባይኖርም የወልድን ዘለዓለማዊ መገኘት ለመረዳት ተከታዩ ምሳሌ ይረዳል፡፡ እስኪ በጊዜ ያልተገደበ ከዘለዓለም ዘመናት በፊት ሲያበራ የነበረ አንድ ኮከብ አስቡ፡፡ ብርሃኑ ኮከቡ በነበረበት ጊዜ ሁሉ አብሮት ነበር፡፡ ነገር ግን የኮከቡ ብርሃን ከኮከቡ የተገኘ ነው፡፡ ብርሃኑ ከሌለ ኮከብነቱ ይቀራል፡፡ ኮከቡ ከሌለ ብርሃኑም ሊኖር አይችልም፡፡ የአብ እና የኢየሱስ ቁርኝትም ልክ እንደዚሁ ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱና አብ አንድ መሆናቸውን፤ እርሱን ያየ አብን ማየቱን እዲሁም እርሱ በአብ አብም ደግሞ በእርሱ እዳለ የተናገረው (ዮሐንስ 14፡9-11)፡፡ “አብ” እና “ወልድ” የሚሉት መጠርያዎች ይህንን ዘለዓለማዊ አንድነት የሚገልፁ ናቸው፡፡

75. ፍልጵስዩስ 2፡8-9 ላይ “ሰው ሆኖ ተገልጦም፤ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ፡፡ “ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አድርገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው” ይላል፡፡ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በከፍተኛ ደረጃ ሥልጣን ከነበረው ለአምላክ ታዛዥ በመሆኑ ወደ ነበረበት ይመለሳል ወይስ እንደ አዲስ “ከፍ” ይደረጋል? ይሰጠዋል? ጥቅሱ እንደ አዲስ ስለ ማግኘቱ እንጂ “ወደ ነበረበት ይመለሳል” አይልም፡፡ አንዱ የሥላሴ ክፍል ሌላኛውን ያዘዋልን? ከፍ ያደርገዋልን? ስጦታ ይሰጠዋልን?

አንዱ የሥላሴ አካል ሌላኛውን ይልከዋል፣ ያዘዋል እንዲሁም ክብርን ይሰጠወዋል (ዮሐንስ 5፡32፣ 6፡39፣ 16፡7 ሉቃስ 24፡49፣ ዮሐንስ 16፡14፣ 17፡1-2፣ 17:4፣ 17፡5)፡፡ ጠያቂው መጽሐፍ ቅዱስን በወጉ ቢያነቡና የክርስትናን አስተምህሮ ቢያጠኑ ኖሮ ይህንን ጥያቄ ባልጠየቁ ነበር፡፡ ጠያቂው ቆርጠው ያስቀሩት የጥቅሱ ቀዳማይ ክፍል ኢየሱስ በባሕርዩ አምላክ እንደሆነና ከአብ ጋር የነበረውን እኩልነት በመተው ሥጋን እንደለበሰ ይናገራል (ቁ. 6-7)፡፡ ጥቅሱ አብ ኢየሱስን ከፍ ስለማድረጉ እንጂ አሕመዲን እንዳሉት ክብርን እንደ አዲስ ስለማግኘቱ አይናገርም፡፡ “እንደ አዲስ አገኘ” የሚል ቃል በጥቅሱ ውስጥ ባለመኖሩ ያልተጻፈውን እያነበቡ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ቀድሞ ክብሩ መመለሱን የምናውቅበት መንገድ አለ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በአምላክነት ክብር ይኖር እንደነበር በዚሁ ጥቅስ ውስጥ ተነግሯል፡፡ ከአምላክ በላይ የከበረ ክብር ባለመኖሩ ወደ ቀድሞ ክብሩ ካልተመለሰ በስተቀር እንደ አዲስ ከፍ ተደረገ ማለት ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፡፡ ወደ መስቀሉ ከመሄዱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ወደ ቀድሞ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ አብን ጠይቋል (ዮሐንስ 17:5)፡፡

76. ኢየሱስ ”አምላክ ነኝ! ተገዙኝ” ብሏን? ካለስ የቱጋ? ካላለስ ለምን ይገዙታል? ነገ ኢየሱስ ”እኔን አምልኩኝ ብዬ መች አስተማርኳችሁ?” ቢልዎ ምን ይመልሱለተል?

ለዚህ ጥያቄ ሌላ ቦታ ላይ ቀደም ሲል የማያዳግም ምላሽ ሰጥተናል፡፡ እዚህ ጋር ተጭነው መልሱን ያንብቡ፡፡

77. 1ኛ ጢሞቴዎስ 2:5 ላይ “አንድ እግዚአብሔር አለና፤ ደግሞም በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል አንድ አስታራቂ አለ፤ እርሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ይላል፡፡ አምላክ ስንት ነው? አንድ፤ እሱም እግዚአብሔር ነው፡፡ ኢየሱስስ? ጥቅሱ ”ደግሞም በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል አንድ አስታራቂ አለ፤” ይላል፡፡ እርሱ ማነው? ከተባለ “ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ይላል፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር አንድ ከሆነ ኢየሱስ ሰው፤ በአምላክና በሰው መካከል አስታራቂ እንደሆነ አምላክ ይሆናል? በምን ስሌት ነው ኢየሱስ የተባለው ሰው አምላክ ልንለው የምንሞክረው?

እስኪ መጀመርያ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ አምላክነት ምን እንደተናገረ እንመልከት፡፡ ኢየሱስ ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘለዓለም የተባረከ አምላክ ነው (ሮሜ 9፡5)፤ ታላቁ አምላክ ነው (ቲቶ 2፡13)፤ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ ክብሩን ጥሎ የመጣ ነው (ፊልጵስዩስ 2፡6)፤ የሁሉ ፈጣሪ ነው (ቆላስይስ 1፡16-17)፤ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነቱ ተገልጦ የሚኖር ነው፣ ይህ ማለት ኢየሱስ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው ነው (ቆላስይስ 2፡9)፤ የሰው ልጆች ሁሉ አንድ ቀን በእግዚአብሔር[11] የፍርድ ዙፋን ፊት ይቆማሉ (ሮሜ 14፡10)፤ የሰው ልጆች በፍርዱ ዙፋን ፊት የሚቆሙት ይህ እግዚአብሔር ኢየሱስ ነው (2ቆሮንቶስ 5፡10)፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሐዋርያው በብሉይ ኪዳን ለያሕዌ እግዚአብሔር የተነገሩትን ጥቅሶች በመውሰድ ለኢየሱስ መነገራቸውን ተናገሯል፤ ይህንን በማድረግም ኢየሱስ ያሕዌ እግዚአብሔር መሆኑን በግልፅ አሳይቷል፡፡ ተከታዮቹን ጥቅሶች ያነፃፅሩ፡- ሮሜ 10፡13 ከኢዩኤል 2፡32 ጋር፣ 1ቆሮንቶስ 2፡16 ከኢሳይያስ 40፡13 ጋር፣ 2ቆሮንቶስ 10፡17 ከኤርምያስ 9፡24 ጋር፡፡

ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱት የሐዋርያው ትምህርቶች ከግምት ውስጥ ሲገቡ ጠያቂያችን በጠቀሱት ጥቅስ ውስጥ ኢየሱስን “ሰው” ብሎ መጥራቱ አምላክ ብቻ አለመሆኑን ነገር ግን ሰውም ጭምር መሆኑን ለማስገንዘብ እንጂ አምላክነቱን አለመቀበሉን የሚያሳይ አይደለም፡፡ በእርግጥ ከእኛ ከሰብዓውያን ወገን ሆኖ ወደ አብ የሚያቀርበን ባሕርዩ ሰብዓዊነቱ በመሆኑ ምክንያት በጥቅሱ ውስጥ አፅንዖት ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ ሰው መሆኑን ተናገረ እንጂ ሰው ብቻ መሆኑን በመናገር በሌሎች ቦታዎች ላይ ስለ አምላክነቱ የተናገራቸውን ነጥቦች አልተጣረሰም፡፡ በጥቅሱ ውስጥ አንድ እግዚአብሔር ተብሎ የተጠቀሰው ፍጥረትን በመዋጀት ተግባር ውስጥ ልጁን የላከልን እና መስዋዕትነቱን የተቀበለው እግዚአብሔር አብ ነው፡፡[12] ሐዋርያው በሌላ ቦታ ኢየሱስን “አንድ ጌታ” ብሎ መጥራቱ አብ ጌታ አለመሆኑን እንደማያሳይ ሁሉ አብንም አንድ እግዚአብሔር በማለት መጥራቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር አለመሆኑን አያሳይም (1ቆሮንቶስ 8፡6፣ ኤፌሶን 4፡5)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አብ መንፈስ መሆኑ ተነግሮናል (ዮሐንስ 4፡23)፤ ወልድም መንፈስ መሆኑ ተነግሮናል (2ቆሮንቶስ 3፡17)፡፡ ነገር ግን በሌላ ቦታ ላይ አንድ መንፈስ (መንፈስ ቅዱስ) ብቻ መኖሩ ተጽፏል (ኤፌሶን 4፡5)፡፡ “አንድ”፣ “ብቸኛ”፣ “ከሁሉ በላይ”፣ “ታላቁ”፣ ወዘተ. የሚሉት ልዩ መሆንን የሚያመለክቱ አነጋገሮች (Exclusive Languages) ለሦስቱም የሥላሴ አካላት በተናጠል ሊነገሩ የሚችሉ ሲሆኑ ሌላውን የሚያገልሉ አይደሉም፡፡ ለበለጠ ማብራርያ መልስ ቁጥር 5 ይመልከቱ፡፡

78. በ1ኛ ቆሮቶስ 8:5-7 ላይ “መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፣ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ ለእኛስ ነገሩ ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን “አንድ አምላክ አብ አለን፣ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን” ይላል፡፡ ይህን ጥቅስ ልብ ብለው ካስተዋሉ ክርስታኖች እንደሚሉት ከአንድ አምላክ ክፍል የሆኑ “አንድ ጌታ” እና “አንድ እግዚአሔር” አይልም፡፡ ነገር ግን ”አንድ አምላክ አብ” ነው የሚለው፡፡ ኢየሱስንም በዚህ አንዱ በተባለው አምላክ ውስጥ አልጨመረምውም፡፡ ለብቻው ነው “አንድ ጌታ” የሚለው፡፡

አሕመዲን በቁጥር 7 ላይ መልስ የሰጠንበትን ጥያቄ ነው የደገሙት፡፡ ጥያቄዎችን በመደጋገም ብዛታቸውን 303 ለማድረስ የፈለጉ ነው የሚመስሉት፡፡ ሐዋርያው ስለ እግዚአብሔር አንድነት አጥብቆ የሚያስተምረው የአይሁድ ሼማ (ዘዳግም 6፡4) አብ እና ወልድን እንደሚያመለክት እያስተማረ ነው (መልስ ቁጥር 7 እና የግርጌ ማስታወሻውን ይመልከቱ)፡፡ የመልዕክቱ ተደራሲያን ይህንን እውነታ ስለሚያውቁ ሐዋርያው አሕመዲን የተናገሩት ዓይነት ሐተታ ውስጥ መግባት አላሻውም፡፡

እንዲህ ሲሉ ጥያቄያቸውን ይቀጥላሉ፡- ይህ ጌትነት አምለክ ውስጥ ካልተጠራ እንዴት ጌታ ከተባሉ ሌሎች ግለሰቦች ለይተን ኢየሱስን “አምላክ” ልንለው ይቻለናል? “ጌታ” እና “እግዚአብሔር” ማለት አንድ ቢሆኑ ለምንድነው በመጽሐፍ ቅዱስ በበርካታ ስፍራ ሰዎች ኢየሱስን “ጌታ” ሲሉት አንድም ጊዜ “እግዚአብሔር” አልያም “እግዚአብሔ አብ” እንደሚባል ”እግዚአብሔር ወልድ/ኢየሱስ” የልተባለው? ካልሆነ ለምንደነው አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በአንድነት በአንዱ አምላክ “እግዚአብሔር” ውስጥ ተካተው ወልድን ያልገለጹት?

የኢየሱስ ጌትነት እንደ ሌሎች ሰዎች ጌትነት የማይሆንበት እና አምላክነቱን የሚያሳይበት ምክንያት አሕመዲን በጠቀሱት በዚያው ክፍል ውስጥ ተነግሯል፡፡ ብዙ ጌቶች የተባሉ ፍጥረታት ቢኖሩም ነገር ግን ኢየሱስ ከእነርሱ የተለየ ብቸኛ ጌታ ነው፡፡ ብቸኛ ጌታ ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ፈጣሪ ብቻ መሆኑን አሕመዲንም ሆኑ ሌሎች ሙስሊሞች የሚክዱ አይመስለኝም፡፡ ታድያ ኢየሱስ ብቸኛ ጌታ ተብሎ እያለ ከሌሎች ጌቶች ለይተን አናየውም ማለት ምን የሚሉት አማርኛ ነው? ኢየሱስ እግዚአብሔር አልተባለም የሚለው የጠያቂያችን አባባል ምን ያህል ከመጽሐፍ ቅዱስ የራቁና የተለቃቀሙ ጥቅሶችን ብቻ የሚያነቡ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ ኢየሱስ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ አምላክ/ እግዚአብሔር ተብሎ ስለመጠራቱ ተከታዮቹን ጥቅሶች ማየት ይቻላል፡- (ዮሐንስ 1፡1-3፣ 20፡28፣ የሐዋርያት ሥራ 20፡28፣ ሮሜ 9፡5፣ ቲቶ 2፡13፣ 2ጴጥሮስ 1፡1፣ 1ዮሐንስ 5፡20)፡፡ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በአንድነት አንዱን ግፃዌ መለኮት ይገልፃሉ እንጂ አሕመዲን እንዳሉት አንዱን የሥላሴ አካል አይገልፁም፡፡ ይህንን ጥያቄ ከምን አኳያ እንደጠየቁ ለእሳቸውም ግልፅ የሆነ አይመስልም፡፡

ማጣቀሻዎች


[1] እግዚአብሔር ማንንም እንደማይፈትን መነገሩ ኃጢአትን ወደ መሥራት የሰዎችን ፍላጎት እንደማይገፋፋ ለማመልከት እንጂ የሰዎችን እምነት እንደማይፈትን ለማመልከት የተነገረ አይደለም፡- ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፥ እንዲህም አለው፦ አብርሃም ሆይ፡፡ አብርሃምም፦ እነሆ፥ አለሁ አለ፡፡ የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ” (ዘፍጥረት 221-2)፡፡

[2] በቦታው ላይ የተጠቀሰው “ፕላኽ” የሚለው የአረማይክ ቃል ለፈጣሪ ብቻ የሚሰጠውን አምልኮ ያመለክታል፡፡

[3] አዲሱ መደበኛ ትርጉም እና የሚታወቁት የእንግሊዘኛ ትርጉሞች ሁሉ የተወጋው ያሕዌ እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን በሚገልፅ ሁኔታ ተርጉመውታል፡፡ በ1954 ዕትም “ወደ ወጉት ወደ እርሱ” ተብሎ የተተረጎመው ከእብራይስጡ ጋር የሚስማማ ባለመሆኑ የትርጉም ስህተት መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

[4] Tirmidhi 2640; Sunan Abu Dawud 5496, 4597; Ibn Majah Book 36 Hadith 3991

[5] παîς

[6] Vines Complete Expository Dictionary of Old and New Testament Words, 1984, pp. 76, 100 & 562.

[7] ለምሳሌ King James Version, American Bible in Plain English, Jublee Bible 2000, King James 2000 Bible, American King James Version, Douay-Rheims Bible, Webster’s Bible Translation, Young’s Litral Translation ይመልከቱ፡፡

[8] υîός

[9] Vines Complete Expository Dictionary of Old and New Testament Words, pp. 584-585.

[10] Jehovah is the “happy God” and his Son Jesus Christ is called “the happy and only Potentate” (1 Tim. 1:11; 6:15)… (Aid to Bible Understanding, Watch Tower Bible and Tract Society of New York, Inc., 1971], p. 711.

…For this reason, when describing him as “the King of those who rule as kings and Lord of those who rule as lords,” 1 Timothy 6:15, 16 shows that Jesus is distinct from all other kings and lords in that he is “the one alone having immortality.” The other kings and lords, because of being mortal, die, even as did also the high priests of Israel. The glorified Jesus, God’s appointed High Priest after the order of Melchizedek, however, has “an indestructible life.” – Heb 7:15-17, 23-25. (Insight on the Scriptures [Watch Tower Bible and Tract Society of New York, Inc., Brooklyn, NY 1988], Volume 1. Aaron-Jehoshua, p. 1189.

[11] ሮሜ 14፡10 ላይ በቀድሞ ትርጉም “ክርስቶስ” የተባለው በግሪኩ በኩረ ጽሑፍ “ቴዎስ” (እግዚአብሔር) ይላል፡፡ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይመልከቱ፡፡

[12] አንድ እግዚአብሔር የተባለው አንዱ የሥላሴ ግፃዌ መለኮት እንደሆነና ሰው የሆነው ኢየሱስ ሰብዓዊ ማንነቱን ብቻ እንደሚያመለክት የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ ይህ አተረጓጎም እንደ አንድ አማራጭ ሊወሰድ ይችላል፡፡

የኢየሱስ ማንነት ጉዳይ (ክፍል 1)

የኢየሱስ ማንነት ጉዳይ (ክፍል 2)

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ