የኢየሱስ ማንነት ጉዳይ (ክፍል 1)

ምዕራፍ አንድ

የኢየሱስ ማንነት ጉዳይ (ክፍል 1)

1.በሐዋርያት ሥራ 2:36 ላይ “እንግዲህ እግዚአብሔር ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ ይረዳ፡፡” ይላል፡፡ ታድያ እግዚአብሔር ኢየሱስን “ጌታ” ካደረገው መጀመርያ ምን ነበር? “ጌታ” የሚለው የክብር መጠርያ ከሆነ ያስኬዳል፡፡ ነገር ግን “አምላክ” በሚለው ትርጉም ከሆነ የማይመስል ነው፡፡ ለምን ቢሉ ከጊዜ በኋላ “ጌታ (አምላክ) መሆን ይችላልን? ጥቅሱ የሚለው “ጌታም ክርስቶስ እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ ይረዳ” ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በትክክል ጌትነትን ከጊዜ በኋላ ነው ያገኘው የሚል ነው፡፡ አምላክ ደግሞ ዘለዓለማዊ ነው፡፡ ኢየሱስ እንዴት አምላክ (ጌታ) ሊባል ይቻለዋል?

ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደምንረዳው ኢየሱስ “ጌታ (ኩሪዮስ)” የተባለው አምላክ በመኾኑ እንጂ ለነገሥታት በሚኾን መንገድ በማዕርግ አጠራር አይደለም፡፡ የብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉም በሆነው የሰብዓ ሊቃናት (ሰብቱጀንት) ትርጉም ውስጥ “ያሕዌ” የሚለው የእግዚአብሔር የተፀውዖ ስም “ኩሪዮስ (ጌታ)” ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ይኸው ቃል በግሪክ አዲስ ኪዳን ኢየሱስን ለመግለፅ የገባ ሲሆን ለፍጥረታት በሚሆን መንገድ እንዳልሆነ ማረጋገጫው በብሉይ ኪዳን ነቢያት ለያሕዌ የተነገሩ ጥቅሶች በአዲስ ኪዳን ስለ ኢየሱስ የተነገሩ መሆናቸው መገለፁ ነው፡፡ ተከታዩን ሳጥን ይመልከቱ፡-

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

የያሕዌን ስም የሚጠራ ኹሉ ይድናል (ኢዩ. 2፡32) የኢየሱስን ስም የሚጠራ ኹሉ ይድናል (ሐዋ. 22፡14-16፣ ሮሜ 10፡9-13)
ያሕዌ የጌቶች ጌታ ነው (መዝ. 136፡3፣ ዘዳ. 10፡17) ኢየሱስ የጌቶች ጌታ ነው (ራዕይ 1፡5፣ 17፡14፣ 19፡16)
ያሕዌ የኹሉ ጌታ ነው (ዘዳ. 10፡14፣ ኢያሱ 3፡11-13፣) ኢየሱስ የኹሉ ጌታ ነው (ሐዋ. 10፡36፣ ሮሜ 14፡8-9፣ ማቴ. 28፡18)
ጉልበት ኹሉ ለያሕዌ ይንበረከካል (ኢሳ. 45፡21-23) ጉልበት ኹሉ ለኢየሱስ ይነበረከካል (ፊል. 2፡10-11)
ያሕዌ ፊተኛውና ኋለኛው ነው (ኢሳ. 44፡6) ኢየሱስ ፊተኛውና ኋለኛው ነው (ራዕይ 1፡17-18፣ 22፡12-13)
ያሕዌ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል (መዝ. 130፡7-8) ኢየሱስ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል (ማቴ. 1፡21)
ያሕዌ ለእያንዳንዱ ሰው እንደየሥራው ይከፍለዋል (ኢሳ. 40፡10) ኢየሱስ ለእያንዳንዱ ሰው እንደየሥራው ይከፍለዋል (ራዕይ 22፡12-16)
ለያሕዌ መንገድ የሚጥርግ መልዕክተኛ ይመጣል (ኢሳ. 403) ለኢየሱስ መንገድ የሚጠርግ መልዕክተኛ (መጥምቁ ዮሐንስ) መጥቷል (ማር. 1፡2-3)

በሳጥኑ ውስጥ በተጠቀሱት የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ውስጥ የሚገኘው “ያሕዌ” የሚለው ስመ-እግዚአብሔር በሰብዓ ሊቃናት የግሪክ ትርጉም “ኩሪዮስ(ጌታ)” ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን እነዚሁ ጥቅሶች ኢየሱስን ለማመልከት በግሪክ አዲስ ኪዳን ውስጥ መጠቀሳቸው ኢየሱስ “ጌታ(ኩሪዮስ)” ተብሎ መጠራቱ አምላክነቱን ለማሳየት እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ “ጌታ” የተባለው ነገሥታት ለክብር በሚጠሩበት መንገድ ካልሆነና አምላክነቱን በሚያረጋግጥ መንገድ ከሆነ ጠያቂው የጠቀሱት የጴጥሮስ ንግግር ትርጉሙ ምን ይኾን?

በዚህ ቦታ የተነገረው ስለ ኢየሱስ ጌትነት ብቻ ሳይኾን ስለ መሢህነቱም ጭምር መኾኑን ልብ ይሏል፡፡ የጠያቂውን አመክንዮ ከተቀበልን “ኢየሱስ ከመጀመርያው መሢህ (ክርስቶስ) አልነበረም ነገር ግን መሢህ የሆነው ከስቅለቱ በኋላ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ እንገደዳለን፡፡ ነገር ግን በቁርኣንም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ኢየሱስ ሲወለድ ጀምሮ መሢህ መባሉን እናያለን (ሱራ 3፡45)፡፡

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሉቃስ ወንጌል ቀጣይ ክፍል በመኾኑ ምክንያት የዚህን ኃይለ ቃል ትክክለኛ ትርጉም ለመረዳት ወንጌላዊው ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ጌትነትና ክርስቶስ ስለመኾኑ በወንጌሉ ውስጥ የጻፈውን መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡ በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ በልደቱ ወቅት እንኳ ጌታና ክርስቶስ ተብሎ ተጠርቷል (ሉቃ. 1፡41-44፣ ሉቃስ 2፡11)፡፡ ጴጥሮስን ጨምሮ ሐዋርያቱ  ጌታና ክርስቶስ መኾኑን በተደጋጋሚ መስክረዋል (ሉቃ. 9፡18-20፣ 10፡17-22)፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው እየተናገረ ያለው ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ጌታና ክርስቶስ ስለመኾኑ ሳይኾን ጌታና ክርስቶስ መኾኑን ከሙታን በማስነሣት እግዚአብሔር አብ ማረጋገጫ (Vindication) መስጠቱን ነው፡፡ ይህንን የበለጠ ለመረዳት ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውን አንድ ቃል እንመልከት፡-

“ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ኾኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” (ሮሜ 1፡4-5)፡፡

በዚህ ክፍል ግልፅ ኾኖ እንደሚታየው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው በትንሣኤው ወቅት ሳይኾን እግዚአብሔር ለዓለም ኹሉ ተዓምራዊ በሆነ ኹኔታ ይህንን ያረጋገጠው በትንሣኤው ወቅት መኾኑን እንገነዘባለን፡፡ ጌትነቱና መሢህነቱም እንደዚያው ነው፡፡

ሌላው መታወስ ያለበት ጉዳይ ቢኖር ጌታችን ወደ ምድር የመጣው ክብሩን ጥሎ የባርያን መልክ በመያዝ እንጂ እንደ ጌታና እንደ ንጉሥ እንዳልነበረ ነው (ሉቃ. 22፡27፣ ማቴዎስ 12፡15-21፣ ሮሜ 15፡8፣ ፊልጵሲዩስ 2፡5-8)፤ መለኮታዊ ባሕርዩ ባይለወጥም ነገር ግን በምድር ላይ የተመላለሰው ፍጹም ሰው በመኾን ነበር፡፡ በማንነቱ ጌታ ቢሆንም ሰብዓዊ ባሕርይን በመላበስ በግብር (Function) አገልጋይ ኾኖ ነበር፡፡ የጌትነት ደረጃውን በሙላት የተቀዳጀው ከእርገቱ በኋላ ነው፡፡ ሐዋርያው እግዚአብሔር አብ ኢየሱስን “ጌታና ክርስቶስ እንዳደረገው” ሲናገር ቀደም ሲል እንደተባለው እግዚአብሔር አብ በትንሣኤ አማካይነት የጌትነቱን ማረጋገጫ ከመስጠቱም በተጨማሪ ተልዕኮውን በመፈፀሙ ምክንያት የጌትነቱን ክብር በተግባር ማቀዳጀቱን ለመግለፅ እንጂ  ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ጌታ ሆነ ለማለት ፈልጎ አይደለም፡፡ የጠያቂው ትርጓሜ ከሉቃስ ጽሑፎች ጋር፣ ብሎም ከመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ነገረ ክርስቶስ ጋር ይጣረሳል፡፡

2. መጽሐፍ ቅዱስ በሉቃስ ወንጌል 22: 3 -5 “ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ከተቆጠረው አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በተባለው በይሁዳ ገባበት፤  ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከመቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ፡፡ እነርሱም ደስ አላቸው፥ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ፡፡ እርሱም በነገሩ ተስማማ” ይላል፡፡ ሰይጣን በይሁዳ ገብቶ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ካደረገውና ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስም ተይዞ ከተሰቀለ ሰይጣን ለክርስቲያኖች ባለ ውለታ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ለምን ቢሉ ክርስቲያኖች እንደሚሉት በኢየሱስ መሰቀል ነውና “ድነው ከኃጢአት ነጻ የወጡት፤ ገነትም ወራሽ የሆኑት፡፡”  ይህ ነው የክርስትና መዳኛ መንገድ፡፡ ስለዚህ ሰይጣን በይሁዳ ገብቶ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ አደረገው፡፡ ከዚያም ክርስትና እንደሚለው ኢየሱስ ተይዞ ተሰቀለ፡፡ በጥሞና ካስተዋልነው ክርስቲያኖች “ድነናል” ያሉበት “ስቅለት” እንዲሳካ ሰይጣን ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የመዳኛውን መንገድ ዘርግቷል፡፡ ታድያ የክርስትና አብዩ አስተምህሮትና መዳኛው የሰይጣን ሊሆን አይደል? ሰይጣን በይሁዳ ገብቶ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ባያደርግ ኖሮ ስቅለት ይሳካ ነበር? ክርስትና እንደሚለው ክርስቶስ ባይሰቀል ክርስትያኖች ከኃጢአት ይነጹ ነበርን? ክርስትና የሚባል እምነትስ ይኖር ነበርን? በፍፁም!! ታድያ እንደ ሰይጣን ማን መልካም ሰሪ አለ? ኢየሱስን አሰቅሎ ክርስትያኖችን አድኖ የለም እንዴ?

አሕመዲን ጀበል ይህንን ጥያቄ ያቀረቡበት መንገድ ከምሑራዊ አካሄድ ያፈነገጠ፣ ድፍረትና ንቀት የታከለበት እንዲሁም የክርስትናን ትምህርት በሚያንቋሽሽ አነጋገር ነው፡፡ አካሄዳቸውን በማበላሸት ገና ከጅምሩ ኩሬውን መርዘውታል፤ የማስተማር ፍላጎታቸውንና ቅንነታቸውንም እንድንጠራጠር አድርገውናል፡፡

የክርስቶስ ወደ ምድር መምጣትና ስለ ሰው ልጆች ኃጢኣት መሞት የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ እቅድ እንጂ የየትኛውም ፍጥረት ዕቅድ አልነበረም (ራዕይ 13፡8፣ የሐዋርያት ሥራ 4፡27-28)፡፡ ወደ ምድር የመጣውም በገዛ ፈቃዱ ነፍሱን ስለ ብዙዎች ቤዛ ለማድረግ እንጂ ተገዶ አይደለም (ዮሐንስ 10፡11፣ 10፡15፣ 10፡17-18 15፡13፣ ማርቆስ 10፡45)፡፡ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው አስቀድሞ መናገሩን በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ እናነባለን (ማቴዎስ 12፡38-40፣ 16፡21፣ 17፡22-23፣ 20፡18-10፣ 21፡33-46፣ 26፡21-32፣ 26፡36-40፣ 26፡61-62፣ ማርቆስ 8፡31፣ 9፡9፣ 9፡30-31፣ 10፡33-34፣ 10፡45፣ 12፡1-12 14፡18-28፣ 14፡32-40፣ ሉቃስ 9፡22፣ 11፡29-30፣ 13፡32-33፣ 20፡9-19፣ 22፡15-20፣ 22፡39-46፣ ዮሐንስ 3፡13-14፣ 8፡28፣ 12፡32-34)፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ሞት በሰይጣን የታቀደ አልነበረም፡፡ ሰይጣንም ሆነ በአፅናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኝ የትኛውም ፍጥረት በእግዚአብሔር እንደተፈጠረ፣ በእርሱ ሉኣላዊ ሥልጣን ስር እንደሚገኝና እግዚአብሔር አምላካችን የሁሉ የበላይ እንደሆነ ክርስትና ያስተምራል (ዳንኤል 4፡35፣ 2ዜና 29፡14፣ 20፡6፣ ዘዳግም 10፡14፣ ነህምያ 9፡6፣ ራዕይ 4፡11)፡፡ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጪ እንደሆነ ማሰብና የእግዚአብሔር ተፎካካሪ አካል አድርጎ መሳል የእግዚአብሔርን ሉኣላዊ ሥልጣን ያለማወቅ ነው፡፡ ሰይጣን የይሁዳን ክፉ ምኞት በመጠቀም ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ሲያደርገው የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ ዕቅድ በመረዳትና የራሱን የሽንፈት መንገድ እያመቻቸ መሆኑን በማወቅ አልነበረም፡፡ ይህንን በማድረጉ እንደ ይሁዳ ሁሉ ሰይጣንም ራስን የማጥፋት ተግባር ፈፅሟል፡፡ የኢየሱስ ሞት ሰይጣንን አዋርዶታ፡፡ ትንሣኤው ደግሞ እስከ ወዲያኛው ኃይሉን አንኮታኩቶታል! ሰይጣን በየዘመናቱ የእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ለማበላሸት ቢሞክርም እግዚአብሔር ግን የዕውቀቱን ምጡቅነት እና የጥበቡን ልቀት በማሳየት ሰይጣንን ሲያዋርደው እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ ያህል ሰይጣን ኢዮብን ሲፈትነው ፃድቅ የሆነውን ኢዮብን ከእግዚአብሔር በመለየት ለማጥፋ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን የሰይጣንን ፈተና የኢዮብን እምነትና ፅድቅ ለመግለጥ እና ለትውልዶች ሁሉ ማስተማርያ ለማድረግ ተጠቅሞበታል፡፡ ሰይጣንም ዕቅዱ ግቡን ሳይመታ ቀርቶ አፍሯል፡፡ የኢየሱስም ስቅለት እንደዚያው ነው፡፡ የተዋረደው ሰይጣን ዛሬ በእነ አሕመዲን በኩል በመምጣት ውርደቱንና ሽንፈቱን ለማስተባበል ቢሞክር አንሰማውም፣ አንቀበለውም፡፡

3. ኢየሱስ ሰው መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ላይ ይናገራል (አሕመዲን ለዚህ ማስረጃ የሚሆኑ 20 ጥቅሶችን ጠቅሰዋል)፡፡ አምላክ ከሆነ ለምን በርካታ ስፍራ ላይ “የሰው ልጅ” “ሰው” ተባለ? አምላክ ሰው ነውን? የሚከተሉት ጥቅሶች አምላክ ሰው እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡-

ሀ) “ይዋሽ ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፤ ይፀፀትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፡፡” (ዘኁልቁ 23:19)

ለ) “የእስራኤል ክብር የሆነው እግዚአብሔር አይዋሽም፤ አይፀፀትም፤ እርሱ ይፀፀት ዘንድ ሰው አይደለምና፡፡” (1ኛ ሳሙኤል 15:29)

ሐ) “እኔ በመካከላችሁ ያለሁ ቅዱስ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና፤ በቁጣ አልመጣም፡፡” (ትንቢተ ሆሴዕ 11:9)

“ኢየሱስ ፍፁም ሰው፣ ፍፁም አምላክ ነው” ስንል “አምላክ ሰው ነው” እያልነው ነው፡፡ ይህ ታድያ አምላክ ሰው እንዳልሆነ የተገለፀውን መፃረር አይደለምን?

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት “የሰው ልጅ” የሚለው ማዕርግ ጠያቂው ካሰቡት በተፃራሪ ኢየሱስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ መሆኑን ያሳያል (ዳንኤል 7፡13፣ ይህንን ጥቅስ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ደጋግመን ስለምናነሳው የክርስቶስን አምላክነት በተመለከተ የሚሰጠንን ምልከታ ግልፅ እናደርጋለን)፡፡ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ እንደሆነ እንጂ ሰው ብቻ፣ አምላክ ብቻ፣ ግማሽ ሰው ግማሽ አምላክ፣ ወደ ሰው የተለወጠ አምላክ፣ ወዘተ. እንደሆነ አያምኑም፡፡ ጠያቂው ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት ከራሳቸው የተሳሳተ መረዳት በመነሳት ነው፡፡ ክርስቲያኖች “አምላክ ሰው ነው” አይሉም፡፡ ነገር ግን “ኢየሱስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ነው” በማለት ያምናሉ፡፡ ሰው የሆነው የኢየሱስ ባሕርይ አምላክ አይደለም፡፡ አምላክ የሆነውም የኢየሱስ ባሕርይ ሰው አይደለም፡፡ እነዚህ የኢየሱስ ሁለቱ ባሕርያት ሳይነጣጠሉና ሳይቀላቀሉ ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ባሕርያት ስላልተቀላቀሉ በብሉይ ኪዳን ዘመን አምላክ ሰው አለመሆኑ መነገሩ በአዲስ ኪዳን አምላክ በሥጋ የመገለጡን እውነታ አይፃረርም፡፡ በተጨማሪም እነዚህ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች የሚናገሩት አምላክ እንደ ሰው ልጆች ኃጢአተኛና ቃሉን የሚያጥፍ አለመሆኑን እንጂ በእነዚህ የሰው ልጅ ችግሮች ባልተበከለ ሁኔታ በሥጋ መገለጥ አለመቻሉን እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር በሰው አምሳል የተገለጠባቸው ጊዜያት ነበሩ (ዘፍጥረት 18፡1-33፣ 32፡24-32)፡፡

አሕመዲን እንዲህ በማለት ይጠይቃሉ፡- ሌላው አጠያያቂ ነጥብ ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወይም ከመላእክት የላቀ አካል መሆኑን ከተቀበሉ ክርስቶስን “ሰው” ብለው መጥራታቸው ለምን ይሆን? ሐዋርያት የኢየሱስን አምላክነት ከተቀበሉ በኋላ “ሰው” ነበረ ብለው ማስተማራቸው ክብሩን መንካትና ደረጃውን መቀመቅ መክተት አይሆንምን?

ሐዋርያት እርሱ ያልሆነውን አላሉም፡፡ ስለዚህ አምላክም ሰውም መሆኑን መናገራቸው የእርሱን ክብር የሚነካ አይደለም፡፡ ሰው እንዲሆን ያደረገው ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ነው፡፡ ይህ ከሰው ልጆች እጅግ ርቆ ለሚገኝ የምናብ “አምላክ” የሚቻል አይደለም፡፡ አምላካችን ግን የቅርብና አፍቃሪ አምላክ በመሆኑ ይህንን አድርጓል፡፡

ጠያቂው አሁንም ይቀጥላሉ፡- ሐዋርያት ኢየሱስን አይተውታል፡፡ አናግረውታል፡፡ አብረው ተመግበዋል፡፡ ይህን ሁሉ ሲፈጽሙ ግን ኢየሱስ ልክ እንደ እነሱ ሰብአዊ ፍጡር መሆኑን ቅንጣት ታህል ተጠራጥረው አያውቁም፡፡ ታድያ በዚህ ሁኔታ እያለ ኢየሱስ ሰው ሳይሆን “የዓለማት ፈጣሪ አምላክ ነው” ቢባል የሚሰማቸው ድንጋጤና ግርምት እኛ አንድ የምናውቀው ሰው አምላክ ወይም የዓለም ፈጣሪ ነው ብንባል የሚሰማንን ያህል ነው፡፡ ለምን? ቢሉ ኢየሱስ በርካታ ሰዋዊ ተግባራት ሲፈፅም ፤ ስኬትና ውድቀት ሲፈራረቅበት፤ ሀሴትና ሀዘን ሲመላለስበት ተመልክተዋል፡፡ ታድያ ይህ መሰሉ ሁኔታ የአምላክነት ክብርና ደረጃውን እንዲያስቡ አድርጓቸው ነበር ብሎ ማሰብ ያስኬዳልን? አይመስለኝም!

ለእርስዎ ባይመስልዎትም እነርሱ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ መሆኑን ተቀብለውና ጽፈውልን አልፈዋል፡፡ ውድ አሕመዲን፣ ሁሉን ቻዩ አምላክ ወደ ምድር መጥቶ ሰው በመሆን በመካከላችን የመኖር ችሎታ ያንሰዋል ብለው ያምናሉን? እንደርሱ ብለው የሚያምኑ ከሆነ የፈጣሪን ሁሉን ቻይነት ስለካዱ ንስሐ መግባትና ሁሉን ቻይነቱን መቀበል ያሻዎታል፡፡ ሐዋርያት ምስክርነታቸውን ከሰጡ ከ 600 ዓመታት በኋላ ምስክር በሌለበት ወደ ዋሻ ገብቶ በመውጣት ይህ ሁሉ ነገር ትክክል እንዳልሆነ መልአክ እንደነገረው የነገርዎትን ሰው ስብከት በጭፍን ተቀብለው ከሆነ ደግሞ ከባድ ስህተት ፈፅመዋል፡፡ የሐዋርያትን ትምህርት የሚክደውን የሰውየውን ትምህርት ሲቀበሉ እውነት ስለመናገሩ ምን ያህል ጥናትና ምርምር አድርገዋል? ለእውነተኛነቱስ የሚያቀርቡት ማስረጃ ምንድነው? የአንድን ሰው ምስክርነት በጭፍን ከማመንና ቃላቸው እውነት መሆኑን እስከ ሞት ድረስ በመታመን የመሰከሩትን የዓይን ምስክሮች ዘገባ ከማመን የትኛው ይመረጣል? ትክክለኛ ውሳኔ መወሰን እንዲችሉ እግዚአብሔር ልቦና ይስጥዎት!

4. ቆላሳይስ 1፡15 ላይ ስለ ኢየሱስ “እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው፤” ይላል፡፡ እንዲሁም በሮሜ 8፡29 ላይ “እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፡፡ ይኸውም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኩር እንዲሆን ነው” ይላል፡፡ ኢየሱስ “የፍጥረት በኩር” ወይም መጀመሪያ የተፈጠረ ከሆነ እንዴት ከፍጡርነት አልፎ ፈጣሪ ይሆናል? ይህ ሁኔታ የክርስቶስን ማንነት እንድንፈትሽ አይጋበዝምን?

ይህ የሙግት ሐሳብ “ከይሖዋ ምስክሮች” (አርዮሳውያን) የተቀዳ ነው፡፡ በአርዮሳውያን ትምህርት መሠረት ኢየሱስ በይሖዋ የተፈጠረ የመጀመርያው ፍጡር ነው፡፡ ነገር ግን የግሪኩን ንባብ፣ ማለትም አዲስ ኪዳን መጀመርያ የተጻፈበትን ቋንቋ እንዲሁም “በኩር” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለባቸውን የተለያዩ አውዶች ስንመለከት የእነርሱን ሐሳብ የሚደግፍ ሆኖ አናገኘውም፡፡ ከዚያም አልፎ ኢየሱስ የመጀመርያው ፍጡር ነው የሚለው አባባል ፍጡርን ከጊዜና ከስፍራ ስለሚያስቀድም ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ ከፈጣሪ በስተቀር ፍጡራን ሁሉ በጊዜና በቦታ የተገደቡ በመሆናቸው ኢየሱስ ፍጡር ከሆነ እንደ ሌሎቹ ፍጡራን ጊዜና ስፍራ ከተፈጠሩ በኋላ ነበር መፈጠር የነበረበት፡፡

አዲስ ኪዳን አስቀድሞ በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ “መጀመርያ የተፈጠረ” ለሚለው ሐረግ አቻ ቃል “ፕሮቶኪቲሲስ” የሚል ሲሆን “በኩር” ለሚለው ደግሞ “ፕሮቶቶኮስ”[1] የሚል ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ የመጀመርያ ፍጡር መሆኑን ሊነግረን ፈልጎ ቢሆን ኖሮ የመጀመርያውን ቃል ይመርጥ ነበር፡፡ ነገር ግን መጀመርያ መፈጠርን የሚያሳየው ቃል በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ኢየሱስን ለማመልከት ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “በመጀመርያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ” ይላል እንጂ “ኢየሱስን ፈጠረ” አይልም (ዘፍጥረት 1፡1)፡፡ “በኩር” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሁለት መንገዶች ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ የመጀመርያው በጊዜ ቀዳሚነትን ለማመልከት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የበላይነትን ወይም ላዕላይ ደረጃን ለማመልከት ነው፡፡ ሁለተኛውን ሐሳብ የሚደግፉ ሁለት ጥቅሶችን እንጠቅሳለን፡-

“ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት… እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፥ ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል” (መዝሙር 89፡20፣ 27)፡፡

ዳዊት በውልደት የቤቱ ታናሽ እንደሆነና ሁለተኛው የእስራኤል ንጉሥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከምድር ነገሥታት ሁሉ በኩር እንደሚያደርገው ተናግሯል፡፡

“…እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኵሬ ነውና” (ኤርምያስ 31፡9)፡፡

ኤፍሬም ሁለተኛው የዮሴፍ ልጅ መሆኑ ይታወቃል (ዘፍጥረት 49፡13-19)፡፡

ብኩርና ወራሽነትንና የበላይነትን ስለሚያመለክት ከአንዱ ወደ ሌላው ሊተላለፍ የሚች መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ዕብራውያን 12፡16)፡፡

አሕመዲን በጠቀሷቸው ክፍሎች ውስጥ “በኩር” የሚለው ቃል ኢየሱስ የበላይና ወራሽ መሆኑን ለማመልከት እንጂ የመጀመርያ ፍጡር መሆኑን ለማመልከት አልገባም (ሮሜ 8፡17፣ 29፣ ዕብራውያን 1፡1-3፣ ማርቆስ 12፡6-8)፡፡ ከአርዮሳውያን በተኮረጀው የጠያቂው ሙግት መሠረት ኢየሱስ የመጀመርያው ፍጡር ቢሆን በአላህ አማካይነት በእናቱ ማህፀን ውስጥ እንደተፈጠረ የሚናገረው የእስልምና ትምህርት ውድቅ ስለሚሆን ሙግታቸው እስልምናን የሚያፈርስ እንጂ የሚጠቅም አይደለም፡፡

5. እውነተኛ አምላክ ኢየሱስ ነው ወይንስ እግዚአብሔር? የሚከተሉት ጥቅሶች እግዚአብሔር እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ይገልጻሉ ፦

  • ? ”እርሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነ አምላክ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘለዓለም ክብር ይሁን አሜን፡፡” (ሮሜ 16:27) ይህ ጥቅስ “እርሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነ አምላክ” ይላል ጥበበኛው የኢየሱስ አምላክ ብቻ ከሆነ ኢየሱስ ምን ሊባል ነው?

እግዚአብሔር አብ ብቻ ጥበበኛ አምላክ ከሆነ ኢየሱስ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው፡- “ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው (1ቆሮንቶስ 1፡24)፡፡ እግዚአብሔር አብ ጥበብ አልባ የነበረበት ጊዜ ባለመኖሩ ኢየሱስን ከእርሱ ልንነጥል አንችልም፡፡

  • ? “እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም፡፡” (ኤርምያስ 10፡10)

ይህ ጥቅስ ከሥላሴ አካላት መካከል አንዱ የሆነውንና እውነተኛ አምላክ የሆነውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያገለለ ስለመሆኑ ጠያቂው ማስረጃ አላቀረቡም፡፡ ከዚህ በተፃራሪ ጌታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እውነተኛ አምላክ ተብሎ ተጠርቷል፡- “የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው” (1ዮሐንስ 5፡20)፡፡

  • ? ኢየሱስ እንዲህ ይላል“እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘለዓለም ሕይወት ናት” (የዮሐንስ ወንጌል 17:3)፡፡ ታድያ ኢየሱስ አምላክ ከሆነ ለአምላኩ ሲፀልይ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ያውቁ ዘንድ ይህች የዘለዓለም ሕይወት ናት፡፡” ለምን አለ? ኢየሱስ እውነተኛው አምላክ ራሱ ሳይሆን የላከው አምላክ መሆኑን እንዴት ገለፀ?

ሙስሊም ሰባኪያን የኢየሱስን አምላክነት በማወጅ ከሚጀምረው መጽሐፍ፣ ከዮሐንስ ወንጌል ውስጥ አምላክነቱን የሚፃረር ሐሳብ መፈለጋቸው በእጅጉ የሚያስገርም ነው፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ኢየሱስ የዘለዓለም ሕይወት የሚገኘው እርሱንና አብን በማወቅ መሆኑን “ካይ”[2] የሚለውን የግሪክ መስተፃምር በመጠቀም ከአብ ጋር ያለውን እኩልነት ግልፅ አድርጓል፡፡ አንድ ሰው የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ፈጣሪና ፍጡርን አንድ ላይ ደምሮ ማወቅ አለበት የሚል ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም፡፡ እስልምናም ቢሆን እንደርሱ አያስተምርም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ምዕራፉን በሙሉ ስናነብ ጌታችን ስለ ራሱ የተናገራቸው ብዙ ነገሮች አምላክነቱን የሚያሳዩና ለጠያቂው የተሳሳተ ትርጓሜ ችግር የሚፈጥሩ ናቸው፡-

  • ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው (The Son, not a son) (ቁ.1-2)፡፡
  • የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣል (ቁ.1-2)፡፡ (ከአምላክ በስተቀር የዘለዓለምን ሕይወት መስጠት የሚችል ማን ሊሆን ይችላል? እግዚአብሔርስ ይህንን ችሎታ ለፍጡራን ያጋራልን?)
  • ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በክብር ከአብ ጋር ነበር (ቁ.5)፡፡
  • አብ እንዲያከብረው ጠይቋል (ቁ.1-2)፡፡ ፍጡር እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የማቅረብ መብት አለውን?
  • የአብ የሆነው ሁሉ የእርሱ መሆኑን ተናግሯል (ቁ.10)፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር በድፍረት መናገር የሚችል ከፍጡራን መካከል ሊገኝ ይችላልን?

አሕመዲን ጀበል ይህ ሁሉ የኢየሱስን አምላክነት የሚያሳይ ሐሳብ ከሞላበት ምዕራፍ ውስጥ አንድ ጥቅስ ነጥለው በማውጣት በራሳቸው የነጠላ አሃዳዊነት መነፅር በመመልከት የኢየሱስን አምላክነት ለመካድ ይሞክራሉ፡፡ የሚመቸንን ብቻ በራሳችን መንገድ በመተርጎም የማይመቸንን መጣል ህሊና ቢስነት መሆኑን እያስገነዘብን ይህ ጥቅስ ኢየሱስ አምላክ አለመሆኑን ለማሳየት ፈፅሞ ሊጠቀስ የማይችልባቸውን አምስት ምክንያቶች እንደሚከተለው እናስቀምጣለን፡-

  • በክርስትና አስተምህሮ መሠረት በሥላሴነት የሚኖረው አንዱ አምላክ ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ነው፡፡ የአጠቃላዩ ገንዘብ (General Property) የእያንዳንዱ ገንዘብ (Particular Property) በመሆኑ የብቸኛው ግፃዌ መለኮት ተካፋይ የሆነ እያንዳንዱ የሥሉስ አካል ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡ ይህ እርስ በርሱ እንደማይጣረስ ለመረዳት መሠረታዊ የሥነ አመክንዮ ዕውቀት በቂ ነው፡፡
  • ኢየሱስ በአካል ከአብ ልዩ ቢሆንም የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ቃል (ሎጎስ) ስለሆነ በመለኮት ከአብ የተነጠለ ባለመሆኑ ምክንያት አብ ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ከሆነ የአብ ዘለዓለማዊ ቃል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ነው (ዮሐንስ 1፡1)፡፡
  • ኢየሱስ ክርስቶስ አብን ብቸኛ እውነተኛ አምላክ እያለ ያለው ከሌሎች አማልክት አንፃር እንጂ በመለኮት ከእርሱ ጋር አንድ ከሆነው ከራሱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በማነፃፀር አይደለም፡፡
  • ይህ ሐሳብ የተነገረው ሥጋ በመሆን ወደ ምድር ከመጣው ከወልድ ዕይታ (Perspective) አኳያ እንጂ ከሌሎች ሰዎች ዕይታ አኳያ አይደለም፡፡
  • ወልድም “ብቸኛ” ተብሎ የተጠራባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይህ የቋንቋ አጠቃቀም ሌሎች የሥላሴ አካላትን ለማግለል የታለመ አለመሆኑን ግልፅ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ፡-“ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ” (ይሁዳ 1፡4)፡፡

የጠያቂውን ሙግት ከተቀበልን ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ብቻውን ያለ ንጉሥና ጌታ እንደሆነ በመነገሩ ምክንያት አብ ጌታ አይደለም ልንል ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊያን ከጠያቂው በተፃራሪ እንዲህ ዓይነቱ የቋንቋ አጠቃቀም ከእግዚአብሔር ማንነት አኳያ ችግር ሊፈጥር እንደማይችል ተገንዝበዋል፡፡ ጠያቂው የነጠላ አሃዳዊነት መነፅራቸውን ማውለቅ እስካልቻሉ ድረስ ይህንን ግንዛቤ ሊያገኙ አይችሉም፡፡

6. አምላክ አምላክ አለውን? ከላይ በጠቀስናቸው የክርስትና ሃይማኖት አስተምሮዎች ውስጥ ቀጥተኛና ግልፅ በሆነ መልኩ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን አላስተማረም፡፡ ለዚያም ነው በክርስቶስ አምላክነት ዙርያ የማይነጥፉ ጥያቄዎች የሚነሱት፡፡

ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በግልፅ እና በማያሻማ ሁኔታ አስተምሯል፡፡[3] ይህ ባይሆን ኖሮ ሐዋርያቱ አምላክነቱን ተቀብለው ባላመለኩት ነበር፡፡ አሕመዲን ግን የሰው ልጅ የማይከራከርበት እና የማይለያይበት አንድም እውነታ እንደሌለ መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በጣም ግልፅ ሊባሉ የሚችሉ ነገር ግን ሙስሊሞች በተለያዩ አንጃዎች በመከፋፈል እርስ በርሳቸው የሚከራከሩባቸውና የሚፋለሙባቸው አስተምህሮዎች አሉ፡፡ አሕመዲን የሚከተሉት የሰለፊ (ወሃቢ) ጎራ አላህ እንደ ሰው እጅ፣ እግር፣ ዓይን፣ አፍንጫ፣ ወዘተ. ያለው አምላክ መሆኑን ያስተምራል፡፡ ሌሎች ሙስሊሞች ደግሞ አላህ በዚህ መልኩ ሊገለፅ የማይችል ረቂቅ መሆኑን ያምናሉ፡፡ በቁርኣን ውስጥ እጅግ ግልፅ ከሚባሉት ትምህርቶች መካከል አንዱ የሙሐመድ የመጨረሻ ነቢይነት ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን የሚክዱ፣ ጥቅሱን በተለየ መንገድ የሚተረጉሙ አሕመዲያ በመባል የሚታወቁ ሙስሊሞች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ትምህርታቸው የተነሳም በሌሎች ሙስሊሞች ከፍተኛ ስደት ይደርስባቸዋል፡፡ ዒሳ እንዳልተሰቀለና ወደ ሰማይ እንደተወሰደ ቁርኣን እንደሚናገር በሱኒ ሙስሊሞች ዘንድ በፅኑ ቢታመንም የአሕመዲያ ሙስሊሞች መሰቀሉን ነገር ግን በመስቀል ላይ አለመሞቱን ያስተምራሉ፡፡ ብዙ ሙስሊሞች ቁርኣን ዘለዓለማዊ የአላህ ቃል መሆኑን የሚያምኑ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ በጊዜ ውስጥ የተፈጠረ ቃል መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይህ ርዕስ ሙስሊሞችን በመከፋፈል ለክፍለ ዘመናት ሲያገዳድላቸው ኖሯል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የቁርኣንንና የሐዲሳትን ግልፅነት ቢጠየቁ አሕመዲን በአዎንታ እንደሚመልሱ ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን “ግልፅ” የተባሉት ጉዳዮች ሙስሊሞችን ለክፍፍልና እርስ በርስ ለመገዳደል ዳርገዋል፡፡ ግልፅ በሆኑት ጉዳዮች ላይ መለያየት የሰው ልጆች ባሕርይ በመሆኑ በግልፅ የተቀመጠውን የኢየሱስን አምላክነት የሚክዱ ግለሰቦችና ቡድኖች መገኘታቸው ሊያስደንቀን አይገባም፡፡

አሕመዲን ይቀጥላሉ፡- እስቲ አሁን ደግሞ የሚከተሉትን ማገናዘቢያዎች ከስሜታዊንት በፀዳ መልኩ ለማስተዋል እንሞክር፡፡ ኢየሱስ አምላክ እንዳለው በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ ተገልጿል ፦

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” (1ኛ ጴጥሮስ1:3)

ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም፤ የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ፡፡ (ወደ ኤፌሶን 1:16-17)

ለወደደንና ከኃጢአታችን በደሙ ነፃ ላወጣን፣ አምላኩንና አባቱን እንድናገለግል መንግስትና ካህን ላደረገን ለእርሱ ክብርና ኃይል ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን አሜን” (የዮሐንስ ራእይ 1:6)፡፡

(ከነዚህ ጥቅሶች በተጨማሪ ጸሐፊው 2ቆሮንቶስ 11፡31፣ ሮሜ 15:5-6፣ ኤፌሶን 1:3፣ ማርቆስ 12:29፣ ዮሐንስ 20:17፣ ማርቆስ 15:34፣ ማቴዎስ 27:46 እና 2ቆሮንቶስ 1:3 ጠቅሰዋል፡፡)

ኢየሱስ አምላክ እያለው እንዴት ራሱ አምላክ ይሆናል? አምላክ ሌላ አምላክ አለው? ክርስትያኖች የሚያመልኩት አምላክ እራሱ አምላክ አለው ማለት ነውን?

በክርስትና ትምህርት መሠረት ኢየሱስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑን ቀደም ሲል ገልፀናል፡፡ ፍፁም ሰው እንደመሆኑ አብ አምላኩ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ፍፁም አምላክ እንደመሆኑ ደግሞ ከአብ ጋር እኩል ነው፡፡ ኢየሱስ በሰውነቱ አምላክ የለሽ (Atheist) አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላም እንደምንመለከተው ብዙዎቹ ጥያቄዎች ይህንን እውነታ ካለመረዳት የመነጩ መሆናቸውን እናስተውላለን፡፡

7. አምላክ አንድ ብቻ ከሆነ ኢየሱስ እንዴት አምላክ ሊሆን ይችላል? በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ አምላክ አንድ ብቻ መሆኑ ተገልጿል፦ ሮሜ 3:30፣ 1ኛ ጢሞቴዎስ 2:5፣ ማርቆስ 12:32፣ ያዕቆብ 2:19፣ ሚልኪያስ 2:10፣ 1ቆሮንቶስ 8:6፣ ኤፌሶን 4:5-7 እና ዘዳግም 6:4-5፡፡ አምላክ አንድ ብቻ መሆኑን ከተስማማን በኋላም ግን ክርስቲያኖች ኢየሱስ አምላክ ነው ይላሉ፡፡ ለምንድን ነው ታድያ በ1ኛ ቆሮንቶስ 8:6 ላይ “አንድ አምላክ” የተባለው ኢየሱስ ሳይሆን አብ የሆነው? ታድያ ብቸኛው አምላክ አብ ከሆነ የኢየሱስ አምላክነት ምኑ ላይ ነው?

አሁንም ጸሐፊው በራሳቸው ንፅረተ ዓለም የነጠላ አሃዳዊነት መነፅር ነው ጥቅሶችን እየተረጎሙ የሚገኙት፡፡ ክርስቲያኖች በአንድ አምላክ ነው የሚያምኑት፡፡ የሥላሴ ትምህርት ልብ አምላክ አንድ ነው የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አምላክ ሦስት አካላት አሉት፡፡ ሦስቱም የሥላሴ አካላት ብቸኛ አምላክ ተብለው መጠራታቸው ከሥላሴ ትንተና ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ለመረዳት ለጥያቄ ቁጥር 5 የተሰጠውን መልስ ይመልከቱ፡፡ እስኪ ጸሐፊው የጠቀሱት 1ቆሮንቶስ 8፡6 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ሐሳባቸውን ይደግፍ እንደሆን እንመልከት፡፡ ጥቅሱ እንዲህ ይነበባል፡- “ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን፡፡”

የጥቅሱ ሁለተኛ አጋማሽ የሁሉ ፈጣሪ የሆነ አንድ ጌታ ኢየሱስ መሆኑን ይናገራል፡፡ አብ አንድ አምላክ ስለተባለ ኢየሱስ አምላክ አይደለም ከተባለ በተመሳሳይ መንገድ ኢየሱስ የሁሉ ፈጣሪ አንድ ጌታ ስለተባለ አብ የሁሉ ፈጣሪና ጌታ አይደለም ሊባል ነውን? በፍፁም! ሐዋርያው ጳውሎስ አብንም ሆነ ወልድን አንድ አምላክ አንድ ጌታ ብሎ መጥራቱ የአንዱ ግፃዌ መለኮት አካላት መሆናቸውንና የተነጣጠሉ አለመሆናቸውን መረዳቱን ያመለክታል፡፡ ከዚህም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ዘዳግም 6፡4 ላይ የሚገኘውን የአይሁድ ሼማ በሥላሴ አስተምህሮ መሠረት በመተርጎም ማቅረቡን የለዘብተኛ ሥነ መለኮት ምሑራን ሳይቀሩ ይስማሙበታል፡፡[4] “እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፡፡” “Hear, O Israel: The Lord our God is one Lord.” ይህ የሚያመለክተው አብ እና ወልድ የተለያዩ ሁለት አማልክት ወይም አንዱ ፈጣሪ አንዱ ፍጡር ሳይሆኑ የአንዱ ግፃዌ መለኮት (Godhead) አካላት መሆናቸውን ነው፡፡

8. አምላክ የማይሞት መሆኑ በ1ኛ ጢሞቴዎስ 1:17፣ ሮሜ 1:21-23፣ ሮሜ 1:25 እና 1ኛ ጢሞቴዎስ 6:16 ላይ ተገልጿል፡፡ ኢየሱስ ሟች ነው፤ አምላክ የማይሞት ከሆነ ኢየሱስ ሟች መሆኑ አምላክ አለመሆኑን አያሳይምን? ኢየሱስ ሲሞት “ሰውነቱ” ነው ወይስ “አምላክነቱ” ነው የሞተው? በሰውነቱ ከሞተስ እንዴት ሰው የዓለምን ኃጢአት ሊሸከም ይችላል? የአምላክ ወደ ምድር መምጣት ያስፈለገው ሰው ሊሸከመው ስለማይችል ነው ብለው ክርስትያኖች ያምኑ የለም? አቋሞን በማስረጃ ቢያስደግፉ?

ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የሞትን ትርጉም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት በአዳም ኃጢኣት ምክንያት የመጡ ሁለት ዓይነት ሞቶች አሉ፡፡ የመጀመርያው ሞት የመንፈስ ሞት ነው፡፡ የመንፈስ ሞት ማለት በኃጢኣት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ነው (ዘፍጥረት 2፡15-17፣ 3፡22-24፣ ኢሳይያስ 59፡2፣ ዕንባቆም 1፡13፣ ኤፌሶን 2፡1-5)፡፡ ሁለተኛው የሞት ዓይነት ደግሞ አካላዊ ሞት ነው፡፡ አካላዊ ሞት የነፍስ ከሥጋ መለየት እንጂ የህልውና ማክተም አይደለም (ዕብራውያን 12፡22-24፣ ያዕቆብ 2፡26፣ ራዕይ 6፡9-11)፡፡ ጠያቂው “ሞት” የሚለውን ቃል የህልውና ማክተም አድርገው የተረጎሙት ይመስላል፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሁለቱም የሞት ዓይነቶች የህልውና ማክተምን ስለማያስከትሉ ጠያቂያችን እየተናገሩ ባሉበት መንገድ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልሞተም (ህልውናው አላከተመም)፡፡ ኢየሱስ መለኮት እንደመሆኑ መጠን ህልውናው ሊያከትም አይችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ኢ-ሟቲነት ሲናገር ከዚህ አኳያ ነው፡፡ ሌሎች ፍጥረታት በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ቢሆን እንጂ ህልውናቸው ሊጠፋ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሞት ማለት የህልውና ማክተም ተደርጎ እስካልተተረጎመ ድረስ የኢየሱስ መሞት እግዚአብሔር ኢ-ሟቲ መሆኑን ከሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር አይጣረስም፡፡ ምክንያቱም የኢየሱስ መለኮታዊ ባሕርይ መኖር ያቆመበት ጊዜ አልነበረምና፡፡

የሰው ልጆች ሁሉ ኃጢአተኞች በመሆናቸው ምክንያት የሌላውን ኃጢአት የመሸከም ብቃት የላቸውም፡፡ ኢየሱስ ግን ንፁህና ኃጢአት አልባ በመሆኑ የሌሎችን ኃጢአት የመሸከም ብቃት አለው፡፡ አምላክ በተሠግዎ ወደ ምድር መምጣት ያስፈለገበት ምክንያት ፍፁም የሆነና ከኃጢአት የራቀ ሰው በመታጣቱ ነው (ኢሳይያስ 59፡13-17)፡፡ ኢየሱስ ኃጢአታችንን የተሸከመው በክቡር ሥጋው ነው (1ጴጥሮስ 2፡24)፡፡ ኃጢአታችንን ያስተሰረየው ደግሞ ቅዱስ ደሙን በማፍሰስ ነው (ሮሜ 3፡25፣ 5፡9፣ ኤፌሶን 1፡7፣ ራዕይ 1፡4-5፣ 1ጴጥሮስ 1፡18-19፣ ዕብራውያን 9፡22)፡፡ ይህ ሥጋና ደም የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ የማንነቱ አካል በመሆኑ ኃጢአታችንን የመሸከም ብቃት አለው፡፡

9. የሐዋርያት ሥራ 10:38እግዚአብሔር የናዝሬቱ ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስና በኃይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ስልጣን ስር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ፡፡” ይላል በመጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በአንድም ስፍራ ላይ “እግዚአብሔር” ባይባልም ክርስቲያኖች “ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው” ይላሉ፡፡

አሕመዲን ግልፅ ቅጥፈት ስለፈፀሙ እዚህ ጋ እናስቁማቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በአንድም ስፍራ ላይ “እግዚአብሔር” አልተባለም ብለዋል፡፡ ኢየሱስ እግዚአብሔር የተባለበትን አንድ ጥቅስ እናሳያቸው፡- “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ… ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን” (ዮሐንስ 1፡1፣ 14)፡፡ ስለዚህ ጠያቂው በመጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በአንድም ስፍራ ላይ “እግዚአብሔር” አልተባለም ማለታቸው አንባቢያንን ለማሳሳት ሆነ ብለው የዋሹት ውሸት ነው አለበለዚያም ደግሞ ባለማወቅ የተናገሩት ነው፡፡ ሆነ ብለው ከዋሹ መንፈሳዊ ትምህርት የማስተማር የሞራል ብቃት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ባለማወቅ ከተናገሩ ደግሞ ይህንን ቀላል እውነታ ማወቅ የተሳነው ሰው ጥልቅ የሆኑ ሥነ መለኮታዊ ጉዳዮችን ለመወያየትም ሆነ ክርስትናን ለመተቸት የሚያስችል ብቃት ሊኖረው አይችልም፡፡

  • ? እርሱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለነበረ” በሚለው ጥቅስ “እርሱም” እና “እርሱ” የሚሉት ቃላት ኢየሱስን ለመግለጽ በጥቅሱ ውስጥ ስለተገለፁ እንዲሁም ክርስቲያኖች ኢየሱስን “እግዚአብሔር ወልድ” ስለሚሉት ቃላቶቹን በእግዚአብሔርም” ብንተካው “እግዚአብሔርም (እርሱም) እግዚአብሔር (ከእርሱ) ጋር ስለነበረ ይሆናል፡፡ ስንት እግዚአብሔር ሆኑ? ክርስትያኖች ሦስት የሆኑትን “አንድ” ቢሉ እውን ሦስትነታቸውን ትተው አንድ ይሆናሉን? በዚህ ጥቅስ ”እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን በኃይል ቀባው ” የሚለውን ብናጤን ፣ እግዚአብሔር (አብ) ፣ ኢየሱስ (እርሱንም ክርስቲያኖች “እግዝአብሔር ነው “ይላሉ፡፡) እና መንፈስ ቅዱስ (እንደሚሉት እርሱም ከሥላሴዎች አንዱና ራሱም እግዚአብሔር ነው፡፡) ይህ ማለት ከሦስቱ ሥላሴዎች እና ራሳቸውም እግዚአብሔር ከሆኑት ፣ አንደኛው እግዚአብሔር ሁለተኛውን እግዚአብሔርን በሦስተኛው እግዚአብሔር ቀባው ማለት ነው፡፡ ይህ ትክክለኛ እሳቤ ነው ብለው አእምሮዎን ማሳመን ይችላሉን?

ጠያቂው መልሰው መላልሰው የሥላሴን አስተምህሮ በመዘንጋት እግዚአብሔር በመለኮትም በአካልም ነጠላ መሆኑን እንደ ቅድመ ግንዛቤ በመያዝ ይሞግታሉ፡፡ በሥላሴ አስተምህሮ መሠረት አንድ አምላክ ብቻ ነው ያለው፡፡ የአንዱ አምላክ ሦስቱ አካላት እያንዳንዳቸው አምላክ ተብለው ቢጠሩም ነገር ግን አንዱን ግፃዌ መለኮት የሚካፈሉ ሦስት አካላት እንጂ የሦስት መለኮታት ድምር ባለመሆናቸው ሦስት አማልክት ወይም ሦስት እግዚአብሔሮች አይደሉም፡፡ ጸሐፊው ለዚህ የክርስትና ትምህርት ጆሯቸውን ባይደፍኑና እስላማዊ አስተምህሯቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመጫን ባይሞክሩ ኖሮ ባልተደናገሩ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አገልግሎቱን ይፈፅም የነበረው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነበር፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ “ክርስቶስ” የሚለው ማዕርግ ትርጉም አልባ ይሆን ነበር፡፡ “ክርስቶስ” ወይም “መሲህ” ማለት የተቀባ ማለት ሲሆን የኢየሱስን ንግሥና፣ ክህነት እና ነቢያዊ አገልግሎት የሚገልፅ ነው፡፡ ክርስቶስ በምድር ላይ እንደ አገልጋይ በነበረበት ጊዜ መሲሃዊ አገልግሎቱን ይፈፅም ስለነበር በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተቀብቷል፡፡ ጸሐፊው ምክንያታዊ ሙግት ከማቅረብ ይልቅ የቃላት ጫወታ በመጫወት የአንባቢያኑን ስሜታዊ ውሳኔ መጠየቃቸው የረባ ቁምነገር ያዘለ አይደለም፡፡

10. ማርቆስ 13፡32 ላይ “ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ከአብ በቀር ፣ የሰማይ መላእክትም ፣ወልድም ቢሆን ፣ ማንም አያውቅም” እንደተባለው ስለ ትንሣኤ ኢየሱስንም ጨምሮ ማንም ከአብ በቀር የሚያውቅ እንደሌለ ተገልጿል፡፡ ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ ከአብ እኩል ከሆነ እንዴት የትንሣኤን ጊዜ ማወቅ ተሳነው? አንዱ አምላክ አውቆ ሌላኛው “አምላክ ” ሳያውቅ እንዴት ቀረ? ኢየሱስ ሁሉንም የማያውቅ ከሆነ እንዴት አምላክ ነው ልንል እንደፍራለን? አንዳንድ ክርስቲያኖች “ወልድ ሰው ስለሆነ ነው የማያውቀው ” ይላሉ፡፡ ግና ሰው ብቻ ነውን? ኢየሱስ ወደ ምድር ሳይመጣ በፊትና ወደ ሰማይ ካረገ በኃላ “ወልድ ” አይባልምን ታድያ ጥቅሱ “ወልድም ቢሆን” እንጂ “ምድር ሳለ፣ ስጋ በለበሰ ጊዜ” አይል?

ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት እስኪ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሁሉን አዋቂነት የሚናገረውን እንመልከት፡-

ሁሉን እንድታውቅ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን አሉት፡፡ ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ አሁን ታምናላችሁን?” ዮሐንስ 16፡30-31

“ሦስተኛ፦ ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው፡፡ ኢየሱስም፦ በጎቼን አሰማራ፡፡” ዮሐንስ 21፡17

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ልብ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ይናገራል (1ነገሥት 8፡39)፡፡ የሰዎችን ልብና ኩላሊት በመመርመር እንደየሥራቸው መስጠት የእግዚአብሔር ሥልጣን መሆኑን ያስገነዝባል፡-  እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ፡፡” (ኤርምያስ 17፡10)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያንን የሚያደርገው እርሱ መሆኑን ተናግሯል፡-

“አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ፡፡” ራዕይ 2፡23፡፡ (በተጨማሪም ማቴዎስ 9፡3-4፣ ሉቃስ 9፡46-47፣ ዮሐንስ 6፡60-66፣ 1ቆሮንቶስ 4፡5፣ ማርቆስ 2፡5-12)፡፡

ታድያ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎች ብዙ ቦታዎች ኢየሱስ መለኮታዊ ዕውቀት እንዳለው ቅዱሱ መጽሐፍ ካረጋገጠ ስለ ምፅዓቱ እንደማያውቅ ስለምን ተነገረ? ደጋግመን እንደገለፅነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም አምላክ የመሆኑን ያህል ፍፁም ሰው ነው፡፡ በሰውነቱ በጊዜና በቦታ የተገደበ እንደነበረ ሁሉ እውቀቱም የተገደበ ነበር፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮ ፍፁም ሰው ሊሆን ባልቻለም ነበር፡፡ ነገር ግን በመለኮቱ ዘለዓለማዊ፣ ሙሉዕ በኩላሄና አእማሬ ኩሉ ነው፡፡  ይህንን ምላሽ ጸሐፊው ጥቅሱ ወልድ ስለሚልና ሥጋ በለበሰ ጊዜ ስለማይል እንደማያስኬድ ለመሞገት ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን ወልድ የሚለው ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ የሆነውን አንዱን ኢየሱስን ስለሚያመለክት መጽሐፍ ቅዱስ የተገደበውን የወልድን ገፅታ ሲነግረን ስለ ሰብኣዊ ባሕርዩ እየተናገረ እንዳለ ሊገባን ያስፈልጋል፡፡ የተገደበ መሆኑን መናገሩ ብቻ ሰብኣዊ ባሕርዩን የተመለከተ መሆኑን ግልፅ ስለሚያደርግ ሌላ ማብራርያ መጨመር አያሻም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በቅን ልብ እውነትን ለሚፈልጉ ሰዎች እንጂ እንደ አሕመዲን ፀጉር ለሚሰነጥቁ ሐያሲያን አይደለም፡፡

11. ቁጥር 5 ላይ የተመለሰውን ጥያቄ ስለደገሙ ታልፏል፡፡

12. ክርስቲያኖች “ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር ማለት ስለሚችል አምላክ ነው” ይላሉ፡፡” በዮሐንስ 20፡23 ላይ “ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ“ኃጢያታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው፡፡” ይላል ታዲያ በዚህኛው ጥቅስ ላይ ደቀመዛሙርቱ ኃጢያትን ይቅር ማለት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱንም አምላክ ልንላቸው ይሆን?” አይደለም! ለደቀ መዛሙርቱ ይህን ስልጣን የሰጠው ኢየሱስ ነው! ” ሊሉ ይችላሉ፡፡ ግን ይህንን ጥቅስ አላነበቡምን? “ኢየሱስም ደቀመዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ እንዲህ አላቸው ፤ ”ስልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤” ይላል (ማቴዎስ 28፡18)፡፡ ስልጣን የራሱ ቢሆን ኖሮ ግን “ስልጣን ተሰጠኝ” ሳይሆን “ስልጣን አለኝ ” ነበር የሚለው ስለዚህ ለኢየሱስ ስልጣን የሰጠው አምላክ መሆኑን እንረዳለን፡፡

ከአምላክ በስተቀር ማንም ኃጢኣትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንደሌለው እስልምናም ሆነ ክርስትና ይስማሙበታል፡፡ ስለዚህ አሕመዲን የሐዋርያት ኃጢኣትን ይቅር የማለት ችሎታ ማግኘት ከእምነታቸው ጋር የሚጣረስ በመሆኑ ሐሳቡን ከመቃወም ይልቅ ጥቅሱን በመጠቀም የኢየሱስን አምላክነት መሞገት አልነበረባቸውም፡፡ ከዚህ የምንረዳው አንድ ነገር ቢኖር አሕመዲን የኢየሱስን አምላክነት አጠራጣሪ ለማድረግ ያላቸው ጉጉት በራሳቸው እምነት መሠረት ክህደት የሆነውን ጉዳይ እንዲደግፉ እንዳደረጋቸው ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ጥቅስ ሐዋርያት በገዛ ፍቃዳቸው “ይቅር ብለናችኋል!” በማለት ሰዎችን ከኃጢኣታቸው እንደሚያነፁ እንደሚናገር ማሰብ ስለ ኃጢኣት ይቅርታ ከሚናገረው አጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ የአሕመዲንን ሐሳብ የሚደግፍ አይደለም፡፡ ሐዋርያቱም ለአፍታ እንኳ ቢሆን እንዲህ ያለውን ሥልጣን ሲለማመዱም ሆነ ይህ ሥልጣን እንዳላቸው ሲናገሩ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ኃጢኣትን ይቅር እንዲሉ ሥልጣን እንደሰጣቸው የተነገረው ሐዋርያት እንደ እርሱ የኃጢኣት ይቅርታ ምንጭ መሆን እንደሚችሉ ለማመልከት ሳይሆን የኃጢኣት ይቅርታ ምክንያት የሆነውን የእርሱን ወንጌል በማስተማር ለሰዎች የኃጢኣትን ይቅርታ እንደሚያስገኙ ለማመልከት ነው (ሉቃስ 24፡45-48)፡፡ ጌታችን ሐዋርያት ወንጌልን ማስተማር ያለባቸው ለሚሰሟቸው ሰዎች መሆን እንዳለበት ነግሯቸዋል (ማቴዎስ 10፡14-15፣ ማርቆስ 6፡11፣ ሉቃስ 9፡5-6፣ 10፡11-12)፡፡ ስለዚህ በአንድ አካባቢ የሚደርስባቸውን ስደት ታግሶ በመቆየት የኃጢአት ይቅርታን የሚያስገኘውን ወንጌልን ማስተማር በሐዋርያት ፍላጎት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ወንጌልን በመስበክ የኃጢአት ይቅርታን ማስገኘትም ሆነ ለማይቀበሏቸው ሰዎች ባለመስበክ ኃጢአታቸው እንዳይሰረይ የማድረግ ሥልጣን አላቸው፡፡  ሐዋርያት ለመታከም ፈቃደኛ የሆኑ ህመምተኞችን በማከም እንደሚፈውሱ ዶክተሮች ሲሆኑ መድኃኒቱ ደግሞ ክርስቶስ ነው፡፡ ዶክተሮቹ መድኃኒቱን በመስጠት ይፈውሳሉ፡፡ መድኃኒቱ ከሌለ ግን ዶክተሮቹ መፈወስ አይችሉም፡፡ ዶክተሮቹ መድኃኒት በመስጠት መፈወሳቸው የፈውስ ምንጭ አያደርጋቸውም፡፡ የፈውሱ ምንጭ ዶክተሮቹ ሳይሆኑ መድኃኒቱ ነው፡፡ ሐዋርያት ኃጢኣትን ይቅር እንዲሉ፣ ማለትም የኃጢኣት ይቅርታ ምንጭ የሆነውን ክርስቶስን ለሰው ልጆች እንዲሰብኩ ሥልጣን የሰጣቸው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ ሥልጣኑ የገዛ ራሳቸው እንዳልሆነና የክርስቶስ ሥልጣን እንደሆነ ያሳያል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎችን የኃጢአት ይቅርታ በማወጅ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው በተደጋጋሚ አሳይቷል (ማርቆስ 2፡5-9፣ ሉቃስ 7፡46-49)፡፡ ይህ ደግሞ የፈጣሪ የብቻው ስልጣን ነው፡፡

ኢየሱስ ራሱ ሥልጣን እንደተሰጠው መናገሩ ይህ ሥልጣን የራሱ አለመሆኑንና አምላክ አለመሆኑን አያመለክትምን? ይህንን ጥያቄ የሚጠይቁ ሰዎች እግዚአብሔር አንድ አካል ብቻ እንዳለው ቅድመ ግንዛቤ የያዙ ናቸው፡፡ የሥሉስ አካላት አንዳቸው ከሌላቸው የመቀበላቸውና አንዳቸው ለሌላቸው የመገዛታቸው እውነታ መታየት ያለበት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የአንዱ ግፃዌ መለኮት አካላት መሆናቸውን በሚናገረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ መሠረት እንጂ በነጠላ አሃዳዊነት መሠረት መሆን የለበትም፡፡ ጸሐፊው ግን ከሞላ ጎደል በእያንዳንዱ ጥያቄያቸው ውስጥ ይህንን መሠረታዊ ሃቅ በመዘንጋት የራሳቸውን ቁርአናዊ እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ይስተዋላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ከአብ እንደሚቀበል ብቻ ሳይሆን ለአብ እንደሚሰጥም ጭምር ይናገራል፡- “በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል” (1ቆሮንቶስ 15፡24)፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በመለኮት አንድ ቢሆንም በአካል ግን ሦስት በመሆኑ አንዱ የሥላሴ አካል ከሌላው መቀበሉ ከአንዱ ግፃዌ መለኮት ውጪ ከሚገኝ ሌላ አካል እስካልተቀበለ ድረስ አምላክነቱን ሊያጠራጥር አይችልም፡፡ ሌላው መረሳት የሌለበት ነጥብ በባሕርዩ ፍፁም አምላክ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩን ጥሎ የባርያን መልክ በመያዝ ወደ ምድር መምጣቱ ነው (ዮሐንስ 6፡38፣ ማቴዎስ 20፡24-28፣ ፊልጵሲዩስ 2፡5-8)፡፡ ስለዚህ ተልዕኮውን ከፈፀመ በኋላ አብ አክብሮታል፡-

“በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው” (ፊልጵሲዩስ 2፡9-11)፡፡

በማቴዎስ 28፡18 ላይ የሚገኘውን ቃል በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ከተመለከትን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን ለአባቱ ታዞ በራሱ ፈቃድ ትቶት የመጣውንና መለኮታዊ መብቱ የሆነውን ሥልጣን መልሶ ተቀበለ እንጂ የእርሱ ያልሆነውን ስላልተቀበለ ይህ አባባል አምላክነቱን አጠራጣሪ ለማድረግ ምክንያት አይሆንም፡፡ በሦስተኛ ደረጃ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ከተሠግዎ በፊት ጌታችን ፍፁም አምላክ እንደነበረና ከተሠግዎ በኋላ ግን አምላካዊ ባሕርዩ ሳይለወጥ ፍፁም ሰው መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ክብሩ የተመለሰው ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ሆኖ ነው፡፡ የአባቱን ፈቃድ ያለ ምንም እንከን ከዳር በማድረሱ መለኮታዊ ባሕርዩ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ባሕርዩም ጭምር ክብርን ተቀዳጅቷል፡፡ ይህ ደግሞ በስሙ የሚያምኑት ቅዱሳን የርስቱ ወራሽ እና የግዛቱ ተካፋይ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው (ሉቃስ 22፡29-30፣ ዮሐንስ 17፡24፣ ሮሜ 8፡17፣ ራዕይ 2፡26-27፣ ራዕይ 3፡21)፡፡

አሕመዲን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣንን ከአብ መቀበሉን የሚናገረውን ቃል ብቻ ነጥለው ጠቀሱ እንጂ ሙሉ አውዱን ቢያነቡት ኖሮ የኢየሱስን አምላክነት አሻሚ ባልሆነ ሁኔታ በተመለከቱ ነበር፡፡ እስኪ በክፍሉ አውድ ውስጥ የሚገኙትን ደምቀው የተጸፉትን ቃላት ልብ ብለን እንመልከት፡-

“አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፥ ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ፡፡ ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ፡፡ እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴዎስ 28፡16-20)፡፡

በዚህ ቦታ ላይ ሐዋርያት ለኢየሱስ ሰግደዋል፡፡ የአሕመዲን ሃይማኖት አጥብቆ እንደሚያስተምረው ኢየሱስ ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ሌሎች ቅዱሳን ሰዎችና መላዕክት እንዳደረጉት ሐዋርያቱ እንዳይሰግዱለት በነገራቸው ነበር (የሐዋ. ሥራ 10፡25-26፣ ራዕይ 22፡8-9)፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ አንድም ጊዜ ያንን አድርጎ አያውቅም፡፡ ኢየሱስ በሰማይና በምድር ሥልጣን ሁሉ እንደተሰጠው ተናግሯል፡፡ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እና ወራሽ ባይሆን ኖሮ አብ እንዴት በሰማይና በምድር ሥልጣንን ሁሉ ይሰጠው ነበር? የጥምቀቱ ደግሞ ከሁሉም በላቀ ሁኔታ አምላክነቱን ይገልጣል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የእግዚአብሔር ስም ባሕርዩን ይወክላል (ዘፀአት 33፡17-23፣ 34፡5-7)፡፡ የእግዚአብሔርን ስም ማመስገን ማለት እግዚአብሔርን ማመስገን ማለት ነው (መዝሙር 7፡17)፡፡ የእግዚአብሔር ስም ረዳታችን እንደሆነ መናገር እግዚአብሔር ረዳታችን እንደሆነ መናገር ነው (መዝሙር 124፡8፣ 121፡2)፡፡ በእግዚአብሔር ስም መምጣት ማለት በእግዚአብሔር ኃይል መምጣት ማለት ነው (1ሳሙኤል 17፡45፣ ዮሐንስ 5፡43)፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርና ስሙ አይነጣጠሉም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀት የገዛ ስሙ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ እኩል እንዲጠቀስ በማዘዝ አንድ ስም እንዳላቸው ግልፅ አድርጓል፡፡ ይህም ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በባሕርይም ሆነ በአገዛዝ አንድ መሆኑን ያሳያል፡፡ ማንም ፍጡር እንዲህ ዓይነት ነገር ቢናገር በእውነተኛው አምላክ ላይ ክህደትን መፈፀም በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ አሁንም በዚሁ ስፍራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደሚሆን በመናገር በሁሉም ቦታ መገኘቱን አስታውቋል፡፡ በእርግጥ በሁሉ ቦታ መገኘት መቻሉን ሲናገር ይህ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም (ማቴዎስ 18፡20 ይመልከቱ)፡፡ ማንም ሰው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥልጣን ከአብ መቀበል በዚህ አውድ ውስጥ በማንበብ መረዳት ያስፈልገዋል እንጂ ከአውዱ ገንጥሎ በማውጣት የተለየ ትርጉም መስጠት የለበትም፡፡ አሕመዲን እና መሰሎቻቸው ይህንን ሐሳብ በደንብ መረዳት ይችሉ ዘንድ እስኪ በዚህ ጥቅስ ውስጥ በኢየሱስ ፋንታ ሙሐመድን እናስቀምጣቸውና ይቀበሉት እንደሆን እንይ፡-

“ከሰሃባዎች[5] መካከል አስራ አንዱ ግን ሙሐመድ ወዳዘዛቸው ተራራ ሄዱ፥ ባዩትም ጊዜ ለሙሐመድ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ፡፡ ሙሐመድም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ፡፡ እንግዲህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአላህ በሙሐመድ እና በጂብሪል[6] ስም እየገረዛችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው አስልሟቸው፤ እነሆም እኔ ሙሐመድ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡

ከላይ የሰፈረው ሐሳብ ከእስልምና አስተምህሮ ጋር በእጅጉ ስለሚጣረስ መቼም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱን አባባል የሚቀበል ሙስሊም አይኖርም፡፡ አሕመዲን ሦስት ምርጫ ብቻ ነው የሚኖራቸው፡፡ የኢየሱስን ንግግር በመቀበል አምላክ መሆኑን አምነው መጠመቅ፣ ኢየሱስ ተሳስቷል ብሎ በመደምደም ከእስልምናም ሆነ ከክርስትና ጋር መጣላት ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል የሚለውን ማስረጃ የሌለውንና ጊዜ ያለፈበትን መዝሙራቸውን እየዘመሩ በሃይማኖታቸው መፅናት፡፡

13. የጥያቄው የመጀመርያ ክፍል በቁጥር 7 ላይ መልስ የተሰጠበትን ሐሳብ የሚደግም በመሆኑ ታልፏል፡፡ የጥያቄው ቀጣይ ክፍል እንዲህ ይላል፡- ኢየሱስ “ጌታ” ስለተባለ አምላክ ሊባል ይቻላልን? እንዲህማ ከተባለ በመጽሐፍ ቅዱስ እነ ሙሴ (ዘኊልቁ 12፡11፣ ዘኊልቁ 11፡28) መላዕክት (ዘካርያስ 6፡4 ኢያሱ 5፡13-14)፣ ዮሴፍ (ዘፍጥረት 42፡33፣ ዘፍጥረት 45፣8-9)፣ ዳዊት (1ኛ መጽሐፍ ነገስት 1፡11-13፣ ኢዮአብ (2ኛ ሳሙኤል 11፡11)፣ ኤልያስ (1ኛ ነገስት 18 ፡7) እና ሳኦል (1ኛ ሳሙኤል 24፡8 ) “ጌታ” ተብለው የተጠሩትን ሁሉ “ጌታ” ስለ ተባሉ ለምን አምላክ አንላቸውም?

“ጌታ” መባል ብቻውን አምላክ እንደማያሰኝ ያስማማናል፡፡ ነገር ግን ቃሉ የተጠቀሰበት አውድ ወሳኝ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎችና መላእክት አምላክ ተብለው ሊጠሩ የማይችሉበት ምክንያት አውዱ ክቡራን ፍጥረታት እንጂ ፈጣሪ መሆናቸውን ስለማያሳይ ነው፡፡ አሕመዲን በዚህ ጥያቄያቸው የመጀመርያው ክፍል ላይ 1ቆሮንቶስ 8፡6 ላይ አብ “አምላክ” ተብሎ ኢየሱስ ግን “ጌታ” መባሉ ኢየሱስ እንደ አብ አምላክ አለመሆኑን እንደሚያሳይ ለመሟገት ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን ጥቅሱ ኢየሱስ ፈጣሪ መሆኑን እንደሚናገር አላስተዋሉም፡፡ እኛን ጨምሮ ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረው አካል አምላክ ካልተባለ ምን ሊባል ነው? ሐዋርያት ይህንን ስለተረዱ ነው ክርስቶስ አምላክ መሆኑን የመሰከሩት (ዮሐንስ 20፡27-29፣ ቲቶ 2፡12-13)፡፡

14. ኢየሱስ ተዓምር ሲያሳይ ተአምራቱን ያዩ ሰዎች ተደንቀዋል፡፡ በማቴዎስ 9፡8 ላይ “ሕዝቡም አይተው ተደነቁ፤ ለሰውም እንዲህ አለ ሥልጣን የሰጠ እግዚአብሔርን አከበሩ” ይላል፡፡ ታዲያ ይህን ተአምር ያየው ሕዝብ ሁሉ ከሃዲ ነውን? ለምን ቢሉ “ኢየሱስ አምላክ ስለሆነ በራሱ ስልጣን ተአምራቱን አደረገ” ብለው እንደ ዛሬዎቹ ክርስቲያኖች አላመኑም፡፡ “ለሰውም እንዲህ አለ ስልጣን የሰጠ እግዚአብሔርን አከበሩ” ይላል፡፡ ታዲያ ኢየሱስ አምላክ ቢሆንና በራሱ ስልጣን ቢኖረው ለምን እግዚአብሔር ይህን ተአምር እንደሰጠው ገለፀ? እግዚአብሔር የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የጋራ ጥምረት ከሆነና “እግዚአብሔር” የሚለው ኢየሱስን የሚጨምር ከሆነ ህዝቦቹ እግዚአብሔርን ሲያከብሩ ኢየሱስንንም ይጨምሩት ነበር፡፡ ነገር ግን “ሰው ነው” ብለው አመኑበት፡፡ ታድያ ያንን ሁሉ ታላላቅ ተአምራት ያየውንና ኢየሱስን የተከተለውን ህዝብ እምነት ትተን በተቃራኒ ማመን አግባብ ነውን?

ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ፍፁም ሰው ሆኖ የገዛ ፈቃዱን ሙሉ በሙሉ ለአብ በማስገዛት ከአብ በተቀበለው ሥልጣንና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይሰራ ስለነበር ሕዝቡ አልተሳሳተም፡፡ ሆኖም ሕዝቡ የኢየሱስን አምላክነት ተረድቷል ብሎ ማለት አይቻልም፡፡ ሕዝብ በወቅቱ ካየውና ቀደም ሲል ከነበረው ቅድመ ግንዛቤ በመነሳት የተሳሳቱ ድምዳሜዎች ላይ መድረስ መቻሉ መረሳት የለበትም፡፡ ስለዚህ በሕዝብ አስተያየት ላይ በመመስረት ነገረ መለኮታዊ አስተምህሮን መገንባት ፈፅሞ የተሳሳተ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ሕዝብ ጳውሎስና በርናባስ ተዓምራትን ሲያደርጉ በማየቱ ምክንያት “አማልክት በሰው ተመስለው ወርደዋል” በማለት ሊሰዋላቸው ተነስቶ ነበር (የሐዋ. ሥራ 14፡11)፡፡ ኢየሱስን የተቀበለው ያው ሕዝብ እንዲሰቀል ጲላጦስን ተማፅኗል፡፡ ሕዝብ አንዳንዴ እውነትን ቢናገርም ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ የተሳሳተ ነገር ይናገራል፡፡ ስለዚህ አስተምህሯችንን የምንመሰርተው በሕዝብ አስተያየት ላይ ሳይሆን ኢየሱስ ራሱ በተናገረውና በእርሱ የተመረጡት ሐዋርያት ባስተማሩት ትምህርት ላይ ነው፡፡ አሕመዲን ኢየሱስ ጌታ፣ አምላክና አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የመሰከሩትን የሐዋርያትን ምስክርነት ችላ በማለት ብዙ ጊዜ በመሳሳት የሚታወቀውን የሕዝቡን ምስክርነት ለመስማት መምረጣቸው ለምን ይሆን? (2ጴጥሮስ 1፡1-3፣ ዮሐንስ 1፡1-3፣ 1ዮሐንስ 5፡20፣ ዮሐንስ 20፡28-29)፡፡ ለሕዝብ አስተያየት ይህን ያህል ቦታ የሚሰጡ ከሆነ ነቢዩ ሙሐመድንና ከሊፋዎቹን ከመስማት ይልቅ እስልምናን ባለመቀበሉ ምክንያ በሰይፍ ስለት የታጨደውን ሌላውን ሕዝብ ለምን አልሰሙም?

15. ከኢየሱስ በፊት የነበሩት ነብያት አምላክ አንድ መሆኑን ፣ ብቸኛና ኃያል መሆኑን ሰብከዋል፤ ሕዝቡም ተቀብሎ አምኗል፡፡ ምእመናን ደግሞ አምላክ በትንሣኤ እለት ለፍርድ እንደሚመጣ ተምረው ተቀብለዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም አምላክ እግዚአብሔር እንደሚፈርድ በመዝሙር 75፥2 ላይ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- “ፍርዱ የሚሰጥበት ጊዜ ወስኛለሁ፤ በዚያን ጊዜ በቅንነት እፈርዳለሁ” እንዲሁም በመዝሙር 75፥7 ላይ ፡- “በአንዱ ላይ የሚፈርድ ሌላውን ነጻ የሚያወጣ ቅን ፈራጅ እግዚአብሔር ነው፡፡” ሲል ይገልጻል፡፡ ስለዚህ እርሱ እንደሚፈርድ አምነው ተቀብለውታል፡፡ በአዲስ ኪዳን ግን ኢየሱስ የተባለ “የአምላክ ልጅ” መኖሩንና እርሱም እንደሚፈርድ ወዘተ. ጳውሎስ አስተምሯል፡፡ ታዲያ ነገ በትንሣኤ ከኢየሱስ በፊት የነበሩት አማኞች የአምላክን ፍርድ ለማየት ሲጠባበቁ ዳኛው ሌላና ኢየሱስ የተባለ ሰው ሆኖ ሲያገኙት ምን ይመስላቸዋል? ያስተማሩዋቸውን ነብያት “ሐሰተኛ” ሊሉ ነውን? ኢየሱስ በማን አስተምሮት ነው የሚፈርድባቸው?

ጠያቂው የኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅነት እና ፈራጅነት ሐዋርያው ጳውሎስ ብቻ ያስተማረ በማስመሰል ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ልጅነቱንም ሆነ ፈራጅነቱን ኢየሱስ ራሱና ሌሎች ደቀ መዛሙርቱ በተደጋጋሚ በአፅንዖት አስተምረዋል (ስለ ልጅነቱ፡ ማቴዎስ 14፥33፣ 16፡16፣ 16፡27፣ 26፡63-64፣ 27፡43፣ ማርቆስ 1፡1፣ 9፡7-9፣ 12፡6፣ 14:61-62፣ 15፡39፣ ሉቃስ 1፡35፣ 4፡41፣ 8፡28፣ ዮሐንስ 1፡34፣ 1፡50፣ 3፡18፣ 5፡25፣ 6፡40፣ 6፡69፣ 10፡36፣ 11፡4፣ 11፡27፣ 17፡1-2፣ 19፡7፣ 20፡31፣ 1ዮሐንስ 3፡9፣ 4፣15፣ 5፡5፣ 5፡10-13፣ 5፡20፣ 2ዮሐንስ 1፡3፡፡ ስለ ፈራጅነቱ፡ ማቴዎስ 16፡27፣ 25፡31-32፣ ማርቆስ 16፡62፣ ዮሐንስ 5፡27)፡፡

መገለጥ ርምደታዊ (Progressive) እንደመሆኑ ከብሉይ ኪዳን ይልቅ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ራሱን በሙላት ገልጧል፡፡ በዘመነ ብሉይ የእግዚአብሔር ሥላሴነት ለቅዱሳን ነቢያት ግልፅ ቢሆንም ለአንድነቱ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ብሉይ ኪዳን ይበልጥ አጽንኦት በመስጠት የሚናገረው ስለ እግዚአብሔር አንድነት ቢሆንም በአንድነቱ ውስጥ ብዝኃነት መኖሩንም የሚናገሩ የተለያዩ ጥቅሶች አሉ፡፡ ለምሳሌ በእብራይስጥ ኤሎሂም የሚለው የእግዚአብሔር መጠርያ ነጠላ ቁጥርን ሳይሆን ብዙ ቁጥርን የሚያመለክት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ እግዚአብሔር አንድነት ከሚናገሩ ጥቅሶች ሁሉ ዋነኛው ዘዳ. 6፡4-5 ላይ የሚገኘው ሲሆን አይሁዶች ይህንን “ሼማ” በማለት ይጠሩታል፡፡ ይህ ጥቅስ በእብራይስጥ ቋንቋ ሲነበብ “ሼማ ይስራኤል ያሕዌ ኤሎሂኑ ያሕዌ ኢኻድ” ይላል፡፡ የእግዚአብሔርን አንድነት አፅንኦት በመስጠት የሚናገር ቢሆንም ነገር ግን በአንድነቱ ውስጥ ብዝኃነት መኖሩንም ይጠቁማል፡፡ እብራይስጥ “አንድ” ለሚለው ቃል “ያኽድ” እና “ኢኻድ” የሚሉ ሁለት ቃላት አሉት፡፡ “ያኽድ” ነጠላ አንድነትን የሚያመለክት ሲሆን “ኢኻድ” የሚለው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአመዛኙ የብዙ አንድነትን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የተጠቀሰው ቃል የብዙ አንድነትን የሚያመለክተው “ኢኻድ” የሚለው ቃል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የባልና የሚስትን አንድነት ለመግለፅ ይህንኑ ቃል ተጠቅሟል (ዘፍ. 2፡24)፡፡

  • የእግዚአብሔርን ሥላሴነት የሚናገሩ ጥቂት የማይባሉ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች አሉ (ዘፍ 1፡26፣ 3፡22፣ 11፡7፣ ኢሳ 6፡8)፡፡
  • አንዱ የእግዚአብሔር አካል ለሌላው ሲናገር በተለያዩ ትንቢታዊ ጥቅሶች ውስጥ እናያለን፡፡ ለምሳሌ፡- ኢሳ 48፡16፣ ዘካ 2፡7-11
  • የሥላሴን ጽንሰ ሐሳብ ለመረዳት የአዲስ ኪዳን እገዛ ያስፈልገናል ምክንያቱ ደግሞ ብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን ሙሉ ስለሚሆን ነው፡፡

አሕመዲን የጠቀሷቸው በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ የእግዚአብሔርን ፈራጅነት የሚናገሩ ጥቅሶች ከሥላሴ አካላት መካከል አብን ብቻ ለይተው እንደሚያመለክቱ ወይም ደግሞ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስን ያገለሉ ስለመሆናቸው ማስረጃ አልሰጡም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር” ሲል አንዱን ግፃዌ መለኮት ወይም ከሥላሴ አካላት መካከል አንዱን ሊያመለክት ይችላል፡፡ በተደጋጋሚ እንደታየው አሕመዲን እስላማዊ መነጽራቸው መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል እንዳይረዱ ደንቃራ ሆኖባቸዋል፡፡

16. የሉቃስ ወንጌል 2፡52 ላይ“ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ፡፡” ይላል፡፡ ኢየሱስ አምላክ ከሆነ እንዴት አምላክ በጥበብ ያድጋል? ከማደጉ በፊትስ? ፍፁም የሆነው አምላክ ሁሉን አዋቂ ነው፡፡ የቀድሞውንም፤ የአሁኑንም ሆነ የወደፊቱን ያውቃል ፡፡ ኢየሱስ ግን ከዚህ በኋላ ነው በጥበብ ያደገው፡፡ ታድያ እንዴት አምላክ ይሆናል?

በመለኮቱ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው፡፡ ስለዚህ በጥበብ ማደግ አያስፈልገውም (1ቆሮንቶስ 1፡24)፡፡ ይህ ጥቅስ ስለ ኢየሱስ ሰብዓዊ ባሕርይ እንጂ ስለ መለኮታዊ ባሕርዩ የሚናገር አይደለም፡፡ ኢየሱስ ፍፁም ሰው ስለነበረ የሰው አካልና የሰው አዕምሮ ነበረው፡፡ ስለዚህ በቁመት ማደግ እንዳስፈለገው ሁሉ በጥበብም ማደግ አስፈልጎታል፡፡

17. መጽሐፍ ቅዱስ (የ1980 እትም) በዕብራዊያን 5፡7-8 ላይ ስለ ኢየሱስ እንዲህ ተገልጿል፡- “እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤እግዚአብሔርንም ስለመፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ” ይላል፡፡ ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ “አምላክ” ከሆነ አምላክ እንዴት ከልምድ ይማራል? ጥቅሱ ይቀጥልና “እግዚአቢሔርንም ስለመፍራቱ ተሰማለት” ሲል ይገልጻል፡፡ ኢየሱስ እግዚአብሔር ከሆነ እግዚአብሔር ራሱን ይፈራልን? ኢየሱስ አምላክን እንደሚፈራ በዚህ ጥቅስ ተገልጿል፡፡ ታዲያ “ኢየሱስ አምላክ ነው” ከተባለ እንዲሁም “አምላክ አንድ ነው” ካልን ኢየሱስን የፈራው እራሱን ነው ማለት አይሆንምን? እንዴትስ አምላክ ራሱን ይፈራል? ወይስ ከሦስት አማልክ ውስጥ አንዱ ሌላኛውን ይፈራል?

ጠያቂው የጠቀሱትን ጥቅስ ትኩረት ሰጥተው ቢያነቡት ኖሮ ባልተደናገሩ ነበር፡፡ ጥቅሱ “እርሱም በሥጋው ወራት…” በማለት ነው የሚጀምረው፡፡ ስለ ኢየሱስ ሰብዓዊ ባሕርይ እንጂ ስለ መለኮታዊ ባሕርዩ እየተናገረ አይደለም፡፡ ጌታችን በምድር ላይ የኖረው ፍፁም ሰው በመሆን ስለነበር ለአብ በመገዛት ፍፁም ሰው የሆነ ሰብዕ ለአብ ሊሰጥ የሚገባውን ተገቢውን ክብር በመስጠት ነበር፡፡ ጠያቂው ደግመው ደጋግመው የሥላሴን አስተምህሮ በመዘንጋት ከራሳቸው የተሳሳተ ዕይታ አንፃር የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ትእግስትን የሚፈታተኑ ናቸው፡፡

18. እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ “ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው” አምላክ መሆኑ ተገልጿል፡፡ እነርሱም ፡- ሮሜ 10፡9፣ ገላቲያ1፡1፣ ኤፌሶን 1፡20-21፣ ቆላስይስ 2፡11-12፣ 1ኛ ጴጥሮስ 1፡21፣ የሐዋርያት ሥራ 2፡23-24፣ 3፡15፣ 10፡40፣ 13፡33-34፣ 3፡26፣ 4፡10፣ 13፡37፣ 6፡14 ናቸው፡፡ በቀረበው ማስረጃ “ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው” አምላክ ከሆነ ታድያ እንዴት “ኢየሱስ ሞትን ድል አደረገ “ይባላል? እንዴትስ “በሞት ላይ ስልጣን ስላለው ተነሳ” ልንል እንችላለን?

መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ትንሣኤ የሦስቱም የሥሉስ አካላት ተግባር እንደነበር ይናገራል፡፡ ጠያቂው በጥያቄያቸው ውስጥ በጠቀሷቸው ጥቅሶች መሠረት የአብ ተግባር መሆኑ ተነግሯል፡፡ የሚከተሉት ጥቅሶች ደግሞ የኢየሱስ ተግባር እንደነበር ይነግሩናል፡-

“ስለዚህ አይሁድ መልሰው፦ ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት፡፡ ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው፡፡ ስለዚህ አይሁድ፦ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት፡፡ እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር፡፡ ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ” (ዮሐንስ 2፡18-22)፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ ኢየሱስ አይሁድ ቢገድሉት በሦስት ቀን ውስጥ መልሶ ራሱን እንደሚያስነሳ ተምሌታዊ በሆነ መንገድ እየነገራቸው ነው፡፡

“ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ” (ዮሐንስ 10፡17-18)፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ ኢየሱስ በገዛ ፍቃዱ እንደሚሞትና ራሱን በራሱ እንደሚያስነሳ፤ የመሞትም ሆነ የመነሳት ሥልጣን የእርሱ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ሌሎች ጥቅሶች ደግሞ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሳው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ይናገራሉ (ሮሜ 8፡11፣ ሮሜ 1፡3-4)፡፡

ከነዚህ ጥቅሶች የምንረዳው አንድ ነገር ቢኖር የክርስቶስ ትንሣኤ ሦስቱም የሥሉስ ቅዱስ አካላት የተሳተፉበት መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ አብ ኢየሱስን እንዳስነሳው መነገሩ ኢየሱስን ከአብ የሚያሳንስ አይደለም፡፡

19. በዮሐንስ 14፡12 ላይ ኢየሱስ“እውነት እላችኋለሁ በኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሰራ፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፤ ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል” ብሏል፡፡ እንግዲህ ክርስቲያኖች “ኢየሱስን አምላክ ነው” እንደሚሉት ካሰብን በኢየሱስ የሚያም ሰው ከአምላክ በላይ ሥራን መስራት ሊችል ነው ማለት ነው፡፡ ታድያ ከአምላክ መብለጥ ተቻለ ማለት አይደል? ከአምላክ እንኳን ሊበልጥ ይቅርና ሊነፃፀር የሚችል ስራ ማን መስራት ይችላል?

ይህ ጥቅስ ስለ ክርስቶስ የምድር አገልግሎት የሚናገር ነው፡፡ ጌታችን በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ብዙ ተዓምራትን አድርጓል፣ የምሥራቹንም ለብዙዎች አድርሷል፡፡ ነገር ግን ይህንን ኀላፊነትና ሥልጣን ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት ወደ ሰማይ አርጓል፡፡ “ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል” ሲል ሐዋርያት እርሱ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ከነበረው ተደራሽነት በላይ ተደራሽነት እንደሚኖራቸው ለመናገር እንጂ ከእርሱ የበለጠ ተዓምራትን የማድረግ ኃይል ይኖራቸዋል ለማለት አይደለም፡፡ ንግግሩም ብዛትን እንጂ ጥራትን የሚያመልክት አይደለም፡፡ ቀድሞውኑ ተዓምራትን እንዲያደርጉና ወንጌልን እንዲሰብኩ ሥልጣንን የሰጣቸው ራሱ ክርስቶስ ነው (ማቴዎስ 10፡1፣ ማርቆስ 6፡7፣ ሉቃስ 9፡1፣ 10፡19፣)፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ በስሙ እንጂ በራሳቸው ስም አይደለም (ማርቆስ 9፡39፣ ማርቆስ 16፡17፣ ሉቃስ 10፡17፣ የሐዋርያት ሥራ 3፡1-8፣ 3:16፣ 16፡16-18)፡፡ ስለዚህ ይህ የኢየሱስ ንግግር ሐዋርያት ከእርሱ እንደሚበልጡ ለማሰብ እንኳ የሚያስደፍር አይደለም፡፡

20. ዮሐንስ 10፡36 ላይ “ታዲያ፤ “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” ስላልሁ፣ አብ ለራሱ ለይቶ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን፣ ተሳድበሀል ብላችሁ ለምን ትወነጅሉኛላችሁ?” ይላል፡፡ ኢየሱስም “አምላክ ነው” ከተባለ ፣ እንዴት አምላክ ይቀደሳል? ኢየሱስ ተለይቶ ከመቀደሱ በፊት ምን ነበር? እንዴትስ አምላክ ይባላል?

ጠያቂው የክርስቶስን አምላክነት በግልፅ ከሚናገረው ከዚህ ምዕራፍ ውስጥ አምላክነቱን የሚቃወም ሐሳብ ለመፈለግ መሞከራቸው በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ የሚከተሉትን ነጥቦች ግልፅ አድርጓል፡-

  • የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣል (ቁ. 28)
  • በጎቹን (ምዕመናንን) ማንም ከእጁ መንጠቅ አይችልም (ቁ. 28)
  • እነርሱን የሰጠው አባቱ ከነጣቂዎቹ ሁሉ ይበልጣል፤ እርሱና አብ ደግሞ አንድ ናቸው (ቁ. 29 እና 30)
  • አብ በእርሱ ነው እንዲሁም እርሱ በአብ ነው (ቁ. 38)

እነዚህን ሁሉ ነገሮች ከሰሙ በኋላ አይሁድ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን እየተናገረ እንደሆነ በማሰብ ሊወግሩት መፈለጋቸው አያስገርምም፡- “አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብህ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት” (ቁ. 38)፡፡ እርሱም ንግግራቸውን ከመቃወም ይልቅ ከብሉይ ኪዳን ጥቅስ በመጥቀስ አምላክነቱን ሲያረጋግጥላቸው እናያለን፡- “ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፦ ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?” (ቁ. 34-36)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዝሙረ ዳዊት 82 ላይ የተጠቀሱት ሰብዓውያን ባለ ሥልጣናት “አማልክት” የሚል ማዕርግ ከተሰጣቸው አብ ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ያከበረውና ወደ ዓለም የላከው አንድያ ልጁ አምላክ ቢባል ምን ያስገርማል? እያለ ነው፡፡ በሌላ አባባል እነዚህ ሰብዓውያን ምፀታዊ በሆነ ሁኔታ “አማልክት” የሚል መጠርያ ቢሰጣቸውም እርሱ ግን የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ በመሆኑ ምክንያትና አብ በእርሱ ውስጥ እርሱም በአብ ውስጥ እንደመኖሩ አምላክ መባሉ ተገቢ መሆኑን እየተናገረ ነው፡፡ ወደ አሕመዲን ጥያቄ ስንመጣ ስህተታቸው የመነጨው “መቀደስ” ማለት “መለየት” ማለት መሆኑን ካለማወቅ ነው፡፡ “ሀጊያዞ” የሚለው የግሪኩ አቻ ቃል በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ ለምሳሌ ያህል ጌታችን ባስተማረው ጸሎት ውስጥ “ስምህ ይቀደስ” ተብሏል፡፡ በቀጥታ ከተተረጎመ የእግዚአብሔር ስም ቅዱስ ስለሆነ እኛ ልንቀድሰው አንችልም፡፡ “ስምህ ይቀደስ” ስንል የእግዚአብሔርን ስም እንደሌሎች ስሞች እንደማንመለከትና ተገቢውን ክብር እንደምንሰጥ ለመናገር ነው፡፡ 1ጴጥሮስ 3፡15 ላይ “ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት” ይላል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ቅዱስ በመሆኑ እርሱ ይቀድሰናል እንጂ እኛ ልንቀድሰው አንችልም፡፡ ይህ ቃል በልባችን ጌታችን ኢየሱስ ልዩ መሆኑን እውቅና መስጠት እንደሚገባን የተነገረ እንጂ እኛ ለእርሱ ቅድስናን መስጠት እንችላለን ለማለት የታለመ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ “አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን” ሲል የሰው ልጆችን ለመዋጀት ተልዕኮ እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደመረጠና ወደ ዓለም እንደላከ ያመለክታል፡፡ ስለዚህ የቃሉን ትርጉም በትክክል ከተረዳን “ኢየሱስ ከመቀደሱ በፊት ምን ነበር?” ብሎ የሚያስጠይቅ ምክንያት የለም፡፡

ማጣቀሻዎች


[1] πρωτότοκος

[2] kάi

[3]  ማስረጃዎቹን ምዕራፍ 8 ላይ ይመልከቱ፡፡

[4] The Oxford Bible Commentary, edited by John Barton and John Muddiman, Oxford University Press, 2001, p. 1121

[5] የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች መጠርያ ነው

[6] ሙስሊሞች መንፈስ ቅዱስ መልአኩ ገብርኤል (ጂብሪል) ነው ይላሉ


የኢየሱስ ማንነት ጉዳይ (ክፍል 2)

የኢየሱስ ማንነት ጉዳይ (ክፍል 3)

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ