ምዕራፍ 3: አምላክ ሥጋ ለብሶ ሰዉ ሆኗልን? : ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ

ምዕራፍ 3

አምላክ ሥጋ ለብሶ ሰዉ ሆኗልን?

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡

90. በመጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ ታይቶ እንደማይታወቅ በ1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡1፤ 1ኛ ዮሐንስ መልእክት 4፡12፤ ዮሐንስ 1፡18 እና ዮሐንስ 5፡57 ላይ ተገልጧል፡፡ ለአብነት ያህል በ1ኛ ጢሞ 6፡16 ላይ “እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘለዓለም ኃይል ይሁን፤ አሜን” ይላል፡፡ እንዲሁም በዮሐንስ 1፡18 ላይ “ከቶዉንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፡፡” ይላል፡፡ ኢየሱስ ግን ታይቷል፡፡ ተዲያ አምላክ የማይታይ ከሆነ ኢየሱሱ አምላክ እንዳልሆነ አያሳይምን?

ለዚህ ጥያቄ በተለያዩ መንገዶች መልስ መስጠት ይቻላል፡፡ የመጀመርያው የኢየሱስ ሰብዓዊ ባሕርይ እንጂ መለኮታዊ ባሕርዩ በሰዎች ዓይን አልታየም የሚል ነው፡፡ ነገር ግን አሕመዲን የጠቀሷቸው ጥቅሶች እግዚአብሔር በምንም ዓይነት ሁኔታና መንገድ አልታየም ከሚለው የተሳሳተ ትርጓሜ ሲፋቱ ሁለተኛና ይበልጥ ጠንካራ የሆነ ምላሽ እናገኛለን፡፡ እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔርን ሙሉ በሆነው መለኮታዊ ክብሩ ማንም ማየት እንደማይችልና በዚያ ሁኔታ እንዳልታየ የሚናገሩ ሲሆኑ ውሱን በሆነ ሁኔታ እንዲሁም በራዕይ እግዚአብሔርን ያዩት ሰዎች ስለመኖራቸው መጽሐፍ ቅዱስ በበርካታ ቦታዎች ላይ ይናገራል፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-

“ሙሴም አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤ የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማይ መልክ የሚያበራ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ፡፡ እጁንም በእስራኤል አዛውንቶች ላይ አልዘረጋም፤ እነርሱም እግዚአብሔርን አዩ፥ በሉም ጠጡም፡፡” (ዘጸአት 24፡9-11)

“እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በፊቴ ሞገስ ስላገኘህ በስምህም ስላወቅሁህ ይህን ያልኸውን ነገር አደርጋለሁ አለው፡፡ እርሱም፦ እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ… ደግሞም፦ ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ፡፡ እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፥ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም፡፡” (ዘጸአት 33፡17-23፣ ኢሳይያስ 6፡1-4)፡፡

ጸሐይ ከመሬት በብዙ እጥፍ እንደምትበልጥና ትንሽዬ የጸሐይ ቅንጣት መሬት ላይ ብትወድቅ ይህችን ፕላኔት ሙሉ በሙሉ የማጥፋት አቅም እንዳላት ይነገራል፡፡ አፅናፈ ዓለማትን ሁሉ የፈጠረው ሃያሉ አምላክ ምንኛ ታላቅና የሚያስፈራ ይሆን! እግዚአብሔር ግርማው የሚያስፈራ እጅግ ታላቅ አምላክ ነው፡፡ የሰው ልጆች ሙሉ ክብሩን አይተው መትረፍ አይችሉም፡፡ ለሰው አቅም ሊመጥን በሚችልበት ሁኔታ ለሰዎች የታየባቸው ጊዜያት እንደነበሩ እነዚህ ጥቅሶች ቢናገሩም ይህ “መታየት” ከታላቅነቱና ከግርማው ጋር ሲነፃፀር እንዳለመታየት ይቆጠራል፡፡ ይህ “ማየት” የእስክሪፕቶ ጫፍ የምታክለውን የጸሐይ ቅንጣት በማየት ጸሐይን እንዳየን የመናገር ያህል ከማየት የሚቆጠር አይደለም፡፡

በዚህ መሠረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ አምላክነቱ በተወሰነ ደረጃ ቢታይም ነገር ግን ፊልጵስዩስ 2 ላይ እንደተጻፈው ወልድ ወደ ምድር ሲመጣ መለኮታዊ ክብሩን በመተው ስለነበር ሙሉ የሆነው መለኮታዊ ግርማው በሰዎች ዓይን አልታየም፡፡

91. ክርስቲያኖች “ኢየሱስ አምላክ ነዉ፤ ወደ ምድር የሰዉ ስጋ ለብሶ መጥቷል” ይላሉ፡፡ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላስ በስጋ እንዳለ ይቆያል ወይስ አስቀድሞ ነበረ በተባለበት ሁኔታ ይመለሳል?? ኢየሱስ የሰዉ ሥጋ በመተዉ አስቀድሞ ነበረ ወደ ተባለበት አምላካዊ ሁኔታ ይመለሳል? መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸዉ ግን ኢየሱስ የሰዉ ሥጋ ለብሶ እስከ መጨረሻዉ መቀጠሉን እንጂ ሰዉነቱን (ሥጋ መልበሱን) እንደሚተዉ አይናገርም!! ታዲያ አንዱ የሥላሴ አባል ኢየሱስ እስከ መጨረሻ ሰዉ ነዉን?

አሕመዲን ይህንን ጥያቄ የጠየቁት ክርስቲያኖች ኢየሱስ ወደ ምድር ሲመጣ ሰው ወደ መሆን እንደተቀየረ ያምናሉ የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ስለያዙ ነው፡፡ ስለዚህ በእሳቸው አመለካከት መሠረት ኢየሱስ ወደ ሰማይ ያረገው ከመለኮትነት ወደ ሰብዕነት የተቀየረውን ባሕርዩን በመተው ባለመሆኑ አሁን በሰማይ አምላክ ሆኖ ሊኖር አይችልም፡፡ ይህንን የተሳሳተ መረዳታቸውን በጥያቄ ቁጥር 25 ላይ አንጸባርቀዋል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ሰው የሆነው አምላክ መሆኑን በመተው (ከአምላክነት ሰው ወደመሆን ተቀይሮ) ባለመሆኑ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እንደሆነው ሁሉ በሰማይም ሰውም አምላክም ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ባሕርያት ሳይከፋፈሉና ሳይደባለቁ በአንዱ የክርስቶስ ማንነት ውስጥ ይኖራሉ፡፡

92. ዕብራውያን2:17 ላይ “ስለዚህ በሁሉም ነገር ወድሞቹን መምሰል ተገባው” ይላል፡፡ ታድያ ክርስቲያኖች እንደ ሚሉት ኢየሱስ በሁሉም ነገር እንደኛ ከሆነ፣ እንዴት ፍፁም (100°/°) ሰው እንደዚሁም ፍፁም (100°/°) አምላክ ይሆናል? እንደኛ ሲሆን እኛስ ፍፁም አምላክ ልንሆን ነው ማለት ነውን?

ይህ ቃል የተነገረው በእርሱ በማመን የልጅነትን ሥልጣን አግኝተው አብረው ወራሾች ለሆኑት ለክርስቲያኖች እንጂ የእግዚአብሔር ልጆች ተብሎ መጠራትን እንደ ክህደት ለሚቆጥሩት “የአላህ ባርያዎች” ባለመሆኑ አሕመዲን በዚህ መደብ ውስጥ ራሳቸውን መቁጠራቸው ስህተት ነው፡፡ ይህንን በማድረግ አላህ ልጅ እንደሌለው የተነገረውን የቁርኣን ቃል ስለተጣረሱ በሃይማኖታቸው ላይ ክህደትን ፈፅመዋል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ሙስሊም ሰባኪያን የሚያቀርቡት ሙግት ክርስትናን የሚገዳደር መስሎ እስከታያቸው ድረስ በገዛ ሃይማኖታቸው ላይ እንኳ ክህደትን ከመፈፀም ወደ ኋላ እንደማይሉ ነው፡፡

ኢየሱስ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን የመሰለው በሰብዓዊ ባሕርዩ እንጂ በመለኮቱ አይደለም፡፡ ይህንን የጥቅሱ አውድ ራሱ ግልፅ ያደርጋለ፡- “እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም፡፡ ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው፡፡ እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና፡፡” (ዕብራውያን 2፡14-18)፡፡

93. በጥያቄ ቁጥር 25 ላይ የጠየቁትን ስለደገሙ ታልፏል፡፡

94. አንድ የክርስትና እምነትጸሐፊ እዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ምንም እንኳ የእስልምና ሃይማኖት ባይቀበልም፣ ለክርስቶስ ፍጹም አምላክ መሆንና ፍጹም ሰው መሆን ከተልዕኮው አኳያ እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ የክርስቶስ ዋና ተልዕኮ ደግሞ የሰው ልጅን ከኃጢያታቸው ማዳን በመሆኑ ምንም እንኳን ክርስቶስ ሁለት ባህሪያት አሉት ማለት ለሰው አዕምሮ ከበድ ያለ ነገር መስሎ ቢታይም እግዚአብሔር በሁሉን ቻይነቱ ያደረገው የክርስቶስ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው መሆን እውነት ነው ፡፡” (ምህረቱ ጴ. ጉታ፣ መልስ ይኖረው ይሆን? ኤስ አይ ኤም ማተምያ ቤት ታትሞ፣ 4ኛ ዕትም፣ 1998፣ ገፅ 63)

ሀ) እዴት ኢየሱስ “ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ” ይሆናል? እንዴት ሁለት ነገር ፍፁም ይሆናል? አንድን ሰው “ከሰዎች ሁሉ ረጅሙ እርሱ ነው፡፡ አጭሩም እርሱ ነው፡፡” ማለት ይቻላል?

አሕመዲን ለመፈላሰፍ ቢሞክሩም ነገር ግን እሳቸው የሰጡት ምሳሌና ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ የሚያምኑት አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ከሰው ሁሉ ረጅም እና ከሰው ሁሉ አጭር የማይባልበት ምክንያት ርዝመት እና እጥረት ከአንድ መደብ፣ ማለትም የወርድ ርዝመት ስለሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ውፍረት እና ርዝመት ሁለት የተለያዩ ፅንፎች በመሆናቸው አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ከሰዎች ሁሉ አጭር እና ከሰዎች ሁሉ ወፍራም ወይም ከሰዎች ሁሉ ረጅም እና ከሰዎች ሁሉ ቀጭን ሊሆን ይችላል፡፡ ሰውና አምላክ እንደ ርዝመት እና እንደ እጥረት ከአንድ መደብ ስላልሆኑ ኢየሱስ በአንድ ጊዜ ሰውም አምላክም መሆን የማይችልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡

ለ) “ኢየሱስ ፍፁም ሰውም ፍፁም አምላክም ነው” ከተባለ ይህ አስተሳሰብ ከሎጂክ አንፃር ብቻ ሳይሆን ከመጽሐፍ ቅዱስም ጭምር የሚጋጭና የማያስኬድ ነው፡፡ አምላክ ፍፁም ኃያል፣ ሁሉን አዋቂ፣ ፍፁም ጥበበኛ ነው፡፡ ሰው ደግሞ በተቃራኒው ኃያል ያልሆነ፣ ሁሉን የማያውቅ፣ ፍፁም ጥበበኛ ያልሆነ ነው፡፡ “አምላክ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ነው” ማለት፦ “አምላክ (ኢየሱስ) ሁሉን አዋቂ የሆነና ሁሉን አዋቂ ያልሆነ ነው፡፡ አምላክ ኃያል የሆነና ኃያል ያልሆነ ነው፡፡ አምላክ ፍፁም ጥበበኛ የሆነና ፍፁም ጥበበኛ ያልሆነ ነው” ማለት ነው፡፡ ይህ ትርጉም የሚሰጥ ነውን?

ክርስትና ኢየሱስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑን እንጂ ጠያቂው ባስቀመጡት መንገድ “አምላክ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ነው፤ አምላክ ሁሉን አዋቂ የሆነና ሁሉን አዋቂ ያልሆነ ነው፤ አምላክ ኃያል የሆነና ኃያል ያልሆነ ነው፤ አምላክ ፍፁም ጥበበኛ የሆነና ፍፁም ጥበበኛ ያልሆነ ነው” በማለት አያስተምርም፡፡ ውሱንነት የሚታይበት ባሕርዩ ስለ እኛ ሲል የለበሰው ሥጋው እንጂ መለኮቱ አይደለም፡፡

ሐ) የሆነ ነገርን “ፍጹምም ነው፤ ፍጹምም አይደለም” ማለት ልክ የሆነን ነገር “ይህ ነገር ክብም፣ አራት ማአዘንም ነው፤” እንደ ማለት ነው፡፡ “አራት ማዕዘን ነውም” ስንል “ክብ አይደለም” ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህ ሁለት የማይገናኙትን ባህሪያት ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ፍፁም መሆን ይችላልን?

አሁንም አሕመዲን ለመፈላሰፍ ይሞክራሉ ነገር ግን ፍልስፍናውን አላወቁበትም፡፡ ክብ እና አራት ማዕዘን ከአንድ መደብ፣ ማለትም ከቅርፅ መደብ ናቸው፡፡ ስለዚህ አንድ ነገር በአንድ ጊዜ ክብ እና አራት ማዕዘን ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር በአንድ ጊዜ ክብ እና አረንጓዴ ወይም አራት ማዕዘን እና ቀይ ሊሆን ይችላል፡፡ ቅርፅ እና ቀለም ሁለት የተለያዩ መደባት እንደሆኑት ሁሉ ሰውና አምላክም ሁለት የተለያዩ መደባት በመሆናቸው ኢየሱስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑ ምንም የሚያስከትለው የሥነ አመክንዮ ችግር የለም፡፡ የአሕመዲን ምሳሌ የተሳሳተና ስለ ኢየሱስ ከተነገረው ጋር አብሮ የማይሄድ ነው፡፡

መ) ሁለት ተቃራኒ የሆኑ ነገሮች በአንድነት ነው ማለት በፍፁም የማይሆን ነው፡፡ ለምሳሌ “አምላክ አለ” ብንል አንድ ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ “አምላክ የለም” ብንል ደግሞ ሌላ ተቃራኒ ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ ሁለቱም ትክክል ሊሆኑ በፍፁም አይችሉም፡፡ ክርስቲያኖች እንደ ሚሉት “ሁለት ተቃራኒ ነገሮች በአንድነት ሊኖሩ ይችላሉ” ብንልና “አምላክ አለ፤ እንደዚሁ አምላክ የለም፡፡” ብንል፤ ሁለት ተቃራኒ ዐረፍተ ነገሮች ናቸው፡፡” አምላክ ሁሉን ቻይ ስለሆነ ምን አለበት፣ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል፡፡ ምን ይሳነዋል?” ማለት ይቻለናልን?

ጠያቂው ሰውና አምላክ ፍፁም ተቃራኒ ባሕርያት እንዳላቸው ማሰባቸው ትልቅ ስህተት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ አምሳል ስለፈጠረ የተወሰነ ዕውቀት፣ የተወሰነ ኃይል እና የተወሰነ ጥበብ ሰጥቶታል፡፡ ፍቅርን፣ ዕውቀትን፣ ነፃ ፈቃድን እና ምጋቤን ጨምሮ ውሱን በሆነ መጠን በሰዎች ውስጥ የሚገኙ ብዙ የእግዚአብሔር ባሕርያት አሉ፡፡ እነዚህ የእግዚአብሔር ባሕርያት በሰው ውስጥ ከመኖራቸው የተነሳ ሰውና አምላክ ተቃራኒ እንደሆኑ እንድንናገር የሚያስችለን የሎጂክ ሕግ የለም፡፡ ኢየሱስ ሰውም አምላክም ነው የሚለው አባባል አምላክ አለ እንደዚሁም አምላክ የለም ከሚለው እርስ በርሱ የተፋለሰ አባባል ጋር የሚመሳሰል አይደለም፡፡ ኢየሱስ ሰው በመሆኑ ሰብዓዊ ባሕርይን አከለ እንጂ እንደ አምላክ የነበረው ሕልውና አልጠፋም፡፡

95. ዮሐንስ 1፡1 የኢየሱስን “አምላክነት” ይገልፃል ብለው ያምናሉን?“በመጀመሪያ ቃል ነበር፡፡ ቃልም እግዚያብሔር ዘንድ ነበር፡፡ ቃልም እግዚያብሔር ነበር” ይላል፡፡ “እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበር፡፡” (ዮሐንስ 1:2)

ሀ) “በመጀመሪያ” ሲባል የምን መጀመሪያ? ለመሆኑ አምላክ መጀመሪያ አለውን? እንዴት “በመጀመሪያ” ይባላል? ዘለዓለማዊ አይደለምን?

ጠያቂው ጥቅሶችን በትክክል ያለማንበብ ችግር በእጅጉ ይስተዋልባቸዋል፡፡ በመጀመርያ፣ ማለትም መጀመርያ የተባለው ቅፅበት ሲፈጠር ቃል ነበረ፡፡ ቃል በመጀመርያ ወደ መኖር የመጣ ሳይሆን በመጀመርያ የነበረ ነው፡፡ ይህ ቃል ጊዜና ቦታን (Time and Space) ጨምሮ የሁሉ ፈጣሪ በመሆኑ (ቁ.3) ለመኖር ጊዜና ቦታ አያስፈልገውም፡፡ ይህ ባሕርይ ደግሞ የአምላክ እንጂ የሌላ ሊሆን አይችልም፡፡

ለ) “የአምላክ ቃል” የሚባለው ኢየሱስ ክርስቲያኖች እንደ ሚሉት “ዘለዓለማዊ ነው” ከተባለ እንዴት “መጀመሪያ” ይኖረዋል?

በዚህ ቦታ ኢየሱስ በመጀመርያ እንደነበረ እንጂ መጀመርያ እንደነበረው አልተጻፈም፡፡ ጠያቂው አንብቦ የመረዳት ችሎታቸው ደካማ ነው፡፡

ሐ) በዮሐንስ 1:1 በሦስተኛው ዐረፍተ ነገር ቃልና እግዚአብሔር አንድ መሆናቸውን ተነግሮናል፤ ቃል በሚለው ምትክ “እግዚአብሔር”ን ብንተካ “በመጀመሪያ” እግዚአብሔር ነበር፤ እግዚአብሔርም እግዚአብሔር ዘንድ ነበር፤ እግዚአብሔርም እግዚአብሔር ነበር” ይሆናል፡፡ የትኛው እግዚአብሔር ነው እግዚአብሔር ዘንድ የነበረው? አእምሮ መጠቀም አይሻልምን? ኧረ እባካችሁ እናስብ!!

አሕመዲን ኧረ ባክዎትን ከሐዋርያት፣ ከቅዱሳን አባቶች፣ በየዘመናቱ ከኖሩት ክርስቲያን ሊቃውንት እና ከመላው ሕዝበ ክርስቲያን ይልቅ እርስዎ የተሻለ የማሰብ ችሎታ እንዳሎት በማስመሰል አይንጠባረሩ! ያልገባዎትንና ልክ ያልመሰልዎትን ነገር በትህትና ከመጠየቅ ይልቅ ራስዎን ብቻ አሳቢ ሌላውን ማሰብ የተሳነው ማስመሰሉ ለምን አስፈለገ? የዚህች የተለመደች የአላዋቂዎች ስላቅ ምንጭ እንኳ እርስዎ እንዳልሆኑ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡

ሐዋርያው እየተናገረ ያለው ከሥላሴ አካላት መካከል ስለ ሁለቱ ሲሆን ሁለቱንም “እግዚአብሔር ብሎ መጥራቱ የሚያመለክተው አብ እና ወልድ በመለኮት አንድ በአካል ግን ልዩ መሆናቸውን ነው፡፡ ጥቅሱ እየተናገረ ያለው እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ስለመኖሩ ነው፡፡ ከአሕመዲን በስተቀር ይህንን ሐቅ ሊስት የሚችል አሳቢ አዕምሮ ያለው ሰው ሊኖር አይችልም፡፡

96. 1ኛ ቆሮንቶስ 15:29 “ትንሳኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሱ ከሆነ ፣ ሰዎች ለእነሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ?” ይላል፡፡ እነማን ናቸው “ለሞቱ ሰዎች” ብለው የሚጠመቁት? ክርሥቲያኖች “ለሞቱ ሰዎች” ብለው ነው እንዴ የሚጠመቁት? ወይስ ምን? እነማንስ ናቸው?

ይህ ጥያቄ የኢየሱስን ማንነት ከተመለከተው የመጽሐፉ ርዕስ ጋር በምን ይገናኛል? ጠያቂው እንደ ምንም ብለው የጥያቄዎቹን ብዛት 303 ለማድረስ የፈለጉ ይመስላል፡፡ ለማንኛውም ማንየአዲሱ መደበኛ ትርጉም የግርጌ ማጥኛ ለዚህ ጥያቄ ጥሩ መልስ ሰጥቷል፡፡

ለሞቱ ሰዎች የሚጠመቁት የሚለው ግሥ የአሁን ጊዜ መሆኑ በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ለሙታን ሲሉ ይጠመቁ እንደነበር ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ ጳውሎስ ስለዚህ ልማድ ተጨማሪ ማብራርያ ባለመስጠቱ ይህንን ሐሳብ ለማብራራት ብዙ ተሞክሯል፡፡ ከእነዚህ ሦስቱ የሚከተሉት ናቸው፡- (1) በሕይወት ያሉ አማኞች ሳይጠመቁ ለሞቱ አማኞች ይጠመቁ ነበር፤ ይህንንም የሚያደርጉት ባለመጠመቃቸው የሚጎድልባቸው ነገር እንዳይኖር በማለት ነው፡፡ (2) ክርስቲያኖች የሙታንን ትንሳኤ ተስፋ በማድረግ ይጠመቁ ነበር (3) በሞት የተለዩ ክርስቲያኖችን ስፍራ ለመሙላት ሲሉ ክርስቲያኖች ይጠመቁ ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ሰዎችን ያነሣው እግረ መንገዱን ነው፡፡ ይህ ልማድ የተነሳው ተቀባይነት ስላለው ሳይሆን የሙታን ትንሳኤ እንዳለ ለማስረዳት ነው፡፡ ምናልባትም የዚህ ሐረግ ትርጉም ስውር እንደሆነ ይኖራል፡፡[1] ጳውሎስ ግን ይህንን ሐሳብ የጠቀሰው በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ ሰዎች ለሙታን እየተጠመቁ የሙታን ትንሳኤን መካዳቸው በራሳቸው ልምምድ መሠረት እንኳ ትክክል አለመሆኑን ለማሳየት ያህል እንጂ ተግባሩን በመደገፍ አይደለም፡፡ የአዲስ ኪዳን የጥምቀት ፅንሰ ሐሳብም ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡

ኡስታዝ ከዚሁ ሐሳብ ሳይወጡ ሙስሊሞች ለሞቱት ዘመዶቻቸው ሲሉ ለምን ሰደቃ እንደሚያደርጉና ሐጅ እንደሚፈፅሙ እንዲያስረዱን እንጠይቃቸዋለን፡፡

97. ሮሜ 11:26 “ስለዚህ እስራኤል ሁሉ ይድናሉ” ይላል፡፡ እስራኤላዊያን ግን ያኔ በኢየሱስ ዘመንም ሆነ ዛሬ በኢየሱስ ክርስቶስ አላመኑም፡፡ የአይሁድ እምነት (ጁዳይዝምን) ተከታይ ናቸው፡፡ ታድያ በኢየሱስ ሳያምኑ ዳኑ? ወይስ ጥቅሱ ውሸት ነው?

የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች እስራኤላውያን ነበሩ፡፡ ኢየሱስ ራሱ እስራኤላዊ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አይሁድ ክርስቲያኖች በመላው ዓለም ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ ኢየሱስን እንደካዱ በጅምላ መናገር ስህተት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ እስራኤል ሁሉ መዳን ሲናገር በዘካርያስ 12፡10 ላይ በተጻፈው መሠረት እስራኤል ብሔራዊ ንስሐ በማወጅ ከእግዚአብሔር ጋር ስትታረቅ እና ወደ መሲሁ ስትመለስ የሚኖረውን ትውልድ ለማለት እንጂ በዘመናት መካከል መሲሁን ክደው ክፋትን እያደረጉ የኖሩትን ሁሉ ለማለት አይደለም፡፡

98. ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ ከወጡ አብ ከሁለቱ መቅደሙ ግልጽ ነው፡፡ ታድያ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሳይወጡ እርሱ (አብ) ብቻ አልነበረንም? ከነበረስ ታድያ እንዴት ሦስቱሞ (አብ ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱሥ) “እኩል ለዘለዓለም ነበሩ” ይባላል?

ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በዘለዓለማዊ መገኘት (Eternal Generation) ከአብ ስለወጡ በመካከላቸው የጊዜ መቀዳደም የለም፡፡ የበለጠ ለመረዳት ለጥያቄ ቁጥር 74 የተሰጠውን ምላሽ ይመልከቱ፡፡

99. ሔዋን የተከለከለችውን ዛፍ በመብላቷ አምላክ ቅጣት አዘዘባት፡፡ በወሊድ ጊዜ በስቃይ ትወልድ ዘንድ፡፡ ዘፍጥረት 3:16 “ሴቲቱንም እንዲህ አላት፤ በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤ በሥቃይም ትወልጃለሽ፤ ፍላጎትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል ፤ እርሱም የበላይሽ ይሆናል” ይላል፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ የክርስቲያን ምሁራን እዲህ ሲሉ ማብራርያ ጽፈዋል ፦ “ሔዋንና ሴቶች ተፈረደባቸው፡፡ ከዚህ የተነሳ ልጅ መውለድ አስጨናቂ ሂደት ሆነ፡፡ ሴቶች ከባሎቻቸው ጋር የነበራቸው የእኩልነት ግንኙነት ተለውጦ ለባሎቻቸው የሚገዙ ሆኑ ፡፡” (ቲሞ ፌሎስ፣ የብሉይ ኪዳን የጥናት መምህርና ማብራርያ 1ኛ መፅሐፍ ገፅ 126)፡፡ እንደ ክርስትና እምነት አዳምና ሔዋን ባጠፉት ጥፍት ምክኒያት የደረሠባቸውን ኃጢአት (“የውርሥ”) ኢየሱስ መስዕዋት ሆኖ በደሙ ከዝርያቸው ላይ አንጽቷል፡፡ ይህ አስተምሕሮት እውነት ከሆነ ታድያ በዚያው ጥፋት ምክንያት ሔዋን ላይ የተጣለው (ጭንቅና ስቃይ) አሁንም ለምን ቀጠለ? ወይንስ “ኢየሱስ ለኛ ሲል ቤዛ ሆነ” የሚባለው ሀሰት ነው?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን በመስቀል ላይ ቤዛ ሆኖ ዕዳችንን ከፍሎልናል፡፡ ይህ ማለት ግን በዚህች ምድር ላይ እስካለን ድረስ በሰው ውድቀት ምክንያት ከመጡት መከራዎች እና ህመሞች ነፃ እንሆናለን ማለት አይደለም፡፡ መዳናችን የሚገለጠው በዳግመኛ ምፅኣቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመለስ ሲሆን ያኔ ከዚህች ዓለም ስቃይ እንገላገላለን፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያላመኑት ሰዎች በመጪው ዓለም ስቃያቸው እጅግ በዝቶ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች የሚኖሩ ሲሆኑ አማኞች ግን ከየትኛውም ስቃይ ነፃ በመሆን ወደ ዘለዓለም ፍስሐ ይሄዳሉ (ሮሜ 8፡18-25፣ ራዕይ 21፡4)፡፡

ስለዚህ ክርስቶስ የኃጢአት ዕዳችንን ሁሉ በመክፈል በውርስ ኃጢአት ከመጡት ሥቃዮች ሁሉ አድኖናል ነገር ግን ይህ መዳናችን እውን የሚሆነው በትንሣኤ ወቅት የሚሞተው ሥጋችን ተለውጦ የማይሞተውን ሲለብስ ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን በዚህች ምድር ላይ የምናሳልፋቸው የትኞቹም መከራዎች ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ የሚያቀርቡንና መጪውን ተስፋችንን በናፍቆት እንድንጠባበቅ የሚያደርጉን አጋጣሚዎች እንደሆኑ በመቁጠር ሳናጉረመርም የጌታችንን መገለጥ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ቁርኣን የመጀመርያዎቹ ሰዎች ኃጢአትን ከሰሩ በኋላ ከገነት እንደተባረሩና አላህን ይቅርታ በመጠየቃቸው ምክንያት ይቅር እንደተባሉ ይናገራል (ሱራ 2፡37)፡፡ ታድያ የኃጢአታቸውን ይቅርታ ከተቀበሉ ለምን እስካሁን ድረስ የሰው ልጆች በሥቃይ ውስጥ ይኖራሉ? ወደተባረሩባትስ ገነት እንዲመለሱ ለምን አልተፈቀደላቸውም?

100. እንደ ዘፍጥረት 3፡13 ሔዋን ያሳሳታት እባብ መሆኑን “እባብ አሳሰተኝና በላሁ” ሥትል ተናግራለች፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እባብን እንዲህ አለው፦ ይህን ሥራ ሠራህ፤ ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ሁን፡፡ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በደረትህ እየተሳብህ ትሄዳለህ፤ ዐፈርም ትበላለህ፡፡” (ዘፍጥረት 3:14) የክርስትናው ጸሐፊ ቲም ፌሎስ በዚህ ጥቅስ ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “እባብ ተፈጥሮው በሆዱ የሚሳብ ሆነ፡፡ በእባብ ተመስሎ የቀረበው ሰይጣን ተፈርዶበት የመጨረሻ ሽንፈቱ ተነገረ፡፡” (ቲም ፌሎስ፣ የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራርያ 1ኛ መፅሐፍ ገፅ 126)

ሀ) “በሕይወት ዘመን ሁሉ … ዐፈርም ትበላለህ፡፡” እንደተባለው እባብ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አፈር ይበላልን?

እባቦች የአካባቢያቸውን ሁኔታ ለማወቅ አፈር እንደሚልሱ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህ አባባል ቃል በቃል አፈር ስለመብላት ሳይሆን ስለ መዋረድ የተነገረ ነው፡፡ “አፈር መብላት” ውርደትን የሚያመለክት የእብራይስጥ ምሳሌያዊ አነጋገር ሲሆን (መዝሙር 72፡9፣ ኢሳይያስ 49፡23) በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ያታለላት ሰይጣን እንደሚዋረድ ለመግለፅ የተነገረ ነው፡፡

ለ) እባብ እንዴት አድርጎ ሄዋንን አሳሳተ? ወይንስ ሰይጣን በእባብ ተመስሎ አሳታት? ታድያ ሰይጣን በእባብ ተመስሎ ካሳታት ለምን እባብ “ይህን ሥራ ሠራህ፤ ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ሁን፤ በሕይወት ዘመን ሁሉ በደረትህ እየተሣብህ ትሄዳለህ፤ ዐፈርም ትበላለህ” ተብሎ ተረገመ? ባልሰራው ኃጢአት?

የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመርያዎቹ ምዕራፎች ቅኔያዊ በመሆናቸው አስተውሎትን ይሻሉ፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር በቀጥታ ለእባቡ ሲናገር የምንመለከት ሲሆን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ ይህ እባብ ሰይጣን መሆኑ ተነግሯል፡- ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ” (ራዕይ 12፡9)፡፡

ከዚህ ጥቅስ በመነሳት እባቡ የዲያብሎስ ተሠግዎ እንደነበር ልንደመድም እንችላለን፡፡ ስለዚህ እባቡ የሰይጣን መጠቀምያ በመሆኑ ተረግሟል፡፡ የሴቲቱ ዘር የእባቡን ራስ እንደሚቀጠቅጥና እርሱም ሰኮናውን እንደሚቀጠቅጥ መነገሩ ጌታችን ወደዚህ ዓለም በመምጣት በመስቀሉ መከራ ሰይጣንን ድል እንደሚነሳ የተነገረ ትንቢት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

[1] መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም፣ ኢንተርናሽናል ባይብል ሶሳይቲ፣ 1993፣ 1ቆሮ. 15፡29 የግርጌ ማጥኛ፣ ገፅ 1759፡፡

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ