ምዕራፍ 4: የኢየሱስ አስተምህሮት ምን ነበር? ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ

ምዕራፍ 4

የኢየሱስ አስተምህሮት ምን ነበር?

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ ካቆምንበት እንቀጥላለን

  1. ኢየሱስ አምላክ ከሆነ ለምንድነው በዮሐንስ 10:29 ላይ “እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፡፡” እንዲሁም በዮሐንስ 14:28 “ብትወዱኝስ አብ ከእኔ ስለሚበልጥ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር” ያለው? እንደዚሁም በዮሐንስ 13:16 እና 1ኛ ቆሮንቶስ 11:3 ላይ አምላክ ከኢየሱስ እንደሚበልጥ ተገልጿል ፡፡ ከአምላክ የሚበልጥ ሌላ አምላክ አለን? ወይስ ኢየሱስ “ትንሹ አምላክ” ነው? አብ ከእርሱ እንደ ሚበልጥ ኢየሱስ ሲናገር ክርስቲያኖችን ግን “በፍፁም እኩል ናቸው” ይላሉ ፡፡ ታዲያ ኢየሱስ ይህን ሲናገር እየዋሸ ነውን? ወይስ ክርሥቲያኖች ናቸው የዋሹት? ኢየሱስ ክርስቶስ “አብ ከእኔ ይበልጣል” ሲል ሰብዓዊ ማንነቱን ብቻ የሚመለከት እንጂ “በመለኮታዊ ባህሪ ደረጃ ግን እኩል ናቸው” ብሎ ማሰብስ የቋንቋ አጠቃቀም ሥርዓትን ትርጉም ማሳጣት አይሆንምን?

በመጀመርያው ጥቅስ ላይ በጎቹን የሰጠው አብ በጎቹን ከእጁ ሊነጥቁ ከሚመኙት ሁሉ እንደሚበልጥ ለመናገር ፈልጎ “እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል” አለ እንጂ ራሱን በማካተት እየተናገረ አይደለም፡፡ ከእርሱም ሆነ ከአብ እጅ በጎቹን ማንም መንጠቅ እንደማይችል ከተናገረ በኋላ እርሱና አብ አንድ እንደሆኑ በማሳወቅ በባሕርይ የተካከሉ መሆናቸውን ግልፅ አድርጓል (ዮሐንስ 10፡30)፡፡ ይህ አንድነት የኃይል አንድነትን የሚገልፅ ነው፡፡ አብና ኢየሱስ በኃይል አንድ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ማንም በጎቹን ከአብ እጅ መንጠቅ እንደማይችል ሁሉ ከኢየሱስም እጅ መንጠቅ የማይችለው፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ቦታ ላይ ለበጎቹ የዘለዓለምን ሕይወት እንደሚሰጥ በመናገር አምላክነቱን የበለጠ ግልፅ አድርጓል (ቁ.28)፡፡ ከአምላክ በስተቀር የዘለዓለምን ሕይወት መስጠት የሚችል አለን? ከዚህ ንግግር በኋላ አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ ያነሱት ኢየሱስ አምላክ መሆኑን እየተናገረ መሆኑ ስለገባቸው ነው፡- አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት (ቁ.31-33)፡፡ (ኢየሱስ በዚህ ቦታ ላይ ስለ ኃይል እንጂ ስለ ዓላማ እየተናገረ ባለመሆኑ በዮሐንስ 17፡20-21 ላይ ለሐዋርያቱ ከተነገረው አንድነት ጋር ማመሳሰል ትክክለኛውን የሥነ ፍታቴ ሥርኣት የሚጥስ ነው፡፡ የሁለቱ አውድ ለየቅል ናቸው፡፡)

በሌሎቹ ጥቅሶች ውስጥ አብ ከኢየሱስ እንደሚበልጥ መገለፁን ጸሐፊው የተመለከቱት በተለመደው የነጠላ አሃዳዊነት ንፅረተ ዓለም መነፅራቸው ነው፡፡ በእሳቸው እምነት መሠረት አምላክ የተባለ አንድ አካል ብቻ በመኖሩ ከዚያ አካል በምንም መንገድ ሊበልጥ የሚችል ነገር መኖሩ ከተነገረ ያ አካል ከመቅፅበት ከአምላክነት ቦታ ይወርዳል፡፡ ክርስትና ግን አንድ አምላክ ብቻ መኖሩን ቢያስተምርም ይህ አንዱ አምለክ ሦስት አካላት እንዳሉት ስለሚያስተምር በነዚህ አካላት መካከል የሥራ ድርሻ (function) ወይም የደረጃ (rank) ብልጫ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ በእግዚአብሔር በራሱ ሕላዌ ውስጥ የሚገኝ እንጂ ከእርሱ ውጪ የሚገኝ ባለመሆኑ በሥላሴነት ከሚኖረው ከአንዱ አምላክ ውጪ የሚገኝ አካል ብልጫ እንዳለው እስካልተነገረ ድረስ ምንም የሚፈጥረው ችግር የለም፡፡ በነዚህ ቦታዎች የተጠቀሰው “ሜይዞን” የሚለው የግሪክ ቃል ደረጃን እንጂ የግድ የባሕርይ ብልጫን የሚያመለክት አይደለም፡፡ አንድ አካል ከሌላው በሥራ ድርሻ፣ በሥልጣን ወይም በደረጃ ይበልጣል ማለት የባሕርይ ብልጫ አለው ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ለምሳሌ ያህል የአንድ አገር መሪ በሥራ ድርሻ፣ በሥልጣንም ሆነ በደረጃ በስሩ ከሚተዳደሩት ዜጎች ይበልጣል፡፡ ይህ ማለት ግን እንደ ሰው ያለው ዋጋ (Value) ከማንም ይበልጣል ማለት አይደለም፡፡ ባል የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ከሚስቱ ሊበልጥ ይችላል ነገር ግን ወንድ እንደ ሰውነቱ ከሴት ይበልጣል ወይም ሴት ከወንድ ታንሳለች ማለት ግን አይደለም፡፡ የግሪክ አዲስ ኪዳን የባሕርይ ብልጫን ለማመልከት “ዲያፎሮስ” የሚል ሌላ ቃል የሚጠቀም ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕርዩ ከመላእክት የላቀ መሆኑን ለማመልከት ዕብራውያን 1፡4 ላይ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በሥላሴ አካላት መካከል የሚገኘውን ግንኙነት ለማመልከት ግን ይህ ቃል ጥቅም ላይ ውሎ አናገኝም፡፡ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አብ ከወልድ መብለጡ መነገሩ የመለኮታዊ ባሕርይ ብልጫን ሳይሆን የሥራ ክፍፍልን እና ወልድ ሥጋን በመልበስ መለኮታዊ ክብሩን ትቶ ወደ ምድር እንደመምጣቱ መጠን (ፈልጵስዩስ 2፡5-11) የደረጃ ብልጫን ብቻ የሚያመለክት በመሆኑ የኢየሱስን አምላካዊ ባሕርይ ከአብ የሚያሳንስ አይደለም፡፡

  1. ኢየሱስ ለምድነው በዮሐንስ 8፡28 ላይ “ከራሴ ምንም ላደርግ አይቻለኝም” ያለው? ታዲያ እንደሚሉት ኢየሱስ አምላክ ሆኖ ከራሱ ምንም ማድረግ የማይችል ከሆነ ምንም ማድረግ የማይችል አምላክ አለ ልንል ነውን? ወይሥ የሰው ስጋ ስለለበሰ? ታድያ በመጽሐፍ ቅዱሥ አንድም ሥፍራ “ኢየሱስ ካረገም በኃላ ሥጋውን ይተዋል” አይልም፡፡ ታዲያ እስከ መጨረሻ ምንም ማድረግ ለማይችለው ኢየሱስ ፍፁማዊ አምላክነትን ልንሰጥ እንዴት ይቻለናል?

ክርስቲያኖች ሦስቱም የሥላሴ አካላት ተነጣጥለው ይሠራሉ የሚል እምነት ስለሌላቸው ኢየሱስ ከአብ ተነጥሎ ከራሱ ምንም ማድረግ አለመቻሉን ከመለኮታዊ ባሕርዩ አኳያ ቢናገር እንኳ የሥላሴን አስተምህሮ የሚያረጋግጥ እንጂ የሚቃወም አይደለም፡፡ በተጨማሪም ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አምላክነቱን ባያቆምም ነገር ግን አምላካዊ ሥልጣኑን በመተው እንደ አገልጋይ ተመላልሷል (ፊልጵስዩስ 2፡5-11)፡፡ ስለዚህ ከራሱ አንዳች ማድረግ እንደማይቻለው መናገሩ ሰብዓዊ ባሕርዩን የሚያመለክት ነው፡፡ የትንሣኤ ሥጋውን ይዞ ወደ ሰማይ ቢያርግም ነገር ግን ወደ ቀደመው መለኮታዊ ክብሩ ስለተመለሰ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው መለኮታዊ ባሕርዩ እንጂ ሰብዓዊ ባሕርዩ ባለመሆኑ የጠያቂው ሙግት ውድቅ ነው፡፡

  1. ኢየሱስበማርቆስ 10:18 ላይ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ?” በማለት “ቸር” ለመባል ካልፈለገ እንዴት አምላክ ይባላል? ኢየሱስ ቸር መባል እንደሌለበትና “ቸር” አንዱ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ካስተማረ፣ ይህ ብቻ አምላክ አለመሆኑን አይገልጽምን? “ቸር” መባልን እዲህ ከተቃወመ “ከአምላክ እኩል ነው የሚለውን ቢሰማ እንዴት ይቆጣ ይሆን?

ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ሰዎች በተቃውሞ መልክም ሆነ አምኖ በመቀበል ሲናገሩ በተደጋጋሚ ሰምቷል ነገር ግን እነርሱ የተናገሩትን ከማረጋገጥ ውጪ ሲቃወም ተሰምቶ አይታወቅም (ዮሐንስ 10፡33፣ 20፡28)፡፡ ሰዎች ለአምላክ የሚገባውን ስግደት እና አምልኮ ሲሰጡት አንድም ጊዜ አልተቃወመም (ማቴዎስ 8፡2፣ 9፡18፣ 15፡25፣ 14፡33፣ 20፡28፣ 28፡9፣ 28፡17፣ ሉቃስ 24፡52፣ ዮሐንስ 9፡38)፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ አምላክ በመሆኑ አምላክ መባሉ ያስደስተዋል እንጂ አሕመዲን እንዳሉት አያስቆጣውም፡፡ ጠያቂው በጠቀሱት ክፍል ኢየሱስ “ቸር አይደለሁም” እያለ አይደለም፤ ነገር ግን ሰውየው ኢየሱስ መምህር ብቻ መሆኑን እያሰበ ከመጣ በኋላ ለአምላክ ብቻ የሚሰጠውን ማዕርግ ስለሰጠው የንግግሩን ትርጉም እንዲገነዘብ ለማሳሰብ “ስለምን ቸር ትለኛለህ?” በማለት ጠይቆታል፡፡ ሰውየው የኢየሱስን ማንነት ተገንዝቦ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ይህንን ባላለ ነበር፡፡ ነገር ግን መምህር ብቻ መሆኑን እያሰበ ለአምላክ ብቻ የሚሰጠውን ማዕርግ መስጠቱ ትክክል ባለመሆኑ ሊያርመው ይህንን ተናገረ፡፡ ተመሳሳይ የግሪክ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከፍጡራን ጋር ተያይዞ ከመጠቀሱ አንፃር (ለምሳሌ ማቴዎስ 12፡35) ይህ የኢየሱስ መልስ ቃሉ በምንም ዓይነት መንገድ ከአምላክ ውጪ ለሌላ ፍጥረት ጥቅም ላይ መዋል የለበትም የሚል ትርጉም የለውም፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ የሰውየውን ልብ ስለሚያውቅ እርሱ በልቡ እያሰበ ባለበት በዚያ መንገድ በራሱ መልካም የሆነው አምላክ ብቻ መሆኑን ሊያሳውቀው ነው ይህንን የተናገረው፡፡ ይህ ደግሞ ኢየሱስ የሰዎችን ልብ የማወቅ መለኮታዊ ችሎታ እንዳለው ያሳያል፡፡ በተጨማሪም ሰውየው የዘለዓለምን ሕይወት ያገኝ ዘንድ ሁሉን ትቶ እርሱን እንዲከተለው በመንገር ለፈጣሪ ብቻ የሚገባውን መሰጠት እና መገዛት ከሰውየው ጠይቋል፡፡ ይህም በክፍሉ ውስጥ የተገለጸ አምላክነቱን የሚያረጋግጥ ሌላ ማስረጃ ነው፡፡

  1. በመጽሐፍ ቅዱስ አንድም ስፍራ ላይ አምላክ “አንድ” እንጂ “ሦስትም አንድም” ሳይባል መጠቀሱ “አምላክ አንድም ሦስትም” የሚለውን ንግግር መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለ መሆኑን አያሳይምን?

“ተውሂድ” የተሰኘው የአላህ አንድነት አስተምህሮ ሦስት ክፍሎች እንዳሉት በቁርኣን ውስጥ ቃል በቃል አለመጠቀሱ ትምህርቱ ቁርአናዊ አለመሆኑን እንደማያሳይ ሁሉ “እግዚአብሔር ሦስትም አንድም” ተብሎ ቃል በቃል አለመጻፉ አስተምህሮው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑን አያሳይም፡፡ ሥላሴን የሚገልፁ እጅግ በርካታ ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ (ማቴዎስ 3፡16-17፣ 28፡19፣ ዮሐንስ 14፡18፣ 1ቆሮንቶስ 12፡4-6፣ 2ቆሮንቶስ 13፡14፣ ዘፍጥረት 1፡1-2፣ 1፡26፣ ዘፍጥረት 3፡22፣ 1ጴጥሮስ 1፡1-2፣ ሮሜ 14፡17-18፣ ዮሐንስ 10፡30)፡፡

  1. የዮሐንስ ወንጌል 17፡3ን በመጥቀስ ኢየሱስ አብን ብቸኛ እውነተኛ አምላክ በማለት ስለመጥራቱ በቁጥር 5 ላይ የተመለሰውን ጥያቄ ስለደገሙ ታልፏል፡፡
  2. በቁጥር 25 ላይ የተመለሰውን ጥያቄ በሌላ አባባል ስለደገሙ ታልፏል፡፡
  3. የዮሐንስ ወንጌል 11፡38-43 ላይ “ኢየሱስ ልቡ ዳግመኛ በኀዘን ተነክቶ ወደ መቃብሩ መጣ መቃብሩም በድንጋይ የተገጠመ ዋሻ ነበር፤ እርሱም “ድንጋዩን አንሱት” አለ፡፡ የሟቹም እህት ማርታ፤ ጌታ ሆይ አሁንማ አራት ቀን ስለቆየ ይሸታል” አለችው፡፡ ኢየሱስም ብታምኝስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርሁሽምን?” አላት፡፡ ስለዚህ ድንጋዩን አነሱ፡፡ ኢየሱስም ወደላይ ተመልክቶ እንዲህ አለ “አባት ሆይ ስለ ሰማኽኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ይህን መናገሬ ግን በዚሁ የቆሙ ሰዎች አንተ እንደላክኽኝ የምኑ ዘንድ ነው፡፡” ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በታላቅ ድምፅ “አልዓዘር ና ውጣ!” ብሎ ተጣራ፡፡ የሞተውም ሰው እጅና እግሩን በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደተጠቀለለ፤ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ፡፡ ኢየሱስም “መግነዙን ፍቱለትና ይሂድ” አለቸው፡፡” ሲል ተገልጿል፡፡ ተዓምሩ የማን ነው? ኢየሱስ ጸልዮ “ስለሰማኽኝ አመሰግንሃለሁ” በማለት ፀሎቱ መሰማቱን ገለጸ፡፡ 

ተዓምራቱ የርሱ ነው በሚል እንደይታለሉ ፀሎቱን ማሰማቱን ለምን እንደተናገረ ሲገልፅ “ይህን መንገሬ ግን በዚህ የቆሙ ሰዎች አንተ እንደ ላከኝ ያምኑ ዘንድ ነው” ብሎ ነበር፡፡ ታድያ ኢየሱስ አምላኩን ለምኖ ተዓምር ቢያደርግ ምን ያስገርማል? አምላክ ከዚህ የበለጠ ላሻው መስጠት አይችልምን? ይህንን ተዓምር ያየችው የሟቹ እህት ማርታ ተዓምሩ የራሱ የኢየሱስ መሆኑን አምና ነበርን? ኢየሱስስ ቢሆን “ብታምኝስ የእግዚአብሔር ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርሁሽምን?“ አይደል ያላት? ታድያ ምነው አምላክ ነው ማለታችን?

አሕመዲን ይህንን ጥያቄ የጠየቁት ኢየሱስ አምላክ ነው የሚለው የክርስቲያኖች እምነት በፈጸማቸው ተዓምራት ላይ የተመሠረተ ነው የሚል የተሳሳተ ቅድመ ግንዛቤ ስለያዙ ነው፡፡ በክርስቲያኖች እምነት መሠረት የኢየሱስ ተዓምራት ስለ አምላክነቱ የተናገራቸውን ነገሮች የሚያረጋግጡ ምልክቶች እንጂ ብቻቸውን ተነጥለው የሚታዩ ምልክቶች አይደሉም፡፡ ጌታችን ማንም ነቢይ ተናግሮ የማያውቃቸውን አምላክ መሆኑን የሚያሳዩ ንግግሮችን ከመናገሩ የተነሳ እነዚህ ምልክቶች የኢየሱስ ንግግሮች እውነት መሆናቸውን የሚያረጋግጡና አብም ከኢየሱስ ንግግሮች ጋር መስማማቱን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ማርቆስ 2፡5-12 ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት መለኮታዊ ሥልጣን እንዳለው ለማረጋገጥ ሽባውን ፈውሶታል፡፡ ማቴዎስ 14፡22-33 ላይ ንፋሱንና ወጀቡን በቃሉ ፀጥ በማሰኘት በተፈጥሮ ላይ ያለውን ሥልጣን ካሳየ በኋላ በታንኳይቱ ውስጥ የነበሩት ሰዎች “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰግደውለታል፡፡ ከዚህም አልፎ ጌታችን ተከታዮቹ በስሙ ተዓምራትን ያደርጉ ዘንድ ሥልጣንን ሰጥቷል፤ ይህንንም በማድረግ ስሙ የአምላክ ስም መሆኑን አረጋግጧል (ማርቆስ 6፡7-13፣ 9፡38-39፣ ሉቃስ 10፡17-20፣ የሐዋርያት ሥራ 3፡1-16፣ 4፡7-12፣ 9፡33-35፣ 16፡16-18)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ሰዎች በነቢያትም ሆነ በየትኛውም ቅዱስ ሰው ስም ተዓምራትን ሲያደርጉ የተመዘገበ ታሪክ የለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተዓምራትን በማድረግ ብቻ ሳይሆን ተከታዮቹ በስሙ ተዓምራትን እንዲያደርጉ ሥልጣንን በመስጠት ስለ አምላክነቱ የተናገራቸው ንግግሮች እውነት መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡

ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከአብ ተነጥሎ ወይንም ደግሞ ያለ አብ ፈቃድ ተዓምራትን ያደርግ እንደነበር ስለማያምኑ አሕመዲን ይህንን ለኛ ለማብራራት መሞከራቸው ስለ እምነታችን ያላቸውን የዕውቀት ጉድለት የሚያሳይ ነው፡፡ ኢየሱስ አብ እንደሰማውና ዘወትር እንደሚሰማው በመግለፅ ካመሰገነ በኋላ አልዓዛርን አስነስቶታል፡፡ ያንን መናገር ያስፈለገው ደግሞ እርሱ ከአብ የተላከ መሆኑን የሚጠራጠሩ በቦታው የነበሩ ሰዎች እንዲያውቁ ለማድረግ እንጂ ለራሱ ብሎ አልነበረም፡፡ እርሱ ተዓምራትን ለማድረግ መጸለይ አያሻውም፡፡ ይህንን ደግሞ በግልፅ ቋንቋ ለማርታ ነግሯታል፡-

ማርታም ኢየሱስን፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው፡፡ ኢየሱስም፦ ወንድምሽ ይነሣል አላት፡፡ ማርታም፦ በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው፡፡ ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት፡፡ እርስዋም፦ አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው፡፡

ማርታ ኢየሱስ በጸሎቱ ሁሉንም ነገር የማድረግ ችሎታ እንዳለው ብታምንም ነገር ግን ወንድሟ በዚያኑ ቅፅበት የመነሳቱን ጉዳይ ስትጠራጠርና በመጨረሻው የትንሣኤ ቀን እንደሚነሳ ስትናገር እናያለን፡፡ ነገር ግን ጌታችን የሕይወት ምንጭ ራሱ መሆኑን “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም” በማለት በማስረዳት ሙታንን ለማስነሳት መጸለይ እንደማያሻው ግልፅ አድርጎላታል፡፡ ትንሣኤና ሕይወት ራሱ ኢየሱስ ከሆነ ሙታንን ለማስነሳት መጸለይ ያስፈልገዋልን? እንዲህ ዓይነት ንግግር መናገር የሚችል ከአምላክ በስተቀር ማን ሊሆን ይችላል?  ኢየሱስ የጸለየው ተዓምራትን ለማድረግ መጸለይ ስለሚያስፈልገው አልነበረም፡፡ ነገር ግን በዚያ የነበሩት ሰዎች በአብ የተላከ አንድያ ልጁ፣ መሲሁ መሆኑን እንዲገነዘቡ ለማድረግ ነበር፡፡

በእስላማዊ ትምህርት መሠረት ከአላህ ዘጠና ዘጠኙ ስሞች መካከል አንዱ “አል-ባሂሥ” የሚል ሲሆን ትርጓሜውም “ከሞት የሚያስነሳ” እንደማለት ነው፡፡ ከእነዚህ ስሞች መካከል አንዱን እንኳ ለፍጡር መስጠት የሽርክ ኃጢአት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ ይህም ማለት ያንን አካል ከፈጣሪ እኩል ማድረግ ማለት ነው፡፡ ጌታችን በዚህ ስም ራሱን በመጥራቱ በእስልምና መስፈርት መሠረት አምላክ መሆኑን በፍፁም ግልፅነት ተናግሯል! ኢየሱስ አምላክ መሆኑን የተናገረበት ቦታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሌለ የሚናገሩት አሕመዲን በራሳቸው ሃይማኖት መስፈርት መሠረት ኢየሱስ አምላክ መሆኑን መናገሩን ሲያዩ መልሳቸው ምን ይሆን?

ኢየሱስ ያደረገው ተዓምር የአብን ክብር የገለጠውን ያህል የእርሱንም ክብር ገልጧል (ዮሐንስ 11፡4)፡፡ የመጀመርያውን ተዓምር ካደረገ በኋላ እንዲህ ተብሎለታል፡- ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ፡፡” (ዮሐንስ 2፡11)፡፡

  1. ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ሕግንና የነቢያትን ቃል ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈፀም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም፡፡” (ማቴዎስ 5፡17) እንዲሁም እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስክያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈፀማል እንጂ ከሕግ አንዲት ፊደል ወይም አንዲት ነጥብ እንኳን ቢተላለፍ ሌሎችንም እንዲተላለፍ ቢያስተምር በመንግስተ ሰማይ ታናሽ ተብሎ ይጠራል፤ ነገር ግን እነዚህን ትእዛዘት እየፈፀመ ሌሎችም እንዲፈፅሙ የሚያስተምር በመንግስተ ሰማይ ታላቅ ይባላል፡፡ (ማቴዎስ 5፡18-19) ይላል፡፡ ትእዛዘትን እየፈፀመ እንዲፈፀም የሚያስተምር ሰው ነው በመንግስተ ሰማያት ታላቅ የሚባለው፡፡ ግን ክርስቲያኖች “በኢየሱስ ለሰው ኃጥአት ቤዛ መሆኑን ያመነ ሰው ነው መንግስተ ሰማያትን የሚገባው ይላሉ፡፡ ትእዛዘትን መፈጸም አስፈላጊ እንዳልሆነ ሁሉ ያሚያስተምሩ ክርስቲያኖችም አሉ፡፡ ታድያ ኢየሱስ ያለው ውሸቱን ነበርን? ወይንስ እንዲህ የሚሉት ክርስቲያኖች ናቸው የዋሹት?

ኢየሱስ በዚህ ቦታ ላይ እየተናገረ ያለው ህግን በመጠበቅ ወደ መንግሥተ ሰማያት ስለመግባት ሳይሆን ህግን በመጠበቅ በመንግሥተ ሰማያት ውስጥ ስለሚገኝ ደረጃ በመሆኑ ጠያቂው ሐሳባቸውን የሚደግፍ ጥቅስ አልጠቀሱም፡፡ ጌታችን ለሰው ልጆች ኃጢአት ቤዛ በመሆን እንደሚሞት በተደጋጋሚ ተናግሯል (ማቴዎስ 20፡28፣ 26፡28፣ 14፡24፣ ማርቆስ 10፡45፣ ዮሐንስ 3፡14-15፣ 10፡11፣ 15፡30)፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ይጠብቃሉ፡፡ ትዕዛዛቱን የሚጠብቁት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ሳይሆን የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች ስለሆኑ ነው፡፡ ሕግን መጠበቅ የደህንነት መገለጫ እንጂ የደህንነት ማግኛ መንገድ አይደለም፡፡ እውነተኛ እምነት በሥራ የሚገለጥ እንጂ በቃል ብቻ የሚሆን ባለመሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንደዳነ የሚናገር ነገር ግን በእርሱ ትዕዛዝ የማይኖር ሰው ሲጀመር አላመነም፡፡  ከነፍስ የተለየ አካል የሞተ እንደሆነ ሁሉ ከሥራ የተለየ እምነትም የሞተ ነው (ያዕቆብ 2፡26)፡፡ በክርስቶስ እንዳመነ የሚናገር ነገር ግን በቀድሞ ክፉ ኑሮው የሚመላለስ ሰው በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ቦታ የለውም (1ቆሮንቶስ 6፡9-10፣ ኤፌሶን 2፡8-10)፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሕግን መሻር እንደማይገባቸው ነገር ግን ማፅናት እንደሚገባቸው አስተምሯል (ሮሜ 3፡31)፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ከኃጢአት ርቀው የሚኖሩት እንደሆኑም አፅንዖት ሰጥቷል (ሮሜ 8፡1-23)፡፡ እስልምና ሰው ገነት የሚገባው ሕግን በመጠበቅ እንደሆነ ሲያስተምር ክርስትና ግን አማኞች ሕግን የሚጠብቁት በክርስቶስ ሥራ በኩል ገነት መግባታቸውን ስላረጋገጡ እንደሆነ ያስተምራል፡፡ ደህንነት በእስልምና የሰው ሥራ ነው፤ በክርስትና ግን የእግዚአብሔር ሥራ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ ፍጹም እንከን የለሽና ዋስትና ያለው ነው፡፡ የሰው ሥራ ግን መቼም ቢሆን ፍጽምና ሊኖረው ስለማይችል ለእግዚአብሔር መንግሥት ሊያበቃ የሚችል ዋስትና የለውም፡፡ ለዚህ ነው ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች በተጻራሪ ወደ ገነት ስለመግባታቸው እርግጠኞች ያልሆኑት፡፡

  1. ዮሐንስ 17፡26 ላይ ምጽሐፍ ቅዱስ “ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፤ እኔም በእነርሱ እንዲሆን፤ አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ እንዲያውቁህም አደርጋለሁ፡፡” ይላል፡፡ ኢየሱስ “አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ” ሲል ነቢይ እንደመሆኑ የርሱ ተግባር ስለ አምላክ ለሕዝቡ ማሳወቅ መሆኑን ገለጸ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ወደ ፊትም ስለ አምላክ የማሳወቁን ሥራ እንደሚቀጥልበት “እንዲያውቁህም አደርጋለሁ፡፡” ሲል የአምላክ ታማኝ አገልጋይ መሆኑን አረገግጧል፡፡ ታዲያ ኢየሱስ የአምልክ አጋልገይና ሕዝቡ ስለ አምላክ እንዲያውቅ ማድረግ ተግባሩ ከሆነ እንዴት ራሱ አምላክ ሊሰኝ ይችላል?

ኢየሱስ አብን ያሳወቀው ነቢያት ባሳወቁት መንገድ ባለመሆኑ የእርሱ ማንነት፣ ሥልጣንና ኃይል ከነቢያት በእጅጉ የላቀ የሆነውን ያህል ተልዕኮውም ከእነርሱ የላቀ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ እርሱ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ነው (ዮሐንስ 3፡16)፡፡ ከአብ ጋር ሲኖር ስለነበር አብን አይቶታል (ዮሐንስ 6፡46)፡፡ እርሱ በአብ አብም በእርሱ እንደመኖሩ መጠን እርሱን ያየ ሰው አብን አይቶታል (ዮሐንስ 14፡9)፡፡ ከእርሱ በስተቀር አብን በትክክል የሚያውቅ የለም፤ እርሱ ሊገልጥለት ከወደደው በስተቀር፤ ማለትም ያለ እርሱ በጎ ፈቃድ አብን ማወቅ የሚችል ማንም የለም (ሉቃስ 10፡22)፡፡ የእግዚአብሔር የመጨረሻው መገለጥ የሆነው ኢየሱስ እንደሌሎች ነቢያት ሳይሆን ሁሉን ወራሽ፣ የዓለማት ፈጣሪና የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡- “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፡፡” (ዕብራውያን 1፡1-2)፡፡ ኢየሱስ አብን ያሳወቀበት መንገድ መለኮታዊነቱን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ጠያቂው የጠቀሱት ጥቅስ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ሲገናዘብ እሳቸው የተረዱትን ሳይሆን ተፃራሪውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

  1. በማቴዎስ 12፡49-50 ላይ “በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፡፡ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፤ ወንድሜ፤ እህቴና እናቴም ነው፡፡” ይላል፡፡ ታድያ የአምላክን እህትና ወንድም ሊሆኑ ነዋ? ወይስ የእምነት ወንድምና እህት ለማለት ነው? እንዲያማ ከሆነ የኢየሱስ እምነት የሐዋርያት እምነት ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ ክርስቲያኖች “ኢየሱስ አምላክ ነው” ስለሚሉ አምላክ ሃይማኖትን ይከተላል፤ አማኝ ነው ማለት ነውን? ገነት የሚገባው የራሱን ፊቃድ የሚደርገው ሳይሆን “በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ” ነው በማለት የአባቱን ፍቃድ የፈጸሙት መሆኑን ሲገልጽ ሐዋርያቶች እርሱ ማን መሆኑን ያውቁ ዘንድ ፈልጎ ይሆን?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፤ ወንድሜ፤ እህቴና እናቴም ነው” ሲል ሁለት ነገሮችን ለማመልከት ነው፡፡ የመጀመርያው በምድር ላይ በነበረ ጊዜ እንደ ማንኛውም ሰው ቤተሰብ ስለነበረው የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈፅሙትን ሰዎች እንደ ቤተሰብ እንደሚቆጥርና ከሥጋ ቤተሰቡ ለይቶ እደማያይ ለመናገር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አማኞች የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል የመሆናቸውን የላቀ ክብር ለማሳየት ነው፡፡ በሰማያት ያለው የአባቱ ፈቃድ ምን እንደሆነ ኢየሱስ ራሱ ስለነገረን መገመት አያስፈልገንም፡- ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፡፡” (ዮሐንስ 6፡39)፡፡ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል መሆን የሚቻለው በልጁ በማመን በመሆኑ ከእርሱ ጋር የሚኖረንን ቤተሰባዊ ቅርበት የገለጠበትን ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ቃል በቃል በመውሰድ ልጁን በአማኞች መደብ ውስጥ መደመር መሠረታዊ የግንዛቤ ችሎታን ከማጣት ይቆጠራል፡፡

  1. በማርቆስ 11፡20-23 ላይ “በማግስቱ ጠዋት በመንገድ ሲያልፉ፤ በለሊቱ ከነሥሯ ደርቃ አዩ፡፡ ጴጥሮስ ነገሩ ትዝ አለውና ኢየሱስን ፤ “መምህር ሆይ! እነሆ የረገምሃት በለስ ደርቃለች” አለው፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “በእግዚአብሔር እመኑ፤ እውነት እለችኋለሁ፤ ማንም ይህን ተራራ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር” ቢለውና ይህንንም በልቡ ሳይጠራጠር ቢያምን ይሆንለታል፡፡” የሚል ጥቅስ ተገልጿል፡፡ ኢየሱስ ለምን እንዲህ አለ? ጴጥሮስ የኢየሱስ እርግማን መፈጸሙን በመገረም ሲነግረው፣ እንደይገረምና ኢርሱም እንዴት ሊፈጽምለት እንደቸለ አይደል ሊገልጽ የፈለገው? ኢየሱስ፡፡ “በእግዚአብሔር እመኑ፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ይህን ተራራ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር” ቢለውና ይህንንም በልቡ ሳይጠራጠር ብያምን ይሆንለታል” ሲል ራሱ በማመኑ እርግማኑ መሳካቱን ገልጿል፡፡ ታድያ በእግዚአብሔር የሚያምነው ኢየሱስ ራሱ አምላክ ነው ሊባል ይችላልን?

ኢየሱስ ስለ ደቀ መዛሙርቱ እምነት እንጂ ስለ ራሱ እምነት እየተናገረ አይደለም፡፡ ኢየሱስ ስለ ራሱ እምነት እንኳ ቢናገር ይህ አምላክነቱን አጠራጣሪ አያደርግም፡፡ ፍፁም ሰው እንደ መሆኑ መጠን በምድር ላይ በነበረ ጊዜ የአብን ፈቃድ ብቻ በማድረግ እና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመታገዝ መሲሃዊ አገልግሎቱን ሲፈፅም ነበር፡፡ ስለዚህ በአብ በማመን ተዓምራትን እንደሚያደርግ ቢናገር እንኳ ምንም የሚያስከትለው ችግር የለም፡፡ እርሱ ብቸኛው የእግዚአብሔር አካል ነው ብንል እና ስለ ገዛ እምነቱ ቢናገር ራሱን ስለሚያምን አሁንም ችግር አይፈጥርም፡፡ ምናልባት የአሕመዲን አምላክ በራሱ አምላክነት እና የማዳን ችሎታ አያምን እንደሆን ግልፅ አይደለም፡፡

  1. ማርቆስ 10፡13-14 ላይ “ኢየሱስም እንዲዳስሳቸው፣ ሰዎች ሕጸናትን ወደርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው፤ ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግስት  እንደነዚህ ላሉት ናትና” ይላል፡፡ የውርስ ኃጢአት እሳቤ እንደሚለው ደግም ሰው ሁሉ ሲወለድ ከኃጢአት ጋር ነው፡፡ ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ሕፃናት ከነውርስ ኃጢአታቸው ለምን  “የእግዚአብሔር መንግስት እንደነዚህ ላሉት ናት” አለ? ሕፃናቱ ራሳቸውን አውቀው ገና “በማመን” የውርስ ኃጢአታቸውን አላስተሰረዩ? በዚህም ላይ ደግም ኢየሱስ ይህን የተናገረው ገና ተሰቀለ ከመባሉ በፊት ስለሆነ እንዴት  የህፃናቱ ንፁህነት ገለፀ? ለመሆኑስ የውርስ ኃጢአት  የሚባል ነገር ለአእምሮ አይጎረብጥምን?

ጌታችን በዚህ ቦታ እየተናገረ ያለው እንደ ህፃናት በቅንነትና በየዋህነት እውነተኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል እንደሚገባን ነው፡፡ የጌታችን መልእክት አንኳር ነጥብ ይህ ሲሆን እግረ መንገዱን ህፃናት እንደሚድኑ ያመላከተ ይመስላል፡፡ የውርስ ኃጢአት እና የህፃናት ደህንነት ጉዳይ የብዙዎች ጥያቄ በመሆኑና በክርስቲያን-ሙስሊም ውይይት ወቅት ተደጋግሞ ከመነሳቱ አንፃር በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ የምናምነውን ሐሳብ ማስቀመጥ አስፈላጊ መስሎ ይታየናል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ህፃናት ሲወለዱ ከኃጢአት ነፃ አይደሉም (መዝሙር 51፡5)፡፡ እያንዳንዱ ሰው የአዳምን የኃጢአት ውጤት ይወርሳል (ሮሜ 5፡12-21)፡፡ ሰው ሁሉ በፍጥረቱ የቁጣ ልጅ ነው (ኤፌሶን 2፡3)፡፡ ጌታችን ህፃንና አዋቂ በማለት ሳይለይ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ ይችሉ ዘንድ ዳግመኛ መወለድ እንደሚያስፈልጋቸው አስተምሯል (ዮሐንስ 3፡1-12)፡፡  ይህ አቋም ህፃናት በክርስቶስ አምነው ዳግመኛ የመወለድን ውሳኔ ማድረግ የሚያስችላቸው የአዕምሮ አቅም ስለሌላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገቡም ወደሚል ድምዳሜ የሚያመራ ይመስላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ፍርድ ደግሞ ፍትሃዊ ከሆነው አምላክ የሚጠበቅ ባለመሆኑ ጥያቄን ያስነሳል፡፡

ለዚህ ጥያቄ ሁለት መልሶች አሉ፡፡ የመጀመርያው እግዚአብሔር ለህፃናት ለደህንነታቸው የሚሆነውን እምነት የመስጠት ስልጣንና ችሎታ አለው የሚል ነው፡፡ ለዚህ ድጋፍ የሚሰጥ አንድ ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል (መዝሙር 22፡9-10)፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ባይገባንም እግዚአብሔር ይህንን ማድረግ እንደሚችል በመጠራጠር ሁሉን ቻይነቱን መዘንጋት የለብንም፡፡

ሁለተኛው መልስ ክፉና ደጉን መርጦ የመሥራት አዕምሯዊ ብቃት የሌላቸውን ሰዎች እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ያስተሰርይላቸዋል የሚል ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፈሪሳውያን ጥያቄ መልስ በሰጠ ጊዜ ይህንን ጉዳይ ግልፅ አድርጓል፡- “ኢየሱስም አላቸው፡- ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን፦ እናያለን ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል፡፡” (ዮሐንስ 9፡41)፡፡ በሌላ አባባል ሰው ክፉውንና ደጉን የመለየት አዕምሯዊ ብቃት ከሌለው ኃጢአቱ አይኖርም (ይስተሰረይለታል) ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ወንጌልን ያልሰሙ ሰዎች ለምን እንደሚፈረድባቸው በተናገረበት ክፍል ላይ ወደ ተመሳሳይ ድምዳሜ የሚመራ ነጥብ አስቀምጧል፡- “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ፡፡” (ሮሜ 1፡21)፡፡ እነዚህ ሰዎች በተፈጥሮ ከሚገኘው መገለጥ የእግዚአብሔርን መኖር እና ታላቅነቱን ቢገነዘቡም ነገር ግን ተገቢውን ክብር ሊሰጡት ስላልወደዱ ከእግዚአብሔር ፍርድ ለማምለጥ ምንም የሚያመካኙት ነገር አይኖራቸውም፡፡ በሌላ አባባል የእግዚአብሔርን መኖር እና ታላቅነቱን ማወቅ የሚችሉበት ምንም መንገድ ባይኖርና ያንን የመገንዘብ ተፈጥሯዊ ችሎታ ቢጎድላቸው ከእግዚአብሔር ፍርድ ለማምለጥ የሚያመካኙት ነገር (Excuse) ይኖር ነበር ማለት ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር ህፃናትን ጨምሮ ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች ቢሆኑም እግዚአብሔር የሚፈርደው ክፉና ደጉን የመምረጥ የግንዛቤ ደረጃ ባላቸው ሰዎች ላይ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ኃጢአትን የመሥራት ዝንባሌ በተግባር የሚሠራበት ዕድሜ ላይ ያልደረሱትን ህፃናት እግዚአብሔር ወደ ገሃነም አይልክም፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ህፃናት ወደ መንግሥቱ እንደሚገቡ ማመላከቻ የሰጠው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የውርስ ኃጢአት ስለሌለባቸው ሳይሆን የውርስ ኃጢአታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት ስለሚነፃ ነው፡፡ ይህንን የምንልበት ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ የመዳኛ መንገድ እንደሌለ ስለሚናገር ነው (የሐዋርያት ሥራ 4፡12፣ ዕብራውያን 9፡22-26)፡፡ መንገድም እውነትም ሕይወትም እርሱ ነው፡፡ በእርሱ በኩል ካልሆነ በስተቀር ማንም ወደ አብ መምጣት አይችልም (ዮሐንስ 14፡6)፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት ከእርሱ በፊት ለነበሩት ሰዎችም ሆነ ከእርሱ በኋላ ለመጡት ሰዎች ሁሉ የመዳን መንገድ ነው (ዕብራውያን 9፡26)፡፡ የኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከዛሬ 2000 ዓመታት በፊት የተከናወነ ቢሆንም ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ዕቅድ ውስጥ የነበረ ነው (ራዕይ 13፡8፣ የሐዋርያት ሥራ 4፡27-28)፡፡

አንድ ነገር ልክ ወይም ስህተት መሆኑ የሚወሰነው በሰው ስሜት እና ምርጫ ላይ ተመስርቶ ባለመሆኑ የውርስ ኃጢአት እሳቤ ለአንዳንዶች አዕምሮ “መጎርበጡ” ትክክል እንዳይሆን አያደርገውም፡፡ በእስልምና የውርስ ኃጢአት እሳቤ እንደሌለ ቢነገርም ነገር ግን የእስልምና መጻሕፍት ይህንን አያመለክቱም፡፡ ሙስሊሞች የውርስ ኃጢአትን መካዳቸው በተፈጥሮ ከሚታያው እውነታ ጋር ብቻ ሳይሆን ከቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸው ጋርም ጭምር እንዲጣሉ ያደርጋቸዋል፡፡

“ከርሷም ሰይጣን አዳለጣቸው በውስጡም ከነበሩበት (ድሎት) አወጣቸው፡፡ «ከፊላችሁም ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ፤ ለናንተም በምድር ላይ እስከ ጊዜ (ሞታችሁ) ድረስ መርጊያና መጣቀሚያ አላችሁ» አልናቸው፡፡ አደምም ከጌታው ቃላትን ተቀበለ፡፡ በርሱ ላይም (ጌታው ጸጸትን በመቀበል) ተመለሰለት፤ እነሆ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡ «ሁላችሁም ኾናችሁ ከርሷ ውረዱ፡፡ ከኔም የኾነ መመሪያ ቢመጣላችሁ ወዲያውኑ መመሪያዬን የተከተለ ሰው በነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም» አልናቸው፡፡” (ሱራ 2፡36-38)፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሚገኘው “ሁላችሁም” የሚለው በአረብኛ ከሁለት በላይ ቁጥርን የሚያመለክት ሲሆን ፍርዱ በአዳም እና በሔዋን ብቻ ያልተወሰነ መሆኑን ያሳያል፡፡[1] አላህ የአዳምን ንስሐ እንደተቀበለ ተነግሯል ነገር ግን ከገነት መባረሩ አላህ ኃጢአቱን ይቅር እንዳላለ ያሳያል፡፡ ኃጢአቱን ይቅር ቢለው ኖሮ ለምን ወደ ገነት አልመለሰውም ነበር? ፀፀቱን ተቀብሎ ኃጢአቱን ይቅር ከማለት ይልቅ ፀፀቱን ተቀብሎ ወደ ፊት ለዘሮቹ የሚሆን መመርያ ለመስጠት እና ይህንን መመርያ የተከተለውን ሰው ብቻ ለመማር እንደወሰነ ከጥቅሱ እንረዳለን፡፡

ቲርሚዚ ሐዲስ አዳም የሰራው ኃጢአት ወደ ዘሮቹ ሁሉ መተላለፉን እንዲህ በማለት ይገልፃል፡- “አደም ስለ ካደ ዘሮቹ ሁሉ ካዱ፡፡ አደም ዝንጉ በመሆን የተለከለከለውን ዛፍ ስለበላ ዘሮቹም ዝንጉዎች ሆኑ፡፡ አዳም ስለተሳሳተ ዘሮቹ ሁሉ ስህተት ፈፀሙ፡፡”[2]

አልቡኻሪ ደግሞ ሙሴ አዳምን “ከገነት እንድንባረር ያደረከን አንተ አባታችን ነህ” በማለት በወቀሰው ጊዜ አዳም መልሶ “አላህ ከመፈጠሬ ከአርባ ዓመታት በፊት ወስኖልኝ ለጻፈብኝ ነገር ትወቅሰኛለህን?” በማለት እንደመለሰለት ዘግቧል፡፡[3]

ሳሂህ ሙስሊም “ከገነት ያስባረራችሁ የአባታችሁ የአደም ኃጢአት ነው” ይላል፡፡[4]

እስላማዊ ምንጮች ከዚህም አልፈው ሴቶች “እስከዛሬ ድረስ ለሚያሳዩት ጸባይ” ሔዋንን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡-

“አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- በእስራኤል ልጆች ምክንያት ባይሆን ኖሮ ሥጋ ባልበሰበሰ ነበር፡፡ በሐዋ ምክንያት ባይሆን ኖሮ የትኛዋም ሴት ባሏን ባልከዳች ነበር፡፡”[5]

በተጨማሪም አል-ጦበረኒ የተሰኘ ጥንታዊ ሙስሊም ጸሐፊ ሴቶች የወር አበባ የሚፈስሳቸውና “በአስተሳሰብ ደካማ የሆኑት” በሔዋን ምክንያት እንደሆነ ጽፏል፡፡[6]

በቁርኣን መሠረት ሰው “ቅጠ ቢስ ሆኖ ተፈጠረ” (ሱራ 70፡19-24)፡፡ “ደካማ ሆኖ ተፈጠረ” (ሱራ 4፡28)፡፡ “በልፋት ውስጥ ሆኖ ተፈጠረ” (ሱራ 90፡4)፡፡ በነዚህ ጥቅሶች መሠረት አላህ ሰውን ከፍጥረቱ ጀምሮ አበላሽቶታል ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ እንደፈጠረ እንጂ ከነዚህ ጉድለቶች ጋር እንደፈጠረ አይናገርም (ዘፍጥረት 1፡26)፡፡ ሰው ለነዚህ ጉድለቶች የተጋለጠው ነፃ ፈቃዱን ተጠቅሞ በኃጢአት ከወደቀ በኋላ ነው (ዘፍጥረት 3፡1-19)፡፡ ጠያቂያችን ክርስትናን ለመተቸት ከመነሳታቸው በፊት የገዛ ሃይማኖታቸውን መመርመር ነበረባቸው፡፡

  1. ዮሐንስ 14፡6 “ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ይለል፡፡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህን ጥቅስ ለኢየሱስ “አምላክነት” መከራከሪያ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ ኢየሱስ “መንገዱ እኔ ነኝ” አለ እንጂ “መድረሻ ነኝ” መች አለ? መንገድ አድረሽ ነው እንጂ መድረሻ አይደለም፡፡ ነቢያት ሁሉ ያስተምራሉ፤ ወደ አምላክ ጥሪ ያደርገሉ፡፡ ማንም ገነት ለመግባት የግድ የነቢያቱን መንገድ መከተል አለበት፡፡ ወደ አምላክ የሚያደርሱ መንገድ ናቸው፡፡ ታድያ ኢየሱስ “አምላክ ነኝ” መች አለ? ኢየሱስ በዘመኑ ብቸኛ የአምላክ መንገድ ነው፡፡ ያለርሱ መንገድነት በቀር (እርሱን ከመከተል ውጭ) ማንም ወደ አምላክ አይቀርብም፡፡ ኢየሱስ በግልጽ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሏል፡፡ ታድያ ክርስቲያኖች ምነው ይህን መመርመር አቃታቸው?

ይህ ጥቅስ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን እንደሚያሳይ ክርስቲያኖች የሚናገሩበት ምክንያት ፍጡር “እውነት እና ሕይወት” (The Truth and the Life) ተብሎ ሊጠራ እንደማይችል ስለሚያምኑ ነው፡፡ አሕመዲን እነዚህን ሁለቱን ነጥቦች ወደ ጎን በማድረግ “መንገድ” በሚለው ላይ ብቻ ማተኮራቸውን ልብ በሉ፡፡ ይህንን ያደረጉበት ምክንያት ደግሞ እነዚህ ቃላት በገዛ ሃይማኖታቸው መስፈርት መሠረት ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ስለሚያረጋግጡ ነው፡፡ ለማንም ፍጡር ሊሰጡ ከማይችሉ 99ኙ የአላህ ስሞች መካከል አል-ሐቅ (እውነት) እና አል-ሐዩን (ህያው የሆነው) የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በእስልምና እምነት መሠረት ከእነዚህ ስሞች መካከል አንዱን እንኳ በቁሙ ለፍጡር መስጠት ያንን ፍጡር አምላክ ማድረግ በመሆኑ ይቅርታ የሌለው “የሽርክ” ኃጢአት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቦታ ከተጠቀማቸው ማዕረጋት መካከል ሁለቱ በእስልምና ሃይማኖት መሠረት እንኳ አምላክነቱን የሚያሳዩ ሆነው ሳሉ አሕመዲን ሁለቱን አይተው እንዳላየ በመሆን አንዱን ብቻ ነጥለው ማውጣታቸው ለእውነት ያደረ ህሊና እንደሌላቸውና አወናባጅ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ሁለቱ ማዕረጋት አምላክ መሆኑን ስለሚያሳዩ ኢየሱስ “መንገድ” ተብሎ መጠራቱ ፍጡር መሆኑን አያሳይም፡፡ ይልቁኑ ሰው መዳንና አብን ማወቅ የሚችለው አንድያ ልጁ በሆነው እና በመለኮት ከእርሱ ጋር በተካከለው በእርሱ በኩል ብቻ መሆኑን ያሳያል፡፡ ኢየሱስ ማንም ሰው በእርሱ በኩል ካልሆነ በስተቀር ወደ አብ መምጣት እንደማይችል ተናገረ እንጂ ይህ ሥልጣኑ በጊዜ የተገደበ መሆኑን ስላልተናገረ የጠያቂው ትንታኔ ከገዛ ኪሳቸው የተገኘ እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ አይደለም፡፡ እውነት መንገድና ሕይወት እንደሆነ የተናገረ ነቢይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ሆነ በእስላማዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለመኖሩ የተጻፈ አንድ ማስረጃ ማቅረብ ይችሉ እንደሆን እንጠይቃቸዋለን፡፡

  1. ማርቆስ 15፡37 “ኢየሱስ በታላቅ ድምጽ ጮኾ ነፍሱን ሰጠ” ይላል፡፡ ለመሆኑ ነፍሱን ለማነው የሚሰጠው? ራሱ ለራሱ ነው ወይስ ሰጪውና ተቀባዩ የተለያዩ ናቸው?

ማርቆስ ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን መስጠቱን እንጂ ምን ብሎ እንደጮኸ አልነገረንም፡፡ ነገር ግን ሉቃስ ነግሮናል፡- “ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፦ አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ፡፡ ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ፡፡” (ሉቃስ 23፡46)፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ነፍሱን የሰጠው ለአብ ነው፡፡

  1. ማቴዎስ 3፡17 “እነሆ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምጽ ከሰማይ ተሰማ” ይላል፡፡ እውን ይህ ከሰማይ የተሰማው ድምጽ የአምላክ ነውን? አምላክ ልጅ አለኝ ይላልን?

ነቢያት ያሕዌ እግዚአብሔር ልጁን እንደሚልክ ተንብየዋል፡፡ ሐዋርያት የልጁን መምጣት መስክረዋል፡፡ ልጁ ከመጣ ከ 600 ዓመታት በኋላ መካ ውስጥ የኖረ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት ያልነበረው ሰው እግዚአብሔር ልጅ እንደሌለው ስለተናገረ ይህ እውነት አይለወጥም፡፡ እኛ ሕያው የሆነውን በባሕርይ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መንፈሳውያን ልጆቹ ያደረገንን አምላከ እስራኤልን እንጂ መካን አምላክ ስለማንከተል እንዲህ ያለውን ክህደት አንቀበልም፡፡

አሕመዲን ይቀጥላሉ፡- “ይህ ከሰማይ የተሰማው ድምጽ” የአምላክ ድምጽ አለመሆኑ እንዴት ይታወቃል? ኢየሱስን “የምወደው ልጄ” እያለው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ኢየሱስ ከዚህ ክስተት በኋላ በዮሐንስ 5፡37 እንዲህ ብሏል፦ የላከኝ አብ ራሱ ስለ እኔ መስክሮአል፤ እናንተ ከቶ ድምጹን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፡፡” ኢየሱስ እንዳለው የአብን (የአባቱን) ድምጽ ካልሰሙ ያ ድምጽ እውን ተሰምቷልን? ከሆነስ የማን ድምጽ ነው? የአሳሳቹ ሳይጣን ቢሆንስ?

የጠያቂው ሙግት እግዚአብሔር ልጅ እንዳለው ሊናገር አይችልም የሚል ሆኖ ሳለ በማቴዎስ 3፡17 ላይ ኢየሱስ ልጁ መሆኑን የተናገረው እግዚአብሔር አለመሆኑን ለማረጋገጥ ኢየሱስ እግዚአብሔርን “አብ” በማለት የጠራበትን ጥቅስ ጠቅሰዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት እርስ በርሱ የሚጠፋፋ ሙግት መጠቀማቸው ለክህደት ትምህርታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ዓይነት ክፍተት ባለመስጠቱ ተስፋ መቁረጣቸውን ያመለክታል፡፡

ኡስታዙ ኢየሱስ ልጁ መሆኑን ከሰማይ የተናገረው እግዚአብሔር ሳይሆን ሰይጣን ሊሆን ይችላል የሚል ዘግናኝ ክህደት “አከብረዋለሁ፣ እውነተኛ ነቢይ ነው” በሚሉት በኢየሱስ ላይ ተናግረዋል፡፡ ኢየሱስ በዚያ ቆሞ ሳለ “ሰይጣን ከሰማይ ሆኖ ‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው› አለው” ሲባል የሚሰሙ ሙስሊሞች ይህንን ስድብ እንዴት ያዩት ይሆን? እንዲህ ዓይነቱን ክህደት በጌታችን ላይ ሊናገር የሚደፍረው ገሃነም መግባቱን ያረጋገጠው ዲያብሎስ ብቻ ነው፡፡ አሕመዲን የአውሬው አፍ በመሆን ይህንን ስድብ በእግዚአብሔርና በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ተናግረዋል፡፡ ዳሩ ግን “እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ” ተብሎ እንደ ተጻፈ ስለምናውቅ አንደነቅም (ራዕይ 13፡6)፡፡ ሰውየው ግን ይህንን ድፍረት በመናገር በእግዚአብሔር የቁጣ እጅ በመውደቃቸው እናዝንላቸዋለን፡፡

ማቴዎስ ከሰማይ ድምፅ መምጣቱን እንጂ አይሁድ ድምፁን ስለመስማታቸው ስላልተናገረ ጠያቂው እንደ ልማዳቸው ያልተጻፈውን እያነበቡ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል የመውረዱ ምልክት የተሰጠው ለመጥምቁ ዮሐንስ በመሆኑ (ዮሐንስ 1፡33) ድምፁንም እርሱና ኢየሱስ ብቻ ሰምተው ሊሆን ይችላል፡፡ ኢየሱስ ሲጠመቅ በዚያ የነበሩት አይሁድ ድምፁን ሰምተዋል ቢባል እንኳ በዮሐንስ 5 ላይ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ የነበሩት ያኔ በቦታው ላይ የነበሩት አይሁድ ስለመሆናቸው እና ሌሎች ስላለመሆናቸው ተሳዳቢው ኡስታዝ ምን ማስረጃ አላቸው?

  1. ዮሐንስ 5፡20 “አብ ወልድን ስለሚወድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ትደነቁም ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ነገር ያሳየዋል” ይላል፡፡ ታድያ አምላክ ኢየሱስን የሚያደርገውን ቢያሳየውምና ተዓምር ቢያደርግ ምን ይገርማል? አምላክ ከዚህ በላይ ማድረግ አይችልምን? በግልጽ ለኢየሱስ አምላክ “የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል” ተብሎ የለምን?

እግዚአብሔር በፍጡራን ተጠቅሞ ተዓምራትን እንደሚያደርግ እንጂ ለፍጡራን ተዓምራትን እንዲያደርጉ እንደሚያሳያቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተነገረም፡፡ በዚህ ቦታ ግን አብ ለኢየሱስ የሚያደርገውን እንደሚያሳየውና ኢየሱስም ያንኑ እንደሚያደርግ ተጽፏል፡፡ ኢየሱስ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ማድረግ እንደሚችል አሕመዲን የዘለሉት ቀዳሚ ጥቅስ ይናገራል፡- “ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና” (ቁ.19)፡፡

በዚህ ክፍል ኢየሱስ አብ ሲያደርግ ያየውን እንጂ ከራሱ ምንም ማድረግ እንደማይችል መናገሩ ለአሕመዲን ክርክር እሳቸው ከጠቀሱት ክፍል ይልቅ ጠቃሚ ነበር፡፡ ነገር ግን የጥቅሱ ሁለተኛው ክፍል አብ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ወልድም ማድረግ እንደሚችል ስለሚናገር የኢየሱስን አምላክነት በማረጋገጥ ሐሳባቸውን ያፈርሳል፡፡ ስለዚህ ሊጠቅሱት አልወደዱም፡፡ በሥላሴ ውስጥ የማቀድ የሥራ ድርሻ የአብ ነው፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች አብ ልብ መሆኑን፣ ወልድ ቃል መሆኑንና መንፈስ ቅዱስ ደግሞ እስትንፋስ መሆኑን የተናገሩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የማቀድ የሥራ ድርሻ የአብ በመሆኑ ወልድ የሚፈፅመው በአብ የታቀደውን ነው፡፡ ስለዚህ አብ ሲሠራ ያየውን እንጂ ከራሱ አንዳች ማድረግ እንደማይችል መናገሩ በሥላሴ አካላት መካከል የሚገኘውን ፍፁም የሆነ መስማማት የሚያመለክት እንጂ የኃይል እጥረት እንዳለበት አያመለክትም፤ ምክንያቱም ሁሉን ቻይ የሆነው አብ የሚያደርገውን ሁሉ ማድረግ እንደሚችል በዚሁ ቦታ ተናግሯልና፡፡ እንደ አብ እርሱም ሁሉን ቻይ ካልሆነ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ማድረግ እንዴት ይቻለው ነበር?

ኢየሱስ በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ አምላክነቱን የሚያረጋግጡ ብዙ ንግግሮችን ተናግሯል፡-

  • “አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል፡፡” (ቁ. 21)፡፡ በገዛ ውዴታው ሕይወትን መስጠት የሚችል ከአምላክ በስተቀር ማንም የለም፡፡
  • “ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም፡፡” (ቁ. 22)፡፡[7] ኢየሱስ አምላክ ባይሆን ኖሮ ሰዎች አብን በሚያከብሩት በዚያው ሁኔታ መከበር እንደሚገባው ባልተናገረ ነበር፡፡
  • “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ፡፡” (ቁ. 25)፡፡ ሕይወት አልባ ሙታን ድምፁን እንዲሰሙ ማድረግ የሚችልና በድምፁ ብቻ ሕይወትን መስጠት የሚችል ከአምላክ በስተቀር ማንም የለም፡፡
  • “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ፡፡” (ቁ. 28-29)፡፡ በመጨረሻው ቀን ሙታንን የማስነሳት ኃይል እና ሥልጣን ያለው ከአምላክ በስተቀር ማንም ሊሆን አይችልም፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ከግምት ውስጥ ሲገቡ ኢየሱስ ከአብ ተነጥሎ መስራት እንደማይችል መነገሩ በሥላሴ አካላት መካከል የሚገኘውን ፍፁም መስማማት የሚገልፅ እንጂ መለኮትነቱን የሚፃረር አለመሆኑን እንገነዘባለን፡፡

  1. ዮሐንስ 5፡26-27 “አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤ ወልድ የሰው ልጅ ስለሆነም እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡” ይላል፡፡ ወልድ ሕይወት እንዴት ሊኖረው ቻለ? ጥቅሱ “ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና” ይላል!
    አብ የወልድ ሕይወት ምንጭ አይደለምን? ክርስቲያኖች እንደሚሉት ወልድ (ኢየሱስ) የመፍረድ ሥልጣን ያገኘው አምላክ ስለሆነ ነውን? ጥቅሱ ወልድ “አምላክ” ስለ ሆነ ነው ይላልን? በፍፁም! “ወልድ የሰው ልጅ ስለሆነም” እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡” ነው የሚለው፡፡ ሳይሰጠው በፊትስ? ታዲያ ክርስቲያኖች ምነው ቆም ብለው ቢያስተነትኑት?

በዘለዓለማዊ መገኘት ከአብ የተገኘው ኢየሱስ እንደ አብ ሁሉ እርሱም በራሱ ሕይወት አለው፡፡ ይህ ማለት ለመኖር በማንም ላይ ጥገኛ ያልሆነው የአብ ሕይወት የወልድም ሕይወት ነው ማለት ነው፡- “እግዚአብሔርም የዘለዓለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው፡፡ ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም፡፡” (1ዮሐንስ 5፡11-12)፡፡

“የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው” (ቁ. 27)፡፡ ጌታችን በዚህ ቦታ የሰው ልጆችን ሁሉ የሚገዛው በዳንኤል 7፡13-14 ላይ የተጠቀሰው የሰው ልጅ ተብሎ የተጠራው መለኮታዊ አካል መሆኑን መናገሩ አምላክነቱን ያሳያል፡፡

ማጣቀሻዎች


[1] Tafsir Ibn Kathir, Abridged: part 1, Surah Al-Fatiah Surah Al-Baqarah, ayat 1 to 141, pp. 109-110

[2] Al-Tirmidhi Hadith, Number 37; (ALIM CD ROM Version)

[3] Sahih al-Bukhari, Volume 8, Book 77, Number 611

[4] Sahih Muslim, Book 001, Number 0380

[5] Sahih al-Bukhari, Volume 4, Book 55, Number 611. Sahih Muslim Book 008, Number 3472

[6] The History of Al-Tabari: General Introduction from the Creation to the Flood, Translated by Franz Rosenthal, SUNY press, Albany, 1998, Volume 1, pp. 280-281

[7] “For the Father judgeth no man, but hath committed all judgment unto the Son: That all men should honour the Son, even as they honour the Father. He that honoureth not the Son honoureth not the Father which hath sent him.” (John 5:22-23) KJV

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ