ምዕራፍ 6 የምስጢረ ሥላሴ ምስጢር: ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ

ምዕራፍ 6

የምስጢረ ሥላሴ ምስጢር

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ ካቆምንበት እንቀጥላለን

  1. የሥነ-መለኮት ምሁር የሆኑት ዶክተር ፓውል እንዝ “ታሪካዊ ሥነ-መለኮት አመጣጡና ትንተናው” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ “የኒቅያው (Nicea) ጉባኤ በ 325 ዓ.ም ታሪካዊውን አስተምህሮ-ሥላሴ አፀደቀ፡፡ በዚህም መሠረት ክርስቶስ ከአብ ጋር የባሕርይ እኩልነት ያለው መሆኑ ግንዛቤ አገኘ፡፡” ሲሉ ጽፈዋል፡፡ በኒቅያው ጉባኤ መሠረት “ክርስቶስ ከአብ ጋር የባሕሪይ እኩልነት ያለው መሆኑ” ግንዛቤ ሳያገኝ በፊት ቤተክርስቲያን የሥላሴን እምነት ሳይሆን የአንድን አምላክ ኃያልነትና ብቸኝነት ስታስተምር ተሳስታ ነበርን? ከኒቂያ ጉበኤ በፊት የነበሩት አማኞችና ሐዋርያትና የኢየሱስን በባህሪ ከአብ ጋር መስተካከል ሳይረዱትና ግንዛቤውን ሳያገኙ ቆይተው በኒቅያ ጉበኤ ተገኝተው በድምጽ ብልጫ የወሰኑት 300 ጳጳሳት ግንዛቤውን አገኙን? እምነት የሚጸድቀው እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በጉባኤ ነው ወይስ በአምላክ ትእዛዝ?

የኒቅያ ጉባኤ የተደረገው አርዮስ የተሰኘ የአሌክሳንደርያ ሰው የኢየሱስን ዘለዓለማዊነትና ፍፁም አምላክነት ክዶ በማስተማር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የፈጠረውን ክፍፍል መርምሮ ለማውገዝ ነበር፡፡ ጉባኤው እንዲደረግ ያስገደደው የአርዮስ ትምህርት በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ምዕመናን መካከል መስፋፋቱ እንጂ በሥላሴ አስተምህሮ ላይ ከዚያ ቀደም ጥርጥር ኖሮ አይደለም፡፡ በአንደኛውና በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ሥላሴን የተመለከተ አስተምህሮ እንደ ችግር ሆኖ አልተዘከረም፡፡[1] የአርዮስ ትምህርት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል ማስነሳቱና የጉባኤ ምክንያት መሆኑ በራሱ ትምህርቱ አዲስ እንደነበረና ከዚያ ቀደም ከነበረው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር የሚጣረስ መሆኑን ያመለክታል፡፡ አርዮስ የኢየሱስን ፈጣሪነት ያልካደ ሲሆን በአብ “የተፈጠረ ፈጣሪ” መሆኑን ነበር ያስተማረው፡፡ ይህንን ትምህርት እንዲቀበል የኖስቲሳውያን አስተምህሮ ተፅዕኖ አሳድሮበታል፡፡[2]

ዶ/ር ፓውል “ክርስቶስ ከአብ ጋር የባሕርይ እኩልነት ያለው መሆኑ ግንዛቤ አገኘ” ሲሉ ከዚያ ቀደም የማይታወቅ አዲስ ነገር መሆኑን ለመናገር ፈልገው አይደለም፡፡ ጠያቂው ጽሑፉን ቆርጠው ስለጠቀሱት ነው እንጂ ሙሉ ሐሳባቸው እንደርሱ አይልም፡፡ ጠያቂው ከጠቀሱት ክፍል አንድ መስመር ከፍ ብለው “አስተምህሮ-ሥላሴም አርዮስ ከተባለ ሰው ተግዳሮት ገጠመው” በማለት አስተምህሮተ ሥላሴ ቀደም ሲል የነበረ ትምህርት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኢየሱስ ከአብ ጋር በባሕርዩ የተካከለ መሆኑና የሥላሴ አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ የተጠቀሱ እውነታዎች ናቸው፡፡ ቅድመ ኒቅያ በነበሩት የአበው ጽሑፎች ውስጥም እናገኛለን፡፡ ይህንን በተመለከተ ጠያቂው የጠቀሱት መጽሐፍ ገፅ 19 “የሐዋርያት አባቶች ትምህርተ እግዚአብሔር” በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር እዲህ ይላል፡- “በሥላሴዎች የማመኑ ጉዳይ የጸና ነው፤ ቀለሜንጦስ የሥላሴን እኩልነት ሲገልጥ፡- ‹‹እግዚአብሔር አብ ሕያው እንደሆነ ጌታ ኢየሱስም ሕያው ነው፤ መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ፤ እነርሱ የምርጦቹ እምነትና ተስፋ ናቸው፤ የአጥናፈ ዓለሙ ፈጣሪና ጌታ፤ እግዚአብሔር ነው›› ብሏል፡፡”[3] ይህ የሮማው ቀለሜንጦስ መልዕክት የተጻፈው በ97 ዓ.ም. ነበር፡፡[4] “የሐዋርያት አባቶች ትምህርተ ክርስቶስ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡- “ስለ ክርስቶስ ያሉት እምነቶች የፀኑና የሚደነቁ ናቸው፡፡ አግናጢዎስ የክርስቶስን መለኮትነት አስመልክቶ ታላቅ ቁምነገሮችን ተናግሯል፡፡ ወደ ሮምና ወደ ኤፌሶን በጻፋቸው ደብዳቤዎቹ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ የኛ አምላክ›› ብሏል፡፡ በአማኞች ስለማደሩ ደግሞ ‹‹እርሱ ራሱ እንደ አምላካችን በእኛ ውስጥ ይኖር ዘንድ›› ካለ በኋላ ክርስቶስ የአብ ‹‹አሳብ››፣ ‹‹የእግዚአብሔር ጥበብ›› እንደሆነና ‹‹ዓለም ሳይፈጠር በፊት ከአብ ጋር እንደነበር›› እንዲሁም ‹‹ወልድነቱን›› ገልጧል፡፡ ፖሊካርፕ የተባለው ሌላ ጸሐፊ ደግሞ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ የኛ አምላክና ጌታ›› ብሏል፡፡ ቀለሜንጦስ እንዲሁ ‹‹ኢየሱስ ከአብ የተላከ›› መሆኑን ገልጧል፡፡”[5] የኢግናጢዎስ መልዕክት በ100 ዓ.ም.[6] የፖሊካርፕ 108 ዓ.ም.[7] የተጻፉ ናቸው፡፡

እምነት የሚጸድቀው እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ ባስቀመጠው መልዕክት ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን መልዕክት ሰዎች ሊገባቸው በሚችል እና ለስህተት አስተማሪዎች ክፍተት ሊሰጥ በማይችል መልኩ በእምነት መግለጫ መልክ ለማስቀመጥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኦፊሴላዊ ጉባኤ ማድረጋቸው ስህተቱ ምኑ ላይ ነው?

2. ዶክተር ፓውል እንዝ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “በአርዮስ ትምህርት የተነሳ የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት በ325 ዓ.ም ኒቅያ በተባለው ስፍራ አንድ ጉባኤ ተካሄደ ፡፡ በጉባኤው ላይ 300 ጳጳሳት ተገኝተው ነበር፡፡ ጉባኤው አርዮስንም ሆነ አርዮሳዊነትን የሚቀበሉትን ሁሉ አውግዟል፡፡ በንጉሡ ካስፀደቀ በኋላም የሚከተለውን የሃይማኖት መግለጫ አወጣ፡-

ሁሉን በሚችል የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በአንዱ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከአብ ብቻውን በተገኘው ከአብ ጋር መገኛው (ኡሲያስ / ousias ) አንድ በሆነው፣ ከአምላክ በተገኘው አምላክ፣ ከብርሃን በተገኘ ብርሃን፣ ከእውነትኛ አምላክ በተገኘ እውነተኛ አምላክ፣ በተፈጠረ ሳይሆን በተወለደ፣ ከአብ ጋር በማንነት (Homoousion) አንድ በሆነ፣ ሁሉ በእርሱ በሆነ፣ በሰማይም ይሁን በምድር ባለው፣ ለእኛ ለሰው ልጆች ደህንነት ወርዶ ሥጋ በሆነ፣ ሰውም በሆነ፣ መከራን በተቀበለበት በሦስተኛውም ቀን በተነሳ፣ ወደ ሰማይ ባረገ፣ በሙታንና በሕያዋን ላይ ሊፈርድ በሚመጣው እናምናለን፡፡” ( ዶክተር ፓወል እንዝ ፣ ታሪካዊ ሥነ- መስኮት አመጣጡና ትንተናው ፣ ገጽ 33 – 34)፡፡

ሀ. ይህ የኒቂያ ጉባኤ ራሱ “በእግዚአብሔር አብ እናምናለን” እንጂ “አንድ እግዚአብሔር በሚሆኑት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፡፡” እንደማይል አስተውለዋልን?

የኒቅያ ጉባኤ ትኩረት ኢየሱስ ከአብ ጋር በባሕርይ አንድ ነው (Homoousion) ወይስ ተመሳሳይ (Homoiousion)? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ስለነበር መግለጫው የሥላሴን ትምህርት በመተንተን ላይ አላተኮረም፡፡ ከላይ በተጠቀሰው የኒቅያ የእምነት መግለጫ ውስጥ “ከአብ ጋር በማንነት (Homoousion) አንድ በሆነ” ተብሎ የተተረጎመው “በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል” ተብሎ ቢተረጎም የተሻለ ይሆናል፡፡ የአገራችን የሥነ መለኮት ሊቃውንትም ከጥንት ጀምሮ ይህንን ቃል ሲተረጉሙ የነበሩት በዚያው መልኩ ነው፡፡

ለ. በዚህ መግለጫቸው ኢየሱስን “ከአምላክ በተገኘው አምላክ” ሲሉት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለውንና ኢየሱስ ራሱ ያላስተማረውን በመግለጫቸው ስላካተቱ እውነት ይሆናል? “ከአምላክ በተገኘው አምላክ” ሲሉም የተገኘ መሆኑን አምነዋል፡፡ ነገር ግን መልሰው ያልተገኘውን ኢየሱስን (እንደነርሱ አባባል) “አምላክ” አሉት፡፡ አምላክ ሕልውናው ዘለዓለማዊ ነው፡፡ ኢየሱስ ግን የተገኘ ነው፡፡ የተገኘና ዘለዓለማዊ ያልሆነው ኢየሱስ “አምላክ” ስለተባለ ብቻ አምላክ ሊሆን ይችላልን?

“የተገኘ” የሚለው ቃል በጊዜ የተገደበ መገኘትን ሳይሆን ዘለዓለማዊ መገኘትን ስለሚያመለክት የኢየሱስ ሕልውና ዘለዓለማዊ አለመሆኑን አያመለክትም፡፡ ይህ መገኘት ዘለዓለማዊና በጊዜ ያልተገደበ ሲሆን የኢየሱስን መለኮታዊ ባሕርይ ከአብ አያሳንስም፡፡ አብ ያሉት ባሕርያተ መለኮት ሁሉ ወልድም አሉት፡፡ አብ በጊዜ ባልተገደበ ከዘለዓለም ዘመናት በፊት ሲያበራ በነበረ ኮከብ የሚመሰል ሲሆን ወልድ ደግሞ ከኮከቡ በሚወጣው ብርሃን ይመሰላል፡፡ በኮከቡና በብርሃኑ መካከል የጊዜ መቀዳደም የለም፡፡ ነገር ግን ብርሃኑ ከኮከቡ የተገኘ ነው፡፡ ኮከቡ ያለብርሃን እውነተኛ ኮከብ ሊሆን አይችልም፡፡ ብርሃኑም ያለ ኮከቡ ሊኖር አይችልም፡፡ አብና ወልድም እንደዚያው ናቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ የተገኘ መሆኑን ደጋግሞ በመናገሩ ጠያቂው ትምህርቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሌለና ኢየሱስ እዳላስተማረ መናገራቸው ቅጥፈት ነው፡፡ “ኢየሱስ አብ ሁሉን በእጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ…” (ዮሐንስ 13፡3)፡፡ “እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና” (16፡27-28)፡፡ “ኢየሱስም አላቸው፦ እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና” (8:42)፡፡ “ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ” (16:28)፡፡ “ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ” (17፡8)፡፡

 ለተጨማሪ ማብራርያ ለጥያቄ ቁጥር 75 የተሰጠውን መልስ ይመልከቱ፡፡

ሐ. “ኢየሱስ የተወለደ ነው” ግና አልተፈጠረም ሲሉ፡- “በተፈጠረው ሳይሆን በተወለደ” ብለዋል፡፡ “ተወለደ” ስንል ከመወለዱ በፊት ነበርን? “በተፈጠረ ሳይሆን” የተባለበት ምክንያት “ተፈጠረ” ካልን “ፍጡር” እንዳይሰኝ ነውን? “ፍጡር” ስላላልን መሆኑ ይቀራልን?

“መወለድ” የሚለው ቃል ኢየሱስ ከአብ ባሕርይ በዘለዓለማዊ መገኘት (Eternal Generation) የተገኘ መሆኑን ለማመልከት በመሆኑ ጊዜን አያመለክትም፡፡ ጠያቂው ቃላትን በራሳቸው መንገድ ከመተርጎም ይልቅ የእምነት መግለጫውን ያወጡት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለማለት የፈለጉትን ለመረዳት ቢሞክሩ መልካም ነበር፡፡

መ. በመግለጫው እንደተባለው “ለእኛ ለሰው ልጆች ደህንነት ወርዶ ሥጋ በሆነ፣ ሰውም በሆነ” ኢየሱስ ለሰው ልጅ ደህንነት ሲል ወርዶ ሥጋ ከሆነ ወደ ሰማይ አርጎ ለምን ሰውነቱን (ሥጋውን) ትቶ ከመውረዱ በፊት ለምድነው “ነበር” ወደተባለበት ሁናቴ ያልተመለሠው? መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላም ሆነ በእለተ ትንሳኤ ሰው ሆኖ (ሥጋ ሆኖ) እንጂ ቀድሞ በነበረበት ሁናቴ ይመጣል አይልም፡፡ ታድያ ኢየሱስ ለሰው ልጅ ሲል አምላክነቱን (ባህሪውን) ሙሉ ለሙሉ ትቶ (ሥጋ ለባሽ) ሆኖ ቀረ ማለት ነው?

ጠያቂው ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ ከአምላክነት ወደ ሰውነት ተለውጧል የሚል የተሳሳተ መረዳት ስላላቸው ጥያቄውን ያቀረቡት ከዚህ የተሳሳተ መረዳት በመነሳት ነው፡፡ ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ ሰብዓዊ ባሕርይን በመለኮታዊ ባሕርዩ ላይ አከለ እንጂ ሰው ወደመሆን አልተለወጠም፡፡ ወደ ሰማይ ያረገውም በትንሣኤው አካል ነው፡፡ አምላካዊና ሰብዓዊ ባሕርያቱ ሳይነጣጠሉና ሳይደባለቁ ይኖራሉ፡፡

ሠ. እውን ኢየሱስ “በሦስተኛው ቀን በተነሳ” እንደተባለው በሦስተኛው ቀን ተነሥቶአልን?

 አዎ በሦስተኛው ቀን ተነስቷል፡፡ “ሦስተኛው ቀን” የተባለው በአይሁድ መረዳት መሠረት በመሆኑ ከኛ ልማድ በመነሳት መተርጎም የለብንም፡፡

ረ. ይህ የኒቅያ ጉባኤ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ኢየሱስ ሲያወሳ “ከአንዱ አምላክ እግዚአብሔር ክፍል ነው፤ ራሱም አምላክ ነው” የሚባለውን መንፈስ ቅዱስን ለምን ዘነጋ? እስከዚያ ጊዜ ድረስ የመንፈስ ቅዱስ “አምላክነት” በኒቅያ ጉባኤ ለተሳተፉት 300ዎቹ ጳጳሳት አልታያቸውም ነበርን?

የኒቅያ ጉባኤ ዋና ትኩረት የክርስቶስ ማንነት እና ከአብ ጋር ያለው የባሕርይ አንድነት በመሆኑ በመንፈስ ቅዱስ ማንነት ላይ አላተኮረም፡፡ ነገር ግን ጠያቂው እንዳሉት የኒቅያ ጉባኤ መንፈስ ቅዱስን አልዘነጋነም፡፡ የመጨረሻው አንቀፅ “በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን” በማለት ይዘጋል፡፡ በወቅቱ በመንፈስ ቅዱስ ማንነት ላይ ጥያቄ ስላልተነሳ ዋና የመወያያ ርዕስ አልሆነም፡፡ ኋላ ላይ አርዮስ “የወልድ የመጀመርያ ፍጡር መንፈስ ቅዱስ ነው” በማለት አዲስ ትምህርት ማስተማር በመጀመሩና መቅዶንዮስ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ “ልክ እንደ መላእክት ፍጡር የሆነና የወልድ ተገዢ ነው” በማለት በማስተማሩ ምክንያት በ381 ዓ.ም. የቁስጥንጢንያ ጉባኤ እነዚህን ኑፋቄዎች ውድቅ የሚያደርግ መግለጫ አውጥቷል፡፡[8]

ሰ. የሥላሴ ምስጢር ለምን እስከ አራተኛው ክ/ ዘመን ሳይታወቅ ቀረ? ለምንስ በኒቅያ ጉባኤ በማስረጃ ብልጫ ሳይሆን በድምፅ ብልጫ ተወሰነ?

የሥላሴ አስተምህሮ እስከ ኒቅያ ጉባኤ ድረስ አልታወቀም የሚለው የጠያቂው አባባል ፍፁም ቅጥፈት ነው፡፡ ሥላሴ (Trinity) የሚለውን የላቲን ቃል ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀመው ጠርጡሊያኖስ የተሰኘ (160-220 ዓ.ም.) የቤተ ክርስቲያን አባት ሲሆን ከኒቅያ ጉባኤ ከመቶ ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው የኒቅያ ጉባኤ ዋና የመወያያ ነጥብ የነበረው ኢየሱስ ከአብ ጋር በባሕርይ አንድ ነው ወይንስ ተመሳሳይ? የሚል እንጂ የሥላሴ አስተምህሮ ትንተና አልነበረም፡፡ ጠያቂው የሥላሴ አስተምህሮ በማስረጃ ብልጫ ሳይሆን በድምፅ ብልጫ እንደፀደቀ የተናገሩት ነጥብ በራሱ ማስረጃ አልባ አሉባልታ ነው፡፡

ሸ. የክርስትና ሃይማኖት ጸሐፊው “በኒቅያው ጉባኤ የሃይማኖት መግለጫ ውስጥ ከሥላሴ አካላት የአንዱ የመንፈስ ቅዱስ አስተምህሮ በግልጥ አልተቀመጠም፡፡ መግለጫው ያረጋገጠው “በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን” የሚለውን ብቻ ነበር፡፡ የቆስጠንጢኒያው ጉባኤ በ381 ዓ.ም. “ጌታ በሆነና ህይወት በሚሰጥ፣ ከአብ በሚወጣና ከአብና ከወልድ እኩል አምልኮን በሚቀበል፣ በነቢያትም በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን” የሚለውን መግለጫ አውጥቷል፡፡ መግለጫው መንፈስ ቅዱስ በህልውና ከወልድና ከአብ ያነሰ ሳይሆን እኩል መሆኑን በፅኑ አረጋግጧል፡፡” ይላሉ፡፡ ታዲያ መንፈስ ቅዱስም እንደወልድ ከአብ የሚወጣ ከሆነ መንፈስ ቅዱስም የፈጣሪ ልጅ ነውን? ካልሆነስ ለምን?

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በመንፈስ ቅዱስና በአብ መካከል ያለው ሕብረት በአባትና በልጅነት አልተገለፀም፡፡ በሥላሴ አካላት መካከል ያለውን ሕብረት የመምረጥና የመግለፅ መብት የሥላሴ እንጂ የሰው ልጆች ባለመሆኑ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ከሰፈረልን በማለፍ አንናገርም፡፡

3. የክርስቲያን ምሁራን ስለ ሥላሴ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡፡ “አስተምህሮተ ሥላሴን አስመልክቶ የነበረው ዋነኛ ችግር ብሉይ ኪዳናዊው የአሃዳዊነት እምነት ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር አንድ ነው ከሚለው ትምህርቷ ጋር የክርስቶስን መለኮትነት እንዴት ነው የምትቀበለው? የሚለው ጥያቄ ዋና ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ገና ከጅማሬዋ የሥላሴን አስተምህሮት በሚመለከት ግልጽ የሆነ ግንዛቤ አልነበራትም፡፡ (ዶክተር ፓውል እንዝ ፣ ታሪካዊ ሥነ- መስኮት አመጣጡና ትንተናው ፣ ገጽ 33-34)

“ክርስቲያኖች እንደሚሉት ቀደምት ነቢያትም ሆኑ ኢየሱስ ስለ ሥላሴ አስተምረው ከነበረ ቤተክርስቲያን እንዴት ግልፅ የሆነ ግንዛቤ አልነበራትም? ክርስቲያኖች ቤተክርስቲያን “በኢየሱስና በሐዋርያት ነው የተመሠረተችው” ይሉ የለ? እነርሱም ግልጽ ግንዛቤ አልነበራቸውም ማለት ነው?

ቤተ ክርስቲያን ግልፅ የሆነውን ትምህርተ ሥላሴ ያገኘችው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ የተጻፈው በነቢያትና በሐዋርያት ነው፡፡ እነርሱ ስለ ሥላሴ ግልፅ ግንዛቤ ባይኖራቸው ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ትምህርቱን ከእነርሱ ማግኘት ባልቻለች ነበር፡፡ የመጀመርያዋ ቤተ ክርስቲያን እስከ ቆስጠንጢኖስ ዘመን ድረስ በስደት እና በመከራ ውስጥ ስላለፈች የተማከለ አስተዳደር አልነበራትም፡፡ ከዚህ የተነሳም ጥልቅ ትንታኔዎችን የሚሹ ሥነ መለኮታዊ ርዕሰ ጉዳዮችን እንደ ሃይማኖት መግለጫ ለማስቀመጥ የምትችልበት ሁኔታ ውስጥ አልነበረችም፡፡ በተጨማሪም በጊዜው በሥላሴ ላይ የተነሳ የጎላ ጥያቄ ባለመኖሩ በኒቅያ ጉባኤ እንደነበረው የሥላሴን አስተምህሮ በሥነ መለኮታዊ ቃላት በማዋቀር በእምነት መግለጫ መልክ ለማስቀመጥ የሚያስገድድ ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡

“አስተምህሮተ ሥላሴን አስመልክቶ የነበረው ዋነኛ ችግር ብሉይ ኪዳናዊው የአሃዳዊነት እምነት ነበር፡፡” ይላሉ፡፡ ታዲያ ክርስቲያኖች ሊከራከሩ እንደሚሞክሩት በብሉይ ኪዳን ዘመን የሥላሴ አስተምህሮት ከነበረ እንዴት ብሉይ ኪዳናዊው አሀዳዊ እምነት ለሥላሴ እምነት ዋና ችግር ይሆናል?

የሥላሴን አስተምህሮ በብሉይ ኪዳን ላይ በመመስረት በተወሰነ መልኩ መግለፅ ቢቻልም በዘመኑ የነበሩት ሕዝቦች አስተምህሮውን በሙላት ለመገንዘብ የሚያስችላቸው አጥጋቢ መረጃ አልነበራቸውም፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ይበልጥ ጎልቶ የተቀመጠው የአብ ማንነት ሲሆን የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስ ማንነት አጥጋቢ በሆነ ሁኔታ የተገለጠው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ነው፡፡ መገለጥ ርምደታዊ እንደመሆኑ መጠን በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩት ሕዝቦች በተገለጠላቸው መጠን እግዚአብሔርን በማወቅ አምነው አልፈዋል፡፡ በአዲስ ኪዳን ደግሞ በብሉይ ኪዳን በመጠኑ የተገለጠው የሥላሴ ትምህርት በበቂ ሁኔታ ስለተቀመጠ ማመንና መቀበል ግድ ይለናል፡፡

4. ኢሳያስ 46:9 “እኔ አምላክ ነኝና ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደኔም ያለ ማንም የለም” ይላል፡፡ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን አሀዳዊውን እምነት ወይስ ከንቂያ ጉባኤ በኋላ የመጣውን የሥላሴን አስተምሮት እንቀበል? ጥቅሱ ግን የጥንቱን ነገር አስቡ እኔ እግዛብሔር ነኝ እንደእኔ ያለም ማንም የለም ፡፡ ይላል፡፡ ታድያ ክርስቲያኖች ምን ነካቸው?

የሥላሴ ትምህርት ልብ የእግዚአብሔር አንድነት በመሆኑ አሐዳዊ ትምህርት ነው፡፡ ጠያቂው ግን “አሐዳዊነት” ሲሉ ነጠላ አሐዳዊነት (Unitarian Monotheism) ለማለት ፈልገው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሥላሴያዊ አሐዳዊነትን (Trinitarian Monotheism) የሚያስተምር መጽሐፍ እንደመሆኑ ጠያቂው የጠቀሱትን ጥቅስ አዲስ ኪዳንን በሚያጠቃልለው የመጨረሻ እና የተሟላ (Final Marching) መገለጥ፣ ማለትም በአስተምህሮተ ሥላሴ መሠረት መረዳት ያስፈልጋል፡፡

5. “አብ፣ ወልድ” እና “መንፈስ ቅዱስ” የሚሉ ቃላቶችን ስናስብ ስለነርሱ ከተገለፀው ጋር ቃላቶቹ በምናባችን የሚፈጥሩት ምስል አለ፡፡ ክርስቲያኖች ሲፀልዩ ለአብ ነው? ወይስ ለወልድ? ወይስ ለመንፈስ ቅዱስ ነው? “አንዱ አምላክ” ብለው ሲለምኑ ማንን ማለታቸው ነው? የሦስቱ አምሳል ነው? ወይስ አንድ አምሳል ነው በዓእምሯቸው የሚመጣው? ወይስ ሦስቱ ተያይዘው አንድ አምሳል ይፈጥራሉ?

ስንጸልይም ሆነ ስለ እግዚአብሔር ስንናገር በአዕምሯችን ውስጥ የምንስላቸው ምስሎች እግዚአብሔርን የሚወክሉ ባለመሆናቸው በነዚያ ምስሎች ላይ በመደገፍ የእግዚአብሔርን መልክ መረዳትም ሆነ ማስረዳት ትክክል አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ አዕምሯችን መንፈሳዊውን ዓለም በቁሳዊው ዓለም መነፅር በማየት የሚፈተን ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን የሚያውቁ ክርስቲያኖች ሲጸልዩ የሥላሴን አካላት በመከፋፈልም ሆነ በመደባለቅ በአዕምሯቸው ውስጥ መሳል ትክክለኛ መረዳት አለመሆኑን ያውቃሉ፡፡ ክርስቲያኖች “አንድ አምላክ” በማለት ሲጸልዩ በሦስት አካላት የሚኖረውን አንዱን አምላክ ማለታቸው ነው፡፡ ወደ እያንዳንዱ የሥላሴ አካልም ሆነ ወደ አንዱ ግፃዌ መለኮት መጸለይ እንችላለን፡፡ ነገር ግን በአዕምሯችን ውስጥ የሚከሰተው ምስል ምንም ይሁን ምን ትክክለኛውን የእግዚአብሔርን ማንነት የሚወክል አለመሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

6. ማቴዎስ ወንጌል 12:32 “ማንም ሰው በሰው ልጅ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ይቅር ይባላል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ግን በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልም” ይላል፡፡ የሥላሴ አቀንቃኞች እንደሚሉት አብ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ሦስቱም አምላክም እኩልም ከሆኑ እንዴት በሰው ልጅ (ወልድ) ላይ የሚነገረው ክፉ ይቅር ሲባል በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚባለው ንግግር ይቅርታ የሌለው ሆነ? ምኑ ላይ ነው ታድያ እኩልነታቸው?

ኢየሱስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ እንደመሆኑ መጠን በምድር ላይ የተመላለሰው እንደ ሰው ነበር፡፡ በወቅቱ ሲመለከቱት የነበሩት ሰዎች ማንነቱን ሳይረዱት በመቅረት በእርሱ ላይ ቃል ቢናገሩ እንደ ማንኛውም ኃጢአት ይቅር ይባልላቸዋል፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መሳደብ (በዚህ አውድ ውስጥ አይሁድ እንዳደረጉት የመንፈስ ቅዱስን ሥራ እንደ ሰይጣን ሥራ በመቁጠር መቃወም) ይቅርታ የሌለው ኃጢአት ነው፡፡ ለዚህ ነው አሕመዲን ጀበልን የመሳሰሉት ሐያሲያን ዛሬ የሚናገሩት ቃል ነፍሳቸውን እንዳያስከፍላቸው መጠንቀቅ የሚገባቸው፡፡

7. በማቴዎስ 26:39 ላይ ኢየሱስ “አባት ሆይ ቢቻልህ ይህ ፅዋ ከእኔ ይለፍ ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” ብሏል፡፡ ይህ አባባል የኢየሱስ ፍላጎትና የአብ ፍላጎት ሁለት የተለያዩ መሆናቸውን ያስረዳል ፡፡ ታድያ አብ እና ወልድ ሁለቱም የአንዱ እግዚአብሔር አካል ከሆኑ እንዴት ሁለት ፍላጎት ኖራቸው?

ኢየሱስ ሰውም አምላክም እንደመሆኑ መጠን ሰብዓዊ ባሕርዩ የመስቀሉን ሥቃይ ከማስተናገድ ይልቅ አለማስተናገድን እንደሚመርጥ ግልጥ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ እርሱ ፈቃድ ሳይሆን እንደ አብ ፈቃድ እንዲሆን ጸለየ፤ ጸሎቱም ተሰማለት፡፡ ይህ ኢየሱስ በመለኮታዊ ባሕርዩ ከአብ የተለየ ፈቃድ እንዳለው እንድንናገር አያስችለንም፡፡

8. ዮሐንስ 8፡29 “የላከኝ እርሱ ከእኔ ጋር ነው፤ ምን ጊዜም የሚያስደስተውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም” ይላል፡፡ እውን ኢየሱስ አምላክ ቢሆን ኖሮ ሌላኛውን አምላክ ማስደሰት እንዴት ፈለገ?

አንዱ የሥላሴ አካል ሌላውን ለማስደሰት መፈለጉ አምላክ አለመሆኑን የሚያሳየው እንዴት ሆኖ ነው? አምላክ ለመሆን ሌላውን የማስደሰት ፍላጎት ሊኖረው አይገባም ማለት ነውን? የሥላሴ አካላት ተፎካካሪ አማልክት ሳይሆኑ ፍፁም በሆነ አንድነት እና ፍቅር የሚኖሩ የአንዱ ግፃዌ መለኮት አካላት ናቸው፡፡

“ምን ጊዜም የሚያስደስተውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም” የማያስደስተውን ቢያደርግ ብቻውን ይተወዋል ማለት አይደል? አምላክ ብቻውን እንዳይሆን የሌላኛውን አምላክ (አብ) ውዴታ ይፈልጋልን?

ምን ጊዜም አብን የሚያስደስት ነገር ማድረግ የኢየሱስ ባሕርይ በመሆኑ ኢየሱስ ባሕርዩን በመፃረር አብን የማያስደስት ነገር አያደርግም፡፡ አብን የማያስደስት ነገር ማድረግ ባሕርዩ ካልሆነ ደግሞ ንግግሩን በመገልበጥ “የማያስደስተውን ቢያደርግ… ” በማለት መናገር ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፡፡ አንድ ሰው “እግዚአብሔር ስለማይዋሽ ተስፋው ይታመናል” ብሎ ቢናገር “አሃ… ከዋሸ ተስፋው አይታመንም ማለት ነው” ብሎ እንደማሰብ ነው፡፡ መዋሸት የእግዚአብሔር ባሕርይ ስላልሆነ ተስፋው ይታመናል ስለዚህ “ቢዋሽ…” ብሎ ማሰብ ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ አብን የማያስደስት ነገር ማድረግ የኢየሱስ ባሕርይ ባለመሆኑ “የማያስደስተውን ቢያደርግ…” ብሎ ማሰብ ራስን ማቄል ነው፡፡

9. ክርስቲያኖች እንደሚሉት ዘፍጥረት 1፡26 ላይ “ሰውን በመልካችን፤ በአምሳላችን እንፍጠር” ሲል ሥላሴን ለማመልከት ከሆነ ታዲያ “በአምሳላችን” ሲል ሰው በየትኛው አምሳል ነው የተፈጠረው ሊባል ነው? በአብ፣ በወልድ ወይስ በመንፈስ ቅዱስ? አልያም በሦስቱ አካላት ውህደት ተፈጠረ? ብሉይ ኪዳንን “ጠብቀው አቆዩ” የሚባሉት አይሁዶችስ ይህንንም ሆነ መሰል በሥላሴ በሚያምኑ ክርስቲያኖች ለማስረጃነት የሚቀርቡ ጥቅሶች ሳይረዱና በሥላሴ ሳያምኑ መጽሐፉን “ጠብቀው አቆዩ” ማለት ያስኬዳልን?

መጽሐፉን ጠብቆ ማቆየት እና መጽሐፉ የሚለውን መረዳት በምን ይገናኛሉ? “ሰዎች በእጃቸው የሚገኘውን መጽሐፍ ትርጉም በትክክል ሳይረዱ ጠብቀው ማቆየት አይችሉም” ማለት ምን የሚሉት አመክንዮ ነው? ጠያቂው የጥቅሱን ትክክለኛ ትርጉም ወደ ዋናው ቋንቋ በመሄድ የማስረዳት አቅም ስለሌላቸው አይሁድ ጥቅሱን ክርስቲያኖች በሚረዱት መንገድ አለመረዳታቸውን እንደ ማስረጃ በመጥቀስ አወናብደው ለማለፍ ጥረት አድርገዋል፡፡[9] የሥላሴን ትምህርት የማይቀበሉ ወገኖች ይህንን ጥቅስ በሁለት መንገዶች ለማብራራት ሞክረዋል፡፡ የመጀመርያው እግዚአብሔር “እንፍጠር” ሲል ከመላእክት ጋር መማከሩ ነው የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ራሱን በማክበር ልክ ነገሥታት “እኛ” በሚሉት መንገድ መናገሩ ነው የሚል ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁለቱ ምላሾች በፍፁም የሚያስኬዱ አይደሉም፡፡ ሰው በመላእክት መልክ እንደተፈጠረ ቅዱሳት መጻሕፍት አያስተምሩም፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረትን በመፍጠር ሂደት ውስጥ መላእክትን እንዳሳተፈ የሚገልፅ አንድም የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃ አናገኝም፡፡ እንዲያውም በተጻራሪው እግዚአብሔር ብቻውን ፍጥረትን እንደፈጠረና አጋዥ እንዳልነበረው ይናገራል (ኢሳይያስ 44፡24)፡፡ ራስን ለማክበር በብዙ ቁጥር መናገር በጥንቱ እብራይስጥ ውስጥ ስለማይታወቅ ሁለተኛውም ምላሽ ሊያስኬድ አይችልም፡፡ እንዲህ ያለ አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ቢሆን ማስረጃ የለውም፡፡ ስለዚህ ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር ከአንድ በላይ አካላት እንዳሉት የሚያመለክት ነው፡፡ ሰው የሥጋ፣ የነፍስ እና የመንፈስ ጥምረት በመሆኑ በእግዚአብሔር የሥላሴያዊ ባሕርይ አምሳል ነው የተፈጠረው፡፡ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩ የእግዚአብሔር ሥላሴያዊነት አንዱ ማስረጃ ነው፡፡

10. እውን ሥላሴ የኢየሱስ አስተምህሮ ከሆነ ይህን ማንም ሊፈታው ያልቻለውን ምስጢር ኢየሱስ ሳያስተምር (ሳይፈታ)፣ ቃሉን እንኳ አንስቶ ሳይናገር እንዴት አለፈ? በሥላሴ የተነሣ ለዘመናት ክርስቲያኖች ሲጋደሉ ነበር፡፡ የክርስትና እምነት ጸሐፊውም እንዲህ ይላሉ፡-“ገና ከጅምሩ ሥላሴ የሚለው ቃል የሥነ-መለኮት እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንዳልሆነ ለመግለፅ እፈልጋለሁ (ጌርሃርድ ኔልስ፣ ለሙስሊሞች ጥያቄዎች የክርስቲያኖች መልሶች፣ ገጽ 137)፡፡ እንዴት ሥላሴ የሚለው ቃል እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልኖረም? የሌለ ነገር የሃይማኖት መሠረት ሆነ ልንል ነውን?

ተከታዩም ጥያቄ ከላይ ከተቀመጠው ጋር ተመሳሳይ ይዘት ስላለው አንድ ላይ መልስ እንሰጣለን፡-

11. በሥላሴ ማመን እና በርሱ ስም መጠመቅ ብቸኛ የመዳኛው መንገድ ከሆነ ኢየሱስ ለምን በግልፅ ትኩረት ሰጥቶ አላስተማረበትም? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ሥላሴ” የምትለው ቃል ስላልሰሙና በወቅቱ የማትታወቅ ስለነበረች እነርሱም አልዳኑም ማለት ነውን?

አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የሚሉትን መጠርያዎች ለመጀመርያ ጊዜ በአንድነት አጣምሮ የጠቀሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ማቴዎስ 28፡19-20)፡፡ በዚሁ ቦታ በሥላሴ ስም የመጠመቅን ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በተጠቀሰው ጥቅስ ውስጥ እነዚህ ሦስቱ አካላት አንድ ስም እንዳላቸው በማመልከት የባሕርይ አንድነታቸውን አስታውቋል፡፡ ሥላሴ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለመገኘቱ አስተምህሮው የለም ማለት አይደለም፡፡ የነገረ መለኮት ሊቃውንት የቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርቶችን ጨምቀው ለማስቀመጥ የሚጠቀሟቸው ብዙ ቃላት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ አይገኙም፡፡ ቃላቱ ፅንሰ ሐሳቦቹን እስከገለፁ ድረስ መጠቀም ስህተት አይደለም፡፡ ጥቅም እንጂ ጉዳትም የለውም፡፡

ሙስሊም ሰባኪያን ብዙ ጊዜ “ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህና እንዲያ የሚሉ ነገሮችን አሳዩን” የሚሉ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን ጥያቄዎቻቸው በአንድ መንገድ ብቻ እንዲመለሱ መጠበቃቸውና ክርስቲያኖችን በእስላማዊ መረዳት ልክ በተሰራ ጠባብ ክፍል ለመገደብ መሞከራቸው ልክ ካለመሆኑም በላይ አስፍቶ አለማሰብ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን አስተምህሮ ለመቀበል አስተምህሮው እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ ብቻ ተጽፎ መገኘት እንዳለበት የሚያምኑ ከሆነና ሥላሴ የሚለውን የመሳሰሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ፅንሰ ሐሳቦችን የሚወክሉ ሥነ-መለኮታዊ ቃላት ክርስቲያናዊ ለመሆን የግድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጠቀስ አለባቸው የሚሉ ከሆነ ይህንኑ መስፈርት በቁርኣን ላይ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመጫን የሚሞክሩትን መስፈርት ለቁርኣን የማይጠቀሙ ከሆነ ለእውነት ታማኞች ያልሆኑ በአባይ ሚዛን የሚመዝኑ ግብዞች መሆናቸውን በራሳቸው ላይ ያስመሰክራሉ ማለት ነው፡፡ እነኚህ ወገኖች ጥያቄዎቻቸው እና መስፈርቶቻቸው ኢ-ምክንያታዊ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ በማድረግ ረገድ ራሳቸው የቀመሙትን መድኃኒት ማቅመስ መተኪያ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡ ስለዚህ በማስከተል በተደጋጋሚ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ወደ እነርሱ በማዞር እንጠይቃቸዋለን፡፡ ዛሬ ሙስሊሞች እየተከተሏቸው የሚገኙት በርካታ ሥርኣቶች እና የሚጠቀሟቸው ጥቂት የማይባሉ እስላማዊ ቃላት በቁርኣን ውስጥ የማይገኙ ናቸው፡፡ ስለ አላህ፣ ስለ ዒሳ እና ስለ ሙሐመድ የሚያምኗቸው በርካታ ነገሮች በእነዚህ አካላት ቃል በቃል በቁርኣን ውስጥ በቀጥታ ያልተነገሩ ናቸው፡፡ ሙስሊም ወገኖች አንድን አስተምህሮ ለመቀበል ወይም አንድን ቃል ለመጠቀም የግድ እነርሱ በሚፈልጉት ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ መገኘት እንዳለበት ካመኑ የሚከተሉትን ቃላት፣ አስተምህሮዎች፣ ንግግሮች እና ትዕዛዛት ከቁርኣን በማውጣት እንዲያሳዩን እንጠይቃቸዋለን፡፡

  • ተውሂድ የሚለውን ቃል፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ፅንሰ ሐሳብ ሥላሴ እንደሚሰኝ ሁሉ የቁርአኑ የአላህ ፅንሰ ሐሳብ ተውሂድ በመባል ይታወቃል፡፡)
  • ሦስቱን የተውሂድ ክፍሎች፣ ማለትም ተውሂድ አሩቡቢያ፣ ተውሂድ አል ኡሉሂያ እና አስማ ወስሲፋት፡፡ (ተውሂድ የሚለውም ቃል ሆነ ሦስቱ ክፍሎቹ ቃል በቃል በቁርኣን ውስት ተጠቅሰው አናገኝም፡፡)
  • “ላ ኢላ ሀኢለላህ መሐመደን ረሱልአላህ” (ከአላህ በስተቀር አምላክ የለም ሙሐመድም መልዕክተኛው ናቸው) የሚለው እስላማዊ የእምነት መግለጫ ልክ በዚህ ሁኔታ የተጻፈበትን ቦታ፡፡ የተቆራረጠውን በማገጣጠም እንድታሳዩን አንፈልግም፡፡
  • በቀን አምስት ጊዜ ስገዱ የሚል ትዕዛዝ፡፡
  • ሙስሊም መገረዝ አለበት የሚል ትዕዛዝ፡፡
  • ዝሙት የሰራ ሰው በድንጋይ ተወግሮ መሞት አለበት የሚል ትዕዛዝ፡፡
  • ሙስሊም የካዕባን ድንጋይ መሳም አለበት የሚል ትዕዛዝ፡፡
  • ኢብራሂም ለመስዋዕትነት ያቀረበው ልጅ ኢስማኤል ነበር የሚል አንድ ጥቅስ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ መሲህ ነኝ ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ ከድንግል ነው የተወለድኩት ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ የአላህ ቃል እና ከእርሱ የሆንኩ መንፈስ ነኝ ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ ሙስሊም ነኝ ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በምድር ላይ እያለ በራሱ አንደበት እኔ አምላክ አይደለሁም ያለበትን ቦታ፡፡ (ወደ ፊት አላህ ሲጠይቀው ይናገራል ተብሎ በቁርኣን ውስት የተጠቀሰ ነገር ካለ አንቀበልም ምክንያቱም ዒሳ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ የተናገረው አይደለምና፡፡ ወደ ፊት ይናገራል ተብሎ የተጠቀሰው ንግግር እውነትም ውሸትም ሊሆን ይችላል፡፡ ጊዜው ሲደርስ የሚታወቅ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ እንደ ዒሳ ንግግር ሊቆጠር አይችልም፡፡)
  • ዒሳ በራሱ አንደበት ቃል በቃል እኔ የአላህ ልጅ አይደለሁም ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ ስለ ሰው ልጆች ኃጢኣት ለመሞት እና በሦስተኛው ቀን ለመነሳት አልመጣሁም ያለበትን ቦታ፡፡
  • አላህ ያወረዳቸው የቁርኣን ሱራዎች 114 ብቻ እንደሆነ የተጻፈበትን ቦታ፡፡
  • የቁርኣን ሱራዎችን ስሞች አላህ እንደገለጣቸው የተነገረበትን ቦታ፡፡
  • የአደም ሚስት ስም ማን መሆኑን የሚናገር ቦታ፡፡ (ቁርኣን ከማርያም ውጪ የትኛዋንም ሴት በስም አልጠቀሰም፡፡ በአማርኛ ቁርኣን ወይንም በሌሎች ትርጉሞች ውስጥ በቅንፍ ተጠቅሰው የምታገኟቸው የሴት ስሞች ሁሉ በአረብኛው ቁርኣን ውስጥ አይገኙም፡፡ የተርጓሚዎቹ ጭማሬዎች ናቸው፡፡)

ውድ አሕመዲን፤ እነዚህን ነገሮች ከቁርኣን አውጥተው ሊያሳዩን የማይችሉ ከሆነ መሰል ጥቄዎችን መጠየቅ ለትክክለኛ ውይይት እንቅፋት ከመሆን የዘለለ ውጤት እንደሌለው ተረድተው ከደረቅ ክርክር ይቆጠቡ ዘንድ እንመክርዎታለን፡፡ ጥያቄዎችዎ በአንድ መንገድ ብቻ እንዲመለሱ በመጠበቅ ክርስቲያኖችን በጠባብ ክፍል ውስጥ ለማሰር የሚሞክሩ ከሆነ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ሲጠየቁ መግቢያ ይጠፋዎታልና አያዋጣዎትም እንላለን፡፡

12. ስለ ሥላሴ አንድም ማስረጃ በሌለበት የኒቅያን መግለጫ ብቻ በመንተራስ ከራሳችን ምሳሌ እየሰጠን ለማሳመን እንዴት እንጥራለን? ስለ ሥላሴ የምናስረዳው በማስረጃ ነው ወይስ በምሳሌ?

ስለ ሥላሴ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ሆነ ቅድመ ኒቅያ በነበሩት ሐዋርያዊ አባቶች ጽሑፎች ውስጥ ኁልቁ መሳፍርት የሌላቸው ማስረጃዎች አሉ፡፡ አሕመዲን ለማስረጃዎቹ ልባቸውን ዝግ ካደረጉ ምንም ልንረዳቸው አንችልም፡፡ ስለ ሥላሴ የምናስረዳው በማስረጃም በምሳሌም ነው (እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ሊገልጥ የሚችል ምሳሌ እንደሌለ ግን እናምናለን)፡፡ ምሳሌዎቹ ማስረጃዎቹን ይበልጥ ለመገንዘብ የሚረዱ ከሆነ መጠቀም ምኑ ላይ ነው ስህተቱ? የፈጣሪን አንድነት በምሳሌ መግለጥ ስህተት ከሆነ ሙስሊሞች የአላህን አንድነት ለመግለጥ አንድ ጣታቸውን የሚቀስሩት ለምን ይሆን?

13. 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡23 “እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፤ ክርስቶስም የእግዚእልብሔር ነው” ይላል፡፡ ክርስቶስ የእግዚያብሔር መሆኑ በዚህ ጥቅስ ተገልጿል፡፡ ታዲያ “የእግዚአብሔር” እና “እግዚአብሔር” አንድ ናቸውን? እንዲያማ ከሆነ በጥቅሱ መሠረት “እናንተ የክርስቶስ ናችሁ፡፡” ስለተባለ ክርስቲያኖችና ክርስቶስ አንድ ናቸው ማለት ነዋ?

አዲስ ኪዳን አውዱ ግልፅ ካላደረገ በስተቀር “እግዚአብሔር” ሲል አብን ማለቱ መሆኑን ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ገልፀናል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ የእግዚአብሔር መሆኑ መገለፁ እርሱና አብ በአካል ልዩ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ኢየሱስ ከአብ ጋር በመለኮት አንድ መሆኑንና ወልድ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ጥቅሶች ስላሉ ይህንን ጥቅስ ኢየሱስ በአካል ከአብ ልዩ መሆኑን ከማመልከት ባለፈ አምላክ መሆኑን ወይም ከአብ ጋር አንድ መሆኑን ለማመልከት አንጠቀምም፡፡

14. “አብ አምላክ ነው፤ ወልድም አምላክ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው፡፡ ግን አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አምላክ አይባሉም፡፡ አብ ጌታ ነው ወልድ ጌታ ነው መንፈስ ቅዱስ ጌታ ነው፡፡ ግን አንድ እግዚአብሔር እንጂ ሦስት ጌቶች አይባሉም፡፡ እንደው የሥላሴን ምስጢር ማን ይሆን የሚፈታው?

ውድ አሕመዲን፤ የእግዚአብሔርን ምስጢር መፍታት የሚችል ፍጥረት ከሰው መካከል የሚፈልጉ ከሆነ ተስፋ ይቁረጡ፤ እርሱን የማድረግ አቅምና ችሎታ ያለው ሰው በምድር ላይ የለም! እግዚአብሔር እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱነቱ ከፍጥረት አዕምሮ ያለፈና የላቀ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በሰው አዕምሮ ለክቶና መርምሮ ለማወቅ መሞከር ከባቢ አየርን በሞላ በሳንባችን የመሳብ ያህል የማይታሰብ ነው፡፡ የእርስዎ አምላክ አሐዳዊነቱ የሒሳብ ቁጥር ሽርፍራፊ የሆነው ሌጣ አንድ ሲሆን በሰው አዕምሮ የተመጠነ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እርስዎ ብዙ ጊዜ ከሚቀስሯት አንድ ጣትዎ ጀምሮ በየትየለሌ ምሳሌዎች ሊገለፅ የሚችል ተራ አንድነት ነው፡፡ አምላካችን ከሰው አዕምሮ ያለፈ፤ አንድነቱና ሦስትነቱ በሰው የሒሳብ ስሌት ሊገለፅ የማይችል፤ ታላቅና ምስጢራዊ አምላክ ነው፡፡

15. ሥላሴ የኢየሱስ እውነተኛ አስተምህሮት ከነበረ ለምንድን ነው አንድም ክርስቲያን ሊፈታው ያልቻለውን ምስጢር ያን ታላቅ የማስተማር ችሎታውን ተጠቅሞ ኢየሱስ ያላብራራው? ሰውንም ግራ ከማጋባት “ሁከት” ያልገላገለው?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፡፡ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” (ዮሐንስ 16፡12-15)፡፡ ጌታችን ስለ አብ፣ ስለ ራሱና ስለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ነገሮችን ያስተማረ ቢሆንም ነገር ግን በወቅቱ ሐዋርያቱ ሊገነዘቡት በሚችሉት መጠን ነበር፡፡ ሐዋርያቱ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ አይሁድ ከዚያ ቀደም ያልተረዱትን የእግዚአብሔርን ሥላሴያዊነት እና የኢየሱስ ክርስቶስን ተልዕኮ ዓላማ በሙላት ተረድተዋል፡፡ በስፋትና በጥልቀትም አስተምረዋል፡፡

16. የሥላሴ አስተምህሮ “ምስጢር” ነው ይባላል፡፡ ሥላሴ አስተምህሮቱም ሆነ ምስጢርነቱ የቱ ጋር ነው የተገለጸው? የሚገርመው ግን ምስጢር ነው እየተባለ ማስተማሩን ይቀጥሉበታል፡፡ ጥያቄ ሲነሳ ግን “ምስጢር ነው” ይባላል፡፡ እምነትና አምልኮ ምን ምስጢር ያስፈልገዋል?

ሙስሊም ወገኖች በድፍረትና በግብታዊነት ከሚናገሯቸው ነገሮች መካከል የከፋው ይኸኛው ነው፡፡ በፈጣሪ የሚያምን ሰው ስለ ፈጣሪ ምስጢራዊነት ሲነገር እንዴት ግራ ይገባዋል? ሥላሴ ምስጢር ነው ስንል ከሰው አዕምሮ በላይ ነው ማለታችን እንጂ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ በድብቅ የሚያዝ፣ ለሌላው ሕዝብ የማይነገር ጉዳይ ነው ማለታችን አይደለም፡፡ መሠረታዊውን የሥላሴ ትንተና መረዳት ቢቻልም ነገር ግን ወደ ውስጥ ጠልቀን ለመረዳት የማይቻልና ከአዕምሮ በላይ የሆነ ነው፤ ምክንያቱም ሥላሴ እግዚአብሔር ነውና! መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በሰው አዕምሮ ሊመረመርና ሊለካ እንደማይችል አጥብቆ ያስተምራል፡- “እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም፡፡ የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም፡፡” (ኢዮብ 36:6)፡፡

በፍጥረተ ዓለም ውስጥ እንኳ ብዙ ያልተፈቱ ምስጢራት ይገኛሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሕዋ ተመራማሪዎች በሕዋ ውስጥ የሚገኙትን አካላት አንድ ላይ አጥብቆ ሊይዝ የሚችል በቂ ስበት እንደሌለ ደርሰውበታል፡፡ ነገር ግን የአፅናፈ ዓለም 26.8 ከመቶ ፀሊም ቁስ (Dark Matter) በተሰኘ ምንነቱ በማይታወቅና በዓይን በማይታይ ነገር እንደተሞላና ይህ ነገር በስበት መልክ ሳይሆን ልክ እንደ ፈሳሽ ማጣበቂያ (Glue) አፅናፈ ዓለምን አንድ ላይ አጣብቆ እንደያዘ ይናገራሉ፡፡[10] በተጨማሪም የአፅናፈ ዓለም 68.3 ከመቶ ደግሞ ፀሊም ኃይል (Dark Energy) በተሰኘ ምንነቱ በማይታወቅ ኃይል የተሞላ መሆኑን፣ ይህም ኃይል አፅናፈ ዓለም በከፍተኛ ፍጥነት ስፋቱ እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ስለ እነዚህ ነገሮች ሲናገሩ “ምስጢር ናቸው” ይላሉ፡፡[11] የፍጥረቱን ምስጢር መርምሮ ያልደረሰበት ውሱን የሆነው የሰው ልጅ ሃያሉ ፈጣሪ ምስጢር አለመሆኑን ለማሰብ እንኳ መድፈሩ በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡

17. በምዕራፍ 6 ቁጥር 5 ላይ የጠየቁትን ስለደገሙ ታልፏል፡፡

18. የሥላሴ ፅንስ ሐሳብ ትክክለኛው ገለጻ የትኛው ነው? ከፊል ክርስቲያኖች “ሥላሴ” ከጣኦት አምላኪዎች ወደ ክርስትና የገባና ፈጠራ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ (የይሖዋ ምስክሮች/ ጀሆቫ ዊትነስ)፡፡ በሥላሴ ያመኑት አብያተ ክርስቲያናትም ቢሆኑ በትርጉሙ ሳይስማሙ “በሥላሴ ማመን ወሳኝ ነው” ይላሉ፡፡ ታዲያ የትኛው አብያተ ክርስቲያን ይሆን ትክክለኛው?

የይሖዋ ምስክሮች ከክርስትና የሚለዩዋቸው ብዙ አፈንጋጭ አስተምህሮዎች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል፡- ይሖዋ ትልቅ አምላክ ሲሆን ኢየሱስ ትንሽ አምላክ ነው፣ ከሙታን በሥጋ አልተነሳም፣ መልአኩ ሚካኤል ነው ይላሉ፡፡ በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ ኃይል ብቻ ነው፣ ሰው ነፍስ የለውም፣ ወደ ሰማይ የሚሄዱት የመጀመርያዎቹ የይሖዋ ምስክሮች ብቻ ናቸው፣ ወዘተ. በማለት ያምናሉ፡፡ ራሳቸውን እንኳ “ክርስቲያን” በማለት አይጠቅሱም፡፡ ታድያ እንዲህ ዓይነት ቡድኖች ክርስቲያን ሊሰኙ ይችላሉን? አስተምህሮተ ሥላሴ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንጂ ከአረማውያን የተገኘ አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን በዚህ መልኩ የሚገልፅ ሃይማኖት በዓለም ላይ ክርስትናና ክርስትና ብቻ ነው፡፡ ይልቁኑ አብ ትልቅ አምላክ፣ ልጁ ደግሞ ፍጡርና ትንሽ አምላክ ነው የሚለው የአርዮሳውያን ትምህርት ከአረማውያን የመድብለ አማልክታዊነት አስተሳሰብ የተቀዳ ነው፡፡ የይሖዋ ምስክሮችን የመሳሰሉት ቡድኖች ክርስቲያናዊ ናቸው ከተባለ በሃኢዝምና ሲክህን የመሳሰሉት ከእስልምና የተገኙ ቡድኖችም እስላማዊ ሊሆኑ ነው፡፡ ይህንን የሚቀበል ሙስሊም ግን የለም፡፡

19. ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ነበርን? ከመወለዱ በፊትስ ነበር ወይንስ አልነበረም? ምላሹ “ነበር” ከሆነ “የነበረው ራሱ ከአብ የተወለደ ነው ትሉ የለምን? “አልነበረም” ከሆነ ታዲያ ከጊዜ በኋላ የተገኘ ነገር “ዘለዓለማዊ” ነው ይባላልን?

መወለዱን ስንናገር ከአብ በዘለዓለማዊ መገኘት (Eternal Generation) መገኘቱን ለማመልከት እንጂ በጊዜ የተገደበ መሆኑን ለማመልከት ባለመሆኑ ይህ ጥያቄ በተሳሳተ መረዳት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ መጀመርያ እንደሌለው ነገር ግን በመጀመርያ እንደነበረ የሚናገር ሲሆን የዓለም ፈጣሪ መሆኑን ያስተምራል (ዮሐንስ 1፡1-18)፡፡ እርሱ የዘለዓለም አባት (ዘለዓለማዊነትን ያስገኘ) እንጂ በጊዜ የተገደበ አይደለም (ኢሳይያስ 9፡6)፡፡

20. 1ኛ ዮሐንስ 5፡7 ″መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው፡፡ የሚመሰክሩት መንፈሱና ውሃው፤ ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ” ይላል፡፡ እነዚህ ሦስት ምስክሮች እኩል ናቸውን? ደም ውኀን ሊተካ ይችላልን? ውኀስ በማንኛውም መልኩ “እንደ መንፈስ ነው” ማለት ይቻለናልን? ልክ መንፈሱ ደሙና ውሃው ሦስት የተለያዩ ነገሮች እንደሆኑት ሦስቱም የመጀመሪያ ምስክሮች እነርሱም አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅድስ የተለያዩ ናቸውን?

ውኀው የክርስቶስን የማንፃት ኃይል የሚያሳይ ሲሆን ደሙ መስዋዕትነቱን ያመለክታል፡፡ ሰው በክርስቶስ ሲያምን የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እንዲሁም የመቀደሱንና የኃጢአት ይቅርታን የመቀበሉን ዋስትና ስለሚያገኝ በእውነተኛ መንገድ ላይ ለመሆኑ ሌላ ውጪያዊ ምስክር አያሻውም፡፡ ጥቅሱ ከዚህ የተለየ መልዕክት ስለሌለው ከሥላሴ ጋር ማያያዝ አስፈላጊ አይደለም፡፡[12]

21. አምላክ “አንድም ሦስትም ነው” የሚል አንድ ጥቅስ እንኳ ማቅረብ ሳንችል እንዴት በሰው አመለካከት ላይ ተንተርሰን አምላክን “ሦስትም አንድም” ልንል ይቻለናል?

የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ከአንድ ጥቅስ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሰፈረው አጠቃላይ መረጃ የተገኘ ነው፡፡ እውነትን የሚፈልግ አስተዋይ ሰው አጠቃላይ መረጃዎችን በማገናዘብ እንጂ በአንድ ጥቅስ ላይ በመንጠልጠል እምነቱን አይመሰርትም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አብ አምላክ መሆኑን (ዮሐንስ 17፡3፣ 1ቆሮንቶስ 8፡8)፣ ወልድ አምላክ መሆኑን (ኢሳይያስ 6፡9፣ ዮሐንስ 1፡1፣ 20፡28፣ ሮሜ 9፡5፣ ቲቶ 2፡13፣ ዕብራውያን 1፡8፣ 2ጴጥሮስ 1፡1)፣ መንፈስ ቅዱስም አምላክ መሆኑን ይናገራል (የሐዋርያት ሥራ 5፡3-4፣ ዮሐንስ 5፡3-4፣ 2ቆሮንቶስ 3፡17)፡፡ ነገር ግን አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ያስተምራል (ዘዳግም 6፡4፣ ኢሳይያስ 43፡10፣ 44፡8፣ ኤርምያስ 10፡10፣ ያዕቆብ 2፡19)፡፡ ሥላሴ የሚለው ቃል ይህንን መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚገልፅ የሥነ መለኮት ቃል ነው፡፡

22. ክርስቲያኖች “አምላክ ነው” የሚሉት “ዘለዓለማዊው ልጅ” (ወልድ) “ሰው” ከሆነና አብና መንፈስ ቅዱስ ካልተለዋወጡ ኢየሱስ ይህን የመሰለ ድንቅ ነገር ለምን ሳይናገር ቀረ?

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን በቃልም ሆነ በተግባር አረጋግጧል፡፡ ይህ ጥያቄ ቁጥር ለመሙላት እንጂ በአስተውሎት የተጠየቀ አለመሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ለመሆኑ አላህ በቁርኣን ውስጥ ስላለመለወጡ ተናግሯልን? እስኪ የቱ ጋር?

23. በዚሁ ምዕራፍ ጥያቄ 2 ለ፣ ሐ፣ 19፣ ላይ የጠየቁትን ስለደገሙ ታልፏል፡፡

24. ከምዕራፍ 1 ጥያቄ 81 ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ታልፏል፡፡

25. ብሉይ ኪዳንን ብንፈትሽ ኢየሱስ ከአብ ስለ መወለዱ አይገልፅም፡፡ አምላክ እንደሚወልድም እንዲሁ፡፡ በክርስትና ነው ይህ ያለው፡፡ ታዲያ ይህ አስተምህሮቱ በአዲስ ኪዳን ዘመን የተፈጠረ መሆኑን አያሳይምን?

ተከታዩ ጥያቄ ከዚህኛው ጋር ስለሚያያዝ አንድ ላይ እንመልሳለን፡-

26. እውን አብ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት አንድ ልጅ (ወልድን) ወልዶ ከነበረ ይህን የሚመስል “ድንቅ” ነገር እንዴት አንዱም ነብይ እንኳን ሳያስተምር አልያም አንዴም ቢሆን ሳይናገር አለፈ? ለምንስ ነው በብሉይ ኪዳን ይህንን የሚመለከት አስተምህሮ ያልተገኘው?

ጠያቂው ከተናገሩት በተፃራሪ እግዚአብሔር ልጅ እንዳለው በዘመነ ብሉይ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፡- “ወደ ሰማይ የወጣ የወረደስ ማን ነው? ነፋስንስ በእጁ የጨበጠ ማን ነው? ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው? የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው? ይህን ታውቅ እንደ ሆንህ፥ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው?” (ምሳሌ 30፡4)፡፡

“አሕዛብ ለምን ያጕረመርማሉ? ወገኖችስ ለምን ከንቱን ይናገራሉ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ፡፡ ማሰርያቸውን እንበጥስ፥ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል… ትእዛዙን እናገራለሁ፤ እግዚአብሔር አለኝ፦ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ…” (መዝሙር 2፡1-12 ከዕብራውያን 1፡5 ጋር ያነፃፅሩ)፡፡

እነዚህና ሌሎች መሲሃዊ ጥቅሶች ስለ እግዚአብሔር ልጅ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ጥቅሶች በብሉይ ኪዳን ውስጥ እንደሌሉ ቢታሰብ እንኳ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ ክርስትና የሚያስተምረው ትምህርት በአዲስ ኪዳን ዘመን ይፋ መሆኑን እንጂ ስህተት መሆኑን አያሳይም፡፡

ብሉይ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር አንድያ ልጅ ከመናገሩም በተጨማሪ የመንፈስ ልጆች እንደሚወልድ ይናገራል፡፡ ይህ “መውለድ” ግን መንፈሳዊ ትርጉም ያላቸውን አባባሎች በሥጋዊ አስተሳሰብ ለሚተረጉሙት ለአሕመዲንና ለመሰሎቻቸው ላይገባቸው ይችላል፡- “እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ፥ ምድርም አድምጪ፤ ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም…” (ኢሳይያስ 1፡2)፡፡

27. አንድ የክርስቲያን ጸሐፊ ስለ ሥላሴ ሦስት አካላት እንዲህ ይላሉ ፡-“ከሦስቱ አካላት እያንዳንዱ አካል በገጹ ፍጹም ነው፡፡ በሦስቱ አካላት ውስጥም መገዛዛት አንዱም ከአንዱ የሚያንስበት በማዓረገ መለኮት አንዱ ከሁለተኛው በልቆ የሚታይበት አንዱም ለሁለተኛው እንደ መልዕክተኛ አድርጎ በሥልጣኑ የሚያዝበት ሁኔታ የለም፡፡ ነገር ግን በአንዱ መለኮት በአንዱ አገዛዝ በአንድ ክብር ሁሉን የሚችል የብርሃን ልዕልና አንድ ናቸው” (መሠረት ሰብሐት ለአብ፣ ሥላሴ በተዋህዶ፣ አዲስ አበባ፣ 1988 ዓ.ም፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ታተመ፣ ገጽ 284)፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል ፡-“ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደሆነ ልታውቁ እወዳለሁ” 1ኛ (ቆሮንቶስ 11፡3)፡፡

ታድያ እግዚአብሔር የክርስቶስ (ወልድ) ራስ እንደሆነ እየተገለጸ ለምን ይዋሻል? በተጨማሪ በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ የሚያገኟቸው በርካታ ጥቅሶች እግዚአብሔር የኢየሱስ (ወልድ) የበላይ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ታድያ እውነታውን መቃረን ለምን አስፈለገ?

በሥላሴ አካላት መካከል ስላለው እኩልነት ስንናገር በመለኮታዊ ባሕርይ (Essence) ማለታችን እንጂ በሥራ ድርሻ (Function) ማለታችን አይደለም፡፡ ከአገራችን ታላላቅ የሥነ መለኮት ሊቃውንት መካከል አንዱ የነበሩት መሠረት ስብሐት ለአብም ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ከቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ ጠቅሰው የጻፉት ይህ አስተምህሮ ጠፍቷቸው ሳይሆን በሥላሴ አካላት መካከል ፍቅር እንጂ በሥልጣንና በኃይል መገዛዛት አለመኖሩን አፅንዖት ለመስጠት ነው፡፡ አንዱ የሥላሴ አካል ለሌላው የሚገዛውና የሚላከው በኃይል፣ በሥልጣን ወይም በመለኮታዊ ባሕርይ ከሌላው ያነሰ በመሆኑ ምክንያት ሳይሆን ፍፁም በሆነ ፍቅር የሚኖሩ በመሆናቸው ነው፡፡

28. በዚሁ ምዕራፍ በጥያቄ 2 ለ እና ሐ ላይ የጠየቁትን ስለደገሙ ታልፏል፡፡

29. በአንደኛው ምዕራፍ ቁጥር 30 ላይ የጠየቁትን ስለደገሙ ታልፏል፡፡

30. “ሐዋርያው” የሚባለው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፡- “ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንምና፤ ይህም እግዚአብሔር በነፃ የሰጠን እናውቅ ዘንድ ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 2፡12)፡፡ እንደ ሥላሴ አስተምህሮት መንፈሱም (መንፈስ ቅዱስም) እግዚአብሔር ነው፡፡ እንደዚህ ጥቅስ “ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ” ሲል «መንፈስ» በሚለው ምትክ «እግዚአብሔር» የሚለውን ከተካን (አንድ ናቸው ስለተባለ) ከእግዚአብሔር የሆነውን እግዚአብሔር የሚል ይሆናል፡፡ ታድያ ስንት እግዚአብሔር ነው ያለው?

መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (የሐዋርያት ሥራ 5፡3-4)፡፡ መንፈስ ቅዱስ “እግዚአብሔር” የተባለው ከአብ እና ከወልድ ጋር የአንዱ መለኮት ተካፋይ በመሆኑ እንጂ ከእነርሱ የተነጠለ ህልውና ስላለው አይደለም፡፡ የሥላሴ አካላት ልዩ (Distinct) እንጂ የተለያዩ (Separated) አይደሉም፤ ስለሆነም ሐዋርያው ከእግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን መቀበላችንን መናገሩ ስለ ሁለት የአንዱ የእግዚአብሔር አካላት እየተናገረ መሆኑን እንጂ ስለ ሁለት እግዚአብሔሮች እየተናገረ መሆኑን አያሳይም፡፡

31. ዮሐንስ 1: 14 “ቃልም ስጋ ሆነ” ይላል፡፡ እንደ ክርስቲያኖች እምነት ‹ቃል› አምላክ ነው፡፡ ታድያ አምላክ ስጋ ሆነ ማለት ነው?

አዎ አምላክ ሥጋ ሆኗል፡፡ ይህ ማለት መለኮታዊ ባሕርዩ ጠፍቶ ወደ ሥጋነት ተለውጧል ማለት አይደለም፡፡ ሥጋውም መለኮት ሆኗል ማለት አይደለም፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ እንደተናገረው “አምላክ ሰው ሆነ” ወይም “ቃል ሥጋ ሆነ” ማለት የሰውን ህላዌ ወሰደ፣ ተቀበለ፣ ተገነዘበ፣ የራሱ አደረገ ማለት ነው፡፡[13]

32. የሐዋርያት ሥራ 12፡24 «የእግዚአብሔር ቃል ግን እንደገና እየሰፋ ሄደ» ይላል፡፡ እንደ ክርስትና አስተምህሮት «ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃልና ራሱም አምላክ ነው፡፡» የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ አምላክ ከሆነ እንደዚህኛው ጥቅስ የእግዚአብሔር ቃል እያደገና እየሰፋ ሄደ ማለት ነው፡፡ ታድያ ይህ የሚመስል ነውን?

የአንድ ቃል ትርጉም የሚወሰነው በአውዱ ነው፡፡ በዚህ ቦታ “ቃል” የተባለው ወንጌል ነው፡፡ እየሰፋ መሄዱ የተነገረው በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ለማመልከት ነው፡፡ ዮሐንስ 1፡1-18 ደግሞ “ቃል” ሲል ፍጥረትን የፈጠረውን፣ የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነውን አንድያ ልጁን ለማለት ነው፡፡ የሁለቱ አውድ ለየቅል ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ቁርኣን የአላህ ቃል መሆኑን ሙስሊሞች ያምናሉ፡፡ መልሰው ደግሞ ዒሳም የአላህ ቃል ነው ይላሉ (ሱራ 4፡171)፡፡ ስለዚህ ዒሳ ቁርኣን ነው ማለት ነውን?

ማጣቀሻዎች


[1] ስሜ ታደሰ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ የጥንቱ እና የመካከለኛው ዘመን፣ የኤስ አይ ኤም ሥነ ጽሑፍ ክፍል፣ 2005 ዓ.ም.፣ ገፅ 121-122

[2] ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 122-123

[3] ዶ/ር ፓውል እንዝ፣ ታሪካዊ ሥነመለኮት አመጣጡና ትንተናው፣ በምኒሊክ አስፋውና ሰለሞን ጥላሁን ወደ አማርኛ የተመለሰ፣ የላፕሲሉ/ብሩክስ ፋውንዴሽን፣ አዲስ አበባ፣ 1991፣ ገፅ 19

[4] ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 18

[5] ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 20

[6] ዝኒ ከማሁ

[7] Geislere. Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 68 (pdf)

[8] ዶ/ር ፓውል እንዝ፣ ታሪካዊ ሥነመለኮት አመጣጡና ትንተናው፣ ገፅ 34

[9] ይህ በሥነ አመክንዮ “the Fallacy of Appeal to Authority” ይሰኛል፡፡

[10] http://www.wikipedia.net/wiki/Dark_matter

[11] htpp://www.wikipedia.net/wiki/Dark_energy

[12] አንዳንድ የመካከለኛው ዘመን የእጅ ጽሑፎች በሦስቱ ምስክሮች ቦታ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስን የተኩ ሲሆን የ1ኛ ዮሐንስ መልዕክት በኩረ ጽሑፍ አካል እንዳልሆነ ተረጋግጧል፡፡

[13] መሠረት ስብሐት ለአብ፣ ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ፣ በጥንታውያን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መምህራን ፍለጋ፣ አርቲስቲክ ማተምያ ቤት፣ 1991 ዓ.ም. ገፅ፣ 77

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ