ምዕራፍ 7: ኢየሱስን ማነው ብለው አመኑበት? ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ

ምዕራፍ 7

ኢየሱስን ማነው ብለው አመኑበት?

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ ካቆምንበት እንቀጥላለን

  1. ዮሐንስ 6፡14 እንዲህ ይላል “ሰዎቹም ኢየሱስ ያደረገውን ተአምራዊ ምልክት ካዩ በኃላ ወደ ዓለም የሚመጣው ነብይ በእርግጥ ይህ ነው አሉ፡፡” ይህን የተናገሩ ሰዎች አማኞች ናቸው ወይስ ከሀዲ? ኢየሱስን ያዩት ሰዎች ነብይ ነው ብለው አመኑ፡፡ ልክ እንደ መስሊሞቹ ታዲያ ክርስቲያኖች ይህንን ለምን ተቃርነው አምላክ ነው አሉት?

ክርስቲያኖች ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን አያምኑም ያለው ማነው? የአገራችን የሥነ መለኮት ሊቅ የነበሩት መሠረት ስብሐት ለአብ የኢየሱስን ነቢይነት በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፡- “በመሲህነቱ ፍጹም ጠባቂ ታላቅ ነቢይና ዓይነተኛ ሊቀ ካህናት ዘለዓለማዊም ንጉሣችን የሆነ በአንዲት ተዋሕዶ ህላዌ የሚሰገድለት ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡”[1]

ኢየሱስ አምላክም ሰውም ከሆነ አምላክም ነቢይም መሆን የማይችልበት ምክንያት የለም፡፡ ነገር ግን የነቢይነት አገልግሎት ቢፈፅምም መለኮታዊ ወልደ እግዚአብሔር ነው፡፡ ጠያቂው ለክርስቲያናዊ አስተምህሮ ፍፁም እንግዳ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡

2. ማቴዎስ 9፡8 “ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ በመደነቅ በፍርሃት ተሞልተው፥ እንደዚህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡” ኢየሱስ አስገራሚ ተአምር ሲያደርግ ኢየሱስ ምንድነው ብለው አመኑ? ተዓምሩስ የማን ነው? አድራጊውስ ማን ነው? ጥቅሱ “እንደዚህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ” ይላል፡፡ ታድያ ክርስቲያኖች ለምን ኢየሱስን ተዓምራትን ሲያሳይ በስፍራው ከተገኙት አማኞች ተቃራኒ እምነት ያዙ?

በሌላ ጊዜ ደግሞ ይኸው ሕዝብ ኢየሱስ በብኤል ዜቡል ኃይል ተዓምራትን እንደሚያደርግ ተናግሮ ነበር (ሉቃስ 11፡15፣ ዮሐንስ 8፡48)፡፡ በአንድ ወቅት የገዛ ዘመዶቹ “አብዷል” ብለው ሊይዙት መጥተው ነበር (ማርቆስ 3፡21)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስና በርናባስ ተዓምር ሲያደርጉ ያዩ ሕዝቦች “አማልክት ናቸው” በማለት ሊሰውላቸው ደርሰው ነበር (የሐዋርያት ሥራ 14፡11)፡፡ የጠያቂው አመክንዮ ትክክል ከሆነ የእነርሱን ድምዳሜ ልንቀበል ነው፡፡ ነገር ግን አስተምህሯችንን መመስረት ያለብን ክርስቶስ እራሱና በእርሱ የተመረጡት ሐዋርያቱ ስለ ማንነቱ ባስተማሩት ትምህርት ላይ እንጂ ብዙ ጊዜ በመሳሳት በሚታወቀው በሕዝብ አስተያየት ላይ መሆን የለበትም፡፡

3. ዮሐንስ 17፡6-9 እንዲህ ይላል፦ “ከነዚህ ከዓለም ለሠጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ፡፡ የአንተ ነበሩ ለእኔ ሰጠኸኝ፣ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል፡፡ የሰጠኸኝ ሁሉ ካንተ እንደሆነ አሁን አውቀዋል፥ ምክኒያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸው ተቀብለዋል፤ እኔም ካንተ እንደወጣሁ በርግጥ አውቀዋል አንተ እንደላክኽኝም አምነዋል፡፡ እነርሱ የአንተ ስለሆኑ፣ እጸልይላቸዋለው፣ ለሠጠኸኝና የአንተ ለሆኑት እንጂ ለዓለም አልጸልይም፡፡” ኢየሱስ እንደነገረን ሐዋርያት ኢየሱስ ምን መሆኑን አመኑ? ከአምላክ መላኩን! ታዲያ ለምን ክርስቲያኖች በተቃራኒው ተረዱ?

በጥቅሱ መሠረት ሐዋርያት ኢየሱስ በአብ የተላከ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ከአብ የወጣ መሆኑንም ጭምር ነው ያመኑት፡፡ ይህ ደግሞ ኢየሱስ ከአብ ባሕርይ የተገኘ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ የመለኮትነቱ ማስረጃ ነው፡፡ በተጨማሪም ሐዋርያቱ “ኢየሱስ በአብ የተላከ ምን መሆኑን ነው የማኑት”? ብሎ መጠየቅም አስፈላጊ ነው፡፡ ሐዋርያቱ ኢየሱስ እንደ ማንኛውም ነቢይ በአብ የተላከ መልዕክተኛ መሆኑን ሳይሆን በአብ የተላከ ቅዱስ ልጁ እና ጌታ መሆኑን ነው ያመኑት (ማቴዎስ 14፡33፣ 16፡16-17፣ ዮሐንስ 13፡13-14)፡፡ ይህ ደግሞ የጠያቂውን እምነት ከስረ መሠረቱ የሚንድ ግንዛቤ ነው፡፡

4. የሐዋርያት ሥራ 11፡25-26 “ከዚህ በኋላ በርናባስ ሳውልን ለመፈለግ ወደ ጠርሴስ ሄደ ባገኘውም ጊዜ ወደ አንፆኪያ አመጣው፡፡ ሁለቱም እዚያ ካለችው ቤተክርስቲያን ጋር በመሆን አንድ ዓመት ሙሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ አስተማሩ፣ ደቀ መዛሙርትም ለመጀመረያ ጊዜ በአንፆኪያ ክርስቲያን ተብለው ተጠሩ፡፡” እንደዚህ ጥቅስ አገላለጽ ሰዎች ለመጀመረያ ጊዜ በአንጾንኪያ “ክርስቲያን” ከተባሉ እንዴት ኢየሱስ ክርስትናን ሰበከ አስተማረ ሊባል ይችላል?

“ክርስቲያን” ማለት “የክርስቶስ ወገን” ማለት ነው፡፡ የክርስቶስን ትምህርት የተከተሉ ሰዎች የእርሱ ወገን ካልተባሉ ምን ሊባሉ ነው? ደቀ መዛሙርት ይህንን ስም እንዲያገኙ ያስቻላቸው የክርስቶስን ትምህርት መከተላቸው ነው፡፡ ማንኛውም የእምነት ቡድን ስያሜውን የሚያገኘው ከተጀመረ በኋላ ነው፡፡ ክርስቶስ ክርስትናን ጀመረ፡፡ እርሱ የጀመረውም ትምህርት ተስፋፍቶ ከተደራጀ በኋላ ስያሜውን ከእርሱ አገኘ፡፡ ስያሜው እርሱ ላስተማረው እምነት የተሰጠ መሆኑን ከተገነዘብን እንዴት ክርስቶስ ክርስትናን አላስተማረም ልንል ይቻለናል?

5. ዮሐንስ 17፡25 “ፃድቅ አባት ሆይ ዓለም ባያውቅህም እኔ አውቅሃለው እነዚህም አንተ እንደላከኽኝ ያውቃሉ፡፡” ይላል፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ እንደተገለጸው ሐዋርያት ኢየሱስን ምን መሆኑን ያውቃሉ ተባለ? “እነዚህም አንተ እንደ ላከኸኝ ያውቃሉ፡፡” ታዲያ ክርስቲያኖች ይህን አምነው መቀበል ለምን ተሳናቸው?

ጉድ! አሕመዲን ጀበል ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ እንደተላከ የማያምን ክርስቲያን የት አገር ይሆን የገጠማቸው?? ሰውየው “303 ጥያቄዎች” የሚለውን የመጽሐፉን ርዕስ አስቀድመው ጽፈውት ኖሮ ቁጥሩን ለመሙላት የተቸገሩ ነው የሚመስሉት፡፡

6. ሉቃስ 24፡19 “እርሱም እንዲህ አለ “በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት በተግባርና በቃል ብርቱ ነብይ ስለነበረው ስለናዝሬቱ ኢየሱስ ነው” ይላል፡፡ እነዚያ ኢየሱስ ተዓምር ሲያደርግ የነበሩና የተመለከቱት ኢየሱስን ማን ብለው ገለፁት? “ነብይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ፡፡” አምላክ ነው ብለው አስበው ነበርን? በጭራሽ ታድያ ክርስቲያኖች እነዚያ ያላመኑትን ምነው ማመናቸው?

አውዱ የሚናገረው ከኢየሱስ ሞት በኋላ ተስፋ ቆርጠው ወደ መንደራቸው ሲሄዱ ስለነበሩት ሁለት ደቀ መዛሙርት ነው፡፡ መሲሁ እንደማይሞት ከሚያምነው የአይሁድ ማሕበረሰብ እንደመምጣታቸው የኢየሱስ ሞት እምነታቸውን ሸርሽሮታል፤ ተስፋም አስቆርጧቸዋል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ከሙታን ተነስቶ ስለነበረ ወደ እነርሱ ቀርቦ አብሯቸው እያዘገመ ያዋራቸው ጀመር፡፡ ከላይ የተጠቀሰውን ቃል የተናገሩት ለእርሱ ለራሱ ነበር፡፡ ኋላ ግን ክርስቶስ እንደሚሞትና እንደሚነሳ ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ካስረዳቸው በኋላ ወደ ቤታቸው ሲደርሱ ማንነቱን አወቁ፡፡ እርሱ ግን ተሰወረባቸው፡፡ ወደ ኢየሩሳሌምም በፍጥነት ተመልሰው የሆነውን ለሐዋርያት ሲነግሩ ሳሉ ድንገት ኢየሱስ ራሱ በተዘጋ ቤት ውስጥ በመግባት በመካከላቸው ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው፡፡ ሉቃስ ታሪኩን ይቀጥልና እስከ ዕርገት ድረስ የነበረውን ሁኔታ በአጭሩ ይነግረናል፡፡ በመጨረሻም እንዲህ በማለት ይደመድማል፡- “ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ፡፡ እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ” (ሉቃስ 24፡51-52)፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ጌትነቱና አምላክነቱ ደብዝዞባቸው ወደ ቀድሞ ኑሯቸው ሲመለሱ የነበሩት ደቀ መዛሙርት እውነቱን ተረድተው ሰግደውለታል፡፡ እኛም እንደ እነርሱ ለጌትነቱና ለአምላክነቱ የሚገባውን ስግደት ብንሰጠው ምኑ ላይ ነው ስህተታችን?

7. ዮሐንስ 6፡14 “ሰዎቹም ኢየሱስ ያደርገውን ተአምራዊ ምልክት ካዩ በኋላ ወደ ዓለም የሚመጣው ነብይ በእርግጥ ይህ ነው አሉ” ይላል፡፡ የኢየሱስን ተአምራዊ ምልክት አይተው የዛሬ ክርስቲያኖች እንደሚሉት “ኢየሱስ ጌታ ነው! አምላክ ነው!” ነበር ያሉት? ጥቅሱ የሚነግረን “የሚመጣው ነብይ በእርግጥ ይህ ነው” እንዳሉ ነው፡፡ ክርስቲያኖች ታድያ ምን ነው ይህን ማመን አልፈለጉም?

ክርስቲያኖች ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን ያምናሉ ነገር ግን ነቢይ ብቻ ነው አይሉም፡፡ ሕዝቡ በገባው መጠን መስክሯል ነገር ግን የሕዝቡን ምስክርነት መሠረት አድርገን ለድምዳሜ አንፈጥንም፡፡ ጠያቂው ኢየሱስን በቅርበት የማያውቀውን ሕዝብ ምስክርነት ከተቀበሉ ኢየሱስን በቅርበት የሚያውቁትን የሐዋርያቱን ምስክርነት ይበልጥ መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ ሐዋርያቱ ተዓምራቱን ካዩ በኋላ የሰጡት ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል፡- “በታንኳይቱም የነበሩት፦ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት፡፡” (ማቴዎስ 14፡33)፡፡ እኛም ከእነርሱ ጋር በመስማማት የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንመሰክራለን፤ እንደ ጌትነቱና እንደ አምላክነቱ መጠን የሚገባውንም ስግደት እንሰጠዋለን፡፡

8. የሐዋርያት ሥራ 2፡22 “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ይህን ቃል ስሙ፤ እናንተ እራሳችሁ እንደምታውቁት እግዚአብሔር በመካከላችሁ ተዓምራትን ድንቅ ነገሮችና ምልክቶችን በእርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል” ይላል፡፡ እነርሱ ምንድን ነው የሚያውቁት ኢየሱስ ተአምራት ያደርገው አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ ብለው ነው? በጭራሽ! በመካከላችሁ “ተአምራትን ድንቅ ነገሮችንና ምልክቶችን በእርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል፡፡” ነው የሚለው ታድያ ክርስቲያኖች ለምን ይህን ተቃረኑ?

እግዚአብሔር አብ ተዓምራትን በእርሱ በኩል በማድረግ ስለ ገዛ ማንነቱ ያስተማራቸው ትምህርቶች ትክክል መሆናቸውን ነው የመሰከረለት፡፡ ኢየሱስ የራሱን ማንነት በተመለከተ የተናገራቸውን ነገሮች በጥንቃቄ ካነበበ በኋላ እንደ ማንኛውም ነቢይ መሆኑን ሊደመድም የሚችል ማንም አይኖርም፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ ጠያቂው የጠቀሱትን ቃል ከተናገረ በኋላ በማስከተል እንዲህ በማለት የክርስቶስን ጌትነት አወጀ፡- “ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፥ ነገር ግን እርሱ፦ ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ፡፡ እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ” (የሐዋርያት ሥራ 2፡34-36)፡፡ ዳዊት ኢየሱስን “ጌታዬ” ብሎ ከጠራው፤ እግዚአብሔር አብም በእርሱ በኩል ተዓምራትን በማድረግ ጌትነቱን ከመሰከረለት ሙስሊም ወገኖች ጌትነቱን የማይቀበሉበት ምክንያት ምንድነው?

9. ከላይ በቁጥር 5 ላይ ከጠየቁት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ታልፏል፡፡

10. በምዕራፍ 1 ቁጥር 61 ላይ የጠየቁትን ጥያቄ ስለደገሙ ታልፏል፡፡

11. ዮሐንስ 7፡16-17 “ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው “የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው፡፡ ማንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ቢፈልግ የእኔ ትምህርት ከእግዚአብሔር ወይም ከራሴ የመጣ መሆኑን ለይቶ ያውቃል” ይላል፡፡ ኢየሱስ የሚያስተምረው ትምህርት ከራሱ ሳይሆን ከላከው አምላክ መሆኑን እየገለጸ እንዴት ክርስቲያኖች ክርስቶስን አምላክ ሊሉት ቻሉ?

ይህንን ጥቅስ ኢየሱስ መለኮታዊ ክብሩን በመተው ራሱን ባዶ አድርጎ የባርያን መልክ ይዞ መምጣቱን በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አውድ ማየት ያስፈልጋል (ፊልጵስዩስ 2፡5-11)፡፡ ኢየሱስ ራሱን ለማክበርና ከፍ ከፍ ለማድረግ ስላልመጣ በአምላካዊ ባሕርዩ ሳይሆን በሰብዓዊነቱ በሰዎች ፊት ለመታየትና ለማገልገል በመወሰኑ ምክንያት ፍፁም ሰው ሆኖ ተመላልሷል፡፡ ይህንንም በቀጣዩ ቁጥር ላይ አስታውቋል፡- “ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም፡፡” (ቁ.18)፡፡ ኢየሱስ የራሱን ክብር ለመፈለግ አለመምጣቱን ከአብ የሰማውን ብቻ በመናገር አሳይቷል፡፡

12. ዮሐንስ 7፡40 ላይ የሚገኘውን በመጥቀስ ስለ ነቢይነቱ ቀደም ሲል የጠየቁትን ስለደገሙ ታልፏል፡፡

13. ዮሐንስ 9፡17 “ስለዚህ አይነ ስውር ወደ ነበረው ሰው ተመልሰው አይንህን ስለከፈተው ሰው እንግዲህ አንተ ምን ትላለህን? አሉት፡፡ ሰውየውም “እርሱ ነብይ ነው አለ” ይላል፡፡ በኢየሱስ ተአምር አይነ ስውርነቱ የተወገደለተ ግለሰብ ኢየሱስን “ነብይ” ካለ ከዘመናት ቆይታ በኋላ የተነሱት ክርስቲያኖች ሙስሊሞች “ኢየሱስ ነብይ ነው” በማለታቸው እንዴት ሊያወግዙ ቻሉ?

ሙስሊሞች ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን በማመናቸው አልተሳሳቱም፡፡ ይህንንም በማመናቸው ምክንያት በክርስቲያኖች አልተወገዙም፡፡ ነገር ግን “ነቢይ ብቻ ነው” በማለት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ስለ አምላክነቱና የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ስለመሆኑ የተገለጡትን እውነቶች በመካዳቸው ነው የተሳሳቱት፡፡ አሕመዲን ንባባቸውን ባያቆሙ ኖሮ ኢየሱስ ማንነቱን ከገለጠለት በኋላ የተፈወሰው ሰው የሰጠውን ምላሽ ማየት በቻሉ ነበር፡- “ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ ሲያገኘውም፦ አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው፡፡ እርሱም መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? አለ፡፡ ኢየሱስም፦ አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው አለው፡፡ እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም፡፡” (ቁ. 35-38)፡፡ ሰውየው መጀመርያ ነቢይ መሆኑን ብቻ ነበር ያወቀው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ሲገነዘብ ደግሞ ጌትነቱን ተቀብሎ በፊቱ በመስገድ የሚገባውን ክብር ሰጥቶታል፡፡

14. ጠያቂው ዮሐንስ 4፡19 ላይ የሚገኘውን በመጥቀስ ኢየሱስ ነቢይ እንጂ አምላክ አይደለም በማለት ይሞግታሉ፡፡ ኢየሱስ “ነቢይ” ከተባለ አምላክ ሊሆን አይችልም የሚለውን የተሳሳተ ግንዛቤያቸውን ቀደም ሲል መልስ ሰጥተንበታል፡፡

15. እዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 6 ላይ የጠየቁትን ስለደገሙ ታልፏል፡፡

16. ሉቃስ 7፡14-16 ላይ ስለ ኢየሱስ ነቢይነት ሕዝቡ የተናገረውን በመጥቀስ የተለመደውን ሙግታቸውን አቅርበዋል፡፡ አዲስ ነገር ስለሌለው ታልፏል፡፡

17. ማቴዎስ 21፡11 “ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜም ከተማዋ በመላ፤ “ይህ ማነው?” በማለት ታወከች፡፡ አጅቦት የመጣው ሕዝብም፤ “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ፡፡” ይላል ፡፡ ኢየሱስን አጅቦት አብሮት ሲጓዝ የነበረው ሕዝብ “ነቢዩ ኢየሱስ ” ሲለው ምነው ክርስቲያኖች “አምላክ” ነው ማለታቸው? አምላክ እንዲሰኝ ፈልገው ይሆንን? አምላክነትስ በፍላጎት ይገኛል እንዴ? ከሙስሊሞችና ከክርስቲያኖች ሊዩነት  ውስጥ አንዱ የኢየሱስ ማንነት ጥያቄ ነው፡፡ ለመሆኑ ኢየሱስ ማን ነው? ኢየሱስ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ “ይህ ማነው?” ነበር የህዝቡ ጥያቄ፡፡ ምላሹንም አጅበው አብረው ወደ ኢየሩሳሌም የመጡት አማኞች እንዲህ ሲሉ ነበር የገለጹት “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው፡፡” ታዲያ ክርስቲያኖች ኢየሱስን አጅበው አብረው ሲጓዙ ከነበሩት አማኞች በልጠው ነው ነቢይነቱን ያልተቀበሉት?

የተወደዱት ጠያቂያችን “ክርስቲያኖች ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን አይቀበሉም”  የሚለውን ቅጥፈት በዚህ ምዕራፍ ከሞላ ጎደል በሁሉም ጥያቄዎች ውስጥ አንፀባርቀዋል፡፡ ይህ ደግሞ ምን ያህል የግንዛቤ እጥረት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር አብዛኞቹ ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው አንብበው ከመረዳት ይልቅ መረጃዎቻቸውን የሚያገኙት ከእንደነዚህ ዓይነት ወገኖች መሆኑ ነው፡፡ ሰውየው የጠቀሱት ጥቅስ የኢየሱስን አምላክነት በግልፅ ከሚናገሩት የአዲስ ኪዳን ክፍሎች መካከል አንዱ መሆኑን አለማስተዋላቸው የሚያስገርም ነው፡፡ በዚያኑ ዕለት “የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም፦ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቁጥተው፦ እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት፡፡ ኢየሱስም፦ እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው፡፡” (ቁ.15-16)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲዘምሩለት የነበሩትን ህፃናት ዝም እንዲያሰኝ በተጠየቀ ጊዜ በቀጥታ በመዝሙረ ዳዊት 8፡2 ለያሕዌ እግዚአብሔር የተነገረውን ጥቅስ በመውሰድ ለራሱ አደረገ፡፡ ይህም የአምላክነቱ ማስረጃ ነው፡፡

በክርስቶስ ዘመን የነበሩት ሕዝቦች የኢየሱስን ማንነት ጠይቀዋል፤ በገባቸው መንገድም ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን ማንነቱን በተመለከተ ከሕዝቡ ምስክርነት ይልቅ እጅግ አስተማማኝ ማስረጃ አለን፡፡ በአንድ ወቅት ኢየሱስ ማንነቱን የተመለከተ ጥያቄ ለደቀ መዛሙርቱ አቅርቦ ነበር፡- “ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፦ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ፡፡ እነርሱም፦ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት፡፡ እርሱም፦ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ፡፡” አዎን፣ በዘመኑ የነበሩት ብዙ ሰዎች ነቢይነቱ ተረድተዋል፡፡ ነገር ግን ያልተረዱት አንድ ትልቅ ጉዳይ ነበር፤ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ትንቢት የተነገረለት መሲህ እና የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን፡፡ ይህንን እውነታ መረዳት የሚችሉት እግዚአብሔር በቅዱስ መንፈሱ ልቦናቸውን ያበራላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የሙስሊም ወገኖቻችንን የልብ ዓይኖች በመክፈት ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ማመን ይችሉ ዘንድ፣ አምነውም በስሙ ሕይወት ይሆንላቸው ዘንድ ይርዳቸው፡፡

ማጣቀሻዎች


[1] መሠረት ስብሐት ለአብ፣ ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ፣ በጥንታውያን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መምህራን ፍለጋ፣ አርቲስቲክ ማተምያ ቤት፣ 1991 ዓ.ም. ገፅ፣ 71

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ