መንደርደርያ

መንደርደርያ

ብዙ ክርስቲያን ወዳጆቼ ከሙስሊም ወገኖች ጋር ረጅም ጊዜ የፈጀ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነገሩ ኹሉ ከርሞ ጥሬ እየሆነባቸው እንደሚቸገሩ ይነግሩኛል፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍትንና የታሪክ ማስረጃዎችን እያጣቀሳችሁ፣ ከክርስቲያናዊ ሙዳዬ ቃላት ተመዝዘው በመልካም ኹኔታ የተሰደሩ ነገረ መለኮታዊ ቃላትን ተጠቅማችሁ፣ በአመክንዮ አዋዝታችሁ ስለ ሥላሴ፣ ስለ ኢየሱስ አምላክነትና ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ተዓማኒነት ካብራራችሁ በኋላ ልፋታችሁ ኹሉ ድንጋይ ላይ ውኀ እንደ ማፍሰስ መና ይኾንባችኋል፡፡ አሰልቺ የጥያቄዎች ናዳ… ደረቅ ክርክር… ማስረጃዎችን በጭፍን መካድ… ብርሃን በበራላቸው መጠን ጨለማ የሚበረታባቸው ወገኖች… ከሙስሊሞች ጋር ውይይት ውስጥ የገባ ሰው ኹሉ ከዚህ ተስፋ አስቆራጭ ኹኔታ ጋር ይጋፈጣል፡፡ ችግሩ ከእስላማዊው መነፅር ሲሆን መፍትሔውም ሙስሊሞች እንዲያወልቁት መርዳት ነው፡፡ ይህንን እስላማዊ መነፅር ያልተገነዘቡ ክርስቲያኖች ከሙስሊሞች ጋር በሚወያዩበት ወቅት ሁለት የተለያዩ ቋንቋዎችን የመናገር ያህል አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ ያልተደመጡም ስለሚመስላቸው መሰል ውይይቶችን በማድረግ ላይ ተስፋ በመቁረጥ ወንጌልን የማድረስ አቅማቸው ይሰለባል፡፡

እስላማዊውን መነፅር አስቀድሞ በመረዳት ቀለል ባለ አገላለፅ ማስረዳት ለፍሬያማ ውይይት ወሳኝ ነው፡፡ በክርስትናና በእስልምና ሥነ መለኮታዊ አስተምሕሮዎች መካከል የሚገኙትን ልዩነቶች ማወቅና በቁርኣን ውስጥ የሚገኙትን የተሳሳቱ ግንዛቤዎች መለየት ሙስሊሞች ጥያቄ ሲጠይቁም ሆነ መልስ ሲሰጡ ከምን አኳያ እንደሆነ እንድንረዳ ስለሚያስችለን ለተሳካ ውይይት በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡

ሙስሊም ወገኖቻችን ንፅረተ ዓለማቸው የተቃኘው በቁርኣን በመኾኑ ክርስትናን የሚመለከቱት በቁርኣን መነፅር ነው፡፡ ቁርኣን በሥነ መለኮታዊ ይዘቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ በእጅጉ የተለየ ከመኾኑም በላይ በክርስቲያናዊ አስተምሕሮዎች ላይ ቀጥተኛ ትችቶችን ይሰነዝራል፡፡ እነዚህ ትችቶችና ተቃውሞዎች ከሞላ ጎደል ክርስቲያናዊውን አስተምሕሮ በተሳሳተ መንገድ በማቅረብ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸው ደግሞ ሙስሊሞች ክርስትናን ለመረዳት በእጅጉ እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል፡፡

ሙስሊም ወገኖች የኢየሱስን አምላክነት ለመቀበል የሚቸገሩት የእግዚአብሔርን ሥሉስ አሓዳዊነት መረዳት ስለሚሳናቸው ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ሥሉስ አሓዳዊነት ለመረዳት የሚቸገሩት ደግሞ በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመርያው እስልምና ስለ ፈጣሪ አንድነት ያለው አመለካከት ነው፡፡ እስልምና ስለ ፈጣሪ አንድነት ያለው ግንዛቤ ፈጣሪ በአካልም በመለኮትም ሌጣ አንድ (Monadic) እንደሆነ ሲሆን ይህ እምነት “ነጠላ አሓዳዊነት” (Unitarian Monotheism) ይሰኛል፡፡ የእስልምና ነጠላ አሓዳዊነት እምነት በፈጣሪ ማንነት ውስጥ ምንም ዓይነት ብዝሐነት መኖሩንና መኖር መቻሉን የሚክድ በመኾኑ ብዙ ሙስሊሞች እግዚአብሔር በመለኮታዊ ባሕርዩ አንድ ኾኖ በሦስት አካላት የተገለጠ መኾኑን የሚያስተምረውን የክርስትናን ትምሕርት እንደ መድብለ አማልክታዊነት እንዲቆጥሩት አድርጓቸዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ስለ እግዚአብሔር አንድነት የሚናገሩትን ጥቅሶች የሚተረጉሙት በዚሁ የነጠላ አሓዳዊነት አመለካከት መሠረት ሲሆን የእግዚአብሔርን ሥሉስ አሓዳዊነት ለመረዳት በእጅጉ ይቸገራሉ፡፡ ኢየሱስ አምላክ መኾኑንና ደግሞም የእግዚአብሔር ልጅ መባሉን ሲሰሙ ግራ የሚጋቡት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ “ኢየሱስ አምላክ ከሆነ እንዴት የአምላክ ልጅ ሊሆን ይችላል? እንዴት ወደ እግዚአብሔር ሊጸልይ ይችላል? እንዴት በእግዚአብሔር የተላከ ሊሆን ይችላል? ወዘተ.” በማለትም ይጠይቃሉ፡፡ እንዲህ ያሉ መደበኛ የሚመስሉ እስላማዊ ጥያቄዎች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በብዛት ተነስተዋል፡፡

ሁለተኛውና ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የቁርኣን ጸሐፊ ክርስቲያኖች በሦስት አማልክት የሚያምኑ በማስመሰል መናገሩ ነው፡፡ ቁርኣን ሱራ 4፡171 ላይ ለክርስቲያኖች “(አማልክት) ሦስት ናቸው አትበሉ” የሚል መልዕክት ያስትላልፋል፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኖች በየትኛውም ዘመን “አማልክት ሦስት ናቸው” በማለት አምነው አያውቁም፡፡ ትክክለኛው የክርስትና አስተምሕሮ አንድ አምላክ ብቻ እንዳለና ይህ አንዱ አምላክ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የተሰኙ ሦስት አካላት እንዳሉት የሚናገር ነው፡፡ የቁርኣን ጸሐፊ “አንዱ አምላክ ሦስት አካላት አሉት አትበሉ” ቢል ኖሮ በእርግጥም ክርስትያናዊውን አስተምሕሮ የሚመለከት አባባል በሆነ ነበር፡፡ ቁርኣን የነቀፈው ይህ አስተምሕሮ ለክርስትና ባዕድ በመኾኑ ይህ ትምሕርት በክርስትና ውስጥ እንደሚገኝ በማስመሰል የተናገረው ሰው ሐሰተኛ ነው፡፡

የቁርኣን ጸሐፊ የሥላሴን አስተምሕሮ በትክክል ያቀረበበት አንድም ጥቅስ የለም፡፡ ሦስቱን የሥላሴ አካላት፣ ማለትም አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስን በጋራ አንድም ጊዜ አልጠቀሰም፡፡ ከዚህ በተፃራሪ ተከታዩን ጥቅስ በመጻፍ ሙስሊሞችን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ የመራ መልዕክት አስተላልፏል፡-

“አላህም፡- የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ አንተ ለሰዎቹ፡- እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን? በሚለው ጊዜ (አስታውስ)፤ ጥራት ይገባህ፤ ለኔ ተገቢዬ ያልሆነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም፤ ብዬው እንደሆነም በእርግጥ አውቀኸዋል፤ በነፍሴ ውስጥ ያለውን ኹሉ ታውቃለህ፤ ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም፤ አንተ ሩቆችን ኹሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና ይላል” (ሱራ 5፡116)፡፡

ይህ ምናባዊ ምልልስ በዕለተ ቂያማ (በፍርድ ቀን) በአላህና በዒሳ መካከል የሚደረግ እንደሚሆን ሙስሊሞች ያምናሉ፡፡ የቁርኣን ጸሐፊ መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ አካል መኾኑ በክርስቲያኖች መታመኑን የጠቀሰበት ቦታ ባለመኖሩ ብዙ ሙስሊሞች ከዚህ ጥቅስ በመነሳት ሥላሴ ማለት አላህ፣ ማርያምና ኢየሱስ እንደሆኑ ያስባሉ፡፡ በዚህ ዘመን የሚገኙት አንዳንድ ሙስሊም ምሑራን አሸማቃቂ የሆነውን ይህንን የቁርኣን ስሁት መረዳት አለባብሶ ለማለፍ የተለያዩ ትርጉሞችን ለመስጠት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጥንታዊያን ሙስሊም ሊቃውንት ይህ ጥቅስ ስለ ሥላሴ የሚናገር መኾኑን በጽሑፎቻቸው አስፍረዋል፤ በዚህ ዘመን የሚገኙት ብዙ ሙስሊሞችም ተመሳሳይ አመለካከት ያንፀባርቃሉ፡፡[1] ለክርስቲያናዊ አስተምሕሮ መሠረታዊ እውቀት የጎደለው ሰው ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ክርስቲያን ሥላሴ ማለት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ መኾኑን ያውቃል፡፡ ክርስቲያኖች ኢየሱስና ማርያም ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች እንደሆኑ አያምኑም፡፡ ነገር ግን አንዱና ብቸኛው አምላክ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ የተሰኙ ሦስት አካላት እንዳሉት ያምናሉ፡፡

የሥላሴን ትምሕርት እንደተገነዘቡ የሚናገሩ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ሙስሊም ወገኖች ደግሞ አስተምሕሮውን ከሰባሊዮስ አመለካከት ጋር ሲያምታቱት ይስተዋላሉ፡፡ ሰባሊዮስ እግዚአብሔር ነጠላ አካል ብቻ እንዳለው ነገር ግን ራሱን እየለዋወጠ እንደገለጠ ያስተማረ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን የኖረ ሰው ነበር፡፡[2] ሱራ 4፡171 ላይ ከተጻፈው ጋር በሚጣረስ ኹኔታ የቁርኣን ጸሐፊ ተከታዩን ሐሳብ ይናገራል፡-

“እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፤ አልመሲሕም አለ፦ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ፤ እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት፤ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡” (5፡72)

መጽሐፍ ቅዱስ መሲሁ ኢየሱስ አምላክ መኾኑን በበርካታ ስፍራዎች ላይ ይናገራል፡፡ (ዮሐ. 1፡1፣ 20፡28 ሮሜ 9፡5፣ ቲቶ 2፡13፣ ዕብራውያን 1፡8-10)፡፡ ከላይ በተቀመጠው የቁርኣን ጥቅስ ውስጥ ክርስቲያኖች “አላህ የመርየም ልጅ አልመሢህ ነው” እንደሚሉ ተነግሯል፡፡ “አላህ” የሚለው እግዚአብሔርን ለማመልከት የገባ የአረብኛ ቃል ነው ብንል “ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው” ማለት እና “እግዚአብሔር ክርስቶስ ነው” ማለት ከፍተኛ የሆነ ልዩነት አላቸው፡፡ በክርስትና አስተምሕሮ መሠረት እግዚአብሔር በመለኮቱ ፍጹም አንድ ቢሆንም ነገር ግን በአካል ነጠላ ስላልሆነ ለአብ እና ለመንፈስ ቅዱስ እውቅናን በመንፈግ “እግዚአብሔር ክርስቶስ ነው” የሚለው አባባል ከክርስትና ትምሕርት ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ምንም ዓይነት ድጋፍ የለውም፡፡ የአብ እና የመንፈስ ቅዱስን ሕልውና በመካድ ኢየሱስ ብቸኛው የእግዚአብሔር አካል እንደሆነ የሚያስተምረው ትምሕርት ሙሐመድ ከመወለዳቸው ከሦስት ክፍለ ዘመናት በፊት በቤተክርስቲያን ተወግዟል፡፡ ሙሐመድ “ነቢይ” ተብለው በምድረ አረብ ከመነሳታቸው በፊት የተጻፉ ኢየሱስ እግዚአብሔር መኾኑን መናገር ትክክል መኾኑን ነገር ግን እግዚአብሔር ኢየሱስ መኾኑን መናገር ስህተት መኾኑን የሚገልፁ ክርስቲያናዊ ጽሑፎች አሉ፡፡[3]

የቁርኣን ጸሐፊ ስለ ሥላሴ አስተምሕሮ ያለው የተሳሳተ አመለካከት በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ እስኪ ተከታዩን ጥቅስ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፡-

“እነዚያ አላህ የሦስት ሦስተኛ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፤ ከአምላክም አንድ አምላክ እንጅ ሌላ የለም፤ ከሚሉትም ነገር ባይከለከሉ፣ ከነሱ እነዚያን የካዱትን አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ይነካቸዋል” (5፡73)፡፡

በክርስትና አስተምሕሮ መሠረት እግዚአብሔር የሦስት ሦስተኛ ሳይኾን በሦስት አካላት የሚኖር አንድ አምላክ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በስፋት እንደምንመለከተው ለዚህ አስተምሕሮ ከበቂ በላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በየትኛውም ዘመን ክርስትያኖች እግዚአብሔር የሦስት ሦስተኛ እንደሆነ አምነው አያውቁም፡፡ ምናልባት ከላይ በተጠቀሰው የቁርኣን ቃል ውስጥ አላህ የተባለው እግዚአብሔር አብን ለማመልከት ከሆነ፤ በሥላሴ ውስጥ እግዚአብሔር አብ መጀመርያ እንጂ ሦስተኛ አይደለም፡፡ ክርስቲያኖች የሥላሴን አካላት ሲጠሩ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በማለት አብን ያስቀድማሉ (ማቴ 28፡19)፡፡ የቁርኣን ጸሐፊ ስለ ክርስትና አስተምሕሮ ምንም ዕውቀት የሌለው ሰው መኾኑ ግልፅ ነው፡፡

የቁርኣን ጸሐፊ ስለ ክርስትና አስተምሕሮ ምንም ፍንጭ ያልነበረው ሰው መኾኑ የተጋለጠበት ሌላው አጋጣሚ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን ለማስተባበል በሞከረበት ወቅት ነው፡፡ ሱራ 23፡91 እንዲህ ይነበባል፡-

“አላህ ምንም ልጅን አልያዘም (አልወለደም)፡፡ ከእርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም…”

እንዲሁም ሱራ 9፡30 ላይ ጸሐፊው ስለ ክርስቲያኖች በእርግማን የታጀበ ንግግር ይናገራል፡-

“አይሁድ ዑዘይር የአላህ ልጅ ነዉ፣ አለች፤ ክርስቲያኖችም አልመሲሕ የአላህ ልጅ ነዉ አሉ፤ ይህ በአፎቻቸዉ (የሚናገሩት) ቃላቸው ነው፤ የነዚያን ከነሱ በፊት የካዱትን ሰዎች ቃል ያመሳስላሉ፤ አላህ ያጥፋቸዉ (ከእዉነት) እንዴት ይመለሳሉ!”

የቁርኣን ጸሐፊ አላህ ልጅ አለመውለዱን ሲናገር ሚስት አግብቶ ልጅ መውለድን ታሳቢ በማድረግ መኾኑን ሱራ 6፡101 ላይ “ለርሱ ሚስት የሌለችው ሲሆን እንዴት ልጅ ይኖረዋል?” በማለት ከተናገረው መረዳት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ሱራ 72፡3 ላይ “…ሚስትንም ልጅንም አልያዘም” ይላል፡፡ ብዙ ሙስሊሞች “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው” የሚለውን ንግግር ሲሰሙ ወደ አዕምሯቸው የሚመጣው ሚስት አግብቶ ልጅ መውለድ የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ በመኾኑ ይህ ንግግር አይዋጥላቸውም፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የሚለው አባባል በእርሱና በእግዚአብሔር አብ መካከል ያለውን ዘላለማዊ ሕብረት ለማመልከት የሚያገለግል መንፈሳዊ አገላለጽ እንጂ ሚስት አግብቶ ልጅ መውለድን የሚያመለክት አይደለም፡፡ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ንግግር በእጅጉ ይቃወማሉ፤ ለመስማትም ይጸየፋሉ፡፡

በአንድ አስተምሕሮ ላይ ትችቶችን ለመሰንዘር መጀመርያ አስተምሕሮውን ማወቅና በትክክል መረዳት አስፈላጊ ቢሆንም አሕመዲን ጀበል መለኪያ መሥፈርታቸውና መነፅራቸው በስህተት የተሞላው ቁርኣን እስከሆነ ድረስ የገዛ ነቢያቸውና አምላካቸው ያልተገነዘቧቸውን ክርስቲያናዊ አስተምሕሮዎች መገንዘብ የመቻላቸው ጉዳይ የማይመስል ነው፡፡ ለመጽሐፋቸው መልስ ለማዘጋጀት ሙግቶቻቸውን ስንፈትሽ ሳለን ቀደም ሲል የተጠቀሱትን የመሳሰሉ ቁጥር ሥፍር የሌላቸውን የተሳሳቱ ግንዛቤዎች በአብዛኞቹ ጥያቄዎቻቸው ውስጥ አስተውለናል፡፡ በቅዱስ መጽሐፋቸው ውስጥ የተሰገሰጉትን እነዚህን የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ማጋለጥ የጥያቄዎቻቸውን ካብ አስቀድሞ መናድ ቢሆንም በመጽሐፋቸው ውስጥ ለተነሱት ጥያቄዎች በሙሉ አንድ በአንድ መልስ እንሰጣለን፡፡


[1] ቀዳሚውን የሙሐመድ ግለታሪክ የከተቡት ኢብን ኢስሐቅና ከነባርሐታቾች (Classical Commentators) መካከል አንዱ የሆኑት አል-ዘመቅሻሪ ይጠቀሳሉ፡፡ Ibn Ishaq, Sirat Rasul Allah, Translated by Alfred Guillaume, Oxford University Press, 1995, pp. 271-272; Helmut Gätje, The Quran and its Exegesis, One Word Publications, 1996, pp. 126-127

[2] ይህ ትምህርት ‘Modalism’ በመባል ይታወቃል፡፡

[3]ኒያል ሮቢንሰን የተሰኙ ሙስሊም ጸሐፊ በ550 ዓ.ም. አካባቢ በሦርያ የተጻፈ ክርስቲያናዊ ሰነድ ይህንን እንደሚገልፅ ከነማስረጃው በመጽሐፋቸው ውስጥ አስፍረዋል፡፡ (Neal Robinson, Christ in Islam and Christianity, State University of New York Press, 1991, p. 197)

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ