መግቢያ

መግቢያ

ላለፉት አሥራ አራት ክፍለ ዘመናት እስልምና በክርስትና ፊት ካስቀመጣቸው ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ሥነ-መለኮታዊ ሲሆን በዘመናችን በሕትመትና በሌሎች የመገናኛ አውታሮች በከፍተኛ ኹኔታ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ ለእነዚህ ተግዳሮት በክርስቲያኖች የተዘጋጁ ምላሾች ቢኖሩም ከዚያኛው ወገን ከሚወነጨፉት ጋር ሲነፃፀሩ በቂና ተመጣጣኝ የመሆናቸው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ በአገራችን ሙስሊሞች የተሰናዱና በባዕዳን ቋንቋዎች ተጽፈው የተተረጎሙ ኁልቁ መሣፍርት የሌላቸው መጻሕፍት ገበያውን አጥለቅልቀውት ቢገኙም መልስ ሳይሰጥባቸው በቸልታ ታልፈዋል፡፡ ብዙዎቹ ይዘታቸው የሚመጥን ባለመኾኑ ምክንያት በቸልታ ማለፍ ተገቢ ቢመስልም ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠንቅቆ በማያውቀው በአብዛኛው ሕዝበ ክርስቲያን ዘንድ የሚፈጥሩት ውዥንብርና ሙስሊም ወገኖች ልባቸውን ለወንጌል እንዳይከፍቱ እንቅፋት በመኾን ረገድ ያላቸው ተፅዕኖ ቀላል ባለመኾኑ ትኩረት ያሻቸዋል፡፡

በአገራችን የሥነ መለኮት ምሑራን በቸልታ ከታለፉት እስላማዊ የሕትመት ውጤቶች መካከል በአሕመዲን ጀበል የተዘጋጀው “ክርስቶስ ማነው? 303 ወሳኝ ጥያቄዎች” የሚል ርዕስ ያለው ባለ 140 ገፅ መጽሐፍ ይገኝበታል፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ በክርስቶስ ማንነት ላይ ብቻ ያነጣጠረ ቢመስልም ይዘቱ ግን ዐበይት የክርስትና መሠረቶችን ለመገዳደር ታልሞ የተዘጋጀ መኾኑ ግልፅ ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የክርስቶስ አምላክነት፣ ወልድነት፣ ስቅለቱ፣ ትንሣኤው፣ የእግዚአብሔር ሥሉስ አሓዳዊነትና የመጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒነት ለጥያቄ ቀርበዋል፡፡ መጽሐፉ ክርስትናን በማንኳሰስ የክርስቲያኖችን እምነት የማናጋትና እስልምናን በማወደስ ሙስሊሞች በእምነታቸው ላይ ያላቸውን መተማመን የማደላደል ጣምራ ዓላማዎችን ያነገበ ነው፡፡ አዘጋጁ ለሙግቶቻቸው ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከቁርኣንና በምሑራን ከተጻፉ መጻሕፍት ወስደዋል፡፡ ጥያቄዎቹ አመክንዮአዊነትን የተላበሱ ቢመስሉም አብዛኞቹ ቅዱሳት መጻሕፍትንና በክርስቲያን ምሑራን የተዘጋጁትን ጽሑፎች ከአውድ ውጪ በመጥቀስና በማጣመም የቀረቡ ናቸው፡፡

በበይነ መረብ (Internet) ላይ ከሙስሊም ወገኖች ጋር ሃይማኖታዊ ውይይቶችን ሳደርግ በነበርኩባቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ይህ መጽሐፍ ለጥያቄዎቻቸው ዋና ምንጭ መኾኑን ተገንዝቤያለሁ፤ አንዳንድ ክርስቲያን ወገኖችም መልስ ለመስጠት ሲቸገሩ አስተውያለሁ፡፡

የመጽሐፉ ይዘት ከሞላ ጎደል የተለመዱ እስላማዊ ጥያቄዎችን የሚደግም ቢሆንም ጸሐፊው በአገራችን ሙስሊም ጸሐፊያን ያልቀረቡ አዳዲስ የሙግት ሐሳቦችን ለማስተዋወቅ ጥረት አድርገዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም የሙግት ሐሳቦቻቸውን በማስረጃ ለማስደገፍ ሞክረዋል፤ ኾኖም ክርስቲያናዊ ምንጮችን ከአውድ ገንጥሎ በማውጣትና በጠቀሷቸው መጻሕፍት ገፆች ላይ የሌሉትን የግል ፈጠራቸውን በማከል ጽፈዋል፡፡ ይህ አካሄድ በሙስሊም ዐቃቤያነ እምነት ዘንድ የተለመደ ሲሆን ምንጮቹን በቀጥታ የማንበብ ዕድል የሌላቸውን ወገኖች ማደናገሩ የማይቀር ነው፡፡ መጽሐፉ በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከል ለሚደረጉት ውይይቶች እንቅፋት መኾኑን ከእነዚህ ኹኔታዎች መረዳት በመቻሌ የማያዳግም ምላሽ በመስጠት ከመንገድ ማስወገድ አስፈላጊ ኾኖ ታይቶኛል፡፡  

ማሳሰብያ፡– ጸሐፊው ለየምዕራፎቹ በሰጧቸው ርዕሶችና በጥያቄዎቹ ተራ ቁጥር ላይ ለውጥ አልተደረገም፡፡ በአሕመዲን መጽሐፍ ውስጥ በምዕራፍ 5 እና 6 ላይ የሚገኙት ርዕሶች የሐሳብ ፍሰትን ለመጠበቅ ሲባል ቦታቸው ተቀያይሯል፡፡ በጥያቄዎቹ ውስጥ የሚገኙትን ጉልህ የፊደል ግድፈቶች በተቻለ መጠን ለማረም ተሞክሯል፡፡ ጸሐፊው የጥያቄዎቻቸውን ብዛት እንደምንም 303 ለማድረስ የተጨነቁ ይመስል ብዙዎቹን የደጋገሙ በመኾኑ አስቀድሞ መልስ የተሰጠባቸውን የመልሱን ተራ ቁጥር በማመላከት አልፈናቸዋል፡፡

ይህንን መጽሐፍ ስታነቡ ሳላችሁ የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና በረከት ይበዛላችሁ ዘንድ ጸሎቴ ነው፡፡

                                             

 

ዋናው ማውጫ