“የት እንደተጻፈ አሳዩን” – ሙስሊም ሰባኪያን በቆፈሩት ጉድጓድ ሲወድቁ

“የት እንደተጻፈ አሳዩን”

ሙስሊም ሰባኪያን በቆፈሩት ጉድጓድ ሲወድቁ

ሙስሊም ሰባኪያን ብዙ ጊዜ “ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህና እንዲያ የሚሉ ነገሮችን አሳዩን” የሚሉ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ መስማት የተለመደ ነው፡፡ የጠየቁትን ቃል ወይንም ሐረግ ክርስቲያን ወገኖች ማሳየት ከተሳናቸው ቃሉ ወይንም ሐረጉ የወከለው አስተምሕሮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑንና የሰዎች ፈጠራ መሆኑን በመደምደም ለክርስቲያኖች ማብራርያ ዕድል በመንፈግ ውይይቱን ይቋጫሉ፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን ጥያቄዎቻቸው በአንድ መንገድ ብቻ እንዲመለሱ መጠበቃቸውና ክርስቲያኖችን በእስላማዊ መረዳት ልክ በተሰራ ጠባብ ክፍል ለመገደብ መሞከራቸው ልክ ካለመሆኑም በላይ አስፍቶ አለማሰብ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

ሙስሊም ወገኖቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን አስተምህሮ ለመቀበል አስተምህሮው እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ ብቻ ተጽፎ መገኘት እንዳለበት የሚያምኑ ከሆነና “ሥላሴ” የሚለውን የመሳሰሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ፅንሰ ሐሳቦችን የሚወክሉ ነገረ-መለኮታዊ ቃላት ክርስቲያናዊ ለመሆን የግድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጠቀስ አለባቸው የሚሉ ከሆነ ይህንኑ መስፈርት በእስልምና ላይ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በክርስቲያናዊ አስተምሕሮዎች ላይ ለመጫን የሚሞክሩትን መስፈርት ለእስልምና የማይጠቀሙ ከሆነ ለእውነት ታማኞች ያልሆኑ በአባይ ሚዛን የሚመዝኑ ግብዞች መሆናቸውን በራሳቸው ላይ ያስመሰክራሉ ማለት ነው፡፡

ሙስሊም ሰባኪያን ጥያቄዎቻቸውና መስፈርቶቻቸው ኢ-ምክንያታዊ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ በማድረግ ረገድ ራሳቸው የቀመሙትን መድኃኒት ማቅመስ መተኪያ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡ ስለዚህ በማስከተል በተደጋጋሚ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ወደራሳቸው በማዞር እንጠይቃቸዋለን፡፡  

ዛሬ ሙስሊሞች እየተከተሏቸው የሚገኙት በርካታ ሥርኣቶችና የሚጠቀሟቸው አያሌ እስላማዊ ቃላት በቁርኣን ውስጥ የማይገኙ ናቸው፡፡ ስለ አላህ፣ ስለ ዒሳ እና ስለ ሙሐመድ የሚያምኗቸው በርካታ ነገሮች በእነዚህ አካላት ቃል በቃል በቁርኣን ውስጥ በቀጥታ ያልተነገሩ ናቸው፡፡ ሙስሊም ወገኖች አንድን አስተምህሮ ለመቀበል ወይም አንድን ቃል ለመጠቀም የግድ እነርሱ በሚፈልጉት ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ መገኘት እንዳለበት ካመኑ የሚከተሉትን ቃላት፣ አስተምህሮዎች፣ ንግግሮችና ትዕዛዛት ከቁርኣን በማውጣት እንዲያሳዩን እንጠይቃቸዋለን፡፡

  • ተውሂድ የሚለውን ቃል፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ፅንሰ ሐሳብ ሥላሴ እንደሚሰኝ ሁሉ የቁርአኑ የአላህ ፅንሰ ሐሳብ ተውሂድ በመባል ይታወቃል፡፡)
  • ሦስቱን የተውሂድ ክፍሎች፣ ማለትም ተውሂድ አሩቡቢያ፣ ተውሂድ አል ኡሉሂያ እና አስማ ወስሲፋት፡፡ (ተውሂድ የሚለውም ቃል ሆነ ሦስቱ ክፍሎቹ ቃል በቃል በቁርኣን ውስት ተጠቅሰው አናገኝም፡፡)
  • “ላ ኢላ ሀኢለላህ መሐመደን ረሱልአላህ” (ከአላህ በስተቀር አምላክ የለም ሙሐመድም መልዕክተኛው ናቸው) የሚለው እስላማዊ የእምነት መግለጫ ልክ በዚህ ሁኔታ የተጻፈበትን ቦታ እንዲያሳዩን እንጠይቃቸዋለን፡፡ የተቆራረጠውን በማገጣጠም እንድታሳዩን አንፈልግም፡፡
  • በቀን አምስት ጊዜ ስገዱ የሚል ትዕዛዝ፡፡
  • ሙስሊም መገረዝ አለበት የሚል ትዕዛዝ፡፡
  • ዘማዊ በድንጋይ ተወግሮ መሞት አለበት የሚል ትዕዛዝ፡፡
  • ሙስሊም የካዕባን ድንጋይ መሳምና መተሻሸት አለበት የሚል ትዕዛዝ፡፡
  • ኢብራሂም ለመስዋዕትነት ያቀረበው ልጅ ኢስማኤል ነበር የሚል አንድ ጥቅስ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ መሲህ ነኝ ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ ከድንግል ነው የተወለድኩት ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ የአላህ ቃልና ከእርሱ የሆንኩ መንፈስ ነኝ ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ ሙስሊም ነኝ ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በምድር ላይ እያለ በራሱ አንደበት እኔ አምላክ አይደለሁም ያለበትን ቦታ፡፡ (ወደ ፊት አላህ ሲጠይቀው ይናገራል ተብሎ በቁርኣን ውስጥ የተጠቀሰ ነገር ካለ አንቀበልም ምክንያቱም ዒሳ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ የተናገረው አይደለምና፡፡ ወደ ፊት ይናገራል ተብሎ የተጠቀሰው ንግግር እውነትም ውሸትም ሊሆን ይችላል፡፡ ጊዜው ሲደርስ የሚታወቅ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ እንደ ዒሳ ንግግር ሊቆጠር አይችልም፡፡)
  • ዒሳ በራሱ አንደበት ቃል በቃል እኔ የአላህ ልጅ አይደለሁም ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ ስለ ሰው ልጆች ኃጢኣት ለመሞትና በሦስተኛው ቀን ለመነሳት አልመጣሁም ያለበትን ቦታ፡፡
  • አላህ ያወረዳቸው የቁርኣን ሱራዎች 114 ብቻ እንደሆኑ የተጻፈበትን ቦታ፡፡
  • የቁርኣን ሱራዎችን ስሞች አላህ እንደገለጣቸው የተነገረበትን ቦታ፡፡
  • የአደም ሚስት ስም ማን መሆኑን የሚናገር ቦታ፡፡ (ቁርኣን ከማርያም በስተቀር የትኛዋንም ሴት በስም አልጠቀሰም፡፡ በአማርኛ ቁርኣን ወይንም በሌሎች ትርጉሞች ውስጥ በቅንፍ ተጠቅሰው የምታገኟቸው የሴት ስሞች ሁሉ በአረብኛው ቁርኣን ውስጥ አይገኙም፡፡ የተርጓሚዎቹ ጭማሬዎች ናቸው፡፡)

ሙስሊም ሰባኪያን እነዚህን ነገሮች ከቁርኣን አውጥተው ሊያሳዩን የማይችሉ ከሆነ መሰል ጥያቄዎችን መጠየቅ ለትክክለኛ ውይይት እንቅፋት ከመሆን የዘለለ ውጤት እንደሌለው ሊረዱት ይገባል፡፡ ጥያቄዎቻችሁ በአንድ መንገድ ብቻ እንዲመለሱ በመጠበቅ ክርስቲያኖችን በጠባብ ክፍል ውስጥ ለማጎር የምትሞክሩ ከሆነ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ስትጠየቁ መግቢያ ይጠፋችኋልና ከማያዋጣ ደረቅ ክርክር ራቁ፤ ወዳጃዊ ምክራችን ነው፡፡

 

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ