የአፅናኙ ማንነትና የሙስሊም ሰባኪያን ማምታቻ

 የአፅናኙ ማንነትና የሙስሊም ሰባኪያን ማምታቻ

ሰሞኑን አዲስ ነገር ፍለጋ በበይነ መረብ ላይ ስዘዋወር ለክርስትና ምላሽ ለመስጠት በሚሞክር እስላማዊ ድረገጽ ላይ የሚገኝ አንድ ጽሑፍ ትኩረቴን ሳበው፡፡ የጽሑፉ ርዕስ “አፅናኙ ማነው? የአፅናኙ ወሬ ትርክትና የክርስቲያኖች መሟገቻ” የሚል ሲሆን አብዛኞቹ ሐሳቦች ከዚህ ቀደም በድረገጻችን ላይ ምላሽ የሰጠንባቸው የተለመዱ ሙግቶች ናቸው፡፡ የሙስሊም ሰባኪያን አመል ሆኖ ጸሐፊው ጥቅሶችን ከአውድ ውጪ ከመጥቀሱ በተጨማሪ በምሑራን የተጻፉትንም መጻሕፍት ደራሲያኑ ባልተናገሩት የተሳሳተ መንገድ ጠቅሷል፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን እንዲህ ያሉ ጽሑፎችን እንደ ጥሩ የሙግት ምንጭ በመቁጠር ስለሚስቱና ክርስቲያኖችንም ለማሳት ስለሚሞክሩ እንዲሁም ምላሽ የሚያሻቸውን ጥቂት ሐሳቦች በውስጡ ስላገኘሁ ምላሽ ልሰጠው ወደድኩኝ፡፡

ማሳሰብያ፡- የአዘጋጁ ስም ላልተጠቀሰበት ወይም ስሙን ለመጥቀስ አስፈላጊ ሆኖ ላላገኘነው ጽሑፍ ምላሽ ስንሰጥ ጸሐፊውን “አብዱል” በሚል የሙስሊም ሰባኪያን የወል ስም እንጠቅሰዋለን፡፡

አብዱል

አፅናኙ ማነው? የአፅናኙ ወሬ ትርክትና የክርስቲያኖች መሟገቻ

በመጽሀፍ ቅዱስ የተነገረለትና የሚመጣው የተባለውን “አፅናኝ” በተመለከተ ከሙስሊሞች ለሚነሱ መከራከሪያዎች ክርስቲያኖች የሚያቀርቧቸው መልሶች ሁሌም በቀዳዳ የተሞሉ ናቸው። ይህ አጽናኝ ተብሎ የተተነበየለት አካል ነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” እንዳልሆኑ ለማስረዳት የሚያደርጉት ክርክር ክፍተቶቻቸውን እና ደካማነታቸውን የሚያጋልጥ ነው። ይህንን አጀንዳ በተመለከተ “አፅናኙ ማነው?” በሚል ርእስ ከአመታት በፊት በድምፅ የሰጠሁትን ትምህርት ብትከታተሉት አሁን ለሚወራው መከራከሪያ እንደ መግቢያ ሙሉ ምስል ያስጨብጣችኃል።

መልስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አፅናኙ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን በግልፅ ተናግሯል፡- “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አፅናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” (ዮሐ. 14፡26)፡፡ በምን ተዓምር አስፈራሪውን ሙሐመድን አፅናኙ ልታደርገው እንደምትችል የምናይ ይሆናል፡፡

አብዱል

ዛሬ ታዲያ ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች የኛን ጥያቄዎች ለመመለስ በሚል የሚያቀርቧቸውን “ማስረጃዎች” በመጠኑ ለመዳሰስ እንሞክራለን። እስኪ ከዚህ በታች ከሚነሱት ሙግቶች ውስጥ ተደጋግሞ የሚጮህላቸውን የተወሰኑ ምላሾች ለያይተን በክፍል እንቃኛቸው፦

፩) የሚልከው ኢየሱስ ከሆነ “በተዘዋዋሪ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን መስክራችኃል” ይሉናል። ለዚህ የሚያነሱት መከራከሪያ የሚከተለውን የዮሐንስ ወንጌል አንቀፅ ነው፦

“ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ፤ መሄዴ ይበጃችኋል። እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድሁ ግን እርሱን ወደ እናንተ እልካለሁ፤”

  — ዮሐንስ 16፥7 (አዲሱ መ.ት)

በዚህ አንቀፅ ኢየሱስ “ወደናንተ እልካለሁ” ስላለ በተዘዋዋሪ እርሱ ላኪ አምላክ መሆኑን መስክራችኃል የሚል ነው። በመሠረቱ መከራከርያው ከተነሳው “የተተነበየተለት ማነው?” ከሚለው ነጥብ ጋር የሚገናኝ ባይሆንም ለቀረበው ጥያቄም ቢሆን አውዱን የሳተ በመሆኑ በቀላሉ የሚታረም ነው። ይህንን አንቀፅ ብቻውን ነጥሎ ለተመለከተው ሰው እንደተባለውም እርሱ በፍቃዱ ላኪ የሆነ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ይህንን ክስተት በተመለከተ ቀደም ብሎ ኢየሱስ የተናገረውን መልዕክት ለተመለከተ አስተዋይ ሰው ግን ሀሳቡ እንደተባለው እንዳልሆነ ይረዳል። ዋናው ነጥብ “ኢየሱስ እልካለሁ” ሲል በምን መልኩ ነው የሚልከው? የሚል ነው። ልክ እንደ አምላክ በራሱ ችሎታና ውሳኔ ነው ወይንስ ሌላ መንገድ አለ? ለሚለው እራሱ ኢየሱስ መልሱን ሰጥቶን መከራከሪያውን አፈርድሜ ያበላዋል። ኢየሱስ እንዲህ ይላል፦

“እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤”

  — ዮሐንስ 14፥16 (አዲሱ መ.ት)

ኢየሱስ በዚህ አንቀፅ በግልፅ የሚከተሉትን መልዕክቶች አስተላልፏል፦

ሀ) የኢየሱስ የ”መላክ” አገላለፅ ልመና ከማድረግና በዚያ ምክንያት ፀሎቱ ከመፈጸም የዘለለ ስልጣን የሌለው እንደሆነ፣

ለ) ሰጭው እርሱ ሳይሆን ሌላ አካል እንደሆነ “ይሰጣችኃል” ሲል በሶስተኛ ወገን ያስቀመጣል።

ስለዚህም ከላይ በመጀመሪያው ነጥብ እንደገለፅነው የኢየሱስ “እልካለሁ” ንግግር የፀሎቱን ውጤት የገለፀ እንጅ የባለቤትነትን መለያ የያዘ አይደለም። መሠል ቃላትን መጠቀሙን በተመለከተ ደግሞ ከመነሻውም በዚህ መልኩ በምሳሌ እንደሚናገር በዮሐንስ ወንጌል 16፥25 ተናግሯል።

መልስ

ሙስሊሙ ሰባኪ ከተናገረው በተጻራሪ የላኪው ማንነት “የተተነበየው ማን ነው?” ከሚለው ጥያቄ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት አለው ምክንያቱም ሙስሊሞች ሙሐመድ በኢየሱስ እንደተላከ የማያምኑ ከሆነና አፅናኙን የሚልከው ኢየሱስ ከሆነ አፅናኙ ሙሐመድ እንደሆነ መናገራቸው ግጭት ነውና፡፡ ሙሐመድን የላከው ኢየሱስ አይደለም ካሉ በኋላ ኢየሱስ “እልክላችኋለሁ” ያለውን አፅናኝ ሙሐመድ ነው ማለት ትርጉም አይሰጥም፡፡

ሙስሊሙ ሰባኪ ኢየሱስ “እልክላችኋለሁ” ማለቱ አፅናኙን ከመላክ ይልቅ የጸሎቱን ውጤት ለመግለፅ የተጠቀመው አባባል መሆኑን የተናገረው በብዙ ምክንያቶች የተሳሳተ መረዳት ነው፡፡

አንደኛ፡- የጸሎትን ውጤት ለመግለፅ “እልክላችኋለሁ” የሚል ሥልጣናዊ ቃል ጥቅም ላይ አይውልም፡፡ ኢየሱስ “እልክላችኋለሁ” ማለቱ በመንፈስ ቅዱስ መምጣት ውስጥ በተግባር ተሳታፊ መሆኑን ያሳያል፡፡ ለዚህ ነው መንፈስ ቅዱስን የሚልከው ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ መሆኑን የተናገረው፡- “እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።” (ዮሐንስ 16፡14)፡፡ “እልክላችኋለሁ” ሲል “የጸሎት መልስ” ለማለት ቢሆን ኖሮ ወደ ሰማይ ሄዶ እንደሚልከው ባልተናገረ ነበር፡፡

ሁለተኛ፡- ሙስሊሞች እንደሚሉት ሙሐመድ ከኢየሱስ የሚበልጥ ከሆነና ኢየሱስ አላህን ለምኖት ከአላህ ተቀብሎ ሙሐመድን ከላከው ኢየሱስ ከሙሐመድ በላይ መሆኑን ስለሚያመለክት ሙስሊም ወገኖች አሁንም ኢየሱስ ከሙሐመድ በላይ ከመሆኑ እውነታ ማምለጥ አይችሉም፡፡ ይህንን እውነታ አለመቀበላቸው ደግሞ በኢየሱስ የተላከው አፅናኝ ሙሐመድ ነው የሚለውን ዲስኩራቸውን ውድቅ ያደርጋል፡፡ በክርስቲያኖች እምነት መሠረት መንፈስ ቅዱስ በባሕርይ ከአብና ከወልድ የተካከለ ቢሆንም በሥራ ድርሻ (Function) ረገድ በአብና በወልድ ይላካል፡፡ ይህም በሥላሴ አካላት መካከል የሥራ ድርሻ መታዘዝ (Functional Subordination) ስላለ ነው፡፡ ወልድ ለአብ እንደሚታዘዘው ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ለአብና ለወልድ ይታዘዛል፡፡ ይህ የባሕርይ ብልጫን ሳይሆን በሰው ልጆች መዳን ውስጥ ሦስቱ የሥላሴ አካላት ከሚኖራቸው ሚና አንጻር የሚገለፅ ነው፡፡ ሙስሊሞች ኢየሱስ ሙሐመድን መላክ በሚያስችለው ቦታ ላይ መቀመጡን ስለማያምኑ “እልክላችኋለሁ” የሚለውን ቃል እየተመለከቱ አፅናኙ ሙሐመድ እንደሆነ መናገር የሚችሉበት መንገድ የለም፡፡

ሦስተኛ፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቦታ የተጠቀመው ἐρωτήσω (ኤሮቴሶ) የሚለው የግሪክ ቃል የግዴታ በጸሎት የሚሆን ልመናን ብቻ ሳይሆን ልመና ያልታከለበት ጥያቄንም ለማመልከት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ለዚህ ነው የቅርብ ዘመን የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በሙሉ እና ከቆዩ ትርጉሞች መካከል ብዙዎቹ “Ask” ብለው የተረጎሙት፡፡ ተከታዮቹን 27 ትርጉሞች ማየት ይቻላል፡-

New International Versio, New Living Translation, English Standard Version, Berean Study Bible, New American Standard Bible, NASB 1995, NASB 1977, Amplified Bible, Christian Standard Bible, Holman Christian Standard Bible, Contemporary English Version, Good News Translation, GOD’S WORD® Translation, International Standard Version, NET Bible, A Faithful Version, Literal Standard Version, Berean Literal Bible, Young’s Literal Translation, Smith’s Literal Translation, Douay-Rheims Bible, Catholic Public Domain Version, Aramaic Bible in Plain English, Lamsa Bible, Godbey New Testament, Weymouth New Testament, Worrell New Testament.

NAS Exhaustive Concordance እንደሚናገረው የቃሉ መነሻ “ኤሮማይ” መጠየቅ (to ask) የሚል ነው፡፡

ቀጥተኛ ትርጉሙ “ጥያቄ ማቅብ ወይም መጠየቅ” (to ask, question) የሚል ነው፡፡

NASB የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ቃሉን በሚከተሉት መንገዶች ጥቅም ላይ አውሏል፡-

ask (15), ask a question (1), asked (14), asking (11), asks (3), beg (1), begging (1), implored (1), imploring (1), make request (1), please (2), question (5), questioned (2), request (4), requesting (1), urging (1).

ቃሉ በመሠረታዊነት “ጥያቄ ማቅረብ” ተብሎ የሚተረጎም ከመሆኑ አንጻር እንዲሁም ጌታችን “እልክላችኋለሁ” የሚል ሥልጣናዊ ቃል መጠቀሙን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያቱ የላከው መንፈስ ቅዱስ እንዲመጣ ተገቢውን ሥራ አስቀድሞ ከፈፀመ በኋላ በመለኮታዊ ባሕርዩ ከአብ ጋር እንደ ተካከለ የሥላሴ አካል አብን በመጠየቅ ነው የሚለው ትክክለኛ ድመዳሜ ነው፡፡ “እልክላችኋለሁ” ሲል እንደ ሥላሴ ሁለተኛ አካል ነው፤ መለኮት የሆነውን የእግዚአብሔርን መንፈስ ራሱ እግዚአብሔር እንጂ ፍጡር ሊልክ አይችልምና፡፡

አራተኛ፡- ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን ወደ ሐዋርያቱ እንደ ላከ የሚናገሩና የመንፈስ ቅዱስ ሰጪ እርሱ መሆኑን የሚናገሩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይገኛሉ፡-

“ዮሐንስም የግመል ጠጉር ለብሶ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ አንበጣና የበረሀ ማርም ይበላ ነበር። ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል። እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር።” (ማርቆስ 1፡6-8)

“ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።” (ሐዋ. 2፡33)

“ኢየሱስም መልሶ፦ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት።” (ዮሐንስ 4፡13-14)

“ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ፦ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ። ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና።” (ዮሐንስ 7፡37-39)

“ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና፦ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።” (ዮሐንስ 20፡21-23)

“እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።” (ሉቃስ 24፡49)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱስ ሰጪ ብቻ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ የአብ መንፈስ እንደሆነው ሁሉ የእርሱም መንፈስ መሆኑ ተገልጿል፡-

“በሚስያም አንጻር በደረሱ ጊዜ ወደ ቢታንያ ይሄዱ ዘድን ሞከሩ፥ የኢየሱስ መንፈስም አልፈቀደላቸውም” (ሐዋ. 16፡7)

“ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ።” (ራዕይ 19፡10)

“ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ።” (ሮሜ 4፡6)

ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን የላከው አብን በመጠየቅ መሆኑ የተነገረው ከአብ ጋር በፈቃድ መስማማቱን ለመግለፅ ነው፤ እናም እርሱ ራሱ የመንፈስ ቅዱስ ሰጪ ስለሆነ ይህ አምላክነቱን በማረጋገጥ የሙስሊሙን ሰባኪ ሙግት ውድቅ ያደርጋል፡፡

አብዱል

በነገራችን ላይ “አፅናኙን” በተመለከተ አሁን ክርስትያኖች በሚከራከሩን መልኩ “መንፈስ ስለሆነ ማንነት” ወዘተ ሳይሆን በጥንታዊ ክርስቲያኖች ዘንድ ስጋ የለበሰ ሰው እንደሆነ ነበር የሚረዱት። በዚህም ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ከህዝቡ መካከል “እኔ አፅናኙ ነኝ” በሚል ብዙ ሐሰተኛ ግለሰቦች ይነሱ እንደነበር በሰፊው ተጠቅሷል። (Institute of Ecclesiastical History, ancient and modern. Volume 1 Page 153-155 ,Page 201)

ሬይመንድ ብራውን እንዴውም ሀሳቡን ከዚያም በማሻገር ተራው አማኝ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሊቃውንትም ጭምር አፅናኙ የሰው ስጋን የለበሰ አካል እንደሆነ ያምናሉ ሲል ፅፏል (The paraclete in the fourth Gospel Raymond E. Brown pg 113)

መልስ

ይህ ሙስሊም ሰባኪ ምሑራንን ጠቅሶ ለመናገር የሞከረበት መንገድ በእጅጉ የተሳሳተና የሙስሊም አፖሎጂስቶችን አወናባጅነት የሚገልጥ ነው፡፡ Institute of Ecclesiastical History በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ደራሲው በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የኖረ ሞንታነስ የተባለ ሰው አፅናኙ እርሱ መሆኑን እንዳስተማረ ይነግረናል፡፡ በሞንታነስ ትርጓሜ መሠረት አፅናኙና ወደ ሐዋርያት የመጣው መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ ሲሆኑ ክርስቶስ አፅናኙ ይመጣል ሲል ሥጋ ለባሽ ሰው ለማለት ነው፡፡ ከዚህ የተሳሳተ ትርጓሜ በመነሳት በሦስተኛው ክፍለ ዘመን የኖረ ማኒ ወይም ማነስ የተሰኘ ግለሰብም አፅናኙ እርሱ መሆኑን ተናግሮ እንደነበር ደራሲው ጠቅሷል፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ሙሐመድም ጭምር እንደዚያ ያለ አመለካከት እንደነበረው የመጽሐፉ ደራሲ ገፅ 151 ላይ ይናገራል፡፡[1] (ነገር ግን የእስልምናው ጀማሪ ሙሐመድ ዒሳ ስለ እርሱ እንደተነበየ ከመናገር በዘለለ ይህንን ጥቅስ በቀጥታ በመጥቀስ ስለ እርሱ እንደሆነ የተናገረበት ማስረጃ እስላማዊ ምንጮች ውስጥ እንደሌለ መታወቅ ይኖርበታል፡፡) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አፅናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” (ዮሐ. 14፡26) በማለት በግልፅ ስለተናገረ ደራሲው የጠቀሰው ዓይነት አመለካከት የተለየ ፍላጎት የነበራቸው የጥቂት ግለሰቦች እንጂ የጥንት ክርስቲያኖች ሁሉ አመለካከት ሊሆን የሚችልበት ዕድል የለውም፡፡ እንዲህ ያሉ የሳቱ ግለሰቦችን አመለካከት የአጠቃላዩ ቀደምት ክርስቲያን ማሕበረሰብ አመለካከት በማስመሰል ማቅረብ ያነበቡትን ነገር ማገናዘብ ያለመቻል አለበለዚያም የአጭበርባሪነት ምልክት ነው፡፡ ደራሲው የአመለካከቱ አራማጆች የነበሩ ጥቂት ግለሰቦችን ጠቀሰ እንጂ ይህ ሙስሊም ሰባኪ እንዳደረገው የጥንት ክርቲያኖች አጠቃላይ መረዳት እንደሆነ አልተናገረም፡፡ በርግጥ ሙስሊሙ ሰባኪ የሆነ ቦታ ያየውን ጽሑፍ ተርጉሞ ከማምጣት በዘለለ መጽሐፉን አላነበበውም፡፡ ቢያነበው ኖሮ ስለ አፅናኙ የሚናገረው ሐሳብ ገፅ 151-152 ላይ እንጂ እርሱ እንደጠቀሰው ገፅ 153-155 ላይ እንዳልሆነ እንዲሁም ገፅ 201 ላይ ስለ ርዕሱ ምንም ነገር እንዳልተባለ ባስተዋለ ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ምሑራዊ ምንጮችን አንብቦ የመረዳት አቅም እንደሌለው ግራ የገባው የምንጭ አጠቃቀሱ ያሳብቃል፡፡

ሙስሊሙ ሰባኪ የሬይመንድ ብራውንን ጥናታዊ ጽሑፍ የጠቀሰበት መንገድ አሁንም ስህተት ነው፡፡ ብራውን “ተራው አማኝ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሊቃውንትም ጭምር አፅናኙ የሰው ሥጋን የለበሰ አካል እንደሆነ ያምናሉ” ብለው አልጻፉም፤ ማስተላለፍ የፈለጉትም ሐሳብ እንደርሱ አይደለም፡፡ ሲጀመር በዚህ ዘመን የትኛው አማኝ ነው አፅናኙ መንፈስ ቅዱስ እንዳልሆነ የሚያምነው? የጽሑፉ ገፅ 113 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ስንመለከት ብራውን ጥርጣሬ እንዳለባቸው የገለጿቸው ሊቃውንት አማኞችን የሚወክሉ ሳይሆኑ ሁሉንም ነገር በመጠራጠር የሚታወቁት እንደ ቡልትማንና ዊንዲሽን የመሳሰሉት ለዘብተኛ ምሑራን ናቸው፡፡[2] ሐሳባቸውም የተገለጸው አፅናኙ መንፈስ ቅዱስ ነው የሚለው የወንጌሉ ኦሪጅናል ሐሳብ ላይሆን ይችላል በሚል የጥርጣሬ አገላለፅ እንጂ በድምዳሜ ሐሳብ አይደለም፡፡ በነገረ መለኮትና በፍልስፍና መሠረታዊ ስልጠና ያለው ሰው ምሑራን አንድን ሐሳብ ሲገልጹ የሚጠቀሟቸውን ቃላት በጥንቃቄ እንደሚመርጡ ስለሚያውቅ ሙስሊሙ ሰባኪ ባቀረበው መንገድ እነርሱ ያላሉትን የግል መረዳቱን የእነርሱ ሐሳብ በማስመሰል አያቀርብም፡፡ የዮሐንስ ወንጌልን በተመለከተ ግንባር ቀደም ሊቅ የሚባሉት ሬይመንድ ብራውን በጥናታዊ ጽሑፋቸው ገፅ 114 ላይ የነዚህ ወገኖች ጥርጣሬ የሚያስኬድ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚሁ ጽሑፍ ገፅ 127 ላይ “የጰራቅሊጦስ ማንነት” በሚል ርዕስ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ አስረድተዋል፡፡

አብዱል

፩) ሁለተኛው መሟገቻ “ከናንተ ጋር እንዲኖር ለዘላለም እሰጣችኃለው ስላለ ነብዩ “ﷺ” አያመለክትም” በሚል የሚቀርበው ነው። እንደ ክርስቲያኖች ገለፃ መሠረት ነብዩ ሙሐመድ “ﷺ”  ዘላለም አልኖሩምና ትንቢቱ እሳቸውን አይመለከትም የሚል ነው። ታዲያ ማንን ይመለከታል? ስንላቸው አንቀፁ የሚመለከተው መንፈስ ቅዱስን እንደሆነ ይነግረናል። እስኪ ስለ ነብዩ ሙሐመድ ያቀረቡትን መቃረኒያ ለጊዜው እናስቀምጠውና በንግግሩ መሠረት መንፈስ ቅዱስን እንፈትሸው። አንቀፁን በማስቀመጥ እንጀምር፦

መልስ

የኛ ሙግት የተመሠረተው ሙሐመድ ለዘላለም አልኖረም በሚል ሐሳብ ላይ ሳይሆን አፅናኙ ይመጣል የተባለው ወደ ሐዋርያት በመሆኑ ከህልፈታቸው በኋላ የመጣው ሙሐመድ ወደ እነርሱ በመምጣት ከእነርሱ ጋር ለዘላለም ሊኖር አይችልም የሚል ነው፡፡ ይህንን ነጥብ ወደ ኋላ እንመለስበታለን፡፡ ጸሐፊው የሚለውን እንስማ፡-

አብዱል

አንቀፁን በማስቀመጥ እንጀምር፦

“እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤”

  — ዮሐንስ 14፥16 (አዲሱ መ.ት)

ይህንን አንቀፅ መሠረት አድርገን እስኪ ስለመንፈስ ቅዱስ የተወሰነ ነገር እንነጋገር፦

ሀ) አንቀፁ የሚለው “ሌላ” አፅናኝ ነው። እንደ ክርስቲያኖች እምነት መሠረት መንፈስ ቅዱስ አንድ አካል እንጅ የሚለዋወጥና በሌላ ቃል የሚጠቀስ ተጨማሪ ማንነት ያለው አይደለም። ኢየሱስ “ሌላ” ሲል የነበረው መንፈስ ቅዱስን የተለየ ማለቱ ነው? መንፈስ ቅዱስ ያለው ባህርይ እንዲህ ነው?

መልስ

Παράκλητον (ፓራክሌቶን) የሚለው የግሪክ ቃል አፅናኝ፣ አጋዥ፣ አበረታታች፣ ጠበቃ፣ ወዘተ. የሚሉ ትርጉሞች አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን “ሌላ ፓራክሌቶን” ብሎ ሲል እርሱም ፓራክሌቶን መሆኑን እያመለከተ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ ክርስቶስ የኛ ፓራክሌቶን መሆኑን ተመሳሳይ ቃል በመጠቀም ገልጿል፡፡ ስለዚህ ጌታችን ከእርሱ ሌላ አፅናኝ የሆነ አካል ወደ ሐዋርያቱ እንደሚመጣ መናገሩ መንፈስ ቅዱስ “የሚለዋወጥና በሌላ ቃል የሚጠቀስ ተጨማሪ ማንነት ያለው” ተብሎ የሚተረጎመው በየትኛው ሀገር ቋንቋ ነው? እንዲህ ያለውን አነጋገር በቀላል አማርኛ “መቀባጠር” እንለዋለን፡፡ ሙስሊሙ ሰባኪ ቀደም ሲል የጠቀሰውን የብራውንን ጽሑፍ በጥንቃቄ ቢያነብ ኖሮ እዚህ ስህተት ላይ ባልወደቀ ነበር ምክንያቱም ብራውን ገፅ 127 ላይ የመጀመርያው ጰራቅሊጦስ ክርስቶስ ራሱ መሆኑን አብራርተዋልና!

አብዱል

ለ) ከኢየሱስ ማረግ በፊት መንፈስ ቅዱስ ከደቀመዛሙርት ጋር አልነበረምን? ከነበረስ ያ የነበረው መንፈስ ቅዱስስ ጊዜያዊ እንጅ ዘላለማዊ አልነበረም ማለት ነው?

ሐ) ኢየሱስ በሌላ ቦታ ላይ ስለዚህ አፅናኝ ሲናገር፦

“እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።”

— ዮሐንስ 16፥7

በዚህ አንቀፅ ኢየሱስ ለአፅናኙ መምጣት እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው የሱን መሄድ ነው። አፅናኙ ሊመጣ የሚችለውም እርሱ ከሄደ ብቻ ነው። ይህ አፅናኝ መንፈስ ቅዱስ ነበረ ካልን ግን ብዙ ነገር እናፋልሳለን። የመጀመሪያው ነገር ኢየሱስ ገና ከእናቱ ማህፀን ሳይወጣ በፊት ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ነበር። ኢየሱስ እራሱ የተፀነሰው በመንፈስ ቅዱስ ነው።

“የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ታሪክ እንዲህ ነው፤ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳይገናኙ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።”

  — ማቴዎስ 1፥18 (አዲሱ መ.ት)

ሲጠመቅም መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ነበር።

“ከውሃው በሚወጣበትም ጊዜ፣ ሰማያት ተከፍተው፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ሲወርድ አየ፤”

  — ማርቆስ 1፥10 (አዲሱ መ.ት)

ሌሎችንም ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። በጥቅሉ ግን ከላይ እንዳየነው መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ በኃላ የሚላክና የማይታወቅ አካል ሳይሆን ከዚያ በፊት የነበረና ለመምጣትም “እኔ ካልሄድኩ ወደናንተ አይመጣም” የሚባልለት አካል አይደለም።

መልስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱስን መምጣት ተስፋ የሰጠው ለሐዋርያቱ መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ ከላይ በሚገኙት ጥቅሶች ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ወደ ሐዋርያቱ ሕይወት መምጣቱን የሚናገር ሐሳብ የለም፡፡ ጸሐፊው “መምጣት” የሚለውን በሜትር የሚለካ አካላዊ ቅርበት አድርጎ የተረዳ ይመስላል፡፡ መንፈስ ቅዱስ መለኮት በመሆኑ በሁሉም ቦታ ይገኛል፡፡ የኢየሱስም አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነበር፡፡ ስለዚህ ለሐዋርያቱ የሰጠው ተስፋ መንፈስ ቅዱስ በኃይል ወደ እነርሱ በመምጣት ልዩ የሆነ መለኮታዊ ሥልጣን በማስታጠቅ ወንጌልን እንዲሰብኩ እንደሚያስችላቸው የሚያመለክት እንጂ ከዚያ ቀደም በምድር ላይ አለመኖሩን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል ጌታችን ኢየሱስ መንግሥተ ሰማያት በሰዎች መካከል መሆኗን አስተምሯል፤ ነገር ግን ደግሞ ገና የምትመጣ መሆኗንም አስተምሯል፡፡ ለሐዋርያቱ “መንግሥትህ ትምጣ” ብለው እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል (ማቴዎስ 6፡10)፤ ነገር ግን ደግሞ በሌላ ቦታ የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣቷን ተናግሯል (ሉቃስ 17፡20-21)፡፡ ይህ ማለት መንግሥተ ሰማያት አሁናዊና መፃዒ ገፅታዎች አሏት ማለት ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ መንፈስ ቅዱስ መለኮት በመሆኑ ምክንያት ምን ጊዜም የነበረ ቢሆንም በሐዋርያት ሕይወት ውስጥ መለኮታዊ ሥራውን ሊሠራ በውስጣቸውም ሊኖር በታላቅ ክብር ወደ እነርሱ የመጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 2)፡፡ ከዚያ ቀደም የነበረው የመንፈስ ቅዱስ አመጣጥ በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ለልዩ ዓላማና ለተወሰነ ጊዜ እንጂ ከግለሰቦቹ ጋር ለመኖር አልነበረም፡፡ የአሁኑ አመጣጡ ግን ለዘላለም ከእነርሱ ጋር ሊኖር ነው፡፡ ይህ “መምጣትና መኖር” በቁሳዊ ቅርበትና ርቀት የሚለካ ጉዳይ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ሕይወት ውስጥ መለኮታዊ ሥራውን ከመሥራቱ አንጻር የሚገለጽ ነው፡፡

አብዱል

ይህንን ካልን ታዲያ ወደተነሳንበት የነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” መከራከርያ እንለፍ። ለዘላለም የሚኖሩ አይደሉምና መልዕክቱ እሳቸውን የሚመለከት አይደለም የሚለው መከራከሪያ አስቂኝና አስገራሚ ነው። እዚህ ጋር ቃልበቃል የሳቸውን ህልውና ብቻ የሚገልፅ አድርጎ መውሰድ ትክክል አይደለም። እሳቸው እንደመላዕክት ወይንም ሰይጣን እስከፍፃሜው ድረስ የሚቅዩ ልዩ ፍጡር አይደለም። እሳቸው እስከ ፍፃሜው ድረስ በአካል ባይኖሩም በመልዕክታቸው ግን ዝንተ ዓለም እስከፍፃሜው ድረስ ህያው ናቸው። የተቀበሉት መልዕክት ዛሬም ነገም ሁሌም ቢሆን ለዘላለም ከኛ ጋር የሚኖር ህያው ነው። የዘላለም መኖር ሁሌ የአካል ህልውናን የሚጠቁም ከመሰልዎት ፈጽሞ ተሳስተዋል። መጽሀፍ ቅዱስ ለአብነት እንዲህ ይላል፦

“ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን #ለዘላለም #ይኖራል።”

  — 1ኛ ዮሐንስ 2፥17 (አዲሱ መ.ት)

ስለዚህም የነብዩ ሙሐመድ መልዕክት ለዘላለም ከኛ ጋር አብሮ ይኖራል፤ ይህ ግልፅና የተብራራ መልዕክቱም በተግባር የሚረጋገጥ እውነታ ነው።

መልስ

ቀደም ሲል እንዳልነው ሙሐመድ ለዘላለም ኖሯል አልኖረም? የሚለው ጥያቄ የሙግቱ አካል አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአፅናኙን መምጣት ተስፋ የሰጠው ለሐዋርያቱ ነበር፤ የሚመጣውም አፅናኝ ምናባዊ ሳይሆን ኀልዎቱ የሚታወቅ ማንነት ነው፡- “አሁን ግን ወደ ላከኝ እሄዳለሁ ከእናንተም፦ ወዴት ትሄዳለህ? ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። ነገር ግን ይህን ስለ ተናገርኋችሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል። እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።” (ዮሐ. 16፡5-7)፡፡ ከሐዋርያት ህልፈት በኋላ ክፍለ ዘመናትን ዘግይቶ በአረብያ የተወለደው ሙሐመድ ከመወለዱ በፊት ህልውና ስላልነበረው ወደ ሐዋርያት በመምጣት ከእነርሱ ጋር አልኖረም፣ አላስተማራቸውም፣ አልመራቸውም፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን ሙሐመድን አምላክ ወይም አንዳች መንፈስ ለማድረግ ካልፈለጉ በስተቀር ትንቢቱ ስለ እርሱ የሚሆንበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም፡፡

ማጠቃለያ


ከላይ እንደተመለከትነው ሙስሊሙ ሰባኪ በጽሑፉ መግቢያ እንደፎከረው ለክርስቲያኖች ምላሽ አፀፋዊ ማስተባበያ ሊሆን የሚችል የረባ ሐሳብ አላቀረበም፡፡ ሐሳቦቹ ሁሉ ሙሐመድን በግድ በመንፈስ ቅዱስ ቦታ የመተካት ቀቢፀ ተስፋዊ መፍጨረርጨር ከመሆናቸውም በላይ የሀገራችን ሙስሊም ሰባኪያን የረባ ሙግት ለማቅረብ የሚያስችል ምሑራዊ ቁመና እንደሌላቸው የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የሙሐመድ ነቢይነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ይቅርና ከእስላማዊ ምንጮች እንኳ አሳማኝ ማስረጃ ሊቀርብለት አለመቻሉ ትልቅ ችግር ቢሆንም ምንጮችን በትክክል አንብቦ መረዳት አለመቻልና ጥቅሶችን በአውዳቸው አለማንበብ በእነዚህ ወገኖች ዘንድ የሚገኘውን የዕውቀት ከፍተት የሚያሳይ ነው፡፡

በመጨረሻም  ጌታችን ስለ አፅናኙ ከተናገራቸው ሐሳቦች አኳያ ሙሐመድ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የመግባት ምንም ዓይነት ተስፋ እንደሌለው የሚያስረግጡ ጥቅሶችን በመመልከት እናጠቃልላለን፡-

  1. አፅናኙ ከአብ የሚወጣ በኢየሱስ የተላከ የእውነት መንፈስ ነው፡-

“ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፡፡” (ዮሐንስ 15፡26)

ሙሐመድ አፅናኙ ከሆነ ከአብ የወጣ የእውነት መንፈስ ነውን? በኢየሱስስ ተልኳልን?

  1. አፅናኙ ከሐዋርያት ጋር ለዘላለም የሚኖር፣ ዓለም የማያየውና የማያውቀው፣ሊቀበለው የማይቻለው፣ ከሐዋርያት ጋር እንዲሁም በውስጣቸው የሚኖር መንፈስ ነው፡-

“ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውስጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።” (ዮሐንስ 14፡15-17)

ለመሆኑ ሙሐመድ ከሐዋርያት ጋር እንዲሁም በውስጣቸው መኖር የሚችል ዘላለማዊ መንፈስ ነበረን? በዓለም አልታየምን? ዓለም አያውቀውምን? እነዚህ አባባሎች ለሥጋ ለባሽ ሊነገሩ የሚችሉ ናቸውን? በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የኖረውን ብዙ የሥነ ምግባር ጉድለቶችን ሲያሳይ የነበረውን ሙሐመድን ሊያመለክቱ የሚችሉበት ዕድልስ ይኖራልን?

  1. አፅናኙ መንፈስ ቅዱስ ነው፣ የተላከውም በኢየሱስ ስም ነው፡-

“አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” (ዮሐንስ 14፡26)

ሙሐመድ በኢየሱስ ስም ተልኳልን? ሙሐመድ መንፈስ ቅዱስ ነውን? ሙስሊሞች መንፈስ ቅዱስ ጂብሪል ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ ጂብሪል ነው እያሉን ነውን?

  1. የአብ የሆነው ሁሉ የኢየሱስ በመሆኑ መንፈስ ቅዱስም ከአብና ከወልድ የሚጻረር ፈቃድ ስለሌለው ከራሱ አይናገርም፣ የኢየሱስ የሆነውን ወስዶ ይናገራል፡፡

“…ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ።” (ዮሐንስ 16፡13-15)

ሙስሊሞች የአብ የሆነው ሁሉ የኢየሱስ መሆኑን ያምናሉን? አምላካቸው አላህስ አብ ወይም አባት መሆኑን ይቀበላሉን? ሁሉም ነገር የኢየሱስ ስለሆነ ሙሐመድ የኢየሱስ የሆነውን ወስዶ እንዳስተማረ ያምናሉን?

ውድ ሙስሊም ወገኖቼ፤ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ቻይ መለኮት እንጂ ሥጋ ለባሽ አይደለም፡፡ ከባባድ የሥነ ምግባር ጉድለቶችን ሲያሳይ የነበረው ሙሐመድ ብዙ ሰዎችን ሲገድልና ሲያሳድድ የኖረ አስፈራሪና አሸባሪ እንጂ አፅናኝ አልነበረም፡፡ ከኃጠአት ሁሉ የከፋው ይቅርታ የሌለው ኃጢአት በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚነገር የስድብ ቃል መሆኑን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስጠንቅቆናል፡- “በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።” (ማቴዎስ 12፡32)፡፡ ዛሬ ሰባኪዎቻችሁ በማያውቁት ገብተው መንፈስ ቅዱስን በሥጋ ለባሽ ለመተካት እያደረጉት ባሉት የድፍረት ተግባር ተሳታፊዎች መሆናችሁ ነፍሳችሁን እንዳያስከፍላችሁ ልትጠነቀቁ ይገባል፡፡ አሁኑኑ ወደ ነፍሳችሁ መድኃኒት ወደ ክርስቶስ ተመልሳችሁ ንስሐ ብትገቡና በስሙ ብታምኑ ቅዱሱን መንፈስ ይሰጣችኋል፤ ከእርሱ ጋርም የዕለት ዕለት ሕብረት ይኖራችኋል፡-

“ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው።” (የሐዋርያት ሥራ 2፡38-39)

“ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ፦ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ። ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና።” (ዮሐንስ 7፡37-39)

እግዚአብሔር አምላክ ይረዳችሁ ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው!


[1] Johann Lorenz Moshei, Institutes of Ecclesiastical History, Ancient and Modern, Vol. 1, (New York: Harper & Brothers, 1839), 151-152.

[2] Raymond E. Brown, “The Paraclete in the Fourth Gospel,” New Testament Studies, Volume 13, Issue 2, January 1967, p. 113.

 


ሙሐመድ