በእስልምና መሠረት ሐዋርያው ጳውሎስ የአላህ መልእክተኛ ነው

በእስልምና መሠረት ሐዋርያው ጳውሎስ የአላህ መልእክተኛ ነው

ሙስሊሞች ክርስትና ሐዋርያው ጳውሎስ የፈለሰፈው ሃይማኖት መሆኑን ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ የትኛውንም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንስተን ልንወያይ ብንሞክር ኢየሱስ ይህን አላስተማረም ነገር ግን ጳውሎስ ፈለሰፈው እንጂ ይሉናል፡፡ ጳውሎስን እጅግ ይጠሉታል፣ ይሰድቡታል፣ ያዋርዱትማል፡፡ ነገር ግን ጳውሎስን የሚቃወሙ ሙስሊም ሰባኪያን ሆን ብለው ራሳቸውንና የሚሰሟቸውን እያሳሳቱ ነው አልያም ደግሞ ስለሚናገሩት ነገር ምንም የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ሆን ብለው እያሳቱ ከሆነ ከልብ ድንዳኔአቸው እንዲመለሱና ልባቸውን ከእልከኛ መንገድ መልሰው ወደ እውነቱ እንዲመጡ እንመክራለን፡፡ ባለማወቅ ከሆነ ደግሞ ከመናገር ማወቅ ይቀድማልና እንዲያነቡ ልባዊ ምክራችን ነው፡፡ ከታች የተዘረዘሩትን እስላማዊ ምንጮች የምንጠቅሳቸው ፍጹም ትክክለኛና እውነተኛ መሆናቸውን አምነን ስለተቀበልን ሳይሆን በኢስላማዊ መዛግብት ክርስትናን ብንመዝነው እንኳ እውነተኝነቱ እንደሚረጋገጥ ለማሳየት ያህል ነው፡፡

ከዚህ በመቀጠል የብዙ አፈ-ታሪኮች ስብስብ ሆኖ ሳለ ከአምላክ ዘንድ የወረድኩ ነኝ የሚለው ቁርአን የሚነግረንን አስገራሚ ታሪክ አንብበን ወደ ማብራሪያው እንገባለን፡፡

ሱረቱ ያሲን (36) :13-29

ለነሱም የከተማይቱን (የአንጣኪያን) ሰዎች ምሳሌ መልክተኞቹ በመጧት ጊዜ፣ (የሆነውን) ግለጽላቸው። ወደነርሱ ሁለት ሰዎችን በላክንና ባስተባበሉዋቸው ጊዜ፣ በሦስተኛው አበረታንና እኛ ወደ እናንተ መልክተኞች ነን ባሏቸው ጊዜ፣ (የሆነውን ምሳሌ ግለጽላቸው)። እናንተ መሰላችን ሰዎች እንጂ ሌላ አይደላችሁም፤ አልረህማንም ምንም ነገር አላወረደም፤ እናንተ የምትዋሹ እንጂ ሌላ አይደላችሁም አሉዋቸው። (መልክተኞቹም) አሉ፦ ጌታችን ያውቃል፤ እኛ ወደናንተ በእርግጥ መልክተኞች ነን፤ በኛ ላይም ግልጽ የሆነ ማድረስ እንጂ ሌላ የለብንም። (ሕዝቦቹም) ፦ እኛ በናንተ ገደቢሶች ሆን፤ ባትከለከሉ በእርግጥ እንወግራችሁዋለን፤ ከኛም አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ያገኛችኋል፤ አሉ። ገደ ቢስነታቸው ከናንተው ጋር ነው ፤ ብትግገሠጹ (ትዝታላችሁን?) በውነቱ እናንተ ወሰን አላፊዎች ሕዝቦች ናችሁ አሏቸው። ከከተማይቱም ሩቅ ዳርቻ የሚሮጥ ሰው መጣ፤ ወገኖቼ ሆይ! መልክተኞቹን ተከተሉ አለ። እነርሱ ቅኑን መንገድ የተመሩ ሲሆኑዋጋንም የማይጠይቋችሁ ሰዎች ተከተሉ (አላቸው)። ያንንም የፈጠረኝን ፤ ወደርሱም የምትመለሱበትን (ጌታ) የማልግገዛ ለኔ ምን አለኝ? (አለ)። ከርሱ ሌላ አማልክትን እይዛለሁን? አልረሕማን በጉዳት ቢሻኝ ምልጃቸው ከኔ (ለመመለስ) ምንም አትጠቅመኝም፤ አያድኑኝም። እኔ ያን ጊዜ በግልጽ ስሕተት ውስጥ ነኝ፤ እኔ በጌታችሁ አመንኩ ፤ ስሙኝም (አለ)። ገነትን ግባ ተባለ ፤ (እርሱም) አለ ፦ወገኖቼ ቢያውቁ እመኛለሁ፤ ጌታዬ ለኔ ምሕረት ያደረገልኝና ከተከበሩትም ያደረገኝ መሆኑን። ከርሱም በኋላ በሕዝቦቹ ላይ (ልናጠፋቸው) ሰራዊትን ከሰማይ አላወረድንም ፤ (በማንም ላይ) አውራጆች አልነበርንም። (ቅጣታቸው) አንዲት ጩኸት እንጂ ሌላ አልነበረችም ፤ ወዲያውኑም እነርሱ ጠፊዎች ሆኑ። 

ይህ ክፍል እንደሚነግረን ከሆነ ሁለት የአላህ መልእክተኞች አንጾኪያ ወደተባለች ከተማ በመጡ ጊዜ የከተማው ሰዎች ሊቀበሏቸው አልፈቀዱም፡፡ ማጠናከርያ እንዲሆን ሌላ ሦስተኛ መልእክተኛም አላህ ጨመረላቸው አሁንም ሰዎቹ የሚቀበሉ አይነት አልነበሩም፡፡ እንደውም እናንተ የአምላክ መልእክተኞች አይደላችሁም አታላዮች እንጂ አሏቸው፡፡ መልእክተኞቹም አምላክ እንደላካቸው ደጋግመው ነገሯቸው፡፡ ሰዎቹም በድንጋይ ወግረው እንደሚገድሏቸውና በሚያሳምም ቅጣት እንደሚያሰቃዩአቸው መዛት ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ሰው እየሮጠ ከከተማው ዳር መጥቶ መልእክተኞቹ እውነተኛ የፈጣሪ መልእክተኛ መሆናቸውን መሰከረ፡፡ ሰውዬም ሊዋሽ ምንም ምክንያት እንደሌለው፣ ከዚያ ይልቅ ፈጣሪውን እንደሚፈራና ሌላ አማልክትን እንደማያመልክ እንዲሁም መልእክተኞቹ የግል ጥቅም ስለሚጠቅሙት ሳይሆን እውነተኛ ስለሆኑ ብቻ እንደመሰከረ ተናገረ፡፡

እንግዲህ ይህንን ታሪክ ካየን ሙስሊሞች ሁለት አስቸጋሪ አጣብቂኝ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ከሁለቱ አንዱን የመምረጥ ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡

የመጀመርያው አጣብቂኝ – በሱረቱ ያሲን 36:13-29 ላይ የተጠቀሱትን መልእክተኞች ቁርአን እንደሚለው አምኖ መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ ሙስሊሞች በኢየሱስና በሙሐመድ መካከል መልእክተኛ አልነበረም ብለው ያምናሉ፡፡ ይህም እምነታቸው በቁርአኑና በተፍሲሮቻቸው ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ሱረቱል አል-ማኢዳህ 5፡19: – እላንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! አብሳሪና አስፈራሪ አልመጣልንም እንዳትሉ ከመልክተኞች በመቋረጥ ጊዜ ላይ ሲኾን (ሕጋችንን) የሚያብራራ ሆኖ መልክተኛችን በእርግጥ መጣላችሁ። አብሳሪና አስፈራሪም በእርግጥ መጣላችሁ። አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው። 

ተፍሲር አል-ጃላላይን 5፡19:- እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ፣ በእውነትም መልእክተኛንም ላክንባችሁ፣ ከመልክተኞች በመቋረጥ ጊዜ ላይ ሕጋችንን የሚያብራራ ሆኖ ላክን፡፡ በእርሱና በዒሳ መካከልም መልእክተኛ አልነበረም፡፡ ለ569 ዓመታት ልዩነት፡፡ ስትቀጡ ወደኛ መልእክተኛም አስፈራሪም አልመጣም ነበር እንዳትሉ፤ በእርግጥ አብሳሪና አስፈራሪም መጥቶላችኋል፡፡ ስለዚህ ምህረት አይደረግላችሁም፡፡ እርሱን (ነቢዩን) ባለመከተላችሁ መቅጣትን ጨምሮ አላህ በነገር ሁሉ ቻይ ነውና፡፡ 

ተፍሲር ኢብን ከሢር ቅፅ 3 ገፅ 135-136 ላይ በኢየሱስና በመሐመድ መካከል መልእክተኛ የለም በሚል አብራርቶት ታገኛላችሁ፡፡ Tafsir Ibn Kathir (Abridge) Volume 3 page 135-136 (Surat Al-Maidah 19)

ስለዚህ ሙስሊሞች አጣብቂኝ ውስጥ የሚወድቁት በኢየሱስና በሙሐመድ መካከል መልእክተኛ ነበር ብለው መቀበል አልያ አልነበረም ብለው መካድ ከቁርአን ጋር ስለሚያጋጫቸው ነው፡፡ መልሳቸው ምን እንደሚሆን ከእነርሱ ብንጠብቅ ይሻላል፡፡

ሁለተኛው አጣብቂኝ  – ከላይ የተጠቀሱት መልእክተኞች የኢየሱስ ሐዋርያት አልነበሩም የሚሉ ከሆነ እነማን እንደነበሩ በሚገባ የማስረዳት ግዴታ አለባቸው፡፡ ክፍሉ ላይ የተጠቀሱት መልእክተኞች ሐዋርያት አይደሉም ብሎ መናገር ከታላላቅ ሙፈሲሮችና የታሪክ ምሁራን ጋር መጋጨት እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡

ሦስተኛው አጣብቂኝ ደግሞ የዘመኑ ሙስሊሞች ከታሪክ ምሁራንና ከታላላቅ ሙፈሲሮች ጋር አለመጋጨትን ከመረጡና መልእክተኞቹ ሐዋርያት ነበሩ ብለው ከተቀበሉ ክርስትና በጳውሎስ የተመሠረተ ነው የሚለውን ተራ ውንጀላቸውንና በጳውሎስ ላይ የሚነዙትን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ማቆም ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሙፈሲሮቹ ጳውሎስ ከሐዋርያቱ ጋር መልእክተኛ እንደነበረ ይናገራሉና፡፡

ሙስሊም ወገኖች ከሦስቱ አማራጮች የፈለጉትን መርጠው መሞገት ቢፈልጉ ዞሮ ዞሮ ውጤቱ ያው ነው፡፡

እነሆ ሙፈሲሮቹ!

የኢየሱስ ደቀመዛሙርት በኢስላማዊ ድርሳናት ውስጥ

ተፍሲር አል-ጃላላይን ሱረቱል ያሲን 36፡13: – “በከተማይቱም (በአንፆኪያ) የተቀመጡትን ሰዎች ምቷቸው… መልእክተኞቹም ማለትም የኢየሱስ ደቀ-መዛሙር ወደዚያ መጡ፡፡” https://quranx.com/Tafsirs/36.13

ታዋቂው የቁርአን ተፍሲር ወደ አንጾኪያ የኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት መጥተው እንደነበር በግልጽ ቋንቋ አስቀምጦልናል፡፡

ተፍሲር ኢብን አባስ :- (ለእነሱም አንድ ምሳሌ ነገራቸው) ለመካ ሰዎችም የከተማይቱን (አንጾንኪያ) ሰዎች እነዚያ ከአላህ ተልከው ወደ እነርሱ በመጡ ጊዜ እንዴት እንዳጠፋናቸው አብራራ፡፡ የኢየሱስ መልእክተኛ የሆነው ስምዖን ጴጥሮስ ወደ እነርሱ በመጣ ጊዜ በእርሱ አላመኑም ተቃወሙትም፡፡ https://quranx.com/tafsirs/36.13

ሌላኛው ታዋቂ ተፍሲር ኢብን አባስ ደቀ-መዛሙርቱ በአላህ ተልከው ወደ አንጾኪያ እንደሄዱ ያስቀምጥልናል፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ መልእክተኞች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ይህ ደግሞ ለየት ያለ ነገር ይጠቁመናል፡፡ ሰዎችን እንደመልክተኛ ለስብከት የሚልከው ማን ነው? አምላክ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በዚህ መሰረት ራሱ ኢየሱስ ሰዎችን እንደመልእክተኛ የመላክ ስልጣን እንዳለው በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ነቢይ ብቻ ሳይሆን አምላክ እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ተፍሲር ኢብን ከሢር፡- (በሦስተኛም አጠነከርናቸው) ማለት፡- በሦስተኛ መልእክተኛ አጠነከርናቸው አበረታናቸው ማለት ነው፡፡ ዋህብ ቢን ሱሌይማን ከሹአይብ አል-ጃባይ የሰማውን ኢብን ጁራይር እንዳወራው “የሦስቱ መልእክተኞች ስም ሸሙን (ስምዖን)፣ ዩሐና (ዮሐንስ) እና ሦስተኛው ደግሞ ቡሎስ (የጳውሎስ ስም በአረብኛ) ነበሩ ከተማይቱም አንጾኪያ ነበረች፡፡(ወደ እናንተ መልክተኞች ላክን) ማለት ከፈጠራችሁና እርሱን ብቻ ያለ አጋር እንድታመልኩት ካዘዛችሁ ማለት ነው፡፡ ይህ ምልከታ የአቡ አል-አልያህ ነው፡፡ ካታዳ ቢን ዲአማህ እነርሱ የመሲሁ (ሰላም በእርሱ ላይ ይሁንና) መልእክተኞች እንደነበሩና ወደ አንጾኪያ ሰዎች ተልከው ነበር ብሏል፡፡  Tafsir Ibn Kathir (Abridged), Volume 8, Surat Yasin (36) Verse 14 to 15

ኢብን ከሢር በበኩሉ ይህን ክፍል ሲፈስር ቀድመው የተላኩ መልእክተኞች ስምዖን ጴጥሮስና ዮሐንስ ሲሆኑ ሦስተኛው ግን ጳውሎስ እንደሆነኑ ቀደምት ሊቃውንትን በመጥቀስ አስቀምጧል፡፡ ኢብን ከሢርም ቢሆን ሐዋርያቱ የኢየሱስ መልእክተኞች እንደነበሩ ይነግረናል፡፡  

አልጠበሪ ጳውሎስ ከጴጥሮስ ጋር ወደ ሮም እንደተላከ ይናገራል፡-

ከሐውርያቱ መካከል የሚከተሉቱና ከእነርሱ በኋላ ያሉት ሐዋርያው ጴጥሮስ እና ጳውሎስ (ሐዋርያ ሳይሆን ደቀመዝሙር የነበረ)፣ ወደ ሮም ሄዱ፡፡ እንድርያስና ማቴዎስ ወደ ሰው በሊታ የጥቁሮች ምድር ሄዱ፡፡ ቶማስ ደግሞ ወደ ምዕራብ ባቢሎን የተላከ ይመስለናል፡፡ ፊሊጶስ ወደ ቃይረዋን እና ካርቴጅ ሄደ፣ ይህም ሰሜን አፍሪካ ነው፡፡ ዮሐንስ የወጣቶችና ባለዋሻ ወደሆነችው ኤፌሶን ሄደ፤ ያዕቆብ  ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ያም አኤሊያ ነው፡፡ በርተለሜዎስ ሂጃዝ ወደሚባል የአረብ አገር፤ ስምዖን ወደ በአፍሪካ ምድር ወደሚገኝ በርበርስ ሄደ፡፡ ይሁዳ ግን ሐዋርያ አልነበረም፡፡ የእርሱ ቦታ በአርየበስ ተወሰደ፡፡ ይሁዳ የሰራው ወንጀል በደብዳቤው ከተገለጸ በኋላ የአስቆሮቱ ይሁዳንም ቦታ ወሰደ፡፡  Tabari, History, Volume IV, p. 123

አልጠበሪ ለመግሥታት የተላኩት መልእክተኞች በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር ሲጽፍ ጳውሎስ የጴጥሮስ አጋር እንደነበረና ሁለቱም ወደ ሮም እንደተላኩና ሌሎች ሐዋርያት የተላኩባቸውን አገራት ጠቅሷል፡፡

ኢብን ኢሳቅም ተመሳሳይ ነገር ጽፈፏል፡-

ሲራት ራሱል አላህ :- አላህ ለሰው ልጆች ሁሉ ልኮኛል (ሙሐመድ)፡፡ ስለዚህ መልእክቴን ተቀበሉኝ፤ አላህ በእኔ ላይ ምህረትን እድርጓልና፡፡ የማርያም ልጅ የኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት በእርሱ ላይ ጀርባቸውን እንዳዞሩ ሁሉ እናንተም በእኔ ላይ ጀርባችሁን አታዙሩ፡፡ እነርሱም እንዴት ጀርባ እንደ ማያዞሩ ሲጠይቁት እርሱም “እርሱም ጠርቷቸው እኔ ለጠራኋችሁ ስራ አሰማራቸው፡፡ አጭር ጉዞ የደረሳቸው ተደስተው ተቀበሉ፡፡ እነዚያ ሩቅ ጉዞ የደረሳቸው ግን ተቆጡ ለመሄድም አንቀደዱም፡፡ ኢየሱስም ስለነሱ በአላህ ላይ አጉረመረመ፡፡ (ከዚያች ሌሊት ጀምሮ) እያንዳንዳቸው የተላኩበትን አገር ቋንቋ መናገር ይችሉ ነበር፡፡ ኢየሱስም ይህ አላህ እንድታደርጉ የፈቀደው ነገር ነውና ሂዱ አለ፡፡ የማርያም ልጅ ኢየሱስም የላካቸው ደቀ-መዛሙርቱና ከነሱ ቀጥለው ያሉቱ ነበሩ፤ በአገሪቱም ሐዋርያው ጴጥሮስና ጳውሎስ (ተከታይ እንጂ ደቀ-መዝሙር አይደለም) ወደ ሮም ሄዱ፡፡ Alfred Guillaume’s The Life of Muhammad p. 653

ኢብን ኢሳቅ ሲራት ረሱል አላህ በተሰኘው ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ በአንድ ወቅት የኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት በእርሱ ላይ አምፀው እንደነበር ከዚያም መልሰው ተስማምተውት እንደላካቸውና የሚሄዱበትን አገር ቋንቋ በሚገባ መናገር ይችሉ እንደነበረ ጠቅሷል፡፡ ከዚህም በላይ ከእውነተኞቹ ሐዋርያት ጋር ጳውሎስም ተልኮ እንደነበረ ይጠቅሳል፡፡

ታላቢም ጳውሎስ መልእክተኛና የጴጥሮስ አጋር እንደነበር እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

ኢየሱስ ከላካቸው ሐዋርያትና ከእነርሱ ጋር ከነበሩት መካከል ጴጥሮስና የእርሱ አጋር ጳውሎስ ይገኙበታል፡፡ Thalabii, Qisas al-Anbiyaa, pp. 389-390

አልጠበሪ እንደጻፈው ጳውሎስ በክርስቶ ላይ ስለነበረው እምነት የተሰዋ ጽኑ ክርስቲያን ነበረ፡፡

አቡ ጃፋር፡- ከጢባርዮስ በኋላ ፍልስጥኤምና ሌሎች የሦርያ አከባቢዎች በጢባርዮስ ልጅ በጋይዮስ ለአራት ዓመት እንደሚመሩ አረጋገጡ፡፡ እሱም በአስራ አራት ዓመት እድሜ ልጅ ተተካ፡፡ ከዚያም ኔሮ ለአስራ አራት ዓመት ገዛ፡፡ እርሱም ጴጥሮስን አሳረደ ጳውሎስን ቁልቁል አስሰቀለ፡፡ Tabari, History, Volume IV, p. 126

በክርስትና እምነት የኢየሱስን ደቀ-መዛሙርት እንደ አምላክ መልእክተኛ ነው የምንቀበላቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን በነብያት ተናግሮ በአዲስ ኪዳን ደግሞ በሐዋርያት በኩል እንደተናገረ እናምናለን፡፡

ኤፌ 2፡20 “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ኢየሱስ ነቢያትንና ሐዋርያትን እንደሚልክ ተናግሮ ነበር፡፡

ማቴ 23፡34 “ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤”

ሐዋርያት ድንቅንና ተዓምራትን ያደርጉ ነበር

ሐዋ 2፡43 “ነገር ግን በሰው ሁሉ ፍርሀት ሆነ፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት ተደረገ።”

ሐዋ 6፡8 “እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር።”

ሐዋ 8፡4-8፡ 12-13 “የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ። ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው። ሕዝቡም የፊልጶስን ቃል በሰሙ ጊዜ ያደርጋት የነበረውንም ምልክት ባዩ ጊዜ፥ የተናገረውን በአንድ ልብ አደመጡ። ርኵሳን መናፍስት በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበርና፤ ብዙም ሽባዎችና አንካሶች ተፈወሱ፤ በዚያችም ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፥ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ። ሲሞንም ደግሞ ራሱ አመነ፤ ተጠምቆም ከፊልጶስ ጋር ይተባበር ነበር፤ የሚደረገውንም ምልክትና ታላቅ ተአምራት ባየ ጊዜ ተገረመ።”

ሐዋርያቱ በአንጾኪያ የሰበኩትና በከተማይቱ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ትክክለኛው ታሪክ

ሐዋ 11፡27-28 “በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ አመለከተ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ሆነ።”

ሐዋ 13፡1-3 “በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ። በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው።” 

ሐዋ 14፡3 “ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለ መሰከረው ስለ ጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ተቀመጡ።”

ሐዋ 15፡32 “ይሁዳና ሲላስም ደግሞ ነቢያት ነበሩና ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጸኑአቸው።”

ሐዋ 21፡8-13 “በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፥ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን። ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ። ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ። እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ። ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል አለ። ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው። ጳውሎስ ግን መልሶ። እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም አለ።”

ማጠቃለያ

ከላይ ካየናቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክፍሎች የምንረዳው በአንጾኪያ የጠነከሩ እና ብርቱ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ነው፡፡ በመካከላቸውም ነቢያት እና ሐዋርያት ነበሩ፡፡

በኢስላማዊ ድርሳናት ደግሞ ሐዋርያት ወደ አንጾኪያ ሄደው እንደነበር በግልጽ ያስቀምጣሉ፡፡ እነዚያም የኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት ነበሩ፡፡ ከእነርሱም መካከል ጳውሎስ አንዱ ነበር፡፡ እንግዲህ መጀመርያ ላይ አንስተን ወደነበርናቸው አጣብቂኞች እንመለስ!

ሙስሊሞች ሆይ

  • በሱረቱል ያሲን (36) ፡13-29 የተነገረላቸው መልእክተኞች እነማን ናቸው?
  • በኢየሱስና በሙሐመድ መካከል መልእክተኛ ነበር ወይስ አልነበረም?
  • በሱረቱል ያሲን የተጠቀሱት ሐዋርያ ከሆኑ ጳውሎስን ጨምሮ ሌሎች ሐዋርያት የኢየሱስና የአላህ ታማኝ መልእክተኛና አገልጋዮች እንደነበሩ ታምናላችሁ?

ነቢዩ መሐመድና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ – እውነተኛው የእግዚአብሔር አገልጋይ ማን ነው?

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ