የቁርኣንን ኩረጃዎች ለማስተባበል የተደረገ ከንቱ ጥረት – ዙር ሁለት – በሳሂህ ኢማን

የቁርኣንን ኩረጃዎች ለማስተባበል የተደረገ ከንቱ ጥረት

ዙር ሁለት

በሳሂህ ኢማን

ውድ የሕያ፤ ሰሞኑን የቁርኣን ኩረጃዎች? የተሰኘውን መጣጥፍህን ተመልክቸዋለሁ፡፡ እኔንም ከአብዱልሐቅ ጀሚል ጋር አጋምደህ ስሜን አንስተሀል፡፡ ወንድሜ ዳንኤል ከልክህ በላይ መልሶልሀል፡፡  ከወንድሜ የጎደለ የመሰለኝን ልሞላ ብዕሬን አንስቻለሁ፡፡ ባለፈው የአብዱልሐቅን መጽሐፍ ለመተቸት ማስታወቂያ ባስነገርክበት ወቅት ገርመኸኝ እርሱን ለመተቸት የሞራልና የዕውቀት ብቃት እንደሌለህ ማስረጃ በመጥቀስ ነግሬህ እንደነበር የምትዘነጋው አይመስለኝም፡፡ ጥቂትም ሐሳቦችን ተለዋውጠናል፡፡ አሁንም ያሳየኸን ያንኑ ዕውቀት አጠርነትህን እንደሆነ ምን ያክል ገብቶህ እንደሆነ አላውቅም፡፡ ለነገሩ ቢገባህ እንዲህ ለመጫጫር አትሞክርም ነበር፡፡ ለማንኛውም ይህች መናኛ የሙግት ጽሑፍህን በጥቂቱ እድፈቷን ላስመልክትህ፡-

  1. የክርስቲያኖችን የሙግት ሐሳብ ማጣመም

“ቁርዓንን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ከሚነሱ የክርስቲያኖች መከራከሪያ ሚዛኑ ከፍ ያለ ጥቀስ ብባል ይህኛውን የሚገዳደር ያለ አይመስለኝም። “ቁርኣን ከመጽሀፍ ቅዱስ ኮርጇል”…”  

ይህ የጸሐፊዎችን የሙግት እምብርት የመገንዘብ እጥረትህን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ እውነት ነው ሐሳቡ እንደ ሙግት ሐሳብ ይነሳል፤ ነገር ግን የትኛውም ክርስቲያናዊ ጸሐፊ የቁርኣንን ኩረጃ እንደ ዋና መከራከሪያ ነጥብ አንስቶ አያውቅም፡፡ ዋነኛውና መሠረታዊው ጥያቄ ነቢዩ ሙሐመድ የእውነተኛው አምላክ መልእክተኛ ናቸውን? የሚለው ነው፡፡ ኩረጃ ደግሞ ነቢዩ ሙሐመድ የእውነተኛው አምላክ መልእክተኛ ላለመሆናቸው እንደ አስረጅ ነጥብ አንድ ተብሎ ይነሳል፡፡ በጠቀስካቸው ክርስቲያናዊ ጸሐፍትም እኔንና ወንድሜን ዳንኤልን ጨምሮ የሆነው ይኸው ነው፡፡

  1. የአብዱልሀቅ “ኢስላም መለኮታዊ ሃይማኖት ነውን?”

አማን ገረመውና አብዱልሐቅ አንድ ሰው ነው አይደለም ለሚለው ግምትህ ወንድሜ ዳንኤል በቂ ምላሽ ስለሰጠህ መድገሙ ስለማያስፈልገኝ እዘለውና ወደ ጠቀስከው የኩረጃ ትችትህ ልለፍ፡-

“አማን ገረመው የተሰኘ ፀሀፊ ስሞቹን የሙስሊም በማድረግ ከሚያሳትማቸው መጽሀፍት ውስጥ አንዱ የሆነው “ኢስላም መለኮታዊ ሀይማኖት ነውን?” በተሰኘው መጽሀፉ ገፅ 103 ላይ የቁርኣን ምንጭ ብሎ ከዘረዘራቸው ውስጥ አንዱ “ነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” መጽሀፉን ከክርስቲያኖች የተማረው” እንደሆነ ለማስረዳት ሲደክም እናየዋለን። የሚያስቀው ክፍል ግን ቀደም ብሎ ከገፅ 63 ጀምሮ ደግሞ “የቁርኣን ምንጭ ሰይጣን ነው” በሚል ሊያስረዳ ሲደክም እንደነበር ስታሳስታውሱ ነው። አንድ ሰው የቁርኣን ምንጭ መጽሀፍ ቅዱስ ነው ብሎ “ከተነተነ” በኃላ መልሶ “ቁርኣን የሰይጣን ቃል ነው” ካለ በተዘዋዋሪ መጽሀፍ ቅዱስ የሰይጣን ቃል መሆኑን መስክሯል ማለት ነው።”

ቀደም ብዬ መጽሐፉ ከአንተ አቅምና ዕውቀት በላይ ነው ያልኩህ ለዚህ ነው፡፡ ምናልባት ጽሑፍህ ደርሶት ምላሽ ይሰጥህ ይሆናል፤ እስከዛው ግን መጽሐፉን በጥንቃቄ እንዳነበበ ሰው ልመልስልህ፡-

  • መጽሐፉን ማንበብህ የሚያስመሰግንህ ቢሆንም እጅግ እንደሞገተህና ከአቅምህ በላይ ሆኖ እንዳስጨነቀህ ጽሑፍህ ያሳብቃል፡፡ በጠቀስካቸው ሁለቱ ገጾች ላይ ያሉት ሐሳቦች በተመለከተ ፍጹም የጸሐፊውን ሐሳብ ልታገኘው አልቻልክም፡፡ በገጾቹ ስለ ቁርኣን ኩረጃ የሚናገር ምንም ነገር እንደሌለ ያነበቡ ሁሉ ምስክሮች ናቸው፡፡ ጸሐፊው ከገጽ 60-109 ባለው ገጾች እያስነበበን ያለው “የመለኮታዊ መጽሐፍ ቁርአናዊ መለኪያዎች” በሚል በአንድ ርዕስ ላይ ነው፡፡ አምስት ቁርአናዊ መለኪያዎችን አውጥቷል፤ በዛም ራሱን ቁርኣንን ይለካል ቁርኣን የራሱን መለኪያዎች እንኳን ማለፍ እንዴት እንደተሳነው ለአንባቢዎቹ ያሳያል፡፡ ልኬታው ቁርኣንን በቁርኣን ሚዛን እንጂ ቁርኣንን በመጽሐፍ ቅዱስ አይደለም፡፡ በቁርኣንና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ስላለ መመሳሰል አለመመሳሰል አንድም ቦታ ላይ አላነሳም፡፡ ታዲያ ከየት አምጥተህ ነው “አንድ ሰው የቁርኣን ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ብሎ “ከተነተነ”” ልትል የቻልከው? ስለዚህ ስተኸዋል አላገኘኸውም፡፡
  • የጠቀስካቸው ገጾች የያዙትን ሐሳብ በተመለከተ፡- በእነዚያ ገጾች በጉልህ ሁለት መለኪያዎች ይታያሉ፤ አንዱ “ከአላህ ዘንድ የወረደ መሆን ይኖርበታል” በሚል መለኪያ ከገጽ 60-66 ድረስ ይዘልቃል፡፡ በዚህ መለኪያ “ቁርኣን እውን ከአላህ ወርዷልን?” በማለት 23 ዓመታት ወደ ነቢዩ ይመላለስ ነበር የተባለውን አካል ማንነት ከኢስላም መዛግብት በማመሳከር ይፈትሻል፡፡ ሙስሊሞችን የሚነዝሩ ማስረጃዎችን ከኢስላም መዛግብት እየመዘዘ የነቢዩ የዋሻ እንግዳ ሰይጣን እንደ ነበርና ቁርኣን ከአላህ እንዳልወረደ ያትምልናል፡፡ ይህንን ሲያደርግም መጽሐፍ ቅዱስና ቁርኣንን በማነጻጸር አይደለም፡፡ በሁለተኛው መለኪያም “ከሰውና ከሰይጣን ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነ” በማለት ከገጽ 101-109 ማስረጃውን ያቀርባል፣ ይለካል፣ ምልከታውን ያቀርባል፡፡ በዚህም እንደ ምድር መንቀጥቀጥ የሚያርገፈግፉ ኢስላማዊ ማስረጃዎችን እያቀረበ ቁርኣን በራሱ መለኪያ የገጠመውን ውድቀት ያሳያል፡፡ ይህንንም ሲያደርግ በመለኪያው ላይ እንደሚታየው ጣልቃ የገቡ የተባሉት “ሰውና ሰይጣን” እንደሆኑና እንዴት ባለ መንገድ ጣልቃ ገብ እንደሆኑ በማስረጃው ያሳያል፡፡ ታዲያ አንተ “የቁርኣን ምንጭ ብሎ ከዘረዘራቸው ውስጥ አንዱ “ነብዩ ሙሐመድ” መጽሐፉን ከክርስቲያኖች የተማረው” የሚለውን ከየት አመጣኸው? እርሱ ከክርስቲያኖች ተኮረጀ ብሏል? አሁንም ስተሃል አብዱልሀቅን አላገነኸውም፡፡ መጽሐፉን ያነበቡ ሊመሰክሩ እንደሚችሉት ስለ ክርስቲያኖቹ ያወራው፣ ስለ ማንንነታቸው ስማቸውን ሳይቀር የተናገሩት ቁርኣንና የኢስላም ጽሑፋት ናቸው፡፡ አብዱልሃቅ የተቸው በዛ ላይ አላህ ተናገረው መባሉን እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቁርኣን ኮረጀ የሚል መደምደሚያ አላስቀመጠም፡፡ ይልቁንም ሰዎች የተባሉት ክርስቲያኖቹ፣ ሱሃባዎቹ፣ ሰይጣናት፣ ዛፍ ለቁርኣን አንቀጾችን አዋጥተውለት የተጻፈ ነው፤ ስለዚህ በራሱ መለኪያ መለኮታዊ መጽሐፍ አለመሆኑን መስክሯል በማለት የትችቱን መደምደሚያ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ ስተሀል፡፡
  1. ቁርኣንና ኩረጃውን በተመለከተ የሰጠኸው ምላሽ

የጀመርከው “መመሳሰል ሁሌም ኩረጃ አይደለም” በሚል ነበር፡፡ በዚህ ስትጀምር በቁርኣንና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል መመሳሰል እንዳለ ማመንህን ያሳያል፡፡ መመሳሰሉ አለ ማለት ሁሌም ኩረጃ አለ ማለት እንዳልሆነ ለማስረዳት ሲትታትር ወንድሜ ዳንኤል ለዛ ከበቂ በላይ ምላሽ ሰጥቶበታል፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በእርሱ በጥልቀት ባልተዳሰሱት ላይ ጥቂት ልበልና የአንባቢን ግንዛቤ ሙሉ እናድርግ፡-

  • መመሳሰሉ አለ ካልክ ከኡስታዝ አቡ ሀይደር ጋር ማን ያስታርቅህ?

አንተ መጽሐፍ ቅዱስና ቁርኣን መሳሰል እንዳላቸው ብታምንም ኡስታዝ አቡ ሀይደር ደግሞ ላለመደናገር ማመሳከር በሚለው መጽሐፉ ከገጽ 41-48 ባለው ቁርኣንና መጽሐፍ ቅዱስ በሐሳብም ሆነ በመልእክት እርስ በእርሳቸው እንደሚቃረኑ ተናግሯል፡፡ ታዲያ ማን ያስታርቅህ? ለማንኛውም መጽሐፍ ቅዱስና ቁርኣን በሐሳብም ሆነ በመልእክት እርስ በእርስ ይቃረናሉ በሚለው የአቡ ሀይደር ሐሳብ እኔም እስማማለሁ፡፡ አብዱልሀቅ ጀሚል የዚህ ሐሳብ ተጋሪ መሆኑ በመጽሐፉ በግልጽ ይታያል፡፡ 

  • የመመሳሰሉን መንስኤ በተመለከተ፡-

“በተመሳሳይ ምንጫቸው አንድ የሆኑ ነብያት ያመጡት መልዕክት በይዘት ቢመሳሰል አንደኛው ከአንደኛው ቀድቶ ሳይሆን መሠረቱ አንድና አንድ ስለሆነ ብቻ ነው።”

የመመሳሰላቸው መንስኤ ከአንድ ምንጭ የተቀዱ መሆናቸው እንደሆነ ለማሳየት ሞክረሃል፡፡ በዚህም በትልቁ ስተሃል፡፡ በትክክል አንብበኸው ቢሆን የጠቀስከው የአብዱልሀቅ “ኢስላም መለኮታዊ ሃይማኖት ነውን?” መጽሐፍ በሁለት ርዕሶች ትንተና ስለሰጠበት ሐሳቡን ከማንሳትህ በፊት ደጋግመህ ታስብበት ነበር፡፡ ለማንኛውም አብዱልሀቅ “የቁርኣን የመለኮታዊ መጽሐፍ መለኪያዎች” በሚለው ትንተናው ቁርኣን መለኮታዊ መጽሐፍ አለመሆኑን፣ ከተለያዩ ምንጮች ተሰባስቦ የተሰደረ፣ ሰይጣንም ያዋጣበት እንደሆነ፣ የዋሻው እንግዳቸውም ገብርኤል መልአኩ እንዳልነበር መረጃን ዋቢ በማድረግ አሳይቷል፤ ስለዚህ  መጽሐፍ ቅዱስና ቁርኣን ሊመሳሰሉም ሆነ ምንጫቸው አንድ ሊሆን አይችልም፡፡ ይመሳሰላሉ ብለህ ድርቅ ካልክም ደግሞ ኩረጃው ትክክል ነው ወደሚል መደምደሚያ ያደርሰናል፡፡ በሁለተኛው “በኢስላም የእውነተኛ ነቢይ መመዘኛ ነቢዩ ሲመዘኑ” በሚለው ርዕስ ነቢዩ አንዱንም የራሳቸውን መለኪያ ባለማሟላት ከእውነተኛ ነቢያት ጎራ ወጥተው ወድቀዋል፡፡ ይህም  መጽሐፍ ቅዱስና ቁርኣን ከአንድ ምንጭ ላለመቀዳታቸውና አንድ አምላክ እንዳክላካቸው ማሳያ ይሆናል፡፡ እንዲህ ሆኖ ሳለ አሁንም መመሳሰሉ እንዳለ ካመንክ ኩረጃው እርግጥ በሆኑን አንተው እያረጋገጥክ ነው ማለት ነው፡፡

እነዚህ ሁለት ነጥቦች የአቡ ሀይደርንና የአብዱልሀቅን መጽሐፍ ቅዱስና ቁርኣን አይመሳሰሉም የሚለውን የሙግት ሐሳባቸውን እርግጥ ያደርገዋል፡፡ ይህ የምጋራውና የማምንበት ነጥብ ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስንና ቁርኣንን በተመለከተ “መመሳሰሎች ሁሌም ኩረጃ አይደሉም” የሚለው የሙግት ሐሳብህ ገለባ ነው፡፡ ይህንን ስል ግን ቁርኣን ከመጽሐፍ ቅዱስ አልተመሳሰለም ማለቴ አልኮረጀም ማለቴ አይደለም፡፡ ከዚህ 66 መጽሐፍትን ካቀፈው ግዙፍ መጽሐፍ ውስጥ ግን ምንም ተመሳሳይ ሐሳብ የለም ማለቴ መሆኑ ግንዛቤ ይያዝልኝ፡፡ እንዲያውም ያልተኮረጀ አንድም እንደሌለ ማስረጃዎቸን ማቅረብ እችላለሁ፡፡

  • በኩረጃ የተፈረጁ ታሪኮች በማለት የተሰጠው ማሳያ/ምሳሌ

ይህንን ሐሳብ ለመሞገት እንዲህ የሚል ማስተባበያ አቅርበሃል፡-

“ተኮርጀዋል በሚል በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ታሪኮች በዋነኛነት ጥንተ ነገር አጥኝዎች/Orentalists/ የገለጿቸው ናቸው። ለዚህ ስራ በብዙዎች ዘንድ እንደ መነሻ ተደርጎ የሚቀርበው በ19ኛው ክፍለ ዘመን አብርሐም ጊገር በተሰኘ አይሁድ የተፃፈው መጽሀፍ ነው። መጽሀፉ እንዲሁ መመሳሰሎችን ከመዘርዘር በዘለለ በነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” ጊዜ የትኛው የአይሁድ መጽሀፍ በየትኛው ክፍል እንደነበር እራሱ አያትትም። ከዚያም በተጨማሪ ነብዩ ሙሐመድን “ﷺ” በምን መልኩ ይህን ሊያውቁ ቻሉ? የትኛው ራባይ አስተማራቸው? የሚለውን አሰመልክቶም ምንም የሚሰጠው ማብራሪያ የለም።”

እንዲህ የሚል ማስተባበያ ለመጻፍ ብዕርኑ የሚያነሳ ሰው በነጥቡ ላይ ዕውቀት አጠርና ለሙግቱ የማይመጥን ሰው መሆኑን ከጅምሩ ይገልጣል፡፡ የኒህን ሰው መጽሐፍ ያውቀዋል? ለእያንዳንዱ ሙግትስ ማስረጃን ላለመስጠታቸው ምን ያክል እርግጠኛ ነው? የትኛውን መጽሐፋቸውን ነው የሚያውቀው? ለማንኛውም ራባይ አብርሃም ጊገር ለጻፏቸው መጽሕፍት በሙሉ ደረጃውን የጠበቀ ይመጥናል ያሉትን ማጣቀሻ ከበቂ በላይ ሰጥተውናል፡፡ የሕያ ያ አይበቃም ካለና ሙሉ መረጃ እንዳልሰጡ ካሰበ አሁን እኛ አለን፤ ይህንን ክፍተት እንሞላዋለን አይዞህ፤ የትኛው ከየትኛው መጽሐፍ እንደተወሰደ በድንቅ ማስረጃ ማቅረብ የምንችልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ ለዚህ ማሳያ በቅርቡ ወንድማችን ዳንኤል ለነቢዩ ሙሐመድ ሱራ 2 እና 3 ትን ስለጻፈላቸው ሰውና ስለ ነቢዩና ስለመገለጣቸው ምን ይል እንደነበር ከቡኻሪ ሐዲስ ጠቅሶ አስነብቦናል፡፡  አብዱልሀቅ ጀሚልም በመጽሐፉ ነቢዩ ከማን እንደተማሩ፣ ማን በእርሳቸው ዙሪያ እንደነበር፣ ምንን ከማን እንዳመጡትና እንዴት እንደተጠቀሙበት፣ የራሳቸው የሆነ አንድም እንደሌለ በማስረጃ አጥግቦ አስነብቦናል፡፡ ለማንኛውም የሕያ እንዳልከው ሳይሆን ነቢዩ ሙሐመድ የትኛውን የቁርኣን ክፍል ከየትኛው መጽሐፍ እንዳመጡት፣ ለዚህም ማንን ሊጠቀሙ እንደቻሉ፣ ያንንም በምን መልኩ ሊያውቁ እንደቻሉ መናገር እጅግ ቀላል ነው አታስብ፡፡

የራባይ አብርሃም ጊገርንና እርሳቸውን ተከተሉ ያልካቸው ወገኖች በቁርኣን ኩረጃ ላይ የሚያነሱትን ሙግት ለማስተባበል ያመጣኸውን ምሳሌ እንመልከት፡-

“የኖህ አስተምህሮና የሙሴ አስተምህሮ መመሳሰል አንደኛው ኮራጅ ነው አያስብልም። ሁለቱም መሠረታቸው ተመሳሳይ ከመሆኑ አንፃር የአስተምህሯቸው መመሳሰል የሚጠበቅ ነው። ከዚያ በዘለለ ደግሞ እርምት የሚያስፈልጋቸው አንዳንድ ቅጥፈቶችም አሉ።ለአብነት አንዳንድ ፀሀፍት ነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” ከብሉይና አዲስ ብቻ ሳይሆን ከአይሁድ ታልሙዶችም ጭምር ወስደዋል የሚሉ ክሶችን በማቅረብ ብዙ መመሳሎችን ይጠቅሳሉ። … ከነዚህ ውስጥ ግን ምናልባት መዳሰስ የሚኖርባቸው የተወሰኑ ቅጥፈቶች ይኖራሉ። ለአብነት በቁርኣን የተጠቀሰው የሰበዕ ታሪክ (በሱራ 27) በአይሁድ መጽሀፍት ውስጥ ይገኛል የሚለው የተዛባ ክስ ነው። ይገኝበታል የተባለው የመጽሀፈ አስቴር “ታርጉም” መጽሀፍ የተፃፈበትን አመት ለተመለከተ ሰው ከነአካቴው ከቁርኣን በኃላ እንደሆነ ይገነዘባል። የመጀመሪያው ታርጉም የተፃፈው በ700 ገደማ ሲሆን ሁለተኛው ታርጉም ደግሞ የተፃፈው በ800 አመት ገደማ ነው። ይህ ማለት ከነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” መሞት ከብዙ አመታት በኃላ ማለት ነው (“Esther”, The Jewish Encyclopedia ገፅ 238)

እንደ ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ ገለፃ ከሆነ ደግሞ የዚህ መጽሀፍ ፀሀፊ የተወሰኑ የአረብኛ ፁሁፎችን እንደምንጭነት ተጠቅሞ ነበር ይለናል (Targum Sheni”, Encyclopaedia Judaica) ይህ ማለት ፀሀፊው እራሱ የነበረው ከነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” ህልፈት ከብዙ አመታት በኃላ ሲሆን ለዚህ ፁሁፉም የተለያዩ አረብኛ ምንጮችን ተጠቅሞ ነበር።…”  

ይህንን እንዳነበብኩ ከጉግል ጎልጉለህ ተርጉመህ የራስህ በማስመሰል ያሳተምከው “አልተሰቀለም” ትዝ አለኝ፡፡ ይህንንም እንደዛው ጎልጉልጉለህ ነው ያመጣኸው፡፡ ራስህ አንብበህ መረጃውን የሰደርክ ቢሆንማ ኖሮ ሁለቱን አውደ ጥበቦች በዚህ መልኩ አትጠቅሳቸውም ነበር፡፡ ለምን አትለኝም?

  1. “Esther”, The Jewish Encyclopedia ገፅ 238 በማለት በጠቀስከው ገጽ ላይ አንተ ያልከው ሐሳብ የለም፡፡ በገጽ 238 ላይ የተመለከተው ገጽ 237 ላይ የጀመረ “Esther, Apocryphal book” ለሚለው ማብራሪያ ነው፡፡ ይህ የመጽሐፉን ዕድሜ ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ ነበረ የመቃቢያን ዘመን ሲወስደው ታይ ነበር፡፡ ስለ አስቴር መጽሐፍ ትርጉም የተጻፈበት ዓመት የሚዘረዝረው ሐሳብ ያለው ግን ገጽ 234 ላይ ነው፡፡ ታዲያ ካልጎለጎልክ በስተቀር ይህንን ቀላል ስህተት እንዴት ልትሳሳት ቻልክ?
  2. Targum Sheni”, Encyclopaedia Judaica ን አንብበህ ቢሆን ኖሮ ትርጉሙ ስለተጻፈበት ዓመት 700 እና 800 ያልከውን አትጽፍም ነበር፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ቁጥሮች አልተጠቀሱምና፡፡

Date፡-

The date of the work cannot be determined exactly. The view of S. Gelbhaus (see bibl.) that it belongs to the amoraic period, in the fourth century, is disproved by the fact that it contains later material. P. Cassel (see bibl.) dates it in the sixth century and explains its mention of Edom to be the rule of Justinian (527–565)… L. Munk (see bibl.) puts its date still later, in the 11th century, but he gives no proof. It seems that the most acceptable view is that which places its composition at the end of the seventh or the beginning of the eighth century, a view that is strengthened by its relationship to the Pirkei de-R. Eliezer.  (“Targum Sheni”, Encyclopaedia Judaica, vol 19, page 513-514)

  1. “ለዚህ ፁሁፉም የተለያዩ አረብኛ ምንጮችን ተጠቅሞ ነበር” የሚለው ነው፡፡ የአረብኛን የስነ ጽሑፍ ታሪክ ብታውቅ ኖሮ ቁርኣን ማለት አለመሆኑን መረዳት በቻልክ ነበር፡፡

ለማንኛውም የሕያ ለማስተባበያ ያቀረባቸው ማስረጃዎች ቁርኣን እንዳልተኮረጀ ማሳያ ሊሆኑ ፈጽሞ አይችሉም፡፡ ለዚህ በርካታ ነጥቦችን ማንሳት ቢቻልም ከራሱ መረጃዎች በመነሳት ጥቂት ልበል፡-

  • Targum Sheni የአራማይስጥ ትርጉም ሲሆን ቀደም ብላችሁ እንዳነበባችሁት ስለተተረጎመበት ጊዜ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ጸሐፍት የተለያዩ የጊዜ መላምቶችን ሰጥተዋል፡-

ይህ አውደ ጥበብ የትርጉም ሥራው ጊዜ በጣም ተቀባይነት ያለው ብሎ ያመነው 7ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እኛ 8ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ መሆኑን ነው፡፡ መላምት መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ ይህ ጊዜ ምንም ነቢዩ ሙሐመድ በሕይወት ያልነበሩበት ጊዜ ቢሆንም ውል ያለው የቁርኣን መጽሐፍ የተጻፈበት ወቅት እንዳልነበር የቁርኣን ታሪክ ያስረዳል፡፡ ራሱ የሕያ “የቁርኣን አሰባሰብ”ን በተመለከተ ለተማሪዎቹ ለማስተማር የቁርኣን ታሪክና ሳይንስ መጽሐፍትን ሲያገላብጥ በዚህ ጊዜ ምን ደረጃ ላይ እንደነበር ያየ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ላይ በአብዛኛው ሙስሊም እጅ ያለው በ1926 ዓ.ም ግብጽ ላይ እንደገና ማሻሻያ የተደረገለት የሐፍስ ቅጅ እንኳን ተጻፈ የሚባለው ከ706–796 ወይም 90–180 AH በኖረው Hafs al-Asadi al Kufi በተባለ ሰው ነው፡፡ ከዚህ ሰው በፊት የተጻፈ አንድም የቁርኣን መጽሐፍ ለምልክት እንኳን ምድር ላይ የለም፡፡ ይህ በቱርኩ ሙስሊም ፕሮፌሰሮች ተረጋግጧል፡፡ የአራማይስጥ ቋንቋም እስከ መዲና ድረስ ይነገር ስለነበር የተተረጎመበትና የትርጉም መጽሐፉ በአካባቢው በነበሩ አይሁዶች ዘንድ የታወቁና የተስፋፉ ነበሩ፡፡ ስለዚህ የቁርኣን ጸሐፊዎች ከእነዛ መጽሐፍት አልኮረጁም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ይሆናል፡-

  • Encyclopedia of Islam vol 1, page 1220

” BILKlS፡- is the name by which the Queen of Sheba is known in Arabic literature. The story of the 1 Queen’s visit to King Solomon (based on I Kings X, i-io, 13) has undergone extensive Arabian, Ethiopian, and Jewish elaborations and has become the subject of one of the most wide-spread and fertile cycles of legends in the Orient. … Although the Kur’an and its commentators have preserved the earliest literary reflection of the complete Bilkis legend, there is little doubt that the narrative is derived from a Jewish Midrash. This judgement is based not only on intrinsic probability and our knowledge of the general influence of the Midrashic genre on early Islam, but is also supported by: …”

ስለዚህ የንግሥቷን ታሪክ የሚጋሩና የእኔ የእኔ የሚሉት ብዙ ሕዝቦች እንደመሆናቸው ከኢስላም በፊት አገር የናኘ አፈ ታሪክ እንደነበር ከዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ታሪኩ እንደተባለው የ7ኛና 8ኛ ክፍለ ዘመን ታሪክ ሳይሆን ከዛ የቀደመ ነው፡፡ ለዚህ አንድ ምሳሌ ከታሪክ አት-ጠበሪ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ መጽሐፍ የተጠቀሰ ጡባ የሚል (the Yemeni leader who ruled between A.D. 410 and 435 and occupied Mecca)  የየመን ንጉሥ እስከ መካ ድረስ ይገዛና ይቆጣጠር ነበር፡፡ ይህ ሰው ከመዲና በወሰዳቸው ሁለት ራባዮች አማካኝነት ይሁዲነትን ተቀብሎ ነበር፡፡ ስለ ንግሥት ሳባ በቅኔዎቹ እንዲህ ይል እንደነበር ታሪክ ዘግቦታል፡-

The History of al-Tabari, vol 5, page 174.

“…Bilgis was my paternal forebear (literally, “aunt”) and ruled over them until the hoopoe came to her”   

ስለሆነም አፈ ታሪኩ ነቢዩ ሙሐመድ ከመወለዳቸው ከ100 ዓመት ቀድሞ የነበርና አካባቢውን ያጥለቀለቀ እንጂ ተርጉም ሸኒ ላይ የጀመረ አይደለም፡፡ ስለዚህ ነቢዩ ይህንን አፈ ታሪክ ከአይሁዳውያን አልኮረጁም ብሎ ለመንፈራገጥ መሞከር ትርፉ መላላጥ ነው፡፡

ሳሂህ ኢማን!

ቸር ይግጠመን!!

ደካማ አመክንዮ የተዛባ ምንጭ

ቅዱስ ቁርኣን