መርዛማ ዕፅዋትን በተመለከተ ሁለተኛ ዙር ምላሽ

ያህያ ኢብኑ ኑህ የተሰኘ አንድ አብዱል ዘፍጥረት 1፡29 ላይ የሚገኘውን ቃል በተመለከተ ላነሳው ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ የሰጠነው ቢሆንም ምላሻችንን በማጣመም “የመልስ መልስ” ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ የእርሱን ሙግትና የኛን ምላሽ የያዘውን ጽሑፍ በዚህ ሊንክ ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-

ያህያ

ይህንን ጥያቄየን አስመልክቶ ምላሽ ለመስጠት የሞከሩ ክርስቲያን ወገኖችን ተመልክቻለሁ። በመጀመሪያ ምላሽ ለመስጠት መሞከራቸውን አከብራለሁ፤ መሠል ልማዶችም እንዲቀጥሉ ምኞቴ ነው።

ወደ መልሱ ስገባ ግን መልሱ እንዳሰብኩት ብዙም አመርቂ ሁኖ አላገኘሁትም። ለምላሽ ተብሎ የተለቀቀው ማብራሪያ በአጭሩ ሲጠቃለል “ትዕዛዙ አዳምና ሔዋንን ብቻ የሚመለከት ነው” የሚል ነው። ይህ መልስ መውጫ ፍለጋ የተዳከረበት “ጥረት” እንጅ ተራ ማስተባበያ እንኳን ሊሆን እንደማይችል “መላሹ” እራሱ ውስጡ ሳይነግረው የሚቀር አይመስለኝም። ሌላው አንባቢም መለስ ብሎ አንቀፁን ብቻ በማየት መልሱ የረባ እንዳልሆነ መረዳት አይከብደውም። ከዚህ በታች በመጠኑ ስህተቱን ለማሳየት እሞክራለሁ።

—-

መልስ

የኛ ምላሽ አጭርና ግልፅ ሆኖ ሳለ እኛ የተናገርነውን በቀጥታ ጠቅሰህ መልስ መስጠት ሲኖርብህ እርባና የሌላቸውን የክርክር ቃላት ማንጋጋህ የሙግት እጥረት እንደገጠመህ ያሳብቃል፡፡  ለማንኛውም “ትዕዛዙ አዳምና ሔዋንን ብቻ የሚመለከት ነው” የሚል ነገር በመልሳችን ውስጥ የለም፡፡ ይህ ያንተ የተሳሳተ መረዳት ነው፡፡ እኛ የተናገርነው ፈቃዱ ከውድቀት በፊት በኤደን ገነት ውስጥ ለአዳምና ለሔዋን የተሰጠ ነው የሚል ነው፡፡ የሰው ዘር አባትና እናት ለሆኑት ለአዳምና ለሔዋን ከተሰጠ ደግሞ ከእነርሱ ለሚወለዱት ሁሉ የተሰጠ ፈቃድ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ችግሩ አዳምና ሔዋን ኃጢአት በመሥራት ከመልካሙ በረከት መጉደላቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሰው ልጆች ሁሉ ከዚህ መልካም ነገር ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ጎበዝ መልስ ከመስጠት በፊት የተሟጋቻችንን ሙግት በትክክል ማንበብ አይቀድምም?

—-

ያህያ

፩- ከላይ ጀምሮ አውዱን ለተመለከተ ማንኛውም ሰው አንቀፁ የተወሰነ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን መላው የሰው ልጅ ትውልድን የሚመለከት እንደሆነ ይረዳል። መቸም ሰማያትና ምድር፤ እፅዋትና እንስሳት ለአዳምና ሔዋን ብቻ የተፈጠሩ አካላት እንዳልሆኑ ሁላችንም እናውቃለን።

—-

መልስ

አዳምና ሔዋን ኃጢአትን ባይሠሩ ኖሮ የሰው ልጆች ጥረው ግረው እንዲበሉ ባልተወሰነባቸው ነበር፤ ለጎጂ ነገሮችም ባልተጋለጡ ነበር፡፡ ምድር ከተረገመች በኋላ የሰው ልጆች ጥረው ግረው እንዲበሉና ከጎጂ እፅዋት ጋር እንዲታገሉ ተፈረደባቸው፡፡ ይህ በግልፅ የተጻፈ ሆኖ ሳለ እኛ ያላልነውን ሙግት ፈጥሮ የተንሻፈፈ ነገር ማውራት አስቂኝ ነው፡፡

—-

ያህያ

፪- አንቀፁ ያለበትን ህፀፅ ለመሸፈን ወስደን ለአዳምና ሔዋን ካደረገን አይቀር ተመሳሳይ አፕሮችም ለተመሳሳይ የእግዚአብሔር ንግግሮች ማድረግ ይኖርብናል ማለት ነው። ለአብነት፦

❝እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።❞ ዘፍጥረት 1: 28

እንደ መላሹ ሎጂክ መሠረት ይህ አንቀፅም የሚመለከተው አዳምና ሔዋንን ብቻ ነው ማለት ነው። አሁን ላይ ያሉ ሰዎች እነዚህ ትዕዛዛት አይመለከታቸውም ሊለን ነው። ይህ ደግሞ ስህተት እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው እውነታ ነው። የሰው ልጅ ከአዳምና ሔዋን በኃላም ቢሆን እየተባዛ የሚኖርና በሌሎች የምድር ፍጥረታትም ላይ ገዥ የተደረገ ነው። መሠል አይነት ሎጂክ እምባዛም የሚረባ አይደለም።

—-

መልስ

ጥቅሱ ምንም ዓይነት ህፀፅ የለበትም፡፡ ነገሮችን በትክክል እንዳትረዳ እንቅፋት የሆነብህ ያንተ አቅጣጫን የሳተ ምልከታ ነው፡፡ አዳምና ሔዋን ከገነት ባይባረሩና እግዚአብሔር ምድርን ባይረግማት ኖሮ እፅዋት ጎጂ ባልሆኑ ነበር፡፡ ይህ ዘፍጥረት 3፡17-18 ላይ በግልፅ ተጽፎልሃል፡፡ ቀደም ባለው ምላሽ ይህንን ጥቅስ ብንጠቅስልህም ለማየት ፈቃደኛ የሆንክ አትመስልም፡፡ ደግመህ እየው፡-

አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ

በገነት ውስጥ ለአዳምና ለሔዋን የተሰጠው በረከት በውድቀት ምክንያት ከኛ ላይ ተወስዷል ወይንም ተቀንሶብናል፡፡ ሰው ለዘላለም እንዲኖር ነበር የተፈጠረው፤ ነገር ግን ከውድቀት በኋላ ሞት ወደ ዓለም ገባ፡፡ ዛሬ እፅዋትን እንበላለን ነገር ግን ብዙዎቹ ለመብል ምቹ ባለመሆናቸው ልንበላቸው አንችልም፡፡ መጀመርያ ግን እንዲህ አልነበረም፡፡ አንተ የጠቀስከውን መባዛትን እንውሰድ፤ ዛሬ የሰው ልጆች ይዋለዳሉ ነገር ግን እናቶች በከፍተኛ የምጥ ህመም ይወልዳሉ፡፡ በወሊድ ምክንያት የሚሞቱት ብዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶች ልጅ መውለድ እየፈለጉ መውለድ ባለመቻላቸው ምክንያት የኀዘን ኑሮ ይኖራሉ፡፡ አያሌ ህፃናት አካላቸው የጎደለና የተዛባ ሆነው ይወለዳሉ፡፡ በፅንስ ደረጃ ሳሉ የሚጨነግፉና እንደ ተወለዱ የሚሞቱ ህፃናትም ብዙ ናቸው፡፡ ታድያ ይህ ሁሉ ሰቆቃ ከገነት ባንባረር ኖሮ ይኖር ነበር? የእፅዋት ጎጂነትም እንደዚያው ነው፡፡ ሰው በኃጢአት ባይወድቅ ኖሮ እፅዋትን ሁሉ ሳይጎዱት መብላት በቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሰው ውድቀት በኋላ ምድር ስለተረገመች ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ ጎጂ አይደሉም ብለን የምንመገባቸው እፅዋትና እንስሳት እንኳ የየራሳቸው የሆነ ጎጂ ጎን (Side Effect) እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ይህንን ቀላል እውነታ መረዳት እንዴት እንደተሳነህ ማሰብ ያዳግታል፡፡

በተረፈ ቁርኣንን የጠቀስነው “ሁሉም ተፈቅዷል” ማለት ሰው የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን አስተውሎ የመምረጥ ችሎታና መብት የለውም ማለት እንዳልሆነ እንድትገነዘብ ነው፡፡ በሱራ 6፡145 መሠረት ከአራቱ ነገሮች ውጪ አንድ ሰው መብላት የሚፈልገውን ሁሉ መብላት እንደሚችል ተነግሯል፡፡ ይህ ማለት ግን ሰው የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን መምረጥ አይችልም ማለት አይደለም፤ ጎጂ ነገሮችንም መብላት አለበት ማለትም አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዳደረከው ነገሮችን አጥምመን እንያቸው ካልን ግን ቁርኣን ከአራቱ ነገሮች ውጪ መበላት የማይችል ምንም ነገር እንደሌለ በመናገር ጎጂ እንስሳትንም ጭምር እንድንበላ ይፈቅዳል ብሎ መተርጎም ይቻላል፡፡  ሱራ 16፡114-115 ላይ “አላህም ከሰጣችሁ ሲሳይ የተፈቀደ ንጹሕ ሲኾን ብሉ” የሚለው ጥቅስ ሁሉንም ነገር መብላት እንደሚቻል ከሚናገረው ሱራ 6፡145 ላይ ከሚገኘው ጥቅስ ጋር ይጋጫል ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡ ወይንም ደግሞ አላህ የከለከላቸው አራቱን ብቻ እንደሆነና የተቀረው ግን የተፈቀደና ንጹህ መሆኑን እየተናገረ እንደሆነ በመቁጠር መተርጎም ይቻላል፡፡ አንተ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀምከውን ቅንነት የጎደለው አካሄድ ከተጠቀምን ነገሮችን እያጣመሙ በብዙ መንገዶች መከራከር ቀላል ነው፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ግን ለማናችንም ጠቃሚ አይደለም፤ እውነትንም ወደ ማወቅ እንድንደርስ አያስችለንም፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ሲፈጥር የሚጎዳውንና የሚጠቅመውን እንዲያውቅ አድርጎ ነው፡፡ እንስሳት እንኳ የትኛው እፅዋት እንደሚስማማቸውና እንደማይስማማቸው ለይተው ያውቁ የል? እግዚአብሔር አምላክ አንዴ የመብላት መብት ከሰጠን እርሱ በሰጠን ዕውቀት የሚስማማንን መርጠን የመጠቀም ኃላፊነት የእኛ ነው፡፡ በሌላ መንገድ ካሰብን ደግሞ ዛሬ ጎጂና መርዛማ ናቸው ያልናቸውን እፅዋት ነገ ዕውቀታችን ሲያድግ ለመብልነት የምናውልበትን ዘዴ መፍጠር እንችላለን፡፡ የሰው ልጆች በዕውቀት እያደጉ በመሆናቸው ትላንት ጎጂ የተባሉትን ዛሬ ጠቃሚ እያደረጉ ነው፡፡ ብዙ መድኃኒቶችም የሚቀመሙት መርዛማ ከምንላቸው እፅዋት ነው፡፡ ስለዚህ ያንተ ሙግት እንደተለመደው ከጥቅሱ አውድ ጋር ብቻ ሳይሆን ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ጋርም የሚጣጣም አይደለም፡፡ ለወደፊቱ በደንብ አስበህ የሚመጥን ሙግት ይዘህ ለመቅረብ እንደምትሞክር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ዳንኤል