መጽሐፍ ቅዱስ መርዛማ እፅዋትን እንድንመገብ ያዛልን?

መጽሐፍ ቅዱስ መርዛማ እፅዋትን እንድንመገብ ያዛልን?

አንድ ሙስሊም እንዲህ ሲል ይጠይቃል፡-

“እግዚአብሔርም አለ። እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ፡፡” (ኦሪት ዘፍጥረት 1:29)

በዚህ አንቀፅ እንደምንመለከተው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ሲመክር ምድር ላይ የፈጠራቸውን የእፅዋት ዘር በጠቅላላ ለምግብነት መጠቀም እንደምንችል ይገልጻል፡፡ እንደሚታወቀው ደግሞ በዚህ ምድር ላይ ያሉ እፅዋት በጠቅላላ ለምግብነት ምቹ አይደሉም፤ መርዛማ ፍሬዎችን ጨምሮ ለሰው ልጅ ተስማሚ ያልሆኑ ፍጥረታትም እንዳሉ አይዘነጋም፡፡

ታዲያ እግዚአብሔር እነዚህን ሳይቀር ያለምንም መለያየት ለመብልነት ፈጠርኩ ሲል ምን ማለቱ ነው? ሌላው ይቅርና እርስዎ ልጅዎትን ከግቢ ውጭ ካሉ እፅዋት ውስጥ የፈለገውን እንዲበላ ይመክሩታል?

——

ይህ በብዙዎቻችን ቤት የሚገኝ የጌጥ ተክል ደምብ ኬን በመባል የሚታወቅ ሲሆን ከተበላ የአፍና የጎሮሮ እብጠት እንዲሁም የድምፅ ማጣት አደጋን ሊያስከትል የሚችል መርዛማ ተክል ነው፡፡

ዶ/ር ዛኪር ናይክ ከዶ/ር ዊልያም ካምቤል ጋር በነበራቸው ክርክር ወቅት ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ የጠያቂው ችግር ቃሉ የትና መቼ እንደተነገረ አለማስተዋሉ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ይህንን ቃል የተናገረው ለአዳምና ለሔዋን ሲሆን ከውድቀት በፊት በኤደን ገነት ውስጥ ነበር፡፡ ሰው በኃጢአት ከመውደቁና ምድር ከመረገሟ በፊት ሁሉም ነገር መልካም እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡-

“ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።” (ዘፍጥረት 1፡12)

ነገር ግን ከውድቀት በኋላ ምድር በመረገሟ ምክንያት እፅዋት ጎጂ ወደመሆን ተለወጡ፡-

“አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ።” (ዘፍጥረት 3፡17-18)

በርግጥ እግዚአብሔር አምላክ ያለ ምንም ልዩነት ሁሉንም እፅዋት እንዲበሉ ለሰው ልጆች ፈቅዷል የሚለው የጠያቂው ምልከታ ስህተት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰዎች ለትዕዛዙ ያላቸውን ታማኝነት ይፈትንበት ዘንድ የፈጠረውን መልካምና ክፉውን ከሚያሳውቀው ዛፍ እንዳይበሉ ከልክሏቸዋል፡-

“እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ … እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” (ዘፍጥረት 2፡8-9፣ 2፡16-17)

በዚህ ጥቅስ መሠረት እግዚአብሔር አምላክ ያበቀላቸው ዛፎች “ለመብላትም መልካም” የነበሩ ሲሆን መብላት የሌለባቸውንም አንዱን ለይቶ ነግሯቸዋል፡፡

ስናጠቃልል ይህ ፈቃድ የተሰጠው ከውድቀት በፊት በኤደን ገነት ውስጥ ለአዳምና ለሔዋን መሆኑ ከግንዛቤ ውስጥ ሲገባ ጥያቄው በተሳሳተ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ግልፅ ይሆናል፡፡

——

አሁን ደግሞ ተራው የናንተ ነው፡፡ እስኪ የገዛ አመክንዮአችሁን ቁርኣን ላይ ተግባራዊ እናድርግና የሚሆነውን እንይ፡፡ ሱራ 6፡145 ላይ በተጻፈው መሠረት የተከለከሉት ምግቦች 4 ዓይነት ብቻ ሲሆኑ ሌላው ሁሉ ተፈቅዷል፡-

“(ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው፡- «ወደእኔ በተወረደው ውስጥ በክት ወይም ፈሳሽ ደም ወይም የአሳማ ስጋ እርሱ ርኩስ ነውና ወይም በአመጽ ከአላህ ስም ሌላ በእርሱ ላይ የተወሳበት ካልኾነ በስተቀር በሚመገበው ተመጋቢ ላይ እርም የኾነን ነገር አላገኝም” (ሱራ 6፡145)

ስለዚህ በዚህ ጥቅስ መሠረት በክት፣ ፈሳሽ ደምና የአሳማ ሥጋ ብቻ ነው የተከለከለው፡፡ ጎጂ እንስሳትም ለምግብነት ተፈቅደዋል ማለት ይሆን?


መርዛማ ዕፅዋትን በተመለከተ ሁለተኛ ዙር ምላሽ

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ