ጌታችን ኢየሱስ “ከፍጥረት በፊት በኩር” ተብሎ መጠራቱ ምንን ያሳያል?

ጌታችን ኢየሱስ “ከፍጥረት በፊት በኩር” ተብሎ መጠራቱ ምንን ያሳያል?


ሙስሊም ሰባኪያን ከይሖዋ ምስክሮች በመቅዳት በማሕበራዊ ገፆች ላይ ከሚያስጮኋቸው ሙግቶች መካከል አንዱ በቆላስይስ 1:15 ላይ የሚገኘውን ቃል መሠረት ያደረገ ሲሆን “ኢየሱስ የፍጥረት በኩር” መባሉ ፍጡር መሆኑን ያሳያል ይሉናል፡፡ እውን እነርሱ እንደሚሉት ይህ ጥቅስ ኢየሱስ ፍጡር መሆኑን ያሳይ ይሆን? በዚህ ጽሑፍ ይህንን ሙግት እንፈትሻለን፡፡ ቃሉ እንዲህ ይነበባል፡-

“እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።” (ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1:15-16)

“Who is the image of the invisible God, the firstborn of every creature: For by him were all things created, that are in heaven, and that are in earth, visible and invisible, whether they be thrones, or dominions, or principalities, or powers: all things were created by him, and for him:” (KJV)

ὅς ἐστιν εἰκὼν τοῦ Θεοῦ τοῦ ἀοράτου, πρωτότοκος πάσης κτίσεως,

በዚህ ጥቅስ ውስጥ “በኩር” (Firstborn) ተብሎ የተተረጎመው ቃል በግሪኩ ንባብ πρωτότοκος (ፕሮቶቶኮስ) የሚል ሲሆን ሰፊ ትርጉም አለው። “መጀመሪያ የተወለደ” ከሚለው በተጨማሪ እንደየአገባቡ ሥልጣንን፣ የበላይነትን፣ ተወዳጅነትንና  ልዩ የሆነ ግንኙነትን ያሳያል። ለአብነት ተከታዮቹን ጥቅሶች እንመልከት፡-

“ያዕቆብም። በመጀመሪያ ብኵርናህን (πρωτοτόκιά) ሽጥልኝ አለው።” (ኦሪት ዘፍጥረት 25:31)

በዚህ ክፍል በሰብዓ ሊቃናት የብሉይ ኪዳን ትርጉም “ፕሮቶቶኪያ” የሚለው ብኩርናን የሚያመለክተው ቃል የገባው ሥልጣንን ለማሳየት እንጂ መጀመሪያ መወለድን ለማሳየት አይደለም። እንደዚያ ቢሆንማ ኖሮ ዔሳው ወደ እናቱ ማህፀን ተመልሶ ከእንደገና ተወልዶ ያዕቆብን በኩር ማድረግ ነበረበት። ነገር ግን ብኩርና መብትና ሥልጣንን የሚያመለክት በመሆኑ ዔሳው ለያዕቆብ ብኩርናውን መሸጡ የተነገረው መብትና ሥልጣኑን አሳልፎ መስጠቱን ለማመልከት ነው፡፡ በትንቢተ ኤርምያስ ውስጥም ተመሳሳይ ሐሳብ እናገኛለን፡-

“በልቅሶ ወጡ እኔም በማጽናናት አመጣቸዋለሁ፤ በወንዝ ዳር በቅን መንገድ አስኬዳቸዋለሁ፥ በእርሱም አይሰናከሉም፤ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኵሬ ነውና። ” (ትንቢተ ኤርምያስ 31:9)

ኤፍሬም ሁለተኛው የዮሴፍ ልጅ መሆኑ ይታወቃል (ዘፍጥረት 49፡13-19)፡፡ ከዚህ ክፍል የምንረዳው የኤፍሬምን ቀድሞ መፈጠር ወይንም መወለድ ሳይሆን እግዚአብሔር ኤፍሬምን ልዩ በሆነ ዓይን እንደሚያይና ከሌሎች በላይ እጅግ በእግዚአብሔር የተወደደ መሆኑን ነው። እግዚአብሔር አምላክ ዳዊትንም ተመሳሳይ ቃል ተናግሮታል፡-

“ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት… እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፥ ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል” (መዝ. 89፡20፣ 27)፡፡

ዳዊት በውልደት የቤቱ ታናሽ እንደሆነና ሁለተኛው የእስራኤል ንጉሥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከምድር ነገሥታት ሁሉ በኩር እንደሚያደርገው ተናግሯል፡፡ ስለዚህ ቃሉ በልደት ቀዳሚነትን ብቻ ሳይሆን ሥልጣንን፣ የበላይነትን፣ ተወዳጅነትንና  ልዩ የሆነ ግንኙነትን ለማሳየት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡

በዚህ ከተግባባን፣ ቆላስይስ 1:15-16 ላይ ኢየሱስ “ከፍጥረት ሁሉ በኩር ነው” ማለት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት አይከብደንም።  ክፍሉ የሚለው “የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና…”   ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ፈጣሪ እንጂ ፍጡር አይደለም፡፡ ይህም በተከታዮቹ ነጥቦች ተረጋግጧል፡-

  1. “… ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና …”(… ἐν αὐτῷ ἐκτίσθη τὰ πάντα … ኤን አውቶ ኤክቲስቴ ታ ፓንታ) ተብሏል፡፡ ሁሉም (πάντα ፓንታ) የተፈጠሩት በእሱ ከሆነ፣ ኢየሱስ ፍጥረት ውስጥ የለም ማለት ነው። “ሁሉንም ፈጠረ” ተብሎ እራሱ ፍጡር ነው ከተባለማ እራሱንም ፈጥሯል እያልን ነው ማለት ይሆናል። ይህ ደግሞ ኢ-አመክንዮአዊ ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ በኩር የተባለው የበላይና ወራሽ መሆኑን ለማመልከት እንጂ የመጀመርያው ፍጡር መሆኑን ለማመልከት አይደለም (ሮሜ 8፡17፣ 29፣ ዕብራውያን 1፡1-3፣ ማርቆስ 12፡6-8)፡፡ ትክክለኛው ፍቺ ኢየሱስ በፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው የሁሉ የበላይ ነው የሚል ነው።
  2. ἐν (ኤን) በግሪክ ቋንቋ መስተዋድድ ስትሆን፣ ትርጉሟ “በ…፣ ከ…፣ …ጋር” የሚሉትን የሚወክል ነው። ነገር ግን ἐν ከተቀባይ ሙያ (Dative) ጋር ከመጣችና የምትገልፀው ስለ አንድ የሆነ አካል ከሆነ ትርጉሟ በሁለት ተከፍሎ ይታያል። አንደኛ፣ እየተገለፀ ያለው አካል በራሱ ሕይወት ወይም ሕልውና የሌለው ነገር (inanimate) ከሆነ፣ ይህ አካል ለተፈፀመው ድርጊት መጠቀሚያ (instrument, means) እንጂ እራሱ የድርጊቱ ፈፃሚ አይደለም። ሁለተኛው ግን እየተገለፀ ያለው አካል ሕልውና ያለው (animate) ከሆነ ለተፈፀመው ድርጊት ይህ አካል መነሻ (source) ወይም እራሱ አድራጊው ነው ማለት ነው። እንግዲህ ቆላስይስ 1:15-16  ላይ እየተገለፀ ያለው አካል ኢየሱስ ነው። የተፈፀመው ድርጊት ደግሞ “መፍጠር” ነው።  ኢየሱስ ደግሞ ሕልውና ያለው (animate) ስለሆነ በዚህ ክፍል ἐν ከተቀባይ ሙያ (Dative) ጋር ስለመጣች የአረፍተ ነገሩ ትርጉም ኢየሱስ እራሱ የድርጊቱ ፈፃሚ ወይም ፈጣሪ መሆኑን ያስረዳል።  (Jeremy Duff, New Testament Greek, p. 49)

ከላይ እንዳየነው በጥቅሱ አውድና ሰዋሰዋዊ አወቃቀር መሠረት ኢየሱስ ፍጥረትን የፈጠረ አምላክና ፈጣሪ እንጂ ፍጡር አይደለም። ከይሖዋ ምስክሮች በተኮረጀው በዚህ ስሁት ሙግት መሠረት ኢየሱስ የመጀመርያው ፍጡር ቢሆን እንኳ በአላህ አማካይነት በእናቱ ማህፀን ውስጥ እንደተፈጠረ የሚናገረው የእስልምና ትምህርት ውድቅ ስለሚሆን ሙግታቸው እስልምናን የሚያፈርስ እንጂ የሚጠቅም አይደለም፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን ከእምነታቸው ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑ መሰል ሙግቶችን መጠቀማቸው በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ ለመሆኑ ሃቀኝነት የሚል ቃል በመዝገበ ቃላታቸው ውስጥ ይኖር ይሆን? ጥቂት ዕውቀት አደገኛ መሆኑን ያልተረዱ ሙስሊም ኡስታዞች እራሳቸው በሰጡን ርዕስ እንዴት መልሰው ወጥመድ ውስጥ እንደሚገቡ ማሳያ ከሆኑ ሙግቶች መካከል አንዱ ይሄ ነው። እግዚአብሔር አምላክ ልቦና ይስጣቸው፡፡


መሲሁ ኢየሱስ