ውበት የእውነት መለኪያ ሊሆን ይችላልን? – የቁርኣን ሚዛን አመክንዮአዊ ችግሮች

ውበት የእውነት መለኪያ ሊሆን ይችላልን?

የቁርአን ሚዛን አመክንዮአዊ ችግሮች

“በባሪያችንም ላይ ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትኾኑ ከብጤው አንዲትን ምዕራፍ አምጡ፡፡ እውነተኞችም እንደኾናችሁ ከአላህ ሌላ መስካሪዎቻችሁን ጥሩ፡፡” (ቁርአን 2፡23፣ በተጨማሪም 11፡10፣ 10፡37-38፣ 17፡88)

እውነተኛ ሙስሊሞች ቁርአን መቶ በመቶ የአላህ ቃል መሆኑን ስለሚቀበሉ ምንም ዓይነት ስህተት እንደሌለበት ያምናሉ፡፡ ስለዚህ ቁርአን ራሱ በተናገረው መሠረት በሥነ ጽሑፍ የቁርአንን ያህል ውበት ያለው ጽሑፍ አልነበረም፣ የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡ ይህ እምነት በድፍን ክበባዊ ምክንዮ (Circular Reasoning) ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ቁርአንን እንደ ፈጣሪ ቃል የተቀበለ ሰው የአባባሉን እውነተኛነት የመፈተሽ ዕድል አይኖረውም፡፡ ለአማኙ ቁርአን ስህተት የሌለበት የፈጣሪ ቃል ስለሆነ እርሱን የሚመስል መጽሐፍ ወይንም ምዕራፍ የመፍጠር የትኛውም ጥረት የግድ ውድቅ መሆን አለበት፡፡ የቁርአን ደራሲ እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ በአንባቢያኑ ውስጥ የማስረፅ ፅኑ ፍላጎት ስለነበረው በተከታዩ አንቀፅ ውስጥ እንዲህ የሚል ማስፈራርያን አክሏል፡-

“(ይህንን) ባትሠሩ ፈጽሞም አትሠሩትምና ያችን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ድንጋዮች የኾነችውን እሳትተጠበቁ፤ ለከሓዲዎች ተደግሳለች፡፡” (ቁርአን 2፡24)

ቁርአን እንደ እውነተኛ ቃል የተቀበሉትን ሰዎች በማስፈራራት ስለሸበባቸውና ፍተሻ እንዲያደርጉ ስላልፈቀደላቸው ሙስሊሞች መመዘኛውን የመቀበል ምንም ዓይነት አዝማሚያ የላቸውም፤ እናም ፍልሚያው ሳይጀመር ቁርአን ድሉን ማወጁ ግድድሩን ትርጉም አልባ ያደርገዋል፡፡ ሲጀመር ይህ “የውበት ተዓምር” በአረብኛ ቋንቋ ብቻ እንደሆነ ስለተነገረ የአላህን ተዓምር በአንድ ቋንቋ ብቻ በመገደብ መለኮታዊ ልዕልናን ያንኳስሳል፡፡ በተጨማሪም የአረብኛ ቋንቋ ዕውቀትን የሚጠይቅ በመሆኑ የአረብኛ ተናጋሪ ለሆኑት የተወሰኑ የዓለማችን ሕዝቦች በማድላት ፈጣሪን አድሏዊ ያስመስላል፡፡

በዘመናት ሁሉ ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖች ቁርአንን የሚመስሉ መጻሕፍትንና ምዕራፎችን መፍጠር መቻላቸውንና የቁርአንን ሥነ ጽሑፋዊ ውበት ያን ያህል ሳቢ ሆኖ እንዳላገኙት ሲናገሩ ኖረዋል፡፡ ይህ ቁርአንን የማጣጣልና በቁርአን ያለመመሰጥ ጉዳይ በመሐመድ ዘመን በነበሩት ሰዎች ጭምር ሲነገር እንደነበር አያሌ የቁርአን ጥቅሶች ይጠቁማሉ (16:24፣ 16:101፣ 21:5፣ 25:4-6፣ 6:25፣ 8:31፣ 10:38፣ 11:13, 35፣ 16:24፣ 83፣ 27:68፣ 46:8-9, 17፣ 52:33፣ 68:15፣ 83:13፣ 6:33፣ 10:41፣ 35:4)፡፡ ሆኖም ሙስሊሞች ይህንን ጉዳይ ሲክዱና ከቁርአን ሐሳብ ጋር ተስማምተው በድርቅና ሲከራከሩ ኖረዋል፡፡ በሙስሊሞች ዳኝነት መሠረት ተግዳሮቱን ማሳካት የቻለ ሰው የለም፡፡ ዳኞቹ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ከሆኑ ደግሞ ይህ ተግዳሮት በተደጋጋሚና በስኬት ተሟልቶ ቁርአን ውድቅ ሆኗል፡፡ በቁርአን የሚያምኑ ሰዎች የቁርአን እስረኞች በመሆናቸው ምክንያት ተግዳሮቱን የመሞከር ዕድል ባይኖራቸውም ቁርአን ግድድሩን ያቀረበላቸው ወገኖች (ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች) ሞክረውት ስኬትን አስመዝግበዋል፡፡ ሙስሊሞች እነዚህን ወገኖች በዕውቀት እጦት፣ በጥላቻ ወይንም በሰይጣን የተሳሳቱ ሰዎች ናቸው በሚል ሊወቅሱና ሊከስሱ ይችላሉ፡፡ ዳሩ ግን እንዲህ ያለው ወቀሳና ክስ ሙስሊሞች የቁርአን እስረኞች መሆናቸውን ከማረጋገጥ ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡

የዚህ ግድድር መሠረታዊው ችግር ውበትን የእውነት መለኪያ አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡ ይህ በሁለት ምክንያቶች ውድቅ ነው፡፡ የመጀመርያው ቋሚ የሆነ የውበት መለኪያ አለመኖሩ ነው፡፡ ከነ አባባሉም “ውበት እንደተመልካቹ ነው”፡፡ ለአንዱ ውብ የሆነው ለሌላው አስቀያሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ባለ አምስት ድምፅ የሆነው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ለኢትዮጵያውያን ተወዳጅ ቢሆንም ለሌሎች ግን ከሰባቱ ድምፆች ሁለቱ መቀነሳቸው ውበቱን ያደበዝዝባቸዋል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የውጪ ሙዚቃዎች ሁለት ድምፆችን በመጨመራቸው ምክንያት ዜማቸው ሳቢ እንዳልሆነ ያስባሉ (ሰባትና ከዚያ በላይ ድምፆችን የሚጠቀሙ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች መኖራቸውን ሳንዘነጋ!)፡፡ ይህ የሚያመለክተን ለውበት ቋሚ መለኪያን ማስቀመጥ አስቸጋሪ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ከየዕለት ኑሯችን እንኳ ማየትና መገንዘብ እንችላለን፡፡

ሌላው ምክንያት ተግዳሮቱ ውብ የሆነ ንግግር ሁሉ እውነት ነው የሚል ቅድመ ግንዛቤን ያዘለ መሆኑ ነው፡፡ ውበት የእውነት አገልጋይ የሆነውን ያህል የሐሰትም አገልጋይ ነው፡፡ ውብ የሆነ ንግግር ሁሉ እውነት አይደለም፤ ውብ ያልሆነ ንግግር ሁሉ ደግሞ ሐሰት አይደለም፡፡ ውበት ጭራሹኑም እውነትና ሐሰትን ለመለየት ሚዛን ሆኖ መቅረብ የለበትም፡፡ ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ተከታዮቻቸውን የሚያጠምዱት በተቀመመ ንግግር መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ያልተጠረበ አልማዝ ወይንም ቅርፅ ያልያዘ ወርቅ በዐይን ሲታዩ ውበት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን አልማዙም አልማዝ፣ ወርቁም ወርቅ ነው፡፡ አንድን ንግግር እውነት ወይም ሐሰት የሚያደርገው ለጆሮ በሚጣፍጥ መንገድ መቅረብ አለመቅረቡ ሳይሆን ይዘቱ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ አጨቃጫቂ አይመስለኝም፡፡

እንዲያውም ትክክለኛ ሚዛን መሆን ያለበት አንድ ንግግር ውብ መሆን አለመሆኑ ሳይሆን ይዘቱ ከንግግር ቅንብሩ ሲፋታ እውነት ሆኖ መቆም መቻል አለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል የተናገረው፡-

“እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና። እኔም በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ፤ እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።” (1ቆሮ. 2፡1-5)

በንግግር ውበት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መልእክት ሐሰት የመሆኑ ሁኔታ ከፍተኛ ነው፡፡ ልክ ነው፤ እውነተኛ መልእክትን በተዋበ ንግግር ማቅረብ ይቻላል ነገር ግን እውነትነቱ የሚገለጠው ጆሮን ሊያምታታ ከሚችል የንግግር ውበት ሲፋታ ሃቀኛ መሆኑ ተረጋግጦና መሬት ረግጦ መቆም ሲችል ብቻ ነው፡፡ በውብ ንግግር የተጀቦነ መልእክት ፍሬ ነገሩ ሲመዘን እንደ እንፋሎት ተንኖ የሚጠፋ ከሆነ የሃቀኝነትን ሚዛን አልጠበቀምና ተቀባይነት የለውም፡፡ ብስለት ያላቸው ሰዎችና የሰለጠኑ ማሕበረሰቦች የንግግርን እውነተኛነት ሃቀኛ መልእክትን በማስተላለፍ አለማስተላለፉ እንጂ በውበቱ አይመዝኑም፡፡ ለዚህ ነው በአንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በምርጫ ቅስቀሳዎች ወቅት መሳጭ ንግግሮችን ያደረጉ ሰዎች ሳይመረጡ ቀርተው በንፅፅር ደከም ያለ የንግግር ክህሎት ያላቸው ሰዎች ድልን ሲቀዳጁ የምንታዘበው፡፡ ኋላ ቀር በሆኑት ማሕበረሰቦች መካከል ግን የንግግር ውበትና ስሜታዊነት ከፍተኛ ዋጋ አላቸው፡፡

የክርስትናና የእስልምና መልእክታት “የንግግር ውበት” የተሰኘውን ባለቀለም መነፅር አውልቀን ስንመለከታቸው እውነት ሆነው የመቆም አቅማቸው ምን ያህል ነው? መመለስ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ ይህ ነው! ሙስሊም ወገኖች ለእውነት ግድ የሚላችሁ ከሆነ “እርሱን የሚመስል ሱራ ፍጠሩ” የሚለውን የማትቀበሉትንና የማትሞክሩትን ትርጉም አልባ ተግዳሮት በመተው የመጽሐፋችሁን መልእክት በሃቀኛ ሚዛን ለመመዘን ፈቃደኞች ሁኑ፡፡

እርሱን የሚመስል አንድ ምዕራፍ

ቅዱስ ቁርአን