ሙሐመድ ቢሳሳት የሚጐዳው ማነው?
የሕያ የተባለ አንድ ሙሐመዳዊ እኛ ላቀረብናቸው የቁርኣን ግጭቶች ዝርዝር ምላሽ የመስጠቱን ኃላፊነት ወስዶ ከዐሥረኛው ተራ ቁጥር ጀምሯል፡፡ የኛን ቅደም ተከተል ከመከተል ይልቅ Answering Islam ላይ የሚገኘውን የግጭት ዝርዝር ተራ ቁጥር ለመከተል እንደወሰነም ያስረዳል፡፡ በገጹ ላይ ከ 160 በላይ ግጭቶች ስለተዘረዘሩና በያንዳንዱ ግጭት ስርም አያሌ ንዑሳን ግጭቶች ስለሚገኙ አቅሙን ተረድቶ እኛ ላቀረብናቸው አጫጭር ጥያቄዎች መልስ ቢሰጥ ያዋጣው ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ወሒድ የተባለ ሰለምቴ ነኝ ባይ እጅ እጅ በሚለው የጻጻፍ ስልቱ ተጠቅሞ ለጻፈው ጽሑፍ በከፊል መልስ መስጠታችን ይታወሳል፡፡ የወሒድ አካሄድ እንደማያዛልቅ ተረድቷል መሰል የሕያ ቁርኣንን ለመታደግ እየተጣጣረ ይገኛል፡፡ ፅናቱን ይስጥህ ብለነዋል፡፡
ወደ መልሱ ስንገባ፡- ምላሽ ለመስጠት የሞከረው ሙሐመድ ሱራ 34፡50 ላይ “ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው ብመራም ጌታዬ ወደኔ በሚያወርደው ነው” በማለት የተናገረውን በተመለከተ ነው፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ሙሐመድ “እኔ ያመንኩትን እመኑ ተከተሉኝ” እያለ መለስ ብሎ ደግሞ “ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው” ማለቱ ትክክል አይደለም የሚል ነው፡፡ አራት ነጥቦችን በማንሳት መልስ ለመስጠት ሞክሯል፡-
- የመጀመርያው ያነሳው ነጥብ ጥያቄው የተኮረጀ ነው የሚል ነው፡፡ የሕያ ስቅለትን በተመለከተ የጻፈውን “መጽሐፍ” በቀጥታ ከድረ ገፅ ላይ ገልብጦ ያሳተመ መሆኑን ስላጋለጥንበት እፍረቱን ለመሸፈን እንዲህ ያለ አፀፋዊ ክስ ማንሳቱ አያስገርምም፡፡ ሙሐመድ ቁርኣን የተባለውን መጽሐፍ ማቀናበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከቁርኣን ግጭቶች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ያልተጠየቁበት ዘመን አልነበረም፡፡ በሙሐመድ ዘመን የነበሩ ብዙ ሰዎች የሙሐመድ መገለጥ እርስ በርሱ እንደሚጣረስ ተረድተው እንደነበርና በዚህም ምክንያት አላህ (በትክክለኛ ማንነቱ ሙሐመድ) ማስተባበያ “ማውረድ” አስፈልጎት እንደነበር ከቁርኣን እንረዳለን (ሱራ 16፡101 አስባብ አን-ኑዙል ይመልከቱ)፡፡ ስለዚህ እነዚህ ጥያቄዎች ቁርኣን ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ሲጠየቁ የነበሩ በመሆናቸው እኛ በጠየቅናቸው ጥያቄዎችና ሌላ ቦታ በሚገኙት ጥያቄዎች መካከል የሚመሳሰል ነገር መኖሩ ያን ያህል ሊያስደንቀው አይገባም፡፡ ብዙ ጥያቄዎች ከኛ በፊት የተነሱ በመሆናቸው የሌሎች ወገኖች ጽሑፎች መነሻ ቢሆኑንም በራሳችን አባባል ለማስቀመጥ ሞክረናል፡፡ እኛ እንደ የሕያ የሰው ሥራ መቶ በመቶ ገልብጠን ቃል በቃል በመተርጎም “በግል ጥናት ያገኘነው” ከሚል መግለጫ ጋር በመጽሐፍ አሳትመን ለሽያጭ አላቀረብንም፡፡ በግል ጥናቶቻችን የተማርናቸውንም ሆነ ከሌሎች ሰዎች የተማርናቸውን ጉዳዮች ለወገኖች ጥቅም ስንል የማንንም የቅጂ መብት በማይነካ መንገድ በራሳችን አቀራረብ በነፃ እናስነብባለን፡፡ ምንጭ መጥቀስም ወሳኝ ሆኖ ሲገኝ ምሑራዊ ሥርዓትን በጠበቀ መንገድ እንጠቅሳለን፡፡ የሰው ሥራ መቶ በመቶ ገልብጦ፣ ቃል በቃል ተርጉሞ፣ አንድ ምንጭ እንኳ ሳይጠቅስ “በግል ጥናት ያገኘሁት ነው” የሚል መግለጫ በመግቢያው ላይ አክሎ ለሽያጭ ገበያ ላይ ያወጣ እንደ የሕያ ያለ ሰው እኛን የመተቸትና በኛ ደረጃ ቆሞ የመናገር የሞራል ብቃት የለውም፡፡ የየሕያን ድረ ገፅ የተመለከተ ሰው ልጁ ምንም ዓይነት ኦሪጅናል ሥራ እንደሌለውና ሁሉም ነገር ከሌሎች ድረ ገፆች ላይ የተኮረጀ መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ ይችላል፡፡ (“ድህረ ገፅ” ብሎ የሚጽፍ ሰው ድረ ገፅ ለመክፈት የበቃ ሆኖ ራሱን መቁጠሩ በራሱ አስገራሚ ነው፡፡) “የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” የሚለው ብሒል የሕያን ጥሩ አድርጎ ይገልፀዋል፡፡ ሁኔታው በአጠቃላይ ጥንብር ብሎ ሰክሮ ጤነኛውን ሰው “ሰካራም!” ብሎ እንደሚሳደብ ሰካራም ሰው ዓይነት ነው፡፡
- ሁለተኛ ላይ ያነሳው ነጥብ ሙሐመድን በቀጥታ እያናገሩ በሚመስል መልኩ የተቀመጡ የቁርኣን አንቀፆች ሁሌም እርሱን ብቻ የሚገልፁ እንዳልሆኑና እርሱን እንደማሳያ በማንሳት ለሁሉም ሙስሊሞች መልዕክትን የሚያስተላልፉ መሆናቸውን የሚገልፅ ነው፡፡ ለዚህም ምሳሌ ይሆነኛል በማለት የተወሰኑ የቁርኣን ጥቅሶችን ጠቅሷል፡፡ ሙሐመድን ብቻ የተመለከቱ ጥቅሶች እንዳሉም በመግለፅ የተወሰኑትን ከቁርኣን አስነብቦናል፡፡ እኛ ጥያቄ ያነሳንበት ጥቅስ፣ ማለትም ሱራ 34፡50 ሙሐመድን የተመለከተ መሆኑን በማመን ከዚያ አንጻር ምላሽ የሰጠ በመሆኑ እዚህ ሐተታ ውስጥ መግባቱ ምን ፋይዳ እንዳለው ግልፅ አይደለም፡፡ እዲህ ሲል ትችቱን ይሰነዝራል፡- “እንደ ጠያቂው እሳቤ መሠረት ነብዩን ጠቅሶ የሚገለፅ ቃል ሁሉ እሳቸውን ብቻ የሚመለከት ነው ማለት ነው። ይህ ለቁርኣን ባይተዋር የሆነ ሰው የሚፈጽመው ስህተት ነው፡፡” በኛ ጥያቄ ውስጥ እንደዚህ ያልንበትን ቦታ ወይንም እንዲህ ያለ እሳቤ ያንፀባረቅንበትን ነጥብ እንዲያሳየን እንጠይቀዋለን፡፡ እርሱ ራሱ ጥቅሱ ሙሐመድን የተመለከተ መሆኑን አምኖ ተቀብሎ ምላሹን ከዚያ አንፃር እስካዘጋጀ ድረስ ይህንን ነጥብ ማንሳቱም ሆነ በኛ ላይ ትችትን መሰንዘሩ የአንባቢን ሐሳብ ከመበተን የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ የተጠቀማት አካሄድ የተለመደች የሙስሊም ሰባኪያን ማወናበጃ ናት፡፡
- በሦስተኛ ደረጃ እንዲህ የሚል ምላሽ ይሰጣል፡- “አንቀፁ የሚያወራው ስለመለኮታዊ ራዕይ ወይንም ስለ አስተምህሮ መዛነፍ ሳይሆን እንደ ሰው በነበራቸው የግል ህይወት ዙሪያ ስለሚፈጠሩ ስህተቶች ነው። አንቀጹ “ብሳሳት” ብሎ የሚገልፀው የሳቸውን ሰብአዊ ባህሪይ ነው። ነብዩ መለኮታዊ ራዕይ የሚወርድላቸው ነብይ ብቻ ሳይሆኑ እንደ ማንኛውም ሰው የግል ህይወት ያላቸው ሰውም ነበሩ። እንደሚታወቀው ደግሞ ነብያት ሰውኛ ባህሪያትንም የተጎናፀፉ ግለሰቦች እንጅ ከስህተት የተጠበቁ መላዕክት አይደሉም። በዚህም ሳቢያ በዕለትተዕለት ህይወታቸው ዙሪያ እንደማንኛውም ሰው ግላዊ ስህተቶችን ሊፈጽሙ ይችላሉ። ያ ስህተት ከሀይማኖታዊ እይታ አንፃር ሳይሆን ከግላዊ ስህተት አኳያ ብቻ ሊታይ እንደሚገባ ቁርኣን በዚህ ክፍሉ ይነግረናል። ከኢማም ኢብን ከሲር ጀምረን የተለያዩ የተፍሲር ሊቃውንትን ስራ ብንመለከት ከዚህ ውጭ የተለየ ፍችን ሰጥተው አናገኝም።”
የሕያ ከተናገረው በተጻራሪ የተለያዩ ተፍሲሮችን ስንመለከት ጥቅሱ ስለ መለኮታዊ መገለጥ እየተናገረ ስለመሆኑ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ያህል ተፍሲር ኢብን አባስ እንዲህ ይላል፡- (Say) to them, O Muhammad: (If I err) from the Truth and guidance, (I err only to my own loss) he says: the punishment of that is against my soul, (and if I am rightly guided) to the Truth and guidance (it is because of that which my Lord hath revealed unto me) that I am guided. … https://www.altafsir.com/Tafasir.asp?tMadhNo=0&tTafsirNo=73&tSoraNo=34&tAyahNo=50&tDisplay=yes&UserProfile=0&LanguageId=2
በኢብን አባስ ማብራርያ መሠረት ጥቅሱ እያወራ ያለው ነፍስን ለጥፋት ስለሚዳርግ ስህተትና ነፍስን ስለሚያድን ምሪት ነው፡፡ ሙሐመድ እያለ ያለው ከመለኮታዊ ምሪት ስቶ ነፍሱን ለጥፋት በሚዳርግ ስህተት ውስጥ ቢገኝ ጥፋቱ ከእርሱ ውጪ ሌላ ማንንም ሰው ሊጎዳ እንደማይችል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ሙሐመድ ራሱን ለሰው ልጆች ሁሉ ምርጡና ወደር የለሽ ምሳሌ አድርጎ ስላቀረበ ነፍስን በሚያጠፋ ስህተት ውስጥ ቢገኝ እርሱን የተከተለ ሰው ሁሉ ለጥፋት መዳረጉ የማይቀር ነው፡፡
በየሕያ መሠረት ሙሐመድ እያወራ ያለው ነፍስን ለጥፋት ሊዳርጉ ስለማይችሉ ከሰው ልጅ የዕውቀት ውሱንነቶች የተነሳ ስለሚያጋጥሙ ተራ ስህተቶች ነው፡፡ በተነጻጻሪነትም ያቀረበው ጌታችን ኢየሱስ ከበለሲቱ ፍሬ ፍለጋ ሄዶ እንዳላገኘባት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ነው (ማርቆስ 11:13)፡፡ የታሪኩን ትክክለኛ ትርጉምና የሚሰጠንን ጥልቅ መንፈሳዊ ትምሕርት በተመለከተ ከዚህ ቀደም በድረ ገፃችን ላይ አስፍረናል፤ ስለዚህ ለየሕያ አጀንዳን የማስለወጥ አካሄድ ቦታ መስጠት አንፈልግም፡፡ ሐሳቡ ሲጠቃለል ከዕውቀት ማነስ የተነሳ የሚፈጠሩ ስህተቶች ከመለኮታዊ ምሪት ጋር የሚገናኙ ወይንም ከኃጢአት የሚቆጠሩ ስህተቶች አይደሉም፤ ከሰብዓዊ ውሱንነት የተነሳ የሚፈጠሩ ከግለሰቡ ያለፈ ጉዳት የማያስከትሉ ተራ ስህተቶች ናቸው የሚል ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ስህተቶች ኃጢአት እንዳልሆኑና የአንድን ነቢይ እውነተኛነትም ጥርጣሬ እንደማይጥሉ ያስማማናል፡፡ ነገር ግን ሙሐመድ እያለ ያለው “መሳሳት” ይህ ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ “አይደለም” የሚል ነው፡፡ ይህንን አስመልክቶ የአል-ጃለላይን ተፍሲር እንዲህ ይላል፡- Say ‘If I go astray from the truth I will be going astray only to my own loss that is to say the sin of my going astray shall be held against me… https://www.altafsir.com/Tafasir.asp?tMadhNo=0&tTafsirNo=74&tSoraNo=34&tAyahNo=50&tDisplay=yes&UserProfile=0&LanguageId=2
በሁለቱ ጃለሎች ተፍሲር መሠረት ሙሐመድ “ብሳሳት” ያለው ኃጢአትን ሊያስከትል የሚችል ከመለኮታዊ ምሪት መሳትን የተመለከተ ስህተት እንጂ የሕያ እንዳለው በዕውቀት ውሱንነት ሳብያ ዕለት ዕለት የሚያጋጥሙ ጥቃቅን ግላዊ ስህተቶች አይደሉም፡፡ የሕያ ተፍሲሮችን ተመልክቶ ሳይሆን በመሰለኝና በደሳለኝ እያወራ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ከታወቁት ተፍሲሮች መካከል አንዱም እንኳ ሙሐመድ እያለ ያለው “ስህተት” ጥፋትን የማያስከትል ተራ የየዕለት ስህተት እንደሆነ የሚገልፅ አላየንም፡፡
ስናጠቃልል ሙስሊሞች ሙሐመድን ከትልልቅ ጉዳዮች እስከ ጥቃቅን ጉዳዮች ሊመስሉት ስለሚሞክሩ (አለባበስ፣ ጢም አቆራረጥ፣ ሽንትቤት አገባብ፣ አስተጣጠብ፣ አተኛኘት፣ ጥርስ አፋፋቅ፣ ወዘተ.) ጥቃቅን በተባሉት ጉዳዮች እንኳ ስህተት ሠርቶ ቢገኝ ራሱን ብቻ ሳይሆን የተከተሉትን ሰዎች በሞላ ያሳስታል፡፡ ሙሐመድ ከተሳሳተ ስህተቱና ጉዳቱ የመላው ሕዝበ ሙስሊም እንጂ የሙሐመድ ብቻ አይደለም፤ ስለዚህ “ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው…” ብሎ ማለቱ የተሳሳተ ንግግር ነው፡፡ ፈጣሪ እንዲህ ያለ ኢ-አመክንዮአዊ ንግግር ስለማይናገር ቁርኣን የሙሐመድና የተባባሪዎቹ ፈጠራ እንጂ እውነተኛ የአምላክ ቃል ሊሆን አይችልም፡፡ ለየሕያና ለመሰሎቹ ያለን መልእክት እስልምናን በጭፍን ይከተሉታል እንጂ አይሟገቱለትም፤ ስለዚህ አሳማኝ መልስ ማምጣት ላትችሉ ነገር በከንቱ ዘመናችሁን አትፍጁ፤ ራሳችሁንም ለትዝብት አትዳርጉ፡፡
———
በመጨረሻም፡- ኩረጃ ሱሱ የሆነው የሕያ ይህንን “መልስ” ከሞላ ጎደል የኮረጀው Answering Christianity ከተባለ ቅራቅንቦ ድረ ገፅ ላይ ነው፡፡ እባክህን “አይደለም” በለኝና እንደተለመደው ላጋልጥህ፡፡
ለተመሳሳይ ጥያቄ የተሰጠ ሌላ ምላሽ ለማንበብ እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ