የቁርኣን ግጭቶች – መልዕክተኞች የተላኩባቸው ከተሞች በሙሉ ክደዋል ወይንስ ያልካዱ አሉ?

15. መልዕክተኞች የተላኩባቸው ከተሞች በሙሉ ክደዋል ወይንስ ያልካዱ አሉ?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ክደዋል:-

34፥34 “በከተማም አስፈራሪን አልላክንም፣ ነዋሪዎችዋ እኛ በዚያ በርሱ በተላካችሁበት ከሐዲዎች ነን ያሉ ቢሆኑ እንጂ።”

ያልካዱ አሉ:-

10፥98 “ያመነች እና እምነትዋ የጠቀማት ከተማ ለምን አልኖረችም? ግን የዩኑስ ሕዝቦች ባመኑ ጊዜ በቅርቢቱ ሕይወት የውርደትን ቅጣት ከእነሱ ላይ አነሳንላቸው፡፡ እስከ ጊዜም ድረስ አጣቀምናቸው፡፡”

መልስ

34፥34 በከተማም አስጠንቃቂን አልላክንም፡፡ ነዋሪዎችዋ “«እኛ በዚያ በእርሱ በተላካችሁበት ከሓዲዎች ነን» ያሉ ቢኾኑ እንጂ፡፡

እዚህ አንቀጽ ላይ “ኢላ” إِلَّا የሚለው አፍራሽ ቃል “ኢስቲስናዕ” اِسْتِثْنَاء‏ ማለትም “ግድባዊት”Exceptional” ሆኖ የመጣ ነው፥ በአንጻራዊና በፍጹማዊ አገባብ ይመጣል። በፍጹማዊ ግድብነት“Absolute Exception” ሲመጣ “ሙጥለቅ” مطلق ይባላል፤ በአንጻራዊ ግድብነት“Relative Exception” ሲመጣ ቀሪብ” قريب ይባላል።

እስኪ ጥቅሱን ደግመን እናንብበው፡- በከተማም አስፈራሪን አልላክንም፣ ነዋሪዎችዋ እኛ በዚያ በርሱ በተላካችሁበት ከሐዲዎች ነን ያሉ ቢሆኑ እንጂ።”

ወደ ከተማ ተልኮ ተቃውሞ ያልገጠመው መልእክተኛ የለም ማለት ነው፡፡ ይህ “ግድባዊ” የሚሆነው በምን መንገድ ነው? እየተናገረ ያለው እኮ ስለ ሁሉም ከተሞችና ስለ ሁሉም መልእክተኞች ነው፡፡

ይህንን ለመረዳት አንድ ጥቅስ ማየት ይበቃል፦

5፥117 በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል፦ “ጌታዬን እና ጌታችሁን አላህን አምልኩ” ማለትን እንጂ ለእነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡

“ኢላ” إِلَّا እዚህ ዐውድ ላይ አንጻራዊ ሆኖ መጥቷል። ዒሣ ለእነርሱ፦ “ጌታዬን እና ጌታችሁን አላህን አምልኩ” ማለትን እንጂ ሌላ አላለምን? እረ ብሏል፦

3፥50 «ከተውራትም ከእኔ በፊት ያለውን ያረጋገጥሁ ስኾን የዚያንም በእናንተ ላይ እርም የተደረገውን ከፊል ለእናንተ እፈቅድ ዘንድ መጣኋችሁ፥ ከጌታችሁም በኾነ ታምር መጣሁዋችሁ፡፡ አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡»

ታዲያ ለምን “ጌታዬን እና ጌታችሁን አላህን አምልኩ” ማለት ብቻ ሆነ ስንል ከዐውዱ አንጻር ነው። ዐውዱ ላይ፦ “እኔን እና እናቴን ከአላህ ሌላ አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን?  ለተባለው ነው፦

5፥116 አላህም፡- «የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! አንተ ለሰዎቹ፡- እኔን እና እናቴን ከአላህ ሌላ አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን?» በሚለው ጊዜ አስታውስ፡፡

ይህ ኢስቲስናዕ በተናጥል ቀሪብ  እንጂ በጥቅሉ ሙጥለቅን አያመለክትም ከተባለ እንግዲያውስ በከተማም አስጠንቃቂ ተልኮላቸው አብዛኛውን  ከጌታዋ ትዕዛዝ ያመጸች እና መጥፎንም ቅጣት የተቀጣች ስለሆነች ነው፦

65፥8 “ከከተማም ከጌታዋ ትዕዛዝ ከመልክተኞቹም ያመጸች፣ ብርቱንም ቁጥጥር የተቆጣጠርናት እና መጥፎንም ቅጣት የቀጣናት ብዙ ናት”፡፡

22፥48 “ከከተማ እርሷ በዳይ ሆና ለእርሷ ጊዜ የሰጠኋትና ከዚያም የያዝኳት ብዙ ናት”፡፡ መመለሻም ወደ እኔ ብቻ ነው፡፡

21፥11 “በዳይም ከነበረች ከተማ ያጠፋናትና ከኋላዋም ሌሎችን ሕዝቦች ያስገኘነው ብዙ ናት”፡፡

“ብዙ ናት” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት። አብዛኛውን ስለካዱ “ኢላ” إِلَّا የሚለው አፍራሽ ቃል በአንጻራዊነት መጥቷል እንጂ ያመኑ በፍጹም ጭራሽ አልነበሩም የሚለውን አያሲዝም። ምክንያቱም የዩኑስ ሕዝብ አምነዋልና፦

10፥98 ያመነችና እምነትዋ የጠቀማት ከተማ ለምን አልኖረችም? ግን የዩኑስ ሕዝብ ባመኑ ጊዜ በቅርቢቱ ሕይወት የውርደትን ቅጣት ከእነርሱ ላይ አነሳንላቸው”፡፡ እስከ ጊዜም ድረስ አጣቀምናቸው፡፡

እስካሁን ያየናቸው አብዛኞቹ መልሶችህ ግጭትን በግጭት ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ናቸው፡፡ በቁርኣን ውስጥ ላለ አንድ ግጭት ያንን የሚመስል ሌላ ግጭት በመጥቀስ መልስ ሰጥቻለሁ ትለናለህ፡፡ አንድ ሰው በአንዱ ቦታ ላይ “እንዲህ እንጂ ሌላ ነገር አልተናገርኩም” ቢልና “ተናገርኩ” ካለው ውጪ ሌላ ነገር መናገሩ ከተረጋገጠ “አልተናገርኩም” ማለቱ ስህተት ነው ማለት ነው፡፡ ለማንኛውም ንግግርን በተመለከተ “እንዲህ እንጂ ሌላ ነገር አልተናገርኩም” ብሎ ማለት ሊያስኬድ ይችላል እንበል፤ ነገር ግን ስለ መልእክተኞችና ስለ ከተማ ነዋሪዎች የተነገረው ታሪካዊ ክስተትን የሚጠቅስ ነው፡፡ አንደኛው ጥቅስ መልእክተኞች ተቃውሞን ያላስተናገዱበት አንድም ከተማ እንደሌለ የሚናገር ሲሆን ሌላኛው ግን የነነዌ ታሪክ የተለየ መሆኑን ይነግረናል፡፡ እዚህ ጋ “ግድባዊ” “አንጻራዊ” የሚሉ ማስተባበያዎች አይሠሩም፡፡ ግድባዊ ከሆነ በአውዱ ውስጥ መታየት ያስፈልገዋል፤ ንፅፅር ነው ከተባለም ከምን ጋር እንደተነጻጸረ ግልፅ መሆን ያስፈልገዋል፡፡ ዝም ብሎ በባዶ ሜዳ “ይህ ግድባዊ ነው ይህ ንፅፅራዊ ነው” ማለት ትርጉም አይሰጥም፡፡

ሲቀጥል “ከተማ” እና “ሕዝብ” ሁለት የተለያዩ ነጥቦች ናቸው። ከተማ ቋሚ እና ሠፊ ሕዝብ የሰፈረበት ቦታ ስትሆን ይህን ቦታ ለየት የሚያደርገው ራሱን የቻለ አስተዳደር ያለው የሚመራው በወጣ ሕግ ነው። ሕዝብ ደግሞ የሰውን የብዙ ቁጥር ማሳያ ነው። በአንድ ከተማ ብዙ የተለያዩ አሕዛብ(ሕዝቦች) ይኖራሉ። እውነት ነው “ያመነችና እምነትዋ የጠቀማት ከተማ አልኖረችም” ግን ከከተማ በተለየ መልኩ የዩኑስ ሕዝብ ባመኑ ጊዜ በቅርቢቱ ሕይወት የውርደትን ቅጣት ከእነርሱ ላይ አላህ አነሳላቸው።

“ከተማ” ሲባል እኮ ሕዝቡን እንጂ መንገዱንና ሕንፃውን አይደለም፡፡ ስለዚህ አንዲት ከተማ አምናለች አላመነችም የምንለው ሕዝቡ አምኗል አላመነም ለማለት እንጂ ሌላ የተለየ ትርጉም የለውም፡፡ በዮናስ ዘመን ነነዌ ታላቅ ከተማ እንደነበረች ስለሚታወቅ ዮናስ የሰበከው ለከተማይቱ ሕዝብ እንጂ ቋሚ አድራሻ ለሌለው ሕዝብ አልነበረም፡፡ ይህንን እውነታ አለማገናዘብህ ለጥያቄው መልስ ማጣትህን ያመለክታል፡፡ ቁርኣን በአንዱ ቦታ ላይ ከከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ተቃውሞን ያላስተናገደ ነቢይ እንደሌለና ተቃውሞን ያላሰማ ሕዝብ አለመኖሩን የነገረን ሲሆን የመጀመርያ ቃሉን በመዘንጋት ዮናስ ተቀባይነትን ማግኘቱንና የከተማዋ ነዋሪዎችም ጥሪውን ተቀብለው መትረፋቸውን ይነግረናል፡፡ ይህ ግልፅ ግጭት ነውአንተም የቃላት ጫወታ በመጫወት ለማምታታት ከመሞከር በዘለለ መልስ መስጠት ተስኖሃል፡፡

የቁርኣን ግጭቶች