ከሃዲዎች በፍርድ ቀን ይናገራሉ ወይንስ አይናገሩም?
ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡
ይናገራሉ፦
35፥37 እነርሱም በርሷ ውስጥ እርዳታን በመፈለግ በኀይል ይጮሃሉ፡፡ «ጌታችን ሆይ! ከእዚያ እንሠራው ከነበርነው ሌላ በጎ ሥራን እንሠራ ዘንድ አውጣን» ይላሉ፡፡ «በእርሱ ውስጥ ያስታወሰ ሰው የሚገሰጽበትን ዕድሜ አላቆየናችሁምን? አስጠንቃቂውም መጥቶላችኋል አስተባብላችኋልም፡፡ ስለዚህ ቅመሱ፡፡ ለበደለኞችም ምንም ረዳት የላቸውም» ይባላሉ፡፡
አይናገሩም፦
16:84 ከየሕዝቡም ሁሉ መስካሪን የምንቀሰቅስበትን ቀን አስታውስ፤ ከዚያም ለነዚያ ለካዱት ንግግር አይፈቀድላቸውም፤ እነሱም በወቀሳ አይታለፉም።
መልስ ለመስጠት እስከተነሳህ ድረስ የጠያቂዎችህን ሙግት መቆራረጥ ለምን እንዳስፈለገህ አላውቅም፡፡ ምናልባት የተሟላውን ሙግት ማስፈር ለመልስ እንዳይቸግርህ አስበህ ይሆናል፡፡ ለማንኛውም በድረገፃችን ላይ የሚገኘው ሙግት የሚከተለው ነው፡-
ከሃዲዎች በፍርድ ቀን ይናገራሉ ወይንስ አይናገሩም?
ይናገራሉ:- 23:105-109 «አንቀጾቼ በእናንተ ላይ የሚነበቡላችሁና በእነርሱ የምታስተባብሉ አልነበራችሁምን» (ይባላሉ)፡፡ ይላሉ «ጌታችን ሆይ! በእኛ ላይ መናጢነታችን አሸነፈችን፡፡ ጠማማዎችም ሕዝቦች ነበርን፡፡ «ጌታችን ሆይ! ከእርሷ አውጣን፡፡ (ወደ ክህደት) ብንመለስም እኛ በደዮች ነን፡፡» (አላህም) «ወራዶች ኾናችሁ በውስጥዋ እርጉ፡፡ አታናግሩኝም» ይላቸዋል፡፡ እነሆ ከባሮቼ «ጌታችን ሆይ! አምነናልና ማረን፡፡ እዘንልንም አንተም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነህ» የሚሉ ክፍሎች ነበሩ፡፡
16:86 “እነዚያም ያጋሩት የሚያጋሩዋቸውን ባዩ ጊዜ፣ ጌታችን ሆይ እነዚህ ከአንተ ሌላ እንግ ገዛቸው የነበርነው ተጋሪዎቻችን ናቸው ይላሉ፤ (አማልክቶቹ) እናንተ በእርግጥ ውሸታሞች ናችሁ፣ የማለትንም ቃል ወደነሱ ይጥላሉ።”
20:102-104 “በቀንዱ በሚነፋ ቀን (ሸክማቸው ከፋ)፤ ከሃዲዎችንም በዚያ ቀን (ዓይኖቻቸው) ሰማያዊዎች ሆነው እንሰበስባቸዋለን። ዐሥርን (ቀን) እንጂ አልቆያችሁም በመባባል በመካከላቸው ይንሾካሸካሉ። በሐሳብ ቀጥተኛቸው፣ አንድን ቀን እንጅ አልቆያችሁም በሚል ጊዜ የሚሉትን ነገር እኛ፣ ዐዋቂዎች ነን።”
አይናገሩም:- 17:97 “አላህም ያቀናው ሰው ቅኑ እርሱ ብቻ ነው፤ ያጠመማቸውም ሰዎች ከርሱ ሌላ ለነርሱ ፈጽሞ ረዳት አታገኝላቸውም፤ በትንሣኤ ቀንም ዕውሮች፣ ዲዳዎች፣ ደንቆሮዎችም ሆነው በፊቶቻቸው ላይ (እየተጎተቱ) እንሰበስባቸዋለን፤ መኖሪያቸው ገሀነም ናት፤ (ነዲድዋ) በደከመች ቁጥር፣ መንቀልቀልን እንጨምርባቸዋለን።”
16:84 “ከየሕዝቡም ሁሉ መስካሪን የምንቀሰቅስበትን ቀን (አስታውስ)፤ ከዚያም ለነዚያ ለካዱት (ንግግር) አይፈቀድላቸውም፤ እነሱም በወቀሳ አይታለፉም።”
77:28-36 “ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው። ወደዚያ በርሱ ታስተባብሉ ወደ ነበራችሁት (ቅጣት) አዝግሙ። ባለ ሦስት ቅርንጫፎች፣ ወደ ሆነው ጥላ አዝግሙ፤ (ይባላሉ) አጠላይ ያልኾነ፤ ከእሳቱም ላንቃ የማያድን ወደ ሆነው፣ (አዝግሙ)። እርሷ እንደ ታላላቅ ሕንጻ የሆኑን ቃንቄዎች ትወርውራለች። (ቃንቄውም) ልክ ዳለቻዎች ግመሎችን ይመስላል። ለአስተባባዮች በዚያን ቀን ወዮላቸው። ይህ የማይናገሩበት ቀን ነው። ይቅርታም ይጠይቁ ዘንድ ለነርሱ አይፈቅድላቸውም።”
በመጀመርያዎቹ ጥቅሶች መሠረት ከሃዲዎች በፍርድ ቀን ከሚያጋሯቸው አማልክት ጋር, ከአላህ ጋር እንዲሁም እርስ በዕርሳቸው የሚነጋገሩ ሲሆን ከዝያ ቀጥለው በተቀመጡ ጥቅሶች መሰረት ግን እንደማይናገሩ ተነግሯል፡፡ ታድያ የቱ ነው ትክክል?
እስኪ መልስህን እንስማ፡፡
መልስ
35፥37 እነርሱም በርሷ ውስጥ እርዳታን በመፈለግ በኀይል ይጮሃሉ፡፡ «ጌታችን ሆይ! ከእዚያ እንሠራው ከነበርነው ሌላ በጎ ሥራን እንሠራ ዘንድ አውጣን» ይላሉ፡፡ «በእርሱ ውስጥ ያስታወሰ ሰው የሚገሰጽበትን ዕድሜ አላቆየናችሁምን? አስጠንቃቂውም መጥቶላችኋል አስተባብላችኋልም፡፡ ስለዚህ ቅመሱ፡፡ ለበደለኞችም ምንም ረዳት የላቸውም» ይባላሉ፡፡
ከሃድያን በፍርዱ ቀን፦ “ጌታችን ሆይ! ከእዚያ እንሠራው ከነበርነው ሌላ በጎ ሥራን እንሠራ ዘንድ አውጣን” ይላሉ። እዚህ ጥቅስ ላይ ካፊሮች በአፋቸው ይናገራሉ የሚል ጥቅስ የለውም። ታዲያ በአንደበታቸው ካልተነጋገሩ በምናቸው ነበር የሚናገሩት? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው። አላህ ካፊሮችን አፎቻቸውን ዘግቶ የሚያናግራቸው በእግሮቻቸው፣ በቆዳዎቻቸው፣ በጆሮዎቻቸው፣ በዓይኖቻቸውና በእጆቻቸው ያናግራቸዋል፣ እርስ በእርሳቸውም በዚህ ሁኔታ ይነጋገራሉ፦
36፥65 ዛሬ በአፎቻቸው ላይ እናትምና እጆቻቸው ያነጋግሩናል፡፡ እግሮቻቸውም ይሠሩት በነበሩት ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡
41፥20 “በመጧትም ጊዜ ጆሮዎቻቸው፣ ዓይኖቻቸውና ቆዳዎቻቸውም ይሠሩት በነበሩት ነገር በእነርሱ ላይ ይመሰክሩባቸዋል”፡፡
41፥21 “ለቆዳዎቻቸውም «በእኛ ላይ ለምን መሰከራችሁብን?» ይላሉ፡፡ «ያ አንዳቹን ነገር ሁሉ ያናገረው አላህ አናገረን፡፡ እርሱም በመጀመሪያ ጊዜ ፈጠራችሁ፡፡ ወደእርሱም ትመለሳላችሁ» ይሏቸዋል”፡፡
ሱራ 20፡102-104 ላይ በሹክሹክታ እንደሚነጋገሩ ይናገራል፡፡ በእጅ፣ በእግርና በቆዳ የሚደረግ “የሹክሹክታ ንግግር” ምን ዓይነት እንደሆነ ልታስረዳን ትችላለህ? ሹክሹክታ ከአፍ ለሚወጣ ድምፅ ነው፡፡ ጥቅሱ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው ቃል በአንደበት የሚደረገውን ንግግር የሚገልፅ ሆኖ ሳለ የእጅ፣ የእግር፣ የአይን፣ የቆዳ፣ ወዘተ. ካደረግነው ቃላት ትርጉም የላቸውም ማለት ነው፡፡ ሱራ 36፡64 ከሃዲያን እጆቻቸውና እግሮቻቸው ጥፋታቸውን በመመስከር ለአላህ መልስ እንደሚሰጡ እንጂ ከቢጤዎቻቸው ጋር ለመነጋገርያነት እንደሚያገለግሉ አይናገርም፡፡ ከከሃዲ ጓዶቻቸው ጋር በዚህ ሁኔታ ስለመነጋገራቸው ማስረጃ ማምጣት ግድ ሊሆንብህ ነው፡፡
ሱራ 77፡34-36 “ለአስተባባዮች በዚያን ቀን ወዮላቸው። የማይናገሩበት ቀን ነው” ይላል፡፡ በአንደበታቸውም ሆነ በሌላ የሰውነት ክፍላቸው ከተናገሩ ይህ ጥቅስ ተቃርኖ አይፈጥርምን? በጥቅሉ “አይናገሩም” ብሎ ከዘጋ በኋላ ሲናገሩ ይታያሉና፡፡ በምንም ይናገሩ በምን “አይናገሩም” ከተባለ አይናገሩም ነው፡፡ ግን ደግሞ ሲናገሩ ይታያሉ፡፡
ሱራ 17:97 እንዲህ ይላል፡- “በትንሣኤ ቀንም ዕውሮች፣ ዲዳዎች፣ ደንቆሮዎችም ሆነው በፊቶቻቸው ላይ (እየተጎተቱ) እንሰበስባቸዋለን፡፡”
አንተ እንዳልከው በአንደበታቸው አይነጋገሩም እንበል፡፡ ነገር ግን ዕውሮች ከሆኑ በሰውነት ክፍሎቻቸው የሚፈጥሯቸውን ምልክቶች በምን አይተው ነው እርስ በርሳቸው የሚነጋገሩት? የሰውነት ክፍሎቻቸው ምልክት ሳይሆን ድምፅ እንደሚያሰሙ ትነግረኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጥቅሱ እኮ ደንቆሮዎች እንደሚሆኑም ነው የሚናገረው፡፡ ታዲያ በምናቸው ሊደማመጡ ነው? እነዚህ ሰዎች ዕውሮች፣ ዲዳዎችና ደንቆሮዎች ከሆኑ መናገር መቻላቸውም ሆነ መስማት መቻላቸው መነገሩ ተቃርኖ ነው፡፡ ዓይን፣ አንደበትና ጆሮ እንደሌላቸው ቢነገር ኖሮ ልዕለ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ማየት፣ መናገርም ሆነ መስማት እንሚችሉ ልናስብ እንችላለን፡፡ ነገር ግን እንደርሱ አይደለም የተባለው፡፡ እነዚህ ሦስቱ ክህሎቶች እንደሚጎድሏቸው ነው የተነገረው፡፡ ማየት፣ መናገርም ሆነ መስማት የማይችሉ ፍጡራን ከሆኑ፤ ማየት፣ መናገርና መስማት መቻላቸውን የሚገልፁ ጥቅሶች ስህተት ናቸው፡፡ እነዚህን ሦስቱን ተግባራት የሚያከናውኑበት መንገድ ለውጥ አያመጣም፡፡
ከሃድያን በፍርዱ ቀን ይቅርታ መጠየቅ አይፈቀድላቸው። የይቅርታ ንግግር አይፈቀድላቸውም፦
77፥34 ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡
77፥35 “ይህ የማይናገሩበት ቀን ነው”፡፡
77፥36 ይቅርታም ይጠይቁ ዘንድ ለእነርሱ አይፈቀድላቸውም”፡፡
ዐውደ-ንባቡን ስንመለከት አስተባባዮች የማይናገሩት ይቅርታ መጠየቅን ነው። ለእነዚያ ለአስተባበሉት ከሃድያን የይቅርታ ንግግር አይፈቀድላቸውም። እነርሱ፦ “ጌታችን ሆይ! ከእርሷ አውጣን፡፡ ወደ ክህደት ብንመለስም እኛ በዳች ነን” ይላሉ፥ አላህም፦ “ወራዶች ኾናችሁ በውስጥዋ እርጉ፡፡ አታናግሩኝም” ይላቸዋል፦
16፥84 ከየሕዝቡም ሁሉ መስካሪን የምንቀሰቅስበትን ቀን አስታውስ፡፡ “ከዚያም ለእነዚያ ለካዱት ንግግር አይፈቀድላቸውም”፡፡ እነርሱም በወቀሳ አይታለፉም፡፡
23፥106 “ይላሉ «ጌታችን ሆይ! በእኛ ላይ መናጢነታችን አሸነፈችን፡፡ ጠማማዎችም ሕዝቦች ነበርን”፡፡
23፥108 አላህም «ወራዶች ኾናችሁ በውስጥዋ እርጉ፡፡ አታናግሩኝም» ይላቸዋል”፡፡
ይቅርታ መጠየቅ እንደማይፈቀድላቸው ከነገርከን በኋላ ሱራ 23፡106 ላይ ይቅርታ ሲጠይቁ የሚታይበትን ጥቅስ መጥቀስህ አስገራሚ ነው፡፡ ቅጥፈትህ እንዳይታወቅ ቆርጠህ ብትጠቅሰውም የሰዎቹ ሙሉ የፀፀት ቃል እንዲህ የሚል ነው፡- «ጌታችን ሆይ! በእኛ ላይ መናጢነታችን አሸነፈችን፡፡ ጠማማዎችም ሕዝቦች ነበርን፡፡ «ጌታችን ሆይ! ከእርሷ አውጣን፡፡ (ወደ ክህደት) ብንመለስም እኛ በደዮች ነን፡፡» (ሱራ 23:105-109)
እነዚህ ሰዎች ጥፋታቸውን አምነዋል፣ አምላካቸው ከፍርዱ እንዲያድናቸው ለምነውታል፣ ዳግመኛ ጥፋታቸውን እንደማይደግሙ ቃል ገብተዋል፡፡ ከዚህ በላይ ይቅርታ መጠየቅ የት አለ? ስለዚህ ሱራ 77፡36 “ይቅርታም ይጠይቁ ዘንድ ለእነርሱ አይፈቀድላቸውም” ከሚለው ጋር ግጭት ፈጠረ ማለት ነው፡፡ የቱ ነው ትክክል? እስከ አሁን ድረስ ግጭት ስትፈጥር እንጂ ግጭት ስትፈታ አላየንህም፡፡