አላህ የሺርክ ኃጢአትን ይቅር ይላል ወይስ አይልም?
ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡
ይቅር ይላል፡-
ሱራ 4፥153 ከዚያም ታምራቶች፣ ከመጡዋቸው በኋላ ወይፈኑን አምላክ አድርገው ያዙ፤ ከዚያም ይቅር አልን። ሙሳንም ግልጽ ስልጣንን ሰጠነው።”
ይቅር አይልም፡-
ሱራ 4፥48 “አላህ በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም፤ ከዚህ ሌላ ያለውንም ኀጢአት ለሚሻው ሰው ይምራል። በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኀጢያት በእርግጥ ቀጠፈ።”
መልስ
አንድ ሰው በዱኒያ እያለ ማንኛውንም ኀጢያት ሰርቶ ነገር ግን በተውበት ወደ አላህ ቢመለስ ይቅር ይባላል፦
39፥53 በላቸው «እናንተ በነፍሶቻችሁ ላይ ድንበር ያለፋችሁ ባሮቼ ሆይ! ከአላህ እዝነት ተስፋ አትቁረጡ፡፡ “አላህ ኃጢኣቶችን በሙሉ ይምራልና፡፡ እነሆ እርሱ መሓሪው አዛኙ ነውና”፡፡
39፥54 «ቅጣቱም ወደ እናንተ ከመምጣቱ እና ከዚያም የማትረዱ ከመኾናችሁ በፊት ወደ ጌታችሁ በመጸጸት ተመለሱ”፡፡ ለእርሱም ታዘዙ፡፡
“ጀሚዓ” جَمِيعًا ማለት “በሙሉ” ማለት ነው። በሞት አሊያም በትንሳኤ ቀን ቅጣቱ ከመምጣቱ በፊት ወደ ጌታችን በንስሃ ከተመለስን አላህ ማንኛውም ኃጢኣት ይምራል። ለዚህ ናሙና የሚሆነው የእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ በአላህ ላይ ወይፈንን አጋርተው ከዚያም ወደ አላህ በተውበት ሲመለሱ ይቅር መባላቸው ነው፦
7፥152 “እነዚያ ወይፈኑን አምላክ አድርገው የያዙ ከጌታቸው ዘንድ ቁጣ በቅርቢቱም ሕይወት ውርደት በእርግጥ ያገኛቸዋል”፡፡ እንዲሁም ቀጣፊዎችን እንቀጣለን፡፡
7፥153 “እነዚያም ኃጢአቶችን የሠሩ ከዚያም ከእርሷ በኋላ የተጸጸቱ ያመኑም ጌታህ ከእርሷ በኋላ በእርግጥ መሓሪ አዛኝ ነው”፡፡
ዐውዱ ላይ “አለዚነ” الَّذِينَ ማለትም “እነዚያ” በሚለው አንጻራዊ ተውላጠ-ስም በፊት መነሻ ላይ “ወ” وَ የሚል አያያዥ መስተጻምር ይጠቀማል። ይህ የሚያሳየው “እነዚያም” የተባሉት ወይፈኑን አምላክ አድርገው የያዙት ሰዎች መሆናቸውን እንረዳለን ማለት ነው። በተለይ “ከእርሷ” ተብላ የተጠቀሰችው ተውላጠ-ስም ከላይ የተጠቀሰውን የኃጢያት ድርጊት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
[“…አንጻራዊ ተውላጠ-ስም በፊት መነሻ ላይ “ወ” የሚል አያያዥ መስተጻምር…” እያልክ በጽሑፎችህ ሁሉ ውስጥ የምታውቃትን ሥነ-ልሳን መደጋገም ዕውቀት መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል፡፡ ወደ ሥነ-ልሳን ትንታኔ እንድትገባ የሚያደርግ አከራካሪ ጉዳይ በዚህ ቦታ የለም፡፡ በሆነው ባልሆነው ሥነ-ልሳንን ወይም ሰዋሰውን እየደነቀረ ነገር የሚያወሳስብና ግልፁን ንግግር የሚያደፈርስ ሰው አለመብሰሉ ግልፅ ነው፡፡]
ከዚያም ድርጊታቸው የተጸጸቱትን አላህ ይቅር ብሏቸዋል፦
4፥153 “ከዚያም ተዓምራቶች በኋላ ወይፈኑን አምላክ አድርገው ያዙ፡፡ ከዚያም ይቅር አልን”፡፡ ሙሳንም ግልጽ ስልጣንን ሰጠነው፡፡
ነገር ግን አንድ ሰው ካጋራ በኋላ ምህረት የሚያገኘው በህይወት ዘመን ቆይታው እንጂ ሞት በመጣበት ጊዜ አሊያም ከኃዲዎች ሆነው ለሚሞቱ አይደለም፦
4፥17 ጸጸትን መቀበል በአላህ ላይ የሚገባው ለእነዚያ ኀጢአትን በስህተት ለሚሠሩና ከዚያም ከቅርብ ጊዜ ለሚጸጸቱት ብቻ ነው፡፡ እነዚያንም አላህ በእነርሱ ላይ ጸጸትን ይቀበላል”፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
4፥18 “ጸጸትንም መቀበል ለእነዚያ ኀጢአቶችን ለሚሠሩ አንዳቸውንም ሞት በመጣበት ጊዜ «እኔ አሁን ተጸጸትኩ» ለሚልና ለነዚያም እነርሱ ከሓዲዎች ኾነው ለሚሞቱ አይደለችም፡፡ እነዚያ ለእነርሱ አሳማሚን ቅጣት አዘጋጅተናል”፡፡
“ከዚያም ከቅርብ ጊዜ” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት። ከኃዲዎች ሆነው የሚሞቱ በትንሳኤ ቀን በሰሩት ነገር ይጸጸታሉ፣ ነገር ግን ምንም አይጠቅማቸውም፦
39፥56 የካደች ነፍስ፦ «እኔ ከሚሳለቁት የነበርኩ ስኾን በአላህ በኩል ባጓደልኩት ዋ ጸጸቴ» ማለቷን ለመፍራት፤
39፥57 ወይም ቅጣቱን በምታይ ጊዜ፣ ለኔ ወደ ምድረ ዓለም አንድ ጊዜ መመለስ በኖረኝና ከበጎ አድራጊዎቹ በሆንኩ ማለቷን ለመፍራት
39፥58 “ወይም ቅጣቱን በምታይ ጊዜ «ለእኔ ወደ ምድረ ዓለም አንድ ጊዜ መመለስ በኖረኝና ከበጎ አድራጊዎቹ በኾንኩ» ማለቷን ለመፍራት መልካሙን ተከተሉ”፡፡
ስለዚህ አንድ ሰው በሞት ጣዕር ላይ አሊያም በሚቀሰቀስበት ቀን በተውበት ቢጸጸት ጸጸቱ ተቀባይነት የለውም። “ላ ኢላሃ ኢለ ሏህ” لَا إِلَٰهَ إِلَّا اللَّهُ ብሎ ጣዖታትን ውድቅ አድርጎ እና አንዱን አምላክ አላህ በብቸኝነት ያመለከ ሰው ለሠራው መጥፎ ሥራ ተውበት ከገባ አላህ መጥፎ ሥራዎቻቸውን በመልካም ሥራዎች ይለውጥለታል፦
25፥70 ተጸጽቶ የተመለሰና ያመነ መልካምንም ሥራ የሠራ ሰው ብቻ ሲቀር፡፡ እነዚያም አላህ መጥፎ ሥራዎቻቸውን በመልካም ሥራዎች ይለውጣል፡፡ አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
16፥119 ከዚያም ጌታህ ለእነዚያ በስሕተት መጥፎን ለሠሩና ከዚያም ከዚህ በኋላ ለተጸጸቱ ሥራቸውንም ላበጁ ጌታህ ከእርሷ በኋላ በእርግጥ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
ነገር ግን “ላ ኢላሃ ኢለ ሏህ” ይዘው በሚሠሩት መጥፎ ሥራ ተውበት ካላደረጉ ብጤዋን እንጅ አይመነዱም፤ በመጥፎም የመጡ ሰዎች ፊቶቻቸው በእሳት ውስጥ ይደፋሉ፤ በክፉም ሥራ የመጡ ሰዎች እነዚህ መጥፎዎችን የሠሩ ይሠሩት የነበሩትን እንጅ አይመነዱም፦
27፥90 በመጥፎም የመጡ ሰዎች ፊቶቻቸው በእሳት ውስጥ ይደፋሉ፡፡ «ትሠሩት የነበራችሁትን እንጅ አትመነዱም» ይባላሉ፡፡
29፥4 ይልቁንም እነዚያ መጥፎዎችን ሥራዎች የሚሠሩት ሊያመልጡን ይጠረጥራሉን? ያ የሚፈርዱት ፍርድ ከፋ፡፡
አማንያን “ላ ኢላሃ ኢለ ሏህ” በመያዛቸው በሠሩት መጥፎ ሥራ ልክ ተቀጥተው አሊያም በነቢያችን ምልጃ የጀነት ናቸው። የነቢያችን ምልጃ በትንሳኤ ቀን የሚያገኘው ከልቡ ወይም ከነፍሱ፦ “ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም” ላለ ሰው ነው፦
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 3, ሐዲስ 41
አቢ ሁረይራ እንደተረከው፦ ”እኔም፦ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! በትንሳኤ ቀን ማነው እድለኛ ሰው የእርስዎን ምልጃ የሚያገኘው? አልኩኝ፤ የአላህ መልእክተኛም፦ “አቢ ሁረይራ ሆይ! ንግግር ለመማር የአንተን ቆይታ ዐውቃለው፤ እንደማስበው ስለዚህ ጉዳይ ከአንተ በፊት ማንም አልጠየቀኝም። በትንሳኤ ቀን የእኔን ምልጃ የሚያገኝ እድለኛ ሰው ከልቡ ወይም ከነፍሱ፦ “ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም” ያለ ነው።
በአላህ አምልኮ ላይ ሌላ ማንነትን እና ምንነት ያላሻረከ ነገር ግን ዐበይት ወንጀሎችን የሠራ በነቢያችን ምልጃ ከጀሃነም ቅጣት ነጻ ወጥቶ ወደ ጀነት ይገባል፦
ጃምዒ አት-ተርሚዚ መጽሐፍ 37, ሐዲስ 2622
አነሥ እንደተረከው፦ “የአላህ መልእክተኛም አሉ፦ ”የእኔ ምልጃ ከእኔ ኡማህ ዐበይት ወንጀሎችን ለሰሩ ሰዎች ነው።
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 81, ሐዲስ 155
ዒምራን ኢብኑ ሑሴይን”ረ.ዐ.” እንደተረከው፦ “ነቢዩም አሉ፦ ”ጥቂት ሕዝብ ከእሳት ወጥተው ወደ ጀነት በሙሐመድ ምልጃ ይገባሉ፤ ጀሀነሚዪን ተብለው ይጠራሉ።
በአላህ ላይ ያላሻረከ ለሠራው ማንኛውም ወንጀል ተውበት እስካላደረገ ድረስ ቅጣቱን በጀሃነም ይቀጣል። ቅጣቱ ሲያልቅ ወደ ጀነት ይመለሳል፦
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 97, ሐዲስ 113
አቡ ዘር እንደተረከው፦ “ነቢዩ እንዲህ አሉ፦ “ጂብሪል ወደ እኔ መጣና፦ “ማንም በአላህ ላይ ሳያጋራ የሞተ ጀነት ይገባል” ብሎ የምስራች ሰጠኝ። እኔም፦ “ቢሰርቅም ዝሙትም ቢሰራ? ብዬ ጠየኩት፥ እርሱም፦ “አዎ ቢሰርቅም ዝሙትም ቢሰራ” አለኝ።
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 10, ሐዲስ 201
አቢ ሁረይራ እንደተረከው፦ “የአላህ መልእክተኛም እንዲህ አሉ፦…. “ከሰዎች መካከል በሥራቸው ለዘላለም በጀሃነም ሲዘወትሩ ሌሎች ደግ ሞ ቅጣት ተቀብለው ከጀሃነም ይወጣሉ፣ አላህ የሻው ከጀሃነም ሰዎች መካከል ምህረት ያደርግለታል። ለመላእክትም፦ “እርሱን ብቻ ያመለከውን አውጡ” ብሎ ያዛቸዋል”።
“ከሰዎች መካከል ለዘላለም በጀሃነም የሚዘወተሩ” በአላህ ላይ ያጋሩ ናቸው። አላህ በእርሱ ማጋራትን በፍጹም አይምርም። ከዚህ ሌላ ያለውንም ኀጢአት ለሚሻው ሰው ቀጥቶ አሊያም በነቢያችን ሸፋዓ ይምራል። የሚያጋራን ሰው አላህ ገነትን በእርሱ ላይ በእርግጥ እርም አደረገ፤ የአጋሪው መኖሪያውም እሳት ናት፦
4፥48 “አላህ በእርሱ ማጋራትን በፍጹም አይምርም፡፡ ከዚህ ሌላ ያለውንም ኀጢአት ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡ በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኀጢአት በእርግጥ ቀጠፈ”፡፡
5:72 “እነሆ በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በእርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት”። ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም።
ሱራ 4፡48 ይህንን ሁሉ ትንታኔህንና የጠቀስካቸውን ጥቅሶች በሙሉ ከንቱ ያደርጋል፡፡ እንዲህ ይላል፡- “አላህ በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም፤ ከዚህ ሌላ ያለውንም ኀጢአት ለሚሻው ሰው ይምራል። በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኀጢያት በእርግጥ ቀጠፈ።”
“በፍፁም አይምርም” ማለት ኢ-አኳሆናዊ (Unconditional) ንግግር በመሆኑ “በምድር ይምራል በሰማይ ግን አይምርም” ተብሎ ሊተረጎም አይችልም፡፡ “ኢንነ አላሀ ላ ያግህፊሩ አን ዩሽረከ ቢሂ!” “አላህ በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም!” ብሎ ከዘጋ በኋላ “በሰማይ አይምርም፤ በምድር ይምራል” ብሎ ማለት ሌላ ግጭት መፍጠር እንጂ ግጭት ማስታረቂያ አይሆንም፡፡ “በፍፁም አይምርም” ካለ በኋላ “እንዲህ ሲሆን ይምራል፤ እንዲህ ሲሆን ደግሞ አይምርም” የሚል ትንታኔ ኢ-አመክንዮአዊ ነው፡፡ ስለዚህ የቁርኣን ደራሲ በአንዱ ቦታ ላይ አላህ ማጋራትን እንደማይምር ከተናገረ በኋላ በሌላ ቦታ ላይ እንደሚምር መናገሩ ግልፅ ግጭት ነው፡፡