2. ጂን እና ሰው የተፈጠሩት ለምንድ ነው?
ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡
ጥያቄ 2
ጂን እና ሰው የተፈጠሩት ለምንድ ነው?
አላህን ለማምለክ:-
ሱራ 52፡56 “ጂን እና ሰው ሊያመልኩኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም”
ለገሃነም:-
ሱራ 7፡179 “ከጂን እና ከሰው ብዙዎችን ለገሃነም በእርግጥ ፈጠርን፡፡”
መልስ
አምላካችን አላህ ብዙ አንቀጾች ላይ “አምልኩኝ” እያለ በመጀመሪያ መደብ ይናገራል፦
29፥56 እናንተ ያመናችሁ ባሮቼ ሆይ! ምድሬ በእርግጥ ሰፊ ናት፤ ብትቸገሩ ተሰደዱ፡፡ ”እኔንም ብቻ አምልኩኝ”፡፡
21፥92 ይህች አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት፤ ”እኔም ጌታችሁ ነኝና አምልኩኝ”፡፡
21፥25 ከአንተ በፊትም እነሆ ”ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና አምልኩኝ” በማለት ወደ እርሱ ”የምናወርድለት” ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም፡፡
ጂን እና ሰው የተፈጠረበት ዓላማ ሁሉንም የፈጠረውን አንዱን አምላክ አላህ በብቸኝነት እንዲያመልኩት ነው፦
51፥56 ጂኒን እና ሰውንም ሊያመልኩኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡
ነጥብ አንድ
“ላም”
51፥56 ጂኒን እና ሰውንም ሊያመልኩኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡
“የዕቡዱኒ” يَعْبُدُونِ በሚለው ግስ መነሻ ቅጥያ ላይ “ሊ” لِ የምትል መስተዋድድ አለች፤ ይህቺ “ላም” ل “ላሙል-ታዕሊል” ማለትም “የመንስኤ መስተዋድድ” prefixed particle of purpose” ትባላለች፤ ይህንን የሰዋስው ሙግት ለመረዳት ለናሙና ያክል አንድ ሌላ አንቀጽ እንመልከት፦
ጽሑፉን አንዛዝተህ የአንባቢያንን ሐሳብ ለመበተን ካልሆነ በስተቀር ከዓረፍተ ነገሩ ሰዋሰው ጋር የሚያያዝ የዓረፍተ ነገሩን ትርጉም የሚለውጥ የሰዋሰው ትንታኔ የሚያሻው ምንም ነገር የለም፡፡ “ጂን እና ሰው ሊያመልኩኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም” የሚለው ዓረፍተ ነገር በአማርኛ በግልፅ እያየነው ካለነው ትርጉም የተለየ ትርጉም እንዲኖረው የሚያደርግ ምን የሚባል የአረብኛ የሰዋሰው ሕግ ነው? በቅድሚያ እርሱን ከገለፅክ በኋላ አንባቢያንን በጥሩ ሁኔታ ለማስገንዘብ ተጨማሪ ምሳሌ ትጠቅሳለህ እንጂ ዘለህ ወደ ሌላ ጥቅስ አትሄድም፡፡ በጥቅስ ላይ ጥቅስ መደረብህ የሙግት እጥረት እንደገጠመህ ያሳብቃል፡፡ ይሁን እስኪ ጥቅሱን እንየው፡-
28፥9 የፈርዖንም ሚስት፦ ለእኔም ለአንተም የዓይኔ መርጊያ ነው፡፡ አትግደሉት፡፡ ”ሊ”ጠቅመን ወይም ልጅ አድርገን ልንይዘው ይከጀላልና» አለች፡፡ እነርሱም ፍጻሜውን የማያውቁ ሆነው አነሱት፡፡
የፈርዖን ቤተሰቦች ሙሳን ከባህር ያነሱበት ዓላማ ሊጠቅማቸው ወይም ልጅ አድርገው ሊያሳድጉት ነው፤ እዚህ ጋር የገባችው “ላም” ل “ላሙል-ታዕሊል” እንደሆነች አንባቢ ልብ ይለዋል፤ ነገር ግን እነርሱ ማለትም የፈርዖን ቤተሰቦች ፍጻሜውን የማያውቁ ሆነው ከባህር አነሱት፤ አላህ ግን ፍጻሜውን ስለሚያውቅ፦ “ለእነርሱ ጠላት ሐዘንም ይሆን ዘንድ አነሱት” ብሎ ነገረን፦
28፥8 የፈርዖን ቤተሰቦችም መጨረሻው “ለ”እነርሱ ጠላት ሐዘንም ይሆን ዘንድ አነሱት፡፡
እዚህ ጋር ነው ነጥቡ፤ የፈርዖን ቤተሰቦች ሙሳን ከባህር ያነሱበት ዓላማ ሊጠቅማቸው ወይም ልጅ አድርገው ሊያሳድጉት ሆኖ ሳለ ነገር ግን ሙሳ ሲያድግ ለእነርሱ ጠላትና ሐዘን ሆነባቸው፤ አላህ ፍጻሜውን ስለሚያውቅ፦ “ለእነርሱ ጠላት ሐዘንም ይሆን ዘንድ አነሱት” አለን፤ እዚህ ጋር “የኩነ” يَكُونَ በሚለው ግስ መነሻ ቅጥያ ላይ “ሊ” لِ የምትል መስተዋድድ አለች፤ ይህቺ “ላም” ل “ላሙል-ዓቂባህ” ማለትም “የውጤት መስተዋድድ” prefixed particle of result” ትባላለች፤ ፍጻሜያቸውና መጨረሻቸው ምን እንደሆነ ቀድሞ በመታወቁ ምክንያት የምትመጣ መስተዋድድ ናት፤ ይህንን የሰዋሰው ሙግት ከተረዳን ጂን እና ሰው የተፈጠሩበት ዓላማ አላህን እንዲያመልክ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ከጂን እና ከሰው በነጻ ፈቃዳቸው ልቦች እያላቸው የማያውቁ፣ አይኖች እያላቸው የማያዩ፣ ጆሮዎች እያላቸው የማይሰሙ ጀሃነም ይገባሉ፤ አላህ የእነዚህን ፍጻሜ ስለሚያውቅ፦ “ከጂኒዎችም ከሰዎችም ብዙዎችን ለገሀነም በእርግጥ ፈጠርን” አለ፦
7፥179 ከጂኒዎችም ከሰዎችም ብዙዎችን ለገሀነም በእርግጥ ፈጠርን፡፡ ለእነርሱ በእርሳቸው የማያውቁባቸው ልቦች አሏቸው፡፡ ለእነርሱም በሳቸው የማያዩባቸው ዓይኖች አሉዋቸው፡፡ ለእነርሱም በሳቸው የማይሰሙባቸው ጆሮዎች አሉዋቸው፡፡ እነዚያ እንደ እንስሳዎች ናቸው፡፡ ይልቁንም እነርሱ በጣም የተሳሳቱ ናቸው፡፡ እነዚያ ዘንጊዎቹ እነርሱ ናቸው።
እዚሁ አንቀጽ ላይ “ጀሃነም” جَهَنَّمَ በሚለው ቃል መነሻ ቅጥያ ላይ “ሊ” لِ የምትል “ላም” ل “ላሙል-ዓቂባህ” የተባለችው የውጤት መስተዋድድ መግባቷ አንባቢ ልብ ይላታል፤ ስለዚህ እነዚያ ዘንጊዎቹ መጨረሻቸው ለገሃነም ናቸው፤ እነዚያን ዘንጊዎቹ የፈጠራቸው አላህ ነው።
መያዣ መጨበጫ የሌለው ነገር ነው የምታወራው፡፡ የመጀመርያው ጥቅስ “ጂን እና ሰው ሊያመልኩኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም” ይላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ “ከጂን እና ከሰው ብዙዎችን ለገሃነም በእርግጥ ፈጠርን” በማለት የመጀመርያውን ያፈርሳል፡፡ በሁለቱም ውስጥ ባለቤቱ/Subject (እንዲያመልኩትም ሆነ በገሃነም እንዲቃጠሉ አስቦ የፈጠረው) አላህ ነው፡፡ ተሳቢ/Object (አላህን እንዲያመልኩት ብቻና ለገሃነም የተፈጠሩት) ሰዎችና ጂኒዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ አድራጊው አላህ እስከሆነ ድረስ ለውጤቱም ኃላፊነቱ የአላህ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ እናም በውጤቱ ላይ ቁጥጥር ያለውን አላህን ከፈርዖን ጋር ማነፃፀር ተገቢም የሚያስኬድም አይደለም፡፡ ፈርዖን ቅድመ ዕውቀትም ሆነ የቅድመ ውሳኔም ሥልጣን የለውም፡፡ አላህ ግን የሁለቱም ችሎታዎች ባለቤት ነው፡፡ ሁለቱን ማነፃፀር በአላህ ሉኣላዊነት ላይ መሳለቅ ነው፡፡
የአረብኛ ሰዋሰው ውስጥ በመግባት የሰጠኸው ትንታኔ አስፈላጊ ካለመሆኑም በላይ ግልፁንና ቀላሉን ጉዳይ ለማወሳሰብና ለማደብዘዝ የተደረገ ተራ ማምታቻ ነው፡፡ የአማርኛው ቁርኣን ተርጓሚዎች እስልምናን እንደሚያስተቹ ከተጠራጠሯቸው ነጥቦች ውጪ በብዙ ሁኔታዎች ቃል በቃል (Literal) የሚባል ዓይነት ትርጉም ስለተጠቀሙ በአረብኛው ውስጥ የሚገኙት ሰዋሰዋዊ ዝርዝሮች በሙሉ በጥቅሶቹ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይህም ሆኖ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ስለዚህ ከሰዋሰው አንፃር ሊቀርብ የሚችል ምንም ዓይነት ሙግት የለም፤ አንተም ፋይዳ የሌለው ዝርዝር ውስጥ ከመግባት የዘለለ ያቀረብከው ሙግት የለም፡፡
ነጥብ ሁለት
“ሚን”
አላህ፦ ”ጂኒዎችም ሰዎችም ለገሀነም በእርግጥ ፈጠርን” አላለም፤ ጂኒዎችም ሰዎችም በሚሉት ቃላት መነሻ ቅጥያ ላይ “ሚን” مِن ማለትም “ከ” የሚል መስተዋድድ አለ፣ ይህም የሚያስረዳው ከጂንዎችና ከሰዎች መካከል ልቦች እያላቸው የማያውቁ፣ አይኖች እያላቸው የማያዩ፣ ጆሮዎች እያላቸው የማይሰሙ የገሃነም መሆናቸውን ነው፤ ይህንን ለመረዳት የሚቀጥለውን አንቀጽ እንመልከት፦
30፥8 ”ከ”ሰዎቹም ብዙዎቹ በጌታቸው መገናኘት ከሓዲዎች ናቸው፡፡
ይህንን ማየት የተሳነው የለም፤ የቀረበውም ሙግት ይህንን የሚክድ አይደለም፡፡ “ብዙዎቹን፣ ጥቂቶቹን ወይንም ሁሉንም” የሚሉ ገላጭ ቃላት መኖር አለመኖራቸው የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ አላህ ሰዎችንና ጋኔኖችን እንዲገዙለት ብቻ እንደፈጠረ ከተናገረ በኋላ ብዙዎቹን ግን ለገሃነም እንደፈጠረ በመናገር መጀመርያ የተናገረውን ቃል አፍርሷል፡፡ ይህ ማስተባበያ የሌለው ግልፅ ግጭት ነው፡፡
አንቀጹ ላይ የሚለው “ሰዎች በጌታቸው መገናኘት ከሐዲዎች ናቸው” ሳይሆን “ከሰዎቹም ብዙዎቹ በጌታቸው መገናኘት ከሐዲዎች ናቸው” ነው፤ “ሰዎች” በሚለው ቃል ላይ “ሚን” مِن የሚል መስተዋድድ አለ፣ ሌላ ናሙና እስቲ እንመልከት፦
4፥124 ”ከ”ወንድ ወይም “ከ”ሴት እርሱ አማኝ ኾኖ ከበጎ ሥራዎች አንዳችን የሚሠራም ሰው እነዚያ ገነትን ይገባሉ፡፡ በተምር ፍሬ ላይ ያለችን ነጥብ ያክል እንኳ አይበደሉም፡፡
ምሳሌ ማብዛት ትርጉም የለውም፡፡ መልስ ሊሆንም አይችልም፡፡
አንቀጹ ላይ የሚለው “ወንድ ወይም ሴት እነዚያ ገነትን ይገባሉ” ሳይሆን “ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ኾኖ ከበጎ ሥራዎች አንዳችን የሚሠራም ሰው እነዚያ ገነትን ይገባሉ” ነው፤ “ወንድ እና ሴት” በሚለው ቃል ላይ “ሚን” مِن የሚል መስተዋድድ አለ፣ ይህ የሚያሳየው ከወንድ ወይም ከሴት መካከል አማኝ ኾኖ ከበጎ ሥራዎች አንዳችን የሚሠራም ሰው ገነትን ይገባሉ ነው፤ እንዲሁ በተቃራኒው ከጂንዎችና ከሰዎች መካከል ልቦች እያላቸው የማያውቁ፣ አይኖች እያላቸው የማያዩ፣ ጆሮዎች እያላቸው የማይሰሙ ጀሃነም ይገባሉ ነው።
ሰዋሰዋዊ አገባብ ወይንም የቃላት አወቃቀር የሚጠቀሰው በሁሉም ሁኔታዎች ሳይሆን ወሳኝ በሆኑት ነጥቦች ላይ ብቻ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ሁኔታ “እንዲህና እንዲያ የሚል መስተዋድድ፣ መስተፃምር፣ ቅድመ ቅጥያ፣ ወዘተ. አለ” እያሉ የሚያውቁትን ስነ ልሳን ሁሉ መዘብዘብ አንባቢን ከማሰልቸት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡
አላህ አስቀድሞ ለገሃነም አስቦ እንደፈጠራቸው እስከተነገረ ድረስ “ልቦች እያላቸው የማያውቁ፣ ዐይኖች እያላቸው የማያዩ፣ ጆሮዎች እያላቸው የማይሰሙ ጀሃነም ይገባሉ” የሚለው አባባል ትርጉም አይሰጥም፡፡ አላህ አስቀድሞ ለገሃነም አልሞ ስለፈጠራቸው ገሃነም አለመግባት አይችሉም፡፡ ይችላሉ ከተባለም ግጭት ነው የሚሆነው፡፡
ነጥብ ሦስት
“አውላዒከ”
“አውላዒከ” أُولَـٰئِكَ ማለት “እነዚያ” ማለት ሲሆን አመልካች ተውላጠ-ስም ነው፤ የአንቀጹን ዓረፍተ-ነገር ከሃረጉ አፋቶ ማንበብ ክፉኛ መሃይምነት ነው፤ ከጂንዎችና ከሰዎች መካከል “እነዚያ” የተባሉት ልቦች እያላቸው የማያውቁ፣ አይኖች እያላቸው የማያዩ፣ ጆሮዎች እያላቸው የማይሰሙ ናቸው፤ ሆን ብለው የአላህን መልእክት ያስተባበሉ ናቸው፤ እነርሱ ልክ እንደ እንስሳ ውሳጣዊ ተፈጥሮአቸው ደንድኗል፣ ታውሯል፣ ደንቁሯል፦
እንደዚያ ያነበበ ማንም የለም ስለዚህ ስድቡን አቆየው፡፡ በጥቅሱ መሠረት አላህ ሆን ብሎ ለገሃነም ከፈጠራቸው እነርሱ ሆን ብለው የአላህን መልእክት እንዳስተባበሉ መናገር ግጭት ነው፡፡ አላህ ሆን ብሎ ለገሃነም ከፈጠራቸው ሆን ብሎ ያሳሳታቸው አላህ ራሱ በመሆኑ ሆን ብለው ሊሳሳቱ አይችሉም፡፡ እንዲሳሳቱ አስቀድሞ ተወስኖባቸዋልና፡፡
25፥44 ይልቁንም አብዛኛዎቻቸው የሚሰሙ ወይም የሚያውቁ መኾናቸውን ታስባለህን እነርሱ እንደ እንስሳዎች እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡ ከቶውንም እነሱ ይልቅ መንገድን የተሳሳቱ ናቸው፡፡
2:171 የእነዚያም የካዱት እና ወደ ቅን መንገድ የሚጠራቸው ሰው ምሳሌ እንደዚያ ድምጽንና ጥሪን በስተቀር ሌላን በማይሰማ እንስሳ ላይ እንደሚጮህ ብጤ ነው፡፡ እነርሱ ደንቆሮዎች፣ ዲዳዎች፣ ዕውሮች ናቸው፤ ስለዚህ እነርሱ አያውቁም፡፡
7፥179 ከጂኒዎችም ከሰዎችም ብዙዎችን ለገሀነም በእርግጥ ፈጠርን፡፡ ለእነርሱ በእርሳቸው የማያውቁባቸው ልቦች አሏቸው፡፡ ለእነርሱም በሳቸው የማያዩባቸው ዓይኖች አሉዋቸው፡፡ ለእነርሱም በሳቸው የማይሰሙባቸው ጆሮዎች አሉዋቸው፡፡ እነዚያ እንደ እንስሳዎች ናቸው፡፡ ይልቁንም እነርሱ በጣም የተሳሳቱ ናቸው፡፡ እነዚያ ዘንጊዎቹ እነርሱ ናቸው።
አላህ ጂኒዎችን ሆን ብሎ ለገሃነም ከፈጠረ በኋላ ለጥፋታቸው እንዲህ መውቀሱ አስገራሚ ነው፡፡ እርሱ አስቀድሞ ለጥፋት ፈጥሯቸው ሳለ እርሱ በፈጠራቸው መንገድና ለዓላማው መኖራቸው ሊያስደስተው እንጂ ሊያማርረው ባልተገባ ነበር፡፡
መደምደሚያ
ከላይ ያለውን ሙግት ከኡስታዙና አቡሃይደር አላህ ይጠብቀው የተማርኩት ሙግት ነው፤ ብዙ ጊዜ ካፊሮች የራሳቸው እያረረባቸው የእኛን ማማሰል ከጀመሩ ሰነበቱ፣ የተረዳነው ነገር ቢኖር መጽሐፋቸው ዞር ብለው እንደማያዩት ነው፣ እስቲ ይህንን ሂስ በነካ እጃችን እንሞግት፤
ሙግቱን ለሁለት አዘጋጅታችሁት እንዲህ ደካማ ከሆነ ብቻህን ያዘጋጀኸውማ ምን ያህል ደካማ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ለማንኛውም የጥያቄያችን ዓላማ በገፁ ጅማሬ ላይ እንዳልነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምታነሱትን ጥያቄ የቁርኣንን ግጭቶች ለማስታረቅ በምትሞክሩበት መንገድ እንድትገነዘቡ መርዳት በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሳሳይ ጥያቄ ማንሳትህ ዓላማችንን አለመረዳትህን ያመለክታል፡፡ የቁርአኑን ችግር እንደፈታህ ካመንክ የመጽሐፍ ቅዱሱን በዚያው መንገድ ለምን አትረዳውም? ለማንኛውም መልስ እንሰጥሃለን፤ በዚያውም “መልስ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትማራለህ፡፡
እግዚአብሔር ኀጥአንን ማለት ኀጢያተኞችን ለክፉ ቀን እንደፈጠራቸው ይናገራል፦
ምሳሌ 16:4 እግዚአብሔር ሁሉን ለእርሱ ለራሱ ፈጠረ፥ ኀጥእን ደግሞ ” ለክፉ ቀን”።
ክፉ ከሚለው ቃል በፊት “ለ” לְ ማለትም ”ለ” የሚለው ቃል መነሻ ቅጥያ ሆኖ የመጣ መስተዋድድ ነው፣ ጥያቄ እግዚአብሔር ኀጢያተኞችን የፈጠረ ለክፉ ቀን ነውን?
ያንን እጅ እጅ የሚለውን የስነ ልሳን ትንታኔህን ወደ መጽሐፍ ቅዱስም አመጣኸው? እስኪ ማን ይሙትና አሁን እዚህ ጋ የስነ ልሳን ትንታኔ የሚያስፈልገው ግልፅ ያልሆነ ምን ነገር አለ?
ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ሉኣላዊ ሥልጣን ያምናሉ፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሔር ክፉ ሰዎችንም ጭምር ለዓላማው የመጠቀም ሉኣላዊ ሥልጣን አለው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሰዎችን ኃጢአተኛ አድርጎ ፈጥሯል የሚል ትርጉም የለውም፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ ፈጣሪ እርሱ በመሆኑ ክፋትን የሚፈፅሙትንም ሆነ እርሱን የሚፈሩትን ሰዎች ሁሉ ፈጥሯል፡፡ ስለዚህ ጻድቁንም ሆነ ኃጥኡን ለዓላማው የመጠቀም መብትም ሆነ ሥልጣን በእጁ ነው፡፡ “ለክፉ ቀን” ማለት ክፉ በተባለ ቀን የእርሱን ሐሳብ ለማስፈፀም ይጠቀምባቸዋል ማለት ነው፡፡ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ክፉዎችን እንኳ ለክፉ ቀን አዘጋጅቷል” ይላል፡፡ ስለዚህ በዚህ ትርጓሜ መሠረት እግዚአብሔር ክፉ የሆኑ ሰዎችን ለክፉ ቀን፣ ማለትም ፍርድንና ጥፋትን ለሚቀበሉበት የቅጣት ቀን አዘጋጅቷቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህም ክፉ ስለሆኑ እንጂ እርሱ ክፉ ስላደረጋቸው አይደለም፡፡
ከዚህ የባሰ ክፋትን የፈጠረውስ? የሚያፈርሰውንም እንዲያጠፋ የፈጠረው እግዚአብሔር መሆኑን ይናገራል፦
ኢሳይያስ 45፥7 ብርሃንን ሠራሁ፥ ጨለማውንም ፈጠርሁ፤ ደኅንነትን እሠራለሁ፥ ”ክፋትንም እፈጥራለሁ”፤ እነነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤
በዚህ ቦታ “ክፋት” የተባለው በተለያዩ የእንግሊዘኛ ትርጉሞች “Calamity” ወይንም በምድር ላይ የሚደርሱ ተፈጥሯዊ አደጋዎችን የሚያመለክት ነው፡፡ እግዚአብሔር ግብረ ገባዊ ክፋትን አልፈጠረም፤ አይፈጥርምም፤ ምክንያቱም እርሱ በባሕርዩ ቅዱስ ነውና፡፡ ነገር ግን ተፈጥሯዊ አደጋዎችንና ሌሎች በሰዎች ላይ ጥፋትን ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮችን ለዓላማው ይጠቀማቸዋል፡፡ (በነዚህ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ውስጥ የዓላማውን ጥልቀትና ምጥቀት ለመረዳት የሰው ልጆች መቸገራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡) ይህ ሆነ ብሎ ሰዎችን ለገሃነም ከመፍጠር ጋር የሚነፃፀር አይደለም፡፡
ኢሳይያስ 54፥16 እነሆ፥ ፍሙን በወናፍ የሚያናፋ ለሥራውም መሣሪያ የሚያወጣ ብረት ሠሪን እኔ ፈጥሬአለሁ፤ ”የሚያፈርሰውንም እንዲያጠፋ ፈጥሬአለሁ”።
ይህ ግልፅና እውነት ነው፡፡ ጥቅሱ የሚያወራው ስለ ጦርነት ነው፡፡ አውዱ እንዲህ ይላል፡-
እነሆ፥ ይሰበሰባሉ፥ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም፤ በአንቺም ላይ የሚሰበሰቡ ሁሉ ከአንቺ የተነሣ ይወድቃሉ። እነሆ፥ ፍሙን በወናፍ የሚያናፋ ለሥራውም መሣሪያ የሚያወጣ ብረት ሠሪን እኔ ፈጥሬአለሁ የሚያፈርሰውንም እንዲያጠፋ ፈጥሬአለሁ። በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፥ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ (ኢሳ. 54፡15-17)
ሁሉን የፈጠረው እግዚአብሔር አይደለምን? በጦርነት ወቅት ክፉዎችን ለመቅጣትና ለማስተማር እግዚአብሔር ጦረኛን አይጠቀምምን? ይህ ሆነ ብሎ ሰዎችን ለገሃነም ከመፍጠር ጋር የሚመሳሰለው በምን መንገድ ነው?
ቢያንስም ቢበዛም ቁርኣን ላይ ላለው ጥያቄ መልስ ተሰጦበታል፣ ይህ ጥያቄ ሲመጣባቸው የሚሰጡት መልሱ፦
ሮሜ 9፥20-24 አንተ ሰው ሆይ፥ ለእግዚአብሔር የምትመልስ ማን ነህ? ሥራ ሠሪውን፦ ስለ ምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ ይለዋልን? ወይም ሸክላ ሠሪ ከአንዱ ጭቃ ክፍል አንዱን ዕቃ ”ለ”ክብር አንዱንም ”ለ”ውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ ሥልጣን የለውምን?
ቀደም ሲል እንዳልነው ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ሉኣላዊ ሥልጣን ያምናሉ፡፡ የሁሉ ሠሪና ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር የወደፊቱንና የሰዎች ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ስለሚያውቅ የሰው ልጆች ነፃ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው እርሱን ወደ ማወቅ የሚመጡበትን የተሻለ ዓለም (the best possible world) ፈጥሯል፡፡ በዚህ ዓለም ውስጥ እያንዳንዱ ሰው ነፃ ፈቃዱን ተጠቅሞ ወደ እርሱ መምጣትም ሆነ አለመምጣት ስለሚችል ለውሳኔው ተጠያቂ የሚሆኑት ግለሰቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህንን ዓለም እግዚአብሔር በገዛ ምርጫው ስለፈጠረ ሉኣላዊ ውሳኔው በእጁ ነው፡፡ ይህ በነገረ መለኮት ሊቃውንት ዘንድ “መካከለኛ ዕውቀት” (Middle Knowledge) ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን የእግዚአብሔርን ሉኣላዊ ቅድመ ውሳኔ ሳይፃረሩና የሰዎችን ነፃ ፈቃድ ሳይክዱ ሚዛናዊ አቋም ለመያዝ ይረዳል፡፡ ይህንን በጥልቀት መተንተን ቢቻልም ለመሠረታዊ ግንዛቤ ያህል በቂ ይመስለናል፡፡
ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ነገር ነው። ጥያቄ እግዚአብሔር ሁሉን የፈጠረው ለራሱ? ወይስ ለክፉ ቀን? ወይስ ለውርደት? ወይስ ለክብር? ሸክላ ሠሪ እግዚአብሔር አንዱን ለውርደት አንዱን ለክብር ለምን ይፈጥራል? ቁርኣን ላይ ሲጠይቁ ልክ የራሳቸው ባይብል ሙሉ መልስ እንዳለው አድርገው ነው የሚጠይቁት፣ ነገር ግን ባይብል ላይ ሲጠየቁ እርርና ምርር ብለው ሲንጨረጨሩና ሲንተከተኩ ነው የሚገኙት፣ አላህ ሂዳያ ይስጣቸው ለእኛም ጽናቱን።
ለሁሉም መልስ ሰጥተናል ስለዚህ ራሳችንን መድገም አያሻንም፡፡ በቁርኣን ላይ ያነሳነው ጥያቄ ከተጠቀሱት ጥቅሶች ጋር ፈፅሞ አይመሳሰልም፡፡ የኛ ኦሪጅናል ጥያቄ በአላህ ቅድመ ውሳኔ ላይ ሳይሆን ሁለት የሚጋጩ ነገሮችን አስቀድሞ በመወሰኑ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ጠያቂው ከመጽሐፍ ቅዱስ የጠቀሳቸው ጥቅሶች እግዚአብሔር የሚጋጩ ቅድመ ውሳኔዎችን መወሰኑን ስለማያሳዩ እኛ በቁርኣን ላይ ከሰነዘርነው ጥያቄ ጋር አይመሳሰልም፡፡ ቁርኣን ሱራ 52፡56 ላይ “ጂን እና ሰው ሊያመልኩኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም” በማለት ለሌላ ለምንም ጉዳይ እንዳልተፈጠሩ ከነገረን በኋላ ሱራ 7፡179 ላይ ይህንን በማፍረስ “ከጂን እና ከሰው ብዙዎችን ለገሃነም በእርግጥ ፈጠርን” ይላል፡፡ ለአላህ አምልኮን መስጠትና በገሃነም ውስጥ መቃጠል አብረው የሚሄዱ ነገሮች አይደሉም፡፡ ስለዚህ አላህ ሰዎችንና ጂኒዎችን እንዲያመልኩት ብቻ ከፈጠራቸው ለገሃነምም ጭምር እንደ ፈጠራቸው መናገሩ ግጭት ነው፡፡ ሙስሊሙ ወገናችን ለዚህ ጥያቄ መልስ ሊሰጥ ይቅርና የሙግታችንን ነጥብ እንኳ አልተረዳም፡፡ እንደገና እንዲሞክር ዕድል እንሰጠዋለን፡፡