የቁርኣን ግጭቶች – ክፋት እና ደግነት ከማነው?

ክፋት እና ደግነት ከማነው?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ክፉም ደጉም ከአላህ፡-

ሱራ 4፡78 “የትም ስፍራ ብትኾኑ፣ በጠነከሩ ሕንጻዎች ውስጥ ብትኾኑም እንኳን ሞት ያገኛችኋል፤ ደግም ነገር ብታገኛቸው ይህች ከአላህ ዘንድ ናት፣ ይላሉ፤ መከራም ብታገኛቸው ይህቺ ከአንተ ዘንድ ናት ይላሉ፤ ሁሉም ከአላህ ዘንድ ነው በላቸው፤ ለነዚህም ሰዎች፣ ንግግርን ሊረዱ የማይቀርቡት ምን አላቸው?”

ክፉ ከሰው ደግነት ከአላህ፡-

ሱራ 4፡79 “ከደግ ነገር የሚያገኝህ ከአላህ  ነው፤ ከመከራም የሚደርስብህ ከራስህ ነው፤ በሰዎችም ሁሉ መልክተኛ ኾነህ ላክንህ መስካሪም በአላህ በቃ።”

መልስ

ፊዕል” فِعْل ማለት “ድርጊት”action” ማለት ሲሆን አራት ነገር ናቸው፤ እነርሱም፦ ጊዜ፣ ቦታ፣ ቁስ እና ነጻ ምርጫ ናቸው፤ እነዚህን ነገሮች የፈጠረው አላህ ነው፤ አላህ የነገር ሁሉ ፈጣሪ ነው፦

39፥62 አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አስተናባሪ ነው፡፡

“ነገር” በሚለው ቃል ውስጥ መልካም ነገር እና መጥፎ ነገር ይካተታሉ፤ አላህ እኛንም እኛ የምንሰራውን ሁሉ የፈጠረ ነው፦

37፥96 አላህ እናንተንም የምትሠሩትንም የፈጠረ ሲኾን፡፡

የምንሠራቸውንም ኃጢአቶች የፈጠረው አላህ ነው ማለት ነው፡፡ በፍጥረተ ዓለም ውስጥ የሚታዩት ክፋቶች ሁሉ በአላህ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ አላህን የክፋት ሁሉ ምንጭ ያደርገዋል፡፡ ይህ እሳቤ ከመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ምንኛ የተለየ ነው!

ቁስን ማለት የምንሰማበት ጆሮ፣ የምናይበት ዐይን እና የምናስብበት ልብ የፈጠረልን አላህ ነው፤ መስሚያ የሚሰማውን የመምረጥ ነፃነቱ፣ ማያም የሚያየውን የመምረጥ ነፃነቱ፣ ልብም የሚያስበውን የመምረጥ ነፃነቱ ስለተሰጠው የእነርሱ ባለቤት ሰው በተሰጠው ጸጋ ተጠያቂ ነው፦

23፥78 እርሱም ያ መስሚያዎችን፣ ማያዎችን እና ልቦችንም ለእናንተ የፈጠረላችሁ ነው፤ ጥቂትን እንጅ አታመሰግኑም፡፡

17፥36 ለአንተም በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር አትከተል፤ መስሚያ፣ ማያም እና ልብም እነዚህ ሁሉ ባለቤታቸው ከእነርሱ ተጠያቂ ነውና።

102፥8 ከዚያም ከጸጋችሁ ሁሉ በዚያ ቀን ትጠየቃላችሁ።

“ነዒም” نَّعِيمِ ማለት “ጸጋ” ማለት ነው፤ በተሰጠን ነጻ ፈቃድና ምርጫ የምንሰራው መልካም ሥራ ሆነ ክፉ ሥራ ያስጠይቀናል፤ ያስመነዳናል፦

21፥23 ከሚሠራው ሁሉ አይጠየቅም፡፡ እነርሱ ፍጥረቶቹ ግን ይጠየቃሉ፡፡

16፥93 ትሠሩት ከነበራችሁትም ሁሉ በእርግጥ ትጠየቃላችሁ፡፡

45፥22 አላህም ሰማያትንና ምድርን ለችሎታው እንደሚያመለክትባቸውና ነፍስም ሁሉ በሠራችው ሥራ ትምመነዳ ዘንድ በትክክል ፈጠረ፡፡ እነርሱም አይበደሉም፡፡

“ዐመል” عَمَل “ሥራ”deed” ማለት ሲሆን በዚህ ሥራችን እንጠየቃለን፤ በምንሠራው ሥራ ሰበቡ እኛው ነን፤ “ሰበብ” سَبَب ማለት “ምክንያት” ማለት ሲሆን አላህ ለሰው የራሱ ነጻ ፈቃድ ሰቶታል፣ አንድ ሰው ፈቃዱን ተጠቅሞ መልካም ነገር ሲፈልግ ያ መልካም ነገር ሰበቡ አላህ ሲሆን ነገር ግን በተቃራኒው መጥፎ ነገር ሲያገኝ የዛ የመጥፎ ነገር ሰበቡ እራሱ ሰውዬው ነው፦

4፥79 ከደግም የሚያገኝህ ከአላህ ነው፤ ከፉዉም የሚደርስብህ ከራስህ ነው፤

“ራስህ” የሚለው ቃል “ነፍሲከ” نَفْسِكَ ሲሆን “ራስነትን”own self-hood” ያመለክታል። በራሳችን በምንሠራው ሥራ ሊፈትነን ሞት እና ሕይወትን ፈጠረ፦

የክፋት ሁሉ ምንጭ እርሱ ከሆነና እኛ የምንፈፅመው ኃጢአት ሁሉ እርሱ የወሰነብን ከሆነ ስለምን እንጠየቃለን? ይህ ፈጣሪን ኢ-ፍትሃዊ አያደርገውምን?

67፥2 ያ የትኛችሁ ሥራው ይበልጥ ያማረ መኾኑን ሊፈትናችሁ ሞትን እና ሕይወትን የፈጠረ ነው፡፡ እርሱም አሸናፊው መሓሪው ነው፡፡

21፥35 ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት፡፡ “ለመፈተንም በክፉም በበጎም እንፈትናችኋለን”፡፡ ወደ እኛም ትመለሳላችሁ፡፡

ልብ አድርግ ሞት እና ሕይወት ከእርሱ ዘንድ የሆኑ መፈተኛዎች ናቸው። በአንጻራዊነት ሞት ክፉ ነገር ሕይወት ደግሞ በጎ ነገር ነው። የትም ስፍራ ብንኾን፥ በጠነከሩ ሕንጻዎች ውስጥ ብንኾንም እንኳ ሞት ያገኘናል። የሞት መከራ ሲያገኘን፦ “ይህቺ ከአንተ ዘንድ ናት” ይላሉ፥ ግን ሞትም ሆነ ሕይወት ሁሉም ከአላህ ዘንድ ነው፦

4፥78 «የትም ስፍራ ብትኾኑ በጠነከሩ ሕንጻዎች ውስጥ ብትኾኑም እንኳ ሞት ያገኛችኋል፡፡ ደግም ነገር ብታገኛቸው ይህች ከአላህ ዘንድ ናት» ይላሉ፡፡ መከራም ብታገኛቸው «ይህቺ ከአንተ ዘንድ ናት» ይላሉ፡፡ «ሁሉም  ከአላህ ዘንድ ነው» በላቸው፡፡ ለእነዚህም ሰዎች ንግግርን ሊረዱ የማይቀርቡት ምን አላቸው?

እንደርሱ ከሆነ ሱራ 4፡79 ላይ ደጉ ከአላህ ክፉው ከሰው መሆኑ ስለምን ተነገረ? “ከደግ ነገር የሚያገኝህ ከአላህ ነው፤ ከመከራም የሚደርስብህ ከራስህ ነው፤ በሰዎችም ሁሉ መልክተኛ ኾነህ ላክንህ መስካሪም በአላህ በቃ።”

እነዚህ ሁለት ጥቅሶች በአንድ አውድ ውስጥ እንደሚገኙ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡-

ሱራ 4፡78-79 “የትም ስፍራ ብትኾኑ፣ በጠነከሩ ሕንጻዎች ውስጥ ብትኾኑም እንኳን ሞት ያገኛችኋል፤ ደግም ነገር ብታገኛቸው ይህች ከአላህ ዘንድ ናት፣ ይላሉ፤ መከራም ብታገኛቸው ይህቺ ከአንተ ዘንድ ናት ይላሉ፤ ሁሉም (ደጉም ክፉዉም) ከአላህ ዘንድ ነው በላቸው፤ ለነዚህም ሰዎች፣ ንግግርን ሊረዱ የማይቀርቡት ምን አላቸው? ከደግ ነገር የሚያገኝህ ከአላህ (ችሮታ) ነው፤ ከመከራም የሚደርስብህ ከራስህ (ጥፋት የተነሳ) ነው፤ በሰዎችም ሁሉ መልክተኛ ኾነህ ላክንህ መስካሪም በአላህ በቃ።”

ጥቅሱ ስለ ሞትና ስለ ሕይወት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ስለ የትኛውም ዓይነት ክፉና መልካም ነገር እንደሚናገር ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ “ደግም ነገር ብታገኛቸው ይህች ከአላህ ዘንድ ናት፣ ይላሉ፤ መከራም ብታገኛቸው ይህቺ ከአንተ ዘንድ ናት ይላሉ፤ ሁሉም (ደጉም ክፉዉም) ከአላህ ዘንድ ነው በላቸው፡፡” ይህንን ካለ በኋላ በዚያው አውድ ተመሳሳይ የአረብኛ ቃላትን ተጠቅሞ “ከደግ ነገር የሚያገኝህ ከአላህ (ችሮታ) ነው፤ ከመከራም የሚደርስብህ ከራስህ (ጥፋት የተነሳ) ነው” በማለት ደግነት ከአላህ፣ ክፋት ደግሞ ከሰው መሆኑን ይናገራል፡፡ በሁለቱም አንቀፆች ላይ ደግነት የሚለውን ለማመልከት “ሐሰነቲን” ክፋት ወይንም መከራን ለማመልከት ደግሞ “ሰይአቲን” የሚሉ የአረብኛ ቃላት ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ቁርኣን እዚያው ምዕራፍ ቁጥር 82 ላይ ደግሞ በሰው ላይ ለሚደርሱት ክፉ ነገሮች ሌላ ተዋናይ፣ ማለትም ሰይጣን መኖሩን ይናገራል (ሱራ 4፡82)፡፡ ቁርኣን በአንድ ምዕራፍ ተከታታይ በሆኑት ጥቅሶች ውስጥ እንዲህ እርስ በርሱ የተምታታ ነገር መናገሩ አስገራሚ ነው፡፡

የቁርኣን ግጭቶች