የሰውን ነፍስ የሚያወጣው ማን ነው?
ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡
መልአከ ሞት (አንድ መልአክ)፡-
ሱራ 32፡11 “በእናንተ የተወከለው መልአከ ሞት ይገድላችሗል፤ ከዚያም ወደ ጌታችሁ ትመለሳላችሁ፣ በላቸው።”
ብዙ መላእክት፡-
ሱራ 47:27 “መላእክትም ፊቶቻቸውንና ጀርቦቻቸውን የሚመቱ ሲሆኑ በገደሉዋቸው ጊዜ (ሁኔታቸው) እንዴት ይሆናል?”
መልስ
ይህ ጥያቄ ከቁጥር 11 ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ አዘዋውሮ መልስ መስጠት ነው። ነፍስ በሞት የሚወስዱ መላእክት ብዙ ሲሆኑ የእነዚህን ሹማምንት የልኡካኑ አለቃ ግን መለኩል መውት ነው፦
32፥11 «በእናንተ የተወከለው መልአከ ሞት “ይወስዳችኃል”፡፡ ከዚያም ወደ ጌታችሁ ትመለሳላችሁ» በላቸው፡፡
7፥37 የሞት መልክተኞቻችንም ”የሚወስዷቸው ኾነው በመጡባቸው ጊዜ” «ከአላህ ሌላ የምትጠሯቸው የነበራችሁት የት አሉ» ይሏቸዋል፡፡ «ከእኛ ተሰወሩን» ይላሉ፡፡ እነርሱም ከሃዲያን እንደነበሩ በነፍሶቻቸው ላይ ይመሰክራሉ፡፡
8፥50 እነዚያንም የካዱትን “መላእክት ፊቶቻቸውንና ጀርባዎቻቸውን እየመቱ «የቃጠሎንም ስቃይ ቅመሱ» እያሉ በሚወስዷቸው ጊዜ ብታይ ኖሮ አስደንጋጭን ነገር ታይ ነበር”፡፡
ስለዚህ አንዱ ሱራ ላይ “ብዙ” መላእክት “ብቻ” እንጂ “አንድ” ብቻ አልወሰደም የሚል እና ሌላ ሱራ ላይ አንድ መልአክ ብቻ እንጂ ብዙ መላእክት አልወሰዱም የሚል የለም። ይህ የመጨረሻ የወረደ ስሁት ሙግት ነው። ይህ በቁርኣን ውስጥ የተለመደ አገላለጽ ነው። ለምሳሌ ወደ መርየም የመጡት መላእክት ብዙ ሲሆን እነዚህን ሹማምንት ወክሎ ሲያናግር የነበረው የልኡካኑ አለቃ ግን ጂብሪል ነው፦
3፥42 “መላእክትም ያሉትን አስታውስ”፡፡ «መርየም ሆይ! አላህ በእርግጥ መረጠሸ፡፡ አነጻሽም፡፡ በዓለማት ሴቶችም ላይ መረጠሽ፡፡»
እዚሁ ዐውድ ላይ ነጠላ መልአክ ያናግራት እንደነበረ ለመግለጽ በነጠላ “ቃለ” قَالَ ማለትም “አለ” የሚል ሃይለ-ቃል አለ፦
3፥47 ፡-ጌታዬ ሆይ! ሰው ያልነካኝ ስኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለች፡፡ ነገሩ እንዳልሽው ነው፡፡ አላህ የሚሻውን ይፈጥራል፤ አንዳችን በሻ ጊዜ ለእርሱ ኹን ይለዋል፤ ወዲውኑም ይኾናል አላት፡፡
ለማርያም የተገለጡላትን መላእክት ብዛት በተመለከተ ግልፅ ግጭት መኖሩን በቁጥር 11 ላይ በተብራራ መንገድ መልስ ሰጥተናል፡፡
ይህንን ለማስረዳት ከራሳችሁ ባይብል ናሙና ላቅርብ። በሳምንቱ የፊተኛው ቀን ወደ መቃብር የመጣው አንድ መልአክ ነው፦
ማርቆስ 16፥5 ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ”።
ማቴዎስ 28፥2 እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ” ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ።
በሳምንቱ የፊተኛው ቀን ወደ መቃብር የመጡት ሁለት መላእክት ናቸው፦
ሉቃስ 24፥4 እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ “ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ”፤
ዮሐንስ 20፥12 “ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው” የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች።
በሳምንቱ የፊተኛው ቀን ወደ መቃብር የመጡት መላእክት ብዛት ስንት ነው አንድ ወይስ ሁለት? መልሱ አንድ “ብቻ” ቢል ኖሮ እና ሌላ ቦታ ሁለት ቢል ኖሮ ግጭት ይሆን ነበር። ግን “ብቻ” የሚለው ገላጭ በዐረፍተ-ነገር ውስጥ እስከሌለ ድረስ አንዱ ያልተረከውን ሌላው አብራራው በሚል ስሌት ከተቀመጠ እንግዲያውስ ከላይ ያለው የቁርኣን አናቅጽ ላይ “ብቻ” የሚል ስለሌለ በዚህ ስሌትና ቀመር መረዳት ይቻላል።
ከላይ የጠቀስካቸውን የመሳሰሉ ልዩነቶች በግጭትነት የማይፈረጁበት ምክንያት አራቱ የወንጌል ዘገባዎች በተለያዩ አራት ሰዎች የተጻፉ በመሆናቸው ነው፡፡ የተለያዩ ጸሐፊያን አንድን ክስተት ተሰባጣሪ በሆኑ የተለያዩ መንገዶች ሊዘግቡ ይችላሉ፡፡ ቁርኣን ግን ከአንድ ግለሰብ የተገኘ መጽሐፍ ሆኖ ሳለ አንዱ ቦታ ላይ አንድ የሞት መልአክ መኖሩንና ሌላ ቦታ ላይ ብዙ የሞት መላእክት መኖራቸውን መናገሩ ግጭት አለመሆኑን ለማመን ዘጋቢው ግለሰብ ሊሳሳት የሚችል አለመሆኑን አስቀድሞ ማመንን ይጠይቃል፡፡ ለማንኛውም በዚህ ጥያቄ ላይ ለሙስሊሞች የጥርጣሬው ሚዛን እንዲያደላላቸው አንፈቅዳለን፡፡ በመግቢያችን ላይ እንዳልነው እነዚህን የግጭት ዝርዝሮች ስናቀርብ ዓላማችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምታቀርቡት የገዛ ሙግታችሁ በቁርኣን ላይ ሲተገበር ምን እንደሚፈጠር ዐይታችሁ በአባይ ሚዛን መጠቀም እንድታቆሙ ማሳሰብ ነው፡፡ መሰል ጥያቄዎችን አስቀድማችሁ ያነሳችሁት እናንተ በመሆናችሁ ከቁርኣን ውስጥ ተመሳሳይ ነገር ስናሳያችሁ መልሳችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ጥቅሶችን የምታሳዩን ከሆነ በሙግቱ መረታታችሁን ማመናችሁን ከማሳየት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ በጌታ ትንሣኤ ወቅት የተገለጡትን መላእክት ብዛት በተመለከተ በተደጋጋሚ የምታነሱትን ጥያቄ በቁርኣን ውስጥ የሚገኙ ተመሳሳይ ክፍሎችን በምትረዱበት መንገድ ለመረዳት መወሰንህ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ዓላማችን በቁርኣን ውስጥ ተቃርኖ መኖሩን ከማሳየት ይልቅ ወደ ተመሳሳይ መረዳት በመምጣት የክርስቲያን ሙስሊም ውይይት በሌሎች ጠቃሚ ርዕሶች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ነው፡፡ እናም ቢያንስ በአንድ ጥያቄ ላይም ቢሆን ዓላማችንን አሳክተናል፡፡