የቁርኣን ግጭቶች – መዳን የሚችሉት እነማን ናቸው?

መዳን የሚችሉት እነማን ናቸው?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ሙስሊሞች ብቻ፡-

ሱራ 3:85 “ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰዉ፣ ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለዉም፤ እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎች ነዉ።”

አይሁድ፣ ክርስቲያኖች፣ ሳቢያኖች፡-

ሱራ 2፥62 “እነዚያ ያመኑ፣ እነዚያም ይሁዳውያን የኾኑ፣ ክርስቲያኖችም፣ ሳቢያኖችም በአላህ እና በመጨረሻው ቀን ያመነ መልካምንም ሥራ የሠራ ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው፡፡ በእነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም፡፡”

መልስ

2፥62 “እነዚያ ያመኑ፣ እነዚያም ይሁዳውያን የኾኑ፣ ክርስቲያኖችም፣ ሳቢያኖችም “በአላህ እና በመጨረሻው ቀን ያመነ መልካምንም ሥራ የሠራ ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው”፡፡ በእነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነርሱም አያዝኑም፡፡

በጌታቸው ዘንድ ምንዳ ያላቸው ይሁዳውያን፣ ክርስቲያን እና ሳቢያን “መን” مَنْ በሚል አንጻራዊ ተውላጠ-ስም ተለይተዋል። እነዚህም በአላህ እና በመጨረሻው ቀን ያመኑና መልካምንም ሥራ የሠሩ ናቸው። “በአላህ እና በመጨረሻው ቀን ያመነ መልካምንም ሥራ የሠራ ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት።

“በአላህ እና በመጨረሻው ቀን” ማመን የኢማን ማዕዘናትን ያቅፋል፥ በአላህ እና በመጨረሻው ቀን ማመን መካከል በመላእክቱም፣ በመጽሐፎቹም እና በመልክተኞቹም ማመን አሉ፦

4፥136 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው በዚያም በመልክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ በዚያም ከበፊቱ ባወረደው መጽሐፍ እመኑ፡፡ “በአላህ እና በመላእክቱም፣ በመጽሐፎቹም፣ በመልክተኞቹም እና በመጨረሻውም ቀን የካደ ሰው” ከእውነት የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ፡፡

ይህ ጥቅስ የተነገረው ከጣዖት አምላኪነት ገና ለመጡት ሙስሊሞች ነበር፡፡ አይሁድና ክርስቲያኖች በቅዱሳት መጻሕፍትና በነቢያት ስለሚያምኑ እንዲህ ያለ መልእክት አያሻቸውም፡፡

“በአላህ ማመን” ማለት እራሱ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም ብሎ በጣዖት መካድና በእርሱ ማመን ነው።

ክርስቲያኖችና አይሁድ አንዱንና እውነተኛውን አምላክ ያመልካሉ፡፡ ሙስሊሞች ክርስቲያናዊውን ትምሕርተ ሥላሴ በተሳሳተ መንገድ መረዳታቸው የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡  ሙሐመድ ራሱ በቁርአኑ ውስጥ እንደተናገረው የክርስቲያኖችና የሙስሊሞች አምላክ አንድ ነው፡-

“የመጽሐፉን ባለቤቶችም በዚያች እርሷ መልካም በሆነችው ክርክር እንጂ አትከራከሩ፤ ከነሱ ነዚያን የበደሉትን ሲቀር በሉም፦ በዚያ ወደኛ በተወረደው፣ ወደናንተም በተወረደው አመንን፤ አምላካችንም አምላካችሁም አንድ ነው፤ እኛም ለርሱ ታዛዦች ነን።”

ሙሐመድ እንዲህ ያለ ምስክርነት ከሰጠ በኋላ ከነቢያት መጻሕፍት ጋር የሚጣረስ “መገለጥ” መናገሩና ሥላሴን መካዱ ሐሰተኛነቱን ከማረጋገጥ ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡

ሳቢያኖችም ቢሆኑ በአንድ አምላክ ያምናሉ፤ “ላ ኢላ ሀ ኢለላህ” (አምላክ የለም ከአላህ በስተቀር) የሚለው እስላማዊ የእምነት መግለጫ ከእነርሱ ነው የተኮረጀው፡፡ የእስላም ነቢይ “መሐመደን ረሱል አላህ” የሚለውን በመጨመር አሰለመው እንጂ፡፡ አል-ጠበሪ በሱራ 2፡62 ላይ በሰጠው ሀተታ መሠረት አብድ አል-ረህማን ኢብን ዘይድ የተሰኘ የስምንተኛው ክፍለ ዘመን ሙስሊም ሊቅ እንደዘገበው የአረብ ፓጋኖች ሙሐመድና ተከታዮቹን ሳቢያኖች እያሉ ይጠሯቸው ነበር፤ ለዚህም ምክንያቱ “ላ ኢላ ሀ ኢለላህ” ማለታቸው ነበር https://www.altafsir.com/Tafasir.asp?tMadhNo=0&tTafsirNo=1&tSoraNo=2&tAyahNo=62&tDisplay=yes&Page=2&Size=1&LanguageId=1 ፡፡ በሙሐመድ ዘመን የነበሩ ሰዎች ሙሐመድን “አስ-ሳቢ” ብለው ይጠሩት እንደነበር አል-ቡኻሪ ይናገራል። https://sunnah.com/bukhari:344

ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም ብሎ በጣዖትም የሚክድ እና በአላህ የሚያምን ሰው ለእርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ፦

2፥256 በጣዖትም የሚክድ እና በአላህ የሚያምን ሰው ለርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ፡፡ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡

31፥22 እርሱ መልካም ሠሪ ሆኖ ፊቱን ወደ አላህ የሚሰጥም ሰው ጠንካራን ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ፡፡ የነገሩም ሁሉ ፍጻሜ ወደ አላህ ነው፡፡

ለአረብ ፓጋኖች እንጂ ለሳቢያን፣ ለአይሁድም ሆነ ለክርስቲያኖች አስፈላጊ መልእክት አይደለም፡፡

“የሰጠ” ለሚለው ቃል የገባው “ዩሥሊም” يُسْلِمْ ሲሆን “ሙሥሊም” مُسْلِم እና “ኢሥላም” إِسْلَٰم የሚሉት ቃላት ከረባበት “አሥለመ” أَسْلَمَ ማለትም “ታዘዘ” “ተገዛ” ”አመለከ” “ሁሉ ነገሩን ሰጠ” ከሚል የመጣ መሆኑ አንባቢ ልብ ይለዋል። ሰው ሢሠልም ጠንካራን ዘለበት ይጨብጣል፤ ይህም ጠንካራን ዘለበት በጣዖትም የሚክድ እና በአላህ የሚያምን ሰው የሚይዘው እሥልምና ነው። አላህ ዘንድ ያለው ሃይማኖት ኢሥላም ብቻ ነው፤ ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ተቀባይ የለውም፤ እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው፦

3፥19 አላህ ዘንድ የተወደደ ሃይማኖት “ኢሥላም” ብቻ ነው፡፡

3፥85 ”ከኢሥላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከእርሱ ተቀባይ የለውም”፡፡ እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው፡፡

ስለዚህ ሳቢያን፣ አይሁድና ክርስቲያን እንደሚድኑ ለምን ተነገረ?

2፥62 ላይ የክርስትና እምነት፣ የአይሁድ እምነት እና የሳቢያን እምነት ትክክል ነው እያለ ሳይሆን ይሁዳውያን፣ ክርስቲያን እና ሳቢያን ግለሰብ በአላህ እና በመጨረሻው ቀን ያመኑ መልካምንም ሥራ የሠሩ ከሆኑ ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው። ምክንያቱም አንድ ሰው በአርካኑል ኢማን ካመነ ሙሥሊም ነውና። ግን አህሉል ኪታብ በአላህ እና በመጨረሻው ቀን ስለማያምኑ ነው በሙሥሊም አገር ውስጥ ጂዚያህ የሚከፍሉት፦

በአርካኑል ኢስላም ያመነ ሰው ሙስሊም እንጂ ሳቢያን፣ አይሁድና ክርስቲያን ተብሎ አይጠራም፡፡ ሳቢያን፣ አይሁድና ክርስቲያን ተብሎ ለመጠራት በሃይማኖታቱ ውስጥ የሚገኙ አስተምሕሮዎችን መቀበልና ማመንን ይጠይቃል፡፡ የለም፣ ከሃይማኖታቱ አስተምሕሮ በማፈንገጥ የእስልምናን አስተምሕሮ የተቀበሉ ናቸው ከተባለ ለምን በነዚህ ስሞች እንደተጠሩ ማብራራት ያስፈልግሃል፡፡

9፥29 “ከእነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ሰዎች እነዚያን በአላህ እና በመጨረሻው ቀን የማያምኑትን”፣ አላህና መልክተኛው እርም ያደረጉትንም እርም የማያደርጉትንና እውነተኛውንም ሃይማኖት የማይቀበሉትን እነርሱ የተዋረዱ ኾነው ግብርን በእጆቻቸው እስከሚሰጡ ድረስ ተዋጉዋቸው፡፡

ልብ አድርግ “አለዚነ” الَّذِينَ ማለትም “እነዚያ” ከሚለው አመልካች-ተውላጠ ስም መነሻ ላይ “ሚን” مِن ማለትም “ከ” የሚል መስተዋድ አለ።

በጣም የሰለቸን ነገር ቢኖር በየአጋጣሚው የሥነ-ልሳንና ሰዋሰው አስተማሪ ለመሆን የምታደርገው ጥረት ነው፡፡ አሁን እዚህ ጋ ይህንን ትንታኔ የሚፈልግ ግልፅ ያልሆነ ምን ነገር አለ?

ይህ የሚያሳየው ከአህሉል ኪታብ በአላህ እና በመጨረሻው ቀን የማያምኑ እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው ከአህሉል ኪታብ በአላህ እና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑ በእነርሱ ላይ ቁርኣን በሚነበብላቸውም ጊዜ “በእርሱ(በቁርኣን) አምነናል፥ እርሱ ከጌታችን የኾነ እውነት ነው፡፡ እኛ ከእርሱ(ከቁርኣኑ) በፊት ሙሥሊሞች ነበርን” ይላሉ።

የሙሐመድ ቁርኣን ከነቢያት ትምሕርት በተጻራሪ የቆመ ባዕድ መጽሐፍ ነው፡፡ አይሁድና ክርስቲያኖች በምን ሚዛን ነው የፈጣሪ ቃል አድርገው የሚቀበሉት?

ከመጽሐፉ ሰዎች ቀጥ ያሉ በሌሊት ሰዓቶች እነርሱ የሚሰግዱ ኾነው የአላህን አንቀጾች የሆነውን ቁርኣን የሚያነቡ ሕዝቦች አሉ፦

28፥52 “እነዚያ ከእርሱ(ከቁርኣን) በፊት መጽሐፍን የሰጠናቸው እነርሱ በእርሱ(በቁርኣን) ያምናሉ”፡፡

28፥53 “በእነርሱ ላይ በሚነበብላቸውም ጊዜ «በእርሱ አምነናል፡፡ እርሱ ከጌታችን የኾነ እውነት ነው፡፡ እኛ ከእርሱ በፊት ሙሥሊሞች ነበርን» ይላሉ”፡፡

3፥113 “የመጽሐፉ ሰዎች ሁሉ እኩል አይደሉም፡፡ ከመጽሐፉ ሰዎች ቀጥ ያሉ በሌሊት ሰዓቶች እነርሱ የሚሰግዱ ኾነው የአላህን አንቀጾች የሚያነቡ ሕዝቦች አሉ”፡፡

አይሁድና ክርስቲያኖች ሙሐመድን ባለመቀበላቸው ምክንያት ግራ የተጋቡትን አረብ ፓጋኖች ለማረጋጋት የተነገረ የሙሐመድ ምኞት ብቻ ነው፡፡ በሙሐመድ ዘመን አይሁድና ክርስቲያኖች በሰይፍ ከተገደዱትና ከአንዳንድ ሆድ አደሮች በተረፈ የሙሐመድን ትምሕርት በአንድ ድምፅ ነበር የተቃወሙት፡፡ በአንድ ወቅት ሙሐመድ በመዲና ወደሚገኝ የአይሁድ ምኩራብ በመግባት 12 አይሁድ እንኳ ነቢይነቱን ቢቀበሉ አላህ የአይሁድን ማሕበረሰብ ከቁጣው እንደሚያድን ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ተናግሮ ነበር፡፡ (Musnad Ahmad Ibn Hanbal, Hadith Number 23464)

እነዚህ ታዲያ ሙሥሊሞች አይደሉምን? እንዴታ! ናቸው እንጂ። የመጽሐፉም ባለቤቶች በአላህ እና በመጨረሻው ቀን ቢያምኑ እና በአላህ እና በመጨረሻው ቀን ከመካድ ቢጠነቀቁ አላህ ኃጢኣቶቻቸውን በእርግጥ ያስተሰርይ እና የመጠቀሚያ ገነቶችንም በእርግጥ ያገባቸው ነበር። ከእነርሱ ውስጥ በአላህ እና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑ ትክክለኞች ሕዝቦች አሉ፡፡

ከእነሱም ብዙዎቹ በአላህ እና በመጨረሻው ቀን በመካድ የሚሠሩት ነገር ከፋ፦

5፥65 “የመጽሐፉም ባለቤቶች ባመኑ እና ከክህደትም በተጠነቀቁ ኖሮ ከእነርሱ ኃጢኣቶቻቸውን በእርግጥ ባበስንና የመጠቀሚያ ገነቶችንም በእርግጥ ባገባናቸው ነበር”፡፡

5፥66 “ከእነርሱ ውስጥ ትክክለኞች ሕዝቦች አሉ፡፡ ከእነርሱም ብዙዎቹ የሚሠሩት ነገር ከፋ!”

ሙስሊም ለመሆን የእስልምናን መሠረታዊ አስተምሕሮ በሙሉ ሳይሸራርፉ መቀበልን ይጠይቃል፡፡ አይሁድና ክርስቲያን መሆንም የእምነታቱን መሠረታዊ አስተምሕሮዎች ሳይሸራርፉ መቀበልን ይጠይቃል፡፡ የእስልምናን አስተምሕሮ ተቀብለዋል ከተባለ በሙስሊምነት እንጂ በሃይማኖታቱ መጠራት የለባቸውም፡፡ ነገር ግን ቁርኣን በሃይማኖታቸው ነው የሚጠራቸው፡፡

ሙሐመድ ሳቢያኖች፣ አይሁድና ክርስቲያኖችን ከጎኑ ለማሰለፍ ከነበረው ጉጉት የተነሳ ሁሉም እንደሚድኑ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን የእነርሱ እስትራቴጂያዊ አስፈላጊነት ሲያከትም መጀመርያ አይሁድን በጠላትነት ከፈረጀ በኋላ (ሱራ 5፡82) ቆይቶ ደግሞ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ሁሉንም በኢ-አማኒነት ፈረጃቸው፤ እስልምናንም ብቸኛው ሃይማኖት አድርጎ አወጀ (ሱራ 9፡30፣ 3፡85)፡፡ የሙሐመድን ፖለቲካዊ አካሄድ የተገነዘበ ሰው ይህ እውነት አይጠፋውም፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን ግን ይህንን ከፖለቲካዊ አስትራቴጂ የመነጨ እርስ በርሱ የሚጣረስ አስተምሕሮ ትክክለኛ የፈጣሪ ቃል እንደሆነና ከሰብዓዊ ተጣርሶዎች የፀዳ መሆኑን ሊያስረዱን ይደክማሉ፡፡

የቁርኣን ግጭቶች