27. ያላመኑ ቤተሰቦችን መወዳጀት ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?
ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡
ተፈቅዷል፡-
ሱራ 31:15 “ለአንተ በርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር በኔ እንድታጋራ ቢታገሉህም፣ አትታዘዛቸው፤ በቅርቢቱም ዓለም፣ በመልካም ስራ ተወዳጃቸው፤ ወደ እኔም የተመለሰን ሰው መንገድ ተከተል፤ ከዚያም መመለሻችሁ ወደኔ ነው፤ ትሰሩት የነበራችሁንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ (አልነው)።”
አልተፈቀደም፡-
ሱራ 9:23 “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አባቶቻችሁና ወንድሞቻችሁ ክሕደትን ከእምነት አብልጠው ቢወዱ፣ ወዳጆች አድርጋቸሁ አትያዙዋቸው፤ ከናንተም ዉስጥ ወዳጅ የሚያደርጋቸው፣ እነዚያ እርሱ በዳዮች ናቸው፡፡”
መልስ
የወላጅ ሃቅ በኢሥላም ትልቅ ቦታ አለው፥ ወላጅን ማመስገን፣ ለወላጅ መልካም መሥራት፣ በጎ መዋል፣ መልካም ንግግር መናገር የወላጅ ሃቅ ነው፦
31፥14 ለእኔም ለወላጆችህም አመስግን በማለት አዘዝነው፡፡ መመለሻው ወደ እኔ ነው፡፡
45፥15 ሰውንም በወላጆቹ በጎ መዋልን በጥብቅ አዘዝነው፡፡
17፥23 ጌታህም እንዲህ ሲል አዘዘ፡- እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፡፡ በወላጆቻችሁም መልካምን ሥሩ፡፡ በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው፡፡ አትገላምጣቸውም፡፡ ለእነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው፡፡
6፥151 «ኑ፤ ጌታችሁ በእናንተ ላይ እርም ያደርገውን ነገር በእርሱም ያዘዛችሁን ላንብብላችሁ» በላቸው፡፡ «በእርሱ በአላህ ላይ ምንንም ነገር አታጋሩ፡፡ ለወላጆችም በጎን ሥራ ሥሩ፡፡
4፥36 አላህንም አምልኩ፤ በእርሱም ምንንም አታጋሩ፡፡ በወላጆች፣ በቅርብ ዝምድና ባለቤትም፣ በየቲሞችም፣ በምስኪኖችም፣ በቅርብ ጎረቤትም፣ በሩቅ ጎረቤትም፣ በጎን ባልደረባም፣ በመንገደኛም፣ እጆቻችሁም ንብረት ባደረጓቸው መልካምን ሥሩ፤ አላህ ኩራተኛ ጉረኛ የኾነን ሰው አይወድም፡፡
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 79, ሐዲስ 47
አቢ በክራህ እንደተረከው፦ “የአላህ መልእክተኛም አሉ፦ “ትላልቅ ወልጀሎችን ልንገራችሁን? እነርሱም፦ “አዎ የአላህ መልእክተኛ ሆይ!” እርሳቸው፦ “በአላህ ላይ ማሻረክ እና ለወላጆች ግዴለሽ መሆን ነው” አሉ”።
ነገር ግን ለወላጅም ቢሆን በትክክል ፍትሕ ቀዋሚዎች እና ለአላህ መስካሪዎች መሆን አለብን፦
4፥135 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በትክክል ፍትሕ ቀዋሚዎች በራሳችሁ ወይም በወላጆች እና በቅርብ ዘመዶች ላይ ቢኾንም እንኳ ለአላህ መስካሪዎች ኹኑ፡፡ ሀብታም ወይም ድኻ ቢኾን አላህ በእነርሱ ከእናንተ ይበልጥ ተገቢ ነው፡፡ እንዳታደሉም ዝንባሌን አትከተሉ፡፡ ብታጠምሙም ወይም መመስከርን ብትተው አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡
እዚህ አንቀጽ ላይ “ተዕዲሉ” تَعْدِلُوا የሚለው ቃል ይሰመርበት፤ ይህ ቃል የስም መደቡ “ዐድል” عَدْل ሲሆን “ፍትሕ” ማለት ነው፤ ፍትሕ ለአላህ ፍራቻ ተብሎ እና አላህ በምንሠራው ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው ተብሎ የሚደረግ ነው። ይህ ለአላህ ተብሎ የሚደረግ ፍትሕ ዝንባሌን ከመከተል ነጻ ያወጣል። አላህ ሰውንም በወላጆቹ በመልካም አድራጎትን እንድንወዳጅ ቢያዘንም ነገር ግን ወላጅ ጣዖት አምልክ ቢለን በዚህ ነጥብ በፍጹም እንዳንታዘዛቸው ከልክሎናል፦
31፥15 ለአንተ በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር “በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህም አትታዘዛቸው፡፡ “በቅርቢቱም ዓለም በመልካም ሥራ ተወዳጃቸው”፡፡ ወደ እኔም የተመለሰን ሰው መንገድ ተከተል፡፡ ከዚያም መመለሻችሁ ወደእኔ ነው፡፡ ትሠሩት የነበራችሁትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፡፡
29፥8 ሰውንም በወላጆቹ መልካም አድራጎትን አዘዝነው፡፡ ለአንተም በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ጣዖት በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህ አትታዘዛቸው፡፡ መመለሻችሁ ወደ እኔ ነው፡፡ ትሠሩት የነበራችሁትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፡፡
“በቅርቢቱም ዓለም በመልካም ሥራ ተወዳጃቸው” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት። “ተወዳጃቸው” የሚለው ቃል “ሷሒብሁማ” صَاحِبْهُمَا ሲሆን “ሷሒብ” صَىٰحِب ማለትም “ባልደረባ” ከሚለው የስም መደብ የረባ ሲሆን “ባልደረባ ሁናቸው” ማለት ነው። በመልካም ሥራ ባልደረባነት ማለት ወላጅን ማመስገን፣ ለወላጅ መልካም መሥራት፣ በጎ መዋል፣ መልካም ንግግር መናገር እና ጡረታ መጦር ወዘተ ነው። እርሱም ቢሆን በቅርቢቱም ዓለም ጉዳይ ላይ ነው። ግን በተቃራኒው፦ “ለአንተም በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ጣዖት በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህ አትታዘዛቸው” የሚለውን ሃይለ-ቃል ይሰመርበት። ይህንን ክህደት ከእምነት አብልጠው ቢወዱ እረዳቶች አድርጋችሁ አትያዙዋቸው፡፡ ከእናንተም ውስጥ እረዳት የሚያደርጋቸው እነዚያ እነርሱ በዳዮች ናቸው፦
9፥23 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! “አባቶቻችሁና ወንድሞቻችሁ ክህደትን ከእምነት አብልጠው ቢወዱ ወዳጆች አድርጋችሁ አትያዙዋቸው፡፡ ከእናንተም ውስጥ ወዳጅ የሚያደርጋቸው እነዚያ እነርሱ በዳዮች ናቸው።
እዚህ አንቀጽ ላይ “አውሊያ” أَوْلِيَاءَ በብዜት የመጣው “ወሊይ” وَلِىّ ለሚለው ብዙ ቁጥር ነው፥ “ወሊይ” ማለት “እረዳት” ማለት ነው። በመልካም በማዘዝ በመጥፎ በመከልከል ለአማኞች ወሊይ እራሳቸው አማኞች እንጂ ከሃድያን ወላጆች ወሊይ አይደሉም፦
9፥71 “ምእምንና ምእምናትም ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፡፡ በደግ ነገር ያዛሉ፤ ከክፉም ይከለክላሉ”፡፡ ሶላትንም ይሰግዳሉ፡፡ ዘካንም ይሰጣሉ፡፡ አላህንና መልክተኛውንም ይታዘዛሉ፡፡ እነዚያን አላህ በእርግጥ ያዝንላቸዋል፡፡ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና፡፡
ይህ ወደ ሺክር የሚያመራ ወዳጅነት በትንሳኤ ቀን፦ “ዋ ጥፋቴ! እገሌን ወዳጅ ባልያዝኩ ኖሮ እመኛለሁ” የሚያስብል ጸጸት ነውና እንጠንቀቅ፦
25፥28 «ዋ ጥፋቴ! “እገሌን ወዳጅ ባልያዝኩ ኖሮ እመኛለሁ”፡፡
ስለዚህ የዚህ ሁሉ ሐተታ መቋጫው ከቤተሰብ ጋር ያለ ግንኙነት ወደ ሺርክ የሚመራ ከሆነ ተከልክሏል፤ ካልመራ ግን ተፈቅዷል የሚል ነው፡፡ ቁርኣን ግን እያለ ያለው እንደርሱ አይደለም፡፡ ጥቅሶቹን ደግመን እናንብብ፡-
ሱራ 31:15 “ለአንተ በርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር በኔ እንድታጋራ ቢታገሉህም፣ አትታዘዛቸው፤ በቅርቢቱም ዓለም፣ በመልካም ስራ ተወዳጃቸው፤ ወደ እኔም የተመለሰን ሰው መንገድ ተከተል፤ ከዚያም መመለሻችሁ ወደኔ ነው፤ ትሰሩት የነበራችሁንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ (አልነው)።”
በዚህ ጥቅስ መሠረት ከሃዲ ወላጆች ወደ ሺርክ ከመጥራትም አልፈው አንድን ሙስሊም ቢታገሉት እንዳይታዘዝ ብቻ ነው የተነገረው፤ በምድራዊ ጉዳይ ግን ከእነርሱ ጋር መወዳጀት ይችላል፡፡
ሱራ 9:23 “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አባቶቻችሁና ወንድሞቻችሁ ክሕደትን ከእምነት አብልጠው ቢወዱ፣ ወዳጆች አድርጋቸሁ አትያዙዋቸው፤ ከናንተም ዉስጥ ወዳጅ የሚያደርጋቸው፣ እነዚያ እርሱ በዳዮች ናቸው፡፡”
በዚህ ጥቅስ መሠረት ደግሞ ወደ ሽርክ መጣራትና ሙስሊሙን መታገል ሳይጀምሩ በግላቸው ክህደትን ከእምነት አብልጠው በመውደዳቸው ብቻ እነርሱን መወዳጀት ተከልክሏል፡፡
ቁርኣን በአንዱ ቦታ ላይ ሙስሊሞች ወደ ሺርክ ሊመልሷቸው የሚታገሏቸውን ቤተሰቦቻቸውን መወዳጀት እንደሚችሉ የተናገረ ሲሆን በሌላ ቦታ ላይ ግን እንኳንስ ወደ ሺርክ ለመመለስ የሚታገሉትን ይቅርና በግላቸው ክህደትን ከእምነት አብልጠው የወደዱትን መወዳጀት እንደማይቻል ይናገራል፡፡ ስለዚህ ጥያቄውን ጠምዝዘህ ወደ ሌላ ወሰድከው እንጂ አልመለስከውም፡፡