የቁርኣን ግጭቶች – መልእክተኞች ሆነው የተላኩት ሰዎች ብቻ ወይስ ሌሎች ፍጥረታትም ጭምር?

29. መልእክተኞች ሆነው የተላኩት ሰዎች ብቻ ወይስ ሌሎች ፍጥረታትም ጭምር?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ጥያቄ 29

መልእክተኞች ሆነው የተላኩት ሰዎች ብቻ ወይስ ሌሎች ፍጥረታትም ጭምር?

ሰዎች ብቻ፡-

ሱራ 12:109 “ካንተ በፊትም ከከተሞች ሰዎች ወደነርሱ ራዕይ የምናወርድላቸው የሆኑን ወንዶችን እንጂ አልላክንም፤ በምድር ላይ አይኼዱምና የነዚያን ከነሱ በፊት የነበሩትን ሰዎች መጨረሻ አይመለከቱምን? የመጨረሻይቱም አገር፣ ለነዚያ ለተጠነቀቁት በእርግጥ የተሻለች ናት፤ አታውቁምን?”

ሌሎች ፍጥረታትም ተልከዋል፡-

ሱራ 22:75 “አላህ ከመላእክት ውስጥ መልክተኞችን ይመርጣል፤ ከስዎችም፣ (እንደዚሁ) አላህ ስሚ ተመልካች ነው።”

መልስ

“ወሕይ” وَحْى የሚለው ቃል “አውሓ” أَوْحَىٰٓ “ገለጠ” ወይም “አወረደ” ከሚል ግስ የመጣ ሲሆን “ግልጠተ-መለኮት” ወይም “ግህደተ-መለኮት”Revelation” ማለት ነው። አምላካችን አላህ ወሕይ የሚያወርድላቸው ነቢያት ሰዎች ብቻ ነበሩ።

ጉዳዩ “ወሕይ” ከሚል ቃል ጋር የተያያዘ ሳይሆን መልእክተኞች ሆነው ወደ ሰው ከተላኩት ፍጥረታት ምንነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቁርኣን በአንዱ ቦታ ላይ ሰዎች ብቻ እንደተላኩ ተናግሮ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ መላእክትም ጭምር እንደተላኩ ይናገራል፡፡ ጥቅሱን በጥንቃቄ አንብበው፡- “ካንተ በፊትም ከከተሞች ሰዎች ወደነርሱ ራዕይ የምናወርድላቸው የሆኑን ወንዶችን እንጂ አልላክንም…” ስለዚህ ከሙሐመድ በፊት ወደ ሰዎች የተላኩት ወሕይ (ራዕይ) የሚወርድላቸው ሰዎች ብቻ ከሆኑ ሌላ ወሕይ የሚወርድለትም ሆነ የማይወርድለት ፍጥረት አልተላከም ማለት ነው፡፡

ይህንን ያስተባበሉት ዐረብ ሙሽሪኪን፦ “ይህ ብጤያችሁ ሰው እንጅ ሌላ ነውን? በማለት ተናገሩ፦

21፥3 ልቦቻቸው ዝንጉዎች ኾነው እነዚያም የበደሉት ሰዎች መንሾካሾክን ደበቁ፡፡ ”ይህ ብጤያችሁ ሰው እንጅ ሌላ ነውን?” እናንተም የምታዩ ስትኾኑ ”ድግምትን ለመቀበል ትመጣላችሁን?”» አሉ፡፡

ዐረብ ሙሽሪኪን፦ “ይህ ብጤያችሁ ሰው እንጅ ሌላ አይደለምና ይህ መልክተኛ ምግብን የሚበላ፣ በገበያዎችም የሚኼድ ሲኾን” ምን አለው አስጠንቃቂ ይኾን ዘንድ እርሱ መልአክ አይወረድም ኖሯልን? አሉ፦

25፥7 ለእዚህም ”መልክተኛ ምግብን የሚበላ፣ በገበያዎችም የሚኼድ ሲኾን” ምን አለው ከእርሱ ጋር ”አስጠንቃቂ ይኾን ዘንድ ወደ እርሱ መልአክ አይወረድም” ኖሯልን? ”አሉ”

25፥21 እነዚያም መገናኘታችንን የማይፈሩት፦”በእኛ ላይ ለምን መላእክት አልወረደም”፡፡ ወይም ጌታችንን ለምን አናይም ”አሉ”፡ በነፍሶቻቸው ውስጥ በእርግጥ ኮሩ፡፡ ታላቅንም አመጽ አመፁ፡፡

አላህም ከዚህ በፊት አስጠንቃቂ ይኾኑ ዘንድ ወሕይ የምናወርድላቸው የኾነን ሰዎችን እንጂ ሌላን አላክንም፤ ምግብን የማይበሉ አካልም አላደረግናቸውም፤ የማታውቁም ብትኾኑ የመጽሐፉን ባለቤቶች ጠይቁ ብሎ ምላሽ ሰጠ፦

21፥7 ከአንተም በፊት ወደ እነርሱ ወሕይ የምናወርድላቸው የኾነን ”ሰዎችን እንጂ ሌላን አላክንም”፡፡ የማታውቁም ብትኾኑ የመጽሐፉን ባለቤቶች ”ጠይቁ”

21፥8 ”ምግብን የማይበሉ አካልም አላደረግናቸውም”፡፡ ዘውታሪዎችም አልነበሩም

25፥20 ከአንተ በፊትም ”ከመልክተኞች እነርሱ በእርግጥ ምግብን የሚበሉ በገበያዎችም የሚኼዱ ኾነው በስተቀር አልላክንም”

ምላሹ ትክክል አይደለም እያልን ነው፡፡ አረብ ፓጋኖች “ለምን መልአክ አይወርድም?” በማለት ለጠየቁት ጥያቄ ምላሹ “ካንተ በፊትም … ራዕይ የምናወርድላቸው የሆኑን ወንዶችን እንጂ አልላክንም” የሚል መሆን አልነበረበትም፤ ምክንያቱም ከዚያ ቀደም መላእክት ወደ ሰዎች ተልከዋልና፡፡

አላህ ጠይቁ ያለው ጠያቂዎች ዐረብ ሙሽሪኮችን መሆኑን ካየን ጠይቁ የተባሉት ጥያቄ፦ “ከነቢያችን በፊት ወሕይ ሲወርድላቸው የነበሩት ሰዎች ወይስ መልአክ? የሚለውን ነው።

አይደለም፡፡ ጥቅሱን እያጣመምክ ነው፡፡ አላህ አለ የተባለው “ካንተ በፊትም … ራዕይ የምናወርድላቸው የሆኑን ወንዶችን እንጂ አልላክንም” የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ጥያቄው አላህ ከሙሐመድ በፊት ወደ ሰዎች የላከው ወሕይ (ራዕይ) የሚወርድላቸውን ሰዎች ብቻ ወይንስ መላእክትንም ጭምር? የሚል ነው፡፡ አንተ ወሕይ የምትለዋን ቃል ማጠንጠኛ አድርገህ ለማጣመም እየሞከርክ ነው፡፡ ማጠንጠኛው ግን “ሰዎች” ወይም “ወንዶች” የሚለው ቃል ነው፡፡

ዐረብ ሙሽሪኮች ከእነርሱ ውስጥ ወደ ኾነ አንድ ሰው አላህ ወሕይ ማውረዱ ድንቅ ስለሆነባቸው ያንን ወሕይ ድግምት ነው፤ መልእክተኛውን ድግምተኛ ነው ብለው አስተባበሉ፦

10፥2 ”ሰዎችን አስጠንቅቅ”፤ እነዚያንም ያመኑትን ለእነርሱ ከጌታቸው ዘንድ መልካም ምንዳ ያላቸው መኾኑን ”አብስር”» በማለት ”ከእነርሱው” ወደ ኾነ አንድ ሰው ”ራእይን ማውረዳችን ለሰዎች ድንቅ ኾነባቸውን” ከሓዲዎቹ፡- «ይህ በእርግጥ ግልጽ ድግምተኛ ነው» ”አሉ”

38፥4 ”ከእነርሱ የሆነ አስጠንቃቂም” ስለ መጣላቸው ተደነቁ፡፡ ከሓዲዎቹም፦ ”ይህ ድግምተኛ ውሸታም ነው”» ”አሉ”

50፥2 ይልቁንም ”ከእነርሱ” ጎሳ የኾነ ”አስጠንቃቂ” ስለ ”መጣላቸው” ተደነቁ፡፡ ”ከሓዲዎቹም” «ይህ አስደናቂ ነገር ነው» ”አሉ”

አላህም ነቢያችንን”ﷺ”፦ “ለእናንተም እኔ መልአክ ነኝ አልልም፤ ቢጤያችሁ ሰው ብቻ ነኝ” በላቸው በማለት ተናግሯል፦

6:50 «ለእናንተ የአላህ ግምጃ ቤቶች እኔ ዘንድ ናቸው አልልም፡፡ ሩቅንም አላውቅም፡፡ ”ለእናንተም እኔ መልአክ ነኝ አልልም”፡፡ ወደ እኔ ”የሚወርድልኝን” እንጅ ሌላን አልከተልም» በላቸው

18፥110 «እኔ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ወደ እኔ የሚወረድልኝ ”ቢጤያችሁ ሰው ብቻ ነኝ”፡፡ የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፤ መልካም ሥራን ይሥራ፡፡ በጌታውም መገዛት አንድንም አያጋራ» ”በላቸው”

የአረብ ፓጋኖች ጥያቄም ሆነ ጥርጣሬ እዚህ ጋ ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡ “ለምን መላእክት አልተላኩልንም?” ወይንም “ለምን መላእክት አብረውት አልተላኩም?” የሚል ጥያቄ ለሚያነሱ ወገኖች “አላህ ራዕይ የሚያወርድላቸውን ሰዎች እንጂ ሌላ ፍጥረት ልኮ አያውቅም” ብሎ ምላሽ መስጠት ስህተት ነው፡፡ መላእክት ወደ ሰዎች የተላኩባቸው ጊዜያት ነበሩና፡፡

አላህ መላእክትን ወደ ነቢያት እና ወደ ሙዕሚኒን ይልክ ስለበር መላእክት መልእክተኞች ተብለዋል፦

 22፥75 “አላህ ከመላእክት ውስጥ መልክተኞችን ይመርጣል፥ ከሰዎችም እንደዚሁ ይመርጣል”፡፡  አላህ ሰሚ ተመልካች ነው፡፡

“መላእክት” በሚለው ቃል መነሻ ቅጥያ ላይ “ከ” የሚል መስተዋድድ መምጣቱ በራሱ አላህ መላእክትን እንደሚልክ እና እነዚያ መላእክት እንደ ሰው የማይመገቡ መሆናቸው ተገልጿል፦

11፥69 መልእክተኞቻችንም ኢብራሂምን በልጅ ብስራት በእርግጥ መጡት፡፡ ሰላም አሉት፡፡ ሰላም አላቸው፡፡ ጥቂትም ሳይቆይ ወዲያውኑ የተጠበሰን የወይፈን ስጋ አመጣ፡፡

11፥70 እጆቻቸውም ወደ እርሱ የማይደርሱ መኾነቸውን ባየ ጊዜ ሸሻቸው፡፡ ከእነርሱም ፍርሃት ተሰማው፡፡ «አትፍራ እኛ ወደ ሉጥ ሕዝቦች ተልከናልና» አሉት፡፡

ስለዚህ “ካንተ በፊትም … ራዕይ የምናወርድላቸው የሆኑን ወንዶችን እንጂ አልላክንም” የሚለው አባባል ስህተት ነው፡፡

“ሰዎች” በሚለው ቃል መነሻ ቅጥያ ላይ “ከ” የሚል መስተዋድድ መምጣቱ በራሱ አላህ ነቢያትን እንደሚልክ እና እነዚያ ነቢያት የሚመገቡ መሆናቸው ተገልጿል፦

25፥20 ከአንተ በፊትም ”ከመልክተኞች እነርሱ በእርግጥ ምግብን የሚበሉ በገበያዎችም የሚኼዱ ኾነው በስተቀር አልላክንም”

“መነሻ ቅጥያ ላይ “ከ” የሚል መስተዋድድ…” ብለህ በያንዳንዱ መጣጥፍህ ውስጥ የምትደጋገመው ነገር ፋይዳው ምንድነው? የሞኝ ዘፈን አስመሰለብህ እኮ!

እዚህ አንቀጽ ላይ “ኢላ” إِلَّا የሚለው አፍራሽ ቃል “ኢስቲስናዕ” اِسْتِثْنَاء‏ ማለትም “ግድባዊት”Exceptional” ሆኖ የመጣው አንጻራዊ ሆኖ ነው፥ “ምግብ የሚበሉ በገበያዎችም የሚኼዱ ኾነው በስተቀር አልላክንም” ማለት “ምግብ እዲበሉ በገበያዎችም እንዱኼዱ ኾነው ብቻ ነው የተላኩት” የሚለውን አያሲዝም። ምክንያቱም በአንጻራዊነት ስለመጣ።

እንደዚያ ያለ ሰው የለም፡፡ ጥያቄያችን “መልእክተኞች ሆነው የተላኩት ሰዎች ብቻ ወይስ ሌሎች ፍጥረታትም ጭምር?” የሚል እንጂ “ምግብ ይበላሉ አይበሉም? ገበያ ይሄዳሉ አይሄዱም   ?” የሚል አይደለም፡፡ እነዚህ ነገሮች የተጠቀሱት መልእክተኞቹ ሰው ብቻ መሆናቸውን አፅዖት ለመስጠት ነው፡፡

ለምሳሌ፦

51፥56 ጂኒን እና ሰውንም ሊያመልኩኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡

6፥164 በላቸው «እርሱ የሁሉ ጌታ ሲኾን ከአላህ በቀር ሌላን ጌታ እፈልጋለሁን ነፍስም ሁሉ በራሷ ላይ እንጅ ክፉን አትሠራም፡፡

2፥174 እነዚያ አላህ ከመጽሐፍ ያወረደውን የሚደብቁ በርሱም በመደበቃቸው ጥቂትን ዋጋ የሚገዙ እነዚያ በሆዶቻቸው ውስጥ እሳትን እንጂ አይበሉም”፡፡ አላህም በትንሣኤ ቀን አያናግራቸውም፤ ከኃጢኣት አያጠራቸውምም፡፡ ለነርሱም አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡

“ጂኒን እና ሰውንም ሊያመልኩኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም” ማለት ሰዎች እንዳይበሉ እንዳይጠጡ እንዳይጋቡ አልተፈጠሩም ማለትን አያሲዝም፥

ተሳስተሀል፡፡ ጥቅሱ የሚናገረው ስለ ሕይወት ዓላማና የመጨረሻ ግብ እንጂ ስለ አላፊው ኑሮ አይደለም፡፡ አላህ ሰዎችን የፈጠረበት ዋና ዓላማ (Ultimate Purpose) እርሱን እንዲያመልኩት ብቻ ነው፡፡ መብላት፣ መጠጣት፣ መጋባት፣ እግረ መንገድ የሚፈፀሙ እንጂ በዚህ መደብ ውስጥ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ቁርኣን ሱራ 7፡179 ላይ “ከጂን እና ከሰው ብዙዎችን ለገሃነም በእርግጥ ፈጠርን” በማለት የሰው ልጆች የተፈጠሩበትን ዋና ዓላማ በገሃነም መቃጠል አድርጎ በማቅረብ የመጀመርያ ሐሳቡን ተጣርሷል፡፡ ይህንን ግጭት በ ቁጥር 2 ላይ አንስተናል፤ አንተም ምላሽ መስጠት ተስኖሃል፡፡

“ነፍስም ሁሉ በራሷ ላይ እንጅ ክፉን አትሠራም” ማለት እራሷን ትጎዳለች ለማለት ተፈልጎ እንጂ ሌላውን ሰው አትጎዳም ማለትን አያሲዝም፥ “ሆዶቻቸው ውስጥ እሳትን እንጂ አይበሉም” ማለት ምግብ አይበሉም ማለትን አያሲዝም። ልክ እንደዚሁ ከላይ ያለውን ጥቅስ በዚህ ልክና መልክ መረዳት ይቻላል።

የነዚህ ጥቅሶች አነጋገር ጥያቄን የሚያስነሳ ቢሆንም የጥርጣሬ ሚዛኑ ለሙስሊሞች እንዲያደላ እንፈቅዳለን፡፡ ነገር ግን ከላይ የተነሳው ጥያቄ ከነዚህ ጥቅሶች ጋር አይመሳሰልም፡፡ ቁርኣን በአንዱ ቦታ ላይ ራዕይ ከሚወርድላቸው ሰዎች ውጪ ወደ ሰው ልጆች የተላኩ ፍጥረታት እንደሌሉ ከተናገረ በኋላ በሌሎች ቦታዎች ላይ መላእክት ወደ ሰው ልጆች የተላኩባቸውን አጋጣሚዎች በመጥቀስ እርስ በርሱ ተላትሟል፡፡ ይህንን ሃቅ እንደ ንግግር ዘይቤ ብቻ በመቁጠር በቀላሉ የምናልፈው አይደለም፡፡ ስለዚህ ጥያቄያችንን አልመለስክም፡፡

የቁርኣን ግጭቶች