የቁርኣን ግጭቶች – ሰዎችን የሚያጠመው ማን ነው? አላህ ወይንስ ሰይጣን?

3. ሰዎችን የሚያጠመው ማን ነው? አላህ ወይንስ ሰይጣን?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ጥያቄ 3

ሰዎችን የሚያጠመው ማን ነው? አላህ ወይንስ ሰይጣን?

አላህ፦

ሱራ 7፡186 “አላህ የሚያጠመውም ሰው ለእርሱ ምንም አቅኚ የለውም፡፡”

ሰይጣን፦

ሱራ 4፡119-120 “በእርግጥም አጠማቸዋለሁ ከንቱም አስመኛቸዋለሁ… የማይፈፀመውን ተስፋ ይሰጣቸዋል ያስመኛቸዋልም፡፡ ሰይጣንም ለማታለል እንጂ አይቀጥራቸውም”

“ሂዳያህ” هداية የሚለው ቃል “ምሪት” ማለት ሲሆን “ሁዳ” هُدً ማለትም “መሪ” ከሚለው ቃል የመጣ ነው፣ የሂዳያህ ተቃራኒ ደግሞ “ደላላህ” ضاله ሲሆን “ጥመት” ማለት ሲሆን “ደላል” ضلال ማለትም “ጠማማ” ከሚለው ቃል የመጣ ነው፣ አላህ በቁርኣን ከገለጻቸው ስሞቹ መካከል “አል-ሃዲ” اللَهَادِ ሲሆን ትርጉሙ “አቅኚ” አሊያም “መሪ” ማለት ነው፦

22፥54 አላህም እነዚያን ያመኑትን ወደ ቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ መሪ ነው፡፡

25፥31 እንደዚሁም ለነቢዩ ሁሉ ከአመጸኞች የኾነ ጠላትን አድርገናል፡፡ “መሪ እና ረዳትም በጌታህ በቃ”፡፡

“ሃዲ” لَهَادِ ማለት “አቅኚ” ከሆነ የአቅኚ ተቃራኒ ቃል ደግሞ “ሙዲል” مُضِلٌّ ሲሆን ትርጉሙ “አሳሳች” አሊያም “አጥማሚ” ማለት ነው፣ በቁርኣን አንድም ቦታ ላይ አላህ “ሙዲል” ተብሎ አይታወቅም፣ የሚሺነሪዎች ሙግት ዜሮ ገባ፣ ነገር ግን ሙዲል የተባለው ሸይጣን ነው፦

28፥15 ይህ ከሰይጣን ሥራ ነው፡፡ እርሱ ግልጽ “አሳሳች” ጠላት ነውና አለ፡፡

ሙስሊሙ ወገናችን በጠቀሰው ሱራ 28፡15 ላይም ሆነ  እኛ በጠቀስናቸው ሁለቱ ጥቅሶች ውስጥ ለአላህ አጥማሚነትና ለሰይጣን አጥማሚነት የገባው የአረብኛ ቃል ከተመሳሳይ ስርወ ቃል የተገኘ ነው፡፡ አላህ “ለሚያጠመው” ለሚለው يُضْلِلِ (ዩድሊሊ) የሚል ቃል የገባ ሲሆን ሰይጣን “አጠማቸዋለሁ” ሲል ደግሞ وَلَأُضِلَّنَّهُمْ (ወላኡዲለነሁም) የሚል ቃል ነው የገባው፡፡ ሁለቱም ضاله (ዳላህ) ወይም “ጥመት” ከሚለው ተመሳሳይ ቃል ጋር የተዛመዱ ናቸው፡፡ ስለዚህ የአላህ ተግባርና የሰይጣን ተግባር በተመሳሳይ የአረብኛ ቃል ተገልጿል፤ እናም ሙስሊሙ ወገናችን ሰይጣን በሌላ ቦታ “ሙዲል” መባሉን በመጥቀስ የተናገረው ነገር “አላህ ያጠምማል ነገር ግን አጥማሚ አልተባለም” የሚል ትርጉም አልባ ሙግት ነው፡፡ ዋናው ነገር ስም ሳይሆን ተግባር ነው፡፡ አላህም ሆነ ሰይጣን በተመሳሳይ ተግባር ውስጥ ተሳትፈዋል፤ እናም አንዱ አጥማሚ ተብሎ ሌላው አለመባሉ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡

ሸይጣን አጥማሚነቱ የተገለጸው በስም መደብ “አጥማሚ” ተብሎ ነው፣ ይህም የሸይጣን መደበኛ ባህርይ መሆኑ ያስገነዝባል፣ ነገር ግን አላህ አቅኝነቱ የተገለጸው በስም መደብ “አቅኚ” ተብሎ ሲሆን ይህም የአላህን መደበኛ ባህርይ መሆኑ ያስገነዝባል፣ በቁርኣን አላህ እደሚያጠም በግስ መደብ “ያጠማል” የሚል ቃል ተቀምጧል።

ዋናው ስም ሳይሆን ግብር ነው፡፡ “ያጠምማል ግን አጥማሚ ሳይሆን አቅኚ ነው” ብሎ ማለት ትርጉም አይሰጥም፡፡ ይህ እስልምና የሽብር ሃይማኖት ሆኖ ሳለ “ኢስላም ማለት ሰላም ማለት ስለሆነ እስልምና የሰላም ሃይማኖት ነው” እንደምትሉት ዓይነት ከንቱ ሙግት ነው፡፡ በተግባር አሸባሪ በስም ግን ሰላም ቢሆን ፋይዳ የለውም፡፡ አላህ በተግባር አጥማሚ ሆኖ በስም አቅኚ መባሉም እንደዚያው ነው፡፡

አላህ ያጠማል ማለት ሂዳያ አይሰጥም ማለት ነው። ለእነማን ነው ሂዳያ የማይሰጠው? ስንል የኢሥላም መልእክት ሰምተው ሆን ብለው ካስተባበልሉ አዎ አላህ ሂዳያ አይሰጥም። እውነትን ከመስማትህና ከማወቅህ በፊት በፍጹም ማንምም አያጠምም። ከእውነት በተዘነበልክ ጊዜ አላህ ልብህን አዘነበለብህ፤ አላህም እውነት ከመቀበል ይልቅ ያመጸን አመጸኛ አያቀናም፤ አላህ በሕዝቦች ዘንድ ያለውን ጸጋ በነፍሶቻቸው ያለውን ኹኔታ በራሳቸው እስከሚለውጡ ድረስ ሂዳያን በመንሳት አይለውጥም፦

ይህ ለመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ይሠራል፤ ለቁርአኑ አላህ ግን በፍፁም አይሠራም፡፡ ለምን ይህንን እንዳልን በቀጣይነት ግልፅ ስለሚሆን ማንበባችሁን ቀጥሉ፡፡

61፥5 ”ከእውነት በተዘነበሉም ጊዜ አላህ ልቦቻቸውን አዘነበላቸው፡፡ አላህም አመጸኞችን ሕዝቦች አያቀናም”፡፡

13፥11 አላህ በሕዝቦች ዘንድ ያለውን ጸጋ በነፍሶቻቸው ያለውን ኹኔታ እስከሚለውጡ ድረስ አይለውጥም፡፡ አላህም በሰዎች ላይ ክፉን በሻ ጊዜ ለእርሱ መመለስ የለውም፡፡ ለእነርሱም ከእርሱ ሌላ ምንም ተከላካይ የላቸውም፡፡

“እመኑ” ተብሎ ጥሪ ቀርቦላቸው፣ ስለ እምነት ተነግሯቸው፣ መልክተኛውም እውነት መኾኑን ተመስክሮላቸው፣ የተብራሩ አንቀጾችም ከመጡላቸው በኋላ የካዱን ሕዝቦች አላህ እንዴት ያቀናል! አላህ በዳዮችንም ሕዝቦች አያቀናም፦

4፥170 እናንተ ሰዎች ሆይ! መልክተኛው እውነትን ከጌታችሁ አመጣላችሁ፡፡ “እመኑም” ለእናንተ የተሻለ ይኾናል፡፡ ብትክዱም አትጐዱትም”፡፡ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ነውና፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡

3፥86 ከእምነታቸው እና መልክተኛውም እውነት መኾኑን ከመሰከሩ የተብራሩ አንቀጾችም ከመጡላቸው በኋላ የካዱን ሕዝቦች አላህ እንዴት ያቀናል! አላህ በዳዮችንም ሕዝቦች አያቀናም፡፡

3፥125 ”አላህም ሊመራው የሚሻውን ሰው ልቡን ለኢሥላም ይከፍትለታል፡፡ ሊያጠመውም የሚሻውን ሰው ደረቱን ጠባብ ቸጋራ ወደ ሰማይ ለመውጣት አንደሚታገል ያደርገዋል”፡፡

አላህ ሆን ብሎ ሰዎችን እንደሚያጠምና አስቀድሞ በመወሰን አጥምሞ እንደፈጠረ የሚናገሩ ጥቅሶች በቁርኣን ውስጥ ስለሚገኙ የተሟጋቹ ትንታኔም ሆነ የጠቀሳቸው የቁርኣን ጥቅሶች በሙሉ ዋጋ የላቸውም፡፡

በቁርኣን መሠረት አላህ ሰዎችን የሚያጠመውም ሆነ የሚያቀናው በዘፈቀደ ነው፡፡ የፈለገውን ያጠማል የፈለገውን ያቀናል፤ ይህንን የሚወስነው የሰዎቹ ሁኔታ ሳይሆን የአላህ የግል ምርጫና ፈቃድ ብቻ ነው፡-

ሱራ 16፡93 “አላህ በሻም ኖሮ አንዲት ህዝብ ባደረጋችሁ ነበር ግን የሚሻውን ሰው ያጠማል የሚሻውንም ሰው ያቀናል፡፡ ትሰሩት ከነበራችሁትም ሁሉ ትጠየቃላችሁ፡፡”

ሚሽካት አል መሳቢህ የሐዲስ ስብስብ ውስጥ እንደተገለጸው ሙሐመድ ነጮች ለገነት እንደተፈጠሩና ጥቁሮች ደግሞ ለገሃነም እንደተፈጠሩ ተናግሯል፡-

አቡ ደርዳ እንዳወራው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡– ‹‹አላህ አዳምን በፈጠረ ጊዜ የቀኝ ትከሻውን መታና እንደ ምስጥ የነጡ ነጫጭ ዘሮች ወጡ፡፡ የግራ ትከሻውን ሲመታ ደግሞ እንደ ከሰል የጠቆሩ ጥቁር ዘሮች ወጡ፡፡ ከዚያም ከቀኝ ትከሻው የወጡትንገነት ትገባላችሁ ምንም ግድ የለኝምአላቸው፡፡ ከግራ ትከሻ የወጡትን ደግሞእነዚህ ለገሃነም የተዘጋጁ ናቸው ምንም ግድ የለኝምአለ፡፡ ይህ ሐዲስ በአሕመድ የተላለፈ ነው፡፡” (Al-Tirmidhi Hadith, Number 38; ALIM CD ROM Version) እንዲሁም  (Mishkat Al Masabih, English translation with explanatory notes by Dr. James Robson [Sh. Muhammad Ahsraf Publishers, Booksellers & Exporters, Lahore-Pakistan, Reprint 1990], Volume I, Chapter IV, Book I.- Faith, pp. 31-32)

ለሰዎች እንዲያምኑም ሆነ እንዳያምኑ የሚፈቅደው አላህ ራሱ ነው፡-

ሱራ 10፡100 “ለማንኛዋም ነፍስ በአላህ ፈቃድ ቢሆን እንጂ ልታምን (ችሎታ) የላትም፡፡ (አላህ ለከፊሎቹ እምነትን ይሻል)፡፡ በእነዚያም በማያውቁት ላይ ርክሰትን ያደርጋል፡፡”

ስለዚህ በቁርኣንና በእስላማዊ ሐዲሳት መሠረት አላህ ገነትና ገሃነም የሚገቡትን አስቀድሞ ለይቶ ከፈጠረ፤ የሚሻውን ሰው በዘፈቀደ የሚያጠም ከሆነ፤ ማንም ማመንም ሆነ አለማመን የሚችለው አላህ ከፈቀደ ብቻ ከሆነ ለሰዎች መጥመምም ሆነ መቃናት በቀጥታ ኃላፊነቱ የአላህ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ሰይጣንም በፊናው ሰዎችን የማጣመም ተግባር የሚፈፅም ሲሆን የሰዎች ነፃ ፈቃድ ከስሌቱ ውጪ ነው፡፡ ከዚህ በተፃራሪ የሚናገሩት የቁርኣን ጥቅሶች ከዚህ ግልፅ የቁርኣን ሐሳብ ጋር የሚጋጩ በመሆናቸው እነርሱን መጥቀስ ሌላ ግጭት መፍጠር እንጂ የመጀመርያውን ግጭት አይፈታም፡፡

አላህ ይፈትናል ማለት እና ሸይጧን ይፈትናል ማለት ለየቅል እንደሆነ ሁሉ አላህ ያጠማል ማለት እና ሸይጣንም ያጠማል ማለት ለየቅል ነው። እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው። ሰይጣን ፈታኝ ነው፦

ዘፍጥረት 22፥1 ከእነዚህም ነገሮች በኋላ “እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው”፥

ማቴዎስ 4፥3 “ፈታኝም” ቀርቦ፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው።

እግዚአብሔር ፈታኝ ሰይጣን ነውን? ማነው ፈታኝ? እግዚአብሔር ወይስ ሰይጣን?

በቁርኣን መሠረት የአላህ ማጥመምም ሆነ የሰይጣን ማጥመም ግቡ አንድ ነው፤ እርሱም ሰዎችን ገሃነም መክተት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ግን የእግዚአብሔር ፈተና እምነታችንን ማሳደግ፣ ማጥራትና እኛን ወደ ራሱ ማቅረብ ሲሆን የሰይጣን ፈተና ግን እኛን በኃጢአት መጣልና ከእግዚአብሔር መነጠል ነው፡፡ በአማርኛ ሁለቱም ፈተናዎች “ፈተና” ተብለው የተቀመጡ ቢሆንም በእንግሊዘኛ ግን የእግዚአብሔር ፈተና “Test” የተባለ ሲሆን የሰይጣን ፈተና ግን “Temptation” ተብሏል፤ ስለዚህ ሁለቱ ለየቅል ናቸው፡፡ ሙግትህ ትርጉም አይሰጥም፡፡

እግዚአብሔር አጥፊ ተብሏል። ሰይጣንም አጥፊ ተብሏል፦

ዘጸአት 12፥12 እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ አገር አልፋለሁ፥ “በግብፅም አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ”።

ዕብራውያን 11፥28 “አጥፊው” የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ።

ራእይ 9፥11 “በእነርሱም ላይ ንጉሥ አላቸው እርሱም የጥልቅ መልአክ ነው፥ ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን በግሪክም አጶልዮን ይባላል”።

በዕብራይስጥ “አብዶን” ማለት እና በግሪክ “አጶልዮን” ማለት ትርጉሙ “አጥፊ” ማለት ነው። እግዚአብሔር የጥልቁ መልአክ ሰይጣን ነውን? ማነው አጥፊ? እግዚአብሔር ወይስ ሰይጣን?

የማይገናኙ ነገሮችን ለማገናኘት እየጣርክ ነው፡፡ ሲጀመር የጥልቁ መልአክ “ሰይጣን ነው” የሚል ግልፅ ማስረጃ የለም፡፡ ማንነቱ ለተለያዩ ትርጉሞች ክፍት ነው፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ያጠፋ ዘንድ በጥልቁ ላይ የሾመው መልአክ ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን የጨቆኑትን የግብፃውያንን በኩር አጥፍቷል፡፡ እግዚአብሔር የኃጢአተኞች አጥፊ ነው፡፡ የጥልቁም መልአክ እግዚአብሔር ለእርሱ አሳልፎ የሰጣቸውን ኃጥኣን ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው፡፡ በተጨማሪም ዕብራውያን ላይ “አጥፊው” አጶሊዮን ሳይሆን “ኦሎትሬኡ” ነው የተባለው፡፡  ሁለቱ አንድ ናቸው የሚያስብል ምንም ምክንያት የለም፡፡

በቁርኣን መሠረት ግን ሰይጣን ሰዎች ገሃነም ይወርዱ ዘንድ እንደሚያጣምም ሁሉ አላህም በተመሳሳይ ሰዎች ገሃነም ይወርዱ ዘንድ በግድ የለሽነት ያጣምማል፡፡ አላህ ሰይጣን የሚፈፅመውን ክፉ ተግባር እንደሚፈፅም ስለተነገረ ነው ጥያቄ ያነሳነው፡፡ ጥያቄያችን እንዴት እውነተኛውና ፍትሃዊው አምላክ እንደ ሰይጣን ሁሉ ሰዎች ገሃነም ይወርዱ ዘንድ ሆን ብሎ ያጣምማል? የሚል እንጂ ፈጣሪ ኃጢአተኞችን ለምን ያጠፋል? የሚል አይደለም፡፡

እግዚአብሔር ሰዎችን የጠማምነትን መንፈስ በውስጣቸው በመደባለቅ ያጠማቸዋል፤ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል?

ኢሳይያስ 19፥14 እግዚአብሔር የጠማምነትን መንፈስ በውስጥዋ ደባልቆአል፤

የጥቅሱ አውድ ክፉዎች ስለነበሩት ስለ ግብፃውያን የሚናገር ነው፡፡ እናንብበው፡-

የጣኔዎስ አለቆች ፍጹም ሰነፎች ናቸው፤ ፈርዖንን የሚመክሩ ጥበበኞች ምክራቸው ድንቍርና ሆነች። ፈርዖንን፦ እኛ የጥበበኞች ልጆች የቀደሙም ነገሥታት ልጆች ነን እንዴት ትሉታላችሁ? አሁንሳ ጥበበኞችህ የት አሉ? አሁን ይንገሩህ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በግብጽ ላይ ያሰበውን ይወቁ። የጣኔዎስ አለቆች ሰነፎች ሆነዋል፥ የሜምፎስም አለቆች ተሸንግለዋል፤ የነገዶችዋ የማዕዘን ድንጋዮች የሆኑ ግብጽን አሳቱ። እግዚአብሔር የጠማምነትን መንፈስ በውስጥዋ ደባልቆአል፤ ሰካር በትፋቱ እንዲስት እንዲሁ ግብጽን በሥራዋ ሁሉ አሳቱ። (ኢሳይያስ 19፡11-14)

አዲሱ መደበኛ ትርጉም “የጠማምነትን መንፈስ” የሚለውን “የድንዛዜ መንፈስ” ይለዋል፡፡ የጥንት ግብፃውያን እጅግ ክፉዎችና ከእግዚአብሔር የራቁ ሰዎች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በኃጢአታቸው ሊያጠፋቸው ስለወደደ ለድንዛዜን መንፈስ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ይህ በኃጢአታቸው ምክንያት የመጣባቸው እንጂ እንደ ቁርአኑ አላህ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ገሃነም ይገቡ ዘንድ በግዴለሽነት አላጠመማቸውም፡፡

መክብብ 7:13 የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል?

የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር እንዲጠምሙ የሚያደርገው ጥመትን የመረጡ ኃጥአንን እንጂ ንፁሃንን አይደለም፡፡ ቀደም ሲል የአላህን አጥማሚነት ለማፅደቅ ይህንን ሙግት መጠቀምህ ለአላህ የማይሠራው አላህ በምክንያት ሳይሆን በግብታዊነት እንደሚያጣምም የሚናገሩ የቁርኣን ክፍሎች በመኖራቸው ነው (ሱራ 16፡93፣ 10፡100)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን እንደሚያጣምም ይናገራል፡-

 “እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድሀ አደጎችንና ባልቴቶችን ይቀበላል፤ የኃጢአተኞችንም መንገድ ያጠፋል።” (መዝሙረ ዳዊት 1469)

በዚህ ቦታ ላይ “የኃጢአተኞችንም መንገድ ያጠፋል” በሚለው ውስጥ “ያጠፋል የሚለው ቃል ምሳሌ 17፡13 ላይ “ጠማማ” ተብሎ ከተተረጎመው ጋር አንድ ነው፤ እርሱም “አባሥ” የሚል የእብራይስጥ ቃል ነው፡፡  እናም እግዚአብሔር ኢ-ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ንፁሃንን እንደማያጠምም መጽሐፍ ቅዱሳችን ግልጽ አድርጓል፡፡  የቁርአኑ አላህ ግን ጠማማ አድርጎ በመፍጠርና የፈለገውን በግብታዊነት በማጥመም ኢ-ፍትሃዊ ተግባር ይፈፅማል፤ እንደ ሰይጣን ሁሉ ሰዎችን ገሃነም ለመክተት በማቀድ ያጠምማል፡፡ ሁለቱ በምንም መስፈርት የሚመሳሰሉ አይደሉም፡፡

ለነገሩ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር የሆነውን ክፉን መንፈስ ይልካል፤ ይህም ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ጋር እተመካከረ ለእግዚአብሔር ያሳስትለታል፤ የሚሳሳተው ሰው እና የሚያሳስተው ክፉ መንፈስ ለእግዚአብሔር ናቸው፦

2ኛ ተሰሎንቄ 2፥12 ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፥ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል።

ይህም ከላይ ከተቀመጠው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ጥቅሱ ራሱ “በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ” በማለት ግልፅ ስላደረገ ይህንን እንደ ጥያቄ ማምጣትም አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ግልፅ ነው፡፡ እግዚአብሔር አመፀኞችን ከሚቀጣባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ጥበቃውን በማንሳት የሐሰትን አሠራር በማመን ይጠፉ ዘንድ አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ ይህ ኢ-ፍትሃዊ ከሆነው የቁርአኑ አላህ የማጥመም ተግባር ጋር በምንም መንገድ አይመሳሰልም፡፡

መሣፍንት 9፥23 እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ሰዎች መካከል ክፉን መንፈስ ሰደደ፤

አውዱን እናንብበው፡-

“እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ሰዎች መካከል ክፉን መንፈስ ሰደደ፤ የሴኬምም ሰዎች በአቤሜሌክ ላይ ተንኰል አደረጉ። ይህም የሆነው፥ በሰባ የይሩበኣል ልጆቹ ላይ የተደረገው ዓመፅ እንዲመጣ፥ ደማቸውም በገደላቸው በወንድማቸው በአቤሜሌክ ላይ፥ ወንድሞቹንም እንዲገድል እጆቹን ባጸኑአቸው በሴኬም ሰዎች ላይ እንዲሆን ነው።” (መሣፍንት 9፡23-24)

አቤሜሌክ ክፉ መስፍን ስለነበር የጌዲዎንን 70 ያህል ልጆች በአንድ ድንጋይ ላይ አርዶ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የሴኬም ሰዎች ይህ ግፍ ሲፈፀም በዝምታ ሲመለከቱና ሲተባበሩ ስለነበር፤ ግፈኛውንም አቤሜሌክን በላያቸው ስላነገሡ እግዚአብሔር አቤሜሌክንም የሴኬምንም ሰዎች ሊቀጣ ስለፈለገ እንዳይስማሙ የሚያደርግ ክፉ መንፈስ ሰደደባቸው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን በማድረጉ ኢ-ፍትሃዊ ነው ብለህ ልትከስሰው ትደፍራለህን? ይህ ከአላህ ኢ-ፍትሃዊ የማጥመም ተግባር ጋር በምን ይመሳሰላል?

1ኛ ነገሥት 22:20-23 እግዚአብሔርም፦ ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው? አለ። አንዱም እንዲህ ያለ ነገር፥ ሌላውም እንዲያ የለ ነገር ተናገረ። መንፈስም ወጣ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ፦ እኔ አሳስተዋለሁ አለ። እግዚአብሔርም፦ በምን? አለው እርሱም፦ ወጥቼ በነቢያቶቹ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም፦ ማሳሳትስ ታሳስተዋለህ፥ ይሆንልሃልም ውጣ፥ እንዲሁም አድርግ አለ። አሁንም፦ እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በላይህ ክፉ ተናግሮብሃል።

አክዓብ ክፉ ንጉሥ ነበር፤ ነቢያቱም ለእንጀራ ብለው የሚተነብዩ ሐሰተኞች ነበሩ፡፡ እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ የነበረው ነቢዩ ሚክያስ ግን ነቢያቱ ሐሰተኞች መሆናቸውን ቢነግረውም አክዓብ ግን ወደ እስርቤት ወርውሮት የሐሰተኞቹን ነቢያት ምክር በመስማት ወደ ሰልፍ ቦታ ሄዶ ሞተ፡፡ ታሪኩ በአጭሩ ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔር ነቢያቱን እንዲየስት ለክፉ መንፈስ ፈቃድ የሰጠው ለጥቅም ብለው የሚተነቢዩ ሐሰተኞች ስለነበሩ ነው፤ አክዓብም እንዲስትና እንዲሞት የፈቀደው ክፉ ንጉሥ ስለነበረ ነው፡፡ ሆኖም አክዓብ እንዲመለስ ነቢዩ ሚክያስን በመላክ የመጨረሻ ዕድል ሰጥቶት ሁሉንም ነገር እንዲያብራራለት አድርጓል፡፡ አክዓብ ግን ልቡ ደንዳና ስለነበር ሐሰተኞችን አደመጠ፤ የሚገባውንም ቅጣት አገኘ፡፡ ይህ እግዚአብሔርን ኢ-ፍትሃዊ አያሰኘውም፡፡ ከቁርአኑ አላህ ኢ-ፍትሃዊ ተግባር ጋርም ሊነፃፀር አይችልም፡፡

ኢዮብ 12፥16 ኃይልና ጥበብ በእርሱ ዘንድ ናቸው፤ የሚስተውና የሚያስተው ለእርሱ ናቸው።

እግዚአብሔር ሉኣላዊ ሥልጣን ስላለው የወደደውን መንገድ ዓላማውን ለማስፈፀም ይጠቀማል፡፡ ስለዚህ ጥቅሱን እንዳለ ብንቀበለው የእግዚአብሔርን ሉኣላዊነት የሚገልፅ እንጂ ጥያቄን የሚፈጥር አይደለም፡፡ የኛ ጥያቄ በእግዚአብሔር ሉኣላዊ ሥልጣን ላይ ሳይሆን የቁርአኑ አላህ ከሰይጣን ጋር ኢ-ፍትሃዊ በሆነ ተመሳሳይ ተግባር ውስጥ መሳተፉ ነው፡፡ ነገር ግን አዲሱ መደበኛ ትርጉም የእብራይስጡን ሐሳብ በትክክል በሚገልፅ መንገድ እንዲህ ተርጉሞታል፡- “አታላዩም ተታላዩም በእርሱ እጅ ናቸው፡፡”  ስለዚህ በዚህ ትርጉም መሠረት ያንተን ሐሳብ የሚደግፍ ምንም ነገር በቦታው ላይ የለም፡፡

እግዚአብሔር፦ “ነቢዩም ቢታለል ያንን ነቢይ ያታለልኩት እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ይለናል፤ ሕዝቅኤልን፣ ኤርሚያስን እና ኢሳይያስን ያታለላቸው እርሱ እንደሆነ እራሳቸው ይናገራሉ፦

ሕዝቅኤል 14፥9 ነቢዩም ቢታለል ቃልንም ቢናገር፥ ያንን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥

ለምን ቆርጠህ ጠቀስከው? ሙሉ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፡- “ነቢዩም ቢታለል ቃልንም ቢናገር፥ ያንን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ እጄንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ ከሕዝቤም ከእስራኤል መካከል አጠፋዋለሁ።” (ሕዝቅኤል 14፡9)

ሐሰተኛ ነቢያት ሐሰትን ሲናገሩ እግዚአብሔርን ያታለሉ ይመስላቸዋል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሐሰትን ስለወደዱ የሐሰት መንፈስ እንዲጠቀምባቸው ጥበቃውን በማንሳት አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ በክፋታቸውም ምክንያት ይቀጣቸዋል፡፡ ስለዚህ የተታለሉት እነርሱ እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ ይህ አሁንም የአላህን ኢ-ፍትሃዊ የማጣመም ተግባር ለማፅደቅ የሚረዳ አይደለም፡፡

ኤርሚያስ 20፥7 አቤቱ፥ አታለልኸኝ እኔም ተታለልሁ፥

በዚህ ቦታ “አታለልኸኝ” ተብሎ የተተረጎመው “ፓሣህ” የሚለው የእብራይስጥ ቃል ብዙ ትርጉሞች አሉት “ማታለል፣ ማነሳሳት፣ ሐሳብን ማስለወጥ፣ ወዘተ.”፡፡ ለዚህ ነው አዲሱ መደበኛ ትርጉም በግርጌ ማስታወሻው ላይ “ሐሳቤን አስለወጥኸኝ” የሚል ትርጉም በአማራጭነት ያስቀመጠው፡፡ ስለዚህ ኤርምያስ ትንቢት በመናገሩ ምክንያት ብዙ መከራ ይደርስበት ስለነበር ላለመናገር ከወሰነ በኋላ እግዚአብሔር ሐሳቡን አስለውጦት እንዲናገር እንዳደረገው ለማመልከት ይህንን አለ እንጂ እግዚአብሔር አታላይ ነው ለማለት አይደለም፡፡

የቁርኣን ሲሆን አረብኛውን እያጣቀስክ “መስተዋድድ፣ መስተፃምር፣ ቅድመ ቅጥያ፣ ገለመሌ” እያልክ ለማብራራት እንደምትጥረው ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱሱን ዋናውን እብራይስጥ በመመልከት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመረዳት ለምን አልሞከርክም?

ኢሳይያስ 63፥17 አቤቱ፥ ከመንገድህ ለምን “አሳትኸን”? እንዳንፈራህም ልባችንን ለምን አጸናህብን? ስለ ባሪያዎችህ ስለ ርስትህ ነገዶች ተመለስ።

አዲሱ መደበኛ ትርጉም የእብራይስጡን ሐሳብ በማገናዘብ እንዲህ ተርጉሞታል፡- “እግዚአብሔር ሆይ ከመንገድህ እንድንወጣ ልባችንን በማደንደን ለምን እንዳንፈራህ አደረከን? ስለ ባሮችህ ስትል ስለ ርስትህ ነገዶች ስትል እባክህ ተመለስ፡፡”

ሲጀመር ይህ የነቢዩ ጸሎት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ብዙ ነቢያትን በመላክ በመንገዱ ላይ እንዲሄዱ መክሯቸዋል፡፡ ነገር ግን እስራኤላውያን ሊሰሙ አልወደዱም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ከእነርሱ በመራቅ ለልባቸው ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ እስራኤላውያንም ብዙ ጊዜ በኃጢአታቸው ተቀጡ፡፡ እግዚአብሔር እንደ እስራኤል ራሱን የገለጠለትና የታገሰው ሕዝብ በዓለም ታሪክ ማን አለ? እነርሱ አመፀኞች ሲሆኑ በአመፃቸው ፀንተው ይቀጡ ዘንድ እግዚአብሔር ከእነርሱ መራቁ ኢ-ፍትሃዊ አያሰኘውም፡፡

እግዚአብሔር አታላይና አሳሳች ሰይጣን ነውን? ማነው አታላይና አሳሳች? እግዚአብሔር ወይስ ሰይጣን? አይ “እግዚአብሔር አታላይና አሳሳች የተባለው ሰይጣን አታላይና አሳሳች በተባለበት ስሌት አይደለም” ካላችሁ እንግዲያውስ ከላይ ያለውንም ጥያቄ በዚህ ሒሳብ ተረዱት። ይህንን ጉድ ይዞ ከላይ የቁርኣንን አናቅጽ መተቸት ማለት የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ እንደማለት ነው። አላህ ሂዳያ ይስጣችሁ፥ ለእኛም ጽናቱን!

ከአጣማሚው አላህ በተማርከው መሠረት አጥምመህ የተረጎምካቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ትክክለኛ ሐሳብ በማስቀመት ያቀረብካቸው ክሶች ገለባ መሆናቸውን አረጋግጠናል፡፡ አላህ (የተባለ አምላክ የለም እንጂ ቢኖር) ሒዳያ ለማን መስጠት እንዳለበት ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ አስቀድሞ ስለወሰነ አንተ ስለለመንከው ምንም የሚመጣ ነገር የለም፡፡ እንዲያውም እንደ ሰይጣን ሁሉ ሰዎች ገሃነም ይገቡ ዘንድ ሆን ብሎ የሚያጣምምና ገሃነምን በሰዎች ለመሙላት ምሎና ተገዝቶ ሰዎችን የፈጠረ ነው፡-

ሱራ 11፡119፡- “ጌታህ ያዘነለት ብቻ ሲቀር፤ ከመለያየት አይወገዱም፤ ለዚሁም ፈጠራቸው፤ የጌታህም ቃል፣ ገሀነምን ከአጋንንትና ከሰዎች ከሁሉም በእርግጥ እሞላታለሁ በማለት ተፈጸመች። መጨረሻው ይህ ኾነ።”

ሰይጣንን እንኳ አጥምሞ የፈጠረው ኦሪጅናል የጥመት ምንጭ ያንተ አላህ ነው፡- ሱራ 7:16-18 ፦ “ስለአጠመምከኝም ለእነርሱ በቀጥተኛው መንገድ ላይ በእርግጥ እቀመጥባቸዋለሁ አለ።”

ሱራ 15:39 “ኢብሊስ አለ «ጌታዬ ሆይ! እኔን በማጥመምህ ይኹንብኝ ለነርሱ በምድር ላይ እሸልምላቸዋለሁ፡፡”

አላህ ለሌላው ሒዳያ ሊሰጥ ይቅርና ሙስሊሞችን እንኳ ገሃነም ለመክተት አስቀድሞ ወስኗል፡-

ሱራ 19:71 “ከእናንተም ወደ እርሷ ወራጅ እንጂ አንድም የለም፡፡ መውረዱም ጌታህ የፈረደው ግዴታ ነው፡፡”

ቁርኣን ወደ ገሃነም ትወርዳለህ፤ አላህ ወስኖብሃል ይልሃል፡፡ “ሲራጥ ላይ አልፋለሁ፤ እሳት አይነካኝም” የሚል ተረት አይሠራም፡፡ “ወደ እርሷ ትወርዳለህ” ተብለሃል፡፡ የአላህ ሒዳያ አንተን እራስህን ገሃነም መክተት ሆኖ ሳለ እንዴት ስለ ሌላው ሒዳያ ልትለምን ትችላለህ?

ያንተ አላህ “ከአታላዮች ሁሉ የሚበልጥ አታላይ” መሆኑን በኩራት የሚናገር ነው፡-

ሱራ 3፡54፡- “አላህም ከአድመኞች ሁሉ በላጭ ነዉ።” ومكروا ومكر الله والله خير الماكرين “ወአላሁ ኸይሩ አል-መክሪን” ማለት አላህ ከአታላዮች ሁሉ የበለጠ አታላይ ነው” ማለት ነው፡፡ God (is) the best (of) the cheaters/deceivers.

ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸው በርካታ የቁርኣን አናቅፅ ይገኛሉ (ሱራ 7፡99፣ 8:30፣ 10:21፣ 13:42)፡፡ ነገር ግን የአማርኛ ቁርኣን ተርጓሚዎች የተለያዩ ቃላትን በመተካትና በማዛባት ቢተረጉሙም ቀጥተኛው ትርጉም አላህ ከአታላዮች ወይም አጭበርባሪዎች ሁሉ የከፋው አታላይ ወይም አጭበርባሪ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ከአላህ ስሞች መካከል አንዱ “አል-መክር” ወይም አታላዩ የሚል ነው፡፡ ብዙ የአረብኛ ዲክሺነሪዎችም ቃሉን “አታላይ፣ አጭበርባሪ፣ ተንኮለኛ፣ ወዘተ.” በማለት ይተረጉማሉ፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ግን ቅዱስ፣ ጻድቅና ፍትሃዊ ነው፡፡ ፍላጎቱ የሰው ልጆች ሁሉ ይድኑ ዘንድ ነው፤ ለዚህ ነው አንድያ ልጁን እስከመስጠት ድረስ ፍቅሩን የገለፀልን፡-

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐንስ 3፡16)

ውድ ወገናችን፤ ጥያቄያችንን አልመለስክም፤ በዚህ ሁኔታ መመለስ የምትችል አይመስለንም፡፡ አላህና ሰይጣን ሰዎችን በክፋትና በተንኮል በማጥመድ ገሃነም ለማስገባት እንደሚሠሩ ቁርኣን በግልፅ ይናገራል፡፡ ቁርኣን የሰይጣንን በሕርይ የፈጣሪ ባሕርይ በማስመሰል በማቅረብ በእውነተኛው አምላክ ላይ ተሳልቋል፡፡ ይህንን የጥፋት መንገድ ትተህ ወደ ነፍስህ ጌታ ትመለስ ዘንድ የፍቅር ጥሪ እናቀርብልሃለን፡፡ ጌታ እግዚአብሔር የልብ ዐይኖችህን በመክፈት ወደ ፍቅሩ መንግሥት ይመልስህ ዘንድ ጸሎታችን ነው፡፡

 

የቁርኣን ግጭቶች