የቁርኣን ግጭቶች – የሙሐመድ ገነት መግባት እርግጥ ነው ወይስ አይታወቅም?

30. የሙሐመድ ገነት መግባት እርግጥ ነው ወይስ አይታወቅም?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

የሙሐመድ ገነት መግባት እርግጥ ነው ወይስ አይታወቅም?

እርግጥ ነው፡-

ሱራ 48፡1-2 “እኛ ላንተ ግልጽ የሆነን መክፈት ከፈትንልህ። አላህ ከኃጥያትህ ያለፈውንና የሚመጣውን ላንተ ሊምር ጸጋውንም ባንተ ላይ ሊሞላ ቀጥተኛውንም መንገድ ሊመራህ፣ (ከፈተልህ)።”

አይታወቅም፡-

ሱራ 46:9 “ከመልክተኞች ብጤ የሌለኝ አይደለሁም በኔም በናንተም ምን እንደሚሠራም አላውቅም ወደኔ የሚወረደውን እጅግ ሌላን አልከተልም እኔም ግልጽ አስፈራሪ እንጅ ሌላ አይደለሁም በላቸው፡፡”

 መልስ

ነቢያችን ወሕይ ከመጣላቸው በኃላ በቀጥተኛው መንገድ ላይ እንደሆኑ አምላካችን አላህ ተናግሯል፦

43፥43 ያንንም ወደ አንተ የተወረደልህን አጥብቀህ ያዝ፡፡ አንተ በቀጥተኛው መንገድ ላይ ነህና፡፡

አላህ ነቢያችን በቀጥተኛ መንገድ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ጀነት ገብተውም በጀነት ያለው ፀጋ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸዋል፦

108፥1 እኛ በጣም ብዙ በጎ ነገሮችን ሰጠንህ፡፡

በዚህ አንቀጽ ላይ “በጎ ነገር” ተብሎ የተቀመጠው ቃል “ከውሰር” كَوْثَر ሲሆን በጀነት ውስጥ ያለ ከወተት የነጻና ከማር የጣፈጠ ወንዝ ነው፤ ይህ ከውሰር ለነቢያችን የተሰጠ ዋስትና ነው፦

ጃምዒ አት-ተርሚዚ መጽሐፍ 47, ሐዲስ 3684

አነስ ኢብኑ ማሊክ እንደተረከው፦ “እኛ ከውሰርን ሰጠንህ” ነቢዩም አሉ፦ ”በጀነት ወንዝ ነው፤ በጀነት ወንዝ ድንኳኖቹ ከድንጋይ የተሠሩ አየው፤ ጂብሪል ሆይ! ምንድን ነው? አልኩት፤ እርሱም ከውሰር ነው፤ አላህ ለአንተ የሰጠህ” አለኝ”።

ነቢያችን ጀነት አይደለም መግባት በተጨማሪ የጀነት ጀረጃቸውንም አላህ እንደነገረን ከላይ ያለው አንቀጽ በወፍ በረር ለቅምሻ ያክል በቂ ነው፤ ታዲያ ይህ ዋስትና እያለ አላህ ነቢያችንን “በእኔም በእናንተም ምን እንደሚሠራም ዐላውቅም” በል ሲላቸው እውን ሚሽነሪዎች እንደሚሉት “ወደ ፊት የት እንደምንገባ ዐናውቅም” በል ማለታቸውን ያሳያልን? ይህንን የተንሸዋረረና የተወላገደ መረዳት ጥንልልና ጥንፍፍ ባለ መልኩ እንየው፦

እስከ አሁን የተናገርከው በሙሉ የግጭቱን የመጀመርያ ክፍል በተመለከተ ነው፡፡ አዎን በብዙ የቁርኣንና የሐዲስ ጥቅሶች መሠረት ሙሐመድ ገነት እንደሚገባ ተነግሮለታል፡፡ ነገር ግን ከላይ በጠቀስነው ጥቅስና በብዙ ሐዲሶች መሠረት የሙሐመድ ገነት መግባት እርግጥ አይደለም፡፡ እነዚህ “ሚሽነሪዎች” ካንተ በተሻለ ቁርኣንንና እስላማዊ ምንጮችን አብጠርጥረው ስለሚያውቁ ቁጭ አድርገው ያስተምሩሃል፡፡

46፥9 ከመልክተኞች ብጤ የሌለኝ አይደለሁም፤ በእኔም በእናንተም ምን እንደሚሠራም ዐላውቅም፤ ወደ እኔ የሚወረደውን እጅግ ሌላን አልከተልም፤ እኔም ግልጽ አስጠንቃቂ እንጅ ሌላ አይደለሁም በላቸው።

ከነቢያችን በፊት የመጡት በእርግጥ ምግብን የሚበሉ፣ በገበያዎችም የሚሄዱ ሰዎች ነበሩ፣ በተመሳሳይም ነቢያችን ሰው ናቸው፣ በደረጃ እንጂ በሃልዎት ከሰው የተለዩ አልነበሩም፣ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆኑ መልክተኛ ነበሩ፦

36፥3 አንተ በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነህ።

2፥252 አንተም በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነህ፡፡

3፥144 ሙሐመድም ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፤

ነቢያችን በራሳቸውና በሰዎች ምን እንደሚከናወን የወደፊቱን ዐያውቁም፣ ያ ማለት ሰዎች የሚያስጠነቅቁበት ቅርብ ይሁን እሩቅ ዐያውቁም፣ ከሚወርድላቸው ግህደተ-መለኮት ውጪ ምንም ዐያውቁም፦

6፥50 «ለእናንተ የአላህ ግምጃ ቤቶች እኔ ዘንድ ናቸው አልልም፡፡ ሩቅንም አላውቅም፡፡ ለእናንተም እኔ መልአክ ነኝ አልልም፡፡ ወደ እኔ የሚወርድልኝን እንጅ ሌላን አልከተልም» በላቸው፡፡

7፥188 አላህ የሻውን በስተቀር ለራሴ ጥቅምንም፣ ጉዳትንም፣ ማምጣት አልችልም፣ ሩቅንም የማውቅ በነበርኩ ኖሮ ከመልካም ነገር ባበዛሁና ክፉም ነገር ባልነካኝ ነበር፤ እኔ ለሚያምኑ ሕዝቦች አስጠንቃቂና አብሳሪ እንጂ ሌላ አይደለሁም” በላቸው።

21፥109 እምቢም ቢሉ በማወቅ በእኩልነት ላይ ሆነን የታዘዝኩትን አስታወቅኋችሁ፤ የምትስፈራሩበትም ነገር ቅርብ፣ ወይም ሩቅ፣ መሆኑን ዐላውቅም፤ በላቸው።

21፥111 እርሱም ቅጣትን ማቆየት ምናልባት ለእናንተ ፈተናና እስከ ጊዜው መጣቀሚያ እንደኾነም “አላውቅም”፤ በላቸው።

ወደ ነቢያችን የሚወርደው ለቀደሙት መልክተኞች የሚወርደው የነበረው የአንድ አምላክ አስተምህሮት ነው፣ ከነቢያችን በፊት ለነበሩት መልክተኞች የተባለው ይህ የተውሒድ ተስተምህሮት ነው ነቢያችን የሚከተሉት፦

21፥108 «ያ ወደ እኔ የሚወረደው፦ ”አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው” ማለት ነው፤ ታዲያ እናንተ ፍጹም “ታዛዦች” ናችሁን» በላቸው፡፡

18፥110 እኔም ቢጤያችሁ ሰው ብቻ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚወረድልኝ፦ ”አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው” ማለት ነው”፤ የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፤ መልካም ሥራን ይሥራ፡፡ በጌታውም አምልኮ አንድንም አያጋራ» ”በላቸው”፡፡

21፥25 ከአንተ በፊትም፣ እነሆ ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና አምልኩኝ፣ በማለት ወደ እርሱ የምናወርድለት ቢሆን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም።

41፥43 ከአንተ በፊት ለነበሩት መልክተኞች የተባለው ቢጤ እንጅ ለአንተ ሌላ አይባልም፤

ስለዚህ ከላይ ያለውን አንቀጽ የወረደበትም ዐውድ ስንመለከተው ነቢያችን ጀነት ስለ አለመግባታቸው ምንም የሚያወራው ነገር የለም። ዐውዱ ለማስተላለፍ የፈለገውን በግድ ጠምዝዞ ይህን ለማለት ነው የፈለገው ብሎ ማጣመም ከሥነ-አፈታት ጥናት “hermeneutics” ጋር መላተም እና የደፈረሰ የተሳከረ መረዳት ነው፣ ይህ ሙግት የዐውድ ሙግት”contextual approach” ታሳቢና ዋቢ ያደረገ ነው።

ከላይ ያወራኸው ሁሉ ከገዛ ኪስህ የወጣ እንጂ በሐዲስም ሆነ በተፍሲር ተደግፎ የቀረበ ማብራርያ አይደለም፡፡ እኛ የምናውቀው ሙስሊም ሊቃውንት ሐዲስና ተፍሲር እያመሳከሩ ቁርኣንን ሲያብራሩ እንጂ እንዲህ እንደ አንተ በዘፈቀደ ቁርኣንን ሲተረጉሙ አይደለም፡፡ ሱራ 46:9 ላይ “ከመልክተኞች ብጤ የሌለኝ አይደለሁም በኔም በናንተም ምን እንደሚሠራም አላውቅም…” የሚለው ጥቅስ የሙሐመድን የዘላለም መዳረሻ በተመለከተ መሆኑን የተለያዩ ሐዲሶችና ሙስሊም ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ በሐዲስ እንጀምር፡-

… ኡም አል-ዓላ እንዳወራችው፡- ኡሥማን ቢን መዝዑን ከእነርሱ ጋር (ማለትም ከኡም አል-ዓላ ቤተሰብ ጋር) ለመኖር ወሰነ፤ ኡሥማን ታመመና እስከሞተበት ጊዜ ድረስ አጠባሁት፤ ከዚያም በልብሶቹ ሸፈንነው፡፡ ከዚያም ነቢዩ ወደ እኛ በመጣ ጊዜ (አስክሬኑን) እንዲህ አልኩት፡- “አቡ አስ-ሳዒብ ሆይ የአላህ እዝነት ባንተ ላይ ይሁን! አላህ እንዳከበረህ እመሰክራለሁ፡፡” ከዚያም ነቢዩ እንዲህ አሉ፡- “አላህ እዳከበረው እንዴት አወቅሽ?” እንዲህ ስል መለስኩ፡- “አላውቅም፡፡ እናቴና አባቴ መሥዋዕት ይሁኑልዎ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! (ኡሥማን ካልሆነ በስተቀር) ይህ የተገባው ማን ነው?” እሳቸውም እንዲህ አሉ፡- “እርሱ እንደሆን በአላህ ይሁንብኝ ሞት አሸንፎታል፤ መልካሙንም እመኝለታለሁ፡፡ በአላህ ይሁንብኝ እኔ የአላህ መልእክተኛ ብሆንም አላህ ምን እንደሚያደርግብኝ አላውቅም፡፡” በአላህ ይሁንብኝ ከሱ ወዲያ ማንንም ጸድቋል ብዬ መናገር አልችልም… (ሳሂህ አል-ቡኻሪ፣ ቅፅ 5፣ መጽሐፍ 58፣ ቁጥር 266)

ከላይ ከተጠቀሰው ሐዲስ በግልፅ እንደሚታየው ሴትዮዋ ኡሥማን ከሞት በኋላ መልካም ነገር እንደሚገጥመው በመናገሯ ምክንያት ሙሐመድ ግራ ሲጋባና እንዴት ልታውቅ እንደ ቻለች ሲጠይቃት እንመለከታለን፡፡ ከዚያም በመቀጠል “በአላህ ይሁንብኝ እኔ የአላህ መልእክተኛ ብሆንም አላህ ምን እንደሚያደርግብኝ አላውቅም” በማለት በአላህ ስም ምሎ ከሞት በኋላ ምን እንደሚገጥመው አለማወቁን ተናግሯል፡፡ ይህም ሱራ 46፡9 ስለ ሙሐመድ የዘላለም ፍጻሜ የሚናገር መሆኑን የሚያረጋግጥ ሲሆን ያንተን ትርጓሜ መሠረት የለሽነት የሚያሳይ ነው፡፡

ኢብን ሐጃር አል-አስቀላኒ የተሰኙት ታላቅ ሊቅ ይህ ሐዲስ ከሱራ 46፡9 ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ (Ibn Hajar al-Asqalani, Fathul Bari, Kitab al-Janaaiz, Bab al-Dukhool ‘Ala al-Mayyit Ba’d al-Mawt izhaa Adraja fi Akfaanihi, Commentary on Hadith no. 1166)

ታዋቂው ሱኒ ሐታች ኢብን ከሢር ጥቅሱን ሲያብራሩት ስለ ሙሐመድ የዘላለም ሕይወት የሚናገር መሆኑን በመቀበል ነገር ግን የሙሐመድ ኃጢአቶች ይቅር እንደተባሉለት በሚናገረው ጥቅስ የተሻረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኢብን ከሢር ጥቅሱ “ተሸሯል” ብለው ማለታቸው የሙሐመድን ገነት መግባት በእርግጠኝነት ከሚናገሩት ጥቅሶች ጋር ማስታረቅ እንደቸገራቸው ማሳያ ነው፡፡ እርስ በርስ የሚሻሻሩ ጥቅሶች መጣረሳቸው ግልፅ ነውና፡፡ ኢብን ከሢር ከላይ የቀረበውን ሐዲስ በመጥቀስም ማንም ሰው ገነት መግባቱን በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡ ጥቅሱን በተለየ መንገድ የተረጎሙ ሐታቾች ቢኖሩም በሐዲስ የተደገፈውና ትክክለኛው ትርጓሜ ይህ ነው፡፡ (https://quranx.com/tafsirs/46.9)

ስናጠቃልል ቁርኣን በብዙ ቦታዎች ላይ ሙሐመድ ገነት እንደሚገባ ቢናገርም ሱራ 46፡9 ላይ ከዚህ ጋር የሚጣረስ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ይህ ደግሞ በሐዲስና በሊቃውንቱ የተረጋገጠ እውነታ ነው፡፡

ሲጀመር የሰው ልጆች የዘለዓለም ዋስትና የሚኖራቸው ነቢያትና ሐዋርያት በመሰከሩለት በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ሙሐመድ ራሱን ለማፅናናት ስለ መዳኑ በቁርኣን ውስጥ ደጋግሞ ቢናገርም ጥርጣሬውን መደበቅ አልቻለም፡፡ ይህ ደግሞ በቁርኣንና በሐዲሳቱ ውስጥ ግጭት እንዲኖር ምክንያት ሆኗል፡፡

የቁርኣን ግጭቶች