የቁርኣን ግጭቶች – ለጦርነት ላለመዝመት ሙሐመድን ፈቃዱ የጠየቁት ሁሉ ተወቃሾች ናቸው ወይስ አይደሉም?

33. ለጦርነት ላለመዝመት ሙሐመድን ፈቃዱ የጠየቁት ሁሉ ተወቃሾች ናቸው ወይስ አይደሉም?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ሁሉም ተወቃሾች ናቸው፡-

9፡44-45 “እነዚያ በአላህና በመጨረሻዉ ቀን የሚያምኑት በገንዘቦቻቸዉና በነፍሶቻቸው ከመታገላቸው ለመቅረት ፈቃድን አይጠይቁህም፤ አላህም የሚፈሩትን ዐዋቂ ነው። ፈቃድን የሚጠይቁህ እነዚያ በአላህና በመጨረሻዉ ቀን የማያምኑት ልቦቻቸዉም የተጠራጠሩት ብቻ ናቸው፤ እነሱም በጥረጣሬያቸው ዉስጥ ይዋልላሉ።”

የማይወቀሱ አሉ፡-

9፡93 “የወቀሳ መንገዱ በነዚያ እነሱ ባለጸጋዎች ሆነዉ ሳሉ ለመቅረት ፈቃድ በሚጠይቁህ ሰዎች ላይ ብቻ ነዉ፣ ከቀሪዎቹ ጋር መኾናቸውን ወደዱ፤ አላህም በልቦቻቸው ላይ አተመባቸው፣ ስለዚህ እነሱ አያውቁም።”

መልስ

9፥44 ”እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑት በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው ከመታገላቸው ለመቅረት ፈቃድን አይጠይቁህም”፡፡ አላህም የሚፈሩትን ዐዋቂ ነው፡፡

በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑት ምዕመናን በገንዘቦቻቸውና በጉልበታቸው ጂሃድን ከመታገላቸው እንቅር ብለው ነቢያችንን ፈቃድ አይጠይቁም። ምክንያቱም በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑ ሙዕሚን ስለሆኑ በራስ ለመታገል አቅም አላቸው ለመለገስም ገንዘብ አላቸው። ግን በራስ ለመታገል አቅም የሌላቸው ደካሞች፣ በሽተኞች እንዲሁ ገንዘብ የሌላቸው ለአላህና ለመልክተኛው ፍጹም ታዛዦች ከኾኑ ባይወጡም ወቀሳ የለባቸውም፦

8፥91 በደካሞች ላይ በበሽተኞችም ላይ በነዚያም የሚያወጡት ገንዘብ በማያገኙት ላይ ለአላህና ለመልክተኛው ፍጹም ታዛዦች ከኾኑ ባይወጡም ኃጢኣት የለባቸውም”፡፡ በበጎ አድራጊዎች ላይ የወቀሳ መንገድ ምንም የለባቸውም፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡

ይቀጥልና ዐውዱ የሚወቀሱት ዐቅም ኖራቸው ትግሉን ለመቅረት ነቢያችንን ፈቃድ የሚጠይቁ ተጠራጣሪዎች ብቻ ነው፦

9፥93 የወቀሳ መንገዱ በእነዚያ እነርሱ ባለጸጋዎች ኾነው ሳሉ ለመቅረት ፈቃድ በሚጠይቁህ ሰዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ ከቀሪዎቹ ጋር መኾናቸውን ወደዱ፡፡ አላህም በልቦቻቸው ላይ አተመባቸው፤ ስለዚህ እነርሱ አያውቁም”፡፡

“አላህም በልቦቻቸው ላይ አተመባቸው” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት። እነዚህ አላህ በልቦቻቸው ላይ ያተመባቸው ከሃድያን በዐቅም ጉዳይ ቀሪዎች ከሆኑት ደካሞች ጋር መቅረትን ፈለጉ፥ እነዚህ ነቢያችንን ለመቅረት ፈቃድ የሚጠይቁት እነዚህ ዐቅም ኖሯቸው በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑት እና ልቦቻቸውም የተጠራጠሩት ናቸው፦

9፥45 ”ፈቃድን የሚጠይቁህ እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑት እና ልቦቻቸውም የተጠራጠሩት ብቻ ናቸው”፡፡ እነርሱም በጥርጣሬያቸው ውስጥ ይዋልላሉ፡፡

“ወ” وَ ማለት “እና” ማለት ሲሆን አያያዥ መስተጻምር ነው። ይህም መስተጻምር በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑት እና ልቦቻቸውም የተጠራጠሩት ለመለየት የገባ ነው። “ልቦቻቸውም የተጠራጠሩት”

በመጠራጠራቸው አላህም ልቦቻቸው ላይ ያተመባቸው ናቸው። ልቦቻቸውም የተጠራጠሩት ልባቸው ታትሟል፦

63፥3 ይህ እነርሱ በምላስ ያመኑ ከዚያም በልብ የካዱ በመኾናቸው ነው፡፡ በልቦቻቸውም ላይ ታተመባቸው፤ ስለዚህ እነርሱ አያውቁም፡፡

47፥16 እነዚህ እነዚያ በልቦቻቸው ላይ አላህ ያተመባቸው ዝንባሌዎቻቸውንም የተከተሉ ናቸው፡፡

ስለዚህ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑት በገንዘቦቻቸውና በጉልበታቸው አቅም የሌላቸው ደካሞች፣ በሽተኞች እንዲሁ ገንዘብ የሌላቸው ለመቅረት ቢጠይቁ ወቀሳ የለባቸውም። በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑት በገንዘቦቻቸውና በጉልበታቸው አቅም ያላቸው ጂሃድ ለመቅረት አይጠይቁም። እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑት ባለጸጎች ሆነው በገንዘቦቻቸውና በጉልበታቸው አቅም ያላቸው ጂሃድ ለመቅረት የሚጠይቁት ይወቀሳሉ።

ከላይ የሚገኘው “ምላሽ” ግጭቱን ለማድበስበስ የተደረገ ጥረት እንጂ ከመልስ የሚቆጠር አይደለም፡፡ እስኪ ጉዳዩን በሰከነ መንፈስ እንመልከተው፡፡

ሙሐመድ በመጀመርያው ጥቅስ ላይ ከጦርነት ዘመቻ ለመቅረት ፈቃድ የሚጠይቁት “በአላህና በመጨረሻዉ ቀን የማያምኑት ልቦቻቸዉም የተጠራጠሩት ብቻ” እንደሆኑ በመግለፅ ሁሉንም ተወቃሽ ሲያደርግ ይታያል፡-

ፈቃድን የሚጠይቁህ እነዚያ በአላህና በመጨረሻዉ ቀን የማያምኑት ልቦቻቸዉም የተጠራጠሩት ብቻ ናቸው፤ እነሱም በጥረጣሬያቸው ዉስጥ ይዋልላሉ።” (ሱራ 9፡44-45)

ይህንን ጥቅስ ያነበበ ማንኛውም ሰው “እንዴት ሁሉንም በከሃዲበት ይፈርጃል? በጤናና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ፈቃድ የሚጠይቁ ወገኖች አይኖሩም ወይ?” የሚል ጥያቄ ያድርበታል፡፡ መጀመርያ ላይ ሁሉንም በከሐዲነት የፈረጀው ሙሐመድም ይህንን ስህተት ለማረም እንዲህ ሲል ተናገረ፡-

 “የወቀሳ መንገዱ በነዚያ እነሱ ባለጸጋዎች ሆነዉ ሳሉ ለመቅረት ፈቃድ በሚጠይቁህ ሰዎች ላይ ብቻ ነዉ… (ሱራ 9፡93)

ልብ በሉ፤ መጀመርያ ላይ ፈቃድን የሚጠይቁት ከሃዲያንና ተጠራጣሪዎች ብቻ እንደሆኑ በመግለፅ ከዘጋ በኋላ ትንሽ ቆይቶ ተወቃሾቹ ባለጸጋዎች ሆነው ሳሉ ለመቅረት ፈቃድ የሚጠይቁ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ይናገራል፡፡ ሙሐመድ ተመሳሳይ ስህተት ከሠራ በኋላ ማስተካከያ ሲሰጥ ይህ የመጀመርያው አይደለም፡፡ ሱራ 4፡95 ላይ አካል ጉዳተኞችን ሳያገናዝብ ሁሉንም ከወቀሰ በኋላ አንድ አካል ጉዳተኛ ጥያቄ በማቅረቡ ምክንያት መገለጡን እንዳሻሻለ፤ ዛሬ በቁርኣን ውስጥ የሚገኘውም የተሻሻለው “መገለጥ” እንደሆነ በሳሂህ አል-ቡኻሪ ሐዲስ ውስጥ እንዲህ ተጽፏል፡-

“አል-በራ እንዳስተላለፉት፡- ‹ተቀማጮቹና በአላህ መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው የሚታገሉት አይተካከሉም› የሚል ሱራ ወርዶ ነበር (4፡95)፡፡ ነቢዩ እንዲህ አሉ፡- ‹እስኪ ዘይድን ጥሩልኝ መጻፍያ ሰሌዳ፣ የቀለም ገንቦና (እንደ ብዕር የሚያገለግል) አጥንት ያምጣልኝ…› ከዚያ፡- ‹ተቀማጮቹና በአላህ መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው የሚታገሉት አይተካከሉም… ብለህ ጻፍ› አሉት፡፡ በዚህ ጊዜ ዓይነ ስውሩ አምር ቢን ኡም መክቱም አጠገባቸው ተቀምጦ ነበር፡፡ እርሱም እንዲህ አለ፡- ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ለኔስ የሚሰጡት ትዕዛዝ ምንድነው? እኔ ዓይነ ስውር ሰው ነኝ፡፡› ስለዚህ በዚህኛው አንቀፅ ፋንታ ተከታዩ አንቀፅ ወረደ፡- ‹ከምእመናን የጉዳት ባለቤት ከኾኑት በቀር ተቀማጮቹና በአላህ መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው የሚታገሉት አይተካከሉም፡፡›” (Sahih al-Bukhari: vol. 6, bk. 61, no. 512; also Sahih Muslim: bk. 20, no. 4676-4677)

ከላይ በሚገኙት ጥቅሶች ውስጥ የሆነው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ሙሐመድ በጦርነቱ ወቅት በነበረው ግርግር ምክንያት በተረበሸ ስሜት ውስጥ ሆኖ ፈቃድ የተጠቁትን በሙሉ በከሃዲነት ፈረጀ፤ ትንሽ ሲረጋጋ ደግሞ ሁሉም ከሃዲዎች እንዳልሆኑና የእውነት የተቸገሩ ሰዎች መኖራቸውን አስተዋለ፤ እናም የመጀመርያ ንግግሩን አረመ፡፡ ከዚህ የተለየ ምንም ተዓምር የለም፡፡ ከፈጣሪ ዘንድ የሆኑ መገለጦች ፍፁማን በመሆናቸው እንዲህ ያሉ ማሻሻያዎች አያሹዋቸውም፡፡ ይህንን ፍፁም ሰብዓዊ የሆነ የቁርኣን ገፅታ ማየት የተሳነው ሰው ጭፍን አማኝ መሆን አለበት፡፡

 

የቁርኣን ግጭቶች