የቁርኣን ግጭቶች – ሙሴ ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት በተላከ ጊዜ ያመኑለት ጥቂት ወገኖቹ ብቻ ወይንስ የግብፅ ደጋሚዎችም ጭምር?

34. ሙሴ ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት በተላከ ጊዜ ያመኑለት ጥቂት ወገኖቹ ብቻ ወይንስ የግብፅ ደጋሚዎችም ጭምር?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ጥቂት እስራኤላውያን ብቻ፡-

10፡83 “ለሙሳም ከፈርዖንና ከሹማምንቶቻቸው ማሰቃየትን ከመፍራት ጋር ከወገኖቹ የኾኑ ጥቂቶች ትውልዶች እንጂ አላመኑለትም፡፡ ፈርዖንም በምድር ላይ በእርግጥ የኮራ ነበር፡፡ እርሱም በእርግጥ ወሰን ካለፉት ነበር፡፡”

የግብፅ ደጋሚዎችም ጭምር፡-

7፡120-122 “ድግምተኞችም ሰጋጆች ኾነው ወደቁ። አሉ፦ በዓለማት ጌታ አመንን፤ በሙሳና በሃሩን ጌታ።” (እንዲሁም 20፡56-73፣ 26፡29-51)

መልስ

20፥70 ”ድግምተኞቹም ሰጋጆች ኾነው ወደቁ፡፡ «በሃሩንና በሙሳ ጌታ አመንን» አሉ”፡፡

እዚህ አንቀጽ ላይ እያወራ ያለው ስለ ድግምተኞቹ መሆኑን ልብ ይለዋል፣ ድግምተኞቹ የሙሳ አምላክ በሰራው ታምር አምነዋል፦

26፥47 እነሱም አሉ «በዓለማት ጌታ አመንን”፡፡

እዚህ ድረስ ከተግባባን ይጋጫል የተባለውን ሁለተኛውን አንቀጽ እስቲ እንመልከት፦

10፥83 ለሙሳም ከፈርዖንና ከሹማምንቶቻቸው ማሰቃየትን ከመፍራት ጋር ”ከወገኖቹ የኾኑ ጥቂቶች ትውልዶች እንጂ አላመኑለትም”፡፡ ፈርዖንም በምድር ላይ በእርግጥ የኮራ ነበር፡፡ እርሱም በእርግጥ ወሰን ካለፉት ነበር፡፡

“ወገኖቹ” በሚለው ቃል መነሻ ቅጥያ ላይ “ከ” የሚል መስተዋድድ ይጠቀማል። ስለዚህ ከወገኖቹ ጥቂት እንጂ አላመኑም፥ ግን ከወገኖቹ ውጪ ድግምተኞቹ በሃሩንና በሙሳ ጌታ አምነዋል። ሲቀጥል “ቀውም” قَوْم የሚለው የዐረቢኛ ቃል በአንድ አካባቢ ተመሳሳይ ባህል፣ ቋንቋ፣ አኗኗር፣ ታሪክ፣ መንግሥት እና ቦታ ያለው ማህበረሰብን ያመለክታል። ይህንን ከተረዳን ድግምተኞቹስ ከጥቂት ትውልድ መካከል የማይሆኑበት ምን ምክንያት አለው? አላህ ሙሳን ወደ ህዝቦቹ “በታምራት” እንደላከው እነዚያም ህዝቦች “ፈሮዖንና ሹማምንቶቹ” የሚጠቀልል መሆኑን ለማመልከት፦ “ወደ ፈሮዖንና ወደ ሹማምንቶቹ በእርግጥ ላክን” በማለት ይናገራል፦

14፥5 ሙሳንም ”ወገኖችህን ከጨለማዎች ወደ ብርሃን አውጣ አላህንም ቀኖች አስገንዝባቸው በማለት በተዓምራታችን በእርግጥ ላክነው”፡፡

43፥46 ”ሙሳንም በተዓምራቶቻችን ወደ ፈርዖንና ወደ ሹማምንቶቹ በእርግጥ ላክን”፡፡ «እኔ የዓለማት ጌታ መልክተኛ ነኝ» አላቸውም፡፡

ከሹማምቶቹ መካከል ድግምተኞቹ የሙሳ አምላክ በሰራው ታምር አምነዋል።

ይህ ምላሽ ዓይን ያወጣ ማጭበርበር ነው፡፡ ቁርኣን በግልፅ እንዲህ ነው ያለው፡- “ከወገኖቹ የኾኑ ጥቂቶች ትውልዶች እንጂ አላመኑለትም” “But NONE believed in Moses except some of the children of HIS people” (Muhammad Sarwar Translation)፡፡ ይህ ማለት ለሙሴ ያመኑለት ከወገኖቹ የሆኑ ጥቂት ትውልዶች ብቻ ናቸው፡፡ የእንግሊዘኛውን ትርጉም ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፡፡ “በሙሴ ማንም አላመነም፤ ከጥቂት የሕዝቦቹ ልጆች በስተቀር” የሚል ትርጉም ነው ያለው፡፡ ስለዚህ በግልፅ እንደተቀመጠው ከወገኖቹ ከሆኑት ጥቂት ትውልዶች ውጪ ያሉት ወገኖች አላመኑለትም፡፡ አባባሉ በእስራኤላውያን የተገደበ ሳይሆን እስራኤላውያንንም ሆነ ከእስራኤል ወገን ያልሆኑ ያላመኑ ወገኖችን በሙሉ ያጠቃልላል፡፡

ሢሰልስ “ኢላ” إِلَّا የሚለው አፍራሽ ቃል “ኢስቲስናዕ” اِسْتِثْنَاء‏ ማለትም “ግድባዊት”Exceptional” ሆኖ የመጣው አንጻራዊ ሆኖ ነው፥ “ከወገኖቹ የኾኑ ጥቂቶች ትውልዶች እንጂ አላመኑለትም” ማለት “ወገኖቹ ብቻ አመኑ” የሚለውን አያሲዝም። ምክንያቱም በአንጻራዊነት ስለመጣ። ለምሳሌ፦

43፥59 እርሱ በርሱ ላይ የለገስንለት ለእስራኤለም ልጆች ተዓምር ያደረግነው የኾነ “ባሪያ እንጅ ሌላ አይደለም”

“ባሪያ እንጅ ሌላ አይደለም” ማለት ነቢይና መልእክተኛ አይደለም ማለትን እንደማያሲዝ ሁሉ ከላይ ያለውን ጥቅስ በዚህ ልክና መልክ መረዳት ይቻላል።

በፍጹም አይቻልም፡፡ አንጻራዊ ሲባል ከምን ጋር እንደተነጻጸረ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ እርስ በርስ የሚጋጩ ጥቅሶችን ለማድበስበስ ሲባል ዝም ብሎ በዘፈቀደ “አንጻራዊ ሆኖ ነው የመጣው” ማለት ትርጉም አይሰጥም፡፡ በምሳሌነት ያቀረብከው ጥቅስና የግጭት መነሻ የሆነው ጥቅስ ደግሞ የሚመሳሰሉ አይደሉም፡፡ ሱራ 43፡59 ላይ “ባሪያ እንጅ ሌላ አይደለም” ማለቱ ነቢይና መልእክተኛ አይደለም የሚል ትርጉም የማይሰጥበት ምክንያት ነቢያትና መልእክተኞች የአምላክ ባርያዎች ስለሆኑ ነው፡፡ ነቢይነትና መልእክተኝነት የፈጣሪ ባርያ በመሆን መደብ ስር ስላሉ “ባርያ እንጂ ሌላ አይደለም” ቢል ግጭት አይፈጥርም፡፡ እየተነጋገርንበት ያለነው ጥቅስ ግን “ከወገኖቹ የኾኑ ጥቂቶች ትውልዶች እንጂ አላመኑለትም” የሚልና የአማኝ አላማኞችን መደባት የተመለከተ ስለሆነ ከእነ እገሌ ውጪ ሌሎች እንዳላመኑ ከተናገረ ከተጠቀሰው ቡድን ውጪ ያሉትን በሙሉ አግልሏል፡፡

ስናጠቃልል ቁርኣን በአንድ ቦታ ላይ የግብፅ ድግምተኞች በሙሴ ማመናቸውን ከተናገረ በኋላ በሌላ ቦታ ላይ ግን ከሙሴ ወገኖች የሆኑ ጥቂት ትውልዶች እንጂ ሌሎች አለማመናቸውን በመግለፅ ግልፅ ግጭት ፈጥሯል፡፡ ለዚህ ግጭት ምላሽ ለመስጠት የሞከረው ሰው ጉዳዩን በማድበስበስ ለማወናበድ ቢሞክርም አልተሳካለትም፡፡

የቁርኣን ግጭቶች