የቁርኣን ግጭቶች – ዒሳ ፈጣሪ ነው ወይስ አይደለም?

37. ዒሳ ፈጣሪ ነው ወይስ አይደለም?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ፈጣሪ ነው፡-

“ወደ እሥራኤልም ልጆች መልክተኛ የደርገዋል፤ (ይላልም) ፡-እኔ ከጌታዬ ዘንድ በታምር መጣኋችሁ። እኔ ለናንተ ከጭቃ አንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ፤ በርሱም እተነፍስበታለሁ፤ በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል።” (ሱራ 3፡49)

አይደለም፡-

በሌሎች የቁርኣን ክፍሎች ግን የኢየሱስ ፈጣሪነት ተክዷል፡፡ ይህም ግልፅ ግጭት ነው፡፡

መልስ

3፥49 ወደ እስራኤልም ልጆች መልክተኛ ያደርገዋል፡፡ ይላልም፡- «እኔ ከጌታዬ በተዓምር ወደ እናንተ መጣሁ፡፡ እኔ ለናንተ ከጭቃ እንደ ወፍ ቅርፅ እፈጥራለሁ፡፡ በርሱም እተነፍስበታለሁ፡፡ በአላህም ፈቃድ ወፍ ይኾናል፡፡ በአላህም ፈቃድ ዕውር ኾኖ የተወለደን፣ ለምጸኛንም አድናለሁ፡፡ ሙታንንም አስነሳለሁ፡፡ የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፡፡ የምታምኑ እንደኾናችሁ ለእናንተ በዚህ ውስጥ በእርግጥ ተዓምር አለበት»

“እኔ ከጌታዬ ዘንድ በታምር” መጣኋችሁ” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት። ይህ የሚያሳየው ከዛ በኃላ የሚያደርጋቸው ሥራዎች ለነብይነቱ ማስረጃ ነው።

ባንተ ማሳሰብያ መሠረት ኃይለ ቃሉን አስምረን በቀጣይ የፈጣሪ መለያና የብቻው ሥልጣን የሆነውን የመፍጠር ተግባር ሲፈፅም ከተመለከትን የተሰመረው ኃይለ ቃል ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ከእግዚአብሔር ልዩ ባሕርያት መካከል አንዱ ፈጣሪነቱ ነው፡፡ ፈጣሪነቱ ከሁሉም ነገር ልዩ የሚያደርገው ሲሆን መታወቂያው ነው፡፡ ይሁን እጂ በቁርኣን ውስጥ ኢየሱስ ይህ የፈጣሪ ልዩ ባሕርይ እንዳለው የተነገረ ሲሆን አላህ ሰዎችን በፈጠረው ተመሳሳይ መንገድ ወፎችን ሲፈጥር እንመለከታለን፡፡   በቁርኣን መሠረት ይህ የአፈጣጠር መንገድ አላህ አዳምን ከአፈር አበጅቶት የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ካለበት ጋር ተመሳሳይ ነው፡-

“ጌታህ «ለመላእክት እኔ ሰውን ከጭቃ ፈጣሪ ነኝ ባለ ጊዜ» (አስታውስ)፡፡«ፍጥረቱንም ባስተካከልኩና ከመንፈሴ በነፋሁበት ጊዜ ለእርሱ ሰጋጆች ኾናችሁ ውደቁ» (አልኩ)፡፡” (ሱራ 38፡71-75)

ይህ ኢየሱስ ወፍ ከፈጠረበት መንገድ ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው፡-

“…እኔ ከጌታዬ ዘንድ በታምር መጣኋችሁ። እኔ ለናንተ ከጭቃ አንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ፤ በርሱም እተነፍስበታለሁ፤ በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል። በአላህም ፈቃድ ዕዉር ሆኖ የተወለደን፥ ለምጸኛንም፥ አድናለሁ፤ ሙታንንም አስነሳለሁ። የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ የምታምኑ እንደሆናችሁ ለእናንተ በዚህ ዉስጥ በእርግጥ ታምር አለበት።” (ሱራ 3፡49)

እግዚአብሔር አምላክ ሕይወትን የመፍጠር ችሎታውን ከማንም ጋር አይጋራም፡፡ ዒሳ ልክ አላህ አዳምን በፈጠረበት ሁኔታ ከጭቃ ወፍ ፈጥሮ እፍ ብሎበት ሕይወት እንዲኖረው አደረገ የሚለው የቁርኣን ትረካ በሌሎች የቁርኣን ጥቅሶች መሠረት ፍጡር እንደሆነ ለተነገረ አካል የመፍጠርን መለኮታዊ ሥልጣን የሚያጎናፅፍ በመሆኑ በእስልምና አስተምሕሮ ውስጥ ግጭት እንዲኖር ሰበብ ሆኗል፡፡

ሙሳም በተመሳሳይ ከጌታችሁ በተዓምር በእርግጥ መጣኋችሁ ብሏል፦

7፥105 በአላህ ላይ ከእውነት በቀር አለመናገር ተገቢዬ ነው፡፡ ”ከጌታችሁ በተዓምር በእርግጥ መጣኋችሁ”፡፡ የእስራኤልንም ልጆች ከእኔ ጋር ልቀቅ፡፡

ሙሳ በምን አይነት ታምር ነው የመጣው? ስንል ማንኛው ሰው ሊፈጥረውን የሚችለውን ቅርፅ ሳይሆን ለደረቅ እንጨት ህይወት መስጠት የሚያስችል ታምር ነው፦

7፥106 ፈርዖንም «በተዓምር የመጣህ እንደኾንክ ከውነተኞቹ ከኾንክ እርሷን አምጣት» አለው፡፡

7፥107 ”በትሩንም ጣለ፡፡ እርስዋም ወዲያውኑ ግልጽ እባብ ኾነች”፡፡

ታዲያ የቱ ታምር ይበልጣል? የወፍ ቅርፅ መስራት ወይስ በትር እባብ ማድረግ? እባብም ሆነ ወፍ እንስሳ ናቸው፤ ልዩነቱ በትሩን እባብ ያደረገው ሆነ የጭቃውን ቅርፅ ወፍ ያደረገው አላህ ነው። ለሙሳ ነብይነት ሆነ ለኢየሱስ ነብይነት የተሰጣቸው ታምር ከራሳቸው ያገኙት ሳይሆን ከአላህ የተሰጣቸው ፀጋ ነው።

የማይመሳሰሉ ነገሮችን እያመሳሰልክ ነው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በቁርኣን መሠረት ኢየሱስ ከጭቃ የወፍ ቅርፅ ከመሥራት ያለፈ ተግባር ነው የፈፀመው፡፡ ልክ አላህ አዳምን ከጭቃ እንደሠራው የወፍ ቅርፅ ሠራ፡፡ በማስከተል ልክ አላህ አዳምን እፍ ብሎበት ሕይወት እንደሰጠው ኢየሱስም ጭቃው ላይ እፍ ብሎበት ሕይወት እንዲዘራ አደረገ፡፡ ይህ የሚያሳየው እንደ አላህ ሁሉ ኢየሱስም ሕይወት ሰጪ መሆኑን ነው፡፡ የሙሴ ተዓምር ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለሙሴ በትሩን እንዲወረውር በነገረው ጊዜ ሊከሰት ስላለው ጉዳይ ሙሴ ምንም አላወቀም ነበር፡፡ በትሩ ወደ እባብ ስትለወጥ እግዚአብሔር በሠራው ተዓምር በመደናገጥ ከእባቡ ሸሽቷል፡፡ ሙሴ በትሩ እባብ እንዲሆን ምንም ዓይነት አስተዋፅዖ አላደረገም፡፡ በትሩን የእባብ ቅርፅ አላስያዘም፤ ሕይወት እንዲዘራ እፍ አላለበትም፡፡ ይህ የሙሴ ታሪክ እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረበት በዚያው ሁኔታ ኢየሱስም ወፎችን መፍጠሩን ከሚናገረው የቶማስ ወንጌል ከተሰኘው የአፖክሪፋ መጽሐፍ ከተቀዳው የቁርኣን አፈታሪክ ሙሉ በሙሉ የተለየ ነው፡፡

ሲቀጥል “ከሀይዓህ” كَهَيْئَﺔ ማለት “ቅርጽ” ማለት ነው፣ ጥቅሱ ላይ ዒሣ ወፍ ፈጠረ አይልም፤ “የወፍ ቅርጽ” ማለትና “ወፍ” ማለት በይዘትም ሆነ በአይነት፣ በመንስኤም ሆነ በውጤት ሁለት የተለያዩ ቃላት ናቸው። ምነው የወፍ ቅርጽ መስራትና መፍጠር ፈጣሪ የሚያሰኝ ከሆነማ ዛሬ የሰው ቅርጽ የሚፈጥሩ ሞልተው የለ እንዴ? በመርካቶ ገበያ መዞሩ በቂ ነው።

አስቂኝ ነገር ነው የምታወራው፡፡ በቁርኣን መሠረት ኢየሱስ ቅርፁን ፈጠረ፣ ቅርፁ ሕይወት እንዲዘራ እፍ አለበት፣ ቅርፁም ሕይወት ዘርቶ ወፍ ሆኖ በረረ፡፡ መርካቶ ውስጥ ይህንን የሚያደርግ ሰው አይተህ ታውቃለህ? ማን ያውቃል ምናልባት ሊኖር ስለሚችል ትንሽ ዞር ዞር ብለህ ተመልከትi

ሢሰልስ “አኹሉቁ” أَخْلُقُ ማለት “አበጃለውም” ይሆናል፤ በዐማርኛ እንኳን እከሌ “የመፍጠር ችሎታው ይገርማል” ስንል መቼም አላህ ነው እያልን አይደለም፤ ዐረቢኛ ሰፊ ቋንቋ ነው “ኸልቅ” خَلْق ማለትም “መፍጠር” የሚለው ቃል “ተስዊር” تصویر ማለትም “መቅረጽ” በሚል እንደሚመጣ ዐታውቁምን? “ኸለቀ” خَلَقَ የሚለው ቃል “ሰወረ” صَوَّر ማለትም “ቀረጸ” በሚል የመጣበት ሰዋስው እንመልከት፦

37፥125 በዕልን ትገዛላችሁን? ”ከሰዓሊዎቹ ሁሉ ይበልጥ በጣም አሳማሪ የሆነውንም አምላክ ትተዋላችሁን?”

23፥14 ”ከሰዓሊዎችም ሁሉ በላጭ የሆነው አላህ ላቀ”፡፡

አየህ “ሰዓሊ” የሚለው ቃል “ኻሊቅ” خَٰلِق ሲሆን የብዙ ቁጥሩ ደግሞ “ኻሊቂን” خَالِقِين ማለትም “ሰዓሊዎች” ነው። ታዲያ “ኻሊቂን” ካለመኖር ወደ መኖር ህይወትን መስጠት ማለት ነውን? በፍጹም ቅርጽ መፍጠር ማለት ነው እንጂ ፤ “ኻሊቅ” خَٰلِق የሚለው ቃል “ሙሰዊር” مُصَوِّر ማለትም “ቅርፅን ቀራጺ” በሚል መጥቷል፤ ስለዚህ ስዕል የሚያበጁና የሚቀርፁ ሰዎችን ፈጠሩ ካላቸው ዒሣን የወፍ ቅርጽ ፈጠረ ወይም አበጀ ቢለው ምን ያስደንቃል? አላህ በትንሳኤ ቀን ለሸርና ለሺርክ አገልግሎት ስዕል የሳሉትንና ቅርፅ የቀረጹትን ሰዎች እንዲህ ይጠይቃቸዋል፦

ኢማም ቡኻሪይ መጽሐፍ 67 ሐዲስ 116

ዓኢሻህ እንደተረከችው፦ “የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” አሉ፦ “የምስል ባለቤቶች በትንሳኤ ቀን ይቀጣሉ፤ የፈጠራችሁን” ህያው አድርጉት ይባላሉ”።

“የፈጠራችሁትን” ተብሎ የተቀመጠው ቃል “ኸለቅቱም” خَلَقْتُمْ ሲሆን “ኸለቀ” خَلَقَ ከሚል ግን የመጣ እንደሆነ አንባቢ ልብ ይለዋል። አላህ “የፈጠራችሁትን” ሕይወት ስጡት ብሎ ይጠይቃቸዋል፤ አየህ ሕይወት መስጠቱ ነው ቁም ነገሩ እንጂ መቅረጻቸው አይደለም። መቅረጻቸውንማ “የፈጠራችሁትን” በማለት እንደፈጠሩት ያሳያል። እንዲሁ ጥቅሱ ላይ ዒሣ የወፍ ቅርጽ ፈጠረ ማለት አበጀ እንጂ ወፍ አላደረገም አልፈጠረም።

ትርጉም የሌለው ሐተታ ነው ያስነበብከን፡፡ ለመሆኑ ኢየሱስ ያደረገው ከጭቃ የወፍ ቅርፅ መሥራት ብቻ ነውን? ቀጣዩን ሐረግ የማታነበው ለምንድነው? የወፍ ቅርፅ ፈጠረ ካለ በኋላ፣ እፍ ብሎበት ሕይወት እንደሰጠውና እንዳበረረው ይነግርሃል፡፡ ዋናው ነጥብ እርሱ ነው፡፡ ቁርኣን የተናገረው ከጭቃ የወፍ ቅርፅ ስለ መሥራት ብቻ ይመስል ግዑዙን ጭቃ እፍ ብሎበት ሕይወት እንዲኖረው የማድረጉን ጉዳይ ችላ ብለህ ቅርፅ ስለመሥራቱ ብቻ ማውራትህ አወናባጅ መሆንህን የሚገልፅ ነው፡፡ ዳሩ ግን የምታታልለው የገዛ ራስህን ብቻ ነው፡፡

እሩቅ ሳንሄድ በክርስትና የምድረ-በዳ አበው የሚባሉት ምንኩስናን ፈጥረዋል፦

57፥27 ከዚያም በዱካዎቻቸው ላይ መልክተኞቻችንን አስከታተልን፡፡ የመርየምን ልጅ ዒሳንም አስከተልን፡፡ ኢንጂልንም ሰጠነው፡፡ በእነዚያም በተከተሉት ልቦች ውሰጥ መለዘብን እና እዝነትን አደረግን፡፡ በእነርሱ ላይ አዲስ ”የፈጠሩዋትንም” ምንኩስና አልጻፍናትም፡፡ ግን የአላህን ውዴታ ለመፈለግ ሲሉ ፈጠሩዋት”፡፡ ተገቢ አጠባበቋንም፤ አልጠበቋትም፡፡ ከእነርሱም ለእነዚያ ላመኑት ምንዳቸውን ሰጠናቸው፡፡ ከእነርሱም ብዙዎቹ አመጸኞች ናቸው፡፡

“የፈጠሩዋትንም” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት። እውን የምድረ-በዳ አበው ፈጣሪ ናቸውን?

ምንኩስና ሥርዓት ወይም የሕይወት ዘይቤ ነው፡፡ ወፍ ደግሞ ሕያው ፍጥረት ነው፡፡ የአኗኗር ሥርዓትን የፈጠረ ሰው ፈጣሪ አይደለም፡፡ ሕይወትን የፈጠረ ግን ፈጣሪ ነው፡፡ ቁርኣን ኢየሱስ ሕይወትን እንደፈጠረ ነው የሚነግርህ፡፡ ምኑን ከምን አገናኘኸው!

“ኸልቅ” ጠቢባን ለሚጠበቡት ፈጠራ “ተስዊር” ሲሆን አላህ ለፈጠረበት ግን “ፊጥራህ” فِطْرَت ነው። አላህ “ፋጢር” فَاطِر ነው፤ ይህ በስም መደብ “ፋጢር” ሲሆን በግስ መደብ ደግሞ “ፈጠረ” فَطَرَ ነው፤ ይህ ቃል ለፍጡራን አግልግሎት ላይ የዋለበት ጥቅስ የለም፦

6፥14 «ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ ከኾነው አላህ እርሱ የሚመግብ የማይመገብም ሲኾን ሌላን አምላክ እይዛለሁን» በላቸው፡፡

ኢየሱስ የፈጠረው ጠቢባን ነገሮችን በሚፈጥሩበት መንገድ ሳይሆን ልዕለ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ሕይወትን ነው የፈጠረው፡፡ በተግባር ፈጣሪ የሆነ አካል ፈጣሪ ካልተባለ ምን ሊባል ነው? አንድን አካል ፈጣሪ የሚያሰኘው ነገሮችን ካለመኖር ወደ መኖር ማምጣት መቻሉ ነው፡፡ ስም የተግባር መገለጫ እስከሆነ ድረስ ሕይወትን መፍጠር ከቻለ በቁርኣን ተባለም አልተባለ ፈጣሪ ነው፡፡ አላህ የፍጥረት ፈጣሪ መሆኑን ለማሳየት በተለያዩ የቁርኣን ጥቅሶች “ፋጢሪ” ቢባልም አዳምን መፍጠሩን ለማሳየት “ኢንኒ ኻሊቁን በሸረን ሚን ጢኒን” (እኔ … ከጭቃ ፈጣሪ ነኝ) በማለት ነው የተናገረው (ሱራ 38፡71-72)፡፡ በተመሳሳይ ኢየሱስ ወፍ መፍጠሩን ለማሳየት “አንኒ አኽሉቁ ለኩም ሚነ አል-ጢኒ” (እኔ ለናንተ ከጭቃ … እፈጥራለሁ) ብሏል (ሱራ 3፡49)፡፡ ቃሉ ለአላህ ሕይወትን በመፍጠር አውድ ጥቅም ላይ እንደ ዋለው ሁሉ ለኢየሱስም በተመሳሳይ መንገድ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

ሲያረብብ “ቢኢዝኒሏህ” بِإِذْنِ اللَّه ማለት “በአላህ ፈቃድ” ማለት ሲሆን ዒሣ ያበጀውንና እፍ ያለበትን የወፍ ቅርጽ አላህ ነው በፈቃዱ ወፍ ያረገው እንጂ ዒሣ ወፍ አደረገ አሊያም ፈጠረ የሚል የለም። የወፍ ቅርጽ መፍጠር ሁሉም ሰው የጭቃ ንጥረ-ነገር ከተሰጠው ይፈጥራል እፍ ብሎም እላዩ ላይ መተንፈስ ይችላል። ቁም ነገሩ ግን ሰዎች የፈጠሩትን ቅርጽ እና እፍ ያሉበትን ጭቃ አላህ ህይወት አይሰጥም። ነገር ግን ለዒሣ ነብይነት ማረጋገጫ አላህ በራሱ ፈቃድ ዒሣ የሰራውን የወፍ ቅርጽ ወፍ አድርጎታል። ሙግቱ የስነ-ቋንቋና የዐውድ ሙግት ታሳቢና ዋቢ ያደረገ ነው።

ቁርኣን ውስጥ ዒሳ በአላህ ፈቃድ መሠረት ይህንን እንደፈፀመ ቢነገርም ዳሩ ግን መፍጠር ፈጣሪ ከማንም ጋር የማይጋራው መለያው በመሆኑ ምክንያት ይህ የዒሳን አምላክነት ውድቅ አያደርግም፡፡ ፈጣሪ ይህንን ችሎታ ለዒሳ ካጋራው ዒሳ የፈጣሪን ልዩ ችሎታ ተጋርቷል ማለት ነው፡፡ ፈጣሪ ይህንን ችሎታ ለሌሎች የሚያጋራ ከሆነ ደግሞ ልዩ መሆኑ ይቀራል፡፡ ስለዚህ “በአላህ ፈቃድ” የሚለው ሐረግ የቁርኣን ደራሲ እንደ ተምታታበት ከማሳየት በዘለለ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡  በጥቅሱ መሠረት ዒሳ ፈጣሪ ነው፡፡ ሌላው ክርስቲያኖች የኢየሱስን አምላክነት ቢያምኑም የሥላሴ አካላት ተነጣጥለው ሳይሆን ፍፁማዊ በሆነ አንድነት እንደሚሠሩ ስለሚያምኑ ኢየሱስ በአብ ፈቃድ እንደሚሠራ መነገሩ ከእምነታቸው ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ ኢየሱስ የመፍጠር መለኮታዊ ሥልጣን አለው ነገር ግን የሚፈጥረው በአባቱ ፈቃድ መሠረት ነው፡፡ ይህ ክርስቲያናዊ አስተምህሮን የሚደግፍ እንጂ የሚቃወም አይደለም፡፡ ሙስሊሞች ሊያስቡበት የሚገባው ጉዳይ ፈጣሪ ሕይወትን የመፍጠር ልዩ ችሎታውን ለፍጡራን ያጋራል ወይ? የሚል ነው፡፡

ከላይ የቀረቡትን የቁርኣን የቋንቋ ሙግት ነጥቦች አልገባህ ካላችሁ በቀላሉ ለማስረዳት ከራሳችሁ ባይብል አንድ የቋንቋ ሙግት ለናሙና እንይ፦

ኤርምያስ 10፥16 የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፤ እርሱ የሁሉ ”ፈጣሪ” יוֹצֵ֤ר ነውና፤ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፤ ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።

ኤርምያስ 51፥19 የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፥ እርሱ የሁሉ ”ፈጣሪ” יוֹצֵ֤ר ነውና፤ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።

እነዚህ አናቅጽ ላይ “ፈጣሪ” ተብሎ የተቀመጠው ቃል በዕብራይስጡ “ዮውሰር” יוֹצֵ֤ר ሲሆን ትርጉሙ “ፈጣሪ” ወይም “ሠሪ” ሲሆን ለሰዎች ቃሉ ውሏል፦

መዝሙር 2፥9 በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፥ እንደ ሸክላ ”ሠሪ” יוֹצֵ֣ר ዕቃዎች ትቀጠቅጣቸዋለህ።

ኢሳይያስ 41፥25 አንዱን ከሰሜን አነሣሁ መጥቶአልም፤ አንዱም ከፀሐይ መውጫ ስሜን የሚጠራ ይመጣል፤ በጭቃ ላይ እንደሚመጣ ሰው አፈርም እንደሚረግጥ ”ሸክለኛ” יוֹצֵ֣ר በአለቆች ላይ ይመጣል።

ኤርምያስ 19፥1 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ሂድ፥ ከሸክላ ”ሠሪ” יוֹצֵ֣ר ገምቦ ግዛ፥ ከሕዝቡም ሽማግሌዎችና ከካህናት ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤

ሰቆቃው ኤርምያስ 4፥2 ቤት። ጥሩ ወርቅ የሚመስሉ የከበሩ የጽዮን ልጆች፥ የሸክላ ”ሠሪ” יוֹצֵ֣ר እጅ እንደ ሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ እንዴት ተቈጠሩ!

እና ሸክላ ሰሪ ሸክለኛ ሁሉ ፈጣሪዎች ናቸውን? አይ ቃሉ ሳይሆን ቃሉ የወከለው ሃሳብንና ዓረፍተ-ነገር ይወስነዋል ከሆነ መልሱ እንግዲያውስ ከላይ ያለውንም የቁርኣን ቃል በዚህ ቀመርና ስሌት ተረዱት፤ በሰፈሩት ቁና መሰፈር ይሉሃል እንደዚህ ነው።

አንተ በትክክል እንዳስቀመጥከው የትኛውም ቃል በተለያዩ አውዶች የተለያዩ ትርጉሞች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ መፍጠርን የሚያመለክተው የእብራይስጥ ቃል ሸክላ ሠሪዎችን ለማመልከት ቢገባ ሸክላ ሠሪዎች መሆናቸውን ከማሳየት የዘለለ ሌላ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ከሸክላ ቅርፅ ሠርቶ ያንን ቅርፅ እፍ ብሎበት ወፍ ሆኖ እንዲበርር ካደረገና በዚያው አውድ “መፍጠር” የሚለው ቃል ከገባ ሕይወትን የመፍጠር ችሎታውን ማሳየቱ አከራካሪ አይደለም፡፡ በቁርኣን መሠረት ኢየሱስ ምን አደረገ? ከጭቃ የወፍ ቅርፅ ፈጠረ፣ ቅርፁ ላይ እፍ አለበት፣ ቅርፁም ሕይወት ዘርቶ ወፍ ሆኖ በረረ፡፡ ይህም የኢየሱስ እስትንፋስ መለኮታዊ መሆኑን ያሳያል፡፡ በቁርኣን መሠረት አላህ ያደረገው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ ከጭቃ የሰው ቅርፅ ሠራ፣ እፍ አለበት፣ ቅርፁ ነፍስ ዘርቶ ሰው ሆነ፡፡ ሁለቱም ተመሳሳይ ነገር ስላደረጉ በጥቅሱ ውስጥ “እፈጥራለሁ” የሚለው ቃል የኢየሱስን ፈጣሪነት ያሳያል፡፡

ስናጠቃልል፡- ኢየሱስ ከጭቃ ወፍ ሠርቶ እንዳበረረ የሚናገረው ታሪክ የቁርኣን ደራሲ መገለጡን ከሰማይ ሳይሆን ከምድራዊ ምንጮች ይቃርም እንደነበር ከሚያረጋግጡ አጋጣሚዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የቁርኣን ደራሲ ይህንን ታሪክ የቀዳው “የቶማስ ወንጌል” በመባል ከሚታወቅ የአፖክሪፋ መጽሐፍ ነው (The New Testament Apocrypha, vol. 1, rev. ed. by W. Schneemelcher, trans. R. McL. Wilson, Westminster / John Knox, 1991, p. 444)፡፡ የቶማስ ወንጌል በኖስቲሳውያን የተዘጋጀ የአፖክሪፋ ጽሑፍ ሲሆን ሐዋርያዊ መሠረት የለውም፡፡ የመጽሐፉ ይዘት ከሞላ ጎደል በ1945 ዓ.ም. በግብጽ ተገኝቷል፡፡ ይህንን መጽሐፍ አንዳንድ ለዘብተኛ ሊቃውንት ከኢየሱስ ዘመን ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ገምተው የነበረ ቢሆንም በሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ የተጻፈ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ የሙስሊሞች ተወዳጅ የክርስትና ተቃዋሚ የሆነው ባርት ኤህርማን መጽሐፉ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ የተጻፈ መሆኑ ጥርጥር እንደሌለው ተናግሯል (Bart D. Ehrman. Lost Scriptures፡ Books that Did Not Make it into the New Testament; Oxford University Press, 2003, p. 20)፡፡

የቁርኣን ደራሲ የኮረጀው ታሪክ የእንግሊዘኛ ትርጉም ይህንን ይመስላል፡-

1. “I, Thomas, an Israelite, judged it necessary to make known to our brethren among the Gentiles, the actions and miracles of Christ in his childhood, which our Lord and God Jesus Christ wrought after his birth in Bethlehem in our country, at which I myself was astonished; the beginning of which was as follows. 2. When the child Jesus was five years of age and there had been a shower of rain that was now over, Jesus was playing with other Hebrew boys by a running stream, and the waters ran over the banks and stood in little lakes; 3. But the water instantly became clear and useful again; they readily obeyed him after he touched them only by his word. 4. Then he took from the bank of the stream some soft clay and formed out of it twelve sparrows; and there were other boys playing with him. 5. But a certain Jew seeing the things which he was doing, namely, his forming clay into the figures of sparrows on the Sabbath day, went presently away and told his father Joseph, 6. Behold, your boy is playing by the river side, and has taken clay and formed it into twelve sparrows, and profanes the Sabbath. 7. Then Joseph came to the place where he was, and when he saw him, called to him, and said, Why do you that which is not lawful to do on the Sabbath day? 8. Then Jesus clapping together the palms of his hands, called to the sparrows, and said to them: Go, fly away; and while you live remember me. 9. So the sparrows fled away, making a noise. 10. The Jews seeing this, were astonished and went away and told their chief persons what a strange miracle they had seen wrought by Jesus.”

The Second Gospel of the Infancy of Jesus Christ: Chapter 1:1-10

የቶማስ ወንጌል ደራሲ የኢየሱስን አምላክነት ስለሚያምን ከጭቃ ወፎችን መፍጠሩን ለአምላክነቱ እንደ ማሳያ ነው የጠቀሰው፡፡ የቶማስ ወንጌል ደራሲ ትረካውን ሲጀምር “ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገው ተዓምር…” በማለት ነው፡፡ የታሪኩ ትርጉም ያልገባው የቁርኣን ደራሲ ግን የኢየሱስን አምላክነት ለማሳየት የተጻፈውን ታሪክ በመቅዳት ወደ ቁርኣን የጨመረ ሲሆን “በአላህ ፈቃድ ነው የፈጠረው” የሚል ሐሳብ በማከል ለማስለም ሞክሯል፡፡ ይህንን ታሪክ ከአፖክሪፋ መጽሐፍ ላይ መኮረጁ መገለጡ ከሰማይ የመጣ አለመሆኑን ከማሳየቱም በተጨማሪ ሳያውቀው የኢየሱስን አምላክነት በማረጋገጥ በሌሎች የቁርኣን ክፍሎች ከተናገራቸው ትምህርቶቹ ጋር ተጋጭቷል፡፡ ይህ ማለት ቁርኣን ከእውነተኛው አምላክ ዘንድ አለመሆኑ በኩረጃና በግጭት ከጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ ተረጋግጧል ማለት ነው፡፡

የቁርኣን ደራሲ ሳያውቀው የኢየሱስን አምላክነት የሚያሳዩ ሐሳቦችን ወደ ቁርኣን ሲጨምር ይህ የመጀመርያው አይደለም፡፡ ተከታዮቹን ጽሑፎች ይመልከቱ፡-

የቁርኣን ግጭቶች