የቁርኣን ግጭቶች – ኢብሊስ መልአክ ወይንስ ጂን?

38. ኢብሊስ መልአክ ወይንስ ጂን?

 

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

መልአክ-

2:34 “ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ አስታውስ፡፡ ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፤ ኮራም ከከሓዲዎቹም ኾነ፡፡”

ጂን- 18:50 “ለመላእክትም ለአደም ስገዱ፥ ባልናቸው ጊዜ የሆነውን አስታውስ። ወዲያውም ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፤ ከጋኔን ነበር፤…”

መልስ

“ጂን” جِنّ የሚለው ቃል “ጀንነ” جَنَّ ማለትም “ተሰወረ” ወይም “ተደበቀ” ከሚል ግስ የመጣ ሲሆን “ስውር” ወይም “ድብቅ” ማለት ነው፤ “ጅኒ” جني ደግሞ የጂን ብዙ ቁጥር ነው፤ ጂኒዎች የተፈጠሩት ከሰው በፊት ነው፤ ሰው የተፈጠረበት ንጥረ-ነገር ዐፈር እንደሆነ፤ መልአክ የተፈጠረበት ንጥረ-ነገር ብርሃን እንደሆነ ሁሉ ጂን የተፈጠረበት ንጥረ-ነገር ደግሞ እሳት ነው፦

15፥27 ጃንንም ከሰው በፊት ከእሳት ነበልባል ፈጠርነው፡፡

ኢማም ሙስሊም መጽሐፍ 55, ሐዲስ 78

ዓኢሻህ”ረ.ዐ.” እንደተረከችው የአላህ መልእክተኛም  እንዲህ አሉ፦ ”መላእክት ከብርሃን ተፈጥረዋል፤ ጂንዎች ከእሳት ነበልባል ተፈጥረዋል፤ አደም ለእናንተ እንደተገለጸላችሁ ከሚጭለቀለቅ ሸክላ ተፈጥሯል”፡፡

ጂኒዎች የተፈጠሩበት አላማ የፈጠራቸው አላህ እንዲያመልኩ ነው፦

51፥56 ጂኒን እና ሰውንም ሊያመልኩኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡

“ኢብሊሥ” إِبْلِيس በተፈጥሮው ከሰው ወይም ከመልአክ ሳይሆን ከጂን ሲሆን በመጥፎ ባህርይው ደግሞ “ሸይጧን” ነው፤ ለአደም አልሰግድም ብሎ በአላህ ላይ ያመጸው እርሱ ነው፦

18፥50 ለመላእክትም ለአደም ስገዱ፥ ባልናቸው ጊዜ የሆነውን አስታውስ ። ወዲያውም ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር ከጂን ነበር፤ ከጌታውም ትእዛዝ ወጣ”፡፡

“ከጂን ነበር” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት። አምላካችን አላህ “ለመላእክትም ለአደም ስገዱ” ብቻ ሳይሆን ለኢብሊስም ስገድ ብሎታል፥ ይህንን ማለቱ እዚሁ አንቀጽ ላይ፦ “ከጌታውም ትእዛዝ ወጣ” በማለት አላህ አዞት እንደነበር ይናገራል፦

አላህ፦ «ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ?» አለው”፡፡ «እኔ ከእርሱ የበለጥኩ ነኝ፡፡ ከእሳት ፈጠርከኝ፡፡ እርሱን ግን ከጭቃ ፈጠርከው» አለ፡፡

“ባዘዝኳችሁ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ? ሳይሆን “ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ? አለው፥ “ባዘዝኩህ” የሚለው ሃይለ-ቃል ለአደም ስገድ ብሎ አዞት እንደነበር ቁልጭና ፍንትው አድርጎ ያሳይል።

ጥቅሱን ደግመን እናንብብ፡- “ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ አስታውስ፡፡ ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፤ ኮራም ከከሓዲዎቹም ኾነ፡፡”

ከጥቅሱ በግልፅ እንደሚታየው አላህ ስገዱ ያለው ለመላእክት ነው፡፡ ሁሉም ትዕዛዙን ተቀብለው ወዲያውኑ ሲሰግዱ ኢብሊስ ግን ሳይሰግድ ቀረ፡፡ በዚህ መሠረት ቀጥተኛው መረዳት ኢብሊስም ከመላእክት ወገን መሆኑ ነው፡፡ ዲያብሎስ  ባለመስገዱ አላህ «ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ?» ብሎ መጠየቁ ግላዊ ኃላፊነትን እንጂ ለእርሱ ለብቻው ነጥሎ የሰጠው ትዕዛዝ መኖሩን አያመለክትም፡፡ ለኢብሊስ የተሰጠው ትዕዛዝ ለመላእክት በተሰጠው ውስጥ መጠቃለሉ እንጂ ለብቻው ተነጥሎ የተሰጠው ትዕዛዝ መኖሩ በጥቅሱ ውስጥ አልተገለፀም፡-  “ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ አስታውስ፡፡ ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር…” የሚለው አገላለፅ አላህ ለመላእክት የስግደትን ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ሁሉም ታዛዦች ሆነው አንዱ ብቻ ማመፁን በግልፅ ያሳያል፡፡ ስለዚህ በጥቅሱ መሠረት ኢብሊስ መልአክ ነው፡፡

“ለመላእክትም ብቻ ለአደም ስገዱ” ቢል ኖሮ “ብቻ” የሚለው ገላጭ ቅጽል ስላለ አደም ከመላእክት ነበር ብለን እንደመድም ነበር። ነገር ግን “ለ” የሚለው መስተዋድድ መኖሩ በራሱ ለመላእክት ብቻ የሚለውን አያሲዝም። ለምሳሌ፦

7፥179 ከጂኒም ከሰዎችም ብዙዎችን ለገሀነም በእርግጥ ፈጠርን፡፡ ”ለ”እነርሱ ልቦች አሏቸው፥ ግን አይገነዘቡበትም፡፡ “ለ”እነርሱም ዓይኖች አሉዋቸው፥ ግን ዐያዩበትም፡፡ “ለ”እነርሱም ጆሮዎች አሉዋቸው ግን አይሰሙበትም”፡፡ ይልቁንም እነርሱ በጣም የተሳሳቱ ናቸው፡፡ እነዚያ ዘንጊዎቹ እነርሱ ናቸው።

“ለሁም ቁሉብ” لَهُمْ قُلُوب “ለሁም አዕዩን” لَهُمْ أَعْيُن “ለሁም አዛን” آذَانٌ የሚሉትን ቁልፍ ቃላት አስምሩበት። “ለ”ዘንጊዎች ልቦች፣ ዓይኖች እና ጆሮዎች አሉዋቸው ማለት ሌላው ልቦች፣ ዓይኖች እና ጆሮዎች የለውም የሚለውን እንደማያሲዝ ሁሉ ለመላእክት ስገዱ ማለቱ ለኢብሊስ ስገድ አለማለቱን አያሲዝም። “ለ” የሚለው መስተዋድድ በመነሻ ቅጥያ መምጣቱ “ብቻ” የሚለውን መደምደሚያ አያስደርስም።

ትዕዛዙ መላእክትን ብቻ የሚመለከት መሆኑን ለመረዳት የግድ “ብቻ” የሚል ቃል መግባት የለበትም፡፡ መላእክት ስገዱ ተብለው ሁሉም ሰግደው ኢብሊስ ብቻ ሳይሰግድ እንደቀረ ከተገለፀ ኢብሊስም መልአክ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ መልአክ ካልሆነ ትዕዛዙ የተሰጠው ለመላእክት በመሆኑ እርሱን አይመለከትም፡፡ ስገዱ የተባሉት መላእክት እስከሆኑ ድረስ ከመላእክት ወገን ያልሆነ ሌላ ፍጥረት ለምን እንዳልሰገደ የሚጠየቅበት ምክንያት የለም፡፡ ሙግትህን ለማስረዳት የተጠቀምክበትን ምሳሌ ደግሜ ደጋግሜ ባነበውም ምንም ትርጉም ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡

ሲቀጥል “ኢብሊስ ብቻ ሲቀር” በሚለው ሃይለ-ቃል ላይ “ሲቀር” የምትለዋን ይዘን ኢብሊስ ከመላእክት ነበር ማለት አሁንም የቁርኣንን ሰዋስው ካለመረዳት የሚመጣ ጥራዝ-ነጠቅ ዕውቀት ነው፦

26፥77 ”«እነርሱም ለእኔ ጠላቶች ናቸው፡፡ ግን የዓለማት ጌታ ሲቀር እርሱ ወዳጄ ነው”፡፡

ኢብራሂም፦ “ለእኔ ጠላቶች ናቸው። ግን የዓለማት ጌታ ሲቀር” ማለቱን አስተውል። “ሲቀር” የሚለውን አፍራሽ ቃል ይዘን ከዓለማቱ ጌታ ውጪ ለኢብራሂም ሁሉም ጠላት ነውን? አማንያን፣ ነቢያት፣ መላእክት፣ እንስሳትስ ጠላት ናቸውን? አይ “በቀር” የሚለው የአላህን ወዳጅ ለመሆን የገባ እንጂ “ሁሉን ጠላት ናቸው ከአላህ በቀር” ማለቱን አያሳይም ከተባለ እንግዲያውስ “በቀር” የሚለው ኢብሊስ ብቻ አለመታዘዙን እንጂ መላእክት ውስጥ መካተቱን አያሳይም።

ምንም የማይገናኝ ምሳሌ ነው የሰጠኸው፡፡ በቁርአኑ ጥቅስ መሠረት አብርሃም እያወራ የነበረው ስለ አማልክት ነው፡- “እነሱም (ጣዖቶቹ) ለእኔ ጠላቶች ናቸው፡፡ ግን የዓለማት ጌታ ሲቀር (እርሱ ወዳጄ ነው)፡፡” በዚህ አባባል መሠረት ከአላህ ውጪ እነዚህ ሰዎች የሚያመልኳቸው አማልክት በሙሉ ለአብርሃም ጠላቶች ናቸው፡፡ አላህ በልዩነት (Exception) የመጣው በአማልክት መደብ በመሆኑ አባባሉ ትርጉም ይሰጣል፡፡ አብርሃም ጠላት ናቸው እያለ ያለው ፍጥረትን ሁሉ ሳይሆን ጣዖታትን ሁሉ ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች በአማልክትነት ከያዟቸው ነገሮች ሁሉ አላህ ብቻ የእርሱ ወዳጅ መሆኑን መናገሩ ምንም የሚያምታታ ጉዳይ አይደለም፡፡ አንተ ግን ይህንን እውነታ ለማድበስበስ የአማርኛ ተርጓሚዎች የንግግሩን አውድ ለማሳየት በቅንፍ ያስገቡትን (ጣዖታት) የሚለውን ማብራርያ ቆርጠህ ጠቅሰሃል፡፡ ይህ አጭበርባሪነትህን ያሳያል፡፡

ከመነሻው መላእክት በባሕያቸው ውስጥ ኩራትና አመጽ የለም፦

16፥49 ለአላህም በሰማያት ያለው ከተንቀሳቃሽም በምድር ያለው ሁሉ፣ ”መላእክትም ይሰግዳሉ፡፡ እነርሱም አይኮሩም”፡፡

21፥19 በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉም የእርሱ ነው፡፡ ”እርሱ ዘንድ ያሉትም መላእክት እርሱን ከመገዛት አይኮሩም”፡፡ አይሰለቹምም፡፡

66፥6 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ነፍሶቻችሁንና ቤተሰቦቻችሁን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ደንጋዮች ከኾነች እሳት ጠብቁ፡፡ በእርሷ ላይ ጨካኞች፣ ኀይለኞች የኾኑ መላእክት አሉ፡፡ ”አላህ ያዘዛቸውን ነገር በመጣስ አያምጹም፤ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ”፡፡

መላእክት አላህ ያዘዛቸውን ነገር በመጣስ አያምጹም፤ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ። ኢብሊስ ግን ከመላእክት ስልላሆነ ኮራ፥ በጌታውም ትእዛዝ አመጸ፦

38፥74 ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፡፡ ”ኮራ”፤ ከከሓዲዎቹም ነበር፡፡

18፥50 ለመላእክትም ለአደም ስገዱ፥ ባልናቸው ጊዜ የሆነውን አስታውስ ። ወዲያውም ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር ከጂን ነበር፤ ከጌታውም ትእዛዝ ወጣ”፡፡

ሱራ 16፡49 ላይ የሚገኘውን ቃል እስኪ ልብ ብለህ አንብበው፡- ለአላህም በሰማያት ያለው ከተንቀሳቃሽም በምድር ያለው ሁሉ መላእክትም ይሰግዳሉ፡፡ እነርሱም አይኮሩም” ይላል፡፡ ነገር ግን ከሰው ልጆች መካከል ፈጣሪያቸውን የካዱ ከሃዲያን እንዲሁም ሰይጣንና እርኩሳን ጭፍሮቹ ፈጣሪያቸውን እንደማያከብሩ ስለሚታወቅ “በሰማያት ያለው ከተንቀሳቃሽም በምድር ያለው ሁሉ” ያለ ኩራት ለፈጣሪው እንደሚሰግድ መነገሩ ሐሰት ነው፡፡ ለመሆኑ ቁርኣን ጥያቄን የማያጭር ጥቅስ ይኖረው ይሆን?

በማስከተል እንደምንመለከተው በጥንታውያን ታላላቅ ሙስሊም ሊቃውንት መሠረት ዲያብሎስ ከመላእክት ወገን በመሆኑ መላእክት ከአላህ ትዕዛዝ እንደማይወጡ መነገሩ የቁርኣን ጸሐፊ የፈፀመው ሌላ ግጭት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አላህ ለመላእክት ለአደም ስገዱ ብሎ ከመካከላቸው አንዱ ካልሰገደ መላእክት በአላህ ትዕዛዝ ላይ አያምፁም ከሚለው ጋር ይጋጫል ማለት ነው፡፡

ጥንታውያን ሙስሊም ሊቃውንት ሱራ 18፡50 “…ኢብሊስ ብቻ ሲቀር ከጂን ነበር፤ ከጌታውም ትእዛዝ ወጣ” የሚለው ጥቅስ ከሌሎች ጥቅሶች ጋር ያለውን ግጭት ለማስታረቅ ጂኒዎችም መላእክት መሆናቸውንና ኢብሊስም ከጅኒ ወገን የሆነ መልአክ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአት-ጠበሪ መሠረት ኢብሊስ ከመላእክት ነው የሚለው የብዙኀኑ አመለካከት ነው፤ እንደ ኢብን ዓባስ፣ ኢብን መስዑድ፣ ኢብን ጁራይጅ፣ ኢብን አል-ሙሰይብ፣ ቀታዳህ እና ሌሎችም ከዚህ ጋር ይስማማሉ፡፡ በአል-ሼኽ አቡልሐሰን የተመረጠ አመለካከት ሲሆን በራሱ በአልጠበሪም የበለጠ ትክክል ሆኖ ተቀባይነትን ያገኘ አመለካከት ነው፡፡ በነዚህ ሊቃውንት መሠረት “ኢብሊስ ሲቀር” የሚለው ሐረግ ግልፅ ትርጉምም እርሱ ነው፡፡” (The History of al-Tabari Vol. 1: General Introduction and From the Creation to the flood; p. 250-255)

በተመሳሳይ አል-ቁርጡቢ በተፍሲሩ ኢብሊስ መልአክ መሆኑ በአብዛኞቹ ሊቃውንት ዘንድ እንደሚታመን ይገልጻል፡፡[1]

ዘመንኛ ሙስሊሞች ቀደምት ሙስሊም ሊቃውንት የሰጡትን ይህንን ሐሳብ ትክክለኛ አመለካከት ሳይሆን ኢስራኤልያት (ሙስሊም ሊቃውንት ከአይሁድ የሰሙት) ነው በማለት ያጣጥላሉ፡፡ ዘመንኛ ሙስሊሞች የተከበሩ ሊቃውንቶቻቸውን አመለካከት እንዲህ የሚያጣጥሉበትና የማይቀበሉበት ምክንያት ኢብሊስ መልአክ ከሆነ መላእክት ከአላህ ትዕዛዝ ወለም ዘለም እንደማይሉ በሌሎች ቦታዎች ላይ ስለተነገረ ሌላ ግጭት ይፈጥራል በሚል ነው፡፡ ነገር ግን አላህ ለመላእክት የሰጠውን ትእዛዝ ኢብሊስ ባለመተግበሩ ምክንያት ተጠያቂ መሆኑ ኢብሊስን ከመላእክት መደብ ስለሚያደርገው ጂን ነው መባሉም ሌላ ግጭት ነው፡፡ ኢብሊስ መልአክ ሆነም አልሆነም ቁርኣን ከግጭት የሚተርፍበት መንገድ የለም፡፡ መልአክ ከሆነ መላእክት ከአላህ ትዕዛዝ እንደማይወጡ ከሚናገሩት የቁርኣን ጥቅሶች ጋር ግጭት ይፈጠራል፡፡ ጂን ነው ከተባለ ደግሞ ለመላእክት የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለመቀበሉ ተወቃሽ እንደሆነ በመናገር ከመላእክት ወገን ከሚመድቡት ጥቅሶች ጋር ግጭት ይፈጠራል፡፡

ይህንን ሊገባችሁ በሚችለው መልኩ ከራሳችሁ ባይብል ላሳያችሁ፦

ዘፍጥረት 2፥16-18 ”እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና”። እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።

እግዚአብሔር አደምን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ “አትብላ” ብሎ ሲያዘው ሔዋን አልተፈጠረችም። ነገር ግን ሔዋን “አትብሉ” ብሎናል ብላለች፦

ዘፍጥረት 3፥2 ሴቲቱም ለእባቡ አለችው፦ በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ ”እግዚአብሔር አለ፦ “እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም”።

“አትብላ” ብሎ ያዘዘው አዳምን ብቻ ሆኖ ሳለ “አትብላ” የሚለውን “አትብሉ” በሚል ስላስቀመጠች ሁለቱንም አዟቸው ነበር ይባላል እንጂ ሔዋን አዳም ናት ይባላልን? ሔዋንን ሲያዛት የሚያሳይ ጥቅስ አለመኖሩ ሔዋንን አለማዘዙን ያሳያልን? በፍጹም! እንግዲያውስ ከላይ ያለውን የቁርኣን አንቀጽ በዚህ ሒሳብ ተረዱት። ኢብሊስ በፍጹም መልአክ አልነበረም።

እግዚአብሔር አምላክ መልካምና ክፉን ስለሚያሳውቀው ዛፍ የሰጠው ትዕዛዝ ለአዳም ብቻ ሳይሆን ለሰው ሁሉ የተሰጠ ነበር፡፡ አዳም ይህንን ትዕዛዝ ከእግዚአብሔር ሲቀበል ሔዋን በአዳም ውስጥ ሆና እንደተቀበለች ማስታወስም ያስፈልጋል፡-

“እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” (ዘፍጥረት 1፡27)

አዳምና ሔዋን በአንድ መደብ ማለትም በሰብዓዊነት መደብ ውስጥ ናቸው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው ትዕዛዝ ሔዋንንም ሆነ የሰው ልጆችን በሙሉ ይመለከታል፡፡ የመላእክትና የኢብሊስ ግን ከዚህ ይለያል፡፡ ኢብሊስ ከመላእክት መደብ ካልነበረና ትዕዛዙ የተሰጠው ለመላእክት ከሆነ እርሱን በማይመለከተው ትዕዛዝ ተጠያቂ መሆን አልነበረበትም፡፡

በተጨማሪም በአሌክሳድሪየስ ኮዴክስ በሚገኘው በሮሙ ክሌመንት ማለትም በቀለሚንጦስ ደግሞ የሰገዱት እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ እንደሆነ ተገልጿል፦

ክሌመንት 1፥41 አራዊት፣ እንስሳት ወፎች ”እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ” ወደ አዳም ተሰበሰቡ ከፊቱ ቁመው ራሳቸውን አዘነበሉ፤ ለአዳምም ሰገዱ”።

ሰይጣን ለአዳም ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ኃብተ ፀጋ ማለትም “ሁሉም ፍጥረት መስገዳቸው” ባየ ጊዜ ከዚያ ሰአት ጀምሮ ቅንአት አደረበት፤ እግዚአብሔር በሰይጣን ላይ የነበረውን የምስጋና ልብስ እና የግርማ ልዕልና አስወገደ፤ ሰይጣን ብሎ ሰየመው፦

ክሌመንት 1፥46 ”ሰይጣን ለአዳም ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ኃብተ ፀጋ ባየ ጊዜ ከዚያ ሰአት ጀምሮ ቅንአት አደረበት”።

ክሌመንት 1፥47 ”በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር በሰይጣን ላይ የነበረውን የምስጋና ልብስ እና የግርማ ልዕልና አስወገደ፤ ሰይጣን ብሎ ሰየመው፤ በእግዚአብሔር ላይ ታብዮአልና፤ በእግዚአብሔር መንገድ አልሄደምና ለራሱ ክብር ወዷልና”።

በተጨማሪም በመቃብያን ላይ ዲያቢሎስ የወደቀበት ለአደም አልሰግድ በማለቱ እንደሆነ ተገልጿል፦

3ኛ መቃብያን 1፥6 ለሚዋረድልኝ ለአዳም አልሰግድም በማለቴ እግዚአብሔር ስለአባታቸው ስለአዳም ከማዕረጌ አዋርዶኛልና።

የቁርኣን ደራሲ ይህንን ታሪክ ኮርጆ ያቀረበበት መንገድ በቁርኣን ውስጥ ለማስታረቅ የቸገረ ግጭት ፈጥሯል፡፡  በግጭት ቁጥር 7 ላይ እንደገለጽነው ከኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ ጋር የተገኙት የቀለሜንጦስ ጽሑፎች 1ኛ እና 2ኛ ተብለው ስለተከፈሉ በየትኛው ውስጥ ነው የሚገኘው? 1፥41 ስትልስ ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ምክንያቱም 1ኛ ወይንም 2ኛ ቀለሜንጦስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 41 ለማለት ፈልገህ ከሆነ በ1ኛው ውስጥ የመጀመርያው ምዕራፍ፣ 3 ቁጥሮች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ 2ኛው ውስጥ ደግሞ 8 ቁጥሮች ናቸው ያሉት፡፡ ከቁርኣን ጋር የሚመሳሰል ታሪክም በውጡ አላገኘንም፡፡ ልታሳየን ብትችል መልካም ነው፡፡

ከ 3ኛ መቃብያን የጠቀስከው ቃል የሚገኘው 1፡6 ላይ ሳይሆን 1፡15 ላይ ነው፡፡ የቁርኣንን የኩረጃ ምንጭ ስለጠቆምከን እናመሰግናለን፡፡ የታሪኩ ዝርዝር ግን ከአይሁድ የአዋልድ መጽሐፍ የተቀዳ ነው፡፡ ይህንን በተጨባጭና በማይታበል ማስረጃ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ቁርኣን የሰው ሥራ እንጂ ከሰማይ የመጣ የፈጣሪ መጽሐፍ አይደለም፡፡

————–

[1] With the exception of Iblis.

The exception is connected to what was just mentioned before (i.e. the angels), as is generally stated. Ibn ‘Abbas, Ibn Mas‘ud, Ibn Jurayj and others said that Iblis was one of the angels. Ibn ‘Abbas said, “His name was ‘Azazll and he was one of the noblest of the angels. He had four wings and then was deprived of his angelic status. When he disobeyed Allah, He cursed him and he became Shaytan. SaTd ibn Jubayr said, “The jinn were a tribe of the angels, created from fire and Iblis was one of them. The rest of the angels were created from light.” Ibn Zayd, al-Hasan and

Qatada said, “Iblis was the father of the jinn in the same way that Adam was the father of human beings. He was not an angel.” A Similar statement is also related from Ibn ‘Abbas. He said that his name was al-Harith in Arabic. Sahr ibn Hawshab and others say, “He was one of the jinn who were on earth. The angels fought them and captured him as a child and he worshipped with the angels.”

Others find their evidence in Allah’s description of the angels: ‘They do not disobey Allah in respect of any order He gives them and carry out what they are ordered to do, ” (66:6) and in the ayat , “Iblis was one of the jinn.” (18:50) The jinn are not angels. The proponents of the first position answer that nothing prevents Iblis from issuing from the angels as a whole, since Allah knew that he would be wretched and He is not asked about what He does.

Others say that he was one of the guardians of the Garden but not one of the angels of heaven. Sometimes the angels are referred to as “jinn” because of their being hidden from sight in the same way. (TAFSIR AL-QURTUBI; Classical Commentary of the Holy Qur’an, TRANSLATED BY AISHA BEWLEY, VOLUME I, p. 211-212)

 

የቁርኣን ግጭቶች