የቁርኣን ግጭቶች – አማላጆች አሉ ወይንስ የሉም?

4. አማላጆች አሉ ወይስ የሉም?

አሉ፡-  ሱራ 42፡5 “… መላእክትም ጌታቸውን እያመሰገኑ ያወድሳሉ፤ በምድርም ላለው ፍጡር ምህረትን ይለምናሉ…” 

የሉም፡-  “…ከርሱ ሌላ ረዳትም አማላጅም ምንም የላችሁም አትገሠፁምን?”

መልስ

“ሸፋዐህ” شَفَٰعَه ማለት “ምልጃ” ማለት ሲሆን ምልጃ ሥስት ማንነቶችን ያቅፋል፤ እነርሱም፦ አንደኛው የሚማለደው ተማላጅ፣ ሁለተኛው የሚማለድለት ተመላጅ እና ሥስተኛው የሚማልደው አማላጅ ናቸው፤ አላህ የሁሉም ነገር ፈጣሪና አስተናባሪ በመሆኑ የሚማለድ ተማላጅ ነው፤ ከፍጡሮቹ መካከል ደግሞ እርሱ የፈቀደላቸው ፍጡሮቹ ደግሞ ተመላጆች እና አማላጆች ናቸው። ይህ ሦስቱ ሂደት “ምልጃ” ሲባል ይህ የምልጃ ፈቃድ የአላህ ብቻ ነው፦

39፥44 *”ምልጃ በሙሉ የአላህ ብቻ ነው፤ የሰማያትና የምድር ሥልጣን የእርሱ ብቻ ነው፡፡ ከዚያም ወደ እርሱ ትመለሳላችሁ”* በላቸው፡፡

34፥23 *ምልጃም እርሱ ለፈቀደለት ሰው ብቻ ቢሆን እንጂ እርሱ ዘንድ ምንም አትጠቅምም*፡፡

20፥109 *በዚያ ቀን ለእርሱ አልረሕማን የፈቀደለትን እና ለእርሱም ቃልን የወደደለትን ሰው ቢኾን እንጅ ምልጃ አንድንም አትጠቅምም*፡፡

ነገር ማንዛዛት ትወዳለህ፡፡ የተጠየቀው ጥያቄ ቀላልና ግልፅ ነው፡፡ ለምን በቀጥታ አትመልስም?

ነጥብ አንድ

“አማላጅ”

“ሸፊዕ” شَفِيع ማለት “አማላጅ” ማለት ሲሆን በአላህ ፈቃድ የሚያማልዱት መላእክት፣ ነቢያት፣ ሙዑሚን ናቸው፤ ለምሳሌ መላእክት፦

53፥26 *በሰማያት ውስጥ ካለ መልአክም ብዙዎች ሊማለዱለት ለሚሻው እና ለሚወደው ሰው ከፈቀደ በኋላ ቢኾን እንጅ ምልጃቸው ምንም አትጠቅምም*፡፡

21፥28 በፊታቸው ያለውንና በኋላቸው ያለውንም ሁሉ ያውቃል፡፡ *ለወደደውም ሰው እንጅ ለሌላው አያማልዱም*፡፡ እነርሱም እርሱን ከመፍራታቸው የተነሳ ተጨናቂዎች ናቸው፡፡

“ለወደደውም ሰው እንጅ ለሌላው አያማልዱም” የሚለው ሃይለ-ቃል መላእክት ለአማንያን እንደሚያማልዱ ያሳያል፤ ሌላው አማላጆች አላህ ቃል ኪዳን የገባላቸው ነብያት ናቸው፦

19፥87 *አልረሕማን ዘንድ ቃል ኪዳንን የያዘ ሰው ቢኾን እንጂ ማማለድን አይችሉም*፡፡

2፥255 *ያ እርሱ ዘንድ በፈቃዱ ቢኾን እንጅ የሚያማልድ

33፥7 *ከነቢያትም የጠበቀ ኪዳናቸውን ከአንተም፣ ከኑሕም፣ ከኢብራሒምም፣ ከሙሳም እና ከመርየም ልጅ ከዒሳም ጋር በያዝን ጊዜ አስታውስ፡፡ ከእነርሱም የከበደን ቃል ኪዳን ያዝን*፡፡

እስከ አሁን ያለው ለመልሱ አስተዋፅዖ የሌለው ሐተታ ነው፡፡

ነጥብ ሁለት

“አማላጅ የለም”

ከላይ በግልፅና በማያሻማ መልኩ አላህ የፈቀደለት አማላጅ እና የሚማለድለት ተመላጅ ሰው እንዳለ ተቀምጧል፦

አዎ፤ ነገር ግን ቁርኣን ሌላ ቦታ ላይ ከአላህ ውጪ ሌላ አማላጅ እንደሌለ በመናገር ይህንን ሐሳብ ያፈርሳል!

10፥3 *ከእርሱ ፈቃድ በኋላ ቢኾን እንጂ አንድም አማላጅ የለም፡፡ እነሆ! አላህ ጌታችሁ ነውና አምልኩት፤ አትገሰጹምን?*

“ከእርሱ ፈቃድ በኋላ ቢኾን እንጂ አንድም አማላጅ የለም” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት “አንድም አማላጅ የለም” ነገር ግን “ከእርሱ ፈቃድ በኋላ ቢኾን እንጂ”።

ነገር ግን ጣዖታውያን ቁሬሾች ከአላህም ሌላ የማይጎዳቸውን የማይጠቅማቸውንም ያመልካሉ፤ “እነዚህም አላህ ዘንድ አማላጆቻችን ናቸው” ይላሉ፤ እነዚህም በትንሳኤ ቀን፦ “እነዚያንም እነርሱ በእናንተ ውስጥ ለአላህ ተጋሪዎች ናቸው የምትሉዋቸውን አማላጆቻችሁን ከእናንተ ጋር አናይም” ይባላሉ፦

10፥18 *ከአላህም ሌላ የማይጎዳቸውን የማይጠቅማቸውንም ያመልካሉ፤ “እነዚህም አላህ ዘንድ አማላጆቻችን ናቸው” ይላሉ*፡፡

6፥94 *እነዚያንም እነርሱ በእናንተ ውስጥ ለአላህ ተጋሪዎች ናቸው የምትሉዋቸውን አማላጆቻችሁን ከእናንተ ጋር አናይም፤ ግንኙነታችሁ በእርግጥ ተቋረጠ፡፡ ከእናንተም ያ ያማልደናል የምትሉት ጠፋ* ይባላሉ፡፡

እነዚያ ጣዖታውያን በአላህ ሌላ የሚያጋሩትን ጣዖታት፦ “አማላጆቻችን ናቸው” ይበሉ እንጂ ለእነርሱ ወደ አላህ የሚያማልድ አማላጅ የላቸው፦

6፥51 *እነዚያንም ከእርሱ ሌላ ረዳት እና አማላጅም የሌላቸው ሲኾኑ ወደ ጌታቸው መስሰብሰብን የሚፈሩትን ይጠነቀቁ ዘንድ በእርሱ በቁርኣን አስጠንቅቅ*፡፡

40፥18 *ለበዳዮች ምንም ወዳጅ እና ተሰሚ አማላጅ የላቸውም*፡፡

32፥4 *ከእርሱ ሌላ ለእናንተ ረዳት እናም አማላጅም ምንም የላችሁም፤ አትገሰጹምን?*

ሙሐመድ በአንድ ወቅት ሦስቱ የአረብ ጣዖታት፤ አል-ላት፣ መናትና ኡዛ አማላጆች መሆናቸውን አላህ እንደነገረው በመናገር የአረብ ጣዖታውያንን አስፈንድቆ እንደነበር እስላማዊ ትውፊቶች ይናገራሉ፡፡ ኋላ ላይ ሙሐመድ ሰይጣን አሳስቶት እንደነበር ስለተናገረ ጥቅሶቹ “ሰይጣናዊ ጥቅሶች” በመሰኘት ከቁርኣን ውስጥ ተወግደዋል፡፡ ይህ ታሪክ በመጀመርያዎቹ ሁለት የእስልምና ክፍለዘመናት በተጻፉት ጽሑፎች ውስጥ በስፋት የተዘገበ ሲሆን ዘመንኛ ሙስሊሞች ግን ይክዱታል፡፡ ስለዚህ ታሪክ የበለጠ ለማወቅ ይህንን ሊንክ ይከተሉ http://www.ewnetlehulu.net/am/muhammad/01-2/

“አትገሰጹምን” የሚለው ያልተገሰጹትን በዳዮች ነው፤ “ለበዳዮች ምንም ወዳጅ እና ተሰሚ አማላጅ የላቸውም” የሚለው ይሰመርበት፤ “ማ ለኩም ሚን ዱኒሂ ሚን ወሊይ” مَا لَكُمْ مِنْ دُونِهِ مِنْ وَلِيٍّ ማለትም “ከእርሱ ሌላ ለእናንተ ረዳት የላችሁም” ማለት ሲሆን ከአላህ ውጪ በጀነት ለመጥቀምና በጀሃነም ለመቅጣት የሚችል ማንም እረዳት የላቸውም፤ “ሚን ዱኒሂ” مِنْ دُونِهِ ማለትም “ከእርሱ ሌላ” የሚለው ተሳቢ ተውላጠ-ስም ከሰዋስው አንፃር አላህ ብቻ በመጥቀምና በመጉዳት ረዳት መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፦

18፥26 *ለእነርሱ ከእርሱ በቀር ምንም ረዳት የላቸውም፤ በፍርዱም አንድንም አያጋራም*።

አንቀጹ ላይ፦ “ወላ ሸፊዒን” وَلَا شَفِيعٍ ማለት “እና አማላጅም የላችሁም” ማለት ሲሆን ከመጀመሪያው ሀረግ ለመለየት “ወ” وَ የሚል መስተዋድድ ይጠቀማል፤ ያ ማለት “በተጨማሪም አማላጅም የላችሁም” ማለት ነው፤ “ላ” لَا የሚለው “ሐርፉ ነፍይ” አፍራሽ ቃል ነው፤ ስለዚህ በመጀመሪያው ሀረግ ላይ “ማ” مَا የሚለው “መስደሪያ” አፍራሽ ቃል ሆኖ ገብቶ በተጨማሪ በሁለተኛው ሃረግ ላይ “ላ” لَا የሚለው አፍራሽ ቃል መደገሙ ጣኦታውያን ጣኦቶቻቸውን ወደ አላህ በማማለድ ያቀርቡናል ብለው የሚናገሩላቸውን ጣኦታት አማላጆች አለመሆናቸውን ለማሳየት “አማላጅ የላችሁም” በማለት ዘግቶታል፤ ለእነርሱም ከሚያጋሩዋቸው አማላጆች አይኖሯቸውም፦

30፥13 *ለእነርሱም ከሚያጋሩዋቸው አማላጆች አይኖሯቸውም*

ስለዚህ “አማላጅም ምንም የላችሁም” ማለት “ከእርሱ ፈቃድ በኋላ ካልሆነ በቀር እናንተ ከምታጋሯቸው የሚያማልድ አንድም አማላጅ የለም” ማለት ነው እንጂ በአላህ ፈቃድ የሚያማልዱ አማላጆች የሉም ማለት አሊያም አላህ አማላጅ ነው ማለት አይደለም። ከአላህ ሌላ ከቅጣት ሊያድናቸው የሚችል ረዳት የላቸውም፤ እንዲሁ ቅጣት እንዳይቀጡ ወደ አላህ የሚያማልዱ አማላጅ የላቸውም ማለት ነው፦

36፥23 *”ከእርሱ ሌላ አማልክትን እይዛለሁን? አልረህማን በጉዳት ቢሻኝ ምልጃቸው ከእኔ ለመመለስ ምንም አትጠቅመኝም፤ አያድኑኝምም*፡፡

ቁርኣን በመጨረሻው የፍርድ ቀን ለማንም ምንም ዓይነት አማላጅ እንደሌለ የሚናገርባቸው ሌሎች ክፍሎች ስላሉ ሱራ 32፡4 ስለ ከሐዲያን ብቻ የሚናገር መሆኑን መሟገት የትም አያደርስህም፡፡ ቁርኣን እንዲህ በማለት ማሰርያውን ያጠብቅብሃል፡-

“የእስራኤል ልጆች ሆይ! ያችን በናንተ ላይ የለገስኳትን ጸጋዬንና እኔም በዓለማት ላይ ያበለጥኳችሁ (አባቶቻችሁን በጊዜያቸው ከነበሩት ዓለማት ያበለጥኩዋቸው) መኾኔን አስታውሱ፡፡ (ማንኛዋ) ነፍስም ከ(ሌላዋ) ነፍስ ምንንም የማትመነዳበትንከርሷም ምልጃን የማይቀበሉባትን፣ ከርሷም ቤዛ የማይያዝበትን፣ እነርሱም የማይረዱበትን ቀን ተጠንቀቁ፡፡” (ሱራ 2፡47-48)

በዚህ የቁርኣን ጥቅስ ውስጥ በግልፅ እንደተቀመጠው በፍርድ ቀን ማንኛዋም ነፍስ ከሌላዋ ነፍስ እርዳታንና ምልጃን አታገኝም፡፡ ነፍስ ሲል ነፍስ የሆነችውን ነፍስ ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ለዚህ ነው ተርጓሚዎቹ የአረብኛውን ሐሳብ ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ (ማንኛዋም) በማለት የተረጎሙት፡፡ ሌላ ቦታ ላይም ተመሳሳይ ሐሳብ እናገኛለን፡-

“የእስራኤል ልጆች ሆይ! ያችን በናንተ ላይ የለገስኳትን ጸጋዬንና እኔም በዓለማት ላይ ያበለጥኳችሁ መኾኔን አስታውሱ፡፡ (አማኝ) ነፍስም ከ(ከሓዲ) ነፍስ ምንንም የማትጠቅምበትን፣ ከርሷም ቤዛ የማይወሰድበትን፣ ምልጃም ለርሷ የማትጠቅምበትን፣ እነርሱም የማይረዱበትን ቀን ተጠንቀቁ፡፡” (ሱራ 2፡122-123)

የአማርኛ ተርጓሚዎች በቅንፍ የጨመሯቸው ቃላት ዓላማ እዚህ ጋ ግልፅ አይደለም፡፡ ያለ ብዥታ መልእክቱን ለመረዳት በእንግሊዘኛ ትርጉም እናንብበው፡-

“And fear a Day when no soul will suffice for another soul at all, and no compensation will be accepted from it, nor will any intercession benefit it, nor will they be aided.”

በነዚህ ጥቅሶች መሠረት ማንኛዋም ነፍስ በፍርድ ቀን ለሌላዋ አማላጅ ሆና ልትቀርብ አትችልም፡፡ ስለዚህ በቁርኣን መሠረት ወሳኝ በሆነውና አማላጅ በሚፈለግበት የፍርድ ቀን ማንም ለማንም ማማለድ አይችልም ማለት ነው፡፡ አክሎም ቁርኣን በፍርድ ቀን ማንም ለማንም ምንም ማድረግ እንደማይችል ይናገራል፡-

“ከዚያም የፍርዱ ቀን ምን እንደኾነ ምን አሳወቀኽ? (እርሱ) ማንኛይቱም ንፍስ ለሌላይቱ ነፍስ ምንም ማድረግን የማትችልበት ቀን ነው። ነገሩም ሁሉ በዚያ ቀን አላህ ብቻ ነው።” (ሱራ 82፡18-19)

“ምንም ማድረግ የማትችልበት ቀን” የሚለውን ልብ ይሏል፡፡ ይህ ምልጃን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር ያጠቃልላል፡፡

አልፎ ተርፎም ቁርኣን በእምነታቸው ደካማ የሆኑትና ምልጃ የሚያሻቸው ሙስሊሞችን ጨምሮ ማንም ሰው ከአላህ ውጪ ምንም ዓይነት አማላጅ እንደሌለው በግልጽና በማያሻማ መንገድ ይናገራል፡-

“እነዚያንም ሃይማኖታቸውን ጨዋታና ላግጣ አድርገው የያዙትን ቅርቢቱም ሕይወት ያታለለቻቸውን ተዋቸው፡፡ በእርሱም (በቁርኣን) ነፍስ በሠራችው ሥራ እንዳትጠፋ አስታውስ፡፡ ለእርሷ ከአላህ ሌላ ረዳትና አማላጅ የላትም፡ በመበዢያም ሁሉ ብትበዥ ከርሷ አይወሰድም፡፡ እነዚህ እነዚያ በሠሩት ሥራ የተጠፉት ናቸው፡፡ ለነሱ ይክዱ በነበሩት ምክንያት ከፈላ ውሃ መጠጥና አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡” (ሱራ 6፡70)

“ለእርሷ ከአላህ ሌላ ረዳትና አማላጅ የላትም” ማለት ባንተ ቋንቋ ምን ማለት ይሆን? “it will find for itself no protector or intercessor except Allah” “ከአላህ ውጪ ረዳትም አማላጅም የሚሆናትን አታገኝም” ይልሃል፡፡ ዐይንህን ግለጥ፡፡ ስለዚህ በቁርኣን መሠረት ምልጃ የሚያሻቸውን ሙስሊሞችን ጨምሮ ማንኛውም ሰው ከአላህ ውጪ ሊረዳውም ሆነ ለእርሱ ሊማልድ የሚችል ምንም ዓይነት ረዳትና አማላጅ የለውም፡፡ አከተመ፡፡ በሌላ ቦታ ግን አማላጆች መኖራቸውን በማተት ይህንን ሐሳብ ያፈርሳል፡፡ ግጭቱ ግልፅ ነው፡፡ ክህደት አንተን ትዝብት ላይ ከመጣል የዘለለ ምንም አይጠቅምህም፡፡

ሙፈሲሮችም በዚህ መልኩ ነው ተረድተው ያስቀመጡት:-

ተፍሲሩል ኢብኑ ከሲር 32፥4

*”ከእርሱ ሌላ ለእናንተ ረዳት የላችሁም” ማለት “እርሱ ብቻ ሉአላዊ የሁሉንም ጉዳዮች ተቆጣጣሪ፣ የሁሉም ነገር ፈጣሪ፣ ሁሉን ነገር አድራጊ ነው፤ ከእርሱ ሌላ ፈጣሪ የለም” ማለት ነው። “እናም አማላጅም ምንም የላችሁም” ማለት “ከእርሱ ፈቃድ በኋላ ቢኾን እንጂ አንድም አማላጅ የለም” ማለት ነው*።

ቁርኣን “ከአላህ ውጪ አምላክ የለም” ሲል ያው አምላክ የለም ማለቱ ነው፡፡ ነገር ግን “ከአላህ ውጪ ረዳትም አማላጅም የለም” ሲል ትርጉሙ በተቃራኒው “ከአላህ ውጪ ረዳትም አማላጅም አለ” ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ምን የሚሉት አመክንዮ ነው? እንዲህ ያለ ትርጉም አልባ ትርጓሜ እንኳንስ በኢብን ከሢር ይቅርና በአላህ በራሱ ቢነገር ዞሮ ዞሮ ትርጉም አልባ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህ በስነ አመክንዮ ሕግ “Fallacy of Appeal to Authority” ይሰኛል፡፡ ንግግሩ ትክክል ሲሆን ትክክል ይሆናል እንጂ ኢብን ከሢር ወይንም ሌላ ታዋቂ ሊቅ ስለተናገረ ትክክል አይሆንም፡፡ ቁርኣን በግልፅ “ላሓ ሚን ዱኒል-ላሂ ዋሊዩን ወላ ሻፊዑን” ብሏል! ከአላህ በስተቀር ረዳትም ሆነ አማላጅ ምንም የለም!

ዘመንኛ ሙስሊሞች ቁርኣን በግልፅ አማላጅ እንደሌለ በመናገሩ ምክንያት “አማላጅ አለ” የሚለውን ሐሳብ ይዞ ከመቆየት ይልቅ አማላጅ እንደሌለ የሚናገረውን በመቀበል አቋማቸውን እያሳወቁ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የእስልምናው ዓለም ትልቁ ተቋም የሆነው ዓለም አቀፍ የሙስሊሞች ሊግ እንዲህ ሲል አቋሙን ገልጿል፡-

Islam stresses the human character of the Prophet … Therefore, any kind of mediation is not permissible or recognized in Islam. Prophets are mere messengers of God; they cannot fnetive anyone if he commits a sin or exempt him from the punishment he deserves. They cannot also intercede with God on anybody’s behalffor Islam does not recognize the idea of intercession as such.” (The Muslim World League Journal, May-June 1983, Volume 10, Number. 8, p. 9; Quoted in David Goldmann, Islam and the Bible: Why Two Faiths Collide, p. 65)

በእስልምና ውስጥ ሙሐመድን ጨምሮ ማንኛውም ፍጥረት ለማንም እንደማያማልድና እስልምና የምልጃን አስተምሕሮ እንደማይቀበል በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በአፅንዖት ተገልጿል፡፡ እስልምና “ምልጃ” የሚለውን ሐሳብ በጭራሽ እንደማያስተናግድም ተነግሯል፡፡ እነዚህ ወገኖች ይህንን አቋም አማላጆች መኖራቸውን ከሚናገሩት የቁርኣን ጥቅሶችና ሐዲሳት ጋር እንዴት እንደሚያስታርቁ ባናውቅም ነገር ግን ከሚጋጩት ከሁለቱ አቋሞች አንዱን በመያዝ ሌላኛውን አሽቀንጥረው ጥለውታል፡፡ ይህም የሚያሳየው በቁርኣን አማላጆች የሉም የሚለው አቋም አማላጆች አሉ ከሚለው እኩል ወይንም የበለጠ ሊስተባበል የማይችል መሆኑን ነው፡፡ አንተ ግን ለማስተባበል እየጣርክ ነው፡፡

መላእክት፣ ነቢያት፣ ሙዑሚን ያማልዳሉ ማለት እና እኛ ወደ ፍጡራን በሌሉበት መለማመን፣ መጠየቅ እና መጸለይ ይለያያል፤ ወደ ፍጡራን በሌሉበት መለማመን፣ መጠየቅ እና መጸለይ ምልጃ ሳይሆን ሺርክ ነው። የሁሉንም ፍጥረት ልመና፣ ጥያቄ እና ጸሎት ጊዜና ቦታ ሳይወስነው ሁሉን የሚሰማ፣ ሁሉን የሚያይ እና ሁሉን የሚያውቅ የዐለማቱ ጌታ አላህ ብቻ ነው።

ሙግታችን እንደርሱ ስለማይል ለምን እንዲህ ያለ ሐሳብ አምጥተህ ራስህን ችግር ላይ እንደጣልክ አልገባኝም፡፡ የኛ ሙግት ቁርኣን አንዱ ቦታ ላይ ከአላህ ውጪ ምንም ዓይነት አማላጅ እንደሌለ ከተናገረ በኋላ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ፍጥረታትም እንደሚያማልዱ መናገሩ ላይ ነው፡፡ ጉዳዩን አንዛዝተህ ውሉን ከማጥፋት በዘለለ የሰጠኸው የረባ ምላሽ የለም፡፡

እሺ አንተ እንዳልከው በእስልምና ወደ ፍጡራን መጸለይ ካልተቻለ ሙሐመድን በሌለበት ለምን ታናግሩታላችሁ? “አሰላሙ ዐለይከ አዩሃ ን-ነቢዩ ወ ራመቱላሂ ወ በረከቱሁ” ወይም “የአላህ ነቢይ ሆይ የአላህ ሰላም፣ እዝነትና በረከት ባንተ ላይ ይሁን” እያላችሁ ሙት የሆነውን ሙሐመድን ስለምን ታናግሩታላችሁ? በትርሚዚ ሐዲስ መሠረትስ ሙሐመድ አንድን ዐይነ ስውር ወደ እርሱ እንዲጸልይ ለምን ነገረው?

“Oh Allah, I ask You and turn to You through my Prophet Muhammad, the Prophet of mercy; O MUHAMMAD (YA MUHAMMAD), I SEEK YOUR INTERCESSION with my Lord for the return of my eyesight…

አላህ ሆይ የእዝነት ነብይ በሆኑት በነቢዬ በሙሐመድ በኩል ወደ አንተ ተመልሼ እለምንሃለሁሙሐመድ ሆይ፣ ዐይኖቼ እንዲከፈቱልኝ ከጌታዬ ያማልዱኝ ዘንድ ምልጃዎትን እሻለሁ… (Sunan Ibn Majah, Vol. 1, Book 5, Hadith 1385)

ይህንን ጸሎት እንዲጸልይ ለዐይነ ስውሩ የነገረው ሙሐመድ ራሱ ሲሆን በሐዲስ ሊቃውንት ሳሒህ መሆኑ ተነግሮናል፡፡ (Ahmad ibn Naqib al-Misri, Reliance of the Traveller: The Classic Manual of Islamic Sacred Law (Umdat Al-Salik) Nuh Hah Mim Keller, 1997, p. 935)

ስለዚህ ወደ ሰው ለምልጃ መጸለይ ሺርክ ከሆነ ሙሐመድ ሺርክን አስተምሯል ማለት ነው፡፡ ለወደፊቱ እንዲህ ያለ ማጥ ውስጥ ላለመግባት በርዕሱ ላይ ብቻ አተኩር፡፡ እስልምና ጥያቄ ሊነሳበት የማይችል ገፅታ ስለሌለው ከርዕስ ውጪ በሄድክ ቁጥር ነገሮች ይወሳሰቡብሃል፡፡

 

የቁርኣን ግጭቶች