የቁርኣን ግጭቶች – አላህ ያለሚስት ልጅ ሊኖረው ይችላል ወይስ አይችልም?

5. አላህ ያለ ሚስት ልጅ ሊኖረው ይችላል ወይስ አይችልም?

በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ይችላል፡-

ሱራ 39፡4 “አላህ ልጅን መያዝ በፈለገ ኖሮ ከሚፈጥረው ውስጥ የሚሻውን ይመርጥ ነበር ጥራት ተገባው፡፡”

አይችልም፡–

ሱራ 6፡101 “… ለርሱ ሚስት የሌለችው ሲሆን እንዴት ልጅ ይኖረዋል?”

መልስ

አበይት ክርስቲያኖች ኢየሱስ ዓለም ሳይፈጠር ዘመን ሳይቆጠር አብን አህሎና መስሎ ከአብ “ባህርይ ዘእም-ባህርይ አካል ዘእም-አካል” ማለትም ከባህርይው ባህርይ ወስዶ ከአካሉ አካሉን ወስዶ ተወለደ ይሉናል። ልጅ ከአባቱ አብራክ ሲገኝ ልጅ የአባት ቢጤ፣ ተጋሪ እና ወራሽ ነው፤ ሰው ሰውን ሲወልድ ሁለት ሰው እንጂ አንድ ሰው እንደማይባል ሁሉ “አምላክ ዘእም-አምላክ” ማለትም ከአምላክ አምላክ ከተገኘ ሁለት አምላክ ይሆናል። አምላካችን አላህ ቁርኣን ካወረደበት ምክንያት አንዱ እነዚያንም፦ “አላህ ልጅን ይዟል” ያሉትን ሊያስጠነቅቅበት ነው፦

18፥4 *እነዚያንም፦ “አላህ ልጅን ይዟል” ያሉትን ሊያስጠነቅቅበት አወረደው*፡፡

ሕዝበ እግዚአብሔር ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውና መሲሁ ደግሞ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ መሆኑ የነቢያት ሁሉ ትምሕርት ሆኖ ሳለ “ነቢያትን ለማረጋገጥ መጣሁ” ያለው ሙሐመድ በዚህ ጉዳይ ላይ ስለምን ከነቢያት በተጻራሪ ቆመ? የሙሐመድን ሐሰተኛነት ከሚያሳዩ ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው ይህ የክህደት ትምሕርቱ ነው፡፡

ለአላህ ልጅን መያዝ አይገባውም፡፡ ከጉድለት ሁሉ ጠራ፡፡ ነገርን በሻ ጊዜ ለእርሱ የሚለው «ኹን» ነው ወዲያውም ይኾናል፦

19፥35 *ለአላህ ልጅን መያዝ አይገባውም፡፡ ከጉድለት ሁሉ ጠራ፡፡ ነገርን በሻ ጊዜ ለእርሱ የሚለው «ኹን» ነው ወዲያውም ይኾናል*፡፡

4፥171 *ለእርሱ ልጅ ያለው ከመኾን የጠራ ነው፡፡ በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ የእርሱ ነው*፡፡ መመኪያም በአላህ በቃ፡፡

10፥68 *«አላህ ልጅን ያዘ» አሉ፡፡ ከሚሉት ጥራት ተገባው፡፡ እርሱ ተብቃቂ ነው፡፡ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የእርሱ ነው፡፡ እናንተ ዘንድ በዚህ በምትሉት ምንም አስረጅ የላችሁም፡፡ በአላህ ላይ የማታውቁትን ትናገራላችሁን?*

19፥92 *ለአልረሕማን ልጅን መያዝ አይገባውም*፡፡

ልጅ መጫወቻ መደሰቻ ነው፤ ይህም የቅርቢቱም ሕይወት ጨዋታ ነው፦

6፥32 *የቅርቢቱም ሕይወት ጨዋታ እና ላግጣ እንጅ ሌላ አይደለችም*፡፡

“ልጅ መያዝ” ማለት ምን ማለት ነው? የመሲሁንስ ልጅነት የሚጠቅሰው በምን መንገድ ነው? አበይት የክርስትና ቤተ እምነቶች እግዚአብሔር ልጅ እንደያዘ ሳይሆን ልጅ እንዳለው ነው የሚያስተምሩት፡፡ ልጅ ያዘ ማለት ማደጎ (adoption) የሚያመለክት እንጂ ኢየሱስ በዘላለማዊ መገኘት (Eternal Generation) ከአብ መገኘቱን የሚጠቅስ አይደለም፡፡ የቁርኣን ደራሲ የክርስትናን አስተምሕሮ ፈፅሞ አልተገነዘበም፡፡

“ልጅ መውለድ ጫወታና ላግጣ ነው” ስትል ምን ማለትህ ነው? በአምሳለ እግዚአብሔር የተፈጠሩ ክቡራን የሰው ልጆች ወደ ምድር የሚመጡበት የከበረ ሒደት እንጂ “ጫወታና ላግጣ” አይደለም፡፡ እንደርሱ ከሆነ አላህ ጫወታና ላግጣ የሆነ ነገር ፈጥሯል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ተብሎ አይገለፅም፤ ጸያፍ ንግግር ነው፡፡

አላህ ልጅን መያዝ ቢፈል ኖሮ ከእርሱ ዘንድ ይይዝ ነበር፤ ነገር ግን ጥራት ይገባው ያንን ሰሪ አይደለም፤ ልጅ አለው የሚሉት ብርቱ ቅጣት አላቸው፦

21፥17 *መጫወቻን ልንይዝ በሻን ኖሮ ከእኛ ዘንድ በያዝነው ነበር፡፡ ግን ሠሪዎች አይደለንም*፡፡

“ከእኛ ዘንድ” ማለት “ከሚፈጥረው” ማለት ነው፤ ለምሳሌ ልጅ ከእርሱ ዘንድ የሚሰጥ ነውና፦

39፥4 *አላህ ልጅን መያዝ በፈለገ ኖሮ “ከሚፈጥረው” ውስጥ የሚሻውን ይመርጥ ነበር፡፡ ጥራት ተገባው፡፡ እርሱ አሸናፊው አንዱ አላህ ነው*፡፡

19፥5 «እኔም ከበኋላዬ ዘመዶቼን በእርግጥ ፈራሁ፡፡ ሚስቴም መካን ነበረች ስለዚህ *ከአንተ ዘንድ ለእኔ ልጅን ስጠኝ*፡፡

“ከሚፈጥረው” እና “ከአንተ ዘንድ” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት፤ “ከእኛ ዘንድ” ማለት እርሱ ዘንድ ያሉትም መላእክት ያመለክታል፤ ምክንያቱም ዐውዱ ላይ፦ “አልረሕማንም ከመላእክት ልጅን ያዘ” ብለዋልና፦

21፥19 በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉም የእርሱ ነው፡፡ *እርሱ ዘንድ ያሉትም መላእክት* እርሱን ከመገዛት አይኮሩም፡፡ አይሰለቹምም፡፡

21፥26 *«አልረሕማንም ከመላእክት ልጅን ያዘ» አሉ፡፡ ጥራት ተገባው፡፡ አይደለም መላእክት የተከበሩ ባሮች ናቸው*፡፡

ይህንን ሁሉ እናውቃለን፡፡ ለጥያቄያችን መልስ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

የፈርዖንም ሚስት፦ “ለእኔ ለአንተም ልጅ አድርገን ልንይዘው” ማለቷ ይህ ልጅ አድርጎ መያዝ የፍጡር ባህርይ ነው፦

28፥9 የፈርዖንም ሚስት፦ “ለእኔ ለአንተም የዓይኔ መርጊያ ነው፤ አትግደሉት፡፡ ሊጠቅመን ወይም *ልጅ አድርገን ልንይዘው ይከጀላልና”* አለች፡፡ እነርሱም ፍጻሜውን የማያውቁ ሆነው አነሱት፡፡

ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ከኃጢአታችን አንፅቶ ልጆቹ እንዳደረገን እናምናለን፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ልጆቹ ማድረጉና በመንግሥቱ ውስጥ የልጅነት መብት እንዲኖራቸው ማድረጉ ከባሕርዩ ጋር የሚጣረሰው በምን መንገድ ነው? ሙሐመድ “አላህ ልጅ የለውም” ብሎ ስላስተማረ ብቻ ያለ ምንም ምክንያትና ሰበብ የነቢያትን ትምሕርት በጭፍን መካድ የዋህነት ነው፡፡

ኸረ ልጅ ያዘ ከማለትም አልፈው ወለደ ብለዋል፤ እነርሱም በእርግጥ ውሸታሞች ናቸው፤ አላህ አልወለደም፤ አልተወለደምም፦

37፥152 ፦ “አላህ ወለደ” አሉ፤ እነርሱም በእርግጥ ውሸታሞች ናቸው፡፡

112፥3 *አልወለደም፤ አልተወለደምም*፡፡

የመካው ጥቁር ድንጋይም አልወለደም አልተወለደም፡፡ አለመውለድና አለመወለድ የፈጣሪነት መስፈርት አይደለም፡፡ ይልቅ ሙሐመድ የኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅነትና ከማርያም መወለድ በተሳሳተ መንገድ በመረዳቱ ምክንያት ከገዛ ምናቡ የፈጠረው ስሁት መረዳት ነው፡፡ ክርስቲያን እንደነበርክ እንደምትናገር ከሰዎች ስለሰማሁ ምናልባት ይህ የሚጠፋህ አይመስለኝም፡፡ ለክርስትና አስተምሕሮ እንግዳ እንደሆኑት ሌሎች ሙስሊሞች የአላዋቂ ንግግር ባትናገር መልካም ነው፡፡

አላህ የሚጋራው ባልደረባ ስለሌለው ልጅም አይኖረውም፤ ምክንያቱም ልጅ የአባት ምትክ፣ ተጋሪ፣ ሞክሼ ስለሚሆን ነው፦

6፥101 እርሱ ሰማያትንና ምድርን ያለ ብጤ ፈጣሪ ነው፡፡ *ለእርሱ ሚስት የሌለችው ሲኾን እንዴት ለእርሱ ልጅ ይኖረዋል? ነገርንም ሁሉ ፈጠረ*፡፡ እርሱም ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡

የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት የመጋራት ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል (ሎጎስ) በመሆኑ ምክንያት ሁለቱ ሊነጣጠሉ አይችሉም፡፡ እግዚአብሔር ካለ ሎጎስ አለ፡፡ ይህ ተጋሪነት ሳይሆን አንድነት ነው፡፡

“የኩኑ” يَكُونُ ማለት “ይኖረዋል” ማለት ሲሆን ባሕርይን ያሳያል፤ አላህ ነገርንም ሁሉ ፈጠረ፤ ልጅ የሚመጣው በሴት ነው። ያለ ሴት እንዴት ልጅ ይኖራል? የሚለው የሥነ-አመክንዮ ጥያቄ ነው። ይህ ባሕርይ ታሳቢ ያደረገ እንጂ ችሎታን ታሳቢ ያደረገ አይደለም። እንዴት ይችላል? ተብሎ አልተጠየቀም።

ልጅ እንዲኖረው የግድ ሴት እንደምታስፈልገው ማሰቡ ስህተት ነው፡፡ ቀደም ሲል በተባሉት መንገዶች፣ ማለትም ከፍጥረቱ መርጦ ልጆቹ ማድረግ ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አማኞች የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ሲናገር በዚያ መንገድ ነው፡፡ አላህ ይህንን ማድረግ እንደሚችል አንተ ራስህ በጠቀስካቸው ጥቅሶች ውስጥ ተናግሯል፡-

ሱራ 394 “አላህ ልጅን መያዝ በፈለገ ኖሮ ከሚፈጥረው ውስጥ የሚሻውን ይመርጥ ነበር፡፡ ጥራት ተገባው፡፡ እርሱ አሸናፊው አንዱ አላህ ነው፡፡”

ይህ የቁርኣን ጥቅስ አላህ በምርጫ ብቻ ልጅ ሊኖረው ይችል እንደነበር ይናገራል፡፡ ስለዚህ ያለ ሚስት ልጅ ሊኖረው ይችላል፡፡ እናም በዚህ ጥቅስ መሠረት የፍላጎት ጉዳይ እንጂ ሊኖረው ይችል ነበር ማለት ነው፡፡ ጉዳዩ እንደዚህ ከሆነ ደግሞ ከላይ ባለው ጥቅስ ውስጥ እንደተባለው “ያለ ሚስት ልጅ ሊኖረው እንደማይችል” መነገሩ ግጭት ነው፡፡

ሌላው በዘላለማዊ መገኘት (Eternal Generation) ልጅ ሊኖረው ስለሚችል የቁርአኑ አላህ ልጅ ሊኖረው የሚችለው ከሴት ጋር ወሲብ በመፈፀም ብቻ እንደሆነ መናገሩ ኢ-አመክንዮአዊም አላዋቂነትም ነው፡፡

ሲቀጥል ከመነሻው “ሚስት” ተብሎ የተቀመጠው ቃል “ሷሒበት” صَٰحِبَة ሲሆን “ባልደረባ” ማለት ነው፤ “አስሐብ” أَصْحَٰب ወይም “ሷሒብ صَاحِب ደግሞ “ባልደረባ” “አጋር” “ሞክሼ” “ባለንጀራ” ከሆነ ፈጣሪ ከመነሻው “ባልደረባ” “ተጋሪ” “አጋር” “ሞክሼ” “ባለንጀራ” የለውም፦

6፥163 *ለእርሱ ተጋሪ የለውም፡፡ በዚህም በማጥራት ታዘዝኩ*፡፡ እኔም የሙስሊሞች መጀመሪያ ነኝ» በል፡፡

ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡ ቁርኣን አንዱ ቦታ ላይ አላህ በምርጫ ብቻ ልጅ እንደሚኖረው ይናገራል፤ በዚህ ቦታ ግን ልጅ ለመውለድ ሚስት አስፈላጊ እንደሆነች ይናገራል፡፡ የችሎታ ጉዳይ አይደለም ብንል እንኳ አላህ ያለ ሚስት በምርጫ ብቻ ልጅ ሊኖረው እንደሚችል ቀደም ሲል የተናገረውን ቃል እዚህ ጋ ስለካደ ግጭቱ እንዳለ ነው፡፡

ከእርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም፤ ምንም ልጅን አልያዘም፤ ለአልረሕማን ልጅ የለውም እንጂ ቢኖረው እንገዛው ነበር ማለት አለመኖሩን የሚያጸና ነው፤ ለምሳሌ አንተ አምላክ ብትሆን አመልክህ ነበር ማለት አምላክ አይደለህም ማለት ነው፤ በተመሳሳይም ልጅ የለውም ማለት ነው፦

23፥91 *አላህ ምንም ልጅን አልያዘም፡፡ ከእርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም፡፡ ያን ጊዜ ሌላ አምላክ በነበረ ኖሮ አምላክ ሁሉ በፈጠረው ነገር በተለየ ነበር፡፡ ከፊላቸውም በከፊሉ ለይ በላቀ ነበር፡፡ አላህ ከሚመጥኑት ሁሉ ጠራ*፡፡

ስለዚህ እንዴት ይኖረዋል ማለት ባሕርይን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን ቢፈልግል ከሚፈጥረው ይይዝ ነበር ማለት ደግሞ ችሎታን ዋቢ ያደረገ ነው።

አላህ በምርጫ ብቻ ልጅ ሊኖረው እንደሚችል ከተናገረ በኋላ “ሚስት የሌለችው ሲኾን እንዴት ልጅ ይኖረዋል?” የሚል ጥያቄ መቅረቡ ግጭት ነው፡፡ ያለ ሚስት በምርጫ ብቻ ልጅ ሊኖረው እስከቻለ ድረስ “ሚስት ስለሌለችው እንዴት ልጅ ይኖረዋል?” የሚል ንግግር የመጀመርያውን ሐሳብ ያፈርሳል፡፡ ለምሳሌ ያህል እኔ “ባቡር ተሳፍሬ መምጣት እችላለሁ” ብዬ ብናገርና ለምን በሰዓቱ እንዳልመጣሁ ደውለህ ስትጠይቀኝ “መኪና የሌለኝ ስሆን እንዴት እመጣለሁ?” ብዬ ብመልስልህ ግጭት አይፈጥርምን? አስቀድሜ ባቡር ተሳፍሬ መምጣት እንደምችል ስለነገርኩህ መኪና ስለሌለኝ መምጣት አለመቻሌን መናገሬ በባቡር መምጣት እንደምችል የተናገርኩትን ሐሳብ ያፈርሳል፡፡ እናም ግጭቱን የሚፈታ የረባ ሐሳብ አላቀረብክም፡፡

የቁርኣን ግጭቶች